Friday, December 28, 2012

ሥጋ፣ ኅሊናና ልቡና


በአሜሪካዋ ኮኔክቲከት ግዛት በሳንዲ ሁክ ትምህርት ቤት ሕጻናትና መምህራን ላይ የተፈጸመው ኢ ሰብአዊ ግድያ ሰሞኑን የዓለም መነጋገርያ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ጉዳዩን አሳዛኝና አሰቃቂ ያደረገው ደግሞ ምንም በማያውቁ ሕጻናትና በሥራ ላይ በነበሩ መምህራን ላይ የተፈጸመ መሆኑ ነበር፡፡ እነዚህ አካላት ከገዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ‹ጠብ ወይም ዝምድና› የሌላቸው፣ ለዚህ ቀርቶ ለቁጣ እንኳን የሚያበቃ ጥፋት በአጥፊው ላይ ያልፈጸሙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሕይወታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከማጣት አልታደጋቸውም፡፡
ምንም በማያውቁና በራሳቸው ዓላማ ምክንያት ተሰባስበው በሚገኙ ወገኖች ላይ የተኩስ እሩምታ እየከፈቱ ሕይወትን መቅጠፍ አሁን አሁን በዓለማችን እየተለመደ የመጣ ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኖርዌይ ሀገሪቱን ጸጥ ያሰኘ ግድያ በአንዲት ደሴት ተሰባስበው በነበሩ ተማሪዎች ላይ ተፈጽሞ ነበር፡፡ እምብዛም ይህን መሰል ወንጀል በማይሰማባት ቻይና እንኳን ሳይቀር በትምህርት ቤት ሕጻናት ላይ እሩምታ መክፈት እየተለመደ መምጣቱን የሚያሳዩ ድርጊቶች ብቅ እያሉ ነው፡፡ 

ምናልባት በጦር መሣርያ ላይ ያላቸው ሕግ መላላት ለዚህ መሰሉ አውሬያዊ ተግባር ጊዜያዊ መነሻ ይሆን እንደሁ እንጂ የሥር ምክንያቱ ግን አይመስለኝም፡፡ አሜሪካኖቹ የጦር መሣርያን በተመለከተ ያላቸው ባህልና ሕግ አዲስ አይደለም፡፡ ለብዙ ዘመን አብሯቸው የቆየ ነው፡፡ ይህ ባሕላቸውም የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የፊልሞቻቸውም ባህል ሆኖ አብዛኞቹ የአሜሪካ ፊልሞች መሣርያን እንደ ዋና ቅመም ይጠቀሙበታል፡፡
ባለፉት ሠላሳና ዐርባ ዓመታት ግን በአሜሪካ የጦር መሣርያን በመያዝ የሚፈጸሙ ጭፍጨፋዎች እየተባባሱ መምጣታቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ እነዚህ በጦር መሣርያ የሚደረጉ ግድያዎች ደግሞ ጠላትነትን ወይም የጥቅም ግጭትን መሠረት ያደረጉ አይደሉም፡፡ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች፣ የተደራጁ ወንጀለኞች አለያም ደግሞ ዘራፊዎች የሚፈጽሟቸው ዓይነቶችም አይደሉም፡፡ ከዚህ መሰሉ ተግባር ጋር ግንኙነት የሌላቸው ድንገት የሚነሡ ግለሰቦች ከውስጥ በሚመጣ ግፊት ተገፋፍተው የሚፈጽሟቸው ጭካኔዎች ናቸው፡፡
ነገሩን ዕንቆቅልሽ የሚያደርገውም ይኼው ነው፡፡
እዚህ ላይ እንደ ሰው ቆም ብለን መመርመር ያለብን ይመስለኛል፡፡ ዓለም አሁን በየትኛው የአስተሳሰብ ጎዳና ላይ ናት? የሚለውን፡፡ እንደ እኔ ዓለም አሁን ለቁሳዊ ነገርና ለቁሳዊ ዕድገት ታላቅ ቦታ የሰጠችበት ጊዜ ላይ ናት፡፡ የሰው ልጅን ሞራላዊና መንፈሳዊ እሴቶች የቀረጹት፣ ከሰው ጋር ተዋሕደው ህልው እንዲሆኑም ያደረጉት ተቋማት፣ ግለሰቦችና አስተሳሰቦች እየቀሩ፣ እየተረሱ፣ እየፈራረሱና፣ ቅርጻቸውንና ማንነታቸውንም እየቀየሩ፣ የሰውን ልጅ ቁስ ብቻ እንዲሆን አጋልጠው የሰጡት ይመስላል፡፡
የሰው ነባር ባህል፣ ማኅበራዊው መስተጋብር፣ እምነት፣ ሞራልና ሥነ ምግባር አሁን ባለው ዓለም ውስጥ የሚቃለሉ፣ የሚናቁ፣ የሚተቹ፣ የሚጥላሉ ብሎም ‹በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች እየሆኑ› ነው፡፡ ዕድገትና ሥልጣኔ ማለት መንፈሳዊና ሞራላዊ፣ ባህላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን የዘነጋ፤ በሚታይና በሚዳሰስ ነገር ላይ ብቻ የተመሠረተ ዕድገት እየሆነ ነው፡፡ የፎቆች ብዛት፣ የመንገዶች ርዝመት፣ የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የመገናኛ መንገዶች መወሳሰብ፣ የጤናና ማኅበራዊ ተቋማት መስፋፋት፣ ሀብት መፍጠርና ማካበት ብቻቸውን የዕድገት ማሳያዎች እየሆኑ ነው፡፡
‹እንበለ ሥጋ ኢትቀውም ነፍስ› ይባላልና ለሰው ልጅ ምቾትና ድሎት፣ ደኅንነትና ጤንነት የሚሆኑ ነገሮች መፈጠራቸው፣ መስፋፋታቸውና ማደጋቸው አይጠላም፡፡ ነገር ግን የሚያድገውም ሰው፤ የሚሠራውም ለሰው ነውና የሰውን ማንነት የዘነጋ መሆን የለበትም፡፡ ሰው ኅሊና፣ ልቡናና ሥጋ ያለው ፍጡር ነውና፡፡
ሥጋው በመብላትና በመጠጣት፣ በመልበስና በመዋብ፣ በመተኛትና በመንቃት፣ ጤናውን በመጠበቅና በስፖርት፣ በመወለድና በመሞት ይረካል፡፡ ይህ ግን በአብዛኛው ከእንስሳትና ዕጽዋት ጋር የሚጋራውና የእነርሱ ዘውግ መሆኑንም የሚያውቅበት ነው፡፡ በአብዛኛውም እነዚህን ለማድረግ ሰው መሆን ላያስፈልገው ይችላል፡፡
ኅሊናው በፍልስፍና፣ በጥበብ፣ በኪነ ጥበብ፣ በሰብአዊ ተግባራት፣ በማኅበራዊ ክዋኔዎች፣ ኃላፊነትን በመወጣት፣ ለሀገርና ለወገን በሚደረጉ ተግባራትና በፈጠራ ሥራዎች ይረካል፡፡ ከእንስሳት የሚለይበት፣ ከመላእክትም የሚለይበት ይህ ነው፡፡ መላእክት ልቡና እንጂ ኅሊና የላቸውም፡፡ ስለዚህም ውበትና፣ ሰብአዊነት፣ የፈጠራ ሥራና ክህሎት፣ ፍልስፍናና ርእዮተ ዓለም እነርሱ ጋር የለም፡፡ እነርሱ አካልና ልቡና ብቻ ነው ያላቸው፡፡ ያውም አካላቸውም ከእኛ የተለየ፣ ልቡናቸው ግን ከእኛ የሚመሳስል ነው፡፡
እዚህ ላይ ሰው በኅሊናው የሚደርስበት አንድ ነገር አለ፡፡ ዕውቀት፡፡ ዕውቀት ሲባል ደግሞ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን መኳተን፣ መፈተን፣ ማረጋገጥ፣ መተንተን፣ ችግርን በዕውቀት መፍታት፣ አዳዲስ ነገሮችን ለማግኘት መትጋትና መጣር፡፡ መሻሻልና ማሻሻል፡፡ ይህ ዕውቀት በልቡና ከሚገኘው ዕውቀት ይለያል፡፡ የልቡና ዕውቀት የመኳተን ዕውቀት ሳይሆን የተገልጦ ዕውቀት ነው፡፡ የአብርሖት ዕውቀት ነው፡፡ አንዴ የሚገኝ፣ ከዚያም የማይጠፋ፣ መርሳትም የሌለበት፣ ጊዜና ቦታም የማይወስነው ዕውቀት ነው፡፡  
የሰው ልጅ ልቡናው በአምልኮና በአብርሖት ዕውቀት ብቻ ነው የሚሞላውና የሚሠራው፡፡ የሚረካውም፡፡  ሰው ማንንም ያምልክ፣ ምንንም ይከተል ግን አምላኪ ፍጡር ነው፡፡ አምልኮቱም የተገዥነት አይደለም፡፡ የተገዥነት አምልኮት የእንስሳት ነው፡፡ የሰው ልጅ አምልኮ የመስተጋብር አምልኮ ነው፡፡ ከሚያመልከው ጋር መገናኘት፣ የሚያመልከውን መጠየቅ፣ መመርመርና ማወቅ፣ መረዳትና ማግኘት ይሻል፡፡ ከእርሱም ጋር መኖር ይፈልጋል፡፡
እንግዲህ ሰው ማለት እነዚህ ሦስቱ ያሉት ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልጉትም ፍጡር ነው፡፡ አሁን አሁን ግን በዓለም ላይ የሚነፍሱ አስተሳሰቦች ሰውን ቁሳዊ ወይም ሥጋዊ ብቻ እያደረጉት ነው፡፡ ለቁስ የሚኖር፣ በቁስ የሚመራ፣ በቁስ የተከበበና ቁስን ብቻ የሚከተል፡፡
ዓለምን ያስደመሙት የፈጠራ ሥራዎችኮ እየቀሩ ነው፡፡ መኪና፣ አውሮፕላን፣ ኮምፒውተር፣ ባቡር፣ ጨረቃ ላይ መውጣት፣ ስልክ፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቭዥን፣ አዳዲስ ዓለማትን ማግኘት፣ የተፈጠሩበትና ሰውን ጉደኛ ፍጡር ያሰኙበት ዘመናትኮ አለፉ፡፡ አሁን ፈጠራውም ‹ግብር እም ግብር ነው›፡፡ በሰዓት አሥር የሚጓዘውን መቶ ማስኬድ ነው፡፡ ያለውን መቀባባት፡፡ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች እኔ ባይ የሆኑ፣ ለሰው ልጆች በጎ መሆን የሚጨነቁ፣ ከግላዊ ጥቅም ባሻገር የሚያዩና ሕይወታቸውንም ለበጎ ሥራ የሚሠው ሰዎችን ይፈልጉ ነበር፡፡ ለዚህም ነው እነዚህን ነገሮች ያስገኟቸው ሰዎች አብዛኞቹ ‹ምኑን ሊቃውንት› የሆኑት፡፡ እነዚህ ኅሊና የነበራቸው ፣ ሥጋቸውንም ለኅሊናቸው ያስገዙ ሰዎች ነበሩ፡፡
ኅሊና ሥራውን እያቆመ ሲሄድ ግን ለምን እለፋለሁ? የሚል ትውልድ መጣ፡፡ አንድን ሳይንሳዊ ግኝት ለማግኘት አርባና ሃምሣ ዓመት ለምን ይለፋል? ሃያ አራት ሰዓትስ እንቅልፍ አጥቶ ለምን በሙከራ ክፍል ሲታትር ይውላል? በቀላሉ ሊደሰት፣ በቀላሉስ ገንዘብ ሊያገኝ፣ በቀላሉስ ሊኖር ሲችል፡፡ እነዚያ በዘጠና ደቂቃ በኢንተቬ፣ ካርቱም ሄዶ ቀረ፣ የኛ ሰው በደማስቆ፣ የስድስቱ ቀን ጦርነት በሚሉት መጻሕፍት ያነበብናቸው ለሀገራቸው የሚብከነከኑ እሥራኤላውያንኮ ዛሬ የሉም፡፡ ‹ለምን ከፊሊፒን ወታደር አንቀጥርም› የሚሉ እሥራኤላውያን ትውልዶችኮ መጥተዋል፡፡
ሰው መኖርን ከቁስ ነገር ጋር ብቻ ስላያያዘው የሚኖረው በዕድሜው ልክ ብቻ ሆኗል፡፡ ሰው ኅሊና ካለው ግን ከዕድሜው በላይ ይኖራል፡፡ ከዕድሜ በላይ ለመኖር ደግሞ ከዕድሜ በላይ ማሰብ ይገባል፡፡
የእምነት ተቋማት እምነትን ወደ ኩባንያ በመለወጣቸው፤ አርአያና አይከን የሚሆኑ የእምነት ሰዎች በመጥፋታቸው፣ በሌሎች የሚታዩት የሞራልና የሥነ ምግባር ድቀቶች በእምነት ተቋማቱም በመታየታቸው፣ ለብዙ ዘመንም በሂስና በጥላቻ በመብጠልጠላቸው ሰውን ልብ አልባ ፍጡር እያደረጉት ነው፡፡ በእምነት ሰዎችና ተቋማት ዘንድ ተከታይነት እንጂ መንፈሳዊነት በመጥፋቱ፤ ሩጫቸውንም ሰው ከማዳን ይልቅ የገበያ ውድድር ስላደረጉት፤ የሰው ልቡናና ሞራል ባለቤት አጡ፡፡
መንግሥትም ቢሆን ሕግ ያወጣል፣ ያስከብራል እንጂ የሰውን አእምሮ ሊቆጣጠርና ሊከታተል አይችልም፡፡ መንግሥት ከኅሊናና ከልቡና ውጭ ነው፡፡ ያማ ባይሆን የታሠሩ እሥረኞች ኅሊናቸውንም ማሠር በተቻለ ነበር፡፡ አካላቸው ወኅኒ ሲቀመጥ ኅሊናቸው ግን ‹በንፋስ ትከሻ ተጭኖ አየረ አየራቱን ይዋኛል›፤ ልቡናቸውም ወደላይ ወደ ፈጣሪ ይደርሳል፡፡ አንድን ሰው አካሉን እንጂ ኅሊናና ልቡን ማሠር አይቻልም፡፡ አካልን እንጂ ኅሊናና ልቡን መቅጣትም አይቻልም፡፡
እስካሁን በምድር ላይ ሰዎች የፈጠሯቸው ሥርዓቶችም ሆኑ ቴክኖሎጂዎች ሥጋን እንጂ ኅሊናን የሚገዙ አይደሉም፡፡ ሰውን በመድኃኒት እንዲወፍርና እንዲከሳ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሰውን በምንም ቁሳዊ ነገር ሃሳቡን እንዲለውጥ ማድረግ ግን አይቻልም፡፡ እንዲያውም ሰው አምባገነኖችንና በሃሳብ ልዕልና የማያምኑትን እንዲሸውድ ያደረገው ይህ ችሎታው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰው ውስጡን ውጩ እንዳይገልጠው ማድረግ ይችላልና፡፡ በመሪና በገዥ መካከል ያለውን ልዩነት የፈጠረውም ይህ ነው፡፡ መሪ ኅሊናን፣ ገዥ ሥጋን ብቻ ይገዛሉ፡፡
አሁን እየታየ ያለው ነገር ዓለም ከፍተኛ የኅሊናና የልቡና ኪሣራ ላይ መሆንዋን ያሳየናል፡፡ ቁሳዊ ዕድገቷ እስካሁን የነበረውን ኅሊናና ልቡና ተጠቅሞ እዚህ ደረጃ ደረሰ፡፡ ቁሳዊ ዕድገቱ ሲመነጠቅ ግን ኅሊናዊና ልቡናዊ ዕድገቱ ባለበት በመቆሙ፣ እንዲያውም ወደ እንስሳነት እንዲወርድ በመደረጉ አሁን ዓለምን ከኪሣራዋ ማዳን አልተ ቻለም፡፡ ቁሳዊም ዕድገቷ አሁን ባላት ኅሊናና ልቡና ከዚህ በላይ አይሄድላትም፡፡ ለዚህም ነው የዓለምን የኢኮኖሚ ቀውስ መፍታት ያልተቻለው፡፡ የኢኮኖሚ ቀውሱ በኢኮኖሚ አስተሳሰቦች ብቻ ሳይሆን ኅሊናዊና ልቡናዊ ብርሃን ባላቸው አስተሳሰቦች ጭምር ሊፈታ ስለሚገባው፡፡
ከሰው ልጅ ሕይወት ኅሊናና ልቡና በመራቃቸው በመግደል የሚደሰቱ፣ ያለ ተፈጥሯቸው በሚኖር ተራክቦ የሚረኩ፣ የሰውን አካል በመቸብቸብ የሚከብሩ፣ የጥፋት ነጋዴዎች እንዲበረክቱ አድርጓቸዋል፡፡ ዓለም ከዘመናት በፊት በኋላ ቀርነት ውስጥ ሥልጣኔን ትታትር ነበር፡፡ እናም ሥልጣኔ ረትቶ ኋላ ቀርነት ተሸነፈ፡፡ አሁን ግን በሥልጣኔ ውስጥ የሚታትር ድብቅ ኋላ ቀርነት እየታየ ነው፡፡ ምንጊዜም ደግሞ የተደበቀ ያሸንፋል፡፡
በእኛ ሀገር እንኳን በልጆችና በእኅቶች ላይ የሚፈጸሙት አደጋዎች መብዛት የኛም ማኅበረሰብ ከልቡናዊነትና ከኅሊናዊነት እየወረደ መሆኑን እያመላከተን ነው፡፡ ሰዎች በጎ ሠሩ የሚለውን የእምነት ሰዎች ታሪክ ንቆና አቃልሎ የተወው ትውልድ፣ ሰዎች ሲጋደሉና ‹መግደል ያባቴ ነው› ብለው ሲፎልሉ የሚያሳየውን የመገዳደል ፊልም ያደንቃል፡፡ ለእርሱም ጀግኖቹ እነዚያ በፊልሙ ላይ ያያቸው የእሩምታ ተኩስ የሚነሠንሱት ናቸውና እርሱም ‹እኔም እንዳይዬ› ብሎ እየወጣ በሕጻናቱ ላይ ቢነሰንሰው ምን ይገርማል?
በተለይ ደግሞ ‹ከለማበት የተጋባበት› ይብሳልና ምዕራባዊውን የኑሮ ዘይቤ እንዳለ በሚገለብጥ ማኅበረሰብና፣ እርሱንም እንደዘመናዊነት በሚቆጥር ሕዝብ መካከል ችግሩ ከዚያኛውም የባሰ ይሆናል፡፡ እናም ዓለም ከወረደችበት ሥጋዊ ጠባይ ከፍ ብላ ኅሊናዊና ልቡናዊ ጠባዮቿንም እንደገና ገንዘብ ካላደረገች ማንም ነሽጦት የተነሣ ሁሉ ዛሬ ጥይት እንዳርከፈከፈው ሁሉ፤ ነገ የነሸጠው መሪ ኑክሌርን ቢያርከፈክፍብን የማን ያለህ እንላለን፡፡
ማስተዋሻ
ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

44 comments:

 1. ዓለም ይፈራችኋል እንጂ አትፈሩትም። “እምነ መንግሥት የዓቢ ክህነት” ትሉታላችሁ.............
  ............በተለይ ደግሞ ‹ከለማበት የተጋባበት› ይብሳልና ምዕራባዊውን የኑሮ ዘይቤ እንዳለ በሚገለብጥ ማኅበረሰብና፣ እርሱንም እንደዘመናዊነት በሚቆጥር ሕዝብ መካከል ችግሩ ከዚያኛውም የባሰ ይሆናል፡፡

  ReplyDelete
 2. ሥጋው በመብላትና በመጠጣት፣ በመልበስና በመዋብ፣ በመተኛትና በመንቃት፣ ጤናውን በመጠበቅና በስፖርት፣ በመወለድና በመሞት ይረካል፡፡ ይህ ግን በአብዛኛው ከእንስሳትና ዕጽዋት ጋር የሚጋራውና የእነርሱ ዘውግ መሆኑንም የሚያውቅበት ነው፡፡ በአብዛኛውም እነዚህን ለማድረግ ሰው መሆን ላያስፈልገው ይችላል፡፡

  ReplyDelete
 3. ከሰው ልጅ ሕይወት ኅሊናና ልቡና በመራቃቸው በመግደል የሚደሰቱ፣ ያለ ተፈጥሯቸው በሚኖር ተራክቦ የሚረኩ፣ የሰውን አካል በመቸብቸብ የሚከብሩ፣ የጥፋት ነጋዴዎች እንዲበረክቱ አድርጓቸዋል፡፡

  ReplyDelete
 4. የሰው ነባር ባህል፣ ማኅበራዊው መስተጋብር፣ እምነት፣ ሞራልና ሥነ ምግባር አሁን ባለው ዓለም ውስጥ የሚቃለሉ፣ የሚናቁ፣ የሚተቹ፣ የሚጥላሉ ብሎም ‹በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች እየሆኑ› ነው፡፡ ዕድገትና ሥልጣኔ ማለት መንፈሳዊና ሞራላዊ፣ ባህላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን የዘነጋ፤ በሚታይና በሚዳሰስ ነገር ላይ ብቻ የተመሠረተ ዕድገት እየሆነ ነው፡፡

  በተለይ ደግሞ ‹ከለማበት የተጋባበት› ይብሳልና ምዕራባዊውን የኑሮ ዘይቤ እንዳለ በሚገለብጥ ማኅበረሰብና፣ እርሱንም እንደዘመናዊነት በሚቆጥር ሕዝብ መካከል ችግሩ ከዚያኛውም የባሰ ይሆናል፡፡

  EOTC has more than 45 mill. followers.so who is responsible for the above cries?

  ReplyDelete
 5. For me, this article is your master pice. Ejeh yibarek.

  ReplyDelete
 6. በጣም ግሩም ጽሑፍ ነው ነገር ግን መላእክት ኅሊና የላቸውም የሚለውን በመረጃ ብታስደግፈው ለኔ ጸነነኝ፣በጣም አዲስ ሆኖብኛል፣አዲስ የፍልስፍና ትምህርት ነው የመሰለኝ፣ዕውቀትካላቸ ውለምንኅኒና የላቸውም ካልከው ጋር ተጋጭቷል

  ReplyDelete
 7. እናም ዓለም ከወረደችበት ሥጋዊ ጠባይ ከፍ ብላ ኅሊናዊና ልቡናዊ ጠባዮቿንም እንደገና ገንዘብ ካላደረገች ማንም ነሽጦት የተነሣ ሁሉ ዛሬ ጥይት እንዳርከፈከፈው ሁሉ፤ ነገ የነሸጠው መሪ ኑክሌርን ቢያርከፈክፍብን የማን ያለህ እንላለን፡፡ Dani minew titerateraleh ende??????? YeFetari yaleh malet eko limadachin new, feteriachin degmo kenukler kitsbet yemeteke yemadan tibeb ena kihlot yebahriw mehonun atirsa!!! Meliaku Kidus Gebriel keminedew kezih alem esat yitadegen!!!

  ReplyDelete
 8. Monkey see, monkey do...
  ሰዎች በጎ ሠሩ የሚለውን የእምነት ሰዎች ታሪክ ንቆና አቃልሎ የተወው ትውልድ፣ ሰዎች ሲጋደሉና ‹መግደል ያባቴ ነው› ብለው ሲፎልሉ የሚያሳየውን የመገዳደል ፊልም ያደንቃል፡፡ ለእርሱም ጀግኖቹ እነዚያ በፊልሙ ላይ ያያቸው የእሩምታ ተኩስ የሚነሠንሱት ናቸውና...

  ReplyDelete
 9. የስነ ፅሑፍ ችሎታህ ‹በሎጂክ› ቢደገፍ መልካም ነው፡፡
  1. አንድን ሰው አካሉን እንጂ ኅሊናና ልቡን ማሠር አይቻልም፡፡ አካልን እንጂ ኅሊናና ልቡን መቅጣትም አይቻልም፡፡
  እዚ ጋ መሰረታዊ የሆነ ስህተት የፈፀምክ ይመስለኛል፡፡ ለሰው ልጅ ከባዱ ቅጣት የኅሊናና የልበና ቀጣት ነው፡፡እነደውም እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች አንዴ ከተጎዱ እና ከጥቅም ውጪ ከሆኑ ድጋሚ ወደነበሩበት መመለስ አይቻልም፡፡ አንዴ ካበደ ወይም በአራዶ ቋንቋ ከለቀቀ ያው ለቀቀ ነው፡፡ ሰለዚህ ለሰው ልጅ ከባዱ ቅጣት የኅልና፣ የልቦናና የምንፈስ ስብራት የሚያደርስ ቅጣት ነው፡፡ ታድያ ከዚህ በላይ እስራት ምን ትፈልጋለህ?
  የሰው ልጅ አካላዊ ቅጣት ግን እንደሁኔታው ሊመስ ወይም ሊጠግን ይችላል፡፡ በተለይ የአካል መጉደል ካልደረስ በጣም ቀላል ነው፡፡ ከግዜ ብዛትም ሊረሳ ይችላል፡፡
  በእርግጥ በቀላሉ የኅልና፣ የልቦናና የምንፈስ ስብራት የሚያደርሱ አካላዊ ቅጣቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ እስገድዶ መድፈር፣ የሚወዱት የቤተ ሰብ አባል በሰው(ግድያ) እጅ ማጣትና ለዓመታት ለፍተው ያካበቱት ንብረት ያለአግባብ መወረስ ወይም መዘረፍ እጅግ በጣም አደገኞች ናቸው፡፡በተለይም ንቃተ ኀሊናቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሰዎች እጅግ ከባድ ነው፤ የራስ ማጥፋት አደጋም ያስከትላል… ካላበደ በቀር፡፡
  2. የእምነት ተቋማት እምነትን ወደ ኩባንያ በመለወጣቸው
  የእምነት ተቋማት ድሮም ዘንድሮም ያው ናቸው፡፡ ያልነቀውን የማኅበረሰብ ክፍል ንብረትና ጉለበት መዝረፍያ መንገድ ነበሩ አሁንም ናችው፡፡የሀይማኖት ሰዎች ለዓለማችን ስይጣናዊ ትርፏቶች ተጠያቂ ናቸው፡፡ ከቀሎ ተማሪነት እስከ ጵጵስና ድረስ በልመናና የስው ንብረት በመመዝመዝ ነው የሚኖሩት፡፡ በተለይ በሃገራችን እነዚህ የእምነት ሰዎች የልመና፣ የልሰሩትን ንብረት የመዝረፍና ያለአግባብ የመበልፀግ፣ የሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ብልሽት ቀንድ ምክንያቶች ናቸው፡፡ነገስታትን ከሰው ልጆች በላይ እድርገው በስበክ ይሾሙና ይሽሩ ነብር፡፡ በሐጥያት መናዘዝ እያሳበቡ የሰዎች ምስጢር በመቀበል እንደድህንነት የሰሩና የአማንያን ስላም ያሳጡ ነበር፡፡ የደባው፣ የተንኮልና ምቀኝነት ተምሳሌቶች ነበሩ አሁንም ናቸው፡፡ ልዩነቱ አሁን ተነቅቶባቸዋል፡፡ ነገር ግን አንተም የነሱ አባል ስልሆንክ ገበናቸውን አፍረጥርጦ በማውጣት ከስህተታቸው እንዲማሩ ከማድረግ ይልቅ የድሮው አሮጌ ስርዓት ወይም ዶግማ እንዲቀጥል ተሰብካለህ፡፡
  አሁን በመገናኛ ብዙሃን አማከኝነት በዓለም የሚፈፀሙ ግፎች ጎልተው ይታዩ እንጂ በብዛትም ሆነ በአፈፃፀማቸው ከድሮው አይወዳደሩም፡፡ ድሮ ግፍ መስራት እንደ ጀግንነት፣ጥበብ፣ፅድቅ የቆጠር ነበር፡፡ አሁን ግን ብያንስ በሕግ የተከለከሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ባርነት፣ የዝርፍያ ዘመቻ፣ ሴቶችን አስገድዶ መድፈርና ጠለፋ ኀሕጋዊ ነበሩ፡፡ እንዳውም በስኬት እንዲጠናቀቁ በሃይማኖት መሪዎች ቡራኬ ይደረግላቸው ነበር፡፡

  አስተያየትህ ገቢ ብቻ መሰረት ያደረገ ባይሆን እመርጣሎሁ፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ማመዛዘን የማይችል፣ ችኩልና የጥላቻ መንፈስ ያደረበት ላለመባል ራስህ(ሽ)ን ለውጥ(ጪ)

   Delete
  2. i think ur not read clearly b4 u speak think twice ''አስተያየትህ ገቢ ብቻ መሰረት ያደረገ ባይሆን እመርጣሎሁ፡፡'' what does it means ..what about ur commante ''ገቢ ብቻ መሰረት ያደረገ አይመስልም ''
   ዲ ዳንኤል እስከዛሬ ካነበብኳቸው የተለየ ፍልስፍና ነው በጣም ገንቢና ቆንጆ ምልከታ በርታ

   Delete
  3. bahunu gize betam sewochin eyasasebe silalew guday betam awontawi behone melk yeqerebe tsihuf nw, kelay comment yaderekew anbabi kedaniel gar yegil tseb yaleh yasmesilibihal. ersu yedirshawin eyeteweta nw. sewochin bematlalatina bemesadeb lewt limeta aychilim hulachinim yeyebekulachinin awontawi astewatsio bemadreg yeteshalech alem lelijohcachin anawirs. yehaimanot abotochinim sihitet siseru megesets ayigebam bayibalim hulunim abatoch bandinet manguatet lemanim ayteqmim...

   Delete
  4. I hate this comment!

   Delete
  5. AS intellectual please be free from biasing. do all priests, pops,and....so on are responsible for the crime you listed there? please revise it. please don't generalize simply as you like. Also i think knowledge related to logic, b/c logic is based on on the objective reality, but what you raised about the logic is not compatible to the principle of logic.

   Gigaa Lakeso

   Delete
  6. hasty generalization, 1st u v 2 b logical n + thinker, may God gives u such kind of attitude, Amen

   Delete
  7. ወንጀል የሠራ ሁሉ አይጸጸትም፡፡ እንዲያውም “ከእሥር ቤት ስወጣ ያልጨረስኩትን እጨርሳለሁ፡፡” የሚሉ በርካታ ወንጀለኞች እኮ አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ዛሬ ወንጀል ሠርቶ ከሚቀጣው የማይማሩ በርካታ “ዕጩ ወንጀለኞችን“ ማየት ብርቅ ያልሆነበት፣ አረመኔ “ጀግና” ተብሎ የሚወደስበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ይህንን እያወቁ ሁሉም ወንጀለኛ የሥነ-ልቦና ቅጣት ይቀጣል ብሎ ማሰብ ምን ዓይነት “ሎጂካዊነት” ይሆን?

   Delete
  8. ‹‹ የቀደመኝ ትውልድ - ባሳብ የሰከረ
   በተራማጅ ባህል- አናቱ የዞረ
   በኢቮልዩሽን ህግ- ጠበል እየጠጣ
   ፈጣሪን ለመግጠም- ወደ ትግል ወጣ፤. . .››
   ግጥም- ስብሐት ገብረ እግዚሐብሔር http://bisrat-views.blogspot.com/

   Delete
  9. It's known you are non christian or anti orthodox. U're full of bad sprit. God be with u

   Delete
 10. Simply superb! I lack the ability to put my thoughts into words as beautifully and precisely as you do it. That's why I appreciate you, this has been going through my mind for ages. In all honesty, the world is going in the same direction thanks to globalization but more importantly because, 'ይህ አለም ጠፊና ሃላፊም ሰለሆነ ነው፧

  ReplyDelete
 11. www.yenetaliterature.blogspot.com (dear daniel please puplish this article as a comment even if it is not relative with the above article you posted)
  ቅንነት ዋጋው ስንት ነው?


  በተለያየ ጊዜ ሁለት ሚስቶች የነበሩት አርበኛ ሰው ከጠላት በተተኮሰች ጥይት በዚያን ሰሞን ሞተ።
  የመጀመሪያ ሚስቱ የቀድሞ ባልዋን ሞት መርዶ ስትሰማ ማልቀስ ቀርቶ ለወግ ያህል እንኳ ከንፈር ከመምጠጥ ቦዝና እንዲህ አለች አሉ፡-
  “ክፉ ሰው ነበር! አንድም ቀን እንኳ ከሀገሩ የተረፈ ጊዜ ኑሮት ተንከባክቦኝ አያውቅም ነበር!”
  ሁለተኛ ሚስቱ ግን መርዶውን ስትሰማ ማቅ ለብሳ ሃዘን ተቀመጠች እንዲህም አለች አሉ፡-
  “አርበኛው ባሌ ኮስታራ ነበር! አንድም ቀን ሲስቅ አይቼው አላውቅም። ለኔ የሚሆን ጊዜም አልነበረውም። ግን ስለማይወደኝ ሳይሆን ከኔ በላይ ሀገሩን ይወድ ስለነበር ነው።”
  መቼም ሰው የሀሳቡ ድምር ውጤት መሆኑ እርግጥ ነው፤ስለራሳችን ብቻ ስናስብ ዉለን ካደርን ለኛ ያልበጀን ነገር ሁሉ ጥቁርቁር ብሎ ይታየናል። ጣፋጭ ምንድነው ሲሉን ያጣጣምነውን ብቻ፣ሰማይ ጥጉ የት ድረስ ነው ሲሉን ማዶ እስከሚታየን አድማስ ድረስ ብቻ፣መጥፎስ ሲሉን እኛን ያስቀየመንን ብቻ...የራሳችንን ቋጠሮና ስልቻ ይዘን ስንዞር መሬት በፀሃይ ቀርቶ በራሳችን ዛቢያ ብቻ የምትሽከረከር ይመስለናል፤እንደ ሟቹ አርበኛ የመጀመሪያ ሚስት!
  ከሆነብን ይልቅ የሆነውን፣ካጣነው ይልቅ የየያዝነውን፣ካየነው ይልቅ ያላየነውን ለማጤን ልቦናችንን ስንከፍት ግን ወደ እውነታችን ሳይሆን በራሱ እዉነት ወደ ሆነው ነገር በግማሽ ተጠግተናል ማለት ነው። ጤናማ የሆነ ራስን መውደድ ለሌሎች ወደ መኖር ቀስ በቀስ ይገፋናል። ሁለተኛዋ የሟች ሚስት ለዚህ ሃሳብ በቂ ምሳሌ ትሆነናለች፤እርሷ ባሏን በከንቱ ውዳሴ እያነሳሳች እንባዋ እንዲወርድላት ብቻ አላሞገሰችውም ደግሞም እንደ መጀመሪያዋ ሴት ጨለምተኛ ሆና የአርበኛውን በጎ ምግባር አላጨለመችውም። ይልቁን በቀናነት ሀገሩን በመዉደዱ ውስጥ እርሷንም እንደሚወዳት ነገረችን እንጅ! ይህ እይታ
  መንፈሳዊም ሆነ ሞራላዊ ለሆነው ሰው ሁሉ የሚያስፈልግና አንዳች አወንታዊ መነሳሳትን የሚፈጥር ብሩህነት ነው።
  በእርግጥ ዛሬ ላይ ሰዎች በተለያየ ቀንበር ተይዘው፣በታመመ ፖለቲካ ተበርዘው፣በማያንሰራራ ኢኮኖሚ ተደልዘውና ከማህበራዊ ትስስር ተነጥለው ሲያዘግሙ “ቀናነት” የሚሉት ቃል የስነ-ልቦና እና የሃይማኖት ድርጅቶች ዕድሜ ማራዘሚያ ብቻ ቢመስላቸው አይፈረድባቸውም። ዛሬ ህይወት በድንጋይ ዘመን የነበረችው ህይወት አይደለችምና፤ዛሬ እዉነት ከመንፈሳዊ አጥር ወጥታለችና ‘አንፃራዊም’ ናት እንጅ ‘አንድ’ ብቻ አይደለችም፤ዛሬ እምነት ከልዕለ ተፈጥሮ እሳቤ በከፊል ተሳናክላለችና እንደ ድሮው ‘በአንድ ፈጣሪ’ ማመን በራስ እንዳለመተማመን ተቆጥሯል በራስ የማመን ሃይማኖትም ተፈጥሯል። እናም በዚህ ዘመን መገኜት በራሱ ልባቸውን መጠበቅ ለሚሳናቸው ሁሉ እድለቢስነት አሊያም ታላቅ ተግዳሮት ነው። ነገር ግን ሰብአዊ ባህሪይ ቋሚ የተፈጥሮ ስጦታ በመሆኑ ‘ሰውነት’ ከጊዜ ጊዜ አለመቀየሩ መልካም ዕድል ሊባል ይችላል።
  እንግዲህ ይህን ዕድል ህገ-ልቦና ብለን ልንጠራው እንችላለን ሰው በመሆናችን ብቻ ውስጣችን ውስጥ ያለ ቀናነት! ህፃን ብንሆን አዋቂ፣ተማሪ ብንሆን ሰራተኛ፣መሃይም ብንሆን ምሁር ልዩነት አያመጣም። በናዚ ሂትለር በአስራ አራት አመቷ በግዞት የተገደለችው አይሁዳዊቷ አና ፍራንክ በዚያ ከአዕምሮ በላይ የሆነ የሰው ልጆች ጭካኔ ውስጥ አልፋ እንኳ “ሰዎች ከመሰረታቸው ጥሩ ናቸው ብየ አስባለሁ!” ማለቷን ልብ ይሏል! እንዲህ ያለ ቅን መረዳት በ mind therapy አይገኝም!
  በደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ቃል እንጠቀምና “ልቡሰ ጥላችን” ውስጥ የተፃፈ አንዳች ህግ መኖር አለበት፤ማንም ሰው የትም ይወለድ የትም ይደግ መግደል ልክ እንዳልሆነ ያለ ህገመንግስቱ ከልካይነት እንዲሁ ያውቃልና!
  አሁን ጥያቄው ታድያ ለምን? የሚለው ነው። ለምን? እንደ መጀመሪያዋ አአርበኛው ሚስት ክፉውን ብቻ የሚያዩ ሰዎች ለምን በዙ? ከተፈጥሮ ስርዓት ውጭ ልቦናችን ላይ የተፃፉ ሰው ሰራሽ መገለጫዎቻችን ለምን እስኪያጎብጡን እንዲጫኑን ፈቀድን? ለምን? የሁለተኛዋ ሴት አይነት ቀናነት ሊጠፋ ጫፍ ደርሶ እንደ ብርቅየ እንስሳቶቻችን ልንታደገው አልቻልንም? ብዙዎቻችሁ ታክሲ ላይ “ቅን መሆን ዋጋ የማያስከፍል ከሆነ ለምን ክፉ እንሆናለን?” የሚል ጥቅስ አይታችሁ ይሆናል። ተራና ለመፃፍ ብቻ የሚቀል የተለመደ አባባል ይመስላል ነገሩ ግን ወዲህ ነው የዚህ ጥቅስ ፀሃፊ ምናልባትም ስሙ “ብሩክ” የሚባል ልጅ ቅን መሆን ዋጋ እንደሚያስከፍል ጠፍቶት ሳይሆን ከሚያስገኘው የህሊና ሰላም አንፃር ኢምንት እንደሆነ ተረድቷል ማለት ነው። እርግጥ ነው ከላይም ለማለት እንደተሞከረው አንዳንድ ለመናገር የሚቀሉን ግን ስንኖራቸው የሚገዝፉብን ነገሮች ልክ ቁጭ ብለን ስንሰቅላቸው ቆመን ለማውረድ የምንቸገር የማይመስሉን እውነታዎች ይኖራሉ ቢሆንም ቅሉ “ቅን እንጅ ቅንቅን አትሁን!” አይነት ብሂሎች የቃላት “ኩመካ” ቢመስሉንምና አንፈፅማቸው ነገር ዳገት ቢያክሉም፣
  ቢመርም ጣዕም ነው ብሎ መቀበል የማንሰራራት ምልክት መሆኑ ማሰብ ብቻ በቂ ነው!
  መቼም ቢሆን ህይወትን ከከበደችው በላይ ያከበዳት ጨለምተኛ አስተሳሰባችን ለመሆኑ የውጭ ተንታኝ ያስፈልገን አይመስለኝም። ያ ለምን ሆነ የኋላ ታሪካችን በጥልፍልፍ የተሞላ፣በሸፍጥ የተተበተበና በጦረኛ አስተሳሰብ የተመረዘ ከመሆኑ አንፃር ሊቃኝ ይችላል የሃውልት ብቻ ሳይሆን የባህርይም ውርስ እንዳለ መዘንጋት የለብንም! በቀላሉ መረዳት ስንችል እልህ ይዞን ያጣነው ወዳጅነት እስከመቼ ያንገብግበን?
  አንዲት ጥቁር አሜሪካዊት የፊልም ተዋናይት በጋዜጠኖች የቀረበላት ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር።
  “ሆሊውድ ውስጥ ካሉት ጥቂት ለትዳራቸው ታማኝ የሆኑ ሰዎች አንዷ አንቺ ነሽ ከባለቤትሽ ጋር አንድም ጊዜ ተጋጭታችሁ አታውቁም ይባላልና ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?”
  “እኔም ሆነ ባለቤቴ ልክ መሆንን አይደለም የምንፈልገው አንዳችን ሌላኛውን መረዳትን (understanding) እንጅ! ያ ሲሆን ስህተቱም ልክ ይሆናል ለምሳሌ እኔ ባሌ ተሳስቶም ቢሆን ልረዳው እሞክራለሁ እሱም እንደዛው ስለዚህ እንዴት ግጭት ሊኖር ይችላል?” በማለት ተዋናይቷ መለሰችላቸው። እንዲህ ለማሰብ የግድ ሆሊውድ መንደር ውስጥ መኖር ወይም የስነ-ልቦና ተንታኝ መሆን አያስፈልግም። በቀላሉ ያዳፈነውን ህገ-ልቦናችንን መቆስቆስና ተፈጥሮ የሰጠችንን እዉነተኛ ባህሪ መግለጥ እንችላለን! ያን ስናደርግ ነው ቀንበር የጣለችብን አድራሻ የሌላት ህይወት ህይወት እያልን የምንጨቀጭቃት አካል ሳትሆን ራሳችን በራሳችን ላይ እንደነበር የሚገባን! ... ሁላችንንም የተሰጠንን እንድናይ ያድርገን! ሻሎም።

  ReplyDelete
 12. What the so called kib said was by itself kib(circle). I think u kib are educated,but not intellectual as to me, because intellectuals will never go to hasty generalization as what u did.I think u know nothing about logic, b/c logic is based on the objective reality.But u drove away from the reality by simply mixing things here and there. do all spiritual persons say priests, pops,pastors,... and so are responsible for the crimes u listed above? please revise it, read and read more bro.

  For Danni i appreciate ur way of teaching peoples on this blog.B/c u did not respond for every nonsense messages u received, this is a really intellectual way. B/c it is not expected from u to throw a stone on every barking of the dogs.

  Sodo wolaita

  ReplyDelete
 13. ለካ ይሔም አለ።

  ReplyDelete
 14. D Daniel Kibret
  Absolutely True , well explained
  May GOD bless u bro.
  እዚህ ላይ እንደ ሰው ቆም ብለን መመርመር ያለብን ይመስለኛል፡፡ ዓለም አሁን በየትኛው የአስተሳሰብ ጎዳና ላይ ናት? የሚለውን፡፡ እንደ እኔ ዓለም አሁን ለቁሳዊ ነገርና ለቁሳዊ ዕድገት ታላቅ ቦታ የሰጠችበት ጊዜ ላይ ናት፡፡ የሰው ልጅን ሞራላዊና መንፈሳዊ እሴቶች የቀረጹት፣ ከሰው ጋር ተዋሕደው ህልው እንዲሆኑም ያደረጉት ተቋማት፣ ግለሰቦችና አስተሳሰቦች እየቀሩ፣ እየተረሱ፣ እየፈራረሱና፣ ቅርጻቸውንና ማንነታቸውንም እየቀየሩ፣ የሰውን ልጅ ቁስ ብቻ እንዲሆን አጋልጠው የሰጡት ይመስላል፡፡
  የሰው ነባር ባህል፣ ማኅበራዊው መስተጋብር፣ እምነት፣ ሞራልና ሥነ ምግባር አሁን ባለው ዓለም ውስጥ የሚቃለሉ፣ የሚናቁ፣ የሚተቹ፣ የሚጥላሉ ብሎም ‹በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች እየሆኑ› ነው፡፡ ዕድገትና ሥልጣኔ ማለት መንፈሳዊና ሞራላዊ፣ ባህላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን የዘነጋ፤ በሚታይና በሚዳሰስ ነገር ላይ ብቻ የተመሠረተ ዕድገት እየሆነ ነው፡፡ የፎቆች ብዛት፣ የመንገዶች ርዝመት፣ የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የመገናኛ መንገዶች መወሳሰብ፣ የጤናና ማኅበራዊ ተቋማት መስፋፋት፣ ሀብት መፍጠርና ማካበት ብቻቸውን የዕድገት ማሳያዎች እየሆኑ ነው፡፡

  ReplyDelete
 15. anten yaberketelen, enamesegnalen!

  Mamush,MN

  ReplyDelete
 16. It would be great if you focus your writing about the turmoil in our church.The Ethioian Orthodox Church is under fierce attack by insiders and outsiders. There is a moral void among the leadership of EOTC. When the highest spiritual leaders don't live as good examples, one cannot be surprized by acts of some disturbed people.

  Please focus on the need for Unity and Peace in your church first.

  ReplyDelete
 17. anten yaberketelen, enamesegnalen!

  ReplyDelete
 18. ሰው መኖርን ከቁስ ነገር ጋር ብቻ ስላያያዘው የሚኖረው በዕድሜው ልክ ብቻ ሆኗል፡፡ ሰው ኅሊና ካለው ግን ከዕድሜው በላይ ይኖራል፡፡ ከዕድሜ በላይ ለመኖር ደግሞ ከዕድሜ በላይ ማሰብ ይገባል፡፡

  ReplyDelete
 19. አበበ ሙ በየነDecember 31, 2012 at 9:18 AM

  ወንድሜ ዳንኤል ለመልካም ዕይታህ እግዚአብሔር ይስጥህ::

  የሰዉ ልጅ ከቁሳዊ አስተሳስብ ተላቆ በህሊናው ካልተመራ ስስቱ ይበዛና አዉሬ ይሆናል:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነመንግስት እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርቴን ስከታተል አንድ የማከብራቸዉ ግራ ዘመም መምህሬ ሶሻሊዝም ዉጤታማ ያልሆነው ሰዉኛ ሰዉነት ላይ በማተኮሩ ሲሆን ካፒታሊዝም ወይንም እምፔርያሊዝም አሁን በአለማችን ላይ ገንኖ የሚታይበት ምስጢር እንስሳዊ ሰዉነት ላይ ስለአተኮረ ነው ይሉን ነበር::

  እንግዲህ ቁሳዊነት ግለኝነትን: ስስትን:ማጨበርበርን: እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ዉድድርን እና መሰል ሁኔታዎችን መጋበዙ አይቀሬ ያደርገዋል:: በዚህ በተጠላለፈ ማህበረሰብ የአደገ እና የተጉዋዘ ትውልድ ደግሞ የጨዋታው ሕግ በሚያዘው መሰረት ሊጉዋዙ ግድ ይለዋል::

  ጥሎ ለማለፍ በሚደረገው ትንቅንቅ አንዱ አንዱን ጨፍልቆ ማለፉም የጨዋታዉ ሕግ ነዉና እርስበርስ መባላቱ ይቀጥላል:: ይህ ሁኔታም ፍትሃዊ ወደአልሆነ የሀብት ክፍፍል ይወስዳል:: ፍትሃዊ ያልሆነው የሀብት ክፍፍልም በሰዎች ህሊና ላይ ጠባሳ መጣሉ አይቀሬ ነው:: ለምን እኔ ብቻ የሚል ጥያቄ ያስነሳና ወደ እንስሳዊ ሰዉነት ያሸጋግረናል::

  በአሜሪካ ኮነትኬት በቅርቡ የተፈፀመው በትምህርት ቤት ላይ የተደርገው የሕፃናት ጭፍጨፋ የዚሁ ድምር ዉጤት ይመስለኛል:: አጥፍቶ ጠፊው እናቱን ጨምሮ ነፍስ ያላወቁ ጨቅላ ሕፃናትን ገድሎ እራሱም ከሞት ተቀላቅሎአል::

  የግድያዉ መላምት እንደሚያሳየው ገዳዩ እናቴ ከኔ አስበልጣ የምታስተምራቸዉን ሕፃናትን ትወዳለች የሚል እንስሳዊ ባህሪ ተላብሶ ለምን እኔ ወደጎን ተገፋሁ በሚል ያንን የመሰለ ግፍ በጠራራ ፀሐይ ፈፀመዉ::

  ስለዚህ እንደእኔ አስተሳስብ ቁሳቁስ ስጋን እንጂ መንፈስን ወይንም ሕሊናን አያረካም:: በመሆኑም ለስጋም ለነፍስም መኖር ያስፈልጋል እላለሁ:: ከሁሉም በላይ በህሊናችን የምንመራ ሰዎችም ያድርገን::

  መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ: የደጋጎች አባት አናቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን

  ReplyDelete
 20. Dn.Daniel, Thanks a lot! what a wonderful observation. As it is well explained on your article, most countries/Nations don't invest in building 'Bego Hilina and bego libona' for their citizens, rather they focus in building good material world for them.I got a chance to see this reality,i.e focusing building material world here in US and some Asian countries.

  Dani, i thought we, Ethiopians, has to learn from others and be prepared to build our country both on Material world and with 'Bego hilina and Turu libona'

  Let Emebirihan tiridan!! Thanks a lot !!

  ReplyDelete
 21. I give Glory to God he give you for us

  ReplyDelete
 22. Dear bro.
  Melkam Eyta

  ReplyDelete
 23. alem gebregziabiher(mekelle)January 1, 2013 at 11:28 AM

  u r right ma bro.i learn d/t interesting things from what u posted...10q dani!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 24. It is nice.Dani,the one who is illuminating light into the dark corners of Ethiopians inside and Overseas.

  ReplyDelete
 25. እናም ዓለም ከወረደችበት ሥጋዊ ጠባይ ከፍ ብላ ኅሊናዊና ልቡናዊ ጠባዮቿንም እንደገና ገንዘብ ካላደረገች ማንም ነሽጦት የተነሣ ሁሉ ዛሬ ጥይት እንዳርከፈከፈው ሁሉ፤ ነገ የነሸጠው መሪ ኑክሌርን ቢያርከፈክፍብን የማን ያለህ እንላለን

  ReplyDelete
 26. እነዚያ በዘጠና ደቂቃ በኢንተቬ፣ ካርቱም ሄዶ ቀረ፣ የኛ ሰው በደማስቆ፣ የስድስቱ ቀን ጦርነት በሚሉት መጻሕፍት ያነበብናቸው ለሀገራቸው የሚብከነከኑ እሥራኤላውያንኮ ዛሬ የሉም፡፡ ‹ለምን ከፊሊፒን ወታደር አንቀጥርም› የሚሉ እሥራኤላውያን ትውልዶችኮ መጥተዋል፡፡ this sounds great!

  ReplyDelete
 27. መንግሥት ከኅሊናና ከልቡና ውጭ ነው፡፡ ያማ ባይሆን የታሠሩ እሥረኞች ኅሊናቸውንም ማሠር በተቻለ ነበር፡፡ አካላቸው ወኅኒ ሲቀመጥ ኅሊናቸው ግን ‹በንፋስ ትከሻ ተጭኖ አየረ አየራቱን ይዋኛል›፤ ልቡናቸውም ወደላይ ወደ ፈጣሪ ይደርሳል፡፡

  ReplyDelete
 28. thank you Dn. dani

  ReplyDelete
 29. Geta libonachinin ena hilinachinin chimir endinitekem yirdan.
  Egziabher Yibarkih!

  ReplyDelete
 30. ይህ አስተያየቴ የመጀመራዮ ነው ብዙ የተማረኩባቸው ጽሁፎች አሉ የአሁኑ የበለጠ ማረከኝ….አስተማረኝ…አለም ይህን ሲያነብ ምን ይል ይሆን ተክለ መድህን ከድራ

  ReplyDelete
 31. Thanks for mentioning this idea! This world is nonsensical because including me we are becoming greedy . We suddenly stoped caring and became a killer of inoccent kids. Let God shorten this suffering and bless us!

  ReplyDelete