በአሜሪካዋ ኮኔክቲከት ግዛት በሳንዲ ሁክ ትምህርት ቤት ሕጻናትና መምህራን ላይ
የተፈጸመው ኢ ሰብአዊ ግድያ ሰሞኑን የዓለም መነጋገርያ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ጉዳዩን አሳዛኝና አሰቃቂ ያደረገው
ደግሞ ምንም በማያውቁ ሕጻናትና በሥራ ላይ በነበሩ መምህራን ላይ የተፈጸመ መሆኑ ነበር፡፡ እነዚህ አካላት ከገዳዩ ጋር ምንም
ዓይነት ‹ጠብ ወይም ዝምድና› የሌላቸው፣ ለዚህ ቀርቶ ለቁጣ እንኳን የሚያበቃ ጥፋት በአጥፊው ላይ ያልፈጸሙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን
ይህ ሁሉ ሕይወታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከማጣት አልታደጋቸውም፡፡
ምንም በማያውቁና በራሳቸው ዓላማ ምክንያት ተሰባስበው በሚገኙ ወገኖች ላይ የተኩስ
እሩምታ እየከፈቱ ሕይወትን መቅጠፍ አሁን አሁን በዓለማችን እየተለመደ የመጣ ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኖርዌይ ሀገሪቱን
ጸጥ ያሰኘ ግድያ በአንዲት ደሴት ተሰባስበው በነበሩ ተማሪዎች ላይ ተፈጽሞ ነበር፡፡ እምብዛም ይህን መሰል ወንጀል በማይሰማባት
ቻይና እንኳን ሳይቀር በትምህርት ቤት ሕጻናት ላይ እሩምታ መክፈት እየተለመደ መምጣቱን የሚያሳዩ ድርጊቶች ብቅ እያሉ ነው፡፡