አሜሪካን ሀገር ወደሚኖሩ ወዳጆቼ ቤት ሄጄ
ነበር፡፡ ከተጋቡ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ቤታቸው ስገባ የቤቱም ዕቃ የቤቱም ሰዎች ዝምታ ውጧቸዋል፡፡ አባ አጋቶን ቤት
የገባሁ ነው የመሰለኝ፡፡ እርሱ ክፉ ላለመናገር ሰባት ዓመት ድንጋይ በአፉ ጎርሶ በአርምሞ ተቀምጧል፡፡ ነገር ዓለሙ አላምር
ሲለኝ ‹ምነው ያለ ወትሯችሁ ዝምታ ዋጣችሁ› ብዬ ተነፈስኩ፡፡ እዚህ ቤት የነበረውን ሳቅና ጨዋታ ስለማውቀው፡፡ ‹ሳቅና ጨዋታ
ዝና ካማራችሁ› ሲባል አልሰማችሁም፡፡
የመለሰልኝም የለ፡፡
በኋላ ነገሩን ሳጠናው ሁለቱም ተኳርፈዋል
ለካ፡፡ ‹‹ለመሆኑ እንዲህ ሳትነጋገሩ ስንት ጊዜ ተቀመጣችሁ› ብዬ ስጠይቅ ስድስት ወር ሆኗቸዋል፡፡ ሁሉም በየሥራው ይውላል፤
ማታ ይመጣል፤ ኪችን ገብቶ ያበስላል፤ በልቶ ቴሌ ቭዥን ያያል፤ ከዚያም ይተኛል፡፡ ቢል ሲመጣ ይህንን እኔ ከፍያለሁ ብሎ አንዱ
ወረቀት ጽፎ ይሄዳል፤ ሌላው በተራው ይከፍላል፡፡ ይቺ ናት ትዳር፡፡
ድሮ የሰማሁትን ቀልድ ነበር ትዝ ያሰኙኝ፤
ባልና ሚስቱ ተኳርፋው አይነጋገሩም አሉ፡፡ ቤቱ እንደ መቃብር በጸጥታ ተውጦ ከርሟል፡፡ አንድ ቀን ባል ሌሊት አሥር ሰዓት
የሚነሣበት ጉዳይ ገጠመው፡፡ ከተኛ መነሣት የሚከብደው ቢጤ ነበርና የመቀስቀሻውን ሰዓት ሊሞላ ሲስበው ተበላሽቷል፡፡ አዘነም፤
ተናደደም፡፡ ምን ያድርግ፡፡ ባለቤቱ ገና ከሥራ አልገባችም፡፡ ‹የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይመርጡ› ነውና፡፡ በቁራጭ ወረቀት
ላይ ‹አሥር ሰዓት ላይ ቀስቅሽኝ› ብሎ ጽፎ በራስጌው ባለው ኮመዲኖ ላይ አስቀመጠና ተኛ፡፡
ሚስቱ ስትመጣ አየችውና ስቃ ተኛች፡፡ ልክ
ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ነቃችና በዚያው በቁራጭ ወረቀት ላይ ‹አሥር ሰዓት ሆኗልና ተነሣ› ብላ ጽፋለት ተኛች፡፡ እርሱ ዕንቅልፉን
ለጥጦ ለጥጦ ሲነሣ ነግቷል፡፡ ተናደደ፤ ግን እንዳይናገራት ለካስ ተኳርፈዋል፡፡ እዚያው ወረቀት ላይ ‹በጣም ታሳዥኛለሽ› ብሎ
ጻፈላት፡፡
እነዚህ ወዳጆቼ ይህን ነበር ያስታወሱኝ፡፡
አሁን እንዲህ ያለው ኑሮ ምን ዓይነት ኑሮ ይባላል? ብዬ ስም ፍለጋ ብዙ ጊዜ አሰብኩ፡፡