Tuesday, October 23, 2012

‹ሲኖዶስ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም›

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣይ ዘመናት የሚመራውን አባት የመምረጡ ታላቅ ሥራ ቅዱስ ሲኖዶሱን ከገጠሙት የዘመናችን ተግዳሮቶች ዋናው ነው፡፡ ይህንን ተልዕኮ ከተግዳሮቶቹ ሁሉ ዋናው የሚያደርጉት አራት ምክንያቶች ናቸው፡፡
የመጀመርያው በአራተኛውና በአምስተኛው ፓትርያርኮች መካከል በተደረገው ሽግግር በተፈጠሩ ወቅታዊና ቀኖናዊ ጉዳዮች ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት ‹ሲኖዶሶችን› ያስተናገደችበት ዘመን ላይ የሚደረግ ምርጫ መሆኑ ነው፡፡ በሀገር ቤትና በውጭ ባሉት አባቶች መካከል እየተከናወነ ባለው የዕርቀ ሰላም ሂደት ውስጥ ዛሬም በሕይወት ያሉት የአራተኛው ፓትርያርክ ዕጣ ፈንታ ቀጣዩን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰላማዊና መንፈሳዊ ብሎም ቀኖናዊ ጉዞ የሚወስነው ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድም አራተኛውን ፓትርያርክ ወደ መንበር ትመልሳለች፣ ያለበለዚያም አራተኛውን በጸሎት ወስና በእንደራሴ ትቀጥላለች፣ ያለበለዚያም ስድስተኛውን ትመርጣለች፡፡ 
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኅብረተሰቡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በንቃትና በቅርበት በሚከታተልበት ጊዜ የሚከናወን ሂደት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተደረጉት የፓትርያርክ ምርጫዎች የሕዝብን በቂ ክትትል ለማግኘት ዕድል አልነበራቸውም፡፡ በአንድ በኩል የመገናኛ አውታሮች እንደልባቸው ያለመሆን፣ በሌላም በኩል ሕዝባችን አስቀድሶ ከመሄድ ባለፈ የቤተ ክህነቱን ጉዳይ ለቤተ ክህነት ሰዎች ብቻ የተወበት ዘመን ስለነበር ምርጫዎቹ የሕዝብን በቂ ትኩረት አላገኙም ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የስብከተ ወንጌል መስፋፋቱና የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የሚዘግቡ ሚዲያዎች መብዛት የፓትርያርክ ምርጫው ጉዳይ ትኩረት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ በመረጃ መረብ እንኳን ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚዘግቡ 26 ብሎጎችና ከስድስት በላይ ድረ ገጾች አሉ፡፡
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ባለፉት ፓትርያርክ ዘመን የተሠሩና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማንነት፣ ትምህርትና ደረጃ ጋር የማይሄዱ ተግባራት ለሕዝብ ይፋ ሲሆኑ መቆየታቸውና ማኅበረሰቡ የስድስተኛው ፓትርያርክን ምርጫ ያለፉት ችግሮች የማይደገሙበት እንዲሆን መፈለጉ ነው፡፡ በጳጳሳት ምርጫ፣ በአስተዳዳሪዎች ሹመት፣ በገንዘብ ምዝበራ፣ የቤተ ክህነቱ በወይዛዝርት ተጽዕኖ ሥር መውደቅ፣ በስብከተ ወንጌል መድረኩ ላይ ይሰሙ የነበሩት ሌሎች ድምጾች፣ የሐውልት መሠራት፣ በየቦታው ይነሡ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት አለመፈለግ፣ የአንዳንድ አባቶች ባልተጠበቀና ባልታሰበ ሁኔታ ማለፍ፣ ወዘተ ሕዝቡ በቤተ ክህነቱ ላይ እንዲያመርር አድርጎታል፡፡ ቀጣዩ ፓትርያርክ እነዚህን ችግሮች የሚያርሙና የሕዝቡን የተሰበረ ልብ የሚጠግኑ እንዲሆኑ የመፈለግ ከፍተኛ ጉጉት አለ፡፡
አራተኛው ምክንያት ይህ ሂደት በተለያዩ አካላት ግፊትና ተጽዕኖ እየደረሰበት ያለ መሆኑ ነው፡፡ ከሰሞኑ እንደሚሰማው ራሳቸውን በየጎራው ያደራጁ አካላት እነርሱ የሚፈልጉትን አባት ለማስመረጥ በሲኖዶሱ ላይ ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ፖለቲካን፣ ዘርንና ጥቅምን አንድ አድርገው የተቧደኑት እነዚህ አካላት ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን ሳይሆን ለእነርሱ የሚጠቅማቸውን አባት ለማምጣት ያስኬዱናል ያሏቸውን ነገሮች ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ተራው የኛ ነው የሚሉ፣ በሌላ በኩል ሙስናውና ዘረፋው እንዲቀጥል የሚፈልጉ፣ በሌላም በኩል ‹በስሜ ይመጣሉ› እንደተባለው በመንግሥት ስም የሚነግዱ ኃይሎች ምርጫውን በሚፈልጉት መንገድ ለመጠምዘዝ በመትጋት ላይ መሆናቸውን የቤተ ክህነቱ ምንጮች እያመለከቱ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ቀጣዩ የፓትርያርክ ‹ምርጫ› ሦስት ነገሮችን የሚያሟላ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት የሚያስጠበቅ፣ ያለፉትን ችግሮች ለመፍታት መንገድ የሚከፍት እና የሕዝቡን አመኔታ የሚያገኝ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ቀጣዩ ፓትርያርክ ምርጫ ሲያስብ የመጀመርያው ነገር ምርጫው የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት የሚያስጠብቅ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ ችግሩ ከተፈጠረ ሃያ አንድ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዚህ መካከል ችግሮች ሲፈጠሩ በአካል የነበሩት፣ ጉዳዩን የሚያውቁትና የጉዳዩም ዋና ዋና ተዋንያን በሞት እየተነጠቁ በመሄድ ላይ ናቸው፡፡
ከሁለቱ ዋና ዋና አካላት መካከል አምስተኛው ፓትርያርክ ዐርፈዋል፣ አራተኛው ፓትርያርክም በጤና እክል ላይ ናቸው፡፡ ከችግሩ መፈጠር በኋላ ዐቃቤ መንበር የነበሩት አቡነ ዜና ማርቆስ ዐርፈዋል፤ ችግሩ ሲፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ታምራት ላይኔ ሌላ መሥመር ውስጥ ገብተዋል፣ በዚያ ወቅት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስም (ነፍሳቸውን ይማርና) አርፈዋል፡፡ ከወዲህ ወገንም በዚያ ዘመን ከነበሩት አበው መካከል ቢያንስ ወደ ስምንት የሚጠጉት ዐርፈዋል፤ በወዲያ በኩልም አቡነ መልከ ጼዴቅና አቡነ ኤልያስ አርጅተዋል፡፡
በመሆኑም ከዚህ ወቅት የተሻለ ችግሩን የመፍቻ ጊዜ አይኖርም፡፡ የኬልቄዶንን ጉባኤ ችግሮች ለመፍታት በዓለም ዐቀፍ ደረጅ ከሃምሳ በላይ ጉባኤያት በየዘመናቱ ተካሂደዋል፡፡ ችግሩን በመፍታት ረገድ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ፍላጎቱ ቢኖርም ሦስት ምክንያቶች ግን እንቅፋት ሆነዋል፡፡ የመጀመርያው ስለ ጉባኤው የተጻፉት መረጃዎች በየወገኑ የተጻፉ መሆናቸው፤ ሁለተኛው ችግሩ በ450 ዓም ከተፈጠረ በኋላ 1600 ዓመታት ማለፋቸውና ጉዳዩ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ታሪክ፣ ጸሎት፣ ሥዕል፣ ገድላትና ድርሳናት ውስጥ የገቡ በመሆናቸው እነዚያን ሁሉ ዶክመንቶች እንደገና መከለሱ ከባድ መሆኑ፣ ከዚያም በላይ ደግሞ ውግዘቱን ያወገዙት አበው ዛሬ በዐጸደ ነፍስ በመሆናቸው የእነርሱን ውግዘት ማንሣቱ አስቸጋሪ መሆኑ ናቸው፡፡
ነገሮች በጊዜያቸው ካልተፈቱና ባለቤቶቹ ዐልፈው መዛግብቶቹ ብቻ ከቀሩ ነገሮችን ወደ መጀመርያቸው ሁናቴ መመለስ በተለይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከባድ መሆኑን ጉባኤ ኬልቄዶን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጉዳዩ የነበሩበት አካላት ፈጽመው ከመለየታቸው በፊት፣ ችግሩም ወደ ሁለተኛ ትውልድ ከመሻገሩ በፊት ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ ችግሩን መፍታቱ ከምንም የተሻለ የሚሆነው፡፡
በርግጥ ይህ ሂደት ሁለት ነገሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በአንድ በኩል በሚደረገው የዕርቅና የአንድነት ሂደት የሚስማሙትንና በተከፈተው በር ለመግባት ፈቃደኛ የሆኑትን ተቀብሎ ለሁሉም በሚስማማ፣ ይበልጥም ቤተ ክርስቲያንን በሚጠቅም መንገድ ችግሩን መፍታት፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍም ሆነ ከሂደቱ በተቃራኒው ለመጓዝ የሚሹትን አካላትም ‹እንደ አረማዊና ቀራጭ ይሁንልህ› በሚለው መሠረት በውግዘት መለየት ናቸው፡፡
ሲኖዶሱ የሚደርሱበትን ተጽዕኖዎች መቋቋም ካሉበት ምክንያቶች አንዱም ለዚህ ሀገራዊም፣ ታሪካዊም፣ ቀኖናዊም ነገር ሲል ነው፡፡ ዕርቅና ሰላም ሁለት ነገር ይጠይቃል፤ ጊዜና ቻይነት፡፡ ሲኖዶሱም ይህንን ታሪካዊ ሥራ ለመሥራት ጊዜና ቻይነት ያስፈልገዋል፡፡ ከየአቅጣጫው ተጽዕኖዎች ይኖራሉ፡፡ በዕርቁ ቤተ ክርስቲያን እንደ ምትጠቀመው ሁሉ በዕርቁ ጥቅማቸው የሚነካ አካላትም ይኖራሉ፡፡ ስለዚህም ትንንሾቹን ሥዕሎች ሳይሆን ትልቁን ሥዕል በማየት የሚከፈለውን መሥዋዕትነት ከፍሎ ችግሩን ለመፍታት መትጋት ይኖርበታል፡፡
በአንድ በኩል የተጽዕኖዎቹ መኖር መልካም ነው፡፡ ተጋድሎ ማሸነፍን፣ በአስጨናቂ ሁኔታዎች ውስጥ መሥራትንና ፈተናን ማለፍን እንማርበታለን፡፡ ችግሮች ላወቀባቸው አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ማጠናከርያዎች ናቸው፣ የበረከት ምንጮችም ናቸው፡፡
የቀጣዩ ፓትርያርክ ምርጫ አንድን አባት ከአባቶች መካከል መምረጥ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ያለፉት ችግሮችን የሚፈታ፣ በቀጣይም ለራሱና ለሀገር ዕድገት የሚሠራ ቤተ ክህነትን ለማየት የሚያስችለን መሆን አለበት፡፡ የቤተ ክህነቱ አሠራር ከሀገሪቱ አሠራሮች ሁሉ ወደ ኋላ የቀረ አሠራር ነው፡፡ ቀበሌዎች እንኳን ያገኙትን የመዋቅርና የሥራ ሂደት ማሻሻያዎችን ቤተ ክህነቱ አላገኘም፡፡ በመሆኑም ሲኖዶሱ ገለልተኛ በሆነ አማካሪ ድርጅት የቤተ ክህነቱን አጠቃላይ አሠራርና አወቃቀር ፣ የሰው ኃይልና የእዝ ሠንሠለት እንዲያጠና ቢደረግ አሁን ሀገሪቱ ለደረሰችበት ዕድገት የሚመጥን አወቃቀርና አሠራርን መዘርጋት ይገባል፡፡ የቤተ ክህነቱ አሠራር ካልተጠናና ካልተስተካከለ ምንም ዓይነት ብቁና ቅዱስ አባት መምረጥና ማስቀመጡ ‹በእሾህ መካከል የተዘራ ዘር› ይሆናል፡፡
ባለፉት ዘመናት የተደረጉት የፓትርያርክ ምርጫዎች ጉምጉምታ የሚሰማባቸው እንደነበሩ በየዘመናቱ የተጻፉ መዛግብትና በዘመኑ የታዘቡ ሰዎች ግምገማዎች ያሳያሉ፡፡ በቅዳሴያችን ላይ ‹እነዚህን ሁለቱን አባቶች በዘመናችን ተቀብለናቸዋል› ይላል፡፡ ይህንንም ብሎ የፓትርያርኩንና የሀገረ ስብከቱን ጳጳስ ስሞች ያነሣል፡፡ ይህ ነጥብ የሚያሳየን ነገር አለው፡፡ ሕዝቡ ‹ይደልዎ› ሊል እንደሚገባ፡፡
በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነትና ተቀባይነት ያለው ምርጫ የሚከተሉትን ነገሮች የሚያሟላ ምርጫ ነው፡፡
 1. መንፈሳዊነትን የተላበሰ ምርጫ፡- መንፈሳዊ ምርጫ መንፈሳዊ ደረጃውን የጠበቀ ከሆነ ሕዝብ ይቀበለዋል፡፡ እኔን ምረጡኝ የሚል ፖለቲካ ያልገባበት፣ እገሌን ምረጡ የሚል ጫና ያልተቀላቀለበት፣ ከእገሌ ዘር ይመረጥ የሚል ሥጋ ያልተጨመረበት፣ በትኁት ሰብእናና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን ብቻ በመሥራት ላይ ከተመሠረተ ሕዝብ ይቀበለዋል፡ ሂደቱ በጸሎትና በጾም ከታጀበ፣ አባቶች ከእኔ ወንድሜ ይሻላል ካሉ፣ እግዚአብሔር እንዲመራ ቦታውን ከሰጡ ሕዝብ ይቀበለዋል፤
 2. ቀኖና የጠበቀ ከሆነ፡- በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የጳጳሳትንና የፓትርያርኮችን ምርጫ፣ መመዘኛና አሠራር የሚደነገጉ አያሌ ቀኖናት አሉ፡፡ እነዚህ ቀኖናት በመንፈስ ቅዱስ በተመሩ አባቶች የተሠሩ በመሆናቸው ችግን በመከላከልና ከተከሰተም በመፍታት ረገድ ወሳኝ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሂደቱ በቤተ ክርስቲያን የተደነገጉትን እነዚህን ቀኖናት የጠበቀ ከሆነ የሕዝብን ታማኝነትና ተቀባይነት ያገኛል፤
 3. ግልጽ ከሆነ፡- እያንዳንዱ ሂደት ዝርዝር አሠራር የተቀመጠለት፣ መመዘኛዎቹ የሚታወቁ፣ አንድ ነገር ለምን እንደተደረገ የሚታወቅበት መንገድ ካለው፣ ከየት ተነሥቶ የት እንደሚደርስ መንገዱ ከተለየ ሕዝብ ሂደቱንም ውጤቱንም ይቀበለዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ወቅት ከሚጠበቁበት ነገሮች አንዱ ግልጽ ዕቅድ አውጥቶ ለሕዝብ ግልጽ ማድረግና ውጤቱንም በየጊዜው መግለጥ ነው፡፡ የሚሰጡ መግለጫዎች ሌላውን የሚገልጡ መሆን አለባቸው እንጂ እነርሱ ራሳቸው ሌላ መግለጫ የሚያስፈልጋቸው ቅኔዎች መሆን የለባቸውም፤
 4. አሳታፊ ከሆነ፡- የሚከናወነው ተግባር የቤተ ክርስቲያን ተግባር ነው፡፡ የሃምሳ አራት ጳጳሳት ተግባር ብቻ አይደለም፡፡ የሚመረጠው አባት ከ45 ሚሊዮን በላይ የሆነውን ምእመን የሚመራ እንጂ ጥቂት የቤተ ክህነት አካላትን ብቻ የሚያስተዳደር አይደለም፡፡ በመሆኑም ምእመናኑ በግልጽ መሳተፍ፣ ድምፃቸውን መስማት፣ ሃሳባቸውን መቀበልና ተረድቶ ማስረዳት ይገባል፡፡ እስካሁን ለምሳሌ ከአድባራት አስተዳዳሪዎች እንጂ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሂደት አስተዋጽዖ ከሚያደርጉ ምእመናንና ምእመናት ጋር ውይይት አልተደረገም፡፡ በዚህ ምክንያት ሐሜትና ወሬ የሕዝቡ የመረጃ ምንጮች እንዲሆኑ ተፈርዷል፡፡ ሲኖዶሱ ሲሆን ከየሀገረ ስብከቱ ተወክለው ከሚመጡ፣ ካልተቻለም በአዲስ አበባና በዙርያዋ ካሉ ታላላቅ ሽማግሌዎች ጋር ሂደቱን በተመለከተ መመካከር ይገባዋል፡፡ ‹ምእመን ለገንዘቡ ብቻ› የሚባልበት ዘመን ያለፈ ይመስለኛል፡፡
ለዚህ ነው ‹ሲኖዶሱ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም›  ያልኩት፡፡ እነዚያን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ፣ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ‹ረዳት› ያስፈልገዋል፡፡ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የምሁራን፣ የምእመናንና  የሌሎችም በጎ አሳቢ አካላት ርዳታ ያስፈልገዋል፡፡ ሲኖዶሱም ብቻውን መሆኑ መልካም አለመሆኑን ዐውቆ የሚመለከታቸውን ባለ ድርሻዎች በመጋበዝ አብሮ መሥራት፣ ባለ ድርሻዎችም እስኪጋበዙ ሳይጠብቁ ቀርቦ ማገዝ ‹ከሚመጣው ቁጣ›  ሁሉንም ያድናል፡፡

41 comments:

 1. የቤተ ክህነቱ አሠራር ከሀገሪቱ አሠራሮች ሁሉ ወደ ኋላ የቀረ አሠራር ነው፡፡ ቀበሌዎች እንኳን ያገኙትን የመዋቅርና የሥራ ሂደት ማሻሻያዎችን ቤተ ክህነቱ አላገኘም፡፡ በመሆኑም ሲኖዶሱ ገለልተኛ በሆነ አማካሪ ድርጅት የቤተ ክህነቱን አጠቃላይ አሠራርና አወቃቀር ፣ የሰው ኃይልና የእዝ ሠንሠለት እንዲያጠና ቢደረግ አሁን ሀገሪቱ ለደረሰችበት ዕድገት የሚመጥን አወቃቀርና አሠራርን መዘርጋት ይገባል፡፡ የቤተ ክህነቱ አሠራር ካልተጠናና ካልተስተካከለ ምንም ዓይነት ብቁና ቅዱስ አባት መምረጥና ማስቀመጡ ‹በእሾህ መካከል የተዘራ ዘር› ይሆናል፡፡

  ReplyDelete
 2. ማኅበረሰቡ የስድስተኛው ፓትርያርክን ምርጫ ያለፉት ችግሮች የማይደገሙበት እንዲሆን መፈለጉ ነው
  እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ቀጣዩ የፓትርያርክ ‹ምርጫ› ሦስት ነገሮችን የሚያሟላ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
  የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት የሚያስጠበቅ፣ ያለፉትን ችግሮች ለመፍታት መንገድ የሚከፍት እና የሕዝቡን አመኔታ የሚያገኝ፡፡


  ሲኖዶሱ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም›
  i agree with ur idea dani . all of us should pray .God have a means for any obstacle .let us .........pray pray pray pls pls pls pls ....................

  ReplyDelete
 3. So you are still insisting in to have new election for patriarchal leadership while the legal patriarch, who was elected by according to church canonical, still alive. Come on!! you do not have to be source of conflict for the church!!.

  ReplyDelete
  Replies
  1. Yes and no Solomon,

   "ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድም አራተኛውን ፓትርያርክ ወደ መንበር ትመልሳለች፣ ያለበለዚያም አራተኛውን በጸሎት ወስና በእንደራሴ ትቀጥላለች፣ ያለበለዚያም ስድስተኛውን ትመርጣለች፡፡"

   The last option we have is chosing the 6th patriach. Here Daniels message, we have to conduct the election very carefully. I strongly agree with him. We should learn from history, we should seek for a best solution for the sake of the church.

   Delete
  2. Pls do not only read and write what you want only. In the piece daniel at first has acknowledge the existence of the the Fourth patriarch. And as I understand the whole procedure he advised also holds to put in position the fourth patriarch. But with out procedure and peace I believe it will be impossible.
   To make history I believe you and me and others should have to buried our feelings and guide literatures, if we feel they are in wrong direction. But this literature in my opinion it is genuine. What we should not forget is that as a person dn daniel has the wright to appreciate the election. The home work to you and me is to debate with him on our ideas. Personally some scarification should be done to end the split.

   Delete
  3. Hello Guys! Thank you for the comments! But, we need to remember that our church was the only physical property that we inherited it from the almighty God when we live on this world. The issue of church is very sensitive and sentimental for those who need the sovereignty and unity of the church. If I am harsh to author,please pray for me for the forgiveness.

   Delete
  4. May God Bless you my brother Solomon ! You have returned from the wrong way of understanding people and ask for forgiveness. This is what many people luck, specially we Ethiopians. May god bring UNITY to our church !!!

   Delete
 4. Not only Sinodos but also human being by it self needs beside.
  God Bless Ur Life,

  ReplyDelete
 5. በማስተዋል የተፃፈ፣ ካለፉት ሁኔታዎች ተምረን ተመሳሳይ ከዚያም አልፎ የከፋ ችግር እንዳይገጥመን ተረጋግተን ግን ደግሞ ሳንዘናጋ በማስተዋል ልንፈጽመዉ የሚገባ የወቅቱ ታላቅ ተግባር፡፡ ዳኒ፡ እግዚአብሔር ያበርታህ!

  ReplyDelete
 6. thank you diakon daniel. if the sinodos follow modernization and orthodox christian followers near to him we will doing special vote and if we should hand to hand (sinodos and christian people) working together we will see the bright church . otherwise the dark church. if we are working together we control all African and Caribbean see under Ethiopian Orthodox union church . else we are not stand together ,we are not agree ,we are under sin ,even control Africans and Caribbean see peoples we are separate into small division."eresbersua yemetleyaye mengest tetefalche "
  "ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤
  በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።" እብ 10፡24-25 so sinodos and the Christan people working together the day is this day ምእመን ለገንዘቡ ብቻ› this word is making dislike the church father and sinodos "እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤" the sinodos and the church father must be give respect to the followers people "


  ReplyDelete
  Replies
  1. first of all try to learn how to write proper English. As far as controlling African and carribian countries-this is not a political agenda! African union is enough for that-instead i want the church to focus at home on Ethiopians-and Horn of Africa at large. Even the church is losing its followers at home according to the recent statistics-the protestants and the Muslims are gaining ground.

   Delete
 7. Dear Dn Dani,

  I dont know how to win the hearts and minds of the people around the church.Something has to be done .Information is the first thing .We are divided on different issues.

  "ሲኖዶሱ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም"
  God bless Ethiopia !!!

  ReplyDelete
 8. it is correct D/N daniel. we have to pray. God will Give us a good father

  ReplyDelete
 9. ዲያቆን ዳንኤል እግዚአብሄር ይባርክህ መልካም መልዕክት ነው። እግዚአብሄር በቃ ብሎን ለአባቶቻችንም ማስተዋሉን ሰጥቶ አንተ እንዳልከው ትልቁን ስዕል በማየት ይህችን ቤተ ክርስትያን ወደ አንድነት ይመልሱ ዘንድ ይርዳን።
  ግን ከአብሮት ጋር ፥ምዕመን ለገንዘብ ብቻ የሚባልበት ዘመን ያለፈ ይመስለኛል፥ የምትለዋ ሃረግ ትንሽ ትከብዳለች፡ ምክንያቱም በተለይ በውጪ ሃገር በምትገኘው ቤተ ክርስትያን ትልቅ ችግር የፈጠረው ይህ አይነት አባባል ነው፡ ደሞዝ የምንከፍላቸው እኛ ነን ካህኑ ተቀጣሪ ነው እኛ የምንፈልገው ነገር ብቻ ይሁንልን ያ ነገር የቤተ ክርስትያንን ስርዓት ጠበቀ አልጠበቀ ጉዳያቸው ያልሆነበት ቦታዎች በብዛት አሉ ለዛ ነው ትከብዳለች ያልኩት። ለቤተ ክርስትያን ስጦታ መስጠት፣ ስዕለት፤ መባእ፤ አስራት በኩራትን ማውጣት ክርስቲያናዊ ግዴታ ይመስለኛል፤ በወንጌሉም የታዘዘ ነውና። ከዛ ውጪ ከትምክህት በጸዳ መልኩ ቤተ ክርስትያኗን በሚያሳድግና በሚጠቅም መልኩ መሳተፉ ተገቢና መልካም ነው። ገንዘብ ስለሰጠ ሳይሆን የተዋህዶ ልጅ በመሆኑ። ይሄን ሁሉ ልል የወደድኩት ፥ ‹ምእመን ለገንዘቡ ብቻ የሚባልበት ዘመን ያለፈ ይመስለኛል። የምትለዋ ሃረግ እዚህ በውጪ ሃገር ትልቅ ችግር እየፈጠረች ስለሆነ ነው። እግዚአብሄር አምላክ ከአባቶቻችን ስብሰባ የእርቅና የሰላም ዜና እንድንሰማ ያብቃን። አሜን

  ReplyDelete
 10. Good idea. Thanks Dani

  ReplyDelete
 11. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
  ሁላችንም የቤተክርስቲያናችን ወቅታዊ ጉዳይ ሊመለከተንና ልንሳተፍበት ይገባል፡፡

  "በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።" 2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 11:27-28  ReplyDelete
 12. The message of your blog is very crucial and timely for the selection process of the Ethiopian Orthodox Church. When I was a university student a decade before, I know that you have a deep rooted love up on our church at that time and you were preaching in very energetic and enthusiastic way. I also see you at some churches today doing the same mission as before and now you are also using the modern technology to expand the message of the gospel to all who would like to hear and listen. It is a nice service you are delivering because you know very well that nothing is more than the words of God. I usually prefer to browse your blogs before I intend to use internet for any other purposes as to what important messages in the areas of our churches are written or powered out. This effort has been extended since I found out your educative blogs right away. And the current message you powered here is very essential one for this particular time where as you mention here with, problems are very common here and there up on the selection process of our spiritual father. The division both at the abroad and internal localities is very common. This indicates that people who have great responsibilities are not working towards unification and reconciliation and is very tragic not to respond to the extent they are expected from them because these people are very rich in the knowledge of the words of God but are not seen to abide by it. They are becoming additional barriers rather to be part of the last solution of the problem. I Suppose that this part is something it needs every ones involvement and should make our enforcement up on any one who is assumed to be obstacle up on the successful accomplishment of the church leader selection because nothing is more than this we should not neglect it. You should also make your suggestions up on the expectations from the church followers and the clergies courageously. because if once we miss the opportunity to curb the situation by not doing what is expected from us we have to be sure that we are inviting another tragedy to our long standing historical as well as spiritual church. Therefore the present unification and reconciliation both in the inside and outside fathers is more than essential ever for the unity of our church and pure spiritual service deliveries. We all should not stand up on the side of our personal interest but should stand for the will of God. If we are doing in such a manner, it is very true that we have had a church we would like to be and God would get pleased with our unity and peaceful coexistence. This is what I need to see forever in our church.
  Any ways I would like to extend my heartfelt gratitude to the effort you are making towards the peaceful return of our church as it was in the very ancient times where real people of God leading it with full spirituality and the power of God bestowed to them to do so.
  May the Grace of Jesus Christ, The Love of God and The Fellowship of His Holy Spirit be with you All, Amen?

  ReplyDelete
 13. በርግጥ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የአበው ስብስብ ነው፣ ስለዚህ ዝንቱ ዘመድ ኢይወጽእ ዘእንበለ ጾም ወጸሎት እንደተባለው ይህንን ዓይነት ፈተና ማለፍ የሚቻለው በጾምና በጸሎት ብቻ ነው፣ አባቶቻችን ውዳሴ ማርያሟ ትደገም እንጂ ፣ አባቶቻችን ለቤተክርስቲያን ሲሉ የእውነት መንገድ ላይ ብቻ መቆም እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው፣ በየአቅጣጫው የሚነፍሰውን ነፋስ ማራገብ ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው፣ የዮናስ ስጋት ልክ ነው ፣ ግን እንደ ዳንኤል አባባል ይህንን ዓይነት አባባል የሚጠቀሙት ጥቅመኞች ካህናት ናቸው፣ እንደ ዮናስም አባባል በቤተክርስቲያን ስም የሚነግዱና መቦጨቅ የለመዱ ምዕመናን የሚያወሩት ተልካሻና የማይጠቅም አስተሳሰብ ነው፣

  ReplyDelete
 14. ከወ/ት መስከረም
  ለወንድሜ ዳንኤል ቃለ ህይወት ያሰማንልን። በሃሳብህ ሙሉ ለሙሉ እስማማለሁ። አንድ የተረሳ መሰረታዊ ችግር ያለ ይመስለኛል። ይሄውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከመንግስት ጋር ያላት አወቃቀር ነው። እንደሚታወቀው ቤተክርስቲያኒቱ የተመሰረተችው በአዋጅ እንደ ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ነው። በዚህም የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት ከመንግስት ተፅእኖ ነፃ ልትሆን አልቻለችም። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለህን ሀሳብ ማወቅ እፈልጋለሁ።

  ReplyDelete
 15. Dear Dn. Daniel,

  What's sad in your piece is the fact that it's not based on any specific provisions of the church's (EOTC's) internal regulations as well as the other laws that infulence its activities such as the Feteha Neguest and the Civil Code. As a result, you offer advice as if the church could and should act with impunity.

  The clear case is that in accordance with the Holy Synod's regulations issued in 1991 EC as well as the Feteha Neguest, a Patriarch cannot resign, as claimed concerning Abune Merqorios. That action and later allegations were completely false! Therefore, if you wish to abide by the laws, as you should, the only option available to our church is to invite Abune Merqorios back to take on the leadership and, finally, achieve the unity and reconciliation that are needed so desperately.

  Another point that you seem to ignore now but about which you could make a huge contribution is to suggest a comprehensive system of nomination, evaluation, and final selection of a Patriarch. I know you could do this because you had made a great contribution to the issue by reporting on the Coptic system which is absolutely admirable in terms of participation, processing and final decision. However, such an initiative will have to be considered later ie after the next Patriarch is fully installed.

  ReplyDelete
 16. The writer of this comment clams that you (Dani) as one of the major challenge to our church peace process. In order to validate this clam,I will only look in to one of your small paragraph below.
  ከሁለቱ ዋና ዋና አካላት መካከል አምስተኛው ፓትርያርክ ዐርፈዋል፣ አራተኛው ፓትርያርክም በጤና እክል ላይ ናቸው፡፡ ከችግሩ መፈጠር በኋላ ዐቃቤ መንበር የነበሩት አቡነ ዜና ማርቆስ ዐርፈዋል፤ ችግሩ ሲፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ታምራት ላይኔ ሌላ መሥመር ውስጥ ገብተዋል፣ በዚያ ወቅት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስም (ነፍሳቸውን ይማርና) አርፈዋል፡፡ ከወዲህ ወገንም በዚያ ዘመን ከነበሩት አበው መካከል ቢያንስ ወደ ስምንት የሚጠጉት ዐርፈዋል፤ በወዲያ በኩልም አቡነ መልከ ጼዴቅና አቡነ ኤልያስ አርጅተዋል፡፡
  Dani let us dichotomize this paragraph and try to understand your position in the peace process of our Holy Church Unity.
  1. አምስተኛው ፓትርያርክ ዐርፈዋል፣
  2. አራተኛው ፓትርያርክም በጤና እክል ላይ ናቸው፡፡
  3. ከችግሩ መፈጠር በኋላ ዐቃቤ መንበር የነበሩት አቡነ ዜና ማርቆስ ዐርፈዋል፤
  4.ችግሩ ሲፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ታምራት ላይኔ ሌላ መሥመር ውስጥ ገብተዋል፣
  5. በዚያ ወቅት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስም (ነፍሳቸውን ይማርና) አርፈዋል፡፡
  6. ከወዲህ ወገንም በዚያ ዘመን ከነበሩት አበው መካከል ቢያንስ ወደ ስምንት የሚጠጉት ዐርፈዋል፤
  7. በወዲያ በኩልም አቡነ መልከ ጼዴቅና አቡነ ኤልያስ አርጅተዋል፡፡
  In my excerpt of your paragraph above, sentences are intentionally bulleted for clarity or understanding.
  According to your writing, bullet number 1, 3, 5 and 6 states about the deaths of about 11 important ``figures`` (I would have said church fathers instead of figures but you made it difficult for me by mixing up the unmixable). I want you to look in to your intention and reflect on why of your R.I.P is given only to the late PM Meles,why not for the rest, is it because he is unarguably holy and lost his life in the fight to unite our church!
  In bullet number 2 you are trying to tell us Patriarch Merkorios is non-functionaly sick (I do not assume you do lack the knowledge of our church’s canon on related matter) but then what is you motive of underlining on this issue and which direction are you leading your readers even if he is sick.
  Bullet number 3 shows that you are still trying to contemplate to win the soul of Abune Zena Markose, confuse your readers and to more complicate the peace process (I think it is too late because he is in the hand of God now).
  Bullet number 4 is a very surprising one to me. Dani are you calming that Tamerat was siding our Holy Church before he joined Protestantism or while he was a Woyane big guy, or are you trying to play naive as if you do not know Tamirat`s role in this division of our Holy Church. I know you are married to Woyane and selling your skin.
  I have no much comment about bullet number 5 I would rather say it is a point where I see your sympathy and care far more than ``your`` church. In both bullet numbers 6 and 7 the phrase ከወዲህ and በወዲያ are ironically showing your intentions, enthusiasms and commitment to the peace process.
  The last bullet which is number 7 is the manifestation of your disrespectfulness and baized mind at this very sensitive and crucial peace process moment. This part is a vivid manifestation and reminder to your readers to question your personal ethics and back ground.
  Dani by the way it won’t take a rocket science to understand the major challenge of this peace process, I think you know it so well that you have a big share of responsibility to take in this regard. I would also like to remind you the judge will not Woyane or any one on earth but is from above. So sleep well man!!
  Thanks

  ReplyDelete
  Replies
  1. I think previously in his post on aba paulos death Daniel said "rest in peace" & a reader gave acomment that it is not appropriate to say the word "rest in peace" for patraiarichs, since they are expected to be holly person. i.e why i think Daniel did to meles only. I don't know, any one who elaborate it more?

   Delete
  2. What about for Tamerat

   Delete
 17. Dear Dacon Daniel !! I always like to comment on your articles, but I rather feel incompetent to do so. Just out of love and respect. However, I have this desire to tell you how great your are doing in preserving and amending the generation in many wasys than one. God always have some one to do things I hope he will bless your effort so we all see the seeds amin!! Back to this particular topic. If the current events come from God for a good causes. I mean if God did what he did to put stop on what take place in Ethiopian orthodox church for the last 21 years .His grace will be with us to do the godly things that lead us to focous on the main objection in bing christian which is obtaining his kingdom. At the moment we are rather overwhelmed on other things that surrounding our church. God graces and mearcy be upon us.

  ReplyDelete
 18. ማስጠንቀቂያ !!!ልናስተውል የሚገባን
  ቅዱስ ሲኖዶስ ምን ግዜም ቢሆን ብቻውን ሆነ አይባልም የጉባኤው መሪ መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ጌታችንና መዳህኒታችን እየሱስ ክርስቶስም እንደ አንድ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ መገኜቱ ይሄን ያጠይቀናል እንደ የአለማዊ አስተሳሰብ የቀበሌ ስብሰባ አይነት እንዳናስብ ይረዳናል ስለዚህ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የሚመለከተው ጳጳሳትን ብቻ መሆን ይገባዋል:: ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ‹ሲኖዶሱ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም› አይባልም እኔ አውቅልሀለሁ ማለት እና መሪ ሀሳቦችን መሰንዘር በመንፈስ ቅዱስ ስራ ጣልቃ ገብነት ነው::በቃ!!!!

  ReplyDelete
  Replies
  1. Betekiristianin (Yekebele mewakir gar yanetsatserem ale) Alemawi Alemehonuan megenzeb yemigeba yimeslegnal. Yihichin Esatawit Betekirstian bemanignawim menged Alemawiwin aserar bemasretse lemadakem Yemideregu sirawochin sinastewil alen " Ersu Balebetu Gin Berasu Yanetsat silehonech ayitewatim Yitadegatal. Endene behaymanot ena bemigbar honen ersunim bemamen Kibirt Behonech Enatu mematsen yitebekibinal. Lelaw yesigachin filagot new.

   Delete
  2. sure!! ልናስተውል የሚገባን !!!!

   Delete
 19. "yetibeb mejemeria Egziabherin mefrat new" yihenin menfes yistegn(yisten)

  ReplyDelete
 20. "ለዚህ ነው ‹ሲኖዶሱ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም› ያልኩት፡፡ እነዚያን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ፣ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ‹ረዳት› ያስፈልገዋል፡፡ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የምሁራን፣ የምእመናንና የሌሎችም በጎ አሳቢ አካላት ርዳታ ያስፈልገዋል፡፡ ሲኖዶሱም ብቻውን መሆኑ መልካም አለመሆኑን ዐውቆ የሚመለከታቸውን ባለ ድርሻዎች በመጋበዝ አብሮ መሥራት፣ ባለ ድርሻዎችም እስኪጋበዙ ሳይጠብቁ ቀርቦ ማገዝ ‹ከሚመጣው ቁጣ› ሁሉንም ያድናል፡፡"

  Dn. Daniel, Kale Hiwot Yasemalin. Asteway lib lalew betam astemari ena mekari hasabe new. Lehulachinm Egziabiher Lib Yisten; Sile Betekrstianm zewotir Enaliqis. Yetewahido Amlak lehulum mefitihe alewuna.

  ReplyDelete
 21. Thank you Daniel for the article. I do not think having many options is the best option. Here is what I think best for the church unity and peace. The 4th patriarch should return from exile and take the seat unconditionally (even if you said or wished he has health problems).If Abune Merkorios is giving up everything for good reasons there should be no other election of the 6th patrirach.The seat should be protected by Akabe menber till we get our Lord’s mercy. I personally do not want to see another patriarch destroying and looting the church again. I do not want another patriarch erect his own monument. I do not want another patriarch build his empire (buy houses, cars, steal money, gather families).For that matter there are some synod members who built houses for themselves and their families. I strongly condemn such acts in the strongest terms. Those people should not be trusted for the greater leadership. I do not want to see another patriarch hits, jails, and persecutes his pope brothers and other liqwents. Please Daniel for the Lord’s sake expose evil and collaborate with truth. This is about our faith. It shouldn’t be treated as kebele kind of election or whatever. There should be one option.One leader,one church,one synod at a time.That way we get stronger than before. Finally, someone says ”United we stand, divided we fall.”

  Gebre, Ke Etissa T/Haymanot

  ReplyDelete
 22. በማስተዋል የተፃፈ፣ ካለፉት ሁኔታዎች ተምረን ተመሳሳይ ከዚያም አልፎ የከፋ ችግር እንዳይገጥመን ተረጋግተን ግን ደግሞ ሳንዘናጋ በማስተዋል ልንፈጽመዉ የሚገባ የወቅቱ ታላቅ ተግባር፡፡ ዳኒ፡ እግዚአብሔር ያበርታህ!

  ReplyDelete
 23. Selam ዲያቆን ዳንኤል
  ለመጣጥፍህ እያመሰገንሁ ፣ ነገር ግን ጽሁፍህን ከወቅታዊነት አስፈንግጠኸዋል። ይህ ወቅት ፣ ኢትዮጵያ ያሉ ዓባቶች ሌላ ፓትሪያርክ በመምረጥ ታላቁን እና የከፋውን ስህተት እንዳይፈጽሙ መማጸን የሚያስፈልበት መሆን አለበት። አንተም በጥቂቱ ነካክተኸው ስታበቃ ፣ ቆየት ብለህ ለቤተክርስቲያኗ ዘለቄታዊ መፍትሄ ከመጠቆም ይልቅ ፣ ልቦናህ የሚፈልገውን “6ኛ” አዲስ ፓትሪያሪክ የመምረጡ ጉዳይ ላይ ብዙ ጻፍህ። ይህ ግን ፈጽሞ ወቅታዊ ጉዳይ አየደለም። የመጀመሪያው ስራ መሆን ያለበት ፣ አቡነ መርቆሪዎስ ቀኖናዊ ፓትሪያሪክነታቸውን አስጠብቆ ፣ ቤተ/ክርስቲያኒቷን በ እንደራሴ ማስተዳደር ብቻና ብቻ ነው መሆን ያለበት። ቀጥሎም ፣ ፈጣሪ አቡነ መርቆሪዎስን በወሰደ ጊዜ ሌላ ፓትሪያሪክ መመምረጥ ነው የሚያስፈልግ።
  በኔ እምነት ይህ መደረግ ያለበት ፣ እርቀ ሰላሙ ስለተሳካ ወይም ስላልተሳካ አይደለም። ጉዳዩ በራሱ የግድ አስፈላጊ ስለሆነ ብቻ ነው። አንተ ግን ይህን ሃሳብ በጥቂት አረፍተ ነገር የጨረፍኸው እንዲሁ አለ ለመባል ካልሆነ በቀር ፣ ውስጥህን ግን ክፉኛ ያስቸኮለው ጉዳይ የ”6ኛው” ምርጫ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ይህ ነገር ከተፈጠረ ፣ ቤተ/ክርስቲያናችን ወደዘላለማዊ ቀውስ ትሸጋገራለች። የኒቆዲያውን ችግር አስመልክቶ ያነሳኸውም ፣ ከታሪክ አንጻር ጠቀሜታ ቢኖረውም ፣ ከኛ ዘመን አንጻር ግን ፍጹም ይለያል። ለምን ቢባል ፣ የኒቆዲያው ልዩነት እጅግ ውስብስብ የሆነ አለማቀፋዊ ገጽታ ያለው ሲሆን ፣ የኛው ችግር መፍትሄ ግን በኛ እጅ ያለ ጉዳይ መሆኑ ነው። እስኪ ይህን ያልሁበትን ምክንያት ልናገር … እንበል ለምሳሌ እነ አቡነ መልከ ጸዲቅ እርቁን አንፈልግም ብለው ቢገፉ እንኳ ፣ የኢትዮጵያው ሲኖዶስ ፣ የፈለገ ቢሆን ሌላ ፓትሪያርክ አልሾምም ብሎ ቢቀመጥ ፤ የአቡነ መርቆሪዎስን ሞት ጠብቆ ምን ሊፈጠር ይችላል?! የውጩ ሲኖዶስ ሌላ ፓትሪያሪክ ልሹም ቢል ፣ ተቀባይነት አይኖረውም ፣ ምክንያቱም ያን ቢያደርግ አዲሱ ተሿሚ በኢትዮጵያው ኦርቶዶክሳዊ ህዝብም ሆነ ሲኖዶስም ተቀባይነት አይኖረውም። የአገር ቤቱ ሲኖዶስ ግን ፣ ይህን ጊዜ ታግሶ ቆይቶ የፈለገውን ፓትሪያሪክ ቢሾም ፤ በሂደት ስለሚያጠናክር ትልቁን መንፈሳዊ የሞራል ሃቅም በውጭ የሚኖሩ አባቶችን ቢያሻው ቢጋብዝ ቢያሻው ቢያወግዝ በታሪክም አይወቅስም። የቤተከርስቲያኗ ችግርም እዚያው ላይ ያቆማል። እምቢተኛው ወገንም እምነቱን አስረክቦ ፖለቲካውን ታቅፎ ይቀመጣል።
  ስለዚህ ይህ ወቅት ፣ ከምንም በላይ አገር ቤት ያሉ አባቶች አዲስ ፓትሪያሪክ የሚባል ነገር የማያስቡበት ወቅት መሆን አለበት። ወቅታዊ የሆነና አስፈላጊ የሆነ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ባምንም ፣ እናግዛለን የሚሉት ግን በራሳቸው ስሜት የታሰሩ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ። ሌላው ቀርቶ ወንድም ዳንኤል እንኳ ስለአረፉት አባቶቻችን ምንም ሳትል ፣ ስለሞተው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጠላት መለስ ዜናዊ ፣ ከስሙ አጠገብ “ነፍሱን ይማር” የሚል ቃል ጨመርህ። …
  እግዚያብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ

  ReplyDelete
 24. mercha lemen asfelege ? Papasu eko behiwet alue

  ReplyDelete
 25. አንድ አድርገንOctober 30, 2012 at 1:27 AM

  ዳንዬ ጥሩ ጀምረህ ደፍረስረስ አደረከው መሰል::

  የምርጫዋን ነገር ገታ አድርገሃት አንድነቱን የሚረዱ ሃሳቦችህን ብታካፍለን እንዴት መልካም ነበር::

  ቅዱስትነታቸው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ መሆናቸው እየታወቀ ( እናንተ "አውቃችሁ" አሁን እረስታችሁት ይሆን ? ) ለምን አዲስ 6ተኛ ፓትርያሪክ ይመረጣል???....???

  በዚህም አለ በዛ አዲስ ፓትርያሪክ መመረጥ የለበትም ፓትሪያሪካችን በህይወት አሉና:: (አራት ነጥብ ይል ነበር አንተ ከሌሎቹ ለይተህ ነፍስ ይማር ያልከው፣ እውነቱን ነበር እኮ )

  ReplyDelete
 26. we hope they might listen our voice!

  ReplyDelete
 27. aye yasazenal, Dani anten egziabeher yibarekeh bezu asebehebet yetsafekew tsehuf endehone eredalehu. Bemegemeriya egziabeher ereke selam endiyawered megnote new. Gin Ethiopia yalew sinod ke tesededut Abat gar mesemamat bayechalew. Ye ethiopia hizeb yale eregna yiker yemil fered yemifered kale yih sew yeminorew ke hager wechi mehon alebet mekeniyatum eregnaw be ereket mekotateriya new betekresetiyanuan yemimeraw? Weyes ya hizeb ke gonu huno yemibarek patriarch ayasefelegewem? Lemanegnawem abatochachinen melekamun yasayachew. Be ereget sanawek yegna merecha ena lemena ende Jacob enat lihon yichil yihonal. Egziabeher gin melekamun yametal. Abatachin Abune merkoriwos bekereb yarefalu, selamachinem yimelesal. Yikereta ende tsafoch tenebit tenagerek endatelugn ''alem kemetetefa ande sew bimot yishalal'' endalut.Ene gin motachewen temegniche ayedelem.

  ReplyDelete
 28. ማስጠንቀቂያ !!!ልናስተውል የሚገባን
  ቅዱስ ሲኖዶስ ምን ግዜም ቢሆን ብቻውን ሆነ አይባልም የጉባኤው መሪ መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ጌታችንና መዳህኒታችን እየሱስ ክርስቶስም እንደ አንድ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ መገኜቱ ይሄን ያጠይቀናል እንደ የአለማዊ አስተሳሰብ የቀበሌ ስብሰባ አይነት እንዳናስብ ይረዳናል ስለዚህ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የሚመለከተው ጳጳሳትን ብቻ መሆን ይገባዋል:: ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ‹ሲኖዶሱ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም› አይባልም እኔ አውቅልሀለሁ ማለት እና መሪ ሀሳቦችን መሰንዘር በመንፈስ ቅዱስ ስራ ጣልቃ ገብነት ነው::በቃ!!!!
  I think some member of the mahibere kidusan are also working against the church order. The topic is wrong.

  ReplyDelete
 29. WE SHOULD PRAY, PRAY ,PRAY, PRAY, PRAY..... FOR THIS BROTHERS AND SISTERS!!

  ReplyDelete
 30. ዲ/ን ዳንኤል እኔ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ነኝ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእኛ እምነት ተሀድሶ ገብቶባታል እየተባለ ይወራል ወሬ ብቻ ሳይሆን ወደ ክ/ሀገር ተሀድሶ የተባሉ ቀሳውስት ህዝቡ እያገለላቸው ቤተክርስቲናችንን በረዙ ስርዓቱን አበላሹ እየተባለ ተቀባይነትን እያጡ ወደ አ/አ እየመጡ ያሉም አሉ እባክህ እስኪ ስለ ተሀድሶና የታደሰውን ነገር በግልጽ አስረዳኝ በመሠረቱ የዱሮው የቤተክርስቲያን ስርዓት አሁን ላይ በተለይ በአ/አበባ የለም በወንዱ መግቢያ በር ሴቶች ይገባሉ በቅዳሴ ሰዓት ዘሎ መግባት የእመቤታችንን ተዓምር ቆሞ አለመስማት እንዲያውም እንደ ትርፍ ነገር ማየት ከብዙው ጥቂቶቹ ተመልክቻለሁ ለምን በተከታታይ ትምህርት እንደማይሰጥበት ሁሉ ይገርመኛል፡፡ ለሁሉም መልስ ከአንተ እፈልጋለሁ፡፡

  ReplyDelete