Tuesday, October 2, 2012

የተሰደዱ ስድቦች

በአንድ ወቅት ነፍሷን ይማረውና ፊርማዬ ዓለሙ አንድ ገጠመኟን በኢትዮጵያ ሬዲዮ አስደምጣን ነበር፡፡ ፊርማዬ በመንገድ ላይ ስትጓዝ ከአንድ ጎረምሳ ጋር ትጋጫለች፡፡ ጎረምሳውም በለመደ አፉ በእናቷ ይሰድባታል፡፡ ፊርማዬ ነገሩን በስድብ ብቻ አላየችውም ነበርና ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ትወስደዋለች፡፡ ፖሊስም ልጁን ሕግ ፊት አቅርቦ ያስቀጣዋል፡፡ ይህንን ነበር ፊርማዬ የነገረችን ‹ስድብን ዝም አትበሉ› ብላ፡፡
ይህንን ፊርማዬን እስከ ክስ የወሰዳትን ስድብ ዛሬ ዛሬ በአዲስ አበባ መንገዶች አልሰማውም፡፡ እኔ ስድብ የመስማት ችሎታ ቀንሷል ወይስ ስድቡ ራሱ ሰው ዘንድ የመድረስ ዐቅሙ ተዳክሟል? አንዳንድ ጊዜም ‹ስድቦቻችን የት ሄዱ?› እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ መቼም ነገሮች ከዘመኑና ከቴክኖሎጂው ጋር ይቀየራሉና ስድቦችም መልካቸውን ቀይረው ሊሆን ይችላል፤ አለያም ደግሞ የመሳደብ ፋሽኑ አልፎበት ይሆናል እያልኩ ነበር የማስበው፡፡
በሚገርም ሁኔታ ግን ስድቦቻችን ለካስ እኔ አልሰማሁም እንጂ አድገው ኖሯል፡፡ ለካስ ተራቅቀው ኖሯል፡፡ ለካስ ዘምነው ኖሯል፡፡ ለካስ በአንደበት ብቻ መሳደብ ፋሽኑ አልፎበት ኖሯል፤ ሳልሰማ፡፡
ስድቦቻችን ለካስ ‹ሃይ ቴክ› ሆነውላችኋል፡፡ ለካ ‹አይ ሲ ቲ› ተምረውላችኋል፡፡ ‹ለካስ ጎዳና ተዳዳሪ› መሆናቸውን ትተው ‹ኢንተርኔት ተዳዳሪ› ሆነዋል፡፡
እነዚያን የተሰደዱትን ስድቦቻችንን ዛሬ ኢንተርኔት ላይ ነው የምታገኟቸው፡፡ ብሎግ ላይ፣ ፌስ ቡክ ላይ፣ ድረ ገጽ ላይ፣ ፓልቶክ ላይ፣ ኢሜይል ላይ፣ ዝንጥ ብለው ታገኟቸዋላችሁ፡፡ kkkkk  እያሉ በእንግሊዝኛ ሲስቁ፡፡
አንዳንዴ ጭንቅላት ይቀየርና ዘመን ሳይቀየር ይቀራል፡፡ ያኔ እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ መሆን ይመጣል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ጭንቅላታቸው ከዘመኑ ቀደመና ካህኑም፣ ምእመኑም፣ ወታደሩም ሲቪሉም ሊተባበራቸው ቀርቶ ሊከተላቸው አልቻለም፡፡ ብቻቸውን ተቃጥለው፣ የቻሉትንም አቃጥለው ዐረፉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ዘመን ይቀየርና ጭንቅላት ሳይቀየር ሲቀር እንደዚህ ስድቦችን ሁሉ ከሀገር አሰድዶ ‹ሃይ ቴክ› ያደርጋቸዋል፡፡
ኢንተርኔትና ፊስ ቡክ፣ ኢሜይልና ብሎግ፣ ፓል ቶክና ድረ ገጽ ተፈጠሩልን እንጂ በአብዛኛው ፈጣሪያቸው እኛ አይደለንም፡፡ መቼም ይህ ዘመን እምቢ ቢባል እንኳን የመገናኛ ዘዴዎቹ ቤት ድረስ መጥተው የሚያንኳኩበት ዘመን ነውና እነዚህ ዕድሎች እኛው ጋ መጡ፡፡ አንዳንዶቻችን ሳንደርስባቸው ደረሱብን፤ አንዳንዶቻችን ሳንሄድባቸው መጡብን፡፡ ያን ጊዜ የመንገዱንና የመንደሩን ልማዳችንን ይዘን እነርሱ ጋ ወጣን፡፡
በባህላችን ‹የቤት ዐመል ገበያ ይወጣል› ነበር የሚባለው፡፡ አሁን እርሱ መቀየር አለበት፡፡ ‹የቤት ዐመል ኢንተርኔት ይወጣል› ነው መባል ያለበት፡፡ ስንቱ ተሳዳቢ፣ ስንቱ ተራጋሚ፣ ስንቱ ተደባዳቢ፣ ስንቱ ልቡ ያበጠበት የፍየል ወጠጤ ከነ ጠባዩ አንዲትም ሳትነካ ኢንተርኔት ላይ ወጥቶላችኋል፡፡
አሁን ስድብ በኢሜይል ነው፤ ስድብ በብሎግ ነው፤ ስድብ በፌስ ቡክ ነው፤ ስድብ በድረ ገጽ ላይ ነው፤ ስድብ በፓልቶክ ነው፡፡ ስድብ በትዊተር ነው፡፡
አንዳንዱማ እንግሊዝኛ አለማቻሉ የስድብ ሐራራውን እንዳይወጣ እያደረገው እንዴት እንደሚናደድ ታዩበታላችሁኮ፡፡ ‹በእንግልጣር አማርኛ› እንደምንም ብሎ የሚችለውን ያህል ይሳደብና አላረካው ሲል የ‹o› መዓት ወይም ደግሞ የ‹u› መዓት ይደረድርላችኋል፡፡ ሲያንባርቅባችሁ ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ይህ አያረካውም የቡጢ ወይም የስድብ ገጽታ ያለው ፎቶ ወይም ሥዕል ይጨምርላችኋል፡፡ ሌላው ከሁለቱም ያጣ ደግሞ ፊቱ ስድቡን እንዲገልጥለት አድርጎ ፎቶ ይነሣና ይለጥፍላችኋል፡፡
እኔ የምለው፣ መቃወም ወይም መደገፍ ማለት መሳደብ ነው ተብሎ በአራዳ መዝገበ ቃላት ላይ ተተረጎመ እንዴ? ስለምንወደው ሰው፣ አርቲስት፣ ተጫዋች፣ የፖለቲካ ሰው ወይም ድርጅት፣ እምነት፣ አመለካከት ወይም አቋም አንዳች ክፉ የመሰለን ነገር የተሰነዘረ እንደሆን ፍቅራችን በውክልና ስድብ ነው እንዴ የምንገልጠው፡፡ ስለምንጠላው ነገር መልካም ሲነገርስ የተቃውሟችን መገለጫው ስድብ ነው እንዴ? እስኪ በዚህ ጉዳይ በብሎግ፣ በድረ ገጽም ሆነ በፌስ ቡክ የሚደረጉ ውይይቶችን ተመልከቱ፡፡ በሃሳቡ ላይ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ሃሳብ ከሚሰጠው ይልቅ ያንን ሃሳብ ወይም ሰው የተቃወመውን ወይም የደገፈውን ‹ሙልጭ› አድርጎ የሚያጥረገርገው ይበልጣልኮ፡፡ ልክ ልኩን የሚነግረው፡፡
ያውም ደግነቱ ሁለት ነገር እያነቀው፡፡ አንዳንዱ የጊዜ ጥያቄ አለበት፡፡ እንደ መንገዱ ላይ ወይም እንደ ሠፈር ውስጥ እንደልቡ ሰዓት ወስዶ የስድብ መዓት ሊያዘንብ አይችልም፡፡ የመሳደቢያ ሰሌዳውም ውሱን ነው፣ የሚኖረውም ጊዜ ውሱን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለመጻፍ መቻሉ አለ፡፡ በአማርኛ ለመጻፍ የሚችለው፣ በአማርኛ ቢጽፍም ደግሞ ቀልጠፍ ብሎ መጻፍ የሚችለው ጥቂት በመሆኑ፤ በልቡ ያመላለሰውን በኩላሊቱ ያጤሰውን ስድብ ሁሉ ሊያወርድ አልተቻለውምና የኮምፒውተሩን ጠረጴዛ በመደብደብ ወይም ደግሞ በቀይ ወጥ ላይ አጥንት እንደመጨመር፣ በስድቡ ላይ አንዳች የሚያውቃትን እንግሊዝኛ ጣል በማድረግ ግንባር ይመታበታል፡፡
ምንም እንኳን
የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው
በእንግሊዝ አናግሪያቸው
እያልን ስንዘፍን ብንኖርም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታችን ለዐቅመ ስድብ የሚያደርሰን ባለመሆኑ እንዴት ተገላግለናል መሰላችሁ፡፡ በእንግሊዝኛ ተጽፈው በእንግሊዝኛ ውይይት የሚደረግባቸው የፌስ ቡክ ገጾች፣ ድረ ገጾችና ብሎጎች ላይ ሄዳችሁ ›የተማሩ› ተወያዮችን ስታዩኮ ‹ስድብ በእንግሊዝኛ› ምን እንደሚመስል ትማራላችሁ፡፡ አንዳንዱ ወደ ውጭ የወጣ ሰው ሀገሩ አስገድዶት እንግሊዝኛ ተማረ እንጂ ሀሳብ እንዳልተማረ፣ ፕሮናውንሴሽን ቀየረ እንጂ አመለካከት እንዳልቀየረ፣ ከተሰደደበት ሀገር ከገንዘብ በስተቀር ምንም እንዳልወሰደ የሚያጋልጠው የእንግሊዝኛ ስድቡ ነው፡፡
ድሮ እናቶቻችን ልጆቻቸውም ሆኑ ጎረቤቶቻቸው አለያም ደግሞ የመንደር ጋጠ ወጥ ሲያስቸግራቸው ‹ያንተን ነገር እግዜር ያሳየኝ› ብለው ነበር የሚራገሙት፡፡ አሁን ግን ርግማኑ ሳቀየር አይቀርም፡፡ ‹ያንትን ነገር በኢንተርኔት ያሳየኝ› መሆን አለበት፡፡
አፍሪካውያን ‹ከበሮን ሰርቀህ መደበቅ ትችላለህ፣ ከበሮን ሰርቀህ ደብቀህ መምታት ግን አትችልም› ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ከበሮን ሰርቀህ ደብቀህ ብትመታ ትያዛለህና፡፡ ድሮ ድሮ ስድብም እንዲሁ ነበር፡፡ ተደብቆ መሳደብ አይቻልም ነበር፡፡ እዚያው ስትፈልግ ወገብህን፣ ስትፈልግ ጭንቅላትህን ይዘህ ትሳደባታለህ እንጂ፡፡ ቢበዛ ነገር እንዳይከርብህ ሰውዬውን ፊት ለፊት ከምትናገረው በሠፈር ዶሮና ፍየል ወይም ውሻ መስለህ ትሳደባለህ፡፡
እድሜ ለኢንተርኔት፡፡ ‹ሽምቅ ተሳዳቢዎችን› አፍርተናል፡፡ እንደ ሽምቅ ተዋጊዎች የበረሃ ስም የሚጠቀሙ፣ ምሽግ ውስጥ የተደበቁ፣ ሸምቀው አደጋ በማድረስ የተካኑ ሽምቅ ተሳዳቢዎች፡፡ በፌስ ቡክ ሲሆን በውሸት ስምና ፎቶ ተሰውረው፡፡ በድረ ገጽና ብሎግ ሲሆን ደግሞ በስም የለሽነት (anonymous) ተደብቀው የስድብ ናዳ የሚያወርዱ፡፡
ምናልባት እነዚህ ሰዎች ‹ታላላቅ› የሚባሉ ሰዎች ይሆናሉ፡፡ የታወቁም ይሆናሉ፣ ባለ ሥልጣናትም ይሆናሉ፣ የሃይማኖት ሰዎችም ይሆናሉ፣ አስተማሪዎችና መካሪዎችም ይሆናሉ፣ የተከበሩና የተፈሩ ሰዎችም ይሆናሉ፡፡ ግን ሁለት ገጽታ አላቸው፡፡ ‹እንደ ጨዋ በመሬት፣ እንደ ዱርየ በኢንተርኔት›፡፡
እነዚህ ጽሑፍ የሰለቻቸው ወገኖቻችን፣ ሃያ አራት ሰዓት ኢንተርኔትና ስልክ ርካሽ በሆነበት ሀገር የሚኖሩ አምሳያዎቻችንን ደግሞ ፓልቶክ ላይ አግኟቸው፡፡ የፓልቶኩ አስተዳዳሪ እያንዳንዱን ተሰብሳቢ ገሥጾ ገሥጾ እየዘጋ እስከሚያባርራቸው ድረስ መጨፋጨፍ ነው፡፡ እንዲያውም ውይይቱ ከተጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጉዳዩ ይረሳና ‹የተሻለ ስድብ ያለው ማነው?› የሚል ውድድር እየተካሄደ ያለ ይመስላችኋል፡፡ ተው ብሎ የሚከራከረውም ሰው ራሱ እየተሳደበ ነው ተው የሚለው፡፡
አንዳንዴ እኛም በሚገባ እንግሊዝኛ አለመቻላችን፣ ፈረንጆችም አማርኛ አለመቻላቸው እንዴት ጥሩ መሰላችሁ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ለማወቅ ድረ ገጾቻችን ሲጎበኙ ስድብ በየዓይነቱ ነበር የሚኮመኩሙት፡፡ አንዳንዴማ በውጭ የሚወለዱትን ልጆች አማርኛ ካላወቃችሁ እያልን መጨቅጨቃችን ስሕተት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምንድን ነበር የሚያነቡት? ምንስ ነበር የሚሰሙት?
ስድቦቻችን ወደ ኢንተርኔት ሲሰደዱ ብዙ ግፍ ደርሶባቸዋል፡፡ አንቱታ ጠፍቶባቸዋል፡፡ ሽማግሌና ወጣት መለየት አቅቷቸዋል፡፡ ሃሳብና ሰው ተደባልቆባቸዋል፡፡ የሚባልና የማይባልን መለየት አቅቷቸዋል፡፡ የሴትና ወንድ አንቀጽ ተምታቶባቸዋል፡፡
በየፌስ ቡኩ፣ በየብሎጉ፣ ድረ ገጹና ፓልቶኩ ላይ በሚጻፉና በሚነገሩ ስድቦች አንድ ሰው ማን እንደሆነ መለየት ከባድ ነው፡፡ ያ ሰው መቼ ከሀገር እንደወጣ ማወቅ ግን ይቻላል፡፡ በንጉሡ ዘመን በነበሩ፣ በደርግ ዘመን በነበሩ፣ በኢሕአዴግ የመጀመርያዎች ዓመታት በነበሩ ስድቦች አሁንም የሚሳደቡ አሉ፡፡ ያኛው ቀርቶ ሌላ ስድብ መምጣቱን እንኳን ያልሰሙ፡፡ ስድብ መተው ቢያቅታቸው ቢያንስ ስድባቸውን ‹አብዴት› ማድረግ ያቃታቸው ሞልተዋል፡፡
ሊቃውንት ‹መንፈሰ ጽርፈት› የሚሉት አለ፡፡ የስድብ መንፈስ ነው፡፡ ተሳደብ ተሳደብ፣ አጥረግርግ አጥረግርግ የሚል መንፈስ፡፡ ይህ መንፈስ ድሮ በየዐመዱና አተላው ላይ ነበር አሉ የሚገኘው፡፡ በዚህ ዘመን ያልሠለጠን ማን አለ? መንፈሰ ጽርፈትም አተላውንና ዐመዱን ትቶ በየኢንተርኔቱ ሆኗል አሉ የሚዞረው፡፡ ድሮ እናቶቻችን ‹በቀትር አትዙሩ ጋኔን ይመታችኋል› ይሉን ነበር፡፡ ወደፊት ግን ‹ኢንተርኔት ላይ አትውጡ ጋኔን ይመታችኋል› ሳይባል አይቀርም፡፡ እርሱ ነው ስድቦቻችን ሁሉ ከከተማው አሰድዶ ኢንተርኔት ላይ የወሰደብን፡፡ ለመሆኑ እንዴት ይሆን ኢንተርኔትን ጠበል መርጨት የሚቻለው?
ቺካጎ፣ ኤሊኖይስ
©ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በተመሳሳይ ኅትመት ላይ ባለማውጣት ተባበሩ

39 comments:

 1. ## completely unrelated with the above text and you don't have to post this.

  Dear Brother,

  once i read in your blog about the word "maintenance" and its impact on our culture.
  and again now I am surprised with the word (may be you may know) " Opposition " and its impact on our culture. You know we don't have a word for the above word too, we have a word only for enemy and ally. opposition is between enemy and ally but unfortunately we don't have a word for that.
  do you think it is a reason that we see a big gap between our politicians on both sides?

  I was surprised when i know this i want to share to you. feel free to use the idea as a starting point, if you want to.

  Little Brother

  quchera@gmail.com

  ReplyDelete
 2. IT IS A GOOD ARTICLE DANI. BERETA , EGZIABEHER KANTE GAR YIHUN.


  OSLO

  ReplyDelete
 3. ታላቅ ምስጋና ዳንኤል:: ያልተቀየሩና ለለውጥ ያልተዘጋጁ ስብእናዎች ገዝፈው የሚታዩበት ልዩ አለም ተፈጥሯል:: ትክክለኛ ማንነትና ምንነት አለመታወቁ ጉስቁልናው እንዲጨምር አግዞታል::

  ReplyDelete
 4. እስካሁን ራሳቸውን ችለው የስድብ ብሎግና ፓልቶክ የከፈቱ ሌሎች አገሮች አላየሁም እኛ ግን አለን:: እርግጥ ነው ስድቦች በኛ ፒሲ ትልቁን ቦታ ይዘዋል ማለት ይቻላል:: ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የምናከብራቸውን ግለሰቦች ስም ጠቅሰው የሚዘልፉም አሉ:: በግል አመለካከታቸው ሰዎች ይሰደባሉ:: በአንድ ዓይነት ድርጊት ያንዱ ጽድቅ የሌላው ኩነኔ ይሆናል:: እንደምሳሌ የጠቅላይ ሚንስትሩን ልቅሶ ኃይሌም ደርሷል ቴዲም ደርሷል ትርጉሙን የለየው ምን እንደሆነ አይታወቅም:: አርቲስቶች ከአርቲስትነታቸው በፊት ሰዎች መሆናቸው ተዘንግቶ ይሁን በሌላ ምክንያት ገጠሙ ተወኑ ፖለተኩ ተብሎ የማይወርድባቸው ስድብ የለም:: ይሁን ወዳጄ አሳብ ሚዛን ደፍቶ ሰዎችን ለመሳብ በሚደረገው የብርዕ ትግልኮ ማሸነፍ የሚቻለው መማረክ የሚቻለው ስሜት መግዛት በሚችሉ የለውጥ አሳቦች እንጂ በስድብ አይደለም:: በዚህ ጉዳይ ሀይማኖተኞች ነን የሚሉ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት ከራሳቸው በፊት ማንም የማይጎዳ መሆኑን የዘነጉ ይመስለኛል:: ስም በመቀየርም ሆነ አገር በመለወጥ ከፈጣሪ መሸሸግ አይቻልም:: እንከባበር!

  ReplyDelete
 5. "ኢንተርኔት ላይ አትውጡ ጋኔን ይመታችኋል"

  ReplyDelete
 6. Betam yemimech tsihuf new abo dani bierhin yatilekilikew. Amen!!!!!

  ReplyDelete
 7. ‹እንደ ጨዋ በመሬት፣ እንደ ዱርየ በኢንተርኔት›፡፡

  ReplyDelete
 8. ዳኒ አሪፍ ጹሁፍ ነው፡፡ በርታ!!!

  ReplyDelete
 9. መልካም ታዝበሃል ዳኒ ተባረክ! በተለይ በተለያዩ የፖለቲካ መወያያ መድረኮች! እግዚኦ ለመሆኑ የስድብ ዩኒቨርስቲዎች ተከፈቱ እንዴ?! እጅግ አሳፋሪ ለአይንም ለጆሮም የሚዘገንኑ ስድቦች ይነበባሉ...መሰልጠን መሰይጠን ከሆነስ ስልጣኔ ባፍንጫዬ ይውጣ!!!

  ReplyDelete
 10. አበበ ሙ በየነOctober 3, 2012 at 9:58 AM

  ወንድሜ ዳንኤል ለተለመደ ድንቅ ሃሳብህ እና አስተምሮተህ ምስጋናዬ ይድረስህ::

  በየድረገፁ እና ብሎጉ ላይ ያሉ ሰድቦችና ሰንካላ ሃሳቦች የምር የሚያሳፍሩ እና የሚያሳዝኑም ጭምር ናቸው:: ሰዎች ሁሉ መቼም አንድ ሆነው አልተፈጠሩምና ተመሳሳይ ሃሳብ እንዲኖራቸው አይጠበቅም:: በአንድ ጭብጥ ላይ የየራሳቸው ሃሳብና አተያይ ይኖራቸዋል:: ይህንን ሃቅ በመሳት ይመስለኛል በአንድ ጉዳይ ላይ የአንተን ሃሳብና ግንዛቤ የገለፅክ እንደሆነ በሃሳበህ ወይም በግንዛቤህ አልስማማም:: ነገርግን ግንዛቤህ ይሄንና ያን የመሰለ ሕፀፅ አለበት እንደማለት ፈንታ ለምን የጭቃ ጅራፍ እንደምናጮህ ሳስበው ይገርመኛል::

  ሃሳብን በነፃ የመግለፅ ነፃነት ሰፍኖበታል ተብሎ በሚታመንበት እወድያኛው ዓለም እየተኖረ የእኔ ሃሳብ ይህንን ይመስላል በማለትህ ብቻ የስደብና ዘለፋ አቁማዳ ለምን ይዘረገፍብሃል:: እንደ እኔ እንደ እኔ የስድብ ካባ ተጎናፅፎ ሌላዉን ስድብ ከማጎናፅፍ ይልቅ በተነሱ ሃሳቦች ላይ የመከራከሪያ ነጥቦችን እያነሱ መከራከር ብስለትን ያሳያል:: በሁለቱም ወገን ብስለቱ ከሌለ ግን እሰጥ አገባ ንትርክ ላይ ይገባና ጥላሸት እንቀባባለን::

  ስለዚህ ዓመልን በጉያ መያዝ ይሻላል እላለሁ:: መቼም መልካሙን እንጂ መሰዳደቡን ከቀደሙ አባቶቻችን እና እናቶቻችን አልተማርንምና ከአንደበት ሰብሰብ ማለትን ማወቅ አለብን::

  ReplyDelete
 11. Thanks for working hard to make us see things differently.

  Change starts today, I will start using my real name. Every moment should worth something. The time which I spend on Internet will be worthy if I am prepared for change.

  እኔ የምለው፣ መቃወም ወይም መደገፍ ማለት መሳደብ ነው ተብሎ በአራዳ መዝገበ ቃላት ላይ ተተረጎመ እንዴ? ስለምንወደው ሰው፣ አርቲስት፣ ተጫዋች፣ የፖለቲካ ሰው ወይም ድርጅት፣ እምነት፣ አመለካከት ወይም አቋም አንዳች ክፉ የመሰለን ነገር የተሰነዘረ እንደሆን ፍቅራችን በውክልና ስድብ ነው እንዴ የምንገልጠው፡፡

  Berta!

  ReplyDelete
 12. እናመሰግናለን ዳኒ!
  ለኛ ነገርየው/ኢንተርኔቱ ከአዎንታዊ ይልቅ የአሉታዊ አስተሳሰብ ሰጥ-አገባ መድርክ ከሆነ ውሎ አድሯል። አንዳንዱማ የስድብ ትምህርት የወሰደ ይመስል ይህን የስድብ ናዳ ሲያወርደው ይውላል። ሌላው ቀርቶ ኢንተርኔት ከፍቶ ኢሜሉን ሳይይ የማህበራዊ ድረ-ገፁን ከፍቶ "ዛሬ ድብድብ አምሮኛል" የሚለውን ራሱ ቴክኖሎጂው ይቁጠረው። ራሱን የገለጠውም ይሁን ራሱን ሳይገልጥ በሽምቅ የሚዋጋውን ጨምሮ ይህን የፕላኔቱን መድረክ የግላችን የሆነ ያህል ቆጥረን ለሌሎች ሳንጠነቀቅ የመሰለንን የምንለጥፍና የምንናገር ስንቶቻችን እንሆን? ስንቶቻችን ነን ሐይማኖት የግል ሐገር የጋራ የሚለውን መርሖ ረስተን ስለሐይማኖታችን የምንለፍፍ ፣ የሌሎችን የምንነቅፍ? የሚገርመው የኛማ በመንግስት/ሕዝብ ኮምፒውተርና ኢንተርኔት መሆኑ። በግልማ አቅሟ ከየት ትመጣለች። ለዛውም ከዛችው ከፈረደባት ከሻይ፣ ሰዎችን ከማናገርና... ከተረፈች መደበኛ የስራ ስምንት ሰአት ላይ ዘርፈን መሆኑ ነገሩን የበለጠ አንገብጋቢ ያደርገዋል።
  እኔ ልብ እንግዛ ነው የምለው!።

  ReplyDelete
 13. ለመሆኑ እንዴት ይሆን ኢንተርኔትን ጠበል መርጨት የሚቻለው?

  ReplyDelete
 14. በጣም ጥሩ እይታ ነው
  ለዚህ እኮ ነው ሰው እውነቱና ውሸቱ ክፍና ደጉ መለየት አቅቶት መደገፍ ያለበትን ሲነቅፍ
  ማቆም ያለበትን ሲቀጥል አጥፊ እያለ አልሚ ፣ህገ ወጥ እያለ በሀግ እና በስረኣት የሚሄዱትን
  ሲያደናቅፉ የሚታየው መቼም እውነትና ንጋት ይባል የለም…

  ReplyDelete
 15. መልካም ታዝበሃል ዳኒ
  እጅግ አሳፋሪ ለአይንም ለጆሮም የሚዘገንኑ ስድቦች ይነበባሉም ይደመጣሉም:በጣምየሚያሳፍሩ እና የሚያሳዝኑም ጭምር ናቸው::
  በርታ!!!

  ReplyDelete
 16. በእርግጥም የስድብ መንፈስ ተቆጣጥሮናል፡፡ በፊት በፊት ስድብን የምንሰማው ከታክሲ ረዳቶች፣ ከመንገድ አዳሪዎች፣ ከሴተኛ አዳሪዎችና መንደሬዎች ወዘተ . . . ነበር አሁን ግን ቢሮ ቁጭ ብሎ በመንግሥት ሰዓት በመንግሥት ንብረት በሆነው በኢንተርኔት ነው አስፀያፊ ስድብን የምናስተናግደው ፡፡ ይህን ምን ይሉታል ? አንደበት እሳት ነው፡፡ ሰውን ያስቀይማል፡፡ ግን ማንን ትቀየማለህ ? ስድቡን ወይስ የብዕር ስሙን፡፡ በጣም መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ፈውስ ያስፈልጋል፡፡ ፀሎት ያስፈልጋል፡፡ በፊት በፊት በጠዋት በመዝገበ ፀሎቱ በዳዊቱ ነበር አይን የሚገለጠው አሁን አሁን ግን በኢቪዲዮ ኢንተርኔት ነው አይናችንን የምንገልጠው፡፡ በተለይ የፌስ ቡክና የብሎግ ሱስ አይጣል ነው፡፡ መቼ ነግቶ ኮምፒዩተር ላይ በተጣድኩ ነው የሁሉም ሰው ቋንቋው “ መጽሐፍ ዘርግቶ ማንበብ ድሮ ቀረ” አሉ የአማርኛ አስተማሪ፡፡ እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ እንበለ 12 ጊዜ፡፡

  ReplyDelete
 17. በእናት መሳደብ is still common here. What a shame!!!!

  ReplyDelete
 18. it was very good I agrre with you d/danel

  ReplyDelete
 19. Thank you Dn. Daniel. There is a man called Buruk in Addis who writes different Quotable quotes in Amharic. You find his works mainly in taxies. Among his quotes the famous one says, "Af sikefet chinkilat yilekal." Really I like it. But now as you mentioned in the article could we say that "Facebook/paltalk/twitter/ or any else, sikefet chinkilat yilekal?"

  ReplyDelete
 20. By the way I am not a fan of sideb.Weak people use it because they don't express thier ideas in civil manner.I am not surprised there are many tesadabis this time. There are leaders who insult their own citizens like late dictator Meles. There are blogs who insult everyone abbaselama.org. There are 'monks' who insult his brothers and sisters like the dude who spoke at Ethiopian Embassy here in usa.There are many associations ,blogs, individuals who keep insulting. In your next article try to focus on insulting machineries not ordinary individuals who can learn good things if they get role models.

  ReplyDelete
 21. እንደ ጨዋ በመሬት፣ እንደ ዱርየ በኢንተርኔት..really touched me!..Thanks Dani!

  ReplyDelete
 22. ‹እንደ ጨዋ በመሬት፣ እንደ ዱርየ በኢንተርኔት›፡ ሰው መሳይ በሸንጎ እንዳሉት አባቶቻችን፡ ዳኒ አምላከ ቅዱሳን ጥበብን ከተሰበረ ልብ ጋር ጨምሮ ጨምሮ ይስጥህ፡፡

  ReplyDelete
 23. The only thing that I have to do now a days is that enforcing my self to be silent though it has drawbacks !!!
  Withstand for truth not for persons!
  Thank you all !

  ReplyDelete
 24. በእኔ እምነት ማንኛውም ሰው ከመስደብም ሆነ ከመሰደብ ነጻ ይሆናል ብየ አላምንም፡፡ ስድብ ሰዎች አሉታዊ ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው፡፡ እርግጥ ነው የስድቡ ዓይነትና ደረጃ ሊለያይ ይችላል፡፡ ተገቢ የሆነ ስድብ አለ፣ ተገቢ ያልሆነ ስድብ አለ፡፡ ለምሳሌ የሚሰርቅ ሰው “ሌባ” ቢባል ተገቢ የሆነ ስድብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራው ነው ይህንን ስም(ስድብ) ያሰጠው፡፡ የማይሰርቅን ሰው ሌባ ማለት ግን ለተሰዳቢው አይስማማውም(አይገልጸውም)፡፡ ይህ ዓይነቱ ስድብ ተገቢ ያለሆነና መስተካከል ያለበት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በራሳችን ስሜት ተነሳስተን ለሰዎች የምንሰጠው ስያሜ አለ፡፡ ለምሳሌ ዲ/ን ዳንኤል አውቆም ይሁን ሳያውቅ “እንደ ዱርየ” በማለት የገለጻቸው አሉ፡፡ በእኔ እምነት “ዱርየ” የሚለው ቃል አሁን ባለው አረዳድ ከስድብ ውጭ መልካም ስም ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ ሰው “ዱርየ” የሚያስብለው ምን ምን ችግር ሲኖርበት ነው የሚለው ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ለሰዎች ያለን አመለካከት ሲዛባ ይህንን ስሜታችንን የሚገልጽ ታርጋ እንለጥፍላቸዋልን፡፡ ስለዚህ ይብዛም ይነስም ሁላችንም ጊዜና ቦታ ጠብቀን ፊት ለፊትም ይሁን በድብቅ፣ በደብዳቤም ይሁን በኢሜል፣ በሽማግሌም ይሁን በሕጻን ፣ ወዘተ… ተቃውሟችንን በስድብ ልንገልጽ እንችላለን፡፡ ይህ ባህርይ በድንገት የሚመጣ ወይም ተፈጥሯዊ ሳይሆን ከምናድግበት ማኅበረሰብ የምንማረው ነው፡፡ አንድን ቃል ወይም አገላለጽ ስድብ ነው የሚያስብለው ማኅበረሰቡ ሲስማማበት ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ቢሳደብምኳ የተሰደበው አካል ስድብ ነው ብሎ እስካልተረዳው ድረስ ስድብ ሊሆን አይችልም፡፡ በሌላ መልኩ አንድ ሰው የሚናገረውን ነገር ጭራሽ ባላሰበው መንገድ ሌላኛው አካል ስድብ አድርጎ ሊረዳው ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ፈረንጆቹ “ I am responsible for what I say, but not what you understand” የሚሉት፡፡ ብዙ ጊዜ በጎ የማያስብ ሰው ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጡ ሃሳቦችን ከጠቀሜታቸው ይልቅ አፍራሽነታቸው ነው የሚታየው፡፡ እናም የስድብ ናዳ የወረደበት ይመስለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ መፍትሄ በራስ መተማመን ነው፡፡ በራሱ የሚተማመን ሰው ራሱን ስለሚያውቅ ቢሰደብም እንኳ ቦታ አይሰጠውም፡፡ እንዲያውም ስድቡን ወደአስተማሪነት በመቀየር ለቀጣዩ የህይወት ጉዞው እንደ ግብዓት ይጠቀምበታል፡፡ ራሱን የማያውቅ ሰው ግን ቢመሰገንም እንኳ የተሰደበ ነው የሚመስለው፡፡ ለማንኛውም ሰዎችን ተሳዳቢ ከማለታችን በፊት እኛ ከመሳደብ የራቅን ስለመሆናችን እርግጠኛ እንሁን፡፡

  ReplyDelete
 25. Like! I share this to my friends. Thanks

  ReplyDelete
 26. ‹እንደ ጨዋ በመሬት፣ እንደ ዱርየ በኢንተርኔት›፡፡ arif eyeta newe dani

  ReplyDelete
 27. ወዳጄ አዱኛ የዲያቆን ዳንኤልን ሀሳብ ያገኘህው አልመሰለኝም፤ ሰውን በግብሩ መጥራት ስድብ አያሰኝም ጌታችን በወንጌል ለዚያች ቀበሮ ሂዱና ነገሩዋት እንዳለ እንዲሁም ቅዱስ ዬሐንስ ይሁዳን ሌባ ነበረ እንዳለው፤ ዳኒ እያለ ያለው ሰዎችን በግብራቸው ስለመጥራት ሳይሆን ጸያፍ ቃላትን ስለመጠቀም እና ሀሳብን ብቻ ስለመደገፍና መቃወም ነው፡፡ ‹ስድብ ሰዎች አሉታዊ ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው፡፡› ያልከው የመግለጽ ችግር ካልሆነ ሰዎችን በምንፈልገው መንገድ ብቻ ካልተንቀሳቀሱ ‹ዋ!› ዓይነት ነው የተሰማኝ፡፡ ‹አንድን ቃል ወይም አገላለጽ ስድብ ነው የሚያስብለው ማኅበረሰቡ ሲስማማበት ነው፡፡› ባልከው ሀሳብ እስማማለሁ አፍሪካውያን አሜሪካውያን ከኒግሮ፣ ጥቁር፣ በመጨረሻም አፍሪካውያን አሜሪካውያን እንዲባሉ እንደፈለጉት፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. እንደ ጨዋ በመሬት፣ እንደ ዱርየ በኢንተርኔት›፡test answer

   Delete
 28. ስድቦች መሰደዳቸው አይደለም ችግሩ ጥገኝነት ካገኙበት አገር ነው:: ዲያቆን ዳኒ በትምህርቱ የችግሩን ሦስት ገጽታዎች አስቀምጧል:: ዘይቤ ቀየረ አለን:: በዚህ ምክንያትም ሀላፊነት የሚወስድ ለሆነ ግብ መልክት የሚያስተላልፈውን አካል አናውቀውም:: ስም ማጥፊያ ይሁን ተግሳጽ በማይታወቅ መልኩ የሚመጣን ስድብ ማንስ ቢሆን ይሸከም ዘንድ ምን ግድ አለበት? ሁለት ለብዙ መልካም አጋጣሚዎች መዋል የሚችለውን ቴክኖሎጂ እውቀትና ጊዜ ያለ አግባብ እያባከንንና ትውልድ እየገደልን መሆናችንን አሳሰበን:: አንዳንዶቻችን ፓልቶክና ብሎጎች ላይ የሚሰራውን የማየት እድሉ ስላላጋጠመን ይሆናል:: ብታምኑም ባታምኑም አዲስ ስድብ ላለው ማይክ የሚለቀቅበት የስድብ ውድድር የሚካሄድበት ፓልቶክ ያውም በሀገራችን ስም ተከፍቶልናል:: ጠቃሚ ቢሆን አድራሻዎቹን አስቀምጥላቹ ነበር እንጂ ብሎግ ከፍቶ ስድድብ እንደ መዝናኛ የሚቆጥር ትውልድ ማፍራታችንን ነው የነገረን:: ሦስተኛም ችግሩ ጸበል የማይረጭ መሆኑን ሲናገር ምን ያህል ችግሩ የከፋ መሆኑን ያጠይቃል::

  አዱኛ ከቅኝት ወጥተሀል:: ያ ሌላ ነው በሌላ መልኩ የሚታይ ይመስለኛል:: ስድብም በበጎ መልኩ የሚገለጽ ገጽታ የለውም:: ማለት የፈለከውን በተገቢ ቃል ትችት ሂስ ተግሣጽ እያልክ መለየት አለብህ:: ያም የራሱ መንገዶች አሉት:: ስድብ ግን ይለያል:: ስድብ የአቅመ ቢሶች /ደካማ ሰዎች/ የሚሰነዝሩት ዱላ ነው:: ስድብን በመንፈሳዊ መነጽር ካየነው ወደ ከፍተኛ ክህደት የሚያደርስ የክፋት መንደርደሪያ ነው:: ስድብ አቅም ካገኘ ከአንደበት አልፎም የግብር ኃጢአት ወደመሆንም ይመጣል:: ቅድመ አያቱ ሀሜት ከሆነ ልጆቹ ደግሞ መደባደብና መገዳደል ይሆናሉ:: ስድብ በቀላሉ ንስሀ እንኳን ለመግባት አቅልለን የምንመለከተው ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ሊሰረይ የማይችለውን ትልቁን ኃጢአት ሊያሠራን የሚችል ክፉ ነገር ነው:: ስለሆነም ዲ/ን ዳንኤል ድንቅ እይታ! ቃለ ሕይወት ያሰማልን መንግሥተ ሰማያት ያውርስልን:: ማኅበራዊ ሂስ ብቻ ሳይሆን ወንጌል ነው:: ይህ መንፈስ ከዘመኑ ጋር ዘምኖ ታላላቅ ኃጢአቶችን የሚያሰራ የክፋት መንፈስ ነው:: እንደ ወንድማችን በጎውን ለወገኖቻችን በመሥራት ቴክኖሎጂውን መቀደስ አያስፈልገንም ትላላችሁ?

  ReplyDelete
 29. ፊርማዬ በመንገድ ላይ ስትጓዝ ከአንድ ጎረምሳ ጋር ትጋጫለች፡፡ ጎረምሳውም በለመደ አፉ በእናቷ ይሰድባታል፡፡ ፊርማዬ ነገሩን በስድብ ብቻ አላየችውም ነበርና ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ትወስደዋለች፡፡ ፖሊስም ልጁን ሕግ ፊት አቅርቦ ያስቀጣዋል፡፡ ይህንን ነበር ፊርማዬ የነገረችን ‹ስድብን ዝም አትበሉ› ብላ፡፡

  ReplyDelete
 30. በታላቁ መፅሐፍ የሚሳደብ ቢኖር ይሙት ይላል፡፡ እየሞት ነው ማለት ነው በተሳደብን ቁጥር፤ አምላክ ይጠብቀን ሀጢአት ከመስራት፡፡

  ReplyDelete
 31. መልካም ታዝበሃል ዳኒ ተባረክ! በተለይ በተለያዩ የፖለቲካ መወያያ መድረኮች! እግዚኦ ለመሆኑ የስድብ ዩኒቨርስቲዎች ተከፈቱ እንዴ?! እጅግ አሳፋሪ ለአይንም ለጆሮም የሚዘገንኑ ስድቦች ይነበባሉ...መሰልጠን መሰይጠን ከሆነስ ስልጣኔ ባፍንጫዬ ይውጣ!!!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ፊርማዬ ነፍስሽን ይማረው
   ዲ/ን ዳኒ እድሜህን ያርዝመው፤
   በፍርድ ቀን አምስቱ የስሜት ህዋሶቻችን ይከሱናል፡፡
   1. ዓይን ክፉ ነገር ለምን አየሽ/ህ
   2. ጆሮ ለምን ክፉ ሰማሽ/ህ
   3. ምላስ ላምን ክፉ ተናገርሽ/ህ (ስድብ…)
   4. አፍንጫ ለምን መጥፎ አሸተትክ
   5. እጅ (ቆዳ) ለምን ክፉ ዳሰስሽ/ህ
   እንዳንከሰስ አስተውሎ መራመድ ለዓለም ህዝብ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ማስተዋልም የሚዳብረው ከመማር (ከማምበብ) ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የአዳምና የሄዋን ዘር ሆይ፤ ጥሩ ሃያሲና ጥሩ ተናጋሪ ለመሆን የንባብ (የማወቅ) ባህላችንን እናዳብር እላለሁ፡

   Delete
 32. ዲ/ን ዳኒ መልካም ታዝበሃል

  ReplyDelete
 33. As always its a great view.Dn Tnank you for the deepest view u have and shair us,so we could change ourself after reading yr message .I just want give one comment about this topic.In this generation ppl could be either good or bad.That is true,but when someone who choose to be a bad and writ,and say some unnessary words,WHY ppl gives attantion for it?? why westing time?? why reading it or responding it????I think we could make a change by ignoring it,by skiping the blog or the topic.Bc internate gives us a lots of knowleges,information,lessons.....whatand how to use it??it's ppl choce.

  ReplyDelete
 34. enezih tesadabiwoch terefe aihud yibalalu. miknyatum ayhud getan sisadebu endeneber zarem kenesu betemarut gibr yisadebaluna.eta fentachew keayihud gar new sewon mesadeb egziabhern mesadeb newa. sew yetefeterew bearya silase silehone.

  ReplyDelete
 35. እኔ በኢንተርኔት ልሳደብ ተዘጋጀቸ ነበር ትቻለሁ ሌሎች 100000…. ሰዎች እንደሚማሩበት ተስፋ አደርጋለሁ ቃለ-ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete