![]() |
ዐቃቤ መንበር አቡነ ጳኩሚስ ድምጽ ሲሰጡ
|
የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 118ኛውን ፓትርያርክ የመምረጡ ሂደት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሻግሯል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ አራት ሂደቶችን
ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ የጥቆማና ማጣራት፣ የመጨረሻዎቹን አምስት ዕጩዎች የመወሰን፣ ለዕጣ የሚቀርቡትን ሦስት አባቶችን መምረጥና የመጨረሻውን
አባት በዕጣ መምረጥ ናቸው፡፡
በዚሁ መሠረት ከተጠቆሙት ወደ አሥራ ሰባት አባቶች መካከል የማጣራቱና አምስቱን የመወሰኑ ሂደት እጅግ ረዥም ጊዜ የወሰደ
መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ ሂደት ሁለት ከባባድ ችግሮች ተጋርጠውበት ነበር፡፡ የመጀመርያው ፈተና በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ከተጻፈውና
የግብጽ ቤተ ክርስቲያንም ሕግ ከሚደነግገው ውጭ ሀገረ ስብከት ያላቸው አባቶች ራሳቸውን ሳይቀር ለዕጩነት መምረጣቸው፣ ከዚህ በፊት
አንዳንድ ችግሮች ተከስተውባቸው የነበሩ አባቶችም በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ መግባታቸው ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ሕግ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ራሳቸውን ከዕጩነት እንዲያገልሉ በአስመራጭ ኮሚቴውና
በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ አባቶችና ሽማግሌዎች የማግባባትና የማረም ሥራ ሲሠራ ነበር፡፡ ለሁለት ጊዜ ያህል ሱባኤ ታውጆ፣ ጳጳሳቱም
ሁሉ ወደ አባ ብሶይ ገዳም ገብተው በጸሎትና በውይይት ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የተወሰኑት አባቶች
‹እኔ በሺኖዳ መንበር መቀመጥ የለብኝም› እያሉ ራሳቸውን ከዕጩነት አግልለዋል፡፡