Thursday, August 16, 2012

ኢምፓላ

እነሆ አሁን በደቡባዊ አፍሪካ በምትገኘው ዚምባቡዌ ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ዋና ከተማዋን ሐራሬን በአውሮፕላን ማረፊያው በኩል ለቅቀን እየወጣን ነው፡፡ የሐራሬ አውሮፕላን ማረፊያ ሲባል እንዲህ እንደ አዲስ አበባው እንዳትጠብቁት፡፡ የጥንቷ የአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያን አስቡና፣ ሩብ ጨምሩባት፡፡ ሀገሪቱ በገጠማት የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት አየር መንገዳቸው ዓለም አቀፍ በረራውን ማቆሙን ሰምቻለሁ፡፡
የዛሬን አያርገውና ሀገሪቱ ፓሪስን በውበቷ፣ አየር ላንድን በእርሻዋ፣ ቺካጎን በከተማ ቅርጽዋ፣ ካናዳን በኢኮኖሚዋ፣ ትጣቀሳቸው እንደነበረች ዛሬም እንኳን መከራውን ተቋቁሞ የሚገኘው ማንነቷ ይናገርላታል፡፡
ከሐራሬ ወጣ ስትሉ ትናንት ሰፋፊ እርሻዎች የነበሩ ሜዳዎች ጦርነት የተካሄደባቸው የአፍጋኒስታን መንደሮች መስለው ይታያሉ፡፡ በእርሻው መካከል እዚህም እዚያም የቆሙ ትራክተሮችን ታያላችሁ፡፡ በላያቸው ላይ ሣር በቅሏል፡፡ የሳቫና የሜዳ ሣር  እንኳን ርግፍ አድርጎ የሚተወው አግኝቶና እንዲያውም እደግ እደግ ይለዋል፡፡ የእርሻ ምርቶች ሲቀነባበሩባቸውና እስከ አሜሪካና ካናዳ ሲላክባቸው የነበሩት የእርሻ ፋብሪካዎች ተገትረው ቀርተዋል፡፡ 
 እነዚህ በነጮች ተይዘው የነበሩትና በኋላ በአዲሱ የመንግሥት አዋጅ የተወረሱ ቦታዎች ናቸው፡፡ እንደማያቸው ግን ነጮቹም ጥቁሮቹም አልተጠቀሙባቸውም፡፡ የሀገሪቱንም ኢኮኖሚ ጎድተውት አልፈዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱን የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ሀገሪቱን እያሰቃዋት ነው፡፡ ዛሬ የዚምባቡዌን ገንዘብ አታዩትም፡፡ ምናልባት እርሱን ለማየት ሙዝየም መሄድ ያስፈልጋችሁ ይሆናል፡፡ በቦታው የአሜሪካ ዶላር ተተክቷል፡፡ በዶላር መጠቀማቸውና አብዛኛውንም ዕቃ ከደቡብ አፍሪካ ማመጣታቸው ተደማመሮ ኑሮውን ሰማይ አስነክሶታል፡፡ አንድ ኪሎ ድንች ዋጋው እስከ ሃምሳ ብር እየደረሰ እንዴት እንደሚኖር ማሰብ ነው፡፡ 
መቼም ቅኝ ገዥዎችም በዘመናቸው ርኅራሄ የላቸውምና ከነጻነት በኋላ ያለውን የሕዝቦችን ግንኙነት ያበላሹታል፡፡ የዚምባቡዌ ነጮች እስከ 80 በመቶ የሚደርሰውን የሚታረስ ለም መሬት ይዘውት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የመንግ ሥትንና የሕዝብን ስሜት ጎድቶታል፡፡ መሬትን ከነጮች ወደ ሀገሬው ሰዎች የማሸጋገሩ ሂደት ግን የተፈለገውን ለውጥ አላመጣም፡፡ ሀገሬውንም የባሰ ድኻ፤ መሬቱንም ጠፍ አደረገው እንጂ፡፡
ይህንን እያሰብንና እያየን ከሐራሬ 22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ምቢዚ ጌም ፓርክ ገባን፡፡ ሀገሪቱ በደኅና መሠረት ላይ የተመሠረተች በመሆኗ አንድ ቦታ ለመሄድ የአቅጣጫ ማመልከቻ መሳርያውን (ጂ..ኤስ.) መጠቀም ይቻላል፡፡ መንገዶቿ ስምና ቁጥር አላቸው፡፡ እያንዳንዱ ቤትም ደረጃውን የጠበቀ ቁጥር አለው፡፡ እኛም ወደ ፓርኩ የተጓዝነው በማመልከቻው እገዛ ነበር፡፡ ‹‹መንገዱን አልፈህ ዛፍ አለ፣ ከዛፉ አጠገብ አንዲት ጉልት የሚሸጡ ሴትዮ አሉ፣ ከእርሳቸው አጠገብ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ አለ፣ ከእርሱ ዘወር ስትል ታገኘዋለህ›› ከሚለው የቦታ ማመልከቻ የምንላቀቅበት ቀን ናፈቀኝ፡፡ ጉልቱም ሲቀር፣ ዛፉም ሲቆረጥ፣ የቆሻሻ ገንዳውም ሲነሣ አድራሻው የሚቀየር ቤት ውስጥ እስከ መቼ እንኖራለን?
እዚህ ፓርክ ጥቂት የዱር እንስሳት ናቸው ያሉት፡፡ አጋዘኑም፣ ቀጭኔውም፣ የሜዳ አህያውም እኛው ሀገር ሞልቷል፡፡ ባይሆን ወጣ ብሎ የማየትና የመዝናናት ልማዱ የለንም እንጂ፡፡ ገንዘቡም ቢኖር እነ እንትና ሥጋ ቤት እያሉ በየት ይተርፈናል፡፡ እኛው ራሳችን ሥጋ በል እንስሳት ሆነን መዋል ስንችል ሥጋ በል እንስሳትን ለማየት ፓርክ መሄድን አበሻነታችን ብዙም የሚቀበለው አይመስልም፡፡
እዚህ ፓርክ ውስጥ እኛ ሀገር የሌሉ ኢምፓላ የሚባሉ እንስሳት አሉ፡፡ ኢምፓላዎች በኬንያ፣ታንዛንያ፣ ስዋዚላንድ፣ ናሚቢያ፣ ቦትስዋና፣ ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ አንጎላ፣ ደቡብ አፍሪካና ዑጋንዳ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ዛሬ አንድ ዝርያቸው ብቻ ይቅር እንጂ ጥንት እጅግ ብዙ ዝርያዎች በምድር ላይ እንደ ነበሯቸው ጥናቶች አሳይተዋል፡፡ በኢትዮጵያም ጠፍቶ እንጂ አንደኛው ዝርያቸው ይኖር እንደነበር በሐዳር በተደረጉ የአርኬዎሎጂ ምርምሮች ላይ በተገኙ የጥንት ቅሬቶች ታውቋል፡፡
 ኢምፓላዎች አጋዝን መልክ ያላቸው፣ ፍየል የሚያክል ቁመት የተጎናጸፉ፣ ቀንዳም የዱር እንስሳት ናቸው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ በጠቅላላው ቁጥራቸው ወደ ሁለት ሚልዮን እንደሚደርሱ ይገመታል፡፡
ኢምፓላዎች በሁለት ቡድን የሚኖሩ እንስሳት ናቸው፡፡ የላጤዎች ቡድንና የአንስት ቡድን፡፡ የላጤዎቹ ቡድን በወጣት ወንዶች የተገነባ ሲሆን በአንድ ቡድን ውስጥ እስከ ሠላሳ የሚደርሱ ላጤዎች ይኖሩበታል፡፡ የአንስቱ ቡድን ግን የዚህን ስድስት ጊዜ እጥፍ ይበልጣሉ፡፡ በአንዱ የአንስት ቡድን ውስጥ እስከ 200 የሚደርሱ አባላት ይኖሩበታል፡፡
ኢምፓላዎች ግዛት አጠር እንስሳት ከሚባሉት ወገን ናቸው፡፡አካባቢያቸውን ይከልላሉ፡፡ ሌሎች ወደ አካባቢያቸው እንዳይገቡም ይከላከላሉ፡፡ የአንስቱ ቡድን የሚመራው በአንድ ድል አድራጊ ወንድ ኢምፓላ ነው፡፡ ይህ ድል አድራጊ ወንድ ኢምፓላ ይህንን ሥልጣን ለማግኘት በአካባቢው የሚገኙትን ወንድ ኢምፓላዎች ሁሉ ድል ማድረግ አለበት፡፡ በቀንዱ እየወጋ ቁም ስቅላቸውን ያሳያቸውና ከአካባቢው እንዲሰደዱ ያደርጋቸዋል፡፡ እዚህ ግዛቱ የሚፈቀደው ለ199 ሴቶችና ለአንድ ወንድ ብቻ ነው፡፡ ሥርዓቱ ባለ አንድ አውራ ነው፡፡
ችግሩ የሚከሰተው እነዚህ 199 ሴቶች ወንድ የወለዱ ጊዜ ነው፡፡ መጀመርያ አካባቢ እነዚህን ሕፃን ወንዶች የሚናገራቸው የለም፡፡ እንደ ልባቸው እየጋጡና እየዘለሉ በዚያው በአንስቱ አካባቢ ይኖራሉ፡፡ የእናታቸውን ጡት ይጠባሉ፤ የገዥውን ኢምፓላም ክብካቤም ያገኛሉ፡፡ ከፍ ሲሉ ግን ነገር ይመጣል፡፡ እነርሱም ወንድነት ይሰማቸዋል፡፡ ትከሻቸው ማበጥ፣ ድምፃቸው መጎርነን፣ ልባቸው መተበት ይጀምራል መሰል፡፡ ገዥውን ኢምፓላም በጎሪጥ ማየት ሳይጀምሩ አይቀሩም፡፡ ‹‹ደግሞ እርሱ ማነው?›› ዓይነት ነገር ያመጣሉ፡፡
ታድያ ገዥው ኢምፓላ ይኼ ነገር አይስማማውም፡፡ ከእርሱ የከፋም ሆነ ከእርሱ የተሻለ ወንድ በአካባቢው እንዲታይ አይፈልግም፡፡ አንስቱም ይህንን ነገር ማወቃቸው ጥሩ አይደለም፡፡ እርሱን የሚያደንቁና የሚከተሉ እንጂ እርሱን የሚያነፃፅሩ መሆን የለባቸውም፡፡ ያን ጊዜ ታድያ ያንን አለሁ አለሁ ማለት የጀመረ ኢምፓላ ገዥው ኢምፓላ በቀንዶቹ ከግራ ከቀኝ እየወጋ መቆሚያ መቀመጫ ይነሣዋል፡፡
ጠባይ ማሣመር፣ ‹‹ከዚህ በኋላ አላደርገውም›› ብሎ መማል ምንም ዓይነት ምሕረት ኣያስገኝም፡፡ ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው፡፡ ያንን የአንስት ቡድን ለቅቆ ላይመለስ መውጣት አለበት፡፡ ይህ የተባረረ ወጠጤ ኢምፓላ ዕድል ገጥሞት ያልሞላ ቡድን ካገኘ ከሌላ የላጤ ቡድን ጋር ይቀላቀላል፤ ያለበለዚያም የተባረሩ ወጠጤዎች እየተሰባሰቡ አንድ የኢምፓላ የላጤ ቡድን ይመሠርታሉ፡፡
የላጤዎቹ ቡድን መሪ የለውም፡፡ ለዐቅመ መሪነት ያልደረሱ ወጠጤዎች የሚከማቹበትና የሚቆዝሙበት ቡድን ነው፡፡ ቁዘማው በሁለት ነገሮች ምክንያት የሚመጣ ነው፡፡ በአንድ በኩል እጅግ ለምለም የሆነውንና ትናንት የነበሩበትን የአንስት ቦታ በማስታወስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ወደፊት ይህንን ገዥ ኢምፓላ እንዴት ማስወገድ እንደሚችሉ በማሰብ፡፡
እነዚህ ወጠጤ ኢምፓላዎች የሚኖሩበት አካባቢ እምብዛም ለም አይደለም፡፡ ለምለሙንና ለኑሮ ምቹ የሆነውን አካባቢ ገዥው ኢምፓላ በሥልጣኑ ክልል ሥር ያደርገዋል፡፡ ያ የርሱ ጥብቅ ግዛት ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ተወዳጅና ተፈቃሪ ይሆን ዘንድ በሚመራው ቡድን ውስጥ ሁለት ነገሮችን እንዲያደርግ ይጠበቅበታል፡፡ ለምለሙን አካባቢ በግዛቱ ውስጥ አድርጎ አንስቱን መመገብና ቡድኑን አድጌያለሁ ከሚል ሌላ ወንድ ኢምፓላ መጠበቅ፡፡
ታድያ በዚህ የተነሣ ወጠጤዎቹ ኢምፓላዎች የሚኖሩበት አካባቢ ለእነርሱ ምቹ ባለመሆኑ ከቦታ ወደ ቦታ እንዲንከራተቱ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በገዥው ኢምፓላ የሚመራው አንስቱ ቡድን ለምለም ግዛቱን የሚለቅቀው የድርቅ ወቅት ከመጣና ምግብ ፍለጋ መጓዝ ግዴታ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
እነዚህ ወጠጤ ኢምፓላዎች እርስ በርሳቸው በቀንዳቸው እየተሞካከሩ ራሳቸውን ለጎበዝ አለቅነት ሲያዘጋጁ ነው የሚኖሩት፡፡ አንድ ቀን ‹‹የፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት›› ቀንዱን በሌሎች ላይ ፈትኖ ፈትኖ ይመጣና ያንን ገዥ ኢምፓላ ይሞክረዋል፡፡ መቼም ጉድ አንድ ቀን አይደል፡፡ ያ ልቡን አሳብጦ ቀንዱንም ሞርዶ የመጣ ወጠጤ ገዥውን ኢምፓላ ገጥሞ ድል ካደረገው የአንስቱን ቡድን የመምራቱን በትረ ሥልጣን እንደ እርሱ ልቡ ያበጠበት እስኪመጣ ድረስ ይረከብና ይቀጥላል፡፡
የቀድሞው መሪ ወዴት ይሄዳል? አትሉም፡፡ የእርሱማ ዕጣ ፈንታ የከፋ ነው፡፡የወጠጤው ቡድን አያስጠጋውም፡፡ ቀድሞ ጨቁኗቸው የለም? በርሱ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፤ የወደቀ ዛፍ ምሣር ይበዛበታልና በዚያ በተሳለ ቀንዳቸው የተሸነፈ ሰውነቱን እየወጉ ድራሹን ነው የሚያጠፉት፡፡ ከአንስቱም ቡድን እኔ ነኝ ባለ ሌላ አሸናፊ ተባርሯል፡፡ ከሁሉም የወጣ ይሆንላችሁና የስደት ኑሮውን ይገፋል፡፡ ወጠጤዎቹም፣ ገዥውም እንዳያገኙት እየተደበቀ ያገኛትን እየቀመሰ ቀሪውን ዘመኑን መግፋት ነው፡፡ ምናልባትም እርሱም በዚህ መንገድ ነበርና ወደ ሥልጣን የመጣው በአንዳንዱ እየተደሰተ፣ በሌላውም እየተቆጨ ይተክዝ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ
‹‹አትበል ምንቅር ምንቅር
አትበይ ምንቅር ምንቅር
እኛም በጊዜያችን እንዲህ አርጎን ነበር›› የሚለውን ዘፈን በኢምፓላኛ ይዘፍን ይሆናል፡፡
የምኒሊክ ዘመን አልፎ በመሐል ሠፋሪ ጦር፣ ቀሪውን ኑሯቸውን በእንጦጦ ማርያም እንዲገፉ ተወስኖባቸው ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ወደ እንጦጦ የወጡት እቴጌ ጣይቱ ጓዛቸውን ጠቅልለው እንጦጦ ሲወጡ ቁስቋም አካባቢ ቆም አሉ አሉ፡፡ ዘወር ሲሉ ቤተ መንግሥቱ እሳት መስሎ ታያቸው፡፡ እንዲህ ሆኖ አይተውት አያውቁም ነበር፡፡ ‹‹ያ ምንድን ነው?›› ብለው ጠየቁ አሉ፡፡ ‹‹እርስዎ የነበሩበት የምኒሊክ ቤተ መንግሥት›› አሏቸው፡፡ ትክዝ አሉና ‹‹ነበር ለካ እንዲህ ቅርብ ኖሯል›› አሉ ይባላል፡፡
ይህንን ታሪክ ልነግረው አስቤ ነበር፡፡ ግን ኢምፓላኛ አልችልም፡፡

12 comments:

 1. Wey Dani ante ayalqibihim. yenegeroch megetatem yilual yih new.ምናልባትም እርሱም በዚህ መንገድ ነበርና ወደ ሥልጣን የመጣው በአንዳንዱ እየተደሰተ፣ በሌላውም እየተቆጨ ይተክዝ ይሆናል፡፡ edilu ketegegne. abo yimechih

  ReplyDelete
 2. betam des yemil tireka new........GOD BE WTH U BRO

  ReplyDelete
 3. diakone danile ibret enedmen kremwale. bezu gezy serawocewoten ektatlalwe ewente btame bezu ngre agenecybacwalwe egezihabhyre qri zmnewote
  ne yebarkelen erso shama nwote
  na. yeqreta enho sle imepala anbbekun Yastemeralem geb esaten besate endmaytfa mane bngracew

  ReplyDelete
 4. I think this is closely associated with the African style of political power transition.

  African leadership needs to think better than their wild- beast & should be able to create an all-encompassing system to all members of their nations. This, I supposes would help them to live a better life at their own home, when they will be out of office & get old.

  Other wise, they will be doomed to live the life of Impalas at their old ages.

  Good piece of history & lesson.
  God bless you & Ethiopia!

  ReplyDelete
 5. 'Beseferut quna mesefer' yilihal yihe new

  ReplyDelete
 6. ውድ ወንድማችን ወግህ ውበት አለው፤ መድረሻው ግን መዝገበ ቃላት ይሻልና...
  አንዳንዴ አንድ ብዕርኛ እንዳለው”የጫማ ቁጥር ስጠየቅ፤ ከበሬው አልጀምርም፡”እንዳለ ወጉን አሳጥረህ
  ኢንፓላዊ መልእክትህ ብታጎላው ምን ይመስልሃል? ምኞቴ ብዙነው ከፍሎሪዳ ጫካ

  ReplyDelete
 7. lemigebaw ejig tilk meliekt alew.Lekas sew ena empala anmuanuaru ena astesasebu and aynet noroal?

  ReplyDelete
 8. አፍሪካውያን ለካ ከመ እንስሳ ሆነናል

  ReplyDelete
 9. Loved it, you are great Auther, thanks Dani

  ReplyDelete
 10. አሪፍ ነው ግን ከምን ተነስተህ ነው መቼም ካለደረሰብህ አታወጣው ግን መልካሙን ጎዳና ተመልከት እውነትን ፈልጋት መልካም ጡመራ

  ReplyDelete