ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር፤ ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቃለ መጠይቅ ማድረግ
በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ በሚገኘው ቢሯቸው ወደ አሥር ሰዓት አካባቢ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር ተገኝቼ ነበር፡፡ ያ ቃለ መጠይቅ
ወደ አራት ሰዓታት ያህል የፈጀና በሐመር መጽሔት ላይ በተከታታይ የወጣ ነበር፡፡
በመካከል ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በወቅቱ የነበረችበትን
ሁኔታ የሚያነሣ አንድ ጥያቄ ተሰነዘረላቸው፡፡ መጀመርያ በመዳፋቸው አገጫቸውን ያዙና ወደ ጠረጲዛቸው አንገታቸውን ደፉ፡፡ በዚያም
ለረጅም ሰዓት አቀርቅረው ቆዩ፡፡ ምን እያሰቡ ይሆን ብለን እናስብ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ቀና ሲሉ ዕንባዎቻቸው በሁለቱም
ጉንጮቻቸው ላይ መንታ ሆነው ይፈሱ ነበር፡፡ ምንም አላሉንም፡፡ ዝም ብለው አዩን፡፡ ከዚያም ይቀረጹበት የነበረውን ቪዲዮ እንዲጠፋ
አዘዙ፡፡ እኛንም ተቀመጡ አሉን፡፡ ግራ ገብቶን ተቀመጥን፡፡
ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያን ዕለት ሲናገሩት የነበረውን ነገር ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ሲናገሩት ሰምቼ አላውቅም፡፡
ሲነግሩን ያለቅሱ ነበር፡፡ እኛም ብንሆን በኀዘን ድባብ ውስጥ ነበርን፡፡