click here for pdf
ማክሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2004 ዓም የተዘጋውን የኢንተርኔት መሥመር ለማስከፈት እዚህ አያት መንገድ ጉርድ ሾላ ያለው የቴሌኮሙኒኬሽን ቅርንጫፍ ሄድኩላችሁ፡፡ በጠዋቱ ሠልፉ ለጉድ ነው፡፡ ምናለ የቀበሌ መስተዳድሮች ለአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሥልጠና ቢሰጡ? ቀበሌ እንኳን የጠፋው ሰልፍ እዚህ ከነ ሙሉ ክብሩ ይንጎማለላል፡፡ አዛውንትና አሮጊቶች እግራቸው እየተንቀጠቀጠ ውጭ በብርድ ቆመዋል፡፡ ያውም ከሠላሳ ደቂቃ በላይ፡፡
እንደምንም ተራ ደርሶኝ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ እዚያም ለካስ ሌላ ሰልፍ አለ፡፡ ደግነቱ እዚህ የምትሰ ለፉት ተቀምጣችሁ ነው፡፡ ፊት ለፊታችን የተገተሩት ኮምፒውተሮች ብዙዎች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ሰዎች ግን ሦስት ኮምፒውተር ለአንድ ሠተራኛ እንዲደርሳቸው ሆነው ነው፡፡ አሁን እነዚህ ሁሉ ኮምፒውተሮች የሚሠራባቸው ከሌለ ለምን ተገዙ? ከተገዙስ ለምን አይሠሩም? ማን መልስ ይሰጣችኋል? ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ አለ ያገሬ ሰው፡፡