Tuesday, June 5, 2012

ከየት እንጀምር


ወዳጄ ሆይ ለምን ከሌለህ ነገር ትጅምራለህ? በሰው ላይ ኀዘን የሚጨምረው፣ ተስፋ መቁረጥም የሚያደርሰው፣ የበታችነትንም የሚያመጣው፣ ቅዠትንም የሚያባብሰው ከሌለ ነገር መጀመር ነው፡፡ እስኪ ራስህን አስበው? ስላላገኘሃቸውና ስላልደረስክባቸው፤ ስላመለጡህና ስላልተደረጉልህ ነገሮች ከማሰብ በእጅህ ስላለውና ስለደረስክበት ነገር ለምን አታስብም፡፡
በአንተ እጅ ያለው ነገር በአንተ እጅ ከሌለው ነገር ይበልጣል ወይስ ያንሳል? በእጄ ያለው ትንሽ ነገር ነው፣ በእጄ የሌለው ግን ዓለም በሙሉ ነው፤ ታድያ እንዴት በእጄ ያለው በእጄ ከሌለው ነገር ሊበልጥ ይችላል? እንደምትል አይጠረጠርም፡፡ ሲገመትም እንደዚያው ነው፡፡
እንደ እውነቱ ግን በእጅህ ያለው ነገር በእጅህ ከሌለው ነገር ይበልጣል፡፡ እንዴት? አልክ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በእጅህ ያለው ነገር ያንተ ነው፡፡ በእጅህ የሌለው ግን ገና ያንተ አይደለም፡፡ ያንተ የሆነው ያንተ ካልሆነው ነገር ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም ያንተ በሆነው ነገር መጠቀም ትችላለህ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልትጠቀም አትችልም፡፡ ያንተ በሆነው ነገር ልታዝዝ ትችላለህ፤ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልታዝ አትችልም፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር ማግኘትህን ርግጠኛ ሆነሃል፡፡ ያንተ ያልሆነውን ማግኘትህን ግን ርግጠኛ መሆን አትችልም፡፡ ያንተ በሆነው ነገር ልትወስንበት ትችላለህ፤ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልትወስን አትችልም፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር ለሌላው መስጠት ትችላለህ፤ ያንተ ያልሆነውን ግን መስጠት አትችልም፡፡ ካለህ ነገር ላይ ቆመህ የሌለህን ማየት ትችላለህ፤ ከሌለህ ነገር ላይ ቆመህ ግን ያለሀን ነገር ማየት አትችልም፡፡
እናም ወዳጄ ስትቆጥር ካገኘኸውና ከሆነልህ ነገር ጀምረህ ቁጠር፡፡ ባላገኘኸው ነገር ከምትበሳጭ ባገኘኸው ነገር ተደሰት፡፡ ባልሆንከው ነገር ከምታዝን በሆንከው ነገር ሐሴት አድርግ፡፡ ባልያዝከው ነገር ከመበሳጨት በያዝከው ነገር ሥራበት፡፡ ባልሆንከው ማንነት ከመቃዠት በሆንከው ማንነት መኖር ጀምር፡፡
ይህ ማለት ምን ይመስልሃል?
ስትጓዝ እያረጋገጠክ ተጓዝ፡፡ መጀመርያ ያለህን ዕወቀው፣ ከዚያም ባለህ ነገር ምን ያህል እንደ ተጠቀምክበት ርግጠኛ ሁን፡፡ ላለህ ነገር ዋጋ ስጠው፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር አክብረው፡፡ ያን ጊዜ የሌለህን ታገኘዋለህ፡፡ የሌላውን ሰው ትዳር አይተህ፣ እርሱን ተመኝተህ፣ እንደዚያ በሆንኩ እያልክ በሌለህ ነገር ከማዘን፤ እስኪ በአንተ ትዳር ውስጥ ምን መልካም ነገሮች አሉ? የትኞቹን ተጠቅመህባቸዋል? የትኞቹን አድንቀሃቸዋል? ለየትኞቹስ ዋጋ ሰጥተሃቸዋል፡፡ የሌለህን ብቻ የምታይ ከሆነ ያለህን ማወቅ አትችልም፡፡ ስለ ሌለህ ነገር ብቻ የምታስብ ከሆነ ባለህ ነገር መጠቀም አትችልም፡፡ አሁን የምትሠ ራበትን ሞያ ወይም ቢሮ ወይንም መስክ በሚገባ ተጠቅመህበታል? ሠርተህበታል? ከዚያስ ማግኘት ያለብህን አግኝተሃል? ወይስ ሌላ ሞያ የምትፈልገው፣ ሌላ ቦታ መቀጠርም የምትመኘው፣ ሌላስ መስክ ላይ መዋል የምትጓጓው ሰዎች አደረግነው ሲሉ ስለሰማህ ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ታች ከፍል በተማሩት ምንም ሳይሠሩበት ወደ ላይ ይወጣሉ፡፡ በመጀመርያ ዲግሪያቸው አንዳች ሳይፈይዱ ሁለተኛና ሦስተኛ ይይዛሉ፡፡ አኗኗራቸውንና አስተሳሰባቸውን ስታየው ግን ታች ክፍል ናቸው፡፡ ለምን ይመስልሃል? መጀመርያ በያዙት ነገር ሳይረኩና ሳይጠቀሙ፣ የያዙትን ነገር ፈጽመው ማወቃቸውን ሳያረጋግጡ ሰው ስላደረገው ብቻ ሌላውን አደረጉ፡፡
በቤታችን ውስጥ ይህኮ የለንም ብለን የገዛናቸው የማንጠቀምባቸው አያሌ ዕቃዎች አሉ፡፡ በየቁም ሳጥናችን ውስጥ ስለሌለን ብቻ የገዛናቸው የማንለብሳቸው ብዙ ልብሶች አሉ፡፡ ምናልባት ግን እነርሱን ከመግዛታችን በፊት ምን እንዳለን ብናስብ ኖሮ እነርሱን የሚተካ ወይንም የሚያስከነዳ ነገር በቤታችን ነበረ፡፡ እስኪ ሰዎችን ስማቸው፡፡ እዚህ መሥሪያ ቤት የተቀጠሩ የሚሠሩበትን እያማረሩ ያኛውን መሥሪያ ቤት ያደንቃሉ፡፡ እዚያ ያሉት ደግሞ ያሉበትን እየረገሙ እዚህ ያለውን ያመሰግናሉ፡፡ ለምን? ሁሉም ሌላ ያያሉ እንጂ ያላቸውን አያዩም፡፡
የት እንደምትሄድ ሳታውቅ አትሂድ፡፡ የት እንደምትሄድ ለመወሰን ደግሞ ከየት እንደተነሳህ ማወቅ የግድ ነው፡፡ ምናልባትምኮ አለመሄዱ ከመሄዱ የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዴት መሄድ ብቻውን ዓላማህ ይሆናል? ለአንዳንዶች መማር ብቻ ዓላማቸው ነው፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ ማግባት፡፡ለአንዳንዶች መነገድ፡፡ ለአንዳንዶች ውጭ ሀገር መሄድ፡፡ ለአንዳንዶች ቤተ ክርስቲያን መሄድ፤ እነዚህ መንገዶች እንጂ መድ ረሻዎች አይደሉም፡፡
ሰውዬው መንገድ ሲሄድ አንድ ሽማግሌ ያገኛል፡፡
«አባቴ ይኼ መንገድ ይወስዳል ይላቸዋል፡፡
«የት ለመሄድ ፈልገህ ነው» አሉት ሽማግሌው፡፡
«የምሄድበትን አላውቀውም» አላቸው፡፡
«የምትሄድበትን ካላወቅከውማ የትኛውም መንገድ ይወስድሃልኮ» አሉት ይባላል፡፡
የት እንደሚሄድ ያልወሰነ ሰው ያለበትን የማያውቅ ነው፡፡ የት እንደምትሄድ ለመወሰንኮ ከየት እንደተነሳህ ማወቅ የግድ ነው፡፡ እንዴት መሄድ ብቻውን ዓላማህ ይሆናል? ለአንዳንዶች መማር ብቻ ዓላማቸው ነው፡፡ ምን? ለምን? እስከየት? ከዚያስ ምን ለመሥራት? መልስ የላቸውም፡፡
የሚሄድበትን በትክክል የማያውቅ ሰው ምንጊዜም ባለው ነገር ሳይሆን በሌለው ነገር ላይ ይመሠረታል፡፡ ምናልባትም የሚሄደው ወደመጣበትም ሊሆን ይችላል፡፡ ያለውን የማያውቅ የሌለውንም ሁሌ የሚናፍቅ ሰው እንደዚህ ነው፡፡
አንድ ሰው አንዲት የከሳች በቅሎ ነበረችው፡፡ አወጣና ሸጣት፡፡ ከዓመታት በኋላ ገበያ ሲወጣ አንድ ሰው እጅግ ያማረች የኮርቻ በቅሎ ይዞ ተመለከተ፡፡ ሰውዬውን ጠጋ ብሎ
«ጌታው ይህችን የመሰለች በቅሎ ከየት ትገኛለች እባክዎ? እኔም ለመግዛት እፈልግ ነበር» አላቸው፡፡
ሰውዬውም «እኔም በአጋጣሚ ከሰው ነው የገዛኋት፡፡ ስገዛት ከስታ ልትሞት ደርሳ ነበር፡፡ የሸጠልኝ ሰው እንደነገረኝ ባለቤቷ ለበቅሎ ግድ አልነበረውም፡፡ እኔ የበቅሎ ጠባይ ስለማውቅ ነው ከሰውዬው የገዛሁዋት፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ በደንብ ስይዛት ጊዜ እንዲህ ያማረች በቅሎ ሆነች» አሉት፡፡
«መቼ ነበር የገዙት አላቸው
«የዛሬ አራት ዓመት ከዚሁ መንደር ገዝቷት ሲሄድ ነው ለምኜ የገዛሁት» አሉት፡፡
ራሱን እየነቀነቀ ተመለሰ፡፡ በቅሎዋ የርሱ ነበረች፡፡ የሰውዬው ያህል ግን የበቅሎውን ዋጋ አላወቀውም ነበር፡፡ ተፈላጊዋን ምርጥ በቅሎ ሽጦ ምርጥ በቅሎ ይፈልጋል፡፡ እኛም ያሉንን ምርጥ ነገሮች እየሸጥን የሌሉንን ምርጥ ነገሮችን እንፈልግ ይሆናል፡፡
አንዳንድ ጊዜኮ የምናማርረው ችግር ስለደረሰብን ብቻ ሳይሆን ያለንን ስለማናውቀው ጭምር ነው፡፡ ችግር በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ችግር ችግር የሚሆነው መፍትሔ መስጠት ለማይችል ሰው ብቻ ነው፡፡ መፍትሔ መስጠት ለለመደ ችግር ትምህርት ቤት ነው፡፡ ችግርኮ የፍች፣ የመለያየት፣ የጠብ፣ የኩርፊያ፣ የክስ፣ የመልቀቂያ፣ መንገድ የሚሆነው ለዐቅመ ቢስ ሰው ነው፡፡ ለብርቱ ሰው ግን ሞት የትንሣኤ መቅድም ነው፡፡
የሌለህን ነገር ብቻ ካሰብክ ያለህንም ታጣዋለህ፡፡ ያለህን ነገር ካሰብክ ግን የሌለህንም ታገኘዋለህ፡፡
እስኪ የአንድ ሰው ታሪክ ልንገርህ፡፡
ሰውዬው በሚስቱ ሞያ ይማረራል፡፡ ገና ወደ ቤቱ ለመምጣት ሲያስብ የሚበላው እንጀራና ወጥ ትዝ ሲለው ሐሞቱ ፍስስ ይላል፡፡ «እንግዲህ ለዚያ ሊጥ ልሂድለት» ብሎ ይመጣል፡፡ ይህ ነገር ሰለቸውና ከሚስቱ ጋር ተፋታ፡፡ ወደ ጓደኛውም ቤት ሄደ፡፡ ጓደኛው አልጋ አንጥፎ ተቀበለው፡፡
ማታ ራት ቀረበ፡፡ ምን የመሰለ ነጭ ጤፍ ላይ አልጫና ቀዩ ተጋድሞ ቀረበለት፡፡ በአንድ በኩል ቃሪያው፣ በአንድ በኩል ስልጆው፣ በአንድ በኩል ፍትፍቱ፣ በአንድ በኩል አተር ክኩ ተሰለፈ፡፡ «ወይ ሞያ እኔማ ኖርኩ አይባልምኮ» እያለ ያማርር ጀመር፡፡ «አንተማ ታድለህ» ይለዋል ጓደኛውን፡፡ «ይሁን እስኪ» ይላል ያኛውም፡፡ ጠላው ሲቀርብ ደግሞ እያደነቀ ጠጣ፡፡ «ከኖሩ ላይቀር እንዲህ ነው» ይል ጀመር፡፡ ያችንም ባለሞያ ሚስት በምስጋናና በአድናቆት አረሰረሳት፡፡
በልተው ሊያጠናቅቁ ሲሉ ጋባዡ ሊጠጣበት ያነሣው ብርጭቆ ተሰበረ፡፡ ደነገጠ፡፡ ሚስት ከጓዳ መጣች፡፡ «ምንድን ነው የተሰበረው አለች፡፡
« የምትወጅው ብርጭቆ ተሰበረ፡፡» አላት ባልዋ በተስለመለመ ድምፅ፡፡ ተናደደችና አንዴ በጥፊ አላሰችው፡፡ ጓደኛው ደነገጠ፡፡ «እንዲህ ሰብረህ ሰብረህ የአባት የናቴን ስጦታ ጨረስከው፡፡ አንተ ምን ታደርግ ተንቀባርረህ ከነ ጓደኛህ ትልፋለህ» እያለች ቁም ስቅሉን ታሳየው ጀመር፡፡ ባልዬው ጠባይዋን ያውቃልና ዝም አለ፡፡ ያም ጓደኛው «ምን ለብርጭቆ ደግሞ ነገ ይገዛል፤ ዋናው ጤና ነው» አለ ነገር ያበረደ መስሎት፡፡ «አንተ ደግሞ አርፈህ ተቀመጥ፤ ሚስትህን እንደዚህ አማረሃት ይሆናል ይኼኔ፤ ቀላዋጭ» አለችና አቀመሰችው፡፡ ተፈታተነው ስሜቱ፡፡ ግን እንግድነቱ በልጦበት «ኧረ የኔዋስ እንዳንቺ» አለና ጀምሮ ተወው፡፡ ወደ ጓዳ ገባችና አንድ ፍልጥ ይዛ መጣች፡፡ እስኪ ጨርሰው አለቺው፡፡ ዓይኑ ተቁለጨለጨ፡፡ «እንዳንቺ የባሰባት አይደለችም» ሲላት ፍልጡን ይዛ መጣች፡፡
ይህንን ሲያይ ባልዬው «ቀስ ብለህ አምልጥ» አለው፡፡
በዚያ ሌሊት እየገሠገሠ የሚስቱ እናት ሄደ፡፡
እናቲቱም «ምነው ልጄ» አሉት
«እማማ፤ ከሌሊት ፍልጥ፣ የቀን ሊጥ ይሻለኛል ብዬ መጣሁ፡፡ አላቸው ይባላል፡፡
ወዳጄ ያለህን ካላሰብከው የባሰው ላይ ትወድቃለህ ያልኩ ለዚህ ነው፡፡
እስኪ ወዳጄ ያለህን ዕወቀው፤ አክብረው፤ አሟጠህ በሚገባ ተጠቀምበት፤ በዚያ ኑርበት፤ አጊጥበት፡፡ ከዚያ ሌላውን ለመያዝ ፈልግ፡፡ ባለህ የማትረካ ከሆንክ ግን ሩጫህ የተሻለ ነገር ፍለጋ ሳይሆን ሌላ ነገር ፍለጋ ብቻ የሆናል፡፡
ሳንሆዜ፣ ካሊፎርንያ

49 comments:

 1.  እጅግ ግሩም ምክር ነው:: እንደው እግዚአብሔር ጤናና እድሜ በረከቱንም ያብዛልህ ::

  ReplyDelete
 2. በእውነት ምን ያህል የሚያስደስት እና የሚያጠነክር ምክር እንደሆነ ለመግለፅ ቃላቶች የሉኝም :: እግዚአብሔር በቸርነቱ በበረከቱ አይለይህ ::

  ReplyDelete
 3. Good Article, thank you Dani

  ReplyDelete
 4. የሌለንን ፍለጋ በጥዋቱ የምንክዋትን ስንቶቻችን እንደሆን እግዜር ይወቅ።አወ ብዙ በጣም ብዙ ነገሮችን ለካንስ አጥተናልና ።በጣም ይገርማል ሰው ለካንስ ከራሱ የበለጠ በማንም አይሞኝም ።
  ዳንኤል እግዚአብሔር ይስጥህ ፣ይበልጥም ፀጋውን ያብዛልህ።

  ReplyDelete
 5. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 6. Thank you so much Dani! I was in the mood of complaining just before I surfed into your blog. Thanks to God who guides us in His way through His servants. May God bless you more!
  'ያለህን ዕወቀው፤ አክብረው፤ አሟጠህ በሚገባ ተጠቀምበት፤ በዚያ ኑርበት፤ አጊጥበት፡፡' LOVE it!

  ReplyDelete
 7. ከሌሊት ፍልጥ፣ የቀን ሊጥ...

  ReplyDelete
 8. what can I say, it touches my daily life
  thanks alot

  ReplyDelete
 9. thank u keep it up !!
  SIMACHEW
  from A.A

  ReplyDelete
 10. ዳኒ እውቀትህን ጌታ ከፍ ያርገው ወዳጄ ያለህን ካላሰብከው የባሰው ላይ ትወድቃለህ ያልኩ ለዚህ ነው፡፡
  እስኪ ወዳጄ ያለህን ዕወቀው፤ አክብረው፤ አሟጠህ በሚገባ ተጠቀምበት፤ በዚያ ኑርበት፤ አጊጥበት፡፡ ከዚያ ሌላውን ለመያዝ ፈልግ፡፡ ባለህ የማትረካ ከሆንክ ግን ሩጫህ የተሻለ ነገር ፍለጋ ሳይሆን ሌላ ነገር ፍለጋ ብቻ የሆናል፡፡
  ዮናስ ከሮም

  ReplyDelete
 11. ዝ ጽፋት ዘአርሳኒ አለ ተነሳሂው አባት:: የዛሬ አራት ዓመት ገደማ የትምህርት እድል አገኘሁና አሜሪካ ቀልጨ ቀረሁ:: ሩጫዬ የተሻለ ነገር ፍለጋ መስሎኝ ነበር ሌላ ነገር ፍለጋ መሆኑን ያረጋገጥሁት በዚህ ጽሑፍ ነው:: እስኪ አስቡት ትምህርቴን እጮኛዬን ሥራዬን አገሬን ወላጆቼን... አጥቻለሁ:: ያለኝን ሁሉ ጥዬ ነበር ሌላ ነገር ስፈልግ የኖርኩት:: እንደተባለው የምሄድበትን አላውቀውም ነበርና መድረሻዬም አይታወቅም:: ይኽው ደስታ እንደራቀኝ አለሁ:: ወዳጄ የሚያሳዝነው ግን አሁንም ከቀኑ ሊጥ የሌቱን ፍልጥ መምረጤ ነው:: ምን አድርግ ትለኛለህ:: አሁን ተነስቼ ከየት እንድጀምር ያምርሀል? ያለኝንማ ጥዬው....

  ReplyDelete
  Replies
  1. እግዚአብሔር ይርዳሽ/ህ

   Delete
 12. Kale hiwot yasemalin!!

  ReplyDelete
 13. ዳንኤል ብዙዎቹን ስብከቶችህን እየጠላሁ ግን አዳምጣለሁ። ብዙዎቹን ታሪክና ወግ ቀመስ ጽሁፎችህን ግን በጣም እወዳቸዋለሁ። አንድ ነገር እንደተረዳሁ ይሰማኛል። እንደእኔ እንደእኔ ስብከቶችህ በእነ ጳውሎስ ለዛ የታሹ ስላልመሰለኝ ይሆናል። የታሪክና የወግ ጽሁፎችህ ግን ከላይ የተሰጠኸህና በጥረትህ የተገለጸ እንደሆነ ለማመን ፈቅጃለሁ። ይህ የኔ ምልከታ ነው። አንተ ራስህን የምታይበት መነጽር የራስህ ነው። በታሪክ ዘገባና በወግ ቅመማ ውስጥ የወንጌሉ ስብከት ስለሚኖር እዚያ ላይ ብታተኩር ምን ይመስልሃል? ለላይኛው ጽሁፍህ ግን በአበው ወግ በዘለሰ አንገት አክብሮቴን ሰጠሁ። በርታ!

  ReplyDelete
 14. ዳኔ በቅድሜየተለመደው ምስጋናየ የድረስህ:: ዝ ጽፋት ዘአርሳኒ አለ ተነሳሂው አባት:: የዛሬ አራት ዓመት ገደማ የትምህርት እድል አገኘሁና አሜሪካ ቀልጨ ቀረሁ:: ሩጫዬ የተሻለ ነገር ፍለጋ መስሎኝ ነበር ሌላ ነገር ፍለጋ መሆኑን ያረጋገጥሁት በዚህ ጽሑፍ ነው:: እስኪ አስቡት ትምህርቴን እጮኛዬን ሥራዬን አገሬን ወላጆቼን... አጥቻለሁ:: ያለኝን ሁሉ ጥዬ ነበር ሌላ ነገር ስፈልግ የኖርኩት:: እንደተባለው የምሄድበትን አላውቀውም ነበርና መድረሻዬም አይታወቅም:: ይኽው ደስታ እንደራቀኝ አለሁ:: ወዳጄ የሚያሳዝነው ግን አሁንም ከቀኑ ሊጥ የሌቱን ፍልጥ መምረጤ ነው:: ምን አድርግ ትለኛለህ:: አሁን ተነስቼ ከየት እንድጀምር ያምርሀል? ያለኝንማ ጥዬው....
  አይዞህ ፍልጡን ሊጥ የሜያደርግ የድንግል ልጅን አጥብቀህ ያዝ ሁሉም ለበጐ ይሆንልሃል ::ከቻልክ ጥሩ መንፈስና ቀና ልቦና ያላቸውን የበተክርስትያን ልጆች ጓደኛ ይኑርህ :: ተሰፉህ ትለመልማለች:: በርታ!

  ReplyDelete
 15. Kale Hiwot Yasemalin...Leteshale nuro ena letimihrt biye metahu Ezih Europe...Yihene Betechrstian betwat weyinim beserk endalhed 800km yahil new yalew, tsebel endalil yelem, bicha besekene menfes salaselasilew Alamayen timihrtna yeteshale nuro adrige yan hulu yehageren yebetechrstianen habtat tewkut, Beselam Lehager endiyabekagn betselot asbugn...Kalehiwotin yasemalin Dn. Daniel Kibret.

  ReplyDelete
 16. betame konjo miker new enamsgnalene.......

  ReplyDelete
 17. Dn Daniel kalehiowt yasemalin, tsegawun yabzalih. Wogenoche yalenin yalemayet abazie enji besewoch sayihon beEgziyabher yetemertech hager Ethiopia'n, nefisachewun yirewuna, ye'abatachin Abune Shinoda'n aserefinot yeteketelu wondimoch Egziyabher setitonal ... yalenin yemiyayina yemiyastekim ayinelibona yisten. Amen !
  ...wub...

  ReplyDelete
 18. Dn Daniel kalehiowt yasemalin, tsegawun yabzalih. Wogenoche yalenin yalemayet abazie enji besewoch sayihon beEgziyabher yetemertech hager Ethiopia'n, nefisachewun yirewuna, ye'abatachin Abune Shinoda'n aserefinot yeteketelu wondimoch Egziyabher setitonal ... yalenin yemiyayina yemiyastekim ayinelibona yisten. Amen !
  ...wub...

  ReplyDelete
 19. ወዳጄ..."በነ ጳውሎስ ለዛ ያልታሹ..."ነው ያልከው? ወይ ይልሺው? የግድ ጥቅስ ተጠቅሶ የጳውሎስ መልክት... የጴጥሮስ መልክት ካልተባለ ስብከት ያለም እንዴ..? ልማር ከተባለ ከምንም መማር ይቻላል። ችግሩ አይነ ልቦና ላይ ነው።እሱ ካልተከፈተ እያዩ መታወርም አለ እኮ።

  ReplyDelete
 20. QALE HIYWOT YASEMALIN DANIYE, EGZIABEHARE ABZITO ,ABZITO TSEGAWIN YISTIH!!

  ReplyDelete
 21. «የዛሬ አራት ዓመት ከዚሁ መንደር ገዝቷት ሲሄድ ነው ለምኜ የገዛሁት» አሉት፡፡
  ራሱን እየነቀነቀ ተመለሰ፡፡ በቅሎዋ የርሱ ነበረች፡፡
  betam yetekemem mikir
  betam ameseginalehu
  long live to you all we have in this country
  bye

  ReplyDelete
 22. Thank you very much my Dear ...

  ReplyDelete
 23. "መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፥ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ"
  ራእ.2:9
  "I know thy works, and tribulation, and poverty, but thou art rich"
  Revelation of John 2:9

  ReplyDelete
 24. Egziabher Yistilin Dn Daniel Yaleninin Akbren Endintekemibet Medhane Alem Hulachininim Yiridan AMEN!!!

  ReplyDelete
 25. Wow, what an article! it has to reach to everyone beyond this blog.

  Long live Dani

  Tg, London

  ReplyDelete
 26. ምርጥ ጽሑፍ !!!!! ልኬን ነገርከኝ፡፡ ተባረክ

  ReplyDelete
 27. lela denq eyeta. !!!!!!!!!

  ReplyDelete
 28. Kal hiwet yasemalne Deyakon. Ysemanewn kal lehewet yadrglen.

  ReplyDelete
 29. Good Article. It sounds like my story. All the things said in the article are absolutely true.


  May God bless your service Dn. Daniel!

  ReplyDelete
 30. What a great article. Learned much. Please keep it up. May God Bless you and ur family.
  May God give you the strength to go on(serving Him)

  YeAwarew

  ReplyDelete
 31. A big lesson! I've found it to be much related with my day to day life, thank u Dani!

  ReplyDelete
 32. አንዳንዶቹ ብሎጋቸውን አርቲ ቡርቲ /ብዙም የማይጠቅሙ/ ጽሑፎች ሲያጨናንቁት ይታያሉ፡፡ ምናለ እንደ አንተ ሰው ልብ ውስጥ ሰተት ብሎ የሚገባ ጽሑፎችን ቢያቀርቡልን፡፡

  ReplyDelete
 33. I found the article as it is really essential for us specially at this particular time.We most of the time are longing for what we haven't in our hand by neglecting of ours.It makes us aware as to how we should pay a sort of attention to prioritize to what we have possessed in our hand before wishing something to have which may not be actualized soon. that we have to give values for we have been rendered whether it is a bad or good one. Because we have to be loyal enough to God both in the time of plenty and adversity in that case we will be getting what ever we deserve to have.So our way of living have to establishing on regional philosophy.

  ReplyDelete
 34. "ለብርቱ ሰው ግን ሞት የትንሣኤ መቅድም ነው፡፡"በተለይ እኔ ባለኝ ነገር ተመስገን ብየ አላዉቅም የእግዚበሄርን ክንድ እንኳን እያየሁት እየረዳኝ ተመስገንን ግን አላዉቀዉም፡፡ ብቻ ባንተ አድሮ ያስተማረን የአባቶቻችን አምላክ ልክ እንደ ሁልጊዜዉ ዛሬም ተናገረኝ፡፡ ልቦና እንዲሰጠኝ ጸልዩልኝ፡፡ አንተን ግን ዲን ዳንኤል እግዚበሄር አምላክ በቤቱ ለዘለአለም ይትከልህ

  ReplyDelete
 35. Thanks! dani it seams my story. you are like a mirror, i see my self in.

  ReplyDelete
 36. ሰናይ ዜና

  ReplyDelete
 37. ወይ ዳኒ ……… እኔን ታውቀኛለህ እንዴ? ሙሉ በሙሉ እኮ ስለ ራሴ ነው የጻፍከው፡፡ ባለኝ ነገር አንድም ቀን፣ ምን አንድ ቀን እላለሁ ለሰከንድ ተደስቼ አላውቅም፡፡ ሁልጊዜ ሽቅብ እንዳየሁ ለሰዎች የሆነላቸው ነገር ሁሌ እንዳስጎመጀኝ አምላኬ ሁሌም እኔን እንደጎዳኝ ነው የሚመስለኝ ግን እኔ በአሁን ሰዓት ያለኝ ደረጃ ባለ ዲግሪ ባለ ሥራ ባለ ቤት በሰው ሰውኛ ለሰው የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ አሉኝ ምናልባት ከትዳር በስተቀር እሱም በመንገዱ ላይ ነኝ ግን በእጄ የያዝኳቸው ነገሮች ሁሉ ከሌሎች የሚያንሱ ስለሚመስሉኝ ሌላ ላይ ከመማተር ቦዝኜ አላውቅም እና ዳኒ በጣም አሪፍ ጽሑፍ ነው ያስነበብከኝ ምናልባት ከሕመሜ ሊፈውሰኝ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

  ReplyDelete
 38. What a nice article at the right time for me!!!! Thanks Dani!!

  ReplyDelete
 39. I really appreciate the writer. I personally believe that the idea as expressed by Danel touches almost every body's life.

  ReplyDelete
 40. ሳሚ (ወ/ሚካኤል)June 23, 2012 at 1:37 PM

  መምህር ዳኒ....ለትንሽ ዘገየህብኝ !!! ሰው በፈንጣጣ ምክኒያት አይኑ ክጠፋ ቡሃላ የፈንጣጣ ምድሃኒት ቢወስድ ምን ዋጋ አለው??? ግን የእይታህ ሃይል ሌላ ዓይን ይተካልና ስለወደፊቱ መጽናኛ ሁኖኛል!!! ዳኒየ ስለእውነት ስሞኑን ባንተ ጽሁፎች የማየው መንፈስ እኔን ለመምከር ያለመ የእግዚአብሄር መንፈስ ሆኖ አግኝቸዋለሁ!!!! አንተም እንደወረደ ስለሞላኸኝ ዋጋህ በሙሉ በመቅደሰ ስላሴ እስከመጨረሻይቱ ህቅታህ ድረስ እወነት ትሁን!!!!! አሁን ግን ነገን በሌላ ዓይን እንዳይ መንገዱን ስላመለከትከኝ ሳይሆን የማለቀው ነገ አስፈርቶኝ ዛሬ በጀ ያለውን ወርቅ የመጣሌን ስህተት ስላጎላህብኝ በእወነት እራሴን አመመኝ!! ተባረክ!!! ሰፊ እድሜን ከዚሀ ማስተዋለ ጋር ላንተ!!!!!አሜን!!!

  ReplyDelete
 41. Fetare Yibarkhi!

  ReplyDelete
 42. betam arief asteyayet new!!! egziabher ewketuen abezeto yesthe!!

  ReplyDelete
 43. አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ጽሁፎችህን ብዙ ጊዜ አላነባቸውም ነበር። ነገር ግን እንደ መዘናግያ ነበብኩት ሀሳብህ ብዙ አሰስተማረኝ፣ አዝናናኝ፣ አሳወቀኝ። ያንቴም የግል ህይወት ባስተማርከን መንገድ የበለጸገ እንዲሆን ብርቱ ምኞቴ ነው። የሰው ልጆች ሁሉ ሊማሩበት የሚገባ ትልቅ እውቀት ያለህ ሰው ነህ። የሰውን ልጅ ማገልገል የሚመስል ታላቅ ስራ የለምና በርታ፣ ማድረግ የሚቻልህን ሁሉ እንድትፈጽመው ትጋ! ጤና ይስጠልኝ!

  ReplyDelete