Wednesday, June 13, 2012

ዕውቀት እንረዳለን

አራተኛ ክፍል እያለሁ የሂሳብ መጽሐፍ ለአራት ነበር የሚታደለን፡፡ ታድያ የቤት ሥራ የተሰጠ ቀን መጽሐፉን ለመውሰድ ተረኞች ያልነበርነው ሦስታችን የቤት ሥራውን ስንገለብጥ ከተማሪው ሁሉ ወደ ኋላ እንቀር ነበር፡፡ ሕፃናት ስለ ነበርን፣ ከዚያም የተሻለ ስላላየን መጽሐፍን ለአራት ለአምስት መውሰድ የዓለም ሥርዓት መስሎን ነበር ያደግነው፡፡ የመጽሐፍ ኮንደሚኒየም አትሉም፡፡
የሚገርመው ነገር ይህ አሠራር በሁለተኛ ደረጃም ሆነ በኮሌጅ ደረጃ ሳይሻሻል ነው እኛ ትምህርት «ጨርሰን» የወጣነው፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ እያለሁ እንድናነብ የሚሰጠንን መጽሐፍ ቤተ መጻሕፍት ሄዶ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሌላ ሰው ቀድሞ ያወጣውና ወረፋ ያዙ እንባላለን፡፡ ወረፋው ሳይደርሰን ፈተናው ቀድሞ ይደርሳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከነ አካቴው መጽሐፉ አይኖርም፡፡ ምነው? ስንል «መምህሩ አውጥቶታል» እንባላለን፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ «በኮርስ አውት ላይኑ» ላይ ያለው የመረጃ መጻሕፍት ዝርዝር ከሌላ የተገለበጠ ይሆንና ቤተ መጻሕፍቱ እንኳን ሊኖረው ሰምቷቸውም አያውቅ፡፡
 እንዲህ እኛ መጽሐፍ ብርቅ ሆኖብን አድገን በኋላ ገዝታችሁ አንብቡ ስንባል ውቃቤ ሊቀርበን አልቻለም፡፡ እኛ በመጽሐፍ መከራ እንጂ መች ደስታ አይተን እናውቅና፡፡ ታች ክፍል እያለን መጽሐፉን እንድንጠቀምበትና እንድንፈተፍተው የሚፈቅድልን አልነበረም፡፡ ወላጆቻችንም አነበባችሁ? ከሚሉን ይልቅ « መጽሐፉ ይቀደድና የሚከፍልልህ አታገኝም» ነበር የሚሉን፡፡
እንዲያውም አምስተኛ ክፍል አንድ ጓደኛችን ትዝ ይለኛል፡፡ በዓመቱ መጀመርያ ለሦስትም ይሁን ለአምስት ከሌሎች ጋር መጽሐፍ ወስዶ ነበር፡፡ አንድ ሦስቱ መጽሐፍ ለግል ይሰጥ ነበር መሰል፡፡ ታድያ ለግል የሚሰጠውን መጽሐፍ የቤት ሥራውን ከሌሎች ተማሪዎች ሲገለብጥ እናየው ነበር፡፡
በዓመቱ መጨረሻ መጽሐፍ ልንመልስ ስንሰለፍ የርሱ መጽሐፍ አበባ እንደመሰለ ነበር፡፡ አንዳንድ ጓደኞቻችን ተናደዱበት፡፡ «አንተ በኛ መጽሐፍ የምትሠራው የራስህ እንዳይበላሽ ነው አይደል እያሉ አፋጠጡት፡፡ እርሱ ግን «ማርያምን» እያለ ይምል ይገዘት ነበር፡፡ ግን ማን ይመነው፡፡ ሲጨንቀውና ከጓደኞቹ ሊቃቃር ሲሆን ጊዜ እውነቱን ነገረን፡፡ «እማዬ ስለቆለፈችበት ነው» አለን፡፡ አንድ ላይ «ለምን አልነው፡፡ «ከተበላሸ የምከፍለው የለኝም ብላ ቆለፈችበት»፡፡ አለን አንገቱን አቀርቅሮ፡፡
ምን ያድርግ ለእርሱ እናት ዋናው ነገር ልጃቸው ያመጣው መጽሐፍ ሳይበላሽና ተጨማሪ ወጭ ሳያስ ከትል መመለሱ እንጂ መጠቀሙ አይደለም፡፡ ልጅ እንዳያጠፋ እንጂ እያጠፋም ቢሆን እንዲሠራ ማን ይፈቅድለታል?፡፡ ትምህርት ቤቱም ቢሆን የሚያስጠነቅቀን እንድንጠቀምበት ሳይሆን እንዳናበላሸው ነው፡፡ እኛም የምንጨነቀው ላለማበላሸት እንጂ ለማንበብ አልነበረም፡፡
ይህንን ሁሉ ያመጣው የኢኮኖሚና የአስተሳሰብ ድህነት ነው፡፡ ሀገሪቱ ለመጽሐፍ የምመድበው በቂ በጀት የለኝም፤ ስለዚህ ያላችሁን አብቃቁ ትላለች፡፡ [እዚህ ላይ አንድ የመንገድ ላይ ትዝታ ላውጋችሁ፡፡ አራት ልጆች ወደ አንድ ከተማ ለሥራ ጉዳይ ሲሄዱ አንድ የምሳ መመገቢያ ከተማ ይደርሳሉ፡፡ እዚያ ከተማ ሲደርሱ ከግራ ከቀኝ የመጡት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ምግብ ቤቶችን ሁሉ ከአፍ እስከ ገደብ ጢም አድርገዋቸዋል፡፡
ያልተጨናነቀ ቦታ ሲፈልጉ ሁለት ለግላጋ ሕፃናት ቦታ እናሳያችሁ ብለው በተለምዶ «ማዘር ቤት» የሚባል ቤት ውስጥ ወሰዷቸው፡፡ እናት ምግብ ሠሪ፣ ልጅ አስተናጋጅ ሆነው አገኟቸው፡፡ ምግብ አዘዙ፡፡ አንዱ ቀይ ወጥ፣ አንዱ አልጫ፣ አንዱ ቅቅል፣ አንዱ ደግሞ ጥብስ፡፡ ልጅቱ ትእዛዝ ተቀብላ ከመሄዷ እናትዬዋ ወገባቸውን በመቀነት ታጥቀው መጡ፡፡ «እኔ አበራሽ አራት ዓይነት ወጥ አልሠራም፤ ተስማሙና አንድ አድርጋችሁ እዘዙ» አሏቸው፡፡
ልጆቹም እየሳቁም፣ እየተገረሙም በቀይ ወጡ ጸኑ፡፡ ጥቂት ጊዜ ወስደው በትልቅ ትሪ ከአራት እንጀራ ጋር አመጡላቸው፡፡ በወጣት አበላል ላፍ ላፍ አደረጉና ቀና ሲሉ እንጀራው ከወጡ በልጦ አገኙት፡፡ «ወጥ አስጨምሪልን» አሏት ልጅቱን፡፡ ገባች ወደ ጓዳ፡፡ አሁንም እናት ወገባቸውን ይዘው መጡ፡፡ አሁን ቀጥ ብለው ወደ ትሪው ነው የሄዱት፡፡ እጃቸውን ሰደዱና በወጥ የራሰውን እንጀራ በጣታቸው እየፈተፈቱ «ምነው አበራሽ፣ ይሄ ወጥ አይደለም? የነካካውን ብሉ፡፡ ወጥ የሚጣፍጠው ሲያብቃቁት ነው» እያሉ ፈተፈቱላቸው፡፡ ወይ እጅ መታጠብ፤ ሦስተኛ ክፍል ቀረ፡፡]
ይሄው መመርያ ነበር የሀገሪቱም መመርያ «አብቃቁት» የሚል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የአስተሳሰብ ድህነት የፈጠረብን ነው፡፡ ወላጆችም፣ መምህራኑም፣ የትምህርት አስተዳ ደሩም እጥረቱን እንደ አርባ ቀን ዕድል ተቀብለውት ያለ መፍትሔ ይቀመጣሉ፡፡ የመጽሐፍ ርዳታ ለመሰ ብሰብ፣ የቀድሞ ተማሪዎችን አስተባብሮ አብያተ መጻሕፍትን ለማጠናከር፣ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድ ተልሞ የመጻሕፍትን ቁጥር ለመጨመር ሲጥር የሚታይ አልነበረም፡፡
በተለይማ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ 2000 ዓምን ኮርስ 1965 ዓም መጽሐፍ መማር እንደ ነውር አይታይም ነበር፡፡ በውጭ ሀገር ካሉት መጽሐፍ ተርፏቸው መጣያ ካጡት ተቋማት ጋር በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ነበሩ፡፡ ግን ምን ያደርጋል ውጭ ሀገር ተምረው የሚመጡት የዩኒቨርሲቲ አመራሮችና መምህራን የስኮላር ሺፑን ያህል አላሳሰባቸውም፡፡ አንዳንዱ የኮሌጅ ቤተ መጻሕፍት «ቤተ መዛግብት» እስከመሆን የደረሰውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ ለዐቅመ ኮሌጅ ያልደረሱ ተማሪዎች ደግሞ «በውሻ እራት ውሻ ቆሞባት» እንደ ሚባለው ያቺኑ ያለችውን መጽሐፍ እየገነጠሉና እየሰረቁ፣ በላይዋ ላይ እየጻፉና እያሠመሩ ደብዛዋን ያጠፏታል፡፡
ኮሌጆቻችን ከሕዝብ ርቀው፣ ንጽሕ ጠብቀው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ምሁራኑም «ዝጉሐውያን ባሕታውያን» ናቸው፡፡ ኮሌጆቹን ሕዝቡ ምን እንደሚሠሩና ምን እንደሚጠቅሙም እንዲያውቅ አይደረግም፡፡ በመን ግሥት በጀት እንጂ በሕዝብ ድጋፍ አይቋቋሙም፡፡ ሕዝቡ የኔ ናቸው፡፡ ልደግፋቸው ይገባል እንዲላቸው አይፈልጉም፡፡ አንድም ቀን ከአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ጋር ተዋውቀው አያውቁም፡፡ በዚህም ምክንያት ከሕዝብ በስጦታ፣ በውርስ፣ በበጀት ድጋፍ፣ በርዳታ፣ በገጽታ ግንባታና በአመራር ሊያገኙ የሚችሉትን ድጋፍ አላገኙም፡፡
ምሁራኑም ለአካዳሚያዊ ክበቡ እንጂ ለሕዝብ የተገለጡ አይደሉም፡፡ የሚጽፉት በእንግሊዝኛ፣ የሚያሳ ትሙት በጆርናሎች፣ የሚከራከሩት በክፍል ውስጥ በመሆኑ ሕዝቡ በዙርያቸው እንጂ አብሯቸው አይደ ለም፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ ምሁር ሞተ ከሚሉት አንድ የዕድር ዳኛ ሞተ ቢሉት ሕዝቡ አብዝቶ ያዝናል፡፡ የማን ሞት እንደሚጎዳው የሚያውቀው እርሱ ነውና፡፡
እንዲህ ሆነን ግን እስከ መቼ? መቼም ሮም በአንድ ቀን አልተሠራችምና ችግሩን ሁሉ በአንድ ጊዜ ላንቀርፈው እንችል ይሆናል፡፡ ግን ለመቅረፍ መጀመር አለብን፡፡ « ! ጨለማን ከመውቀስ አንድ ሻማ ማብራት ይበልጣል» እንዳለው ኮንፊሽየስ ያልሆነበትን ምክንያት ብቻ እያነሣን ከምናትት እስኪ መለወጡን ከራሳችን እንጀምረው፡፡ በተለይ በውጭ ካለው ዳያስጶራ፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ በየትምህርት ቤቱና ኮሌጆቹ ዓመቱ ሲጠናቀቅ መጻሕፍቱ ይቀየራሉ፡፡ አዳዲስ እትሞች ይመጣሉ፡፡ ያለፉት እትሞች ወይ በርካሽ ይሸጣሉ ያለበለዚያም ደግሞ በነጻ ይሰጣሉ፤ ከባሰም ወደ «ድጌ ቤት» (Recycle house) ይላካሉ፡፡
እናም እስኪ ምናለበት የዕውቀት ርዳታ ለሀገራችን ብንጀምር፡፡ በምን መንገድ አትሉኝም፡፡ በየአካባቢያችን ከሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች በርካሽ የምናገኛቸውን መጻሕፍት እንሰብስብ፡፡ በአንዳንድ ኮሌጆች እንዲያውም አፍሪካውያን ተማሪዎች መግለጫና ካርቶን እያስቀመጡ በነጻ ከሚሰጡ ተማሪዎች ሲሰበስቡ አይቻለሁ፡፡ በምዕራቡ ዓለም አንድን ነገር ለብዙ ጊዜ ማስቀመጥ እዳው የቦታ ጥበት ነውና በቶሎ እንዲ ወገድ ይመከራል፡፡ እኛም ይህንን ባህል እንጠቀም፡፡ መጻሕፍቱን እንሰበስብ፡፡
እያንዳንዱ የውጭ ነዋሪም ለራሱ ቃል ይግባ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በሄደ ቁጥር ቢያንስ ሦስት መጽሐፍ ይዞ ለመሄድና በአካባቢው ለሚገኝ በመጽሐፉ ለመጠቀም ለሚችል ትምህርት ቤት ለመስጠት፡፡ ሌላው ቢቀር በአካባቢያችን ለሚማሩ ወጣቶች እንስጣቸው፡፡ በሕዝብ ቤተ መጻሕፍት እናስቀምጣቸው፡፡ ለሠፈራችን ጎበዝ ተማሪዎች እንሸልማቸው፡፡ አያሌ ተማሪዎችን አስፈትኖ መልካም ውጤት ላመጣ ትምህርት ቤት ዳያስጶራው መጻሕፍት ይሸልም፡፡
ቢያንስ በየዓመቱ ወደ አሥር የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ከውጭ ይመጣሉ፡፡ እያንዳን ዳቸው ሦስት መጽሐፍ ቢይዙ፤ በዓመት ሠላሳ መጽሐፍ ወደ ሀገር ይገባል ማለት ነው፡፡ በዐሥር ዓመት ስናስበው ደግሞ 300,000 መጽሐፍ ይሆናል፡፡ ከዚህ በላይ ምን የዕውቀት ርዳታ አለ፡ ሀገሪቱስ ይህንን ያህል በጀት ለመጽሐፍ መመደብ ትችላለች ብላችሁ ነው?
ትምህርት ቤቶች ላይ ካልሠራን ስለ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት፣ ስለ ሥልጣኔና ዕድገት ማውራቱ ቅዠት ይሆናል፡፡ ዕውቀት አጠር ሆኖ ያደገን ትውልድ ሥልጣኔ አጠር አትሁን ማለት ያልተወለደን ልጅ እንደማሳደግ ይቆጠራል፡፡
እስኪ በቤታችሁ ግደግዳ ላይ፣ ወይም በፍሪጃችሁ በር ላይ «ዕውቀት እንረዳለን» ብላችሁ ለጥፉ፡፡ ለሚጠይቋችሁ አስረዱ፡፡ በፌስ ቡካችሁ ላይ ለጥፉ፣ በቢሯችሁ ጠረጲዛ ላይ ጻፉ፡፡ በመኪኖቻችሁ ላይ እንደ ጌጥ ስቀሉ፡፡ ሀገር የሚለወጠው በዕውቀት ነው፡፡ ለውጥ የሚጀመረው ደግሞ ከትምህርት ቤት፡፡
እስኪ ቃል እንግባ፡፡
ሽሮ እናስመጣለን፤ በርበሬ እናስልካለን፣ እኛም በተራችን ዕውቀት እንረዳለን፡፡
ኦክላንድ፣ ካሊፎርንያ

26 comments:

 1. betam kidus hasab
  thank you

  ReplyDelete
 2. ቢያንስ በየዓመቱ ወደ አሥር ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ከውጭ ይመጣሉ፡፡ እያንዳን ዳቸው ሦስት መጽሐፍ ቢይዙ፤ በዓመት ሠላሳ ሺ መጽሐፍ ወደ ሀገር ይገባል ማለት ነው፡፡ በዐሥር ዓመት ስናስበው ደግሞ 300,000 መጽሐፍ ይሆናል፡፡ ከዚህ በላይ ምን የዕውቀት ርዳታ አለ፡ ሀገሪቱስ ይህንን ያህል በጀት ለመጽሐፍ መመደብ ትችላለች ብላችሁ ነው?
  Mamush,MN

  ReplyDelete
  Replies
  1. Is there any one who need books, I will be very happy to give away, I am not comfortable to throw away them.

   Delete
 3. good article,
  dani me i have started before two years, and i advice to do the same.let all this blog readers be examplary

  ReplyDelete
 4. I have nothing to say with what u r writing! Simply,God bless you!!!! You are writing what is inside my mind but I couldnot express it like this! I sent 20 books in average to the high school I used to learn-I will do it in a more organized way! Your title has its own power!
  keep on your writing.Really,I am addicted to your blog. Even if I am tired, I can't sleep unless I check my bank account and your blog!!!

  ReplyDelete
 5. "በአሜሪካና በአውሮፓ በየትምህርት ቤቱና ኮሌጆቹ ዓመቱ ሲጠናቀቅ መጻሕፍቱ ይቀየራሉ፡፡ አዳዲስ እትሞች ይመጣሉ፡፡ ያለፉት እትሞች ወይ በርካሽ ይሸጣሉ ያለበለዚያም ደግሞ በነጻ ይሰጣሉ፤ ከባሰም ወደ «ድጌ ቤት» (Recycle house) ይላካሉ፡፡"

  ዳኒ ምክርህ በጣም ጥሩ ነበር ነገር ግን ችግር አለ:: ባሁኑ ሰአት በአውሮፓ የሶስተኛ ዲግሪዬን በመስራት ላይ ነው ያለሁት:: ባለሁበት ዩኒቨርሲቲ በጣም ብዙ ጊዜ መጻህፍት ሳይሆን ሌሎች ለላቦራቶሪ የሚያገለግሉ በጥሩ status ላይ ያሉ መሳርያዎችን ያስወግዳሉ:: ከማስወገዳቸው በፊት ግን የሚፈልግ ካለ ተብሎ በኢሜይላችን ያሳውቁናል:: በጣም ብዙ መሳሪያዎች ኢትዮጵያ ለምሰራበት ዩኒቨርሲቲ ለመውሰድ እየተመኘሁ ሳልወስድ ትቻለሁ ምክንያቱም በጣም ብዙ ብር ከፍዬ ኢትዮጵያ ማድረስ ብችል እንኳን ኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የሚከፈለውን የጉምሩክ ቀረጥ አልችለውም:: ለዩኒቨርሲቲ በርዳታ የመጣ ነው ብልም ማንም አያምነኝም ከዚህ በፊት አጋጥሞኛልና:: ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ይልቅ አንድ የኔ ቢጤ ፈረንጅ የሚናገረው ነገር ይታመናል::
  ከዚህ በፊት ካጋጠመኝ አንዱን ላጫውትህ:- ላፕቶፕ ማለት በጣም ተራና ማንኛውም ሰው እንደ ሞባል ስልክ ሊይዘው የሚችለው ነገር ነው:: የዛሬ አመት ለመስክ ስራ ኢትዮጵያ ሄጄ እያለሁ የራሴን የምጠቀምበትን የሰራሁት ስራ ሁሉ ያለበትን ላፕቶፕ ቀረጥ ካልከፈልክ ብለውኝ በጣም ለረጅም ሰአት አየር መንገድ ውስጥ ተጉላልቻለሁ:: በጣም ያፈርኩት ግን ከኔ በኋላ የነበረ ፈረንጅ ምንም ሳይጠይቁት አሳለፉት:: ለመሆኑ አበሻ ላፕቶፕ አያስፈልገውም ያለው ማነው? አልኳቸው:: እሱን ለምን አሳለፋችሁት አልኳቸው? “እሱ ይዞ ስለሚመለስ ነው አሉኝ”:: ያሳለፋችሁት ነጭ ስለሆነ እንጂ ነዋሪነቱ ኢትዮጵያ ይሁን የት ይሁን የምታውቁት ነገር የለም አልኳቸው:: መታውቂያውን አላያችሁም:: እዚህ ላሉት ለሚያውቃቸው ኢትዮጵያውያን ትቶላቸው ይመልስ አይመለስ የምታውቁት ነገር የለም አልኳቸው:: ለማንኛውም እኔም ላፕቶፑ የራሴ እንደሆነና የምሰራበት እንደሆነ ወደ ውጭ ይዤው እንደምመለስ ነግሬያችኋለሁ አላመናችሁኝም:: ከፈለጋችሁ ተመላሽ መሆኔን ተመልከቱ ብዬ ፈረንጁ ምንም ሳይናገር አሳልፈውት እኔ ግን ተመላሽ መሆኔን ተናግሬም ባለመታምኔ በጣም እያዘንኩ ፓስፖርቴን (visa) አሳይቼ ላፕቶፔን አሳለፍኩ::
  መጻፊያ ወረቄቴን (ላፕቶፕ) አናሳልፍም ያሉኝ ሌሎች መሳርያዎች ይዤ ብመጣ ማን አምኖ ያሳልፈኛል? ለራሴ ንግድ ልጀምር ያሰብኩ እንጂ ለዩኒቨርሲቲ ወይም ላገሬ አስቤ እንዳመጣሁ የሚገምት የለም:: እዛ አካባቢ የሚሰሩ ሰዎች እራሳቸውን ላገር የሚያስቡ ሌላው ግን አጭበርባሪና ለግሉ ብቻ የሚያስብ አድርገው ይገምታሉ:: እንደ ዳንኤል ክብረት ያሉ ላገራቸው የሚያስቡ በጣም ብዙ ሚሊየን ሰዎች እንዳሉ አያውቁም:: እኔ እንደውም ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ እያለሁ ያጋጠመኝ ነገር ነበር (በኋላ እጽፈዋለሁ) ያን ሁሉ ረስቼ ለመያዝ የሚመቹ በጣም ቀላል የሆኑ ግን ለመግዛት በጣም ውድ የሆኑ ሁለት መሳርያዎች እዚህ ያለሁበት ሀገር ያለው ዩኒቨርሲቲ ሲጥል ወስጄ እቤቴ አስቀምጬ ነበር:: ኢትዮጵያ ለመሄድ ስነሳ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ እያለሁ ጉምሩክ የሰራኝ ስራ ትዝ ብሎኝ መሳርያዎቹን ትቻቸው ሄድኩኝ:: ቀረጥ የማያስከፍሉ ከሆነ ሌላም ጊዜ መላክ ይቻላልና:: የፈራሁት አልቀረም በጣም ተራውን ነገርና በፍጹም ቀረጥ ሊጠየቅበት የማይገባውን ነገር ጠየቁኝ::
  ከዚህ በፊት ሃገር ቤት (ኢትዮጵያ) እያለሁ:: ዩኒቨርሲቲያችንን የጎበኘች ፕሮፌሰር ነበረች:: ቤተሙከራችንን (ላቦራቶሪያችንን) አስጎብኝቻት ነበረና ወዳገሯ ከተመለሰች በኋላ የሷ ቤተሙከራ ወስጥ ትርፍ ማይክሮስኮፕ ስለነበራት አንዱን ለኛ ላቦራቶሪ መላኪያውን ችላ በኔ ስም ላከችልን:: በፖስታ ቤት በኩል ነበር የመጣው:: አዲስ አበባ ዋናው ፖስታ ሄጄ እንድወስድ የሚገልጽ ወረቅት መጣልኝ:: 2000 ብር ቀረጥ መክፈል እንዳለብኝ ተነገረኝ:: እንዴት እንደተላክና ለዩኒቨርሲቲው እርዳታ እንደሆነ አስረዳሁ:: ቢሆንም ባንተ ስም ስለመጣ መክፈል አለብህ ተባልኩ:: ከዩኒቨርሲቲው ላጽፍ ብላቸውም አይሆንም አሉኝ:: አሮጌ መሆኑን በደንብ እንዲያዩት አድርጌ 200 ብር ከፍዬ ተቀበልኩ:: አሁንም ከዚህ ያለሁበት ዩኒቨርሲቲ የሚጥላቸውን ሰብስቤ ባመጣ ከዛ ያነሰ አያጋጥመኝም:: ከዚህ ላገሬ ልውሰድ ብዬ ለአውሮፕላን በጣም ብዙ ብር ከፍዬ ባመጣና እዛ እንዲህ አይነት ችግር ቢገጥመኝ ጭንቅላቴን ያመኛል:: ስለዚህ ያለኝ አማራጭ በጣም በጥሩ status ላይ ያሉ መሳርያዎችን ሲጥሏቸው እያየሁ እንደ ሃብታም ሃገር ልጅ ዝም ማለት ነው የሚያዋጣኝ::

  H.Mariam

  ReplyDelete
  Replies
  1. Plssssssssssss! Let's take action now! This is the time. Let's start from creating facebook group! good idea, let's unit and do what we can.

   Delete
  2. Good job friend. God bless you. but never give up ! "ketagesut hulum yalefal" lebego new".
   i really appreciet you.
   from sweden

   Delete
 6. Here in US, you buy a book with hundreds of dollars. It is funny. I am used to take care of books so I always worry about books when I read. At the end of the term my book is always new to be recycled or thrown away, or if they are still in use to be sold in cheap price.

  ReplyDelete
 7. "ወደ ኢትዮጵያ በሄደ ቁጥር ቢያንስ ሦስት መጽሐፍ ይዞ ለመሄድና በአካባቢው ለሚገኝ በመጽሐፉ ለመጠቀም ለሚችል ትምህርት ቤት ለመስጠት፡፡ ሌላው ቢቀር በአካባቢያችን ለሚማሩ ወጣቶች እንስጣቸው፡፡ በሕዝብ ቤተ መጻሕፍት እናስቀምጣቸው፡፡ ለሠፈራችን ጎበዝ ተማሪዎች እንሸልማቸው፡፡"
  ውድ ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል ቃለ ሕይወት ያሰማልን እይታዎችህ ድንቅ ናችው መቼም:: በተለይ በዚህ በአሜሪካን ያሉ የትምሕርት መጽሕፍት ለመረዳት ግልጽ እና ቀላል መሆናቸውን እኔም እየተማርኩባቸው በመሆኔ መመስከር እችላለው:: ወገን ለወገን ነውና እውነት ነው ቃል እንግባ!"ሽሮ እናስመጣለን፤ በርበሬ እናስልካለን፣ እኛም በተራችን ዕውቀት እንረዳለን፡፡"

  ከሳንፍራንሲስኮ

  ReplyDelete
 8. ዳኒ ግሩም ሃሳብ ነው ይህ ሁሉም ሰው ሊያደርገው የሚገባ የተቀደሰ ሃሳብ

  ከዚሁ ጋር ግን በተያያዝነት በአሁኑ ወቅት በ ሶፍት ኮፒ መጽሐፍትም ስለሚገኙ እሱንም ታሳቢ ማድረጉ መልካም ነው ኮምፒዩተር ያለው በሶፍት ኮፒ እንዲጠቀም ለሌለው ደግሞ ፕሪንት እድርጎ እንዲተቀምበት ማድረግ ይቻላል እና ይህንንንም ሃሳብ ብታካትተው መልካም ነው እኔ ለምሳሌ ቢየንስ ወደ 300 የሚጠጉ መጽሃፍትን ሰብስቤ ወደ አንድ ዩኒቨርስቲ ልኬ ነበር

  ከበደ

  ReplyDelete
 9. "ዕውቀት አጠር ሆኖ ያደገን ትውልድ ሥልጣኔ አጠር አትሁን ማለት ያልተወለደን ልጅ እንደማሳደግ ይቆጠራል፡፡"

  ReplyDelete
 10. ሀይለ ሚካኤልJune 14, 2012 at 10:33 AM

  ለተግባራዊ ምላሽ ተነስቻለሁ

  ReplyDelete
 11. YOU SEE OUR GOVERNMENT EXPENDS MUCH MONEY TO SECURITY AND JAMMING NOT FOR HEALTH AND EDUCATION.SO THIS A RESPONSIBILITY OF GVT.

  ReplyDelete
 12. እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
  ይገርማል እኔም በአንዱ ዩኒቨረሲቲ የድኅረ ምረቃ ተማሪ ነኝ፡ ግን ለአንድ የትምህርት አይነት ሦስት ብቻ መርጃ መጻሕፍት ኖሮት አጋጠመኝ። ለ lab አቃዎች ጊዜዉ አስኪደርስ መጻሕፍቱ ይግቡልን።

  ReplyDelete
 13. dani it is great idea we will do it with my friends. god bless you!

  ReplyDelete
 14. ውድ ወንድሜ፤ለማንቂያ ድውልህ አመሰግናለሁ። የሰላ አእምሮህን አምላክ ይጠብቅ። ልምድን ማካፈል ይጠቅማል ብዬ ስላሰብሁ፤ ትንሽ ስላደረግሁት መዘርዘር ወደድሁ። እኔ አንተው በገለጥበት መንገድ ያደግሁ፤ ችግሩን በተግባር ቀምሸ ክፍለ የተማርሁ ሰው ነኝ። የማይረሳኝ፤11ኛ ክፍል ኬሚስትሪ መጽሐፍ በት/ቤቱ ሁለት ነበር። አንዱን አስተማሪው ይጠቀማል አንደኛውን እኛ በተራ። ይሄ ችግር አእምሮዬ ላይ ስላለ-የሁለተኛ ዲግሪ ለመማር ውጭ አገር እድል ሲያጋጥመኝ-አሮጌ መጽሐፍት(ማንኛውም የትምህርት አይነት) በርካሽ ሰበሰብሁ። ወደ ሃገሬ ስመለስ፤ አዲስ ለተቋቋመ ዩኒቨርስቲ ላይ በራሪ አደልሁ። ለትራንፓርት ወጭ ባወጣም፤ ከሚሰጡት ጥቅም አኳያ ምንም ማለት አልነበረም። አሁን ደግሞ እግዚአብሔር ፈቅዱ የሶስተኛ ዲግሪ ለመስራት እድሉን አገኘሁ። ሁኔታው ተቀይሯል። እድሜ ለቴክኖሎጂ፤ ብዙ ነገር ዲጂታል ሆኗል! ከእኔ የሚጠበቀው፤በእየ ትምህርት አይነቱ ፎልደር መክፈት፤ የተለያዬ አጋጣሚዎችን በመጠቀም መጽሐፍት ሳገን--በከፈትሁት ውስጥ ማጠራቀም!! እንዳንድ ሕገወጥ ዌብሳይቶች በሚሰጡት ነጻ አግልግሎት በመጠቀም እንዲሁ አውራጃለሁ። ይሄን ያደረግሁት-በሃገራችን ፒኤችዲ ትምህርት ቢጀመርም፤ ስለ መጽሐፍት ሲነሳ-ለጀሮ ይሰቀጥጣል። ነገሩ ሁሉ የጨበጣ ነው። እናም ወደ ፊልድ ስሄድ-ቢያንስ ለማውቃቸው ጓደኞቼ አድያቸው ተመልሻለሁ። እኔ አሁንም እያጠራቀምሁ ነው። ሌሎቻችሁም-ቢያንስ ለምታውቋቸውና ላቅራቢያችሁ እንዲሁ አድርጉ። ወዳቼ አቤል እንደሚመለው „“ፊዝ ቡክን“ ቀነስ አድርገን፤ ቁም ነገር እንስራ።

  ReplyDelete
 15. ቤተ መጻሕፍቱ የመጻሕፍትና ቁሳቁስ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጀ፡፡
  ሰኔ 04 ቀን 2004 ዓ.ም
  በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖአምላክ
  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን ቤተ መጻሕፍት እየሰጠ ያለውን አገልግሎት አጠናክሮ ለመቀጠል ይረዳው ዘንድ የመጻሐፍትና ቁሳቁስ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጀ፡፡

  በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ሥር የሚገኘው ቤተመጻሕፍት ፡-“ስትመጣ …በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ” (2ኛ ጢሞ.4÷13) በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው በዚሁ የመጻሐፍትና ቁሳቁስ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር፡-

  • ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ምክርና ትምህርት የሚሰጡ መጻሕፍት፣ መዛግብት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦችን፣ የአስኳላ (አካዳሚካል) መጻሕፍት፣
  • ጥናታዊ ጹሑፎችን እንዲሁም
  • ቤተመጻሕፍቱን ለማደራጀት የሚያግዙ ቁሳቁሶችን በመስጠት ምእመናን የበኩላቸውን እገዛ እንዲያበረክቱ ጠይቋል፡፡

  ‹‹ቤተመጽሐፍቱ ቅዳሜን ጨምሮ በሌሎቹም መደበኛ የሥራ ቀናት ለአንባቢያን አገልግሎት እየሰጠ ነው፤›› ያሉት የቤተ መጻሕፍት አገልጋይ አቶ ደጀኔ ፈጠነ፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ አንባቢያን በቤተ መጻሕፍቱ እየተጠቀሙ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

  ስለመርሐ ግብሩ ዓላማ የተጠየቁት አቶ ደጀኔ “ ቤተ መጻሕፍቱን በመጻሕፍት ዓይነትና ብዛት ክምችቱን ማሳደግ÷ አገልግሎቱን በኮምፒውተር የታገዘ÷ አስፈላጊ በሆኑ የመገልገያ መሣሪያዎች የተሟላ፤ ለተገልጋዮችም ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት የመርሐ ግብሩ ዓላማ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

  ለለጋሾች በቀላሉ መጻሕፍትን ገዝተው ማበርከት ይችሉ ዘንድ በማኅበሩ ሕንፃ ከተዘጋጀው ጊዜያዊ ሽያጭ በተጨማሪ አዲስ አበባ በሚገኙ የማኅበሩ ሱቁች የሽያጭና የመረከብ አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

  ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 17 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ በሚቆየዉ መርሐ ግብር በርካታ መጻሕፍት፣መጽሔቶችና ለቤተመጻሐፍት አገልግሎት የሚረዱ ኮምፒውተሮች፣ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ መደርደሪያዎችና ሌሎች አስፈላጊ መገልገያዎችን ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡

  ReplyDelete
 16. ሰላም ዳኔ: የአውሮፓው ተማሪ: እኔና ልጀ ምሾ ያወጣነለትን ነገር ቀሰቀሰብኝ:: ጉዳዩ እንዲህ ነው:: ልጀ የህክምና ክፍል ተማሪ ነው:: ከሜማርበት ዩንቨርስቴ በኩል አንድዋ ሰለ ኢትዩጵያ የመጽሐፍ እጥረት በሰፊው አትታ ትጽፋለች:: ችግር አያውቀው ልጀም ከአለበት ዩንቨርስቴይ በመሆን ስልክ ይደውልልኛል:: ያው እኔ የማውቀው እሱ ግን የማያውቀውን ችግር በመገረም አወራልኝ:: እኔም አዎ እናት አገር ኢትዩጵያ ከምግብ ባሻገር የመጽሐፍ ችግርም አለባት ስለዚህ ምን አስበኸል ሰል በጥያቄ ንግግሪን አሳረኩት:: ወጣቱ ልጀም ግድ የለሽም እኔ ከናንተ የምፈልገው መጽሐፍቱን ሰብስቤ የማስቀምጥበት ክፍል ብቻ ነው:: በዚህ ከተባበራችሁኝ የአገሪን የመጽሐፍ ችግር እንዲወገድ ጓደኞቸን አሰባስቤ ተግቸ እሰራለሁ አለኝ:: ችግሩ የት እንደሆነ እኒና አባቱ ቤገባንም አገሪ በሜለው ሰሜት እንዲንቀሳቀስ ስለፈለግን የመኪና ማቆሜያ ጋራጅ እንደምንለቅለ ት ቃል ገባነለት :: ለግዜው በዜህ ትብብራችን አመስግኖን ተለያየን ማለት ነው:: መቸስ እንደምታውቁትእናት በልጅዋ እንቅልፍ የላትም ይባል የል:: ልጀ መጽሐፎን ከሰበሰበ በኋላ የሜያጋጥመው ችግር ከመፈጠሩ በፊት እኔው ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ወሰንኩ:: የመጀመሪያ ሙከራየ ዋሽንግተን ዲሴ ካለው የኢትዩጵያ ኢምፖሲ መደወል ነበር:: መልሱ መጓጓዣ ሆነ ቀረጥ መክፈል አይቀሪ መሆኑ ተነገረኝ:: ኢትዩጵያ አዲስ አበባ ዩንቨርስቴን አስጠየኩ ትራንስፖርት ክፈሉ የሜል መልስ መጣ:: ሌላም መጽሐፍ በማከፋፈል የሜታወቅ ድርጅት ጠየኩ መልሱ አጥጋቢ አልነበረም :: በኔ በኩል ውጢት የለለው ድካም ብቻ ሆነ ማለት ነው:: ልጀም መጽሐፎን በሰበሰበው በአመቱ በጣም እያዘነ ሰለ አገሪቱ የጉምርክ ችግርና የትራንስፖርት ውድነት ያወራኝ ጀመር:: ጭራሽ መኪና ይመጣል ጠራርጐ ይጥልልሻል:: ይቅርታ ቦታ በመያዙ በማለት በሀዘኔታ ፊቱ ተቀያየረ:: ይህችን ቀን መቸም አልረሳት:: ወደ ነጥቡ ልመለሰና ለዳኔ መልስ ልሰጥ እፈልጋለሁ:: ኢትዩጵያ ተቀባይ ካለ : የተፈለገው መጽሐፍ አይነትና ብዛት ቤነገረን ለመተባበር እኔና ልጀ አሁንም ዝግጁ ነን:: ግን የአውሮፓው ተማሪ እንዳለህ ኢትዩጵያ ያለውን ውጣ ወረድ ማን የሜጋፏው ይገኛል?? መልሱን ከአዲስ አበባ አንባቢወች እንጠብቃለን:: በመሰረተ ሀሣቡ ግን ከዳኔ ጋር እስማማለሁ::
  የድንግል ልጅ ኢትዩጵያን ይጠብቅ አሜን!

  ReplyDelete
 17. This is a marvelous idea that should be supported and all Ethiopians in the Diaspora should contribute what it is possible. To give an information who is interested, There is a society based in Ethiopia, Named “The Ethiopian Knowledge and Technology Transfer Society (EKTTS)”. This society is established by far sited senior Ethiopians and have many active members. Please visit it’s website www.ektts.org.et
  Ethiopian Knowledge and Technology Transfer Society (EKTTS) is a non-profit organization dedicated to mobilizing educational resources, including books and computers, to support the development of Ethiopia. Working with Ethiopians in the Diaspora and international donor organizations, EKTTS has brought more than 1.5 million books and 4,200 computers valued at more than USD 44.3 million to millions of students all throughout Ethiopia.
  The idea was initiated by two old-time friends, Berhane Abate, a civil engineer and Syioum Gebeyehou, an electrical engineer and Ethiopian American. EKTTS was first formed in the State of California (USA) in on July 2001 as a Nonprofit Public Benefit Corporation Law for charitable purposes within the meaning of Section 501 (C)(3) of the Internal Revenue Code. It was soon re-established in February 26, 2002 in Addis Ababa as a non-profit local NGO under as an indigenous NGO under the Provision of Civil Code of Ethiopia of 1960 and the Association Registration Regulations Legal Notice # 321 of 1966.
  The objective was to organize and coordinate knowledge and technology support from national and international organizations overseas in support of its development endeavors. This was a time when the new EPRDF Government launched a National Rehabilitation and Reconstruction program to recover from the economic crisis following the 17 years of military regime.

  EKTTS' mission is to mobilize and coordinate support from overseas, local organizations, and individuals for transferring knowledge and technology to bring about meaningful and sizable impact to the economic development of Ethiopia.

  EKTTS’ primary activity is in coordinating the logistics of import, transportation and rural distribution of donated educational materials. Through the support of its donors and cost-recovery fees charged to recipients, EKTTS provides access to critical educational materials – ranging from elementary mathematics to medical textbooks – to students who would not otherwise have such resources.
  EKTTS is excited about it’s programs and the impact the society is making in Ethiopian communities. http://www.ektts.org.et and contact us to find out how you can contribute.

  ReplyDelete
 18. Denke hasab newe!!!!!!!

  ReplyDelete
 19. „“ፊዝ ቡክን“ ቀነስ አድርገን፤ ቁም ነገር እንስራ።

  ReplyDelete
 20. Dani be60 yeAmerica cents yeAccounting, yeComputer Science ena Fiction books bebizat yemishetibet bet DC ena Maryland megatemiya lay aychalew. Endalkewum 2 ena 3 books wede Ager bet sinhed binwesd tiru neger new. Bitasebibetina mesmer biyz betam kelal neger new. EGZIHABHER yirdan.

  ReplyDelete
 21. let us promise to start it- in what good I do today list, I hope everybody have this list, written by own
  Sharing negn

  ReplyDelete
 22. Melkam hasab newu. Be gileseb dereja yemiseraw bizum aykebidim. Mewakirawi gudyoch gin astaway halafiwochin yifeligalu yemeslegnal.
  Feterai kantega yihun.

  ReplyDelete