ሰኞ ሰኔ አሥራ አንድ ቀን 2004 ዓም ከቀኑ በሰባት ሰዓት ላይ ከካሊፎርኒያዋ ኦክላንድ ወደ ሳንታ ክሩዝ በመጓዝ ላይ እንገኛለን፡፡ አብረውኝ አስጎብኚዎቼ ኢሳይያስና ቅዱስ አሉ፡፡ ዓለማችን መቼም ዕንቆቅልሻቸው ያልተፈታ አስገራሚ ድንቅ ነገሮች አሏት፡፡ ልክ እንደ ቤርሙዳ ትሪያንግል ከመላምት በስተቀር እቅጩን ነገር ሊናገሩላቸው የማይቻሉ፡፡ ዛሬም የምንጓዘው አሜሪካኖቹ «ብታምኑም ባታምኑ ም» በሚለው የቴሌቭዥን ፕሮግራማቸው ከሚያቀርቧቸው የዓለማችን ድንቅ ነገሮችና ቦታዎች አንዱን ለማየት ነው፡፡
የሀገሬ ሰው ላሊበላ ሲሄድ
እንግዲህ ዲያብሎስ ምን ትበላ?
ትንሹም ትልቁም ሄደ ላሊበላ
የሚለው መዝሙር አሁን ነው ትዝ ያለኝ፡፡ እኔም በተራዬ
እንግዲህ ፊዚክስ ምን ትመልስ
ትንሹም ትልቁም ሄደ ሳንታ ክሩዝ
የሚል የፎገራ ግጥም አማረኝ፡፡