Tuesday, May 22, 2012

ርኅራኄያዊ ግድያ

ባለፈው ጊዜ ዱባይ እያለሁ ነው ይህንን ታሪክ አንዲት እኅት የነገረችኝ፡፡ ከአራት ዓመታት በላይ እዚያ ሠርታለች፡፡ ያገኘችውን ወደ ሀገር ቤት ትልካለች፡፡ ልብሱ፣ የቤት ዕቃው፣ ገንዘቡ፣ ጌጡ፣ ሽቱው አይቀራትም፡፡ መላክ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከጓደኞቿ ጋር ተባብራ ካርጎ ትጭናለች፡፡
እናቷ ደውለው «ከጎረቤትኮ እገሌ ታምሞ መታከሚያ አጣ» ይሏታል ተልካለች፡፡ ወንድሟ «እንዲህ ላደርግ ነበር ገንዘብ አጣሁ» ይላል ትልካለች፡፡ «እገሌ የተባለ ዘመድሽ ምነው ረሳችኝ ብሎሻል» ትባላለች ትልካለች፡፡ አንዳንዴም «እንዴው ለዚህ ቤተ ክርስቲያን ቃል ገብተን ነበረ» ይሏታል ትልካለች፡፡ ብቻ ከራሷ በስተቀር ሁሉንም ልካለች፡፡
የኤምሬትስ ስደት ሲሞላ ሲጎድል ነው፡፡ ቪዛዋ ይሠረዝባታል፡፡ ሰሞን ደግሞ ፖሊሶቹ ተነሥቶባቸው ከየመንገዱ እያፈሱ ወደ ሀገር ቤት ሰውን መላክ ጀምረው ነበር፡፡ አንዳንዴም አበሻ አለበት በሚባለው ሠፈር ፍተሻ ያደርጉ ነበር፡፡ እየተደበቁ መኖሩ ሰለቻት፡፡ መሰልቸት ብቻ ሳይሆን ለብዙ ጊዜ መደበቁ ሥራ እንዳትሠራም አደረጋት፡፡ እጇም እያጠረ መጣ፡፡
 ይኼኔ መረራትና ወደ ሀገሯ ልትገባ ወሰነች፡፡ አስቀድማ ግን እንዲዘጋጁ ለወላጆቿ ለመንገር አሰበችና ደወለች፡፡ «እኔ እዚህ ሀገር ያለ ቪዛ መኖር ሰልችቶኛል፡፡ በየቀኑ መደበቁም አስመርሮኛል፡፡ አሁን ወደ ሀገሬ ልመጣ ነው» አለች፡፡ ይኼኔ አባቷ «ኧረ ልጄ ሲሆን እኅቶችሽንም መውሰድ ነው እንጂ አንቺማ አትምጭ» አሏት፡፡ «እኔ እዚህ ሀገር ከዚህ በኋላ መሰቃየት አልፈልግም፤ ልመጣ ነው፡፡ መሥራትም አልቻልኩም፡፡ ከፖሊሶቹ መደበቅም አልቻልኩም፡፡» ትላቸዋለች፡፡ «አንቺ ከመጣሽኮ የኛ ኑሮ አበቃ ማለት ነው፤ ግዴለም እንደምንም ብለሽ እየተደበቅሽ ሥሪ» ይሏታል፡፡ «እንዴ አባዬ የት እደበቃለሁ፤ መንገድ መሄድኮ አልቻ ልኩም፤ ይይዙኛል» ትላለች፡፡ «አይ እንደው እንደምንም በጫካም ውስጥ እየተደበቅሽ ቢሆን ሥሪ» ይሏታል፡፡
ይኼኔ ዕጢዋ ዱብ ይላል፡፡ «እነዚህ ሰዎች ገንዘቤን እንጂ እኔን አይፈልጉም ማለት ነው ትላለች ለራሷ፡፡ ከዚያ በኋላ ቪዛዋን የምታሠራበትን መንገድ ማፈላለግ ትጀምራለች፡፡ አይገቡ ገብታም በጭንቅ ታገኛለች፡፡ ስልኳን ግን ከቤተሰቧ ለመጨረሻ ጊዜ ሠወረች፡፡ መገናኘትም አቆመች፡፡
ይህንን ታሪክ ዛሬ ያስታወሰኝ እዚህ አሜሪካ አንዲት ሌላ እኅት የነገረችኝ ታሪክ ነው፡፡ ከዋሽንገተን ዲሲ ወደ ኦክላንድ ካሊፎርንያ ለመብረር ዳላስ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እያለሁ አገኘኋትና ማውራት ጀመርን፡፡ «እንዴት ነው ኑሮ በአሜሪካ? አገባሽ? ወለድሽ? ለውጥ የለም ወይ አልኳት፡፡ እየሳቀች የሚከተለውን ታሪክ አወጋችኝ፡፡
«ባለፈው እንዳስተዋወቅኩህ አንድ እጮኛ ነበረኝ፡፡ አንድ አምስት ዓመት አብረን አሳልፈናል፡፡ እኔ ለማግባት ካሰብኩ ቆየት ብያለሁ፡፡ ግን አንድ ሃሳብ ነበረኝ፡፡ መጀመርያ ቤተሰቦቼን ልርዳ የሚል፡፡ ለወላጆቼ ኮንዶሚኒየም ቤት ገዛሁ፡፡ እርሱ ብቻ ነው የተሳካልኝ፡፡ ታናሹ ወንድሜን ኮሌጅ ላስተምር ጀምሬ ነበር፡፡ «አሜሪካ ውሰጅኝ እንጂ አልማርም» አለኝ፡፡ ብለው ብሠራው አይሆንም አለ፡፡ ታናሿ እኅቴ ደግሞ «አንቺ ከዚያ ዕቃ ላኪልኝ እኔ እዚህ ሱቅ ልክፈት» አለች፡፡ መጀመርያ ሳስበው መልካም ሃሳብ ነው ብዬ ጀመርኩት፡፡ ግን ሊዘልቅ አልቻለም፡፡
አንደኛ ሌላ ሥራ ሆነብኝ፡፡ እኔ እዚህ በርካሽ ያለበትን ቦታ ማሠስና ሰው ፈልጎ መላክ ሆነ ሥራዬ፡፡ ከዚያም በላይ ለዕቃው መግዣ ገንዘብ እኔ ነኝ የምከፍለው፡፡ ጥቂት ጊዜ ከረዳኋት በኋላ ከእንግዲህ ራስሽን ችለሽ ሥሪ፡፡ እኔ ይህንን የዘወትር ጉዳዬ ማድረግ አልችልም አልኳት፡፡ አኮረፈችና ሥራውንም ተወችው፡፡
እኔ ሲሰለቸኝ ይህንን ያህል ዘመን ከረዳሁ አሁን ደግሞ ወደራሴ ሕይወት ለዙር ብዬ ትዳር ለመመሥረት አሰብኩ፡፡ ያንን ለቤተሰቦቼ ስነግራቸው አበዱ፡፡ እንዴት እኛ ወንድምሽን አግብተሽ ትወስጅዋለሽ እያልን አንቺ ሌላ ታገቢያለሽ አሉኝ፡፡ ይታይህ እንግዲህ እርሱን አግብቼ ካመጣሁት ከዚህ በኋላ ቢያንስ ሁለት ዓመት መጠበቅ አለብኝ፡ እኔ ደግሞ እድሜዬ እየጨመረ ነው፡፡ እርሱን እንደዚህ ማድረግ አልችልም አልኳቸው፡፡ ካልሆነ አንቺም ሌላ ሰው አግብተሽ ውሰጅ፣ በምትኩም እኅትሽን አግብቶ የሚወስድ ፈልጊ እንጂ አይሆንም አሉኝ፡፡
እስከ መቼ የኔ ሕይወት በሌሎች ፈቃድና ፍላጎት ይመራል ብዬ አሰብኩ፡፡ ለእኔ ሕይወትስ የሚያስብ የለም ወይ? እኔ እኅታቸው ወይንም ልጃቸው ነኝ ወይስ የርዳታ ድርጅታቸው? የኔ የርዳታ መጠንስ እስከየት ድረስ ነው? ብዙ ነገር አሰብኩ፡፡ ሲመረኝም ርግፍ አድርጌ ተውኩት፡፡ አሁን በቃ በራሴ ወስኜ ላገባ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ ግን ሁሉም አኩርፈውኛል፡፡ ባይሆን እናንተ ትድሩኛላችሁ» አለች እየሳቀች፡፡
ብዙ ወገኖቻችን ወደ ውጭ ሀገር ለኑሮና ለሥራ ከሚሄዱበት ምክንያት አንዱ ቤተ ሰቦቻቸውን ለመረዳት ነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸው ማሳለፍ እንደ ትልቅ ስኬት ያዩታል፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን የመደገፍ ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ ግዴታ አለና የሚመሰገን ነው፡፡ ነገር ግን ርዳታችን የት ድረስ መሆን አለበት? የምንረዳው እነማንን ነው? የምንረዳበት ዓላማስ ምንድን ነው? ርዳታችንስ በሰዎቹ ላይ ምን መፍጠር አለበት? መርዳት ያለብን መርዳት ስለቻልን ነው ወይስ መረዳት ስላለባቸው? ውለታን መክፈል የሚቻለውስ በመርዳት ብቻ ነው? የሚሉትን በሚገባ ካልመለስናቸው ርኅራኄያችን ከሚያድናቸው ሰዎች ይልቅ የሚገድላቸው ሰዎች ሊበዙ ይችላሉ፡፡
ርዳታ ሰውን ከችግር ለማውጣትና ሕይወቱ እንዲቀጥል ለማድረግ እንደሚያስችለው ሁሉ ርዳታ ሰውንም ይገድለዋል፡፡ ሰውዬውን ሞራለ ቢስና ጥገኛ አድርጎ ያኖረዋል፡፡ ከነ ሙሉ ክብሩና ግዴታው እንዳይኖርም ያደርገዋል፡፡ ሕልውናውን በሌሎች ላይ ብቻ እንዲመሠርትም ያደርገዋል፡፡ ርዳታ ሰውን ሰነፍና ሃሳብ የለሽ ሊያደርግ ይችላል፡፡
እዚህ አሜሪካ ከሚኖሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ከፊሎቹ በሀገሩ የሚሰጠውን የማኅበራዊ ዋስትና ርዳታ ብቻ በመቀበል የሚኖሩ ናቸው፡፡ መሥራትን እንደ ባህል እንዳይቀበሉት፣ ጥሮና ግሮ መኖርንም እንደ ስቃይ እንዲያዩት አድርጓቸዋል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ርዳታ የሚገኝባቸውን መንገዶች በማፈላለግ ኑሯቸውን በርሱ ላይ ይመሠርታሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በአብዛኛው ርዳታ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡ በርዳታ ተወልደው በርዳታ የሚያድጉ ልጆችን በማፍራታቸውም የርዳታ ተቀባዩ ትውልድ ሠንሠለቱን ማቋረጥ አልተቻለም፡፡ አንዲያውም ርዳታውን በደንብ ለማግኘት ሲባል በልጅነት መውለድንና ብዙ ልጆች ማፍራትን ያዘወትራሉ ይባላል፡፡
የማኅበራዊ ዋስትና ገንዘብ እነዚህን ሰዎች ጠቀማቸው ወይስ ጎዳቸው? የሚል ክርከር እየተነሣ ነው፡፡ ርኅራኄው አድኗቸዋል ወይስ ገድሏቸዋል? ብዙ ልጆችን ከተለያዩ ባሎች እንዲወልዱ፤ ትምህርታቸውን በጊዜ እንዲያቋርጡ፤ ሥራን በአግባቡና በሥርዓቱ እንዳይሠሩ፤ አካባቢያቸው በንጽሕናና በጽዳት የተጠበቀ እንዳይሆን አንዱ አስተዋጽዖ ያደረገው በርዳታ ተደግፈው መኖራቸው ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡
ገንዘቡ እንደልብ የሚገኝና ድካም የማይከፈልበት በመሆኑም በቁጠባ ለዘላቂ ነገር ከማዋል ይልቅ ለአደንዘዥ ዕጽና ለመጠጥ እንዲጠቀሙበት አድርጓቸዋል፤ ወንጀል እንዲበራከትና ግብር መክፈልን ባህሉ የማያደርግ ትውልድ ለማፍራትም አብቅቷቸዋል የሚሉ ተከራካሪዎችም ተነሥተዋል፡፡
በኛም ሀገር ቢሆን ችግረኞችን እንደዚህ ሀገር በተቀናጀ መንገድ እንኳን ባይሆን በየግላችን የመርዳቱ ባህል አለን፡፡ አንዱ ሀብትን ለሌሎች የምናካፍልበት መንገድ ነውና፡፡ በሃይማኖትም ቢሆን ድኾችን መርዳት ግዴታ ነው፡፡ ጥያቄው ግን ድኾች እነማን ናቸው? የሚለውና ድኾችን በትክክለኛው መንገድ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡
በየቤተ ክርስቲያኑና መስጊዱ አያሌ ነዳያን ተኮልኩለው ይገኛሉ፡፡ እዚያ የሚኖሩበት ምክንያትም አላቸው፡፡ ለእነርሱ የመስጠት ሃይማኖታዊ ግዴታ አለብን የሚሉትን ምእመናን የሚያገኟቸው እዚያ ስለሆነ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የተደረገ ጥናት እንዳሳየው በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ዙርያ ያሉ ነዳያን እዚያው በመኖር ብቻ እስከ አራት ትውልድ አፍርተዋል፡፡ ቅድመ አያቷ ወይም ቅድመ አያቱ እዚያ ትለምን የነበረች ወይም ይለምን የነበረ ትውልድ ዛሬም ሳይቀየር እዚያው ቦታ ላይ አለ፡፡ ነዳያን ነዳያንን እየወለዱ ማለት ነው፡፡
የኛ ርዳታ ነዳያኑን ከነዳይነት የሚያወጣ አልሆነም፤ እንዲያውም የነዳያን ትውልድ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ ነው ከርዳታችን ባሻገር ስለ ርዳታ አሰጣጣችን እንድናስብበት የሚያስገድደን፡፡ ርዳታችን ነዳያኑን ሳይኖሩም ሳይሞቱም እንዲቀጥሉ እያደረጋቸው ብቻ ነው፡፡ ርዳታችን ነዳይነት እንዳይቋረጥ እያደረገ ብቻ ነው፡፡ ርዳታችን ችግረኛን እያኖረ እንጂ ችግርን እየፈታ አይደለም ማለት ነው፡፡ ነዳያኑ የልመና ግጥማቸውን እንጂ ሕይወታቸውን መቀየር አላስቻላቸውም፡፡
በአንድ ወቅት ከአዋሳ ከመጣ ወዳጄ ጋር አራት ኪሎ ቅድስት ማርያም በር አጠገብ ቆመን ስናወራ አንድ በአካባቢው በልመና የተሠማራ ጎልማሳ ወዳጄን በስሙ ጠራው፡፡ እርሱም ደንግጦ ዘወር አለ፡፡ አንዴ ላናግርህ እችላለሁ? አለው፡፡ ያን ጊዜ እኔ ፈቀቅ አልኩላቸው፡፡ ከአንድ ከሃያ ደቂቃ በኋላ ራሱን እየነቀነቀ መጣ፡፡ እኔም ምን ሆንክ? አልኩት፡፡
ልጁ እነርሱ መሥሪያ ቤት በአትክልተኛነት ይሠራ የነበረ ነው፡፡ አንድ ቀን አዲስ አበባ ለጉዳይ ይመጣል፡፡ ሲዘዋወር ቆይቶ ይደክመውና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዐረፍ ለማለት ይገባል፡፡ በጣም ደክሞት ስለነበር አንዱ ዛፍ ሥር ጥቅልል ብሎ ይተኛል፡፡ ሲነሣ የሆነው ነገር የሕይወቱን መሥመር አስቀየረው፡፡
ከዕንቅልፉ ሲነሣ በዙርያው ብዙ ብሮችና ሳንቲሞች ተዘርግተዋል፡፡ እየገረመው ዘወር ዘወር ብሎም እያየ ቆጠራቸው፡፡ አሥራ ስምንት ብሮች ተሰባስበዋል፡፡ እርሱ በወር የሚያገኘው ሦስት መቶ ብር ነው፡፡ አሁን ምንም ሳይለፋ አሥራ ስምንት ብር አገኘ፡፡ ታድያ ለምን ጥቂት ጊዜ አልሠራም አለና ጀመረው፡፡ «ይኼው ዓመት ሆነኝ፡፡ አሁን አዋሳ ቤት እየሠራሁ ነው» አለና ነገረው፡፡ እንደዚህ ልጅ ልመናን ቀላል የገንዘብ ማግኛ መንገድ እድርገውት የተሠማሩ «ፕሮፌሽናል ለማኞች» ሞልተዋል፡፡
አንዳንዱ ርዳታ የኛን ርኅሩኅነት እንጂ የችግሩን መልክ የሚያሳይ አልሆነም፡፡ የምንሰጠው ርዳታ የሰውዬውን ችግር ይፍታ አይፍታ? ለሰውዬው የሚያስፈልገው ይሁን አይሁን አናመዛዝንም፡፡ ብቻ መስጠት ግባችን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ርኅራኄያችን ከመጥቀም ይልቅ የሚጎዳበት ጊዜ አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በውጭ ያሉ ወገኖች ለቤተ ሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ወደ ሀገሪቱ ከሚገቡ ገንዘቦች ትልቁን ቦታ እየያዘ መምጣቱ ይሰማል፡፡ ይህ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ላሳደገች ሀገር ውለታ መክፈልም ነው፡፡ ነገር ግን የምንልከው ገንዘብ የሚያድን እንጂ የሚገድል እንዳይሆን መጠንቀቅም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በአሜሪካና በዱባይ ገንዘብ የሚዘንጡ ወገኖችን ማፍራት፤ የሽቱና የጫማ፣ የአይፎንና የአይፖድ ዓይነት እያጠኑ ላኩ የሚሉ ወንድሞችና እኅቶችን ማፍራት በርኅራኄ መግደል ነው፡፡
አንድ በዲግሪ የተመረቀ ወጣት በወር ተጣርቶ ከአንድ አምስት መቶ ብር በላይ አያገኝም፤ አንድ ወንድሙ ወይም እኅቱ መቶ ዶላር በየወሩ የምትልክለት ተመጽዋች ግን በየወሩ አንድ ስምንት መቶ ብር የተጣራ ያገኛል፡፡ ይህንን እያየ ማን ይማራል ታድያ? አንዳንዶቹም «እዚህ ኢትዮጵያ የሚሰጠው ትምህርት አሜሪካ ዋጋ ስለሌለው ለምን እደክማለሁ» ይላሉ አሉ፡፡ ኧረ ሌሎቹ ደግሞ «ነገ አሜሪካ ስሄድ ለማቋርጠው ለምን እማራለሁ» የሚሉም አሉ አሉ፡፡ አካላቸው ኢትዮጵያ ልባቸው አሜሪካ የሆኑት፡፡
አንድ ሰው እንዲያውም «እኔ ሀገር ቤት ስደውል ሁሉም ነገር ተወድዷል፤ መኖር አለተቻለም፤ መቅመስም መላስም አልቻልንም የሚሉኝ ርዳታዬን እንዳላቋርጥ ሳይሆን አይቀርም» ብሎኛል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ኑሮ እየተወደደ ቢሆንም ውጭ ሀገር ያለ ሰው ሲሰማው ግን ቫት 15% የአገልግሎት ክፍያ 10% ተጨምሮበት ነው፡፡ ደግሞ ልጁ እንዳለው የርዳታውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ይመስላል፡፡
ርኅራኄ ከደግ ሰዎች እሴቶች አንዱ ነው፡፡ነገር ግን ርኅራኄ የሚያድን እንጂ የሚገድል መሆን የለበትም፡፡ የኛ ግዴታ የመስጠት ብቻ አይደለም፡፡ ወገኖቻችንንም ከችግር የማላቀቅ ጭምር እንጂ፡፡ አጠቃቀሙን ለማያወቅ ሰው የጋዝ ምድጃ መስጠት መግደል እንጂ መርዳት አይሆንም፡፡ ለአንድ ሰው የት ድረስ እንደሚሄድ ሳይነግሩ መንገድ ማሳየት ማጥፋት እንጂ ማገዝ አይሆንም፡፡
እናም እንርዳ፤ ግን ርዳታችን ሕይወት ለዋጭ እንጂ፤ ልብስ ለዋጭ፣ አይሁን፡፡ አመለካከት ለዋጭ እንጂ ጫማ ለዋጭ አይሁን፡፡ ደረጃ ለዋጭ እንጂ ስልክ ለዋጭ አይሁን፡፡ ራርተን እናድን እንጂ ራርተን አንግደል፡፡
ሳክራሜንቶ፣ ካሊፎርንያ

40 comments:

 1. Dani god bless you thank you for ur views this is such good thing that we have to take attention fron know on...........

  ReplyDelete
 2. በጣም ጥሩ እይታ! እናመሰግናለን! ልብ ያለው ልብ ይበል!

  ReplyDelete
 3. አቤት አቤት ዳንኤል! እንዴት የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ፈላሽ (ስደተኛ) ኮረኮርከው ጃል። እያንዳንዳችን፤ ወደንም ሆነ ተገደን ኑሯችንን በባዕዳን አገራት የመሠረትን የኢትዮጵያ ልጆች በዚህ ጉዳይ ላይ ካሉን ዓያሌ ምሣሌዎች አንድ እንኳን በድረ-ገጽህ እናስፍር ብንል ቦታ እክ አይበቃንም! በኔ አስተያየት አገር ቤት ያሉ የሥጋ ወገኖቻችንንም ይሁኑ የትምህርት ቤት ጓደኞች በተማሩት እና በተሠማሩበት የሥነ ልቦና ፍልስፍና የኛን ኅሊና ከመፈታተን ይልቅ ትኩረታቸውን ወደራሥ መሻሻልና ወደአገር እድገት ቢያዋሉት ኢትዮጵያ የት በደረሰች ነበር። ልብ የማይሉት ግን አንድ ትልቅ ዛፍ ለብዙ ሰው ከፀሐይ ወላፈን መጠለያ ነው፤ ዳሩ ግን የዚያን ዛፍ ቅርንጫፎች ለማገዶም፣ ለአርጩሜም፣ ለቤት መሥሪያም፣ ወዘተ ነጋ ጠባ ቢመለምሉት፤ እንኳን ለሌሎች ጥላ ሊሰጥ ቀርቶ ለራሱም መንምኖ የመሞት ዕጣው ከፍ ያለ መሆኑን ነው።

  ReplyDelete
 4. Thank yo Daneal. It is a very nice article. I have lots of expriences on this with my sisters living in America. My sisters are sending money to our family however this money has not changed the life of the family specialy our brothers. They are supporting our brother who are alcoholic and addicted with Chat but they are not welling to support and encourage other brothers and siters who are straiving for better life. When my younger brother was continueing his higher education in summer by paying all fees, my sisters didn't send him 1USD but they were sending addicted brothers 100USD Per 1 to 2 months for Chat and alcohol. I have discussed this issue with them so many times but no change from their side instead of this they are pushing us to give money to those vulnerable bras. Selezih kebeteseb wuste seaw lemehon yemifecherecheruten merdat lelochun lesera yemiyanesasa lehon yechelal yemil emnet alegn. zebehare Mekan Eyesus

  ReplyDelete
 5. yaa its true all!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 6. Egziabhair Yitebkih.kale hiywot yasemahe.Nuruachinin endih teredalin enji..............................

  ReplyDelete
 7. Daniel betam wesagn agenda new!!

  ReplyDelete
 8. "እንርዳ፤ ግን ርዳታችን ሕይወት ለዋጭ እንጂ፤ ልብስ ለዋጭ፣ አይሁን፡፡ አመለካከት ለዋጭ እንጂ ጫማ ለዋጭ አይሁን፡፡ ደረጃ ለዋጭ እንጂ ስልክ ለዋጭ አይሁን፡፡ ራርተን እናድን እንጂ ራርተን አንግደል፡፡" Dani ante nurilin

  ReplyDelete
 9. እዉነት ነዉ የሰዉን ላብ አልባሌ ቦታላይ እያዋሉ ለራሳቸዉ ሰዉ ሳይሆኑ ሌላዉም ሂዎትን ሳይኖራት ለነሱ መጠቀሚያ ብቻ እንዲሆን የሚሹ አያሌ ቤተሰቦች አሉ ለምሳሌ አንዲት ልጅ 14 አመት ሙሉ አረብ አገር ኑራ ለቤተሰቦቿ ቤት ሰርታ ለእህት ወንድሞቿ የሚገባቸዉን ካደረገች በኋላ አሁን ልመጣ ነዉ ብላ እቃዋን በካርጎ ልካ ብሯን ሁሉ በእህቷ ስም ልካ ካበቃች በኋላ ትኬት ልትቆርጥ ስትል ለምን ገንዘብ ታባክኛለሽ ተጠርፈሽ ብትመጭ ይሻላል እንጂ 6000 ብር ቀላል ማድረግሽ ነዉ እስክትጠረፊ እዚያዉ ቆይ አሏት፡፡ በዚህ መሃል በጣም ታመመችና አገሯ ሳትገባ እናቷንም ሳታይ ሂወቷ በ ሰዉ አገር ለማለፍ በቃ፡፡ ለ 6000 ሽ ብር ሲጨነቁ እሷንም አጡ ለአስክሬን ማምጫም 50000 ብር ከፈሉ፡፡ እንዲህም አለ እና እባካችሁ እናስብላቸዉ፡፡

  ReplyDelete
 10. Nice topic . Not only the topics but the comment of our citizens who are in refuge is very important and interesting for me.so i expect more ideas on this.

  ReplyDelete
 11. እግዚአብሔር ይስጥልን

  ReplyDelete
 12. ዳኒ ከዚህ ታሪክ ጋር የሚሄድ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጸመ አውቃሉ፡፡ በአንድ አርብ አሰራ ስድስት ዓመት ሙሉ እየሰራች የላከችውን ወንድሟ የራሱን ኑሮ ስላደራጀበት ከ16 ዓመት በኋላ ስትመጣ ባዶ እጇን ቀርታ አሁን በጥቃቅንና አነስተኛ ራሷን ለማሸነፍ ትጣጣራለች፡፡

  ReplyDelete
 13. የቤተሰባችንን ታሪክ ማን ነገረህ?
  እህቴ ነፍስዋን ይማረውና ትምህርት አቁማ በስደት አገር መከራዋን ስትበላ እኛ በሚያማምሩ ልብሶች ከሰው በላይ ለመኖር እንጥር ነበር:: እግዚአብሔር ይማርሽ አላልናትም:: መርዶዋን ብቻ ሰማን:: እናታችን በመጀመሪያ ልጅ ሐዘን ተጎድታ ብዙም አልቆየችም በመንገድ ተከተለቻት:: አባቴ የልጅ እጅ እያየሁ እያለ ደስተኛ ባይሆንም በእኔ ድጋፍ እየኖረ ነው:: አግባ ይለኛል አንተስ እለዋለሁ.... ካባቴ ጋር ላረጅ ወስኛለሁ:: ዳኒ እረጅም እድሜ ይስጥህ ተጽናንቻለሁ::

  ReplyDelete
 14. Thanks Dani, this culture or viscous circle problem of supporting one another has to stop.

  Thanks

  ReplyDelete
 15. kale heiwate yasamalen

  ReplyDelete
 16. ያሳዝናል! ዲያስፖራ ሳንሆን የታገትነውስ? እኔ አድርጌዋለሁ: "ስልታዊ ጭካኔ" አማራጭ የለውም!! ተያይዘን ሁላችንም አሠልቺ :ተመሣሣይ ህይወት መግፋት አቆርቈዥ ስለሆነ. . . .give them only what they deserve! እናት አባት ሀገር ቤት ላለ ወንድ ለመዳር ዘሩ ይታወቅ: ዱርዬ ነው :ወዘተ. . . ግን በ internet ለተገኘ ማንነቱ የማይታወቅ የውጭ ዜጋ ለመሸጥ ግን አይመነቱም::why??? የቤተሰብ ፍቅር የሚባለውን ሁለት ዐይኖቻችንን ከፍተን ለማየት እንድፈር!!! I know how much we r poor financially as a whole; but z depth of poverty of intelligence is far beyond malignant than z finance. So why should we pamper IGNORANCE? We must fight it to z end systematically. . . i really understand z fierce reaction . . . but for me to align z deviation we must act unshakably! Thank u dani there r lots of stories abt it!

  ReplyDelete
 17. I absolutely agree with you.
  Be blessed

  ReplyDelete
 18. That is why we still r in poverty quagmire. . . i hate dependency! I heard a story which changed my life. . . He came as a new graduate from Cuba. His younger sister rushed to Addis and stuck wiz him. Her expectation bothered him. Expectation for herself and insisted he must build house for z parents . . . etc. But z reality was his salary hardly enables to support a living. She failed to sense that. He planned to aggressively show her z real life. So when she asked for a pair of shoe he bought her 'congo chama'. She screamed and told her parents he is abusing her. Parents yelled. Despite z pressure he remained firm. Time went by. . . life in Ethiopia was unchanging. He decided and left for Israel. Being there he realized his sister wiz such distorted knowledge of life she would be a burden. And took her to Israel. He lent her some money wiz a binding agreement if she fails to say he would sue. She had no option but crying to her parents. Z family and neighbours all cursed him. He remained defiant. It took his sister years to pay him back coz she has to live by her own. Finally she became free from debt but realized if she work harder she can get much more. Money is sweet! She independently focused on money making and became huge even more than her brother. Now she has no words to thank her "cursed" brother. Real story ladies and gentlemen welcome to z real world. Challenge ur parents, family every one. And be defiant then u'll see the change. I used his model and it's really working! Thanks dani.

  ReplyDelete
 19. Thank yoou agian,

  Just to let you it really hurts to know that no one cares! No one really remembers you. I can not say I helped my family like the people you discussed but I tried. There was a time I did not have any money but I had to pay overdraft fees to the banks. I paused everything so I can go back home and I find out no one cares and I can not blame them in part, because of the distance and the time gap. But it still hurts to know you do not have no one

  ReplyDelete
 20. አጠቃቀሙን ለማያወቅ ሰው የጋዝ ምድጃ መስጠት መግደል እንጂ መርዳት አይሆንም፡፡

  ReplyDelete
 21. Really nice and interesting topic. but it is some times difficult to know who needs help and who does not. challenging our families and any fellow Ethiopian to help them selves should always be in our mind but we need to be also very vigilant not to be on the extreme side like we know some very selfish,luxury and money loving friends of ours who has turned their deaf ear on their families or any needy citizen of our nation

  ReplyDelete
 22. EGZABHER AMELAK Ye Ageliglot Zemenihen Yarzimelh

  westen Yeminka Tsihuf New EGZIABHER Yebarkih D. Danii

  ReplyDelete
 23. some super hero ninja like yours need to show us how to kick the ass of life's cruelty. it is fear which is holding us back. it is narrow understanding of our situation which is keeping us on the sofa. it is wrong perception of things which made us 'looser' and poverty a 'winner. we need to be a ninja to kick ass of fear, boredness, narrow understanding, wrong perception. we need to work our but off if we want to change the image of our country. there is no such thing as 'Emeye Ethiopia' while partying everyday. As for me i've already stopped blaming my relatives and my family. i am the only one responsible for my life. tnx dn. daniel.

  ReplyDelete
 24. ዳኒ የዛሬው ጉዳይ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን የሚነካ ነው
  በተለይ እኔ በጣም መሮኛል በተለይ extended family
  ብቻ እ/ሄር ለሁላችንም ልብ ይሰጠን

  ReplyDelete
 25. «ነገ አሜሪካ
  ስሄድ ለማቋርጠው ለምን እማራለሁ» የሚሉም አሉ

  ReplyDelete
 26. በጣም ጥሩ እይታ! እናመሰግናለን! ልብ ያለው ልብ ይበል!

  ReplyDelete
 27. ohh Daniyie yelibien tenagerkeligne God bless u

  ReplyDelete
 28. dani yehulnem problem tidasslehina amlak yerdah tilk astemarenh

  ReplyDelete
 29. Dani, i usually appreciate your articles. all of them are touchy and up to date. this country needs a person like you. sorry to say this please erase this announcement from your blog 'ብሎግ ሥራዎች ማገዝ ከፈለጉ እነዚህን ይጠቀሙ.' although there are costs to run this blog.
  sincerely your brother,

  ReplyDelete
 30. Dear Daniel
  Once again thank you very much for your insight. It is indeed sad to witness too may families being dependent on the money they get from abroad, but what is more depressing is the fact that those who are at the receiving end are much more better off than those who send the money.Those who send the money earn it the hard way, those who receive it just wast it as if it is not their own money. This is a real paradox. In fact those people who are receiving money from abroad make similar effort to earn the money where they are, i think there is a big chance that they will earn much more than what they get from abroad. I think it is basically poor mentality and lack work ethic. God bless us all, our children and the new generation all.

  ReplyDelete
 31. -በእናተ አድሮ ቤተ ክ/ያንን የጠበቀ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን….. ቃለ ሕይወትን ያሰc

  ReplyDelete
 32. የአምድህ ተከታታይ ነኝ በአሁኑ አባባልህ ግን አልስማማም
  በርግጥ በእናንተ ላብ እኛ ብቻ እንኑር የሚሉ ካሉ በጣም ተሳስተዋል፡፡
  የራሳቸውንም ኑሮ እየኖሩ ቤተሰቦቻቸውን የሚረድ ልጅች እንዳሉ አውቃለሁና
  ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት ይቁጠረው ምግብ በልቶ የሚያድረውን፡፡
  በአሁኑ ስዓት በልቶ የሚያድረገው ወይ ልጅ ከኢትዮጰያ ውጭ
  ያለ ወይም በጉቦ የሚኖር ይህም ስልህ በአሁኑ ስዓት ኢትዮጵያ ውስጥ
  አንድ ነገር ለማግኘት ወደ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ስትሄድ
  ለትንሼ ነገር ብር ትጠየቃለህ ነውር የነበረው ጉቦን እንደ ሐጥያት ሲቆጥርው የነበረ
  ህዝብ በኑሮ ውድነት፣ ኑሮውን ማሸነፍ ስለአቀተው በእግዚአብሔር ዘንድ አታድርግ
  የተባለውን ማድረግ ጀምራል፡፡ እግዚአብሔር ፊቱን ካላዛረልን በስተቀር አገራቸን
  ወደት እየሄደች እንደሆነ እስከማናውቀው ድረስ ጉቦ እየተስፋፋ ነው በእርግጥ እኛ
  ኢትዮጵያኖች እጃችንን ወደ እግዚአብሔር ባለመዘርጋታችን ምክንያት ይህ ሁሉ ደረሰብን
  በሐጢያታችን ምክንያት ለምለም አገር ይዘን ስደተኛች እርሃብተኛች ሆነናል ስለሆነም
  ሁላችንም ወደ ላይ ማንጋጠጥ እንዳለብን ነው አንድ አባባል ላክልበት አትሩጥ አንጋጥ ነው፡፡
  ማንጋጠጡ ለአገራችንም ለእኛም ይበጀናልና፡፡

  ReplyDelete
 33. abet abet D Daniel kibret yehulachen cheger new yegeletekew!yene cheger yeha new!!ahun ahun tilke stress yalebengne yebeteseba gudaye new!
  enesun lemerdat beye collage akumyalehu!
  from usa

  ReplyDelete
 34. Teru Miker Naw Thankyou Dn.Dani!!

  ReplyDelete
 35. TERU MIKER NAW D.DANI!!

  ReplyDelete
 36. Dani behewenet melkam eyeta,yesedetegnawen yeleb tirita yadamete yewestun bisotna sigat yadamete endihum wechi ager wendim weym ehete alegn belew rasachewen kemesrat weiym kememar yelek temetsewach aderegew laskemetu wetatoch yemankiya dewel new. Egzihaber tsegawen yabzalhe!!!

  ReplyDelete
 37. i got one person in different place addis ababa gimma and shaamene he enter in the bus said that my money stolen by thiefs please give for transport

  ReplyDelete
 38. ሳሚ (ወ/ሚካኤል)June 22, 2012 at 5:37 PM

  መምህር ዳኒ ረዘም ላሉ ቀናት ኢነተርኔት አልባ ረፍት ወስጀ በመክረሜ የጡዋት ጸሎቴን የረሳሁ ያህል ካንተ ጽሁፎች መራቄ ቅር ሲለኝ ሰነበተ!!! አሁን ግን ይሄው እጎሰጉሰው ያዝኩኝ!!!! በዚህ ጉዳይ ሰሞኑን ከህቴ ጋርተከስቶብኝ የነበረውን ክርክር በፍትነት እንዳቆምና ለዘመናት የተሰበክነውን ድሆችን የመርዳት ወንጌል በንስር አይን በጥለቀት እንዳየው ስለረዳኸኝ ...የወንጌሉ ባለቤት ቃለህይወት ያሰማልኝ!!! ግን ጽሁፉዋ በጣም ከማጠሩዋ የተነሳ ብዙዎች እንዳይደናገጡ ...ብዙዎች ነገር ፈላጊዎችም ምቹ ግዜ ጠብቀው አንባቢዎችህን ወይም እንደኔ አይነቱ ተማሪህን እንዳያደናግሩ በይበልጥ በቤተክርስቲያናችን ዙሪያ ስላለው ዝቅተኞችን የመርዳት ጽንሰ ሃሳብ ሰፋ ያለ እይታህን ብታቀርብልን ምልካም ነው!!!!! በውነት ውጭ ያሉት በፎቆች ተከበው የጭንቀት ፎቅ የተከመረባቸው ወገኖቸ ሆዴን በሉኝ!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 39. Oh Dany how much it is interesting!!
  So many thanks!! Please write again and again!

  ReplyDelete