Thursday, May 10, 2012

ሦስቱ ማጣርያዎች

አንድ ወዳጄ እንዲህ የሚል የዕውቁን የግሪክ ፈላስፋ የሶቅራጥስን አባባል ላከልኝ፡፡ 

ሶቅራጥስ አንድ ጓደኛ ነበረው አሉ፡፡ አንድ ቀን ይኼ ጓደኛው መጣና «ሶቅራጥስ እገሌ ስለሚባል አንድ ወዳጅህ የሰማሁትን ነገር ታውቃለህ?» አለው፡፡ ሶቅራጥስም ዝም ብሎ ተወው፡፡ ሰውዬው ግን በሰማው ነገር ሳይደነቅ አልቀረምና እየደጋገመ «በጣም የሚገርምኮ ነው፡፡ እንዲህ ይሆናል ብዬ የማልገምተው ነገር ነው» ይለው ነበር፡፡ በነገሩ የተሰላቸው ሶቅራጥስም 
«በጣም ጥሩ፡፡ የሰማኸውን ነገር ትነግረኛለህ፡፡ መጀመርያ ግን ሦስት ጥያቄዎችን መመለስ አለብህ፡፡ የምትነግረኝ ነገር የእነዚህን የሦስት ጥያቄዎች መልሶች የሚያሟላ ከሆነ ብቻ እሰማሃለሁ» አለው፡፡

ሰውዬውም በዚያው ሃሳብ ተስማማ፡፡


«የመጀመርያው ጥያቄዬ የእውነታ ጥያቄ ነው» አለው፡፡ 

«ቀጥል» አለ ሰውዬው

«ለመሆኑ አሁን ለእኔ የምትነግረኝ ነገር መቶ በመቶ እውነት መሆኑን ርግጠኛ ነህ?» አለው፡፡ ሰውዬው ጥቂት አሰበና «መቶ በመቶ እውነት መሆኑን አላረጋገጥኩም፡፡ ነገር ግን የሰማሁት ነገር» ብሎ ሊቀጥል ሲል ሶቅራጥስ አቋረጠውና 

«ስለዚህ ያነሣኸው ነገር እውነት ይሁን ውሸት ርግጠኛ አይደለህም ማለት ነው፡፡ መልካም አሁን ወደ ሁለተኛው ጥያቄ እንለፍ፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ የመልካምነት ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ የተዘጋጀኸው ነገር መልካም ነገር ነው?» አለው፡፡

ሰውዬውም «መልካምማ አይደለም፤ እንዲያውም በተቃራኒው ነው» ሲል መለሰለት፡፡ ሶቅራጥስም «ስለ ወዳጄ የምትነግረኝ ነገር እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፣ ደግሞም መልካም ያልሆነ ነገር ነው፡፡ ይገርማል፡፡ አሁን ሦስተኛው ጥያቄ ይቀርሃል፡፡ ሦስተኛው ጥያቄ የጠቀሜታ ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ስለ ወዳጄ የምትነግረኝ ነገር ለእኔ ምን የሚጠቅም ነገር አለው?» አለና ጠየቀው፡፡

ሰውዬውም «ላንተ የሚጠቅምህ ነገር የለውም፡፡ ግን ብትሰማው መልካም ነው ብዬ ነው» አለው፡፡

«በጣም ጥሩ» አለ ሶቅራጥስ፡፡ «አሁን ስለ ወዳጄ የምትነግረኝ ነገር እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፣ መልካም ያልሆነና ለእኔም ምንም የማይጠቅመኝ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ታድያ ለምን ይህንን ነገር እሰማሃለሁ?» አለና መለሰለት፡፡

እኛን ስለሚወዱንም ሆነ ስለሚጠሉን፡፡ ስለሚያከብሩንም ሆነ ስለሚንቁን፡ ስለምናውቃቸውም ሆነ ስለማናውቃቸው ሰዎች በየጨዋታችን መካከል ይነሣል፡፡ «አንተ እገሌን ታውቀዋለህ? ያ እንኳን እንዲህና እንዲያ ያደረገው፣ ወንድሙ እንደዚህ እኅቱ እንኳን እንዲህ የሆነችው፡፡ በቀደም ዕለት እንኳን እንዲህ ቦታ ያየነው፤ ባለፈው እንኳን እገሌ የነገረን፤ ያ እዚያ መሥሪያ ቤት ያገኘነው» እየተባለ ይነገራል፤ ይተነተናል፡፡ ከቻልን «እ ዐወቅኩት» ብለን እናረጋግጣለን፡፡ ካልቻልንም «እሺ ግዴለም እስኪ ንገረኝ» ብለን ወሬውን እናስኬደዋለን፡፡

ከዚያስ? ከዚያ በኋላማ ሰውዬው እንደ ቄራ ሥጋ ይበለታል፤ እንደ ትንታኔ ዜና ይወራረዳል፤ እንደ ጠቅላላ ሕክምና ሙሉ ምርመራ ይሠራለታል፤ አንዳንዴም ይወገዛል፡፡ ይፈረድበታል፡፡ ይታማል፡፡ ይቦጨቃል፡፡

ደግሞም ስለ ሰው መመርመር፣ ማጣራት፣ መረጃ መሰብሰብ ደስ የሚላቸው፡፡ የዕውቀታቸውን ጣራ ባወቋቸው ሰዎች መጠን የሚለኩም አሉ፡፡ ሰውዬው የማያውቀውን ዝምድና የሚያውቁለት፣ ሰውዬውም የረሳውን አጋጣሚ የሚያስታውሱለት፣ ሰውዬው የተወውንም የሚያነሡለት  «የወሬ ዳታ ቤዝ» ያላቸው አሉላችሁ፡፡ «እገሌን እርሱንማ ዐውቅልሃለሁ፤ እገሊትን የርሷን ነገር ለእኔ ተውት፤ እንዲህ ያለችው ናት አይደል? እዚህ የምትሠራው፣ እዚያ የምትኖረው፣ እንዲህ የምትበላው፣ እንዲያ የምትጠጣው» እያሉ የጫማ ቁጥር ሳይቀር የሚተነትኑ ሞልተውላችኋል፡፡ 

እያንዳንዱ ሰው መቅደስ ነው፡፡ መቅደስ ሦስት ዓይነት ክፍሎች ነበሯት፡፡ የመጀመርያው የውጩ ክፍል ነው፡፡ አደባባዩ፣ የሚያምነውም የማያምነውም የሚገባበት፡፡ ሁለተኛው ቤተ መቅደሱ ነው፡፡ ያመኑ ለአገልግሎት ብቻ የሚገቡበት፡፡ ሦስተኛው ክፍል ግን ካህናቱና ፈጣሪያቸው የሚገቡበት ነው፡፡ የሰውም ሕይወት እንዲሁ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሊገባበት የሚችለው ክፍል አለው፡፡ የሚታየው፣ የሚገለጠው፣ የሚነበበው ሕይወቱ እንዲህ ያለ ነው፡፡ እንደገናም የተወሰኑ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ፣ ዘመዶቹ፣ ብቻ የሚገቡበት ክፍልም አለው፡፡ ደግሞም ማንም የማይገባበት ክፍልም አለው፡፡ እርሱ እና ፈጣሪው ብቻ የሚገቡበት፡፡ 

እዚያ የሰው ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ እርሱም የፈለገውን ሁሉ ማስገባት የለበትም፤ ሌላውም እየዘለለ መግባት የለበትም፡፡ በሩ ተከፍቶ ቢያገኘው እንኳን መግባት ክልክል መሆኑን ግን መረዳት አለበት፡፡ አንዳንዴ ግን እኛም ወደ ሰዎች መቅደስ እንገባለን፤ ሰዎችም ወደ ለእኛ መቅደስ እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡

እንዲህ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ሊቅ እንዲቆጥሩ፣ እንኳን የተከፈተ መቅደስ አግኝተው በተዘጋውም እየሰበሩ እንዲገቡ፣ የሰውን ውሳጤ ማወቅ ሱሳቸው እንዲሆን፣ ያወቁትንም ሁሉ በያገኙበት እንዲዘረግፉ፣ ዘርግፈውም ለዘርጋፊ እንዲሰጡ የምንተባበራቸውም እኛ ነን፡፡ ሰሚና አድናቂ ካላገኘ ማንም አይናገርም፡፡ 

አንዳንዶቻችን እንዲያውም «ወዳጅህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ» የሚለውን ሁሉ ረስተን የምናውቃቸውም ሆነ የማናውቃቸው ሰዎች ሲበለቱ ነገሩን እየጠላነው፣ ሰውዬውንም እየታዘብነው እንኳን ዝም ብለን እንሰማቸዋለን፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ሰሚ ከማግኘታቸውና አድናቂም ከመፍጠራቸው የተነሳ ከዋናው ሂሳብ ይልቅ ቫቱን እያበዘዙ፣ የፈለጉትንም እየጨማመሩ ወደማውራት ደረጃ ተሸጋግረዋል፡፡

አንድ ያልተረዳነው ነገር ቢኖር ዛሬ እኛ የሌሎችን ጉዳይ ያለ ሰዎቹ ፈቃድ እንደ ሰማነው ሁሉ የእኛም ጉዳይ ሌላ ቦታ ይዘረዘራል፡፡ እኛ ወደ ሌሎች መቅደሶች የሚገቡትን 'ሃይ' ሳንል እንደተውናቸው ሁሉ ወደ እኛም መቅደስ ሲገባ 'ሃይ' የሚል አይኖርም፡፡ አንዳንዴ ስለምንጠላቸው ሰዎች መጥፎ ዕድልና ውድቀት የሚነግሩንን ሰዎች «ይበለው፣ ተወው» እያልን እኛ የምንተዋቸውን ያህል እዚያኛውም መንደር ሄደው ይህንኑ ዕድል ሊያገኙ እንደሚችሉ መርሳት የለብንም፡፡

ለዚህ ነው ሶቅራጥስ ሦስቱን ጥያቄዎች የጠየቀው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ የሶቅራጥስ ብቻ ሳይሆኑ የእኛም ጥያቄዎች መሆን አለባቸው፡፡ 

ሰዎች የሌሎችን ሰዎች ጉዳይ ይዘው እኛ ጋር ሲመጡ እንደ ሶቅራጥስ ሁሉ ነገሩ እውነት ነው ወይ? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ የምናምነው ሰው ሊያወራው ይችል ይሆናል፤ ትልቅ የምንለው ሰው ያወራው ይሆናል፤ ልንናገረው የማንችል ሰው ያወራው ይሆናል፤ እጅግ በጣም የሚቀርበን ሰው ያወራው ይሆናል፤ ግን የእውነታ ጥያቄ መጠየቅ አለበት፡፡ ምን ማረጋገጫ አለ? ዜናው የተገኘበት ምንጭ ታማኝ ነወይ?  እየተባለ መጠየቅ አለበት፡፡ የሚታመን ሰው ሁሉ የሚታመን ወሬ አያወራም፡፡

ስለ ሰው እንዲሁ የሰሙትን ሁሉ የሚያወሩ ሰዎች ሦስት ዓይነት ዐመል አለባቸው፡፡ የቀዳዳ ወንፊትነት፣ የግልብነትና ለእውነት አይጨነቄነት፡፡ አንድ ሰው የሰማውን ነገር ሁሉ የሚያምን፤ ከማመንም አልፎ እንደመጣለት የሚያስተላልፍ ከሆነ አእምሮው ውስጥ ያለው የነገር ማጣርያው ወንፊት ተቀድዶበታል ማለት ነው፡፡ የወንፊቱ መቀደድ ብቻም ሳይሆን ግልብነትንም ይጨምራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በቀላሉ ለማመንም በቀላሉ ለመካድም የሚችሉ፣ ማንም እንደፈለገ ሊቀይራቸው የሚችሉ፣ ስለ አንድ ነገር ጥቂት እንኳን ለማሰብ ዐቅም የሌላቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ለእውነት የማይጨነቁ መሆናቸው ነው፡፡ የሚያወራው ሰው «ምስኪን» መሆኑን፣ የሚወራው ወሬ አስደሳች መሆኑ፣ ለማውራት የሚመች መሆኑን፣ የሰው ቀልብ የሚስብ መሆኑን፣ እነርሱም ሊቀበሉት ቀላል መሆኑን እንጂ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ አንዲት ጋት ጭንቀት የላቸውም፡፡ 

ሁለተኛው ጥያቄ የመልካምነት ጥያቄ ነው፡፡ የምንሰማው ነገር የሰውን ውድቀት፣ ገመና፣ ጉድ፣ ከሆነ ምን ያደርግልናል? ስለ ሰው ክፉ መስማት ሰይጣንን ካልሆነ በቀር የትኛዋን ነፍስ ያስደስታታል? በርግጥ በዓለም ላይ ተወለደ ከሚለው ሞተ፣ ተጋቡ ከሚለው ይልቅ ተፋቱ፣ ተስማሙ ከሚለው ይልቅ ተለያዩ፣ ተፋቀሩ ከሚለው ይልቅ ጦር ተማዘዙ፣ መጡ ከሚለው ይልቅ ከዱ፣ አመኑ ከሚለው ይልቅ ካዱ፣ የሚለው ወሬ የሰዎችን ጆሮ የመግዛት ኃይል አለው፡፡ 

በየዜና ማሠራጫዎችም ከመልካም ዜናዎች ይልቅ የአደጋ፣ የጦርነት፣ የጠብ፣ የሽኩቻ፣ የቅሌት፣ የዝርፊያ ዜናዎች የአድማጮችንና የተመልካቾችን ቀልብ በመሳብ ተወዳዳሪ እንደሌላቸው ይነገራል፡፡ 

ለእኛ ግን ስለ ሰዎች ክፉ ክፉውን መስማት ምን ያደርግልናል? እዚያ የምናየው ክፉ ወይንም መልካም ነገር እኛም ላይ ያለ ነው፡፡ ያ ሰው እጅግ የምንጠላውና ክፉውን ለመስማት የምንጓጓለት ሰው እንኳን ቢሆን የእርሱን ክፉ መስማታችን የእኛን ለክፋት የተጠማ ሰይጣናዊ ጠባይ እንጂ የሰውዬውን ክፉነት አያሳይም፡፡ ሰው በውስጡ ክፉነት ከሌለው በቀር የሰውን ክፉ ነገር ለመስማት አይጓጓም፡፡ ሰው በውስጡ መልካምነት ካለው ነፍሱ መልካምነትን ትጠማለች፡፡ ሰው ግን በውስጡ ክፋት ካለ መላው ሕዋሶቹ ክፋትን ሲጠሙ ይገኛሉ፡፡ የሰውን ክፉ መስማትም ሆነ ለመስማት መጓጓት ከሚሰማው ነገር ይልቅ የሰሚውንና የተናጋሪውን ሰይጣናዊ ማንነት ያሳያል፡፡

የመጨረሻው የሶቅራጥስ ጥያቄ ያ የምንሰማው ነገር በኛ ላይ ምን ይጨምርልናል? ምንስ ይጠቅመናል? ለሕይወታችን የሚበጅ ምን ነገር ይኖረዋል? የሚለውን መመዘኑ ነው፡፡ የሰማነው ሁሉ አይጠቅመንም፣ የሚጠቅምንንም ሁሉ አንሰማም፡፡ አንዳንዱ እንዲያውም ወደ ልቡናችን ገብቶ ሌላ ሥራ የሚፈጥርብን፣ ቂም እንድንቋጥር፣ በማያገባን ጉዳይ ገብተን የማንወጣውን ዋና እንድንዋኝ ያደርገናል፡፡ ሌላ ነገር ልናስብበት፣ ልንሠራበትና ልንፈጥርበት የምንችለውን አእምሮም የሚሻማን ጊዜ አለ፡፡

መስማትና ማዳመጥ ይለያያሉ፡፡ መስማት ድምፆችን ሁሉ ነው፡፡ በአካባቢያችን ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ እነዚህን ድምፆች የመስማት ግዴታ ይኖርብን ይሆናል፡፡ የማዳመጥ ግዴታ ግን የለብንም፡፡ ማዳመጥ ልቡናን መስጠት ነውና፡፡ ሰው በጆሮው ይሰማል፣ በልቡናው ግን ያዳምጣል፡፡ ማዳመጥ ልብን መስጠት፣ ስለ ጉዳዩ ማሰብ፣ ማምሰልሰልና ጉዳዩን ማስቀረት ማለት ነው፡፡ 

የማይጠቅሙንን ወሬዎች እንሰማቸው ይሆናል፡፡ምናልባት ሳንፈልጋቸው እየተነሡ ወደኛ ይመጡ ይሆናል፡፡ ልናዳምጣቸው ግን አይገባም፡፡ 

ከዚህ በተሻለ ደግሞ የወሬ ሱስ ያለባቸው ሁሉ «እገሌኮ..» ብለው ሲጀምሩ ሦስቱን ጥያቄዎች እንጠይቃቸው፡፡ ይህንን ብናደርግ ስለ እርሱ የሚወራበትን ሰው ብቻ ሳይሆን የሚያወሩትንም ሰዎች እንጠቅማቸዋለን፡፡ ሞያ ያላቸው መስሏቸው እንዳይኩራሩ፣ ውዱን ጊዜያቸውንም ስለራሳቸው በማሰብ እንዲያውሉ አግዘናቸዋልና፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በተመሳሳይ ኅትመት ላይ ባታውሉትይመረጣል፡

48 comments:

 1. አንድ ሰው የሰማውን ነገር ሁሉ የሚያምን፤ ከማመንም አልፎ እንደመጣለት የሚያስተላልፍ ከሆነ አእምሮው ውስጥ ያለው የነገር ማጣርያው ወንፊት ተቀድዶበታል ማለት ነው፡፡
  mamush,MN

  ReplyDelete
 2. kal hiwote yasemalen dn daniek

  ReplyDelete
 3. ልብ ይስጠን፡፡

  ReplyDelete
 4. አንዳንዶቻችን እንዲያውም «ወዳጅህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ» የሚለውን ሁሉ ረስተን የምናውቃቸውም ሆነ የማናውቃቸው ሰዎች ሲበለቱ ነገሩን እየጠላነው፣ ሰውዬውንም እየታዘብነው እንኳን ዝም ብለን እንሰማቸዋለን፡፡


  ታላቅ ትምህርት ነው በየቢሮው የሠራተኛውን ብዙውን ጊዜ የሚወስደው ይኸው የግሩፕ ግንጠላ ነውና ለሁላችንም ልቦና ይስጠን

  ReplyDelete
 5. I was expecting you to say something about those
  evil guys (jobirawoch) which aggressively running to damage our church.

  ReplyDelete
  Replies
  1. He will never write about them. Oly his "teret-teret".

   Delete
  2. Why you expect all from him, why don't you struggle by your self. "Dedeboch" and "Jezboch"

   Delete
  3. Really why u 2 are filling bad its better if we r good each other,and he is 1 of the best that we have even if we like it or not,and i expect from people knowledge b/c with out others we oll human are nothing.

   Delete
 6. erasen be"ሦስቱ ማጣርያዎች"kulich adrege ayehut. ewnetim "ስለ ሰው እንዲሁ የሰሙትን ሁሉ የሚያወሩ ሰዎች ሦስት ዓይነት ዐመል አለባቸው፡፡ የቀዳዳ ወንፊትነት፣ የግልብነትና ለእውነት አይጨነቄነት፡፡"

  ReplyDelete
 7. When U keep silent people come to your life when you active people go away from your life
  When You stand with the truth your family will kill you , ..... Finaly I become here and there .... the 3rd room should be close even for My self Life LIfe Life ... you Must Go untill the 1000 rooms to Find The Truth ....

  ReplyDelete
 8. ዳንዬዋ ዛሬ እንደ ጉድ ባወረድከው ንባብ እንግሊዞች ምን ይላሉ መሰለህ

  Doni't judge a person by whay other's say. the person may be true to you but not to others Because the same sun which melts the ice hardnes the clay too!!  ዳንዬዋ ኢትዮጵያዊ በሞሆንህ እድለኛ ነን! የቤተክ ልጅ መሆንህ ደግሞ እድል በእድል ዓደርገናል!

  እኔ የምለው እንዲያው ይህን የማይጠገብ ንባብ እንደ ጉድ ታወርደዋለህ እንደ ጉድ እናነባለን በቃ እንደ ጉድ ደስ ይለኛል!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ዮኒዬ ጉድ ምንድን ነው?

   Delete
 9. ''መስማትና ማዳመጥ ይለያያሉ፡፡ መስማት ድምፆችን ሁሉ ነው፡፡ በአካባቢያችን ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ እነዚህን ድምፆች የመስማት ግዴታ ይኖርብን ይሆናል፡፡ የማዳመጥ ግዴታ ግን የለብንም፡፡ ማዳመጥ ልቡናን መስጠት ነውና፡፡ ሰው በጆሮው ይሰማል፣ በልቡናው ግን ያዳምጣል፡፡ ማዳመጥ ልብን መስጠት፣ ስለ ጉዳዩ ማሰብ፣ ማምሰልሰልና ጉዳዩን ማስቀረት ማለት ነው፡፡'' እጅግ ድንቅ ምልከታ ነው። በተግባር ለመተርጎም ግን ተቸግሬአሉ። እውነቱን ለመናገር ለመስማት ሱስ ሆኖብኝ አይደለም። የአገር ጉዳይ ሁኖብኝ ነው። እሬት እሬት የሚሉ እውነቶች በየ ዜና ማሰራጫው እሰማሉ። ሰምቶ መተው እንዳለብኝ ቃል ብገባም፤ አንዳች ላውቀው በማልችል ሃይል ውስጤ ዘልቆ ይገባል። ሁለተኛ እንዲህ አይነት ዜና አላይም፤አላነብም፤አላደምጥም እልና ተመልሼ እዚያው እገኛለሁ። እንዲህ የሚያደርገኝ፤ በብዙ ችግሮች ከተተበተበች አገር መወለዴ ይመስለኛል። አንድም ጥሩ ነገር አልሰማም። በእርግጥ ስለ አገሪቱ መልካም ገጥታ፤ እድገቷ፤ ስለ ሕዝቧ አኗኗር፤ የሚተርኩ ዜናዎች አሉ! ነገር ግን እጅግ ከእውነት የራቁ በመሆናቸው የበለጠ ያበሳጩኛል። እውነት እንነጋገር ከተባለ፤ በአሁኑ ስዓት ከወደ ኢትዮጵያ የሚሰማ አንዳችም መልካም ዜና የለም። መልካም ነገር የማይወራው አገሪቱ መጥፎ ስለሆነችም አይደለም። ሰቅዘው ሊያጠፋት በተነሱ ሰዎች አማካችነት የሚደርስ ጥፋት እንጂ። እንደ ዜጋ ምንም እንኳ መጥፎ ቢሆን፤ እየመረረንም መስማት፤ማዳመጥ እንዲሁም ውስጠ አይምሮ እስኪዞር መፍትሔ መፈለግ ያለብን ይመስለኛል። እንዲያ ካልሆነ፤ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፤ዜጎቿ እንደ ልብ የሚኖሩትን አገር ማዬት አንችልም። እዚህ ደረጃ የደረሱ አገራትን የዃላ ታሪክ ብንፈትሽ፤ ብዙ መራር የሆነ ወሬዎችን ሰምተዋል፤ አስተናግደዋል። ከሰሙት መካከል መረረኝ፤ አቃረኝ፤ አንገሸገሸኝ ያሉ ልባም ሰዎች ናቸው ግፉንና መከራውን አሽቀንጥረው የጣሉ። እናም ወንድሜ ሆን ቢዘገንነንም መስማት፤ ከዚያም አንዳች መፈየድ ያስፈልገናል። ይሄን ስል፤ የሰፈሩ አውደልዳይ የሚያወራውን ልቦለድ፤ ምናባዊ ድስኩር እየደገፍኩ አይደለም! አገራዊ ወራን እንጂ! ኢትዮጵያን ሰቅዞ ይዞ የሚያስጨንቃትን ወሬ! ሁሉ ነገር አልፎ መልካም ወሬ ለመስማት ያብቃን።

  ReplyDelete
 10. ዳኒ ምነው በዋልድባ ጉዳይ ለምን ዝምታን መረጥክ?

  ReplyDelete
  Replies
  1. Everyone is responsible,not only Dn,Danie

   Delete
  2. Do you forgot as Dani is aprt of every one??????Min ayinet eyanebebe yemayigebaw new ebakachihu... He should not wait untill told by some one.

   Delete
 11. Dani,
  As usual this article is very interesting, informative and well articulated. Keep on ....

  I am a little worried about your silence concerning the 20 year anniversary of MK, the dictator meles categorization of MK as terrorist, of all the situation around MK and the our mother church. "Dagetu lay sew tefa " neber yalut prof Mesfin.
  What ever you do, i know that you have a reason. I am just stating my fear .

  May God be with you !

  ReplyDelete
  Replies
  1. neger bidegagem min yiseral bilo yihonal,i mean every body is talking about the 20th anversery of MK and MK is not "AKRARI"(well kown),the truth is not hidden from the population rather talking about it again and again would be wasting time.

   Delete
 12. Daniye Qale Hiywet yasemalin.
  GB
  Oslo

  ReplyDelete
 13. Thanks Dani as usual!

  For those who push Dani in your way: He is himself, not you. He has to contribute in a way he feels is right or better. He can not and should not address everything. And his silence does not mean anything; he has his own gut feeling.

  We need you Dani to write what you feel is good, not what we want you to write!

  HG

  ReplyDelete
  Replies
  1. good view, yes we need Dani, he is a bottle of knowledge " yemayalik ewiket"

   Delete
 14. Article - Good by itself.
  Timing - There are more important things to discuss at this time.
  Advice - Focus my brother, get back in line.

  ReplyDelete
 15. ዲ/ን ዳኒ እዉነት ብሃል እኔ እራሴ እስካሁን ላሸንፈዉ ያልቻልኩት ስሜቴ በተለይ አስቀይሞኛል ስለምለዉ ሰዉ ክፉ መስማት ያስደስተኛል፡፡ መደሰት እንደሌለብኝ ዉስጤ እየነገረኝ እንኳን ለመደሰት አስባለሁ እና ሁልጊዜ በጸሎቴ እግዚአብሄርን እኔ ስላልቻልኩ እርሱ እንዳሸንፍ እንዲረዳኝ እየለመንኩት አሁን እየተስተካከልኩ ነዉ እናም እንደኔ አይነት ከ ጌታ ጋር የሚያጣላ አይነት መንፈስ ያለባችሁ ተግታችሁ ጸልዩ የሌለባችሁ ደግሞ ለኛ ጸልዩልን ስለሰዉ ክሩ ማሰብ ፍጹም ፍቅር ከሆነዉ አምላካችን የሚያርቅ ነዉና፡፡ መምህር አንተንም ሁልጊዜ በምታስነብባቸዉ ነገሮች ምን ያክል ሃጢያተኛ እንደሆንኩ ስለምታሳስበኝ አመሰግንሃለሁ ባንተ አድሮ የሚናገረኝ እግዚብሄርም ፍቅር ሁልጊዜ ያስገርመኛል፡፡

  ReplyDelete
 16. Kale Hiwot Yasemalen! Lehulachenem Asteway Libuna Yadelen.

  ReplyDelete
 17. ዳኒ እንዲህ እማ ልክልካችን ንገረን

  ReplyDelete
 18. it is very intersting issue specially for habeshea it doesnt want to investiget the truth but,only belive what people say .

  ReplyDelete
 19. ውድ ወንድሜ፤-አሁንም እንደ ከዚህ በቀደሙ አድናቆቴ ከፍተኛ ነው። ፍሬ ነገሩ እንዳለ ሆኖ የማልስማማበት ነጥብ አለኝ። የማይጠቅሙ ወሬዎች ማዳመጥ እንደማይገባን የሰነዘርኸው ሃሳብ ለእኔ አልተዋጠልኝም። የሰው ልጅ የሚጠቅመውን ብቻ መስማት የለበትም። የሚሰማው፤የሚያየው፤ እንዲሁም የሚያከናውነው ነገር ለእራሱ የሚጠቅም መሆኑን ብቻ የሚያይ ከሆነ፤ ለእኔ ስግብግብነት ነው። ያ ወሬ ለሰሚው ባይጠቅመው፤ አልፎ ተርፎም በገንዘብም ሆነ አካላዊ ጉዳት የሚያደርስበት ቢሆንም፤ እሱ እራሱ ተጎድቶ ሌላውን ከአለት ነገር መታደግ ከቻለ፤ ለእኔ ይህ ድርጊት የሞራሉን ልዕልና የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ አንድ ጓደኛችን፤ ችግር ላይ ነው እንበል። የሕይወቱን ዋጋ የሚያስከፍል ችግር። ስለዚህ ሰው የተደቀነበት አደጋ፤ ለእኛ አንዳች ጥቅም የለውም እንበል። በተቃራኒው አደጋውን ለማስቀረት መሞከር በራሱ የእኛን ገንዘብና ጊዜ ሊበላ ይችላል እንበል። ነገር ግን በመስማታችን የገንዘብና የጊዜ ዋጋ ከፍለን ያን ሰው ሕይወቱን ማትረፍ እንችላለን። ይህ ውሳጣዉ ረፍትን ይሰጣል። የሰውየውን በሕይወት የመኖር እድል ተካፋይ መሆን ታላቅነት ነው።

  ውድ ወንድሜ ይዘኸው እንደተነሳኸው አሳብ ከሆነ እንዲህ አይነት ወርቃማ አጋጣሚዎችን ልናጣ እንችላለን። እንደ እኔ አመለካከት፤ የምሰማው ወሬ ለእኔ ወይም ለተወራበት ሰው አንዳች ጥቅም ያመጣል ወይ በሚል ቢሰተካከል እመርጣለሁ። አለበለዚያ አለም አሁን እንደምናያት የለከት የለሾች፤ የስግብግቦች መፈኝጫ ትሆናለች።

  ይሄን ሃሳቤን ስዘነዝር፤ እንዲህ መሆን ነው ያለበት ብዬ እንዳስብ ለኳሽ ለሆነው መጣጥፍህ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እይታህ በኢትዮጵያ ሁሉም ስፍራ መነጋገሪያ፤ መመማሪያ፤ የወጎቻችን ማጣቀሻ የሚሆንበትንም ጊዜ እናፍቃለሁ። እሩቅ እንደማይሆንም አምናለሁ።

  ReplyDelete
  Replies
  1. በላይ ልክ ነህ ነገር ግን ጥቅም እኮ ግላዊ ብቻ አይደለም፡፡እንደኔ ጥቅም ጠቅሞ የሚጠቅም ፣የህሊና እርካታም እኮ ጥቅም ነው፡፡ ሰው ደግሞ በሚስራት በጎ ነገር ይደሰታል፣ይረካል፡፡ አለበለዘያማ አነተም እንዳልከው "እኔ ከሞትኩ….." ነው የሚሆነው፡፡ስለዚህ ምን ይጠቅመኛል ማለት ለህሊናዬ ምን በጎ ነገር ያመጣል ማለት ነው፡፡በጎ ነገር በጎ ማሰብ መልካም መስራት ነው፡፡ ባጭሩ ዳኒ ለመግለጽ የፈለገው ሞራላዊ ጠቀሜታውን ይመስለኛል፡፡ጥቅም ዓይነቱ ብዙ ቢሆንም ሞራላዊ ጥቅም ግን ከሁሉም በላይ ነውና፡፡ስለዚህ እኔ ሶቅራጥስ የጠየቀው ዳኒም ያብራራው ጥቅም ከቁሳዊ እና አካላዊ ጥቅሞች የሚበልጠውን ከሞራል ደስታ የሚገኘውን ጠቀሜታ ነው ባይ ነኝ፡፡
   ለማናኛውም ዳኒ በመጻፍ አንተም አንብበህ ሐሳብ በመስጠት በርቱ፡፡

   Delete
  2. "እንደ እኔ አመለካከት፤ የምሰማው ወሬ ለእኔ ወይም ለተወራበት ሰው አንዳች ጥቅም ያመጣል ወይ በሚል ቢሰተካከል እመርጣለሁ::" I don't agree with you because what benefits your brother when you help him is categorized as some thing that is good for you because you are fulfilling one of the great commandments: love your neighbor as your self.

   Delete
 20. ወንድም በላይ ሃሳብህን ወድጀዋለሁ ነገር ግን የ ዲ/ን ዳንኤል ሃሳብ እኔ እንደተረዳሁት ከሆነ ስለሰዉ ክፉ ማዉራትን የሚቃወም እንጂ ተጎድቶ እርዳታን ስለሚሻ ሰዉ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄዎቹን ሳጤናቸዉ ስለ ወዳጅህ ያልተረጋገጠ፤ መልካም ያልሆነ(ስለሱ ክፉ) እንዲሁም የማይጠቅም ወሬን መስማት ምንም አይጠቅምም ወደሚል መልስ ወስዶኛል ይህ ማለት ግን ስለወዳጅህ መታመም፣መራብ፤ መታረዝ መስማትን አይደለም የማይጠቅም ወሬ የተባለዉ ይልቁንስ በተቃራኒዉ ያላደረገዉን ያልሰራዉን ያልሆነዉን ስለሰዉ ክፉ ማዉራትና በዚያም መደሰትን ነዉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነቱን ነገር ከመስማት ብንቆጠብ የተሻለ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ ምክንያቱም ህሊናን ከማቆሽሽ የዘለለ ጥቅም ስለማይኖረዉ፡፡ ዲ/ን ዳንኤልም ወንድም በላይም ስላነሳችሁት ገንቢ ሃሳብ እግዚአብሄር ይባርካችሁ፡፡

  ReplyDelete
 21. የሰው ልጅ ሦስት ሕይወት አለው፡-
  ሀ. በእግዚአብሔር ጸጋ የሆነው መንፈሳዊ ሕይወት
  ለ. ከነፍስ የተነሣ የሆነው ሥጋዊ ሕይወት
  ሐ. በመልካም ስም ላይ የሚመሠረተው ማኅበራዊ ሕይወት

  የመጀመሪያውን (በእግዚአብሔር ጸጋ የምናገኘውን መንፈሳዊ ሕይወት) ኃጢአት ከእኛ ትወስድብናለች፤ ሁለተኛውን (ነፍሳችንን) ሞት ይነጥቀናል፤ ሦስተኛውን (በመልካም ስም ላይ የሚመሠረተውን ማኅበራዊ ሕይወት) ሐሜት ይገፍፈናል፡፡ ሐሜት ግድያ የሚሆነውም በዚህም የተነሣ ነው፡፡

  ሐሜተኛ በአንዲት የምላስ ስንዘራ ሦስት ግድያዎችን ይፈጽማል፡፡ በቅድሚያ የራሱንና የሰሚውን ነፍሶች በመንፈሳዊ ግድያ ከጸጋ እግዚአብሔር ያርቃል፡፡ ቀጥሎም የሚታማውን ሰው ማኅበራዊ ሕይወት ይገድላል፡፡

  ቅዱስ በርናርዶስ “ሐሜተኛ በምላሱ ላይ፣ ሐሜት አድማጩ ደግሞ ጆሮው ውስጥ ሰይጣን አለባቸው፡፡” ይላል፡፡ ዳዊትም ሐሜተኛን አስመልክቶ “ምላሳቸውን እንደ እባብ አሰሉ፡፡” (መዝ 141፡ 3) ይላል፡፡ አሪስጣጣሊስ ደግሞ “የሐሜተኛ ምላስ እንደእባብ ምላስ ጫፉ መንታ ነው በአንዱ የሰሚውን ጆሮዎች በሌላኛውም ጫፍ የሚታማውን ሰው ስም ይመርዛልና፡፡” ማለቱ ይጠቀስለታል፡፡

  ስለሆነም የእግዚአብሔር ወዳጅ ሆይ አንቺ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለሰዎች ክፉ እንዳትናገሪ፡፡ ጎረቤትሽ ያላደረገውን ኃጢኣትም እንዳትጭኚበት፣ ምሥጢር የሆኑትን ስሕተቶቹንም የግድና አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር እንዳታወጪበት፣ የሚታወቁትንም እንዳታጋንኚበት ተጠንቀቂ፡፡ መልካም ሥራውን በክፉ እንዳትተረጉሚ፤ የምታውቂውን በጎ ጎኑንም እንዳትክጂ፡፡ በክፋት ወይም በቃላት እንዳታንኳስሺው፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ ሁሉ መንገዶች በተለይም ደግሞ በሐሰት በመክሰስና እውነትን ሸፍጠሽ ጎረቤትሽን በማንኳሰስ እግዚአብሔርን በእጅጉ ታስቀይሚዋለሽና፡፡

  አንዳንድ ከሁሉም የባሱ ረቂቅና መርዘኛ ተቺዎች ደግሞ ሐሜታቸውን በአክብሮት ወይም በሙገሳ ይጀምራሉ፤ ወይም ቀልዶችን ጣል ጣል ያደርጉበታል፡፡ “እርግጥ ነው እወደዋለሁ” ወይም “እርግጥ ነው ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን እውነቱ መነገር አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት ስሕተት ተሳስቷል፡፡” “በጣም መልካም ሴት ነበረች፤ እንደው በትንሽ ነገር ተሳሳተች፡፡” ይላሉ፡፡ ዘዴያቸውን ትመለከቻለሽ? ቀስትን አርቆ ለመወርወር የሚሻ ሰው ፍላጻውን በተቻለው መጠን ወደራሱ ይስበዋል፡፡ ዓላማው ግን ቀስቱን ላቅ ባለ ኃይል ርቆ እንዲጓዝ ማስቻል ነው፡፡ እነኚህ ተቺዎችም ሐሜታቸውን ወደራሳቸው የሚያቀርቡት ይመስላሉ ዓላማቸው ግን የአድማጮቻቸውን ልብ በኃይል በስቶ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡

  Source:- Introduction to the Devout Life by St. Francis de Sales

  ReplyDelete
 22. ሰው በውስጡ
  ክፉነት ከሌለው በቀር የሰውን ክፉ ነገር ለመስማት አይጓጓም!!!ሰው በጆሮው ይሰማል፣ በልቡናው ግን ያዳምጣል፡፡ ማዳመጥ ልብን መስጠት፣ ስለ ጉዳዩ ማሰብ፣
  ማምሰልሰልና ጉዳዩን ማስቀረት ማለት ነው፡፡ማሰተዋልን ያደለን ጌታ!!!!

  ReplyDelete
 23. welde senbet DallasMay 13, 2012 at 6:54 PM

  First of all I need to appreciate your views. they are very influencial towards the communities as well as the country as a whole.
  Even if you may have your own reason,you are not stating about walidiba,about the
  anniversary of Mahibere kidusan,the jobirawoch letters,and yekidus sinodos sibseba ena chigirochu....
  minew eyitah enezihin alakatetem....Iknow how much you contribute during ziquala gedam katelo.kezia belay yehone yemiakatil guday bebetekiristianachin eyale minew eyitah erake.
  new antem ewunetin mesheshih new.....eyitawochih hulunim yemimeleketu bihon......your little brother dani.
  Just I recoomend you what I feel after I read your tumera here above.

  ReplyDelete
 24. ዳኒ ምነው በዋልድባ ጉዳይ ለምን ዝምታን መረጥክ?

  Difretna Eminet Silata

  ReplyDelete
 25. Since it has negative connotation, better to replace «የወሬ ዳታ ቤዝ» by "Ye'Worie Qwat".

  ReplyDelete
 26. ሰላም ዳኒ፣ መቼም የምትጽፋቸውን ጽሁፎች የህይወቱ መመሪያ ያደረገ ሰው መቼም ሌላ ምንም ተጨማሪ ምክር አያስፈልገውም፡፡ እስቲ ሁላችንም ከአሁን በኃላ እነዚህን ሦስት ጥያቄዎች ወሬ ይዘውልን ለሚመጡ ሰዎች እንጠይቅ። ያን ማድረግ እንኳን ቢከብደን ወሬያቸውን እናስቀይር። አንባቢዎች ያስማማናል አይደል? እንግዲህ አንድ ብለን እንጀምርና የደረስንበትን እንወያይበት።
  አዜብ ዘሚኒሶታ

  ReplyDelete
 27. ሦስቱ ማጣሪዎች አልካቸው ምን ማጣሪያ ጦርነቶች ቢባሉ ይሻላቸዋል ነው የምለው ከወሬ ምንም ላይገኝ አውርተን ምንም ላናተርፍ እያወቅነው እናወራለን በእውነት ነው የምልህ አንዳንዴ ሳስበው ሱስ ሆኖብን ሳይሆን አይቀር ብዪ እፈራሉ ስለዚህ ሁል ግዚ የአንተን ጽኁፍ ሳነብ በጣም እገረማለሁ የውስጤን ሰለሚነግረኝ አስተምህሮ ለእንደኔ አይነቱ ላልተማረው እጅግ ጠቃሚ ነው ራሴን እንዳይበት ያደርገኛል ሁልግዚ በምሰራው ሰራ ተስፋ እቆርጣለሁ የአንተን ጽሁፍ ሳነብ ግን
  ትእግሰት እንዲኖረኝ ተስፋ እንደልቆርጥ ያደርገኛል አንደዋዛ የምታስተምረው ትምህርት ቀላል እንዳይመስል አንደንዴም እቀናብሀለው እግዚአብሔር በሰጠህ ጸጋ እግዚአብሔር የበለጠ ጸጋውን ያብዛልህ እኛንም የተማርነውን ፍሬ እንድንፈራ ያደረርገን፤፤

  ReplyDelete
 28. ለእኛ ግን ስለ ሰዎች ክፉ ክፉውን መስማት ምን ያደርግልናል? እዚያ የምናየው ክፉ ወይንም መልካም ነገር እኛም ላይ ያለ ነው፡፡ ያ ሰው እጅግ የምንጠላውና ክፉውን ለመስማት የምንጓጓለት ሰው እንኳን ቢሆን የእርሱን ክፉ መስማታችን የእኛን ለክፋት የተጠማ ሰይጣናዊ ጠባይ እንጂ የሰውዬውን ክፉነት አያሳይም፡፡ ሰው በውስጡ ክፉነት ከሌለው በቀር የሰውን ክፉ ነገር ለመስማት አይጓጓም፡፡ ሰው በውስጡ መልካምነት ካለው ነፍሱ መልካምነትን ትጠማለች፡፡ ሰው ግን በውስጡ ክፋት ካለ መላው ሕዋሶቹ ክፋትን ሲጠሙ ይገኛሉ፡፡ የሰውን ክፉ መስማትም ሆነ ለመስማት መጓጓት ከሚሰማው ነገር ይልቅ የሰሚውንና የተናጋሪውን ሰይጣናዊ ማንነት ያሳያል፡፡
  kale Hiwot Yasemaln!!!

  ReplyDelete
 29. ለራሴ የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም መስማት አለብኝ፣ምናልባት እኔ ሰምቸው ለሰውየው ችግር የምደረስ ከሆነ፡፡

  ReplyDelete
 30. "የምናምነው ሰው ሊያወራው ይችል ይሆናል፤ ትልቅ የምንለው ሰው ያወራው ይሆናል፤ ልንናገረው የማንችል ሰው ያወራው ይሆናል፤ እጅግ በጣም የሚቀርበን ሰው ያወራው ይሆናል፤ ግን የእውነታ ጥያቄ መጠየቅ አለበት፡፡ ምን ማረጋገጫ አለ? ዜናው የተገኘበት ምንጭ ታማኝ ነወይ? እየተባለ መጠየቅ አለበት፡፡ የሚታመን ሰው ሁሉ የሚታመን ወሬ አያወራም፡፡"

  ይህ በእውነቱ ትልቅ አባባል ነው፡፡ ሁላችንም ልንማርበት ይገባል፡፡ ብዙ ጊዜ የምናውቃቸው ሰዎች ይልቁንም በክርስቲያናዊ ህይዎታቸው ከፍ ያሉ ናቸው ያልናቸው ሰዎች ሲናገሩ እንደወረደ እናዳምጣቸዋለን፡፡ መረጃ አንጠይቃቸውም እኛም ባገኘነው አጋጣሚ እንደ ገደል ማሚቶ ሳያዙን በደረስንበት ሁሉ እናዳርሰዋለን፡፡ በጣም ትልቅ መልክት ነው በልቦናችን ያሳድርብን የህይዎታችን መመሪያ እንዲሆንልን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

  ReplyDelete
 31. ዳኒ ምነው በዋልድባ ጉዳይ ለምን ዝምታን መረጥክ?መልሱን እኔው ተራ ምእመን ልመልሰው: በእርግጠኝነት ጌታ ችግሩን ስለሜፈታው ለዳኒም ሆነ ለአባቶች ዝምታን እንዲመርጡ አደርጓል መልሱ ይኋው ነው::ሁሉ በሱ: ሁሉ ከሱ: እንደሆን ብቻ እመኑ::ጾለትን አናቋርጥ::አሜን!

  ReplyDelete
 32. ለእኛ ግን ስለ ሰዎች ክፉ ክፉውን መስማት ምን ያደርግልናል? እዚያ የምናየው ክፉ ወይንም መልካም ነገር እኛም ላይ ያለ ነው፡፡ ያ ሰው እጅግ የምንጠላውና ክፉውን ለመስማት የምንጓጓለት ሰው እንኳን ቢሆን የእርሱን ክፉ መስማታችን የእኛን ለክፋት የተጠማ ሰይጣናዊ ጠባይ እንጂ የሰውዬውን ክፉነት አያሳይም፡፡ ሰው በውስጡ ክፉነት ከሌለው በቀር የሰውን ክፉ ነገር ለመስማት አይጓጓም፡፡ ሰው በውስጡ መልካምነት ካለው ነፍሱ መልካምነትን ትጠማለች፡፡ ሰው ግን በውስጡ ክፋት ካለ መላው ሕዋሶቹ ክፋትን ሲጠሙ ይገኛሉ፡፡ የሰውን ክፉ መስማትም ሆነ ለመስማት መጓጓት ከሚሰማው ነገር ይልቅ የሰሚውንና የተናጋሪውን ሰይጣናዊ ማንነት ያሳያል፡፡

  ReplyDelete
 33. አንድ ያልተረዳነው ነገር ቢኖር ዛሬ እኛ የሌሎችን ጉዳይ ያለ ሰዎቹ ፈቃድ እንደ ሰማነው ሁሉ የእኛም ጉዳይ ሌላ ቦታ ይዘረዘራል፡፡ እኛ ወደ ሌሎች መቅደሶች የሚገቡትን 'ሃይ' ሳንል እንደተውናቸው ሁሉ ወደ እኛም መቅደስ ሲገባ 'ሃይ' የሚል አይኖርም፡፡ አንዳንዴ ስለምንጠላቸው ሰዎች መጥፎ ዕድልና ውድቀት የሚነግሩንን ሰዎች «ይበለው፣ ተወው» እያልን እኛ የምንተዋቸውን ያህል እዚያኛውም መንደር ሄደው ይህንኑ ዕድል ሊያገኙ እንደሚችሉ መርሳት የለብንም፡፡

  ReplyDelete
 34. በእርግጥ ስለ አገሪቱ መልካም ገጥታ፤ እድገቷ፤ ስለ ሕዝቧ አኗኗር፤ የሚተርኩ ዜናዎች አሉ! ነገር ግን እጅግ ከእውነት የራቁ በመሆናቸው የበለጠ ያበሳጩኛል። እውነት እንነጋገር ከተባለ፤ በአሁኑ ስዓት ከወደ ኢትዮጵያ የሚሰማ አንዳችም መልካም ዜና የለም። መልካም ነገር የማይወራው አገሪቱ መጥፎ ስለሆነችም አይደለም። ሰቅዘው ሊያጠፋት በተነሱ ሰዎች አማካችነት የሚደርስ ጥፋት እንጂ። እንደ ዜጋ ምንም እንኳ መጥፎ ቢሆን፤ እየመረረንም መስማት፤ማዳመጥ እንዲሁም ውስጠ አይምሮ እስኪዞር መፍትሔ መፈለግ ያለብን ይመስለኛል። እንዲያ ካልሆነ፤ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፤ዜጎቿ እንደ ልብ የሚኖሩትን አገር ማዬት አንችልም።

  ReplyDelete
 35. አንዳንድ ከሁሉም የባሱ ረቂቅና መርዘኛ ተቺዎች ደግሞ ሐሜታቸውን በአክብሮት ወይም በሙገሳ ይጀምራሉ፤ ወይም ቀልዶችን ጣል ጣል ያደርጉበታል፡፡ “እርግጥ ነው እወደዋለሁ” ወይም “እርግጥ ነው ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን እውነቱ መነገር አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት ስሕተት ተሳስቷል፡፡” “በጣም መልካም ሴት ነበረች፤ እንደው በትንሽ ነገር ተሳሳተች፡፡” ይላሉ፡፡ ዘዴያቸውን ትመለከቻለሽ? ቀስትን አርቆ ለመወርወር የሚሻ ሰው ፍላጻውን በተቻለው መጠን ወደራሱ ይስበዋል፡፡ ዓላማው ግን ቀስቱን ላቅ ባለ ኃይል ርቆ እንዲጓዝ ማስቻል ነው፡፡ እነኚህ ተቺዎችም ሐሜታቸውን ወደራሳቸው የሚያቀርቡት ይመስላሉ ዓላማቸው ግን የአድማጮቻቸውን ልብ በኃይል በስቶ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ዳኒ ምነው በዋልድባ ጉዳይ ለምን ዝምታን መረጥክ?መልሱን እኔው ተራ ምእመን ልመልሰው: በእርግጠኝነት ጌታ ችግሩን ስለሜፈታው ለዳኒም ሆነ ለአባቶች ዝምታን እንዲመርጡ አደርጓል መልሱ ይኋው ነው::ሁሉ በሱ: ሁሉ ከሱ: እንደሆን ብቻ እመኑ::ጾለትን አናቋርጥ::አሜን!በላይ ልክ ነህ ነገር ግን ጥቅም እኮ ግላዊ ብቻ አይደለም፡፡እንደኔ ጥቅም ጠቅሞ የሚጠቅም ፣የህሊና እርካታም እኮ ጥቅም ነው፡፡ ሰው ደግሞ በሚስራት በጎ ነገር ይደሰታል፣ይረካል፡፡ አለበለዘያማ አነተም እንዳልከው "እኔ ከሞትኩ….." ነው የሚሆነው፡፡ስለዚህ ምን ይጠቅመኛል ማለት ለህሊናዬ ምን በጎ ነገር ያመጣል ማለት ነው፡፡በጎ ነገር በጎ ማሰብ መልካም መስራት ነው፡፡ ባጭሩ ዳኒ ለመግለጽ የፈለገው ሞራላዊ ጠቀሜታውን ይመስለኛል፡፡ጥቅም ዓይነቱ ብዙ ቢሆንም ሞራላዊ ጥቅም ግን ከሁሉም በላይ ነውና፡፡ስለዚህ እኔ ሶቅራጥስ የጠየቀው ዳኒም ያብራራው ጥቅም ከቁሳዊ እና አካላዊ ጥቅሞች የሚበልጠውን ከሞራል ደስታ የሚገኘውን ጠቀሜታ ነው ባይ ነኝ፡፡
  ለማናኛውም ዳኒ በመጻፍ አንተም አንብበህ ሐሳብ በመስጠት በርቱ፡፡

  ReplyDelete
 36. Thank u Dani! In a time of like this, where moral teachers are badly needed but virtually non-existent, you are there for us. I'am proud to have your works so that I can give my daughter to read them and become a good citizen. Barekellahufik (May God bless U).

  ReplyDelete