Tuesday, May 29, 2012

ስኳር

clik here for pdf 
አንድ መምህር ሁለት ትልልቅ የመስተዋት ገንቦዎች ይዞ ወደ ክፍል መጣ፡፡ ሦስት ተማሪዎች ደግሞ በካርቶን ሌሎች ሦስት ነገሮችን ተሸክመውለታል፡፡ ተማሪዎቹ ከመቀመጫ ተነሥተው ተቀበሉት፡፡
መምህሩ ትልልቁን የመስተዋት ገንቦዎች በተማሪዎቹ ፊት ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠው፡፡ ሦስቱን ካርቶኖቹን ደግሞ በጎን አደረጋቸው፡፡ መጀመርያ ትልልቅ ድንጋዮች አነሳና በአንደኛው የመስተዋት ገንቦ ውስጥ እስካፉ ድረስ ከተታቸው፡፡ ከዚያም ተማሪዎቹን አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡

Friday, May 25, 2012

118ኛው የግብጽ ፓትርያርክ

 

117ኛው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ታላቁ አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 3 ሲያርፉ ዓለም በሙሉ ነበር ኀዘኑን የገለጠው፡፡ ክርስቲያኑና ሙስሊሙ፣ ቡድሂስቱና ሺንቶይስቱ፣ የሚያምነውና የማያምነው፣ የቻይናና የአሜሪካ ፖለቲከኞች፣ አንድ ሆነው በአቡነ ሺኖዳ ዕረፍት አዝነው ነበር፡፡
Coptic patriarchs
የእርሳቸውን ዕረፍት ተከትሎም የግብጽ ቤተ ክርሰቲያን እንዲህ ዓለምን በፍቅር አንድ አድርገው የሚገዙ ሌላ አባት ታገኝ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ግብጻውያን ምእመናንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ያሳሰበ ነበር፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ዝግጅቷን ጀምአመራረጥ ራለች፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአዲስ ፓትርያርክ ሥርዓት እጅግ የሚያስደስት፣ ለክርክርና ለሐሜት በር የሚዘጋ፣ አባቶችንና ምእመ ናንን የሚያሳትፍ፤ መንፈሳዊነቱንም የተሞላ ነው፡፡

Tuesday, May 22, 2012

ርኅራኄያዊ ግድያ

ባለፈው ጊዜ ዱባይ እያለሁ ነው ይህንን ታሪክ አንዲት እኅት የነገረችኝ፡፡ ከአራት ዓመታት በላይ እዚያ ሠርታለች፡፡ ያገኘችውን ወደ ሀገር ቤት ትልካለች፡፡ ልብሱ፣ የቤት ዕቃው፣ ገንዘቡ፣ ጌጡ፣ ሽቱው አይቀራትም፡፡ መላክ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከጓደኞቿ ጋር ተባብራ ካርጎ ትጭናለች፡፡
እናቷ ደውለው «ከጎረቤትኮ እገሌ ታምሞ መታከሚያ አጣ» ይሏታል ተልካለች፡፡ ወንድሟ «እንዲህ ላደርግ ነበር ገንዘብ አጣሁ» ይላል ትልካለች፡፡ «እገሌ የተባለ ዘመድሽ ምነው ረሳችኝ ብሎሻል» ትባላለች ትልካለች፡፡ አንዳንዴም «እንዴው ለዚህ ቤተ ክርስቲያን ቃል ገብተን ነበረ» ይሏታል ትልካለች፡፡ ብቻ ከራሷ በስተቀር ሁሉንም ልካለች፡፡
የኤምሬትስ ስደት ሲሞላ ሲጎድል ነው፡፡ ቪዛዋ ይሠረዝባታል፡፡ ሰሞን ደግሞ ፖሊሶቹ ተነሥቶባቸው ከየመንገዱ እያፈሱ ወደ ሀገር ቤት ሰውን መላክ ጀምረው ነበር፡፡ አንዳንዴም አበሻ አለበት በሚባለው ሠፈር ፍተሻ ያደርጉ ነበር፡፡ እየተደበቁ መኖሩ ሰለቻት፡፡ መሰልቸት ብቻ ሳይሆን ለብዙ ጊዜ መደበቁ ሥራ እንዳትሠራም አደረጋት፡፡ እጇም እያጠረ መጣ፡፡

Thursday, May 17, 2012

«ካህናተ ደብተራ»

«እናንተ ደብተራ ከምትባሉት በቀር ይህንን ሁሉ ያደረገ ማነው? ታመሰግኑታላችሁ፣ ታወድሱታላችሁ፣ እንዳንተ ያለ ኀያል ማነው? ትሉታላችሁ፤ እንዳንተ ያለ ድል አድራጊ፣ እንዳንተስ ያለ ለጋሥ በሁሉ ዘንድ ወዴት አለ? እንዳንተ ያለስ ምጽዋት ሰጭ የት አለ? ትሉታላችሁ፡፡ እንዲህ ስታመሰግኑትም በኀጢአት ላይ ኀጢአትን ይጨምራል፡፡»
ይህንን ቃል ከዛሬ ሰባት መቶ ዓመታት በፊት የተናገረው ታላቁ ተጋዳይ አባት አባ በጸሎተ ሚካኤል ዘደብረ ጎል ነው፡፡ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ከክርስትና ሕግ ውጭ የአባቱን ሚስት በማግባቱ እንደ ዮሐንስ መጥምቅና እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ሳይፈራና ሳያፍር ፊት ለፊት በመገሠፁ ብዙ መከራ ደረሰበት፡፡ ተገረፈ፤ ታሠረ፤ ተሰደደም፡፡
አስቀድማ የንጉሡ ሚስት የነበረች በኋላ ደግሞ ንጉሡ ለአንዱ ወታደሩ የሰጣት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ይህቺ ሴት ይህንን ሕይወት ንቃ ንስሐ ገባችና ሥጋወደሙ ተቀበለች፡፡ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን «ሂዳችሁ አምጧት፤ እኔም በመኝታዬ አረክሳታለሁ» ብሎ በድፍረት ተናገረ፡፡ መልክተኛ ወደ ሴቲቱ ሲሄድ እርሷ ወደ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ዘንድ ላከች፡፡

Monday, May 14, 2012

ምን? ወይስ እንዴት?

አንዲትን መንደር ኃይለኛ ሞገደኛ ነፋስ እየተነሣ ያስቸግራታል፡፡ የመንደርዋ ካቢኔ ተሰበሰበና ሦስት ባለሞያዎችን መድቦ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጡ ለማድረግ ወሰነ፡፡ በዚህም መሠረት ሦስት ባለሞያዎች ተጠሩና ችግሩ ተነገራቸው፡፡ ከዚያም በችግሩ ላይ አሉን የሚሉትን መፍትሔ እንዲያቀርቡ የአንድ ሳምንት ጊዜ ተሰጣቸው፡፡

ከአንድ ሳምንት በኋላ ካቢኔው ተሰብስቦ ሃሳባቸውን መስማት ጀመረ፡፡ የሦስቱን ሰዎች ሃሳብ ለመስማት ከተቀመጠው ካቢኔ ጋር በጉዳዩ ላይ ላቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው አንድ ሰው እንዲገኙ ተደርገው ነበር፡፡ የመጀመርያው ሰው «ሞገደኛው ነፋስ ለአካባቢው ነዋሪዎች ሕይወት አስጊ በመሆኑ ነዋሪዎቹን ሌላ ቦታ ማስፈር» እንደሚገባ ሃሳብ አቀረበ፡፡ ሁለተኛው ሰው ደግሞ «ነዋሪዎቹን ወደ ሌላ ቦታ መውሰዱ ከብዙ ማኅበራዊ ነገር ስለሚያፈናቅላቸው እዚያው ባለቡት ሆነው ነገር ግን ሞገደኛው ነፋስ ሲነሣ ሊጠለሉበት የሚችሉበት የመሬት ውስጥ የምሽግ ቤት እንዲሠራ» ሃሳብ ሰጠ፡፡

Thursday, May 10, 2012

ሦስቱ ማጣርያዎች

አንድ ወዳጄ እንዲህ የሚል የዕውቁን የግሪክ ፈላስፋ የሶቅራጥስን አባባል ላከልኝ፡፡ 

ሶቅራጥስ አንድ ጓደኛ ነበረው አሉ፡፡ አንድ ቀን ይኼ ጓደኛው መጣና «ሶቅራጥስ እገሌ ስለሚባል አንድ ወዳጅህ የሰማሁትን ነገር ታውቃለህ?» አለው፡፡ ሶቅራጥስም ዝም ብሎ ተወው፡፡ ሰውዬው ግን በሰማው ነገር ሳይደነቅ አልቀረምና እየደጋገመ «በጣም የሚገርምኮ ነው፡፡ እንዲህ ይሆናል ብዬ የማልገምተው ነገር ነው» ይለው ነበር፡፡ በነገሩ የተሰላቸው ሶቅራጥስም 
«በጣም ጥሩ፡፡ የሰማኸውን ነገር ትነግረኛለህ፡፡ መጀመርያ ግን ሦስት ጥያቄዎችን መመለስ አለብህ፡፡ የምትነግረኝ ነገር የእነዚህን የሦስት ጥያቄዎች መልሶች የሚያሟላ ከሆነ ብቻ እሰማሃለሁ» አለው፡፡

ሰውዬውም በዚያው ሃሳብ ተስማማ፡፡

Thursday, May 3, 2012

ለቤተ መጻሕፍትዎ

ባሕረ ሐሳብ
የቀመርና የሥነ ፈለክ ምሥጢር
አዘጋጅ- አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ
የገጽ ብዛት፡- 214
ዋጋ፡- 50 ብር
ኅትመት፡- ፋርኢስት ትሬዲንግ
ዘመን፡- 2004 ዓመተ ሥጋዌ
ጥቂት ስለ ደራሲው፡- 1915 ዓም የተወለዱት አለቃ ያሬድ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የአቡሻክር ሊቃውንት ዋናውና አንጋፋው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ዋና ዋና ትምህርቶችን በሚገባ የተማሩት አለቃ ያሬድ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅም ለአራት ዓመታት ተምረው ተመርቀዋል፡፡ አለቃ ያሬድ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ 24 ዓመታት ባሕረ ሐሳብን አስተምረዋል፡፡አለቃ ያሬድ ከማስተማር በተጨማሪ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብም ይታወቃሉ፡፡ ይኼኛው አራተኛው መጽሐፋቸው ነው፡፡