Sunday, April 15, 2012

የዘበርጋ ጥያቄ

የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ባሳተመው «ባሕል እና ልማት» በሚለው እስትግቡእ ውስጥ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ስለ ፎክሎር የጻፈው ዕውቀት አዘል፣ ልብ መሳጭ ጽሑፍ አለ፡፡ እዚያ ጽሑፉ ውስጥ ዘበርጋ የሚባል አንድ ሰው በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ወቅት የጠየቀውን አስደናቂ ጥያቄ ለሃሳቡ ማስወንጨፊያ ተጠቅሞበታል፡፡
ዘበርጋ መሠረተ ትምህርት ሊማር ነበር የገባው፡፡ መምህሩ ታድያ ሂሳብ ለማስተማር ወደ ክፍል ገቡና እንዲህ አሉ፡፡ አንድ በግ በአምስት ብር ቢሸጥ አራት በጎች በስንት ብር ይሸጣሉ?
ዘበርጋ ከሁሉም ተሽቀዳድሞ እጁን አወጣ፡፡
መምህሩ ደስ አላቸው፡፡ እንዲህ ሂሳብን ያህል ነገር በቶሎ ተረድቶ የሚመልስ ጎልማሳ በመኖሩ፡፡
«እሺ ዘበርጋ» አሉት፡፡
ዘበርጋ ተነሣ፡፡

«የት አላቸው መምህሩን፡፡ ክፍሉ በሙሉ ሳቀ፡፡
ዘበርጋን ያስጨነቀው አንድ በግ በአምስት ብር ተሽጦ አራት በጎች በስንት ብር ሊሸጡ እንደሚችሉ ያለው ውጤት አይደለም፡፡ ለመሆኑ አሁን መምህሩ ባሉት ዋጋ፣ በአራት ብር በግ የት ነው የሚሸጠው? የሦስት ብር ቮልስ መኪና የሦስት ብር በግ እየጫነ ባለበት ዘመን እኒህ መምህር በአራት ብር የሚሸጥ በግ ከየት ነው ያመጡት? በእውነት በግ በአራት ብር የሚሸጥ ከሆነ ሮጥ ብሎ መግዛት ዛሬ ነው፡፡
ይህ የዘበርጋ ጥያቄ የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው፡፡ ቢያንስ የእኔም ጥያቄ ነው፡፡ ዘበርጋ ይህንን ጥያቄ የጠየቀው ሞኝ ስለሆነ ወይንም ሂሳብ ስለማይገባው አይደለም፡፡ በአንድ በኩል የዘበርጋ ጥያቄ የትምህርት ፍልስፍና ጥያቄ ነው፡፡ ትምህርት እውነታውን ካላንጸባረቀ፣ ችግርንም ካልፈታ ትምህርትነቱ ለጊዜ ማጥፊያ ይሆናል፡፡ የመምህሩ ምሳሌ እና የዘበርጋ ኑሮ አልተጣጣመም ማለት ነው፡፡ በአሜሪካ እንዲህ ነው፣ በአውሮፓም እንዲህ ነው፣ በእስያም እንዲህ ነው እየተባሉ ለሚሰጡት ትምህርቶች የዘበርጋ ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡
አንድ የኅብረተሰብ ሳይንስ መምህር ተማሪዎቹን ሲያስተምር ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ናት? ይላቸዋል፡፡ ወዲያው አንድ አስተዋይ ተማሪ ተነሥቶ «ታድያ ለምን ሥጋ ውድ ይሆናል ሲል ጠየቀው፡፡ እውነቱን ነው፡፡ አንደኛ መውጣት ለቁጥር ብቻ ከሆነ ከብት ከሌላቸው ከነ ዱባይ፣ አብዛኛውን ሥጋ ከውጭ ከሚያስገቡት ከነ ግብጽ ባነሠ ዋጋ ሥጋ ካልተሸጠ አንደኛ መውጣት ትርጉሙ ምንድነው? ቁጥር ብቻ፡፡
የሕግ፣ የሲቪክስ፣ የታሪክ፣ የኢኮኖሚክስ፣ የአካውንቲንግ፣ የአስተዳደር ወዘተ ትምህርቶቻችን በዚህ የዘበርጋ ጥያቄ ሊፈተሹ ይገባቸው ነበር፡፡ ይህ ስለ ሕግ ልዕልና፣ ስለ ተከሰሰ ሰው መብት፣ ካልተፈረደበት እንደ ወንጀለኛ አይቆጠርም ስለሚባለው፣ የዳኞች የኅሊና ነጻነት፣ የፕሬስ ነጻነት፣ በዳኝነት ሥራ ውስጥ ማንም ጣልቃ ስላለመግባቱ የም ንማረው ትምህርት ግን የት ነው የሚተገበረው? ወይስ እንደ ሂሳብ መምህሩ የመማርያ ሰሌዳው ላይ ብቻ ነው ያለው? ዘበርጋ የገረመውኮ ይኼ በሰሌዳው ላይ ያለው የበግ ዋጋ የት ነው በአካል የሚገኘው? የሚለው ነው፡፡ ይኼ ነው የዘበርጋ ጥያቄ፡፡ የእኛም ጥያቄ ይኼው ነው፡፡ ይኼ በሕግ ትምህርት፣ በሕግ ዐዋጆች እና በሕግ ንግግሮች ውስጥ ይፈጸማል የሚባለው የሕግ ልዕልና፣ የሕግ እኩልነት እና የሕግ ነጻነት የት ነው ያለው?
ይኼ በሲቪክስ ትምህርት ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ መብት ማስከበር፣ ስለ ዜጋ፣ ስለ መንግሥት እና ሕዝብ፣ ስለ ሥነ ምግባር የሚሰጠው ትምህርትስ መጽሐፉ ላይ ብቻ ነው ወይስ መሬትም ላይ ይገኛል? ይኼ የአካውንቲንግ ተማሪዎች በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኩባንያዎች ምሳሌነት የሚማሩት፣ ተፈትነው ከኤ እስከ ኤፍ የሚያገኙበት ነገር የት መሥሪያ ቤት ነው ያለው? ለመሆኑ ከትምህርት ቤት ከወጣችሁ በኋላ አግኝታችሁታል? ወይስ እንደ ዘበርጋ መምህር ለምሳሌነት ብቻ ነው የተማራችሁት?
የት? አለ ዘበርጋ እውነቱን ነው፡፡
ብዙ ዕድገቶች፣ ለውጦች እና ብልጽግናዎች በቁጥር ነው የሚገለጡት፡፡ በዚህን ያህል በመቶ አድገናል፤ በዚህን ያህል በመቶ ተለውጠናል፤ በዚህን ያህል በመቶ ድህነት ቀንሷል የሚሉ አኀዞች ሞልተዋል፡፡ ግን እነዚህ አኀዞች በምድር ላይ የት ነው ያሉት፡፡ የስኳር ምርት እጥረት የለም፣ ዘይትም በሽበሽ ነው፣ ስንዴም ከበቂ በላይ አለ የሚሉን ሰዎች ለምን የት የት እንዳለ አይነግሩንም? ስኳር በስንት ልመና እና ዝምድና እያገኘን እንደሆነ አልሰሙም ማለት ነው? ይኼንን ተከማችቶበታል ብለው የሚናገሩለትን ቦታ ለምን አይጠቁሙንም?
እነዚህስ ስኳሩን፣ ዘይቱን እና ስንዴውን ደብቀው የያዙት «አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች» እነማን ናቸው? ካሉ ለምን አይነገረንም? ለምን እነርሱም እንደ ሜትሮሎጂ አንዳንድ እየተባሉ ይጠራሉ? ስም የሌላቸው አድራሻ ያላወጡ ነጋዴዎች ናቸው እንዴ? ወይስ እንደ ዘበርጋ መምህር ወረቀት ላይ ብቻ ነው ያሉት? እነዚህ በየሚዲያው አበረታች እየተባሉ የሚገለጡ ነገሮች መሬቱ ላይ የት ነው ያሉት?
የኃይል እጥረት የለም፤ የቴክኒክ ችግር ገጥሞን ነው ይሉናል፡፡ እጥረት ከሌለ መልካም፡፡ ግን ይኼ የቴክኒክ ችግር በየሁለት ቀኑ ነው እንዴ የሚከሰተው? ወይስ ችግሩ ራሱ በዕቅድ ነው የሚሠራው? ለመሆኑ የት ነው ችግሩ የሚከሰተው? ለምን እቅጩ አይነገረንም? በአንዳንድ ትራንስፎርመሮች፣ በአንዳንድ ማስተላለፊያዎች ማለት ምን ማለት ነው? የቱ ሲበላሽ ነው አንዳንድ የሚባለው?
 እነዚህስ በሚትሮሎጂ አንዳንድ ቦታዎች እየተበላ የሚነገርላቸው፤ እነዚህ እንኳን ዝናብ ያገኛሉ የሚባሉት፡፡ የት ናቸው ያሉት፡፡ ይኼ አንዳንድ የሚለውስ እንደ ክርስትና ስም የሜትሮሎጂ ስማቸው ነው እንዴ?
የኢትዮጵያን ዕድገት ለማቀላጠፍ አንዱ ወሳኝ ተግባር ባለ ሥልጣናት እና ጋዜጠኞች ሦስት ቃላትን እንዳይጠቀሙ ማገድ ነው፡፡ «አንዳንድ፣ አበረታች እና አፈጻጸም»፡፡ እነዚህ የት እንዳሉ የማይታወቁ የዕድገት ዕንቅፋቶች ናቸው፡፡ አንዳንድ ስንት ነው? የት ነው? እነማንን ነው? አይታወቅም፡፡ አበረታች ስንት ነው? እስከየት ነው? የበረታውስ ማነው? መልስ የለም፡፡ አፈጻጸም የት ነው? ማን ነው? አይታወቅም፡፡
ወዳጆቻችሁ ሲያወሩስ ሰምታችሁ አታውቁም «ብዙ ሰው እኮ እንዲህ እያለ ነው፣ ብዙ ሰው እኮ እንዲህ እያደረገ ነው፣ ሕዝቡኮ እንዲህ አለ፣» ሲሉ አልሰማችሁም? እስኪ እንደ ዘበርጋ የት? በሏቸው፡፡ ለመሆኑ ይኼ ሕዝብ የሚባው አካል የት ነው ያለው? መቼ ነው ተሰብስቦ ወይንም ተመካክሮ የወሰነው? ሕዝብ የሚባል አካል ቢኖር ኖሮ ስንቶቹ ተነሥተው በሕዝብ ስም ሲምሉ፣ ሲያሥሩ፣ ሲገድሉ፣ ሲበሉ፣ ሲጠጡ፣ ሀብት ሲያካብቱ፣ ሲነግሡ፣ ሲወጡ፣ ሲወርዱ፣ ራሱ ሕዝብ የሚባለው እውነቱን ይነግረን አልነበረም?
አሁን ሰሞኑን የመምህራን ደመወዝ እያወዛገበ ነው፡፡ መንግሥት ደመወዝ ጨምሬያለሁ፤ የጠየቁትን አሟልቻለሁ ይላል፡፡ መምህራኑ ደግሞ የተሰጠን እራት ሳይሆን ዳረጎት ነው፡፡ ድሮ ሕፃን ሆነን
«የታረደው አምሳ ዶሮ
የደረሰኝ አንድ ዶሮ» እንደምንለው ነው፡፡ እኛ ያልቻልንበት
«ያቺን ይዤ ወደ ጓሮ» የሚለውን ነው ይላሉ፡፡ ምናልባትምኮ ጥያቄው የደመወዝ ጭማሪ ሳይሆን የዘበርጋ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ የተጨመረው ብር የት ነው ያለው? የሚል፡፡
ለመምህሩ ደመወዝ ተጨመረ ተባለ፡፡ የቤት ኪራይ ጨመረ፡፡ ጤፍ ጨመረ፡፡ ምግብ ጨመረ፡፡ ሻሂ ጨመረ፡፡ ዳቦ ጨመረ፡፡ አሁን ጭማሪው የት ላይ ነው ያለው? ነው ጥያቄው፡፡ የተጨመረው ለአከራዩ ነው ለመምህሩ? ለባለ ሆቴሉ ነው ለመምህሩ? ለሱቅ ጫሹ ነው ለመምህሩ) ያቺ የመጣችው ገንዘብ የት ገባች? ወይስ ፔሮል ላይ ብቻ ነው የምትታየው?
ታዋቂው ተረበኛ ናስሩዲን መሬቱን ቆሞ ያሳርሳል አሉ ኢራኖች፡፡ በዚያ ቦታ በፈረስ እየሸመጠጠ አንድ አዳኝ መጣ፡፡
«ሆጃ» አለው አዳኙ፡፡ «አንበሳ ወደ ጫካ ሲገባ አይተዋል እንዴ ሲል ጠየቀው፡፡
ሆጃ ናስሩዲንም «በሚገባ» ሲል በኩራት መለሰለት፡፡
አዳኙ ፈረሱን ነቅንቆ ወደ ጫካው ሸመጠጠ፡፡
ከአራት ሰዓታት በኋላ አዳኙ ፈረሱን እየጎተተ በኀዘን ተመለሰ፡፡
«ምነው ሆጃ» አለው ናስሩዲንን፡፡
«ምን ሆንክ» አለው ናስረዱኒን፡፡
«አንበሳ ወደ ጫካ ሲገባ አይቻለሁ አላሉም» አዳኙ አንገቱን እየነቀነቀ ጠየቀው፡፡
«አዎ አይቻለሁ»
«እኔኮ ጫካውን ሙሉ ፈተሽኩ እንኳን አንበሳ ላገኝ የአንበሳ ዱካ እንኳን ለማየት አልቻልኮምኮ» አለው አዳኙ፡፡
«ልክ ነህ ልታገኘው አትችልም» አለው ናስሩዲን
«እንዴት ሆጃ»
«አንበሳውን ወደ ጫካ ሲገባ ያየሁትኮ እዚህ አይደለም»
«ታድያ የት ነው»
«ቱርክ ውስጥ በሚገኝ ጫካ ነዋ»
«ታድያ ለምን አለፉኝ
«አንተኮ አንበሳ ጫካ ውስጥ ሲገባ አይተሃል ወይ አልከኝ እንጂ፣ አንበሳ እዚህ ጫካ ሲገባ አይተሃል ወይ ብለህ አልጠየቅከኝም» አለው ሆጃ ናስሩዲን፡፡ አዳኙ እያዘነ ወደ መጣበት ሲሄድ ሆጃ ናስሩዲን ድምፁን ከፍ አድርጎ «ለወደፊቱ የት? ብለህ ሳትጠይቅ ወሬ ሰምተህ አትሩጥ» አለና መከረው፡፡
የዘበርጋ ጥያቄ የናስሩዲንም ጥያቄ ነው፡፡ የኛም፡፡
 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡ በሌላ መሰል ኅትመት ባይወጣይመረጣል፡፡

27 comments:

 1. Dani it is good, but you make me cry....so sad on everything.....God where are you?

  ReplyDelete
 2. Thank You Dn Daniel!

  ReplyDelete
 3. "Enqual Lebrhane Tinasaew beselam Adereseh Dn. Daniel."

  Grum eyita! like always, I wonder how your analysis. Thank you very much.

  Welete Amanuel

  ReplyDelete
 4. ይኼ የአካውንቲንግ ተማሪዎች በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኩባንያዎች ምሳሌነት የሚማሩት፣ ተፈትነው ከኤ እስከ ኤፍ የሚያገኙበት ነገር የት መሥሪያ ቤት ነው ያለው? ለመሆኑ ከትምህርት ቤት ከወጣችሁ በኋላ አግኝታችሁታል? ወይስ እንደ ዘበርጋ መምህር ለምሳሌነት ብቻ ነው የተማራችሁት?
  የት? አለ ዘበርጋ እውነቱን ነው፡፡
  Mamush,MN

  ReplyDelete
 5. wow dn. daniel girum tsihuf! enkuan adereseh kenemelaw betesebih geta yitebikih.

  ReplyDelete
 6. Let God bless your mind and brain! Let He keeps you from EPRDF slaugthers! As u keep on writing this eyed-and -teethed fact, be ready to get all types of injuries of federal police through Berket Simon's press bullet!

  ReplyDelete
 7. ዳኒ እውነት ብለሃል፡፡ የዘበርጋን ጥያቄ የማይመልሱ የት እንዳሉ የማይታወቁ፣ ያለጊዜያቸዉ የመጡ፣ ለኛ የማይጠቅሙ፣ የሚጠቅሙትም በጽሑፍ ወይም በወሬ የቀሩ . . . ናቸዉ፡፡

  ReplyDelete
 8. abo tidebiraleh anten bilo tsehafi

  ReplyDelete
  Replies
  1. kehadi neger neh, debaris ante

   Delete
  2. You Idiot! you don't know what you are talking

   Delete
 9. enanem Waizero Zabaregete baloge.10q dani

  ReplyDelete
 10. tinfashien wat adirgie new yanebebkut! yegizew angebgabi tiyakie bemehonu ejig betam mesitognal! Egziabher Yibarkih!!!

  ReplyDelete
 11. በቅድምያ እንኳን ለብርሃነ ትንሳዔው በሰላምና በጤና አደረሰህ፡፡ ሁልጊዜ የምታነሳው ቁም ነገር ወቅታዊና ማህበረሰብ ተኮር በመሆኑ ጥያቄ ያለበት መልስ ነው፡፡ ይህ ምሳሌያዊ ወግ ባለንበት ወቅት በየሚዲያውና የስብሰባ አዳራሾች የምንሰማቸው ቃላት ናቸው፡፡ ቋቅ ያሉን፡፡ የት ናቸው የማይታወቁ፡፡ ስር የላቸው የሚነቀሉ፡፡ ባለቤት እንደሌላቸው እብድ ውሾች የሚያስደነብሩ፡፡ በቁጥርና በካድሬዎች አፍ ብቻ የምንሰማቸው እድገትና ለውጥ፡፡ ሁል ጊዜ በቁጥር መሸርደጃ ብቻ እንደ ጨዋ ተቆጥረን እንድንኖር የሚሹ ባለ መድረኮች የተዋጥንበት፡፡ ከሚቆጠረው ቁጥር ቢሰላ ከ ዜሮ በታች እንኳ ሳይደርሰን ወይም ሳናይ በግድ አግኝታችኋል እመኑ ፤ በየጣብያው የሕንፃ ቁልል እየሳዩ እንቁልልጭ፤ ይህን ያህል ባለሃብት ይሄን ያህል ፋብሪካ ይሄን ያህል ትርፍ ወዘተርፈ ግን የታለ ድሃው የተጠቀመው? ተሻሽሏል የሚባለውስ ኑሮ የትነው ያለው? ዘይትና ስንዴ ፍለጋ እናቶቻችን በሳሳ ሰውነታቸው በቁር ሌሊት ወጥተው በየቀበሌውና ህብረት ሥራ ምናምን በሰልፍ መከራቸውን እያዩ እየታየ የከተማው ነዋሪ ህዝብ ኑሮ በዚህን ያህል በመቶ እድገት አሳይቷል ተባለ እያለ ያ አያልቅበት ኢቴቪ ከተሰለፉት ደካሞች እንኳ ትንሽ ሳይርቅ አይኑን በጨው አጥቦ ይዋሻል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ አረቦቹን ያከበራቸው ነዳጅ እንኳ ቢገኝ አንዳንድ ከሚባሉት በቀር ተጠቃሚ ይኖራል የሚል ግምትም እምነትም አይኖረኝም፡፡ ግን እነኚህ አንዳንድ… የሚባሉትስ ራሳቸው የታሉ??
  ቢሆንም ይህ አይነቱ አካሄድ እገሊት ከተባለችው ሀገር የተገኘ ምርጥ ተሞክሮ ነውና ልንቀበለው ግድ ይለናል፡፡ በቃ አድገናል፡፡ የምንበላው በላይ በላዩ በርካሽ ዋጋ እየቀረበልን ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ ቢጨምርም እኛጋ’ኮ በወር ነው ክለሳው የሚደረግው፡፡ ያውም በሳንቲም ቤት፡፡ ምናላት ታድያ 10 ሳንቲም ለኢትዮጵያ ህዝብ? ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ ሁሌ ዝም ለአምላኩ እየነገረ፡፡ እኔ ግን አልስማማም ምክንያቱም ዝም የሚለው ስለተረፈው ነዋ፡፡ እምም … ለመሆኑ ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ የት ነው ያለው ማለቴ ኑሮው የተሻሻለለት በቀን 3 ጊዜ መብላት የቻለው፡፡ ወይስ ሌላ ኢትዮጵያ ከምድር በታች አለች? ልቡና ይስጣቸው ልብም፡፡

  ReplyDelete
 12. Enquwan Lebrhane Tensaew Beselam Aderesehe
  betam wedejewalhu amelkakthen

  ReplyDelete
 13. I hope most Ethiopians including Dn.Daniel is writing constructing comments about our social and political lives and situations. But our leaders are not readers and Positive thinkers to consider it. ARE THEY MINDLESS!!!
  Please if they have minded consultant tell them our suffering .... TALK TALK TALK ONLY WITH OUT LISTEN EVEN HEAR

  ReplyDelete
 14. betam des yemile newe GOD be with U
  senaiyt Negesse

  ReplyDelete
 15. This is wonderful.

  ReplyDelete
 16. Ejig betam leza yalew astemarim eyita new. Daniel, Tebarek; Kef yale Enjera Yisteh.

  ReplyDelete
 17. Egziabher yibarkih lastewalew tilik yenuro menged new

  ReplyDelete
 18. መልካም እይታ ነው፡፡ አገሪቱ በሙሉ እንደዚያ ነች፡፡ በርታ!

  ReplyDelete
 19. If I am allowed may I ask where Zeberga is now? Is there any one who thinks like Zeberga in MP or in MoFED or any other ministry bureau? Even Zeberga is not in our universities. Zeberga, what a nice script, what an educating piece, what a good thought!

  ReplyDelete
 20. እግዚአብሔር እይታህን ያስፋልህ፡፡

  ReplyDelete
 21. የድርሻችሁን ተወጥታችሁ ዉጤታችሁ ቢርቅም
  የህሊና ጥያቄያችንን በማስተጋባት ህዝብ የሚባለዉ የት እንዳለ አሁንም ንገሯቸው!

  ReplyDelete
 22. you the Diakon! hasab maflikun keto yet temark? anten yemeselu sewoch eko teftew new abesachin yebezaw!! wois endetebalehu siltan yabalga?
  tell me
  ayumenethiopia@gmail.com
  thank you
  A.M

  ReplyDelete
 23. ሳሚ ወ/ሚካኤልApril 27, 2012 at 6:26 PM

  ክርስቶስ ተንስኣ እሙታን በአብይ ሃይል ወስልጣን አሰሮ ለሰይጣን አጋዝኦ ለኣዳም ሰላም እምይዜሰ ኮነ ፍስሃ ወሰላም!!!!!ዳኒየ እንኩዋን አደረሰህ!!!! በትንሺቱ የተረት ጋሪ ስንቱን ጋራ ሸንተረር ቃኘኸው???የንዴትና የግርምት ማኪያቶ አጠጣሃኝ!!! ኢትዮጵያየ ትንሳኤሽ ወዴት አለ??????????????????????????

  ReplyDelete