እነሆ ዛሬ ኢየሩሳሌም በኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች ተሞልታ ነበር፡፡ መንገዱ ሁሉ ነጭ ለብሶ ነጠላ ባጣፋ ሰው ያጌጠ ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ ከዘመናት ሁሉ የዚህ ዓመት የተሳላሚዎች ቁጥር እንደጨመረ ነዋሪዎች እና የገዳማቱ አባቶች ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አራት ምክንያቶችን ይሰጣሉ፡፡
የመጀመርያው በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም በሚገኙ ምእመናን ዘንድ መንፈሳዊ ትምህርት እየተስፋፋ መምጣቱ የተሳላሚዎቹን ቁጥር በዚህ በኢየሩሳሌም ብቻ ሳይሆን በሀገር ቤትም እየጨመረው መጥቷል፡፡ ለዚህም በማሳያነት የሚያቀርቡት ከዚህ ቀደም የኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች በአብዛኛው በእድሜ የገፉ አረጋውያን ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ወጣቶች እና ጎልማሶችም ወደ ኢየሩሳሌም ገዳማት የሚያደርጉት የተሳላሚነት ጉዞ ጨምሯል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ልዩ ልዩ ዓለማት መሰደዳቸው ነው፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ለተሳላሚነት ለመምጣት ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ይህንን ወጭ በውጭ ሀገር የሚገኙ ልጆቻቸው እየከፈሉላቸው ብዙ ወላጆች ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት ላይ ናቸው፡፡
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ከዚህ በፊት ለጉዞ ይጠየቁ የነበሩ መመዘኛዎች እየቀነሱ መምጣታቸው ነው፡፡ በዓለም ላይ የተከሰተውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የቱሪስቶች ቁጥር ቀንሷል፡፡ ይህንን እየቀነሰ የመጣውን የቱሪስቶች ፍሰት ለማበረታታት የቱሪስተ መዳረሻ ሀገሮች የሚጠይቋቸውን መመዘኛዎች እያቀለሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዷ እስራኤል ናት፡፡ ለወጣቶች አለመፍቀድ፤ ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅ፤ ጋብቻን እንደ መሥፈርት ማስቀመጥ እና የመሳሰሉት ወደ እስራኤል የሚመጡ ተሳላሚዎችን የሚገቱ መመዘኛዎች ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ መመዘኛዎች በአንፃራዊነት እየተሻሻሉ መጥተዋል፡፡
አራተኛው ምክንያት የአጓጓዥ ድርጅቶች ቁጥር መጨመር ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ብቻ ይደረግ የነበረው የተሳላሚዎች ጉዞ በአሁኑ ጊዜ ከስድስት በሚበልጡ ድርጅቶች በኩል በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ተጓዦችን ለማበርከት አሠራርን በማስተካከላቸው፣ ኤምባሲው የሚጠይቃቸውን መመዘኛዎች በባለ አደራነት ስለ ተገዡ ሆነው በማሟላታቸው እንዲሁም ተገቢውን ቅስቀሳ በማድረጋቸው የተሳላሚዎች ቁጥር ሊጨምር ችሏል፡፡
በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች የተነሣ በዚህ ዓመት የተሳላሚዎቹ ቁጥር እስከ ሁለት ሺ ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል ስድሳ በመቶው ከኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ከአሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሆላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጀርመን እና ሌሎች ሀገሮችም የመጡ ኢትየጵያውያን ተሳላሚዎች ሌላውን ቦታ ይዘዋል፡፡
ዛሬ የጸሎተ ኀሙስ ቅዳሴ የተከናወነው በዴር ሡልጣን ገዳም ነበር፡፡ ሕዝቡ ከመብዛቱ የተነሣ በቤተ ሚካኤል፣ በቤተ መድኃኔዓለም እና በድንኳን ውስጥ ተቀድሶ ቦታ ሊበቃ ግን አልቻለም፡፡ ያቺ የዴር ሡልጣን ግቢ መላእክት ጌታ በተወለደ ጊዜ መልተው እንደታዩባት ቤተልሔም ሆና ነው የዋለቺው፡፡ ካስቀደሰው ሰው መካከል ከሰማንያ በመቶው በላይ ሥጋውን እና ደሙን ሲቀበል ማየት ስብከተ ወንጌል ፍሬ እያፈራ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
ነገ ከማለዳ ጀምሮ ጌታ ከተገረፈበት ከፕራይቶርዮን ግቢ እስከ ቀራንዮ መካነ ስቅለቱ በሚፈረግ የፍኖተ መስቀል ጉዞ እና የስግደት ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡