Friday, March 9, 2012

«ዲጂታላይዜሽን[1]» እና «ዲጂታል» ሌቦች

click here for pdf
 ከመቀሌ ከተማ የሃያ ደቂቃ መንገድ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው የአቡነ ያሳይ ገዳም አንድ ፈረንጅ ይመጣል፡፡ ሰውዬው የመጣው ብቻውን ሳይሆን ከአንዳንድ ባለ ሥልጣናት ጋር ነበር፡፡ እነዚያ ባለ ሥልጣናት የገዳሙን ሰዎች ጠርተው «ይኼ ፈረንጅ በገዳሙ ያሉ ትን ጽሑፎች በሙሉ በዲጂታል ፎቶ ግራፍ እንዲያነሣ ይፈቀድለት» ብለው መመርያ ይሰጣሉ፡፡እርሱም በሙሉ በዲጂታል ካሜራ ያነሣቸዋል፡፡
እኛ ወደ ገዳሙ ለጥናት በሄድን ጊዜ «ከእናንተ በፊት አንድ ፈረንጅ መጥቶ መጻሕፍቱን ሁሉ በካሜራ አነሣ» ይሉናል፡፡ ገዳማውያኑ ፈረንጁ ፎቶ ማንሣቱን እንጂ፣ ለምን እንዳነሣ፣ አንሥቶ የት እንደሚወስደው፣ ባለቤትነቱ የማን እንደሆነ አልተነገራቸውም፤ እነርሱም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ብቻ በሙዳየ ምጽዋቱ ውስጥ 1970 ብር መጨ መሩን በምስጋና ያስታውሱታል፡፡
እነዚህ ገዳማውያን ይህንን ቅርስ ጠብቀው ለዘመናት የኖሩ ናቸው፡፡ የጥበቡ የባለቤትነት መብት (Intellectual property right) አላቸው፡፡ በእነዚያ ቅርሶች መጀመርያ ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው እነርሱ ነበሩ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ ይህ ፈረንጅ የእነርሱን የሺ ዓመታት ጽሑፎች ቅጅ እየወሰደ መሆኑን ሊነገራቸው ይገባ ነበር፡፡
ይህንን ታሪክ በቁጭት የተናገሩት በኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ ጥናት በማድረግ እና በመጻፍ የታወቁት ዶክተር አየለ በከሪ ናቸው፡፡ «የጥንታዊ ጽሑፎች አያያዝ እና አጠባበቅ በኢትዮጵያ» በሚል ርእስ የካቲት 29 ቀን 2004 ዓም የብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ባዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ፡፡
ኢትዮጵያ ጥንታውያን መዛግብት ከሚገኙባቸው ጥቂት የዓለም ሀገሮች አንዷ ናት፡፡ ዐጽማቸውን ያለምልም፣ ነፍሳቸውንም ይቀበልና አባቶቻችን ዕውቀት ፈላጊዎች፣ ጥበብ አሳሾች በመሆናቸው ከእንግሊዝ እስከ ሕንድ ከግብጽ እስከ ሩሲያ እያሰሱ የዓለሙን ዕውቀት ወደ ሀገራችን አምጥተውልናል፡፡ ብሉይ ከሐዲስ ከነ ሊቃውንቱ ሳይጎድልብን፤ የግሪኮቹን ፈላስፎች የነአሪስቶትልን እና ሶቅራጥስን፣ ብሎም የነፕሉቶን ፍልስፍና በአንጋረ ፈላስፋ፤ የሕንዶቹን ትምህርት እና የሥነ ምግባር እሴት በመጽሐፈ በርለዓም ያገኘነው በዚህ የተነሣ ነው፡፡
እነርሱም ራሳቸው በዘመናቸው የደረሱበትን በብዕራቸው እና በሥዕላቸው አሥፍረውልናል፡፡ ዛሬ አሉ የሚባሉት ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ጥንታውያን የግእዝ መጻሕፍት የእነዚሁ አባቶቻችን የድካም ፈሬዎች ናቸው፡፡
እነዚህን ጥንታውያን የዕውቀት ክምችቶች የመዝረፍ እና ከሀገራቸው የማሰደድ ተግባር የተጀመረው 17ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ሀገሪቱ የመጡ አሳሾች፣ ሚሲዮናውያን፣ የዲፕሎማሲ ሰዎች፣ ነጋድያን እና ተመራማሪዎች እነዚህን የጽሑፍ ቅርሶች እየጫኑ ሲያጓጉዙ ኖረዋል፡፡ እንደነ ጄምስ ብሩስ ያሉት አሳሾች እስከ ሦስት የሚጠጉ መጻሕፍትን ማውጣ ታቸው ይነገራል፡፡
ዐፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ አምባ ላይ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት የመገንባት ዓላማ ስለነበራቸው አብዛኞቹ በጎንደር አድባራት እና አብያተ መንግሥታት የነበሩትን የጽሑፍ ቅርሶች ወደ መቅደላ አምባ አጓጉዘው አከማችተዋቸው ነበር፡፡ መቅደላ አምባ ተሠብሮ ዐፄ ቴዎድሮስ በጀግንነት ራሳቸውን ሲሠው እንግሊዞች የመቅደላን ቅርሶች ዘርፈው ወስደዋቸዋል፡፡ በቅርቡ በተሰጡ ግምቶች ወደ 2 ቢሊዮን ፓውንድ የሚገመት ንብረት ከመቅደላ መዘረፉ ይነገራል፡፡
ከዚያም በኋላ ቢሆን ዝርፊያው አላቋረጠም፡፡ የኢትዮጵያ ቅርሶች ከጃፓን እስከ አሜሪካ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ኖርዌይ ተበትነዋል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይህንኑ ጉዳይ ሲገልጡት «የኢትዮጵያ መጻሕፍት እንደ ጭሮ ያልተዘሩበት፣ እንደ እሥራኤል ዘር ያልተበተኑበት ቦታ የለም» ማለታቸው ይወሳል፡፡
አሁን ዘመኑ በጥንታውያን ቅርሶች ላይ ጠበቅ ያለ ርምጃ የሚወሰድበት እየሆነ ሲመጣ፤ በሌላ በኩልም ታላላቅ መጻሕፍትን በጠረጲዛ ላይ ከማንበብ ይልቅ ቀላል ቅጃቸውን (soft copy) ማንበብ እየተዘወተረ ሲሄድ፡፡ አንድን የብራና መጽሐፍ ለመስረቅ፣ ለማሰረቅ እና ለማጓጓዝ የሚወስደው ጊዜ እና ወጭ እየከበደ ሲመጣ የሌብነት ዓይነቱ ተቀየረ፡፡
ዲጂታል ሌቦች
«ዲጂታላይዜሽን» ጥንታውያን ጽሑፎችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሱ፣ በየጊዜው ለአገልግሎት መጠቀሙ እና በየወቅቱም እነርሱን ፎቶ ማንሣቱ ታሪካዊ ውርጅናሌያቸውን እያጠፋው በመምጣቱ የተፈጠረ ዘዴ ነው፡፡ «ዲጂታላይዜሽን» የጽሑፍ ሥራዎቹን በዲጂታል ካሜራዎች በማንሳት በኮምፒውተር በኩል በተለይም በመሥመር ላይ (on line) ለአንባብያን እና ለተመራማሪዎች የማቅረብ ዘዴም ነው፡፡
በዐውደ ጥናቱ ላይ ተሳትፈው የነበሩ እንደ እና ዶክተር ባሕሩ ዘውዴ ዓይነት ምሁራን «ዲጂታላይዜሽን ቅርሶቹን እንዳይነቃነቁ ለመጠበቅ፣ በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እና የቦታ ጥበትን ችግርን ለመፍታት» ጠቀሜታ እንዳለው ገልጠው ነበር፡፡ «በተለይም አብዛኞቹ የሀገራችን የጽሑፍ ሀብቶች የሚገኙባቸው የእምነት ቦታዎች ከሕዝቡ መኖርያ የራቁ በመሆኑ ለተመራማሪዎች እና ለተማሪዎች የመደረስ ችግር አለባቸው፡፡ ጽሑፎቹን በዲጂታል ቅጅ ማስቀመጥ ይህንን ችግር ይፈታል» ብለዋል፡፡ «ይህ የሚሆነው ግን» አሉ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ «ጣምራ እንቅስቃሴ ሲኖረን ነው»፡፡ እርሳቸው ጣምራ እንቅስቃሴ ሲሉ የገለጡት የባለቤትነትን መብት ከዲጂታላይዜሽን ጋር የማጣመርን ሂደት ነው፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ ለጥቅም የተፈጠረ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ነገር ግን የሂደቱ ባለቤቶች እኛው ራሳችን ሆነን ማን ዲጂታላይዝ ያደርጋል፣ እንዴት? ማን ይፈቅዳል? ባለቤቱ ማነው? የባለቤቱ ተጠቃሚነትስ ምንድን ነው? ቅጅው የት የት ይቀመጣል? የሚሉትን ካልወሰንን በቀር ለዝርፊያ የሚያጋልጠን ነው» ብለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ አያሌ ፈረንጆች እና የፈረነጁ[2] አበሾች በዲጂታል ስርቆት ላይ ተሠማርተው በሀገሪቱ ጥንታውያን ቦታዎች ላይ ላይ ታች በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ስርቆት ላይ የተሠማሩት አካላት ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡
 1. በጥናት እና ምርምር ስም ወደ ሀገር የሚገቡ ፈረንጆች፡፡ እነዚህ ሰዎች ጥናት እና ምርምር እናደርጋለን፣ ጥንታዊ ጽሑፎችን ዲጂታላይዝ እናደርጋለን እያሉ ወደ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ የሚመጡ ናቸው፡፡ ከመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች እና ከእምነት ተቋማት ፈቃድ አግኝተው በየታሪካዊ ቦታዎች በመዘዋወር መጻሕፍቱን እና መዛግብቱን ፎቶ የሚያነሡ ናቸው፡፡
እነዚህ አካላት ስርቆታቸው የተሳካ እንዲሆን ያደረጉላቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡
/ አመለካከት፡፡ ፈረንጅ ሁሉ የተማረ፣ ደግ፣ ሥልጡን እና ቅን ነው ብሎ የማሰብ ችግር በሕዝባችንም ሆነ በተቋሞቻችን ዘንድ አለ፡፡ እናንተ ሐበሻ በመሆናችሁ ስትፈተሹ ፈረንጅ የማይፈተሽባቸው፤ ከእናንተ ከሀገሬው ሰዎች ይልቅ ፈረንጅ ቅድሚያ የሚያገኝባቸው አያሌ አጋጣሚዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
እንዲያውም አንድ የስብሰባው ተሳታፊ በዚህ ጉዳይ የገጠመውን ነገር ነግሮን ነበር፡፡ «እኔ እና አንዲት ፈረንጅ ወደ አንዲት ገዳም አንድ ዓይነት ደብዳቤ ይዘን ሄድን፡፡ የገዳሙ ሰዎች ለእኔ አንዲት መጽሐፍ ብቻ እንድመለከት ሲፈቅዱልኝ እርሷን ግን ፈረንጅ በመሆኗ ብቻ ሁሉንም መጻሕፍት በፎቶ ግራፍ እንድታነሣ ፈቀዱላት፡፡ በወቅቱ ተናድጄ ምክንያቱን ስጠይቃቸው እርሷኮ ፈረንጅ ናት ነው ያሉኝ፡፡»
በአንድ ወቅት በአፋር ክልል የአንትሮፖሎጂ ጥናት ያደረገ ኢትዮጵያዊ ፈረንጅ በመሆናቸው ብቻ የርሱን የጥናት ክልል ለውጭ ሰዎች እንደተሰጠበት በምሬት ሲናገር ሰምቼው ነበር፡፡
/ ሁለተኛው ችግር ደግሞ ነገሮችን ከጊዜያዊ ጥቅም አንፃር የመመዘን ችግር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት እየዘረፉ መሆኑን ፈቃጆችም ሆኑ ቅርሱን የያዙት አካላት አልተረዱትም፡፡ በዚህም የተነሣ በሙዳየ ምጽዋት የሚያስገቡዋቸውን ጥቂት ብሮች እንደ ትልቅ ርዳታ በማየት ዝርፊያውን ይፈቅዱላቸዋል፡፡ የሚተባበሯቸው አካላትም የውሎ አበል ገንዘብ ማግኘታቸውን፣ ከፈረንጅ ጋር መዋላቸውን፣ ጥቃቅን መሣርያዎችን መረዳታቸውን እንጂ ሀገር መሸጣቸውን አልተረዱም፡፡
 1. መንግሥታዊ አካላት፡- ምንም ዓይነት በቂ የሕግ ማዕቀፍ በሌለበት ለእነዚህ ፈረንጆች ፈቃድ በመስጠት በሕግ ሽፋን የሀገር ሀብት እንዲዘረፉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ጥንታዊ ጽሑፎችን ወደ ዲጂታል ስለ መቀየር የወጣ የአሠራር መመርያም ሆነ ሕግ እንደሌለ በዐውደ ጥናቱ ላይ ሲገለጥ ነበር፡፡ በርግጥ አንድ የዲጂታል የደረጃ መመርያ እየወጣ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ስርቆቱ ግን ከሕጉ ቀድሞ እየተፋጠነ ነው፡፡ ምናልባትም ሕጉ ሀብቶቹ ሁሉ ካለቁ በኋላ ሊወጣም ይችላል፡፡
በእነዚህ አካላት ዘንድ የግንዛቤ እጥረት ያለ ይመስላል፡፡ በአካል የሚታየውን የብራና መጽሐፍ መውሰድን እንጂ የብራናውን መጽሐፍ ፎቶ ግራፍ ማንሣትን እንደ ስርቆት አያዩትም፡፡ አንድ ቱሪስት የሚሠራው ሥራ አድርገው ነው የሚገምቱት፡፡ «ተባበሯቸው» ብለው በሁለት መሥመር የሚጽፏት ደብዳቤ «ሀገሪቱን ይዘርፉ ዘንድ ተባበሯቸው» ማለታቸው መሆኑን ስንቶቹ ይሆን የተረዱት?
አንዳንድ በዲጂታል ሥራው ላይ የተሠማሩ ኅሊና ያላቸው ሰዎች መጻሕፍቱን ካነሡ በኋላ ለመንግሥታዊ እና ሃይማኖታዊ አካላት ስስ ቅጅውን (soft copy) በሚሰጡበት ጊዜ የፍላሹን ማነስ በማየት ኃላፊዎቹ መሳቢያቸው ውስጥ አስቀምጠውት እንደሚቀሩ ያጋጠማቸውን የገለጡ ሰዎችም ነበሩ፡፡
3. ተባባሪ አካላት፡- በቤተ ክህነት፣ በእስልምና ጉዳዮች፣ በአስጎብኚ ድርጅቶች፣ በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቦች አካባቢ የሚገኙ፣ ኅሊናቸውን ለጥቅም የሸጡ ግለሰቦች ሥልጣናቸውን እና መብታቸውን በመጠቀም ይህ የሀገር ሀብት እንዲዘረፍ እያደረጉ ነው፡፡
ባለፈው ሰሞን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚሳደብ እና የሚያቃልል ፊልም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት እንዲሠራ የፈቀዱት የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት መሆናቸውን ማስታወሱ ብቻ የእምነት ተቋማት ለፈረንጆች ለሚጽፏቸው ደብዳቤዎች ጥንቃቄ እንደማያደርጉ ማሳያ ይሆናል፡፡
ያንን ፊልም አንድ አበሻ የሚሠራው ቢሆን ኖሮ መጀመርያ ነገር አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ቢፈቀድለትም እጅግ አሰልቺ ደጅ ጥናት ያስፈልገው ነበር፡፡ የመፈርነጅ አመለካከት የቤተ እምነት መሪዎች አንዱ ችግር ነው፡፡ ስለዚሀም አያሌ የፈረንጅ ዲጂታል ሌቦች ከየቤተ እምነቱ ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን የቤተ እምነቶችን «የትብብር ደብዳቤ» እየያዙ በየገዳማቱ እና አድባራቱ፣ በየመስጊዶቹ እና የመድረሳ ቤቶቹ ካሜራዎቻቸውን አንግተው ሲዘርፉ ይውላሉ፡፡
ከፈረንጅ ጋር መዋል፣ ማውራት፣ መታየት እና ፎቶ መነሣትን እንደ ሊቅነት የሚቆጥሩ፣ ከሊቃውንት ጋር ከመዋል ይልቅ ከፈረንጅ ጋር ሲውሉ ምሥጢር የተገለጠላቸው የሚመስላቸው አያሌ የየቤተ እምነቱ «ፊደል ቆጣሪዎች» እና «እንጀራ ፈላጊዎች» ፈረንጆችን ይዘው በየገዳማቱ ሲዞሩ ታገኟቸዋላችሁ፡፡ ብርቱዎቹ መነኮሳት እና ካህናት፣ ጠንካሮቹ ገዳማውያን ቅርሳችንን አናስነካም ሲሉ በሥልጣናቸው እያስ ፈራሩ አንድ ሊቅ እንዳሉት «የሺ ዓመትን ሀብት በአንድ ፍላሽ የሚያስወስዱ» እነርሱ ናቸው፡፡
ዲጂታል ሌቦች በሀገሪቱ ላይ ሦስት አደጋዎች እያደረሱ ነው፡፡
1/ የመጀመርያው የእነርሱ ባልሆነው ቅርስ እያጋበሱት ያለው ትርፍ ነው፡፡ ባልጻፉት፣ ባልጠበቁት እና መሥዋዕትነት ባልከፈሉበት ቅርስ ፈረንጅ ሆነው ካሜራ ስላላቸው ብቻ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ገበያዎች የሀገሪቱን የጽሑፍ ቅርሶች በዲጂታል እየቸበቸቡ ናቸው፡፡
 ይህንን በቀላሉ ለማየት e bay የተሰኘው የመሥመር ላይ የቅርሶች መሸጫ ድረ ገጽን መጎብኘት ይበቃል፡፡ እዚያ ቦታ የኢትዮጵያ ጥንታውያን ሥዕሎች እና ጽሑፎች ያለ ባለቤቶቹ ፈቃድ እየተቸበቸቡ ናቸው፡፡
2/ ሁለተኛው ደግሞ የባለቤትነት መብቱን መውሰዳቸው ነው፡፡ እነዚሀን ቅርሶች ለማዘጋጀት፣ ለመጠበቅ እና ከአደጋ ለመታደግ የሕይወት ዋጋ የከፈሉት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የአእምሮም ይሁን የንብረት ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ገዳማት እና አድባራት፣ ሊቃውንት እና መምህራን ነው፡፡ ዲጂታል ሌቦች ግን ቅርሱን ብቻ ሳይሆን ባለቤትነቱንም ዘርፈውታል፡፡ የሚያያዙበትም፣ የሚያባዙትም፣ ቅጅ የሚሰጡትም እነርሱ ናቸው፡፡ በዚህም የቅጅ መብቱ (Royal payment) የባለቤቶቹ የኢትዮጵያውያን ሳይሆን ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር የቆረጡት የዲጂታል ሌቦች ሆኗል፡፡
አንዳንድ ምሁራን እንዳስረዱት ሌላው ቀርቶ ዲጂታል ሌቦቹን መዛግብቱ እና መጻሕፍቱ ፎቶ ለተነሣባቸው አካላት እንኳን ቅጅዎቻቸውን እንዲሰጡ የሚያስገድዳቸው ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ለምሳሌ የትግራይን ገዳማት መዛግብት እና መጻሕፍት በዲጂታል ካሜራ የሰበሰበ አንድ ፈረንጅ አለ፡፡ እስካሁን ግን ለገዳማቱም ሆነ ለመንግሥታዊ አካላት ቅጅ አለመስጠቱን የገለጡ ነበሩ፡፡
ይህንን ጉዳይ ዶክተር አየለ በከሪ በጤፍ ምሳሌነት ነበር ያስረዱት፡፡
ጤፍ ለብዙ ዓመታት የበቀለው፣ ጥቅም ላይ የዋለው እና ለዓለም የተበረከተው በኢትዮጵያ ከኢት ዮጵያ ነው፡፡ ሆላንዶች በምርምር ስም ወስደው የጤፍን የተጠቃሚነት መብት (patent right) አወጡ፡፡ አሁን የጤፍ ዓለም ዐቀፍ ተጠቃሚዎች ሆላንዶች እንጂ ባለቤቶቹ ኢትዮጵያውያን አልሆኑም፡፡ በጥንታውያን የጽሑፍ ሀብቶቻችንም ላይ የሆነው እንደዚሁ ነው፡፡
3/እነዚህ በምርምር ስም የሚነቃነቁ አካላት እንዴት ዲጂታላይዝ ማድረግ እንዳለባቸው የወጣ ሕግም ሆነ የአሠራር ደረጃ ባለመኖሩ መዛግብቱን እና ጽሑፎቹን ለእነርሱ በሚያመቻቸው መንገድ እያገላበጡ ያነሷቸዋል፡፡ ለጽሑፎቹ ደኅንነት እና ጥንቃቄ አይጨነቁም፡፡ በመተሻሸት፣ በመላላጥ እና በመገላበጥ ለሚደርስባቸው አደጋ ተጠያቂ አይሆኑም፡፡ ይህ ደግሞ እነርሱ ቅርሱን ሲዘርፉ እኛ ግን የቅርሱ የነጡ ድኾች እንድንሆን ያደርገናል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የመጡት ዶክተር አሕመድ ሐሰን «ቆዳን እድሜህ ስንት ነው ቢሉት ቅቤን ጠይቁት አለ» ብለው ተርተው ነበር፡፡ ቆዳ ይህንን ያለው የቆዳን እድሜ የሚያስረዝመው በቅቤ መታሸቱ ስለሆነ ነው፡፡ አሁንም የእነዚህ ጥንታውያን የጽሑፍ ሀብቶቻችን እድሜ ማጠሩ እና መርዘሙ በእኛ ላይ የተመሠረተ ነው ሲሉ ገልጠውት ነበር፡፡
  ምን ይደረግ?
ዲጂታላይዜሽን ጥንታውያን መዛግብትን እና ጽሑፎችን ለመጠበቂያ፣ ለመጠቀሚያ እና ከአደጋ ለመከላከያ ከሚውሉ ዘመናውያን ዘዴዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን በሠለጠነ ባለሞያ፣ በተቀላጠፈ እና በተጠናከረ አሠራር፣ እና ተገቢ በሆነ ሕግ ሲመራ ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል፡፡
እናም ይህንን ችግር ለመከላከል በወቅቱ የነበሩ ባለሞያዎች እና መንግሥታዊ አካላት የሚከተሉትን መፍትሔዎች ጠቁመው ነበር፡፡
 • ማኅበረሰቡ ስለ ዲጂታላይዜሽንን ጥቅም እና ጉዳት የሚያውቅበትን መንገድ መፈለግ
 • ጉዳዩ የሚመለከታቸው የእምነት ተቋማት፣ የባህል ቢሮዎች፣ የቅርስ መሥሪያ ቤቶች፣ አስጉብኚዎች፣ የጉምሩክ ባለሞያዎች፣ የፖሊስ እና ወታደራዊ አካላት፣ የገዳማት እና አድባራት፣ የመስጊዶች እና መድረሳ ቤቶች ኃላፊዎች፣ አባቶች  እና መምህራን ስለ ጉዳዩ ዐውቀው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስተማር
 • የፈቃድ ሰጭ የመሥሪያ ቤቶች አሠራር የደዲጂታል ተጠቃሚነትን እንጂ ስርቆትን በማያበረታታበት መንገድ እንዲቃኝ ማድረግ
 • የጥንታዊ ጽሑፎችን ዲጂታላይዜሽን በተመለከተ ራሱን የቻለ ሕግ ማውጣት፡፡ በሕጉም ለማን ይፈቀዳል? ማን ይፈቅዳል? በምን ዓይነት ሁኔታ? የባለቤትነት መብት፣ የቅጅ መብት፣ ቅጅ የማግኘት አሠራር፣ በምን ዓይነት ጽሑፎች ላይ ይፈቀዳል፣ የአሠራር ደረጃው ምን መሆን አለበት? ከሀገር ከወጡ በኋላ ያለውን ክትትል፣ የሚመለከቱ ጉዳዮች እንዲካተቱ ቢደረግ
 • ቢያንስ ሕግ እስኪወጣ ድረስ አሁን በየቦታው ተሠማርተው መጻሕፍቱን እና መዛግብቱን ፎቶ እያነሡ ያሉትን አካላት ማቀብ ቢቻል
 • በደቡብ አፍሪካ ማሊዎች በቲምቡክቱ አካባቢ እንዳደረጉት እኛም የራሳችን የዲጂታላይዜሽን ማዕከል በሀገራችን ብንከፍት ሥራውን በራሳችን ሰዎች እኛው ለመሥራት የምንችልበት መንገድ ይፈጠር ነበር፡፡ በርግጥ በዚህ ላይ ሁለት ችግሮች መከሰታቸውን አጥኚዎቹ ተናግረው ነበር፡፡ የመጀመርያው እኤአ 2010 ታኅሣሥ ወር ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ተደርጎ የነበረው የአፍሪካ የጥንታውያን ጽሑፎች ጉባኤ የምሥራቅ አፍሪካ የዲጂታላይዜሽን ማዕከል በአዲስ አበባ እንዲቋቋም ወስኖ እና ድጋፍ ለማድረገም ቃል ተገብቶ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች መተከል ያለበት እኔ ነው እያሉ ሲከራከሩ ሁለት ዓመት አለፈ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተተከለ፣ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ግቢ ሁሉም ያው አዲስ አበባ ነበረ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ሀገራዊ ራእይ አጥተን ሌሎች ዕድሉን እንዳይወስዱት ያሰጋል፡፡
ቀማኛ ሲጣላ
ተስማምቶ እንዳይበላ
መንትፋቸው ሄደች ዘዴኛ ቡችላ
ይል ነበር «ተረት በሥዕል» የተሰኘው የልጆች መጽሐፍ፡፡
ሁለተኛው ችግር ደግሞ ሥራዎችን ሁሉ በውጭ ድጋፍ ብቻ የማሰብ የመፈርነጅ ችግር ነው፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ዩኔስኮ፣ ዩኤስ አይዲ ካልገቡበት ገባሬ ሠናይ ቄስ እንደጠፋበት ቅዳሴ ሥራው ይተጓጎላል ብሎ የመስነፍ አመለካከት አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህን የመሰለውን ከታሪካቸው፣ እምነታቸው እና ማንነታቸው ጋር የተሣሠረ ተግባር ለማከናውን ግልጽ፣ ከዘረኛነት እና ፖለቲካዊ ወገንተኛነት የጸዳ አሠራር እስከተዘረጋ ድረስ ሕይወታቸውን ጭምር የሚሰጡ መሆናቸው የተረሳ ይመስላል፡፡
·         በገዳማት እና አድባራት ርዳታ እና ሥራ ላይ የተሠማሩ አያሌ ማኅበራት በኢትዮጵያ አሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት መዛግብቱ እና መጻሕፍቱ ለሚገኙባቸው ቦታዎች ቀረቤታ አላቸው፡፡ በመሆኑም ግንዛቤው እንዲኖራቸው ቢደረግ በሚጓዙበት ቦታ ሁሉ ዕውቀቱን የማስፋፋት ዕድል ይኖራቸው ነበር፡፡
·         በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ የሞቱ መዛግብት(dead files) ተብለው[3] የተወረወሩ ነገር ግን የሀገሪቱን ታሪክ የያዙ ጽሑፎች፣ ደብዳቤዎች እና መዛግብት ወደ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ እንዲላኩ ቢደረግ
በአጠቃላይ ዘመናዊነት ዘመናዊ አኗኗርን ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ስርቆትንም አምጥቷል፡፡ ይህ ዘመናዊ ስርቆት ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ያለ ጥንታዊ ሀብት እና መሠረት የሚያስቀር ነው፡፡ አውሮፓውያን 16 እና 17 ክፍለ ዘመን የሕዳሴውን መንገድ ሲጀምሩ ወደ ጥንታውያን ዕውቀቶቻቸው፣ ትምህርቶቻቸው እና አስተሳሰቦቻቸው በመሄድ አስቀድመው እነዚያን ነበር የመረመሩት፡፡ የጠፉባቸውንም ከዓረብ እና ከአፍሪካ እየፈለጉ በማሟላት ወደ ኋላ ተንደርድረው ወደፊት ተፈትልከዋል፡፡
እኛም ዛሬ እንራመድበታለን ብለን ለምናስበው የሥልጣኔ ጎዳና መንደርደርያዎቻችን እነዚሁ መጻሕፍት እና መዛግብት በመሆናቸው ተዘርፈው ከማለቃቸው በፊት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃልም ተናጋሪ ሆነን ልንነሣ ይገባል፡፡ ዛሬ አንዱ ሲሰረቅ ዝም ካልን እየደጋገሙ እንዲዘርፉ ፈቅደናል ማለት ነው፡፡
አንድ ተሰብሳቢ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ «ሰውዬው ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ዳዊት ሰረቀ፡፡ ካህናቱ አዝነው ዝም አሉ፡፡ አላወቁብኝም መስሎት በድጋሚ ሊሰርቅ መጣ፡፡ ያን ጊዜ ቄሰ ገበዙ «አያ እገሌ ዳዊት ልትደግም መጣህ እንዴ? አሉት ይባላል፡፡»

[1] ዲጂታላይዜሽን የሚለውን ቃል እንዳለ በእንግሊዝኛው የወሰድኩት እርሱን ወደ አማርኛ ሊመልስ የሚችል ቃል አጥቼ ነው፡፡ ያማከርኳቸውም ጥቂት ቀናት ለምነውኛል፡፡ ምናልባት እግዜር ቢፈቅድ ተባብረን እናገኝለታለን፡፡


[2] «መፈርነጅ» ማለት፡ ሁሉን ነገር ለፈረንጅ መስጠት፣ ደግ ፈረንጅ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ፤ ለፈረንጅ ልዩ ትኩረት መስጠት፣ ፈረንጅን መከተል፣ ፈረንጅን ብቻ ማድነቅ፣ ለፈረንጅ ሁሉን ክፍት ማድረግ፣ ማለት ነው፡፡

[3] ሕጉ 25 ዓመት በፊት የተጻፉ መንግሥታዊ እና ድርጅታዊ መዛግብት እንደ ጥንታውያን ጽሑፎች ተቆጥረው ወደ ኤጀንሲው እንዲላኩ እንደሚያዝ ሰምቻለሁ

35 comments:

 1. ዲ.ዳንኤል በጣም ጥሩ እይታ ነው፡፡ .....ይሄ ፎቶ የማንሳት/ዲጂታላይዜሽን ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ የጥንቱን ሃይማኖታዊ ቅርስ ብቻ ሳይሆን በቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮ የሚፈጽመውን ህዝበ ክርስቲያንና ስርዓተ ቅዳሴውን በሚያውክ ሁኔታ የሚደረገው ፎቶ የማንሳት ባህል በቁርጠኝነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ዳንኤል ቤተክርስቲያን የምትጠብቅብንን ሀላፊነት እንድንወጣ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላዕክት ተራዳኢነት፣ የቅዱሳን አባቶች ጸሎት አይለየን፡፡ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ይጠብቅ፡፡

   Delete
  2. It is really a very important issue.I work in Tour and Travel Agency.I have seen many problems on this situation.There must be a strong awareness in Tour and Travel Agencies.Most of tourists come through them.If the main concerned body doesn't work with them,we definitely lose many.

   Delete
  3. አሜን፡፡

   Delete
 2. ድጅታላይዜሽን - በቁጥር ማመስጠር

  ReplyDelete
  Replies
  1. tiru new endezih metegagez melkam newena

   Delete
 3. ድጅታል ካሜራ - በቁጥር አመስጣሪ መቅረፀ ምስል

  ReplyDelete
 4. I have waited long to read this article. God bless you. It is verily informative. All the churches need to be aware of the digital theft and this is a responsibility to every Ethiopian.

  ReplyDelete
 5. Hi dani. "yeshi amet kirs be and(1) flash?". We must stand united and z govt must take a swift and decisive action NOW!

  ReplyDelete
 6. ዲ/ዳንኤል እግዚአብሔር ረጅም እድሜ ያድልህ……………መልካም እይታ ነው…………….አባቶቻችን በመከራ ያቆዩልንን ትልቅ ቅርስ እንደዋዛ እያጣነው ነው…………ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥበቃ የሚያሻው ጉዳይ ነው……………….ለጥቅም ያደራችሁ እባካችሁ ታሪክና ቅርሶቻችንን አሳልፋችሁ አትስጡብን!! እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

  ReplyDelete
 7. ዳኒ እናመሰግናለን፡፡ ሁሌም የምታነሳቸው ሃሳቦች እጅጉን ያማሩና የሚያስተውል ቢገኝ ጥቅማቸው የትየለሌ ናቸው፡፡ ይህ ፈረንጅን የማመን ወይም የማምለክ አባዜ በሕዝባችን አዕምሮ ሰርፆ እነዲገባ ያደረገው ነገር እያንዳንዱ የምንሰማው ሬድዮ፤ የምናየው ቴሌቭዥን ፤ የምናነበው ነገር እንዲሁም በየስብስባው የኛነታችንን አሻራ የሚከድን የፈረንጆቹን ነቁጥ የሚያጎላው አኛነታችን ነው፡፡ ሃገራችን በተለይም ቤተክርስቲያን ያፈራቸቸው ጠበብት አያሌ ሆነው የሚነገርላቸው በዙ እያለ ነገር ግን እድሜ ልካችንን የሚነገረን ስለነ አርስቶትል ሶቅራጥስና ሼክስፒር አባባሎችና ፍልስፍናዎች ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በዋናነት ፈረንጅ ብቻ ልክ እኛ ደግሞ ገልባጭ እንጂ የራሳችን ምንም የሌለን ምንዱባን መስለን እንድንታይ እያደረገን ነው፡፡ እንደውም አድርጎናል፡፡ ስንክሳር፤ የቅዳሴ መጻሕፍት፤ የዜማ መጻሕፍት፤የፀሎት መጻሕፍት እና ሌሎቹም ያላቸው ሥነ ጽሑፋዊ ይዘት ከነ ሼክስፒር ልብ ወለድ መጻሕፍት እልፍ ግዜ ይበልጣሉ፡፡ መንፈሳዊ አንድምታቸው እንኳ ቢቀር፡፡ ስለዚህ ለጊዜያዊ ጥቅም እየተባለ የሃገርን እና የህዝብን ሃብት እንደቀልድ አሳልፎ መስጠት ኋላ ሰማይ ብንቧጥጥ እንኳ የማናገኘው ነው፡፡ የራሳችንን በራሳችን ልንጠቀምበት ይገባናል ባይ ነኝ፡፡ ምንም እንኳ ልቦለድ ቢመስልም ዴርቶጋዳ በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩት ነገር ውስጤ እንዲነድ አድርጎኛል፡፡ ጀርመን ዛሬ የዓለማችን ቁጥር አንድ የመድሃኒት አምራች ለመሆኗ ቁልፉን የተጫወተው ከሃገራችን አንዱ ገዳም የተዘረፈ ስለመድሃኒት አዘገጃጀት ከተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ አስነብቦኛል፡፡ ተመልከት ዳኒ እንዳለከው የጤፍ ባለቤቷ እኛ ሆነን ሳለ ሆላንዶች ባለመብት መሆናቸው የማያንገበግበን ሆነናል፡፡ ነገ ደግሞ ሉሲ ሃገሯ ድረስ መጥትው እንዲጎበኟት ማድረግ ሲቻል ፈረንጆቹ ለምን ይደክማሉ በሚል እሳቤ አሉበት ድረስ ሄዳላቸዋለችና አሜሪካኖቹ ደግሞ የባለቤትነት መብት ለኛ ይገባናል እንዳይሉ እሰጋለሁ፡፡ ቢሉስ ማን ይከለክላቸዋል?(በርናባስ)

  ReplyDelete
 8. Dear Dani;

  I don’t think the problem is the absences of rules, regulations & policy documents.

  The issue here is morality & patriotism.

  Look at the current religious leaders at every level. They are not different from any political appointees. They don’t only luck the spiritual elements but also they are obsessed with worldly lusts.

  Thus, unless, we address the morale & spiritual issues of the matter, I don’t think any earthly law would prevent the theft & exodus of historical & other valuable elements from ETHIOPIA.


  AND GOD BLESSES HITORIC ETHIOPIA!!!

  ReplyDelete
 9. Ohhhhhh, my Gastrites started. what shall we do? Please God help Ethiopia, for our fore fathers sake.

  ReplyDelete
 10. ቃለ ህይወት ሰማልን
  ችግሩን በአግባቡ ተመልክተኸዋል፡፡ አሁን ለማምጣት እያንዳንዳችን መነሳት ይገባናል፡፡ በየገዳማቱ ለጉብኝት የሚመጡ ነጮች በሙሉ ችግር አለባቸው ለማለት ቢከብደኝም አብዛኛዎቹ ቅሰጣ ይበዛባቸዋል፡፡ የእኛ ሰው ደግሞ ነጭ ሲያይ ጥርጣሬው ብዙ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ ውስጣቸው እንደመልካቸው እንዳልሆነ ግን በብዙ ነገር አይቻለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ ለሐበሻ ያላቸው አመለካከት አደገኛ ነው፡፡
  እናም ምዕመናን ችግሩን ተገንዝበን ብንጠነቀቅ፡፡ ገዳማቱም ጥበቃውን ይዘው የኖሩ አባቶቻችንን አደራ ለልጆች ለማስተላለፍ ይልቁንም ዛሬ የበለጠ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡
  በግልጽ ከሚካሄደው በተጨማሪ ስውር ካሜራ(ማይክሮ ሪከርደርስ) በመጠቀም የሚቀርጹትን ደግሞ እግዚአብሐየር ይቁጠረው፡፡
  በድጋሜ ቃለ ሕይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 11. dikon daniel betam tiru neger new yanesahew hulum ybetekirsitiyan akalat lirebarebubet yegebal endihum yemengist akalatim lirebarebubet yigebal. kirsochachin eyetefunewna.

  ReplyDelete
 12. temhert azel bemhonu wedegwalew

  ReplyDelete
 13. kala heiwate yasamalen

  ReplyDelete
 14. dear..daneal, really what you rise the best idea every body who think and measure.. especially legislative bodies..we lost Excellence of taste in fine arts and humanities...symbols that relate humanity to spirituality and, sometimes, to moral values.to sell others week up now!
  ayele,bahir dar

  ReplyDelete
 15. thank you.
  those all previous work enables us to project our success to the future; so what ever the work is it should be maintained.
  thank you Dn.Dani once more

  ReplyDelete
 16. Be'abatu ketema lijiyew tekema.
  Edme le ehadig

  ReplyDelete
 17. Egziabher yistilin, Dn Daniel. Betely beTigray akebabi yalu yebetekiristiyan kirsoch yihe mengest hizbu minim ayametam bemalet hizbu bemenak yimesil sile kirsoch, sile betekiristiyan gid yelesh hunewal. Yetagelnew leHizb new eyalu neger gin yehizb yemenetu maninent yehonu kirsoch kaltebeku min waga alew. Bekirb gize bewaldiba betekiristiyan afrisen limat eniseralen eaylu nachew. Kezih befitim leketema plan tebilo beMekele ye Abune Gebremenfeskidus tsebel afirisiwo dildil sertewal. Ere ebakachihu yemengist na yebetekihinet balesiltanat nen yemitilu lib gizu. Betely Yebetkihinet balesiltanat min eyeserachihu new? Betekiristiyan sifers, kirs sibezebez zimbilachihu eyayachihu new. YeEgziabher tigistu bizu new sibeza gen bemeatu endemiyatefachihu atizengu. Yezih hulu tiliku chigir me'emenanin yedirishachin mewetat alichalinim. Betekiristiya sikatel sifers zimbilen eyayen, minim ayametum bile new mengist yihe hulu gife bebetekiristiyan yemifetsimew. Neger gin Dimtsachin binachoch ye'eyariko ginb yaferese amlak yezim mengist besiltan memekatu endemiyafersew aminalehu. Lehulum Egziabher Lemengistim, Leabatochachinim, Legna miemenanim libona yisten.

  ReplyDelete
 18. ሰላም ላአንተ ይሁን! መልካም ጅምር "የአሳ ግማቱ ከችንቅላቱ" የቤተ ክርሰተያአን አባቶች የመንግሰት ባለስልጧኖች መፈክራቸው ያለውን ማውደም በቻይና እቃ መተካት እኒ ከሞትኩ ስርዶ አይብከል አደል እነዴ፣ ሌላው ባልሙያ የሚባሉት ለምሳሌ ከወመዘክር ካአዲስ አበባ ዩኒበርሰቲ ሙዚየም ጥንታዊ መሳሃፍትን ሲያሳዩ የራሳቸውን ማስታወሻ እንኩአን እንደዛ አያገላብቱም expert ቢሆኑ ኖሮ ሊላው ይቅር ጉዋንት ያረጉ ነበር እግዚአብሄር ይሁነን

  ReplyDelete
 19. «ሀገሪቱን ይዘርፉ ዘንድ ተባበሯቸው» ማለታቸው መሆኑን ስንቶቹ ይሆን የተረዱት?

  ReplyDelete
 20. ሳሚ ወ/ሚካኤልMarch 12, 2012 at 11:00 AM

  ኡሁሁሁሁሁሁ…ምን ልሁነው ኢትዮጵያየ አልቅሸ እንዳልቀብርሽ የናት ሞት ህመሙን አውቀዋለሁ! በዚያ ላይ የቲም ሁኘ የምወድቅበት መዳፍ አንችን የገደለው ነጭ መዳፍ ነውና ለሱ በባርነት ተሰጥቸ ያንችኑ ሃብት ከምቀላውጥ ይልቅ አንችው ኑረሽ ከነጠፈው ሞሰብሽ ስር በድህነት መቆራመትን መረጥሁ! ቆይ ግን እማማየ የሲኦል ደጆች ላይችሉሽ በቤተክርስቲያንሽ በኩል የተገባልሽ ቃል ኪዳንሽ የት ደረሰ? አስራት ተደርገሽ የተሰጠሻት ንግስትስ ወዴት አለች?? በመቅደስሽና በመጻኅፍቶችሽ ላይ ያለው የአምላክሽ ቃል ሲደፈር የለለ እስኪሆን ድረስ ባለቤቱ እንዴት ረሳሽ??! በወንጌል ምሳሌ የምናውቀው ስንዴ በተዘራበት እርሻ ውስጥ ጠላት እንክርዳድ ሲዘራ ነው! ባንች ምድር እያየነው ያለነው ግን የሚዘራውም እየበቀለ ያለውም እንክርዳድ ትውልድ ነው! ዳቦ ሆነው የሚያጠግቡን ስንዴዎችሽ ማን በላቻው?? ባህር ከፋይ አምላክሽ ጠላትን ሲመለከት እኛን ግን ለምን ረሳን ለምንስ አልተመለከተንም??? አዎዎዎዎ ልጠይቅሽ ብየ እንጅ ይህ የሆነበትን ምክንያት በቅዱሳን መጻህፍቶችሽ አቀዋለሁ!! የህዝብሽ ሃጥያት መብዛቱ ለጽዮኒቱ መቅደስ መማረክ ምክንያት ነው!!! በዘር በጎሳ ተከፋፍለን ያነደድነው እሳት የራሳችንን ፊት ለበለበን!!! አምላክሽ ካልተመለከትን በቀር የተደበላለቀውን ቁዋንቁዋ መልሶ የሚያግባባን ከወዴት ይመጣል??? እሱ ብቻ መፍትሄሽ እሱ ብቻ መድሃኒትሽ! ትንሳኤሽ በኅዝብሽ በደል ተቀብሮዋልና በንስሃ አካፋ የትንሳኤሽን ብርሃን እንገልጥ ዘንድ የእግዚአብሄርንን ቃል እየነገሩን ያሉትን ጦማሪ መምህራኖቻችንን ሰሚ ጆሮ ይስጠን!! አቤቱ አንድ አድርገን!!!!!!!!!!!!! አቤቱ የሆነብንን አስብ! አህዛብ ውደርስታችን ገቡ! የቅዱሳኑን መጽሃፍ ለነጭ አሞሮች የመቅደስህን ቅርሶችም ለአውሮፓ አራዊት ሰጡ!!!አቤቱ ወደኛ ተመልከት! ረድኤታችን ሰማይና ምድርን ከፈጠርክ ካንተ ነውና ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና!!!!!!

  የሰመራው

  ReplyDelete
 21. Dani, thank you for this important article.

  we Ethiopians shall give respect to ourselves,our people ,our property and our country.if we don't respect all of those things we are always the looser. let me share you what happened to me before two months.am working in x private company. my work mate is a foreigner, together for work matter we have gone to METEC(Metal Engineering Corporation) at the gate as usual the guard checked us and he asked me to put my cellular phone and i gave him with my identity card but he let the foreigner pass with his telephone. after that day whenever i go with that foreigner before i reach to the gate i always give my telephone to him,and no one will ask him to put it at the gate and am doing like that afterwards. what i see, they are trusting him but not me,am an Ethiopian but he is a foreigner who of us will think for the country security is he? i wonder.

  ReplyDelete
 22. የቤተ ክህነትና የየአጥቢያው አገረ ስብከቶች ምን እየሰሩ ነው??????

  ReplyDelete
 23. እግዜር የመንግሥት አካላትን አዕምሮ ከፍቶልህ የወጡት ህግጋት ሁሉ በስራቸው ለመጠቀም እንጂ የመቅጫ ምክንያቶች እንዳልሆኑ ለመንፈሳውያኑ መሩዎች ደግሞ ለአባቶቼ የተገለጠላቸው የእምነት ምሥጢር እንዲገልጥላቸው በእውነት በእውነት እመኝሃለው፡፡ አሊያ አንተንም ከተናጋሪነት እኛንም ከአንባቢነት አያዘልለንም፡፡

  ReplyDelete
 24. thanks Danny for your view !!!

  ReplyDelete
 25. thank you Dani I agree with you .በጥናት እና ምርምር ስም ወደ ሀገር የሚገቡ ፈረንጆች፡፡ እነዚህ ሰዎች ጥናት እና ምርምር እናደርጋለን፣ ጥንታዊ ጽሑፎችን ዲጂታላይዝ እናደርጋለን እያሉ ወደ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ የሚመጡ ናቸው፡፡ ከመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች እና ከእምነት ተቋማት ፈቃድ አግኝተው በየታሪካዊ ቦታዎች በመዘዋወር መጻሕፍቱን እና መዛግብቱን ፎቶ የሚያነሡ ናቸው፡፡

  ReplyDelete
 26. I am confused what the role of the government is!anyways `jIB KEHEDE WUSHA CHOHE` HONE ENJI,let`s unite together and do some thing.

  ReplyDelete
 27. Selam all;
  I am not sure that I get your message clearly.
  1) If the books are not digitalized we will loose them all at least by the fire we have been witnessing from blogs and MK websites.

  2)If the ferenjis do not take a copy they will definitely take the original as they did in the pre-digitalization era.

  3) If we are unhappy that the ferenjis sell the copy at e-bay MK and other EOTC church orgs can take effective counter-measure. Post the digital forms of the books on the EOTC websites for free.

  ReplyDelete
 28. Dear Dn Daniel,
  Thank you for your observation and shared us this worth information.

  ReplyDelete
 29. ዳኒ እንደምን ሰነበትክ?
  ስለ ዘቓላ ገዳም እያደረክ ስላለህው ማስተባበርና ጥረት እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ።
  አሁን የምጽፈው digital እና digitization ለሚሉት ቃላት የመሰለኝን ለምሰንዘር ነው። digit እና digitus ቃሉ ላቲን ሲሆን ትርጉሙም የእጅ ጣት ማለት ነው። ከዚህ ተንስቶ digital በሁለት በሁለት ቁጥሮች በመወክል መረጃን የመቀየር ስልት ነው። ክዚህ ተንስተን ዲጂታል ለሚለው "ጥምር አሃዝ" አንዲሁም ዲጂታላይዜሽን ለሚለው "ውደ ጥምር አሃዝ ልወጣ" የሚል ፍቺ ይስማማው ይሆን?
  እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
  ሙሉጌታ ሙላቱ
  ቫንኹቨር ድሴት

  ReplyDelete