© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡ በሌላ መሰል ኅትመት ባይወጣ ይመረጣል፡፡
«ከተራበ ይልቅ ለጠገበ አዝናለሁ» ይሉ ነበር አጎቴ፡፡ ለምን ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ «ሰው ተርቦ ከሚደርስበት ጉዳት ጠግቦ የሚደርስበት ጉዳት ይበልጣል» አሉኝ፡፡ «ሰው ጠግቦ ጉዳት ያደርሳል እንጂ ምን ጉዳት ይደርስበታል?» አልኳቸው፡፡ «እርሱኮ ነው ጉዳቱ፡፡ በሰው ላይ ጉዳት አደርሳለሁ ብሎ የሚመጣበት ጉዳት፡፡ ለተራበ ሰው ውድቀት ማለት ከመጀመርያው ደረጃ እንደ መውደቅ ነው፡፡ የጠገበ ሰው ውድቀት ማለት ግን ከመጨረሻው ደረጃ አጓጉል እንደ መውደቅ ነው» አሉ፡፡
ይህ የእርሳቸው አባባል የሕንዶችን ታሪክ ያስታውሰኛል፡፡ ሕንዶች ረሃብም ሆነ ጥጋብ ሁለቱም እኩል ይጎዳሉ ይላሉ፡፡ ረሃብ እና ጥጋብ ሁለቱም የጤንነት፣ የደኅንነት እና የሰላም ዕንቅፋቶች ናቸው ብለውም ይጨምሩበታል፡፡ ረሃብ እና ጥጋብ ሀገርን እኩል ነው የሚጎዷት ሲሉም የሚከተለውን ይተርካሉ፡፡