Wednesday, February 29, 2012

የሁለት ቤት ምክር


ከአማራ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡
የፍየል እና የነብር ግልገሎች በአንድ ሜዳ ላይ አብረው ሲጫወቱ ዋሉ፡፡ ማታ ሁለቱም ወደ የቤታቸው ገቡና ለእናቶቻቸው ውሏቸውን ነገሯቸው፡፡ «እማየ» አለ የነብር ግልገል፡፡ «ዛሬ ወደ ኋላ የተቆለመመ ቀንድ ካለው፡፡ ከኋላው ላይ በቆዳ የተሸፈነ ሥጋ ነገር ከተንጠለጠለበት፤ ሲጮኽ ሚእእእእእእ ከሚል ግልገል ጋር ስጫወት ዋልኩ፡፡ እንዴት ጨዋታ ዐዋቂ መሰለሽ»፡፡
 እናት ከንፈሮቿን በምላሷ አራሰችና «የኔ ሞኝ እኔ እናትህ ቀኑን ሙሉ ስንከራተት የምውለው ምን ፈልጌ መሰለህ፤ እርሱን ፍለጋኮ ነው፡፡ ለመሆኑ ከማን ጋር እንደዋልክ ታውቃልሀ?» አለችው፡፡
ግልገሉ ባለማወቅ አንገቱን ነቀነቀ፡፡
«ሲበሉት ከሚጥመው፣ ሲቆረጥሙት አንጀት ከሚያርሰው ከፍየል ግልገል ጋርኮ ነው»
ግልገሉ በፀፀት አንገቱን ነቀነቀ፡፡
«በል ነገ አብራችሁ የምትጫወቱ መስለህ አንገቱ ላይ በጥርስህ ትጨመድድና እየጎተትክ ታመጣዋለህ» አለችው፡፡ ተቀበለ፡፡ መሸም፡፡
በፍየልም ቤት እንዲህ ነበረ፡፡
«ዛሬ እማዬ ዝንጉርጉር መልክ ካለው፣ ቁመተ ሎግላጋ፣ ሲስቅ ድመት ከሚመስል፣ ረዣዥም ጥፍር ካለው ልዩ ግልገል ጋር ስጫወት ዋልኩ» አላት፡፡ ክው አለች እናቱ፡፡ አሁን የመጣ መስሏትም በግራ በቀኟ ገልመጥ ገልመጥ አለች፡፡ ይሰማት ይመስል ወደ ግልገሏ ጆሮ ተጠግታ
«ከማን ጋር እንደዋልክ ታውቃለህ?» አለቺው፡፡
አንገቱን ወደ ቀኝ እና ግራ ወዘወዘ፡፡
«እርሱኮ የነብር ግልገል ነው፡፡ የነብር ግልገል የነብር ልጅ ነው፡፡ እኔ ነፍሴ እስክወጣ ስሸሽ የምውለው ከርሱ አይደለም ወይ፡፡ የነብር ዓይን ወደ ፍየል የፍየል ዓይን ወደ ቅጠል የሚባለውን አልሰማህም ወይ
ግልገሉም ዕጢው ዱብ አለ፡፡ እዚያው ባለበት ቀዘቀዘ፡፡
«ታድያኮ ነገም ልንጫወት ተቀጣጥረናል» አላት፡፡
«ከነብር ጋር መጫወት ከሞት ጋር መጫወት ነው፡፡ የኛን ዘሮች አድነው የፈጇቸው የርሱ አያቶች እና ቅድመ አያች ናቸው፡፡ ስለ ነብር ስንት ተዘፍኗል፤ ስንት ተተርቷል፡፡ ስንት ተብሏል፡፡ ዛሬ ዛሬ ነው ትንሽ ተንፈስ ያልነው ልጄ፡፡ ምንም ቢሆን የትናንቱን አትርሳ፡፡ አንተ ተደብቀህ ለብቻህ ተጫወት፡፡ በድንገት ካየኽው ሽሽ፣ ከተከተለህም ሮጠህ አምልጥ» አለቺው፡፡
እህ በሚል ስሜት አንገቱን ወደላይ እና ታች ወዘወዘ፡፡ መሸም፡፡
በማግሥቱ የፍየሉ ግልገል ቀስ ብሎ ግራ ቀኝ እያየ ወደ መስክ ወጣ፡፡ ምንም ነገር የለም፡፡ እየፈራ እየቸረ ቅጠል መቀንጠስ ጀመረ፡፡ ጥቂት እንደቀነጣጠበ ድምፅ ሰማ፡፡ ዘወር ሲል የነብሩ ግልገል ወደርሱ እየመጣ ነው፡፡ ፊቱን ወደ ነብሩ ግልገል አዙሮ ወደ ኋላው ማፈግፈግ ጀመረ፡፡
«የት ትሄዳለህ? እንጫወት እንጂ» አለው የነብሩ ግልገል
«አይ እናቴ ትፈልገኛለች፤» እያለ ወደ ኋላው ማፈግፈጉን ተያያዘው፡፡
«ትናንት ለዛሬ ተቀጣጥረን አልነበረም እንዴ» የነብሩ ግልገል ጠየቀ፡፡
«ተቀጣጥረን ነበር»
«ታድያ ለምን ትሸሻለህ »
«አየህ እናንተ ቤት የተመከረው ምክር እኛም ቤት ተመክሯል» አለውና ፈረጠጠ፡፡
ዛሬ ዛሬ በየኮሌጆቻችን እና ዩኒቨርሲቲዎቻችን የሀገሬ ልጆች በሁለት ቤት በሚመከር ምክር ተጠምደው ይታዩኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የነብር እና የፍየል ግልገል አብረው የሚውሉባቸው ተቋማት መሆን ነበረባቸው፡፡ ነብርም አዳኞቹን ፍየልም አራጆቹን ሳይፈራ፣ ፍየል በነብር ሳይጠቃ፣ ነብርም በፍየል ጌቶች ሳይታደን የሚውሉበት መስክ  ነበረ፡፡
ግልገሎቻችን ግን ለዚህ አልታደሉም፡፡ አማራው ለብቻው፣ ትግሬው ለብቻው፣ ኦሮሞው ለብቻው፣ ሶማሌው ለብቻው፣ ወላይታው ለብቻው፣ ሲዳማው ለብቻው፣ አፋሩ ለብቻው፣ ሌላውም ለብቻው ሲመክርበት የሚያድር ቤት እየሆነ ነው፡፡ መምከሩ ብቻውን ደግሞ ባልከፋ፡፡ የሚመከረው ስለ ሌላው መሆኑ እንጂ፡፡ እገሌ ጠላትህ ነው፣ ጨቋኝህ ነው፣ የሚንቅህ ነው፣ ከርሱ ራቅ፣ አብረህ አትዋል፣ አብረህ አትጠጣ፣ በርሱ ቋንቋ አትናገር፣ እየተባለ ነው ሲመከር የሚያድረው፡፡
በሀገሪቱ የመጀመርያው ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ሲቋቋም በአሮጌው ሕንፃ ግድግዳ ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ ነበረ፡፡ «ኩሎ አመክሩ ወሠናየ ግበሩ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም» ያዙ፡፡ የትምህርት ተቋማት መርሕ ይሆን ዘንድ ነበር የተለጠፈው፡፡ ታድያ ይህ ጥቅስ ሁሉን የሚፈትን ሳይሆን የራሱን ብቻ የሚያይ፣ ሌላውንም በጥላቻ የሚቃኝ፣ ብሎም ስለ ሌላው የነብር እና ፍየል ምክር በየጎሬው ሲመክር የሚያድር ተማሪ ሲያይ ምን ይል ይሆን»
የነብሩም የፍየሉም እናቶች ለግልገሎቻችው የነገሯቸው የእነርሱን ቁርሾ ነው፡፡ፍርሃታቸውን ነው፡፡ የነብር እና የፍየል ግልገል አብረው የመዋላቸው ጥቅም አልታያቸውም፡፡ አብረው የመዋላቸው አዲስ ታሪክ አልተሰማቸውም፡፡ አብረው የመዋላቸው ሀገራዊ ጠቀሜታ አልተዋጠላቸውም፡፡
ምንጊዜም ትውልድ ካለፈው የተሻለ ካላሰበ፣ ያለፈውን ችግር ፈትቶ፣ የተሻለ ዓለም ካላሳየ ትውልድነቱ ምኑ ላይ ነው? ግልገሎቹ ለየብቻ፣ ያም በጉሮኖው ይኼም በዋሻው የተመከረውን ብቻ የሚያስፈጽሙ ከሆነ እነዚህ አሮጌ ግልገሎች እንጂ አዲስ ትውልዶች እንዴት ይሆናሉ፡፡
ለመሆኑ ስለ ኦሮሞ ጉዳይ ኦሮሞዎች ብቻ መነጋገር፣ መምከር፣ መጨነቅ አለባቸው? የኦሮሞ ጉዳይ የአማራ፣ የትግሬ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የወላይታ ጉዳይ አይደለም ያለው ማን? ማነው ይህንን አጥር የሠራው? የትግሬን ጉዳይ ማነው የትግሬ ብቻ ነው ያለው? ሌላው አያገባውም? አያስጨንቀውም? አይመለከተውም? ለምንድን ነው በየጉሮኗችን እና በየዋሻችን ብቻችንን የምንመክረው፡፡ የኦሮሞ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም እንዴ? የአማራ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም እንዴ፣ የሲዳማ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም እንዴ፣ የሶማሌ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም እንዴ? ለምንድን ነው ጠብበን እና አጥብበን የመንደር ጉዳይ የምናደርገው፡፡ ጎበዝ እዚያም ቤት እንደ ሚመከረውኮ እዚህም ቤት ይመከራል፡፡ እነ እንቶኔ እንደሚያስቡትኮ እና እንትናም ያስባሉ፡፡
ለምን አብረን አንመክርም? የነብርም ሆነ የፍየል ግልገል ጠላትነቱ የሚቀጥልበትን መንገድ ብቻ ነው በየበኣታቸው ሆነው የመከሩት፡፡ እኛምኮ ከእነርሱ አልተሻልንም፡፡ ለየብቻ ተሰብስበን ከተቻለ ስለ ነባሩ ጠላታችን እንመክራለን፤ ካጣንም ጠላት እንፈጥራለን፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በየበኣቱ ብቻ የሚመከርባቸውና የበኣት ጠላት የሚፈራባቸው ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ ዘር እና እምነት፡፡ በክርስቲያኑም ዘንድ ነብር እና ፍየል አለ፡፡ በሙስሊሙም ዘንድ ነብር እና ፍየል አለ፡፡ እነዚያንም ለብቻ ጠርተው በቤታቸው የሚመክሯቸው አሉ፡፡ እነዚህንም ለብቻ ጠርተው በቤታቸው የሚመክሯቸው አሉ፡፡ የነብር እና የፍየል የማያውቁትን ጠላትነት የገዛ ወላጆቻቸው እንደተከሉባቸው ሁሉ እነዚህንም «እገሌ ጠላትህ ነው ተጠንቀቀው» እያሉ ጠላት ተክለው ጠላት የሚያበቅሉ ሞልተዋል፡፡
መጀመርያ ክርስቲያኑ እና ሙስሊሙ ለየብቻ እንዲመክሩ አድርገው የጠላትነትን መንፈስ ዘሩ፡፡ ቀጠሉና በሙስሊሙ መካከል ነብር እና ፍየል ፈጠሩ፤ በክርስቲያኑ መካከልም ነብር እና ፍየል አፈሩ፡፡ ግን እስከ መቼ ከነብር ተጠንቀቅ፣ ፍየልን እነቅ እየተባልን እንኖራለን? አሁን በሁላችንም ልብ ውስጥ የተጠቂነት ሥነ ልቡና እየሠረፀ ነው፡፡ ሁሉም ተበድያለሁ፣ ተገፍቻለሁ፣ ተጠቅ ቻለሁ፣ ተጨቁኛለሁ፣ ተደፍሬያለሁ፣ ተዋርጃለሁ እያለ ብቻ ነው የሚያስበው፡፡
በአንድ ወቅት ከወንዝ ወዲህ እና ወዲያ የሚኖሩ መንደርተኞች ነበሩ አሉ፡፡ ታድያ የሁለቱ መንደርተኞች ልጆች ወንዙ ሲገናኙ ያዩ ወላጆቻቸው እየጠሩ «እነዚያ መንደርተኞች ቡዶች ናቸውና አትቅረቧቸው» እያሉ ልጆቻቸውን ይመክሩ ጀመር፡፡ የዚህኛውም መንደር ሆነ የዚያኛው መንደር ምክር ተመሳሳይ ነበረ፡፡ እነዚህም እነኛን እነኛም እነዚህን ቡዶች ናቸው ብለው ፈርተው በየመንደራቸው ቀሩ፡፡
ይህንን ያዩ የሁለቱ መንደር ሽማግሌዎች አንድ ቀን ተነጋገሩና ወንዙ ዳር ተገናኙ፡፡ እናም እንዲህ ብለው ጠየቁ «ለመሆኑ ቡዳው ማነው) ያን ጊዜ አንዲት እናት ተነሡና «እነርሱም እኛን ይላሉ እኛም እነርሱን እንላለን½ ቡዳው አልታወቀም ግን እንበላላለን» አሉ አሉ፡፡
የየእምነቱ ሰዎች ችግሩን ከሌላ ቦታ እየፈለጉት እነዚያኞቹን ቡዶች እያልናቸው ነው እንጂ ችግሩ ያለው ከራሳችን ነው፡፡ ኢትዮጰያ ውስጥ አማኞቹን የሚመጥን የእምነት ተቋም እና የእምነት አባት እጥረት ተከስቷል፡፡ በእስልምናም እንሂድ በክርስትና አማኞች በእምነት አመራሮቻቸው እና አባቶቻቸው፣ ተቋሞቻቸው እና አሠራሮቻቸው ሊረኩ አልቻሉም፡፡
አሁን በአማኞች መካከል በየጉሮኗችን እንድንመክር እና ቡዶቹ እነዚያኞቹ ናቸው እንድንል ያደረገን ተቋማዊ ችግሮቻችንን መፍታት ባለመቻላችን ነው፡፡ የአስተዳደር በደል፣ ሙስና፣ ዝርፊያ፣ ለሥልጣን መሯሯጥ፣ የእምነት ሕግጋትን ለጥቅም ሲሉ መሸጥ፣ እግርን ቤተ እምነት አድርጎ ራስን ፖለቲካ ላይ መንተራስ፣ የዘመድ አዝማድ አሠራር፣ ለታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ ግዴለሽ መሆን የኢትዮጵያ ቤተ እምነት ተቋማት የጋራ ጠባያት እየሆኑ ነው፡፡
እነዚህ አካላት እኛ ተስማምተን ወደ እነርሱ እንድናይ ስለማይፈልጉ በየጉሮኗችን ለየብቻ ይመክሩናል፡፡ እኛም የማናውቀውን ጠላት እናውቃለን፣ መንገዳችንም እምነት ተኮር መሆኑ ቀርቶ ጠላት ተኮር ይሆናል፡፡ ይመስለናል እንጂ አንደኛችን አዝነን ሌላችን ልንደሰት አንችልም፡፡ አንዳችን አንገታችን ደፍተን ሌላችን ቀና ልናደርግ አንችልም፡፡ ነፍስ ኄር አባ እንየው ውቤ ዘአሶሳ በደርግ ጊዜ ከዞኑ ኢሠፓ /ቤት ለሠፋሪ ሙስሊሞች የመስጊድ መሥሪያ ቦታ ሊያስፈቅዱ ሲገቡ የኢሠፓ ጸሐፊው «እርስዎ ክርስቲያን ሆነው ስለ ሙስሊሙ የሚከራከሩት ለምንድን ነው ብሎ ሲጠይቃቸው «ወዳጄ ሙስሊሙ እያዘነ ክርስቲያኑ ሊደሰት አይችልም፣ እምነት የግል፣ ደስታ ግን የጋራ ነው» ነበር ያሉት፡፡
ይልቅስ ጎበዝ ሞኞች አንሁን፡፡ በጋራ እንምከርና ጠላትነቱን ትተን ፊታችንን የየራሳችንን ቤት በጋራ ወደማስተካከል እንምጣ፣ ተቋማዊ አሠራሮቻችንን እንፈትሻቸው፡፡ ለምንድን ነው በእምነት ተቋሞቻችን እና በእምነት መሪዎቻችን እኛ ኢትዮጵያውያን ልንረካ ያልቻልነው? ለዚህ ጥያቄ የጋራ ምላሽ እንፈልግ፡፡
ያን ጊዜ ነብር እና ፍየል አብረው ይውላሉ፡፡

58 comments:

 1. ለምን አብረን አንመክርም? የነብርም ሆነ የፍየል ግልገል ጠላትነቱ የሚቀጥልበትን መንገድ ብቻ ነው በየበኣታቸው ሆነው የመከሩት፡፡ እኛምኮ ከእነርሱ አልተሻልንም፡፡ ለየብቻ ተሰብስበን ከተቻለ ስለ ነባሩ ጠላታችን እንመክራለን፤ ካጣንም ጠላት እንፈጥራለን፡፡

  Thanks Daniel!

  ReplyDelete
 2. ለምንድን ነው በእምነት ተቋሞቻችን እና በእምነት መሪዎቻችን እኛ ኢትዮጵያውያን ልንረካ ያልቻልነው? ለዚህ ጥያቄ የጋራ ምላሽ እንፈልግ፡፡how?by what method and technique?ኩሎ አመክሩ ወሠናየ ግበሩ
  God bless you deacon daniel keep on touch by writing such articles,there is one day we trust and proud of our spiritual leaders

  ReplyDelete
 3. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 4. Samuel Abera, Addis Ababa EthiopiaFebruary 29, 2012 at 1:33 PM

  amazing expression go ahead Dani

  ReplyDelete
 5. እግርን ቤተ እምነት አድርጎ ራስን ፖለቲካ ላይ መንተራስ፣ የዘመድ አዝማድ አሠራር፣ ለታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ ግዴለሽ መሆን የኢትዮጵያ ቤተ እምነት ተቋማት የጋራ ጠባያት እየሆኑ ነው፡፡

  ReplyDelete
 6. ግን እስከ መቼ ከነብር ተጠንቀቅ፣ ፍየልን እነቅ እየተባልን እንኖራለን?

  ReplyDelete
 7. ዳኒ በእርትአ ጌኤትአ ጨእምርኦ ጨእምርኦ ይግለፅልህ
  ዮናስ አበበ

  ReplyDelete
 8. Great article, now including me am living in fear of everything, because few EPRDF "kadries" are creating such illusion for 1 or two or three persons political target and few persons stomach.this is the time everybody of us shall be careful for our future.

  ReplyDelete
  Replies
  1. watch out man! Don't write as u like.

   Delete
 9. ነፍስ ኄር አባ እንየው ውቤ ዘአሶሳ በደርግ ጊዜ ከዞኑ ኢሠፓ ጽ/ቤት ለሠፋሪ ሙስሊሞች የመስጊድ መሥሪያ ቦታ ሊያስፈቅዱ ሲገቡ የኢሠፓ ጸሐፊው «እርስዎ ክርስቲያን ሆነው ስለ ሙስሊሙ የሚከራከሩት ለምንድን ነው?» ብሎ ሲጠይቃቸው «ወዳጄ ሙስሊሙ እያዘነ ክርስቲያኑ ሊደሰት አይችልም፣ እምነት የግል፣ ደስታ ግን የጋራ ነው» ነበር ያሉት፡፡

  ReplyDelete
 10. that is great idea!
  God bless you Dani.

  ReplyDelete
 11. truly,it is well elaborated article.this one sideness against z other is visible in all aspects.for eg in campus caffe one ethnic group hold one side chaire&table.u know my question always is zat why&how this divison'goregnet'is created,also who r responsible 2 z consequence thereof.

  ReplyDelete
 12. yes there is confussion in a christian and muslim population .There is conffusion within church .The real problem is the government.why don't they(government) leave us free.Free church and free mosque who teaches our realigious view only.
  I wonder why we pray for our releagious leaders long year.I think God see it as a jock.we hate their administration but we pray for them to lead us.

  ReplyDelete
  Replies
  1. Yes! This is z one we need most. . . . Guys dont u think zat we all r responsible? In a book i read it says "dictators exist coz z people carry them". So we all r responsible!!! Don forget everytime in Our history there were very bad life principles which gave us z worst. . . And so currently we complain of religious and political leaders poor and dire performance . . . U know our (always think of 80mln population) common belief does not deserve a good leader at all! So "hizbe kalemawok yetenesa teftoal" . . .this is for us. But thanks God z land is not totally empty. . . We have like dani and others we dont know them and shamefully we don respect them! Oh when is z time we all cry for Ethiopia together?!

   Delete
 13. አሁን በአማኞች መካከል በየጉሮኗችን እንድንመክር እና ቡዶቹ እነዚያኞቹ ናቸው እንድንል ያደረገን ተቋማዊ ችግሮቻችንን መፍታት ባለመቻላችን ነው፡፡ የአስተዳደር በደል፣ ሙስና፣ ዝርፊያ፣ ለሥልጣን መሯሯጥ፣ የእምነት ሕግጋትን ለጥቅም ሲሉ መሸጥ፣ እግርን ቤተ እምነት አድርጎ ራስን ፖለቲካ ላይ መንተራስ፣ የዘመድ አዝማድ አሠራር፣ ለታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ ግዴለሽ መሆን የኢትዮጵያ ቤተ እምነት ተቋማት የጋራ ጠባያት እየሆኑ ነው፡፡
  Mamush,MN

  ReplyDelete
 14. Keep on Dear Daniel! God Bless You! I will try to get rid of this kind of thinking. God Bless Ethiopians!

  ReplyDelete
 15. I Think we are paying the debt of our poleticians. If things are not going in the right track,may be it will cost more generation. Proud to be Ethiopian.

  ReplyDelete
 16. ቃለ ህይወት ያሰማልን ውድ ዳኒ! ነገሩ ሁሉ ግሩም ነው አንድ አንዴ ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር ይህን ያህል በእግዚአብሄር ኪነ-ጥበብ ተደግፋ ከመፃኢ የተፈጥሮ አደጋና መሰል ነገሮች ተጠብቃ እንኳን ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ ካቃትት ከዚህ የከፋ አደጋ ቢመጣ በየእለቱ የሚሰሙት በሌሎች የአለማችን ክፍሎች የሚፈፀሙት ክፉ ዜናዎች የሚከሰቱባት ሐገር ብትሆን ምን አይነት ገፅታ ይኖራት ይሆን የሚል ሀሳብ ይሞግተኛል፣ እርስ በርሳችን እንደተሳደድን ባላንጣ እንደሆንን የት ድረስ ልንዘልቅ እንደምንችል ሳስበው ከአስራ አምስት አመት በፊት በሩዋንዳ ተከስቶ የነበረው የዘር ጭፍጨፋና አሁንም በናይጀሪያና በአንዳንድ ሌሎች ሐገሮች እየተፈፀመ ያለው ከሀይማኖት ጋር የተያያዘ ከስነምግባርና ከሰብአዊ ፍጡር አስተሳሰብ ውጭ የሆኑ አሰቃቂ ተግዳሮቶች ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ላለመፈፀማቸው ምን ዋስትና አለ እላለሁ (እግዚአብሄር ክፉን ያርቅና)
  እኔ እምለው ኢትዮጵያ የሀይማኖት ሐገር አይደለችም እንዴ? ማንኛውም ሀይማኖትስ ቢሆን አላማው አንድ አይደለም እንዴ? እሱም ሰላምን መስበክ። አንድ ግልፅ አልሆንልህ ያለኝ ነገር ቤተ አምልኮዎቻችን ናቸው የተጣመመ ነገር በመዝራት ህዝቡን ያጠፉት ወይስ ህዝቡ ነው ተጣሞ ዲያቢሎሳዊ አስተሳሰብንና አሰራርን ምርጫው ያደገረገው? እኛ ኢትዮጵያውያን ያጣነው እኮ ያን ሰላም ነው። ሰላማችንን ከሌሎች ሰዎች፣ ማህበረሰቦች፣ ሀይማኖቶች፣ ግብአቶችና መሰል ጉዳዮች ጋር ተብትበነው ገደል ገብተናል። ለሰላማዊ ኑሮ የሚሆኑ አዎንታዊ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን በሙሉ በተቃራኒው ተረድተን ዘርና ሀይማኖት በማንቆሸሽ፣ በመስደብ፣ በማሳደድ፣ በመተናነቅና በመጠፋፋት ሰላማችንን የምናሰፍን መስሎናል። ሰላም ደግሞ ስንፈጠር ከኛው ጋር ይፈጠራል እንጂ በ እንዲህ አይነቱ የተገላበጠ አስተሳሰብና ድርጊት፣ በልምድ፣ በትምህርት፣ በስልጠና አይመጣም በዘር፣ በጎሳ፣ በሀይማኖት… ስለተከፋፈልንና ስለመከርን አይቀናም። ከኛው ጋር ተለጥፎ ያለን እጂ እኛው ጋር መሆኑን ማወቅና መጠቀም እንጂ እጃችንን በእጃችን መፈለግ ምን ይሉታል። ታላቁ የህይወት መፅሀፍስ ቢሆን ህግ ሁሉ በአንድ ተሰብስቦ አንድ ነው እሱም ባልነጀራህን እንደራስህ ውደድ አይደለም እንዴ የሚለው?!

  ReplyDelete
 17. ዲ/ን እግዚአብሄር አባት ይባርክ

  ReplyDelete
 18. Christians pray long age not only for the Church fathers(whether they are good or not) but also for their enemies.This is the command of Our Lord.Have you understand my brother who gave comment before

  ReplyDelete
  Replies
  1. thank you bro they pray for the enemies not to live long (the number of years) they pray for their soul to be saved .

   Delete
 19. Niseha Engeba

  Qale Hiwoten Yasemalin Tsegawin Yabezalih Wendenachin D. Daneal

  ReplyDelete
 20. የልብ ኣድርስ ኣገላለፅ። እግዚኣብሔር ረጅም የኣገልግሎት እድሜ ይስጥህ!!

  ReplyDelete
 21. I really appreciate your views.
  GOD BLESS ETHIOPIA

  ReplyDelete
 22. it is a nice experssion

  ReplyDelete
 23. That is true and correct. the only thing that differ is the advise for the kid of a goat is given by its lovely mother to save his life and secure its life from evils. But the one i.e we are suffering due to the advice from evils for their evil sake. We sh'd be together to tell them stop. Thank You

  ReplyDelete
 24. ሃይማኖት & ፖለቲካ & ኪነ - ጥበብ ጥሩ መሪ ያስፈልጋቸዋል፤ህዝብ ሲመራቸው ችግር ይፈጥራል፡፡ አሁን የሀጉራችን ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ዳኒ እናመሰግናለን፡፡

  ReplyDelete
 25. Dear Dn Daniel,

  Thank you for sharing your ideas. I think the idea is timely which touches all of us, i.e. the entire ethnic group, the entire religion in other words all Ethiopian. As you know most of us victimized with this issue and it might contiue to the new generation if something no done.

  As our Holy Father taught as we should love each other including our enemies so as to see the future Ethiopia which will be comfortable to our children. So lets start from ourselves by teaching the whole family about the advantage to live together so as to see unified Ethiopia.In my thinking the change should start from myself and then continue to the other (family, parents, relatives, freinds, classmates, colleages,bosses, etc).

  So lets focus on the solution since we know about the problem or challenge of it more than we can know.

  Kebede

  ReplyDelete
 26. Selesshi the GollaMarch 1, 2012 at 10:35 AM

  ለእግዚአብሔር አልተመቸንም፡፡ ለእግዚአብሔር ስንመች ይመቹናል እንረካባቸዋለን፡፡ እግዚአብሔር ለበረከትም ለቅጣትም ይጠቀምባቸዋል፡፡

  ReplyDelete
 27. Dear Daniel,

  Keep it up your intervention. We should abide our self to the unity in diversity principle. Aesop stated that, "united we stand, divided we fall." It is time to teach our siblings early on that in diversity there is a beauty and there is strength. I am concur with Mr. Kofi Anana's idea that he said "We may have different religions, different languages, different colored skin, but we all belong to one human race." Thus, let we think inward that must center national feeling.

  ReplyDelete
 28. it is a nice written keep it up on d.daniel

  ReplyDelete
 29. እነዚህ አካላት እኛ ተስማምተን ወደ እነርሱ እንድናይ ስለማይፈልጉ በየጉሮኗችን ለየብቻ ይመክሩናል፡፡ እኛም የማናውቀውን ጠላት እናውቃለን፣ መንገዳችንም እምነት ተኮር መሆኑ ቀርቶ ጠላት ተኮር ይሆናል፡፡ ይመስለናል እንጂ አንደኛችን አዝነን ሌላችን ልንደሰት አንችልም፡፡ አንዳችን አንገታችን ደፍተን ሌላችን ቀና ልናደርግ አንችልም፡፡ ነፍስ ኄር አባ እንየው ውቤ ዘአሶሳ በደርግ ጊዜ ከዞኑ ኢሠፓ ጽ/ቤት ለሠፋሪ ሙስሊሞች የመስጊድ መሥሪያ ቦታ ሊያስፈቅዱ ሲገቡ የኢሠፓ ጸሐፊው «እርስዎ ክርስቲያን ሆነው ስለ ሙስሊሙ የሚከራከሩት ለምንድን ነው?» ብሎ ሲጠይቃቸው «ወዳጄ ሙስሊሙ እያዘነ ክርስቲያኑ ሊደሰት አይችልም፣ እምነት የግል፣ ደስታ ግን የጋራ ነው» ነበር ያሉት፡፡
  thank you

  ReplyDelete
 30. Keep it up Dn. Please write and preach more on this. This is what Ethiopia need.

  ReplyDelete
 31. Egziabeher yistilin Diakon! yihe HIYAW EWUNET NEW!Meftihew andina and new,abro tekerarbo bemetemamen (sayitemamenu adega alewuna)mewoyayet mesirat new!
  Endene asteyayet, huletu (fiyeluan nebrua)kemekerarebachew befit yeyerasachewun wogen masamen mastekakel mekeyer masredat yalebachew yimeslegnal!

  ReplyDelete
 32. Kusilegnaw Yefiyel giligelMarch 1, 2012 at 2:54 PM

  Awaj!Awaj!Yalisemah sima Yesemah Asema. This issue is the issue of all Ethiopian religions. Hulum beyebetu Yegorebetun metfiya Yimekiral tefiwun ande amlak yawukal. Gin hulachin tefakiren medan sinichil lemin metefafatin enishalen. Bewunet Joro Yalew Yisima Ayin Yalew yastewul. Thankyou Daniel keep it up!!!

  ReplyDelete
 33. ዳኒ፣ የተዘራ መብቀሉ የት ይቀራል ብለህ ነው፡፡

  ReplyDelete
 34. that is great God bless you

  ReplyDelete
 35. ግሩም ነው ዳን.ዳንኤል
  ሰው ለምን የተከለከለ ነገር ይጥመዋል?.አድማና ልዩነት መፍጠር የትምህርት ተቛማቱ ስንተኛው(የትኛው) የትምህርት ዘርፍ ነው?ወዳጄ.ከነዚህ ተቋማት የሚገኝው 'ምሁር'ምን አይነት ይሆን?
  የሰለጠነው አለም የናዚን ርካሽ ተግባር እየኮነነ ስለመጭው ትውልድ ብሩህ. ዘመን ይናፍቃል..እኛ ጋ
  ግን ወደ የት ነው?..ጋሼ የምላቸው አንድ አባት "በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ" ይሉ ነበር:እንዲህስ አይሁንብን::ማንንም ምክንያት አናድርግ:"ሰው እራሱ በጨለማ እየተጓዘ በጅብ ያመሃኛል:".ይሉ ነበር ጋሽ ታደገ...ምኞቴ ብዙነህ @ፍሎሪዳ ጫካ

  ReplyDelete
 36. «እነርሱም እኛን ይላሉ እኛም እነርሱን እንላለን½ ቡዳው አልታወቀም ግን እንበላላለን» የቅዱሳን አምላክ እንዲህ አይነቱን ክፉ መንፈስ ከእግራችን በታች ይጣልልን!!

  ReplyDelete
 37. I am not sure if you will publish this comment of mine.A lot of thoughts came through my mind and wanted to express some of them, then I asked myself , what is really the mother of all these problems: discord, animosity,among ourselves; lack of trust towards our institutions( religious or otherwise), and leaders( religious or otherwise). The answer is the the government( read as TPLF).We were drilled on each others differences, how one of us tried to destroy the other, to plunder the other, ...for 20+ years, and most of today's college students are "children's" of revolutionary democracy.Unlearning is more difficult than learning. I am positively pessimistic!!

  Thank you Deacon Daniel,you may perhaps need to redirect you "pen-sword"

  ReplyDelete
 38. Thanks dn.Daniel.It is great.

  ReplyDelete
 39. Dn. Dani,

  Berta ......, May God be with you .

  Edmonton,Canada

  ReplyDelete
 40. “አፍሁ ለፃድቅ ይትመሐር ጥበበ፤ ወልሳኑ ይትነብብ ፅድቀ፤ ወሕግ አምላኩ ውስተ ልቡ።”
  Bless you Danni

  ReplyDelete
 41. የዛሬ ፍርሃት፣ የነገ ሥጋት ለተተኪ ትውልድ የተተከለ መርዝ፣ የሀገር ዕድገት መሰናክና ጥፋት … ጊዜ የማይሰጠዉ ከዛሬ ጀምሮ ልናስብበት እና በጋር ልንመክርበት፣ በዚህ መንገድ መሄዳችን የሚያስደስታቸዉን አካላት እረፉ ልንላቸዉ የሚገባ ተግባር ነዉ፡፡


  ዳኒ ያበርታህ!

  ReplyDelete
 42. Let You explicitly and courageously tell PM Melese to bow for National Reconciliation and all inclusive governance system. What he has beed doing for 20 years is not steady progress of the nation it really is multiplying of the countries problems.

  ReplyDelete
 43. I am very satisfied. Excellent analysis and great advice! Wise and bold! God bless you Daniel!!! Long live to you!

  If you are a preacher, preach like Daniel or Martin Luther! Preaching is not only about talking about the suffering of Israel by Egyptians in the times of Mosses. But, leading the current generation and criticizing the wrong doers!

  United we win,divide we fall!!!

  ReplyDelete
 44. Dear Dani;

  As usual you picked another interesting & sensitive issue

  However, to my understanding the issue of ethnicity in its current ill format has never been the case of individual households & social associations (EDER, MAHABER, EQUEB…etc)

  Rather, the present ethnic mentality (xenophobia) is the product of Diaspora politics with institutional backing of the regime at office since the pasts 20 years plus.

  The other day I was discussing the issue with prospective university students & other youngsters who have been at different colleges. One of them has told me that a group of xenophobic students had cut off the leg of another student from different ethnic group. Even some groups of students have allegedly carrying guns in the vicinity campuses.

  I remember reading a horrifying story of the killing of one student by another group of students in one of the junior high school in Addis.

  It is a very frustrating scenario we are living in!

  What is the future of a country without the vision of its youth?

  If I were an authority (which I never wish to be one) I would severely punish any ethnic base violence’s in any institutions. But above all I will incorporate the art of respect & peaceful cohabitations in the so-called civic education courses.
  We must teach our youngsters from the grass roots as to how thy respect & love each others regardless of their ethnicity & how they live together …

  God Bless Historic Ethiopia!

  ReplyDelete
 45. I am sorry that 99 percent of Addis Ababa University students are members of EPRDF forcefully.This is fact.

  ReplyDelete
 46. "የነብር እና የፍየል የማያውቁትን ጠላትነት የገዛ ወላጆቻቸው እንደተከሉባቸው ሁሉ እነዚህንም «እገሌ ጠላትህ ነው ተጠንቀቀው» እያሉ ጠላት ተክለው ጠላት የሚያበቅሉ ሞልተዋል፡፡" እውነት ብለሃል ቁም ነገሩ እኛ ልጆችም እንደ ፍየል እና ነብር ግልገሎቹ ማመዛዘን አለመቻላችን ነው፡፡

  ReplyDelete
 47. «እርስዎ ክርስቲያን ሆነው ስለ ሙስሊሙ የሚከራከሩት ለምንድን ነው?» ብሎ ሲጠይቃቸው «ወዳጄ ሙስሊሙ እያዘነ ክርስቲያኑ ሊደሰት አይችልም፣ እምነት የግል፣ ደስታ ግን የጋራ ነው» ነበር ያሉት፡፡samuel f

  ReplyDelete
 48. betam betam betam korichebihalew adaniel.ene muslim negn gin besafkew neger rekichalehu.Sihitetochachinin arimen befikir endinihed yiredanal.Hulgize geziwochachin lesiltanachew silu eyafajun ezih derseal.ahun lay gna eerasachin enesun beliten hagerachinin metebek new yalebin.Allah yibarkih

  ReplyDelete
 49. እግዚአብሔር ብርታቱን ይስጥህ! አሁን አሁን ደግሞ በመንፈሳዊ ኮሌጆችም የዘርና የጎጥ መርዝን በመትከል አንዱ የአንዱ ጠላትና አጥፊ እንደሆነ ለሃይማኖቱ በአንድ ልብ እንዳይቆም እየከፋፈሉትና እየበለቱት ያሉት ከአስተዳደር ጀምሮ እስከታች ለጥቅም ያደሩ ብዙ ናቸው! አሳዛኙና አስገራሚው ነገር ደግሞ ያለ እኛ ሰባኪወንጌል ላሳር ሲሉ የሚሰሙትና የሚታዩት እነሱው መሆናቸው ነው! በዚህም ምክንያት ከቤተክርስቲያን አልፈን ለሀገራችንም ጠቃሚ ዜጋዎች እንዳንሆን ግዙፍ የማሰናከያ ድንጋይ ተቀምጦአል ቃለ እግዚአብሔር ያልለወጠን ምን ሊለውጠን እንደሚችል ግራ ያጋባል እናም ችግሩ በውስጣችንም አለና በጸሎት እንተሳሰብ

  ReplyDelete