Wednesday, February 29, 2012

የሁለት ቤት ምክር


ከአማራ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡
የፍየል እና የነብር ግልገሎች በአንድ ሜዳ ላይ አብረው ሲጫወቱ ዋሉ፡፡ ማታ ሁለቱም ወደ የቤታቸው ገቡና ለእናቶቻቸው ውሏቸውን ነገሯቸው፡፡ «እማየ» አለ የነብር ግልገል፡፡ «ዛሬ ወደ ኋላ የተቆለመመ ቀንድ ካለው፡፡ ከኋላው ላይ በቆዳ የተሸፈነ ሥጋ ነገር ከተንጠለጠለበት፤ ሲጮኽ ሚእእእእእእ ከሚል ግልገል ጋር ስጫወት ዋልኩ፡፡ እንዴት ጨዋታ ዐዋቂ መሰለሽ»፡፡

Wednesday, February 22, 2012

ከወንዙ በላይ ወይንስ በታች


ከወንዝ በላይ እና በታች የሚገኙ ሁለት መንደሮች ነበሩ፡፡ ላይኛው መንደር ወንዙ ከሚመነጭበት ከተራራው ላይ የተመሠረተ ሲሆን ታችኛው መንደር ደግሞ ወንዙ ከሚወርድበት ከገደሉ ሥር የተመሠረተ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት መንደሮች እየሰፉ እና ሕዝባቸውም እየበዛ መጣ፡፡ መንደሮቹም ወደ ወንዙ በጣም ተጠጉ፡፡ አልፈውም ከወንዙ እየተሻገሩ ቤት ሠሩ፡፡
በዚህም የተነሣ ዝናብ ዘንቦ ወንዙ በሞላ ቁጥር ከላይኛው መንደርተኞች አያሌዎችን እየጠረገ ወደ ገደሉ ያመጣቸው ነበር፡፡ በመጀመርያው አካባቢ ብዙዎቹ የላይኛው መንደርተኞች በወንዙ እየተወሰዱ ሞቱ፡፡ በኋላ ግን የታችኛው መንደር ነዋሪዎች ዝናብ ዘንቦ ወንዝ በሞላ ቁጥር እየተወሰዱ የሚመጡትን የላይኛውን መንደርተኞች እየዋኙ ያወጧቸው ጀመር፡፡

Sunday, February 19, 2012

የዲ/ን ዳንኤል ክብረት “ራእየ ዮሐንስ - የዓለም መጨረሻ” መጽሐፍ ተመረቀ(አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤)

የዲ/ን ዳንኤል ክብረት “ራእየ ዮሐንስ - የዓለም መጨረሻ” መጽሐፍ ተመረቀ 
(አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤)


18ኛ መጽሐፉ ነው ተብሏል

ከመጽሐፍ ቅዱስ(ዐሥራው) መጻሕፍት ሁሉ በስፋት ያልተተረጎመው የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ራእዩ በምሳሌዎች፣ ምልክቶች እና ትንቢቶች በመሞላቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከአንድምታ ትርጓሜው ባሻገር የዮሐንስ ራእይ ከክብደቱ አኳያ ተጨማሪ ማብራሪያዎች እና መረጃዎች እንደሚያስፈልጉ የነገረ ቤተ ክርስቲያንና ታሪክ ተመራማሪው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያስረዳል፡፡ በዚህ ረገድ የተሻለ መረጃ ለአንባብያን በማቅረብ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ”ራእየ ዮሐንስ - የዓለም መጨረሻ” በሚል ርእስ ያዘጋጀውን መጽሐፍ ባለፈው የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው ትሪያንግል ሆቴል አስመርቋል፡፡

Friday, February 17, 2012

ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም


(click here for pdf) 
አብዮቱ ከመፈንዳቱ አምስት ዓመታት ቀደም ብዬ በተባበ መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥራ ጀምሬ ነበር፡፡ ዋናው ምድቤ ደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል ነበር፡፡ በዚህ ቦታ በመመላለስ ለዐሥራ አምስት ዓመታት በማገልገሌ አካባቢው ያደግኩበትን ቦታ ያህል ዐውቀው ነበር፡፡
1976 ዓም በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ሰው እኔን የደቡባዊ አፍሪካን ጉዳይ በሚከታተለው የመንግሥታቱ ድርጅት አካል ውስጥ ለመሾም ፈለጉ እና አናገሩኝ፡፡ ኃላፊነቱን መቀበሉ ለኔ መልካምም ቀላልም ነበር፡፡ ከባድ የሆነው ነገር የሀገሬን መንግሥት ድጋፍ ማግኘቴ ነበረ፡፡
እኔ ከሀገሬ ወጥቼ መሥራት ከጀመርኩ ያኔ ዐሥራ አምስት ዓመት ሆኖኛል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ መንግሥትም ሥርዓትም ተለውጧል፡፡ አሁን ያሉትን ባለ ሥልጣናት አላውቃቸውም፡፡ እንደ እነርሱም ኮሚኒስት አይደለሁም፡፡

Wednesday, February 15, 2012

የደቡብ አፍሪካውያን ነፃነትና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ድርሻ በቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በታቦ እምቤኪ አንደበት

(click here for pdf)
በፍቅር ለይኩን፡፡ ~ fikirbefikir@gmail.com

 የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ በቅርቡ ዓመቱን የደቡብ አፍሪካዋ Judicial Capital በሆነችው በብሉምፎንቴን በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፣ ይህች ውብ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ታሪክ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ ሁለተኛ የሆነው የቅድስት ሥላሴ ወቅዱስ ያሬድ ገዳምና የካህናት ማሰልጠኛ ተቋም የተቋቋመባትና የተገደመባት ከተማ መሆኗን ልብ ይሏል፡፡ የደቡብ አፍሪካውያኑ ANC ፓርቲ በአፍሪካ ከተቋቋሙ ፓርቲዎች አንጋፋውና ረጅም ዕድሜ ጭምርም ያሰቆጠረ ነው።
የአፍሪካን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ለመዝረፍ አፍሪካን በቅኝ ግዛት የተቀራመቱት አውሮፓውያን በዋነኝነት አፍሪካን ምድር የረገጡበት ምክንያታቸው አፍሪካን በወንጌል ቃል ለማቅናት ነው የሚል ቢሆንም በሂደት ግን የአፍሪካውያን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብትን በመዝረፍ ለአፍሪካውያን ታላቅ ስብራትን ጥሎ ያለፈና ይሄ ነው ተብሎ ሊገመት የማይችል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ታሪካዊ ቀውስንና ክስረትን ሊያተረፍ የቻለ የአፍሪካውያን መራር ጨለማ ዘመን ታሪክ ሆኖ ሊያልፍ በቅቷል፡፡

Tuesday, February 14, 2012

ጩኸት እና ንግግር


 በታክሲ እየሄድኩ ነው፡፡ መካከለኛው ወንበር ነው የተቀመጥኩት፡፡ አንዲት ሴትዮ በስልክ በንዴት ያወራሉ፡፡ በጩኸታቸው መጨረሻ «እንዲያውም ካሁን በኋላ ካንተ ጋር መኖር አልችልም፤ በቃ» ብለው ዘጉት፡፡ በታክሲ ውስጥ የነበርነው ሁሉ በድንጋጤ እያየን ነበር ያዳመጥናቸው፡፡
ወዲያው አንዱ ቀልደኛ «እናቴ ይህንን በቃ የሚል ቃል እንኳን ቢተውት፤ ሌላ ትርጉም ያመጣል» ሲል ሁላችንም ከድንጋጤው ወጥተን ሳቅን፡፡
ስልኩን ሲጨርሱ ሁላችንም ወደርሳቸው መዞራችንን ሲያዩ ደንገጥ አሉ፡፡ አጠገባቸው ተቀምጠው የነበሩት አዛውንትም ፈገግ አሉላቸው፡፡

Monday, February 6, 2012

ሙሉ ወጥ


ሰውዬው እቤቱ ሲገባ ባለቤቱ ያቀረበችለት ምግብ ምንም ሊጥመው አልቻለም፡፡ አንዳች ነገር ጎድሎታል፡፡ አሰበ አሰበና አገኘው፡፡ ቅቤ የለውም፡፡
«ምነው?» አለ፡፡
«ቅቤ አልቋል» ተባለ፡፡
የተዘረጋውን ማዕድ ትቶ ወጣና ወደ ጎረቤቱ ገባ፡፡
«አያ እገሌ ዛሬ ምን አግር ጣለህ» አለና ጎረቤቱ አባ ወራ ተቀበለው፡፡
«ባክህ አንዳች የሚበላ ነገር ካለ ብዬ ነው» አለ እንዳኮረፈ መሆኑን በሚያሳብቅ ድምፅ፡፡
«ውይ በሞትኩት» አለችና የጎረቤቱ ሚስት እንጀራውን በመሶብ ሞልታ ፊቱ ላይ አቀረበችለት፡፡ የምግብ አምሮቱ ተነቃነቀ፡፡

Thursday, February 2, 2012

የድንጋይ ሾርባ


ሰው ሲደክመው እና ሲርበው ምን ይመስላል? ይህንን ለማወቅ ወደዚች መንደር በመግባት ላይ ያለውን መንገደኛ ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ ዓይኖቹ ከፊቱ ላይ ጠፍተው የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡ አፍንጫ እንዳለው ለማወቅ መዳሰስ የግድ ያስፈልጋል፡፡ መታወቂያ ቢኖረው ኖሮ አሁን የእርሱ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ የገዛ ልብሱ ስለከበደው አውልቆ እየጎተተው ይጓዛል፡፡ ሁለት ነገሮች ብቻ በትከሻው አሉ፡፡ ካናቴራው እና በስልቻ የያዛት ድስት፡፡
ረሃብ ምን ያህል ጊዜ ይሰጣል? ነበር ያለው ጸጋ ገብረ መድኅን፡፡ ይህንን ሰው ቢያይ ደግሞ ውኃ ጥም ምን ያህል ጊዜ ይሰጣል? የሚል ድንቅ ግጥም ይጽፍ ነበር፡፡ በበላዔ ሰብእ ታሪክ ጥርኝ ውኃ ሲያገኝ ውኃው በእጆቹ ንቃቃት ላይ የቀረውን ሰው ታስታውሱታላችሁ?