Tuesday, January 10, 2012

እስከ ሰባት ትውልድ


በበዙ የሀገራችን ጥንታውያን መጻሕፍት እና ትውፊቶች ዘንድ ሰባት ትውልድ የሚለው ብሂል የተለመደ ነው፡፡ «እስከ ሰባት ትውልድ እምርልሃለሁ» የሚለው ቃል በየገድላቱ ይገኛል፡፡ እስከ ሰባት ትውልድ አለመጋባት በአያሌ ማኅበረሰቦቻችን ትውፊታዊም ሃይማታዊም ሕግ ነው፡፡
ከቀደምት የአሜሪካ ሕዝቦች አንዱ የሆኑት የኢሮቆዩስ ሕዝቦች በዚህ የሰባት ትውልድ አስተሳሰብ ያምኑ ነበር፡፡ እነዚህ በዛሬዋ ኒውዮርክ እና አካባቢዋ የነበሩ ጎሳዎች ተባብረው የኢሮቆዩስ ፌዴሬሽን የሚባል አስተዳደር መሥርተው ነበር፡፡ የራሳቸውም ሕገ መንግሥት ነበራቸው፡፡ አሜሪካኖቹ የፌዴራሊዝምን ጽንሰ ሃሳብ የወሰዱት ከእነዚህ ማኅበረሰቦች ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡
 ከ500 ዓመታት በፊት በተጻፈው በኢሮቆዩስ ሕገ መንግሥት ውስጥ ይገኙ ከነበሩት ሕጎች አንዱ እንዲህ ይላል «በኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ ስታገለግሉ፣ ሕግ ስታወጡ፣ የመንግሥትንም ሥራ ስታከናውኑ፣ የግል ፍላጎታችሁን ወዲያ አውልቃችሁ ጣሉት፤ ስሕተት ትሠሩ ዘንድ የሚገፋፏችሁን የእኅት እና የወንድ ሞቻችሁን ግፊቶች በኋላችሁ ተዋቸው፤ ነገር ግን እውነት እና ርቱዕ ወደ ሆነው ወደ ታላቁ ሕግ ተመልከቱ፡፡ ለሕዝቡ የሚበጀውን ስሙ፣ ተመልከቱም፡፡ ስትሠሩም የአሁኑን ብቻ ሳይሆን መጭውን ትውልድም አስቡ፤ ገና ይህችን መሬት ያላዩትን፣ ያለተወለዱትን መጭዎቹን ትውልዶች፡፡ የመሪዎች ቆዳ ስስ መሆን የለበትም፤ እንዲያውም ከሌላው ሰባት ጊዜ እጥፍ የወፈረ መሆን አለበት፡፡ ቁጡነትን፣ ተናዳ ፊነትን እና ትችትን መቋቋም እንዲችሉ፤ ይህንንም ሁሉ ታግሠው ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጡ» ይላል፡፡
«በማናቸውም ውሳኔ ጊዜ ውሳኔያችን በሚቀጥሉት ሰባት ትውልዶች ላይ የሚያመጣውን ነገር አስቀድመን ማሰብ አለብን» የሚለው ብሂል እጅግ ከሚጠቀሱት የኢሮቆዩስ አባባሎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አያሌ የፖሊሲ ባለሞያዎች በየአጋጣሚው የሚያነሱት በተለይም የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች የሚከራከሩለት መርሕ ነው፡፡
እንስሳት ያለፈ ታሪክም ሆነ የሚመጣ ተስፋ የላቸውም፡፡ ስለዚህም ለልጅ ልጆቻቸው የሚያስቡትም የሚያስቀምጡትም ነገር የለም፡፡ የእነርሱ ውሳኔ በደመ ነፍስ እና ለጊዜው የሚረዳ ብቻ ነው፡፡ ሰው ግን ከዚህ ይለያል፡፡ የትናንት ታሪክም የነገ ተስፋም አለው፡፡ ከፋም ለማም ሰው የራሱ ዘመን ብቻ ውጤት አይደለም፡፡ ያለፉት ትውልዶች ውሳኔ እና ተግባር ውጤትም ጭምር ነው፡፡ ወላጆቻችን የሚወስኑት ውሳኔ የነገ ማንነታችንን ይወስነዋል፡፡ አስተዳደጋቸው፣ አመራራቸው፣ የሚያስገቡን ትምህርት ቤት፣ የሚያሟሉልን ነገሮች እና የቤተሰቡ አያያዝ ማንነታችንን ይቀርፀዋል፡፡
እነርሱም ቢሆን እነዚህን ነገሮች በእኛ ላይ እንዲወስኑ የሚያደርጓቸው ካለፉት ወላጆች ያገኟቸው ቅርሶች፣ ልምዶች፣ ሀብቶች እና ጠባዮች ናቸው፡፡ እንዲህ እያለም ይቀጥላል፡፡ ሰው የትናንቱን መተው፣ ለነገውም አለመጨነቅ የማይችለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ይህ ትውልድ የዐፄ ቴዎድሮስ፣ የዐፄ ምኒሊክ፣ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ እና የደርግ ፖሊሲዎች፣ አሠራሮች፣ አስተሳሰቦች፣ ውሳኔዎች እና ሥራዎች ውጤት ነው፡፡ ቢፈልገውም ባይፈልገውም የእነርሱ ተጽዕኖ እንዲህ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ በጎ ተግባራቸው ጠቅሞታል፡፡ ስሕተታቸውም ጎድቶታል፡፡ ወይ ሥራ ቀንሶለታል፤ ወይ ሥራ ጨምሮበታል፡፡ የኢሕአዴግም አመራር፣ አሠራር እና አስተሳሰብ እንደዚሁ በቀጣይ ትውልድ ላይ መንፀባረቁ የማይቀር ነው፡፡
እስኪ ፖሊሲዎቻችን እና መመሪያዎቻችን ይታዩ፤ በቀጣዮቹ ሰባት ትውልዶች ላይ ምን ያመጣሉ? እስኪ የምንገነባቸው ግንባታዎች ይመርመሩ? በቀጣዮቹ ሰባት ትውልዶች ዘንድ ምን ያስከትላሉ? የተዋዋልናቸው ውሎች፣ የተበደርናቸው ብድሮች፣ የዘረጋናቸው መሥመሮች፣ የመሠረትናቸው አስተዳደሮች፣ ያቋቋምናቸው ድርጅቶች፣ የፈጠርናቸው ባህሎች፣ ያመጣናቸው አስተሳሰቦች በቀጣዮቹ ሰባት ትውልዶች ዘንድ ምን ሊያመጡ ይችላሉ?
እኛ ስንሞት ሰርዶ ሳይሆን ሀገር ናት መብቀል ያለባት፡፡ ስለ ሰባት ትውልድ የማናስብ ከሆነ ኢትዮጵያ ማለት እያንዳንዱ ትውልድ እንደገና እያፈረሰ የሚሠራት ሀገር ትሆናለች፡፡ ለሰባት ትውልድ ያሰቡ የአሜሪካ መሥራች አባቶች የሠሩት ሕገ መንግሥት እየተሻሻለ ላለፉት ሦስት መቶ ዓመታት ጸንቷል፡፡ ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ በአባቶቹ መሠረት ላይ እየመሠረተ ሕንፃውን እንዳይፈርስ መጠበቅ፣ ይበልጥ ማስዋብ እና የተሻለ ነገር መጨመር እንጂ ከሥር ከመሠረቱ ሲንደው አልታየም፡፡
እኛ ግን የንጉሡን ሕገ መንግሥት ትቶ ደርግ ሌላ አወጣ፣ የደርግን ሕገ መንግሥት ሠርዞ ኢሕአዴግ ሌላ አረቀቀ፡፡ ነገ የሚመጣው ትውልድም የቀደመውን እየሠረዘ እና የየራሱን ሕገ መንግሥት እያረቀቀ የሚሄድ ከሆነ ኢትዮጵያ ማለት እንደ ልጆች ጨዋታ በየጊዜው እየፈረሰች የምትሠራ የዕቃ ዕቃ ቤት ሆነች ማለት ነው፡፡ የሦስት ዘመን ነጻነት ታሪክ እየተናገረች ሁሌ ግን ነጻ የምትወጣ፡፡ «ሀገረ አግዓዝያን» እየተባለች ነገር ግን አያሌ ነጻ አውጭዎች ያሉባት ሀገር፡፡
 በ13ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የጎጃሙ ባለ ቅኔ ተዋነይን ሊጠይቀው ንጉሡ እስክንድር ሄዶ ነበር አሉ፡፡ እንዴት አድርጌ ሀገር ልምራ? ሲል ጠየቀው፡፡ ተዋነይ እንዲህ አለ «ለመሆኑ ስንት ዓይን አለህ ንጉሡም መለሰለት «ሁለት ዓይኖች አሉኝ»፡፡ «መልካም» አለ ተዋነይ፡፡ «አንዱን ዓይንህን አሁን ያለህበትን ዘመን እይበት፤ በሁለተኛው ዓይነህ ግን ነገ የሚመጣውን እይበት፡፡ የዛሬን እና የነገን በሁለቱ የዓይን ሚዛን መዝነህ ሚዛን ሲደፋልህ ሥራ» አለው ይባላል፡፡
የሕዝብ መሪዎች ሁለቱን ዓይናቸውን እንደ ተዋነይ ምክር መጠቀም ቢችሉ እንዴት መልካም ነበር፡፡ ነገን ብቻ ሳይሆን ዛሬንም፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ጨምሮ ማየት፡፡ በመስቀል ጦርነት የአውሮፓን ጦር አሸንፎ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠራት ሳላህዲን የሚነገርለት አንድ አስተውሎት አለው፡፡ ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠረ በኋላ የክርስቶስን መቃብር ለማየት ወደ ጎልጎታ መጥቶ ነበር፡፡ በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን እያስጎበኙት እያለ የስግደት ሰዓት ደረሰበት፡፡ ጒብኝቱንም አቋርጦ ወጣ፡፡ በወቅቱ የነበሩት መነኮሳት እዚያው እንዲሰግድ ጠየቁት፡፡ ሳላህዲን ግን አርቆ አስተዋይ ነበርና «አይሆንም፤ እኔ እዚህ ከሰገድኩ ወደፊት የሚመጡ ሰዎች ሳላህዲን የሰገደበት ነው ብለው በዚሁ ይቀጥላሉ፣ ለእናንተ መልካም አይሆንም» አለና ከጎልጎታ ወጣ ብሎ በነበረው ቦታ ላይ ሰገደ፡፡
ያለው አልቀረም፡፡ በሰገደበት ቦታ ላይ መስጊድ በኋላ ዘመን ተሠርቶበታል፡፡ ሳላህዲን በጎልጎታ ቢሰግድ ኖሮ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ይጠመድ ነበር፡፡ በሳላህዲን አስተዋይነት ቀረ እንጂ፡፡
በሀገራችን «ጉድጓድ ስትቆፍር ማን እንደሚወድቅበት አታውቅምና እጅግ አታርቀው» ይባላል፡፡ ምናልባት ቆፋሪው ራሱ ሊወድቅበት ስለሚችል፡፡ ትናንት በግዴለሽነት የጻፍናቸው እና የተናገርናቸው ነገሮች ሰባት ትውልድ ቆጥረው ዛሬ ዛሬ ጎሳ ከጎሳ እያባሉን፣ ሕዝብ ከሕዝብ እያዋቀሱን እና ዋጋ እያስከፈሉን ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ቤተ መንግሥቶቻቸውን እንጂ እሥር ቤቶችን በሚገባ አልሠሩልንም፡፡ እንኖራለን እንጂ እንታሠራለን ብለው ስላላሰቡ፡፡ በሚገባ ያልተሠሩት እሥር ቤቶች ግን ከታሠረው ተራ ሕዝብ ይልቅ የጎዱት የታሠሩትን እና የሚታሠሩትን መሪዎች ነው፡፡ ድኻውማ ያንን ችግር ቀድሞ ያውቀዋል፡፡ እነርሱ እንጂ፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ 1960ዎቹ ብቅ ሲል በግደል ተጋደል መርሕ ነበር የተቀጣጠለው፡፡ አንዱ ቀይ ሲል ሌላው ነጭ ሽብር እየወለደ ነበር የተካሄደው፡፡ ምታ፣ ደምስስ፣ ርምጃ ውሰድ፣ ረፍርፍ፣ በሚሉ ቃላት ነበር የታጀበው፡፡ ትውልድ ያረደው የጦስ ዶሮ ይኼው እኛ ዘመን ደርሶ ትውልድ ከአሣሪ እና ታሣሪ፣ ከደምሳሽ እና ተደምሳሽ፣ ከመቺ እና ተመቺ፣ ከሕዝብ እና ፀረ ሕዝብ ፖለቲካ መላቀቅ አልቻለም፡፡
እኔ ለልጆቼ ቆሎው ያርብኛል
ያባቴ ውቃቤ ያስገፈግፈኛል
አለች አሉ ሴትዮዋ፡፡ እርሷ በድህነት ጉልት ሽጣ የምትኖር ነበረች አሉ፡፡ ለልጆቿ የላመ የጣመ መብላት ቀርቶ ቆሎ ቆርጥመው ለማደር እንኳን ይቸገሩ ነበር፡፡ በየዓመቱ ግን «የአባቷ ውቃቤ» እያስጓራ ሲያንዘፈዝፋት ለፍታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ወሰራ ዶሮ አርዳ ትለማመነው ነበር፡፡ የውቃቤ ዶሮ ሦስት ጊዜ በጭንቅላት ላይ ዙሮ መንገድ ይጣላል እንጂ ሰው አይበላውም፡፡ እነዚያ ድኾች ልጆቿ የዶሮን ድምፅ ሰምተው እንጂ በልተው አያውቁም፡፡ ከአያት ከቅድመ አያቶቿ የተቀበለችው ውቃቤ ግን ዶሮ እያረደች እንድትበላ ሳይሆን ዶሮ እየወረወረች እንድትኖር ያደርጋታል፡፡
እንዴው ግን እኛም ውቃቤ ይኖርብን ይሆን እንዴ? ለልጆቻችን የሚያስፈልገውን፣ ለሀገር የሚጠቅመውን አስትቶ ለዕለት ዛር መወጫ ሲያስደገድገን የሚኖር፡፡ አንዳንዴ የምንሠራቸውን ለአፍታ፣ ለጊዜው፣ ለሆነ ችግር መወጫ፣ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ፣ የሚውሉ ነገሮች ስታዩ ውቃቤ ያለብን እንጂ ለሰባት ትውልድ የሚሆን ኃላፊነት የተጣለብን ዜጎች አንመስልምኮ፡፡
አሜሪካ ዛሬ የምትቸገርበትን የኢራን የኒኩልየር መሣርያ ለኢራን ያመጣችላት ራሷ ናት፡፡ ኢራናውያን ኒኩልየር እንኳን መኖሩን በማያውቁበት ዘመን በራቸውን አንኳኩታ ኑክልየርኮ ለኃይል ምንጭ ይጠቅማል ግዙኝ ብላ የሄደችው ራሷ ነበረች፡፡ ይኼው አሁን ማጣፊያው አጠራት እንጂ፡፡
እናም ከመወሰናችን፣ ከመገንባታችን፣ ከመሸጣችን እና ከመግዛታችን፣ ከመጻፋችን እና ከመዝፈናችን፣ ከማስተማራችን እና ከመግለጣችን፣ ከማደራጀታችን እና ከማዋቀራችን፣ ከማወጃችን እና ከመፍረዳችን በፊት ይህ ጉዳይ እስከ ስንት ትውልድ ሊጠቅም እንደሚችል ለአፍታ እናስብ፡፡ ለልጆቻችን ውቃቤ እንዳናወርሳቸው፡፡
አቡዳቢ

49 comments:

 1. እኔ ለልጆቼ ቆሎው ያርብኛል

  ያባቴ ውቃቤ ያስገፈግፈኛል

  Z Awassa
  ለልጆቻችን ውቃቤ እንዳናወርሳቸው፡፡

  ReplyDelete
 2. እኛ ስንሞት ሰርዶ ሳይሆን ሀገር ናት መብቀል ያለባት፡፡ ስለ ሰባት ትውልድ የማናስብ ከሆነ ኢትዮጵያ ማለት እያንዳንዱ ትውልድ እንደገና እያፈረሰ የሚሠራት ሀገር ትሆናለች፡፡
  well articulated and nice view Dani. yes u are right we have to try to think out of our box.

  ReplyDelete
 3. ሳላህዲን ግን አርቆ አስተዋይ ነበርና «አይሆንም፤ እኔ እዚህ ከሰገድኩ ወደፊት የሚመጡ ሰዎች ሳላህዲን የሰገደበት ነው ብለው በዚሁ ይቀጥላሉ፣ ያ ለእናንተ መልካም አይሆንም» አለና ከጎልጎታ ወጣ ብሎ በነበረው ቦታ ላይ ሰገደ፡፡

  ReplyDelete
 4. በሀገራችን «ጉድጓድ ስትቆፍር ማን እንደሚወድቅበት አታውቅምና እጅግ አታርቀው» ይባላል፡፡ ምናልባት ቆፋሪው ራሱ ሊወድቅበት ስለሚችል፡፡ ትናንት በግዴለሽነት የጻፍናቸው እና የተናገርናቸው ነገሮች ሰባት ትውልድ ቆጥረው ዛሬ ዛሬ ጎሳ ከጎሳ እያባሉን፣ ሕዝብ ከሕዝብ እያዋቀሱን እና ዋጋ እያስከፈሉን ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ቤተ መንግሥቶቻቸውን እንጂ እሥር ቤቶችን በሚገባ አልሠሩልንም፡፡ እንኖራለን እንጂ እንታሠራለን ብለው ስላላሰቡ፡፡ በሚገባ ያልተሠሩት እሥር ቤቶች ግን ከታሠረው ተራ ሕዝብ ይልቅ የጎዱት የታሠሩትን እና የሚታሠሩትን መሪዎች ነው፡፡ ድኻውማ ያንን ችግር ቀድሞ ያውቀዋል፡፡ እነርሱ እንጂ፡፡ ዮናስ አበበ

  ReplyDelete
 5. egziabiher endezih yale milketa yalachewun sewoch yibarkachew antenim chemiro.

  ahun ethiopia yalech bet hunatie betam yemiasazin new beye dekikaw bemiwetu awajoch,memeriawoch,principle of law yetasu, yenegen yalasebu ena giltsenet yegodelachew new;enen chemiro nege min memeria yimetal eyalin bisigat yetemolabet nuro eyegefan new;ebakachehu lenege enasib

  ReplyDelete
 6. ዲ/ን ዳኒ
  ውቃቢ የሚለው ትርጉም በትክክለኛው ቦታ የገባ አይመስለኝም፡፡

  አንተም ስትፅፍ ስንት ትውልድ እንደሚያነበው አስበህ ብትፅፍ ፡፡

  ReplyDelete
 7. Dear Daniel,

  When we analyze the political history of Ethiopia.We are testified that we built the polity after we completely destroyed it.

  Actually, the modern state formation in Ethiopia was initiated by Tewodrose, elaborated by Yohannis, consolidated by Menelik and finalized by Haileselassie.

  However, the predecessors of them disliked incremental changes at all,they rather destroyed our historical heritage and come back with new and controversial way of thinking that totally affected our future existence.

  The generation that ignores history, has no past and won't have future. It is crystal clear, if you want to understand today, you have to search yesterday. History is a living whole. If one organ be removed, it is nothing but a lifeless mass.

  Hence, we should think for our future seventh generation when we decide to do or not to do something. To sum up, A generation that ignores history has neither past nor future.

  ReplyDelete
 8. Egzaibhere Ke'sega fetena ke'mekera nefese yetebikeh. This is a very nice analysis! I pray so God will give us a leader who thinks for the 7th generation. This is both for Spritual and governmental leaders. Egziabhere ye'tenbit mefesmiya ayargen Amen.

  ReplyDelete
 9. Dear Dani
  Not only our leaders,we(the ordinary people )are part of the game.We clean our homes but pollute the village.We preach about love but we plant hate....aren`t we short sighted?
  Worku

  ReplyDelete
 10. ዳ/ዳኒ በጣም ጥሩ ነው አይ ዳኒ ውቃቤ አልከው ከዚያም በላይ ቢኖር ጥሩ ነበር የእጛ ጉድ አያልክም ለነገ ሳይሆን ስለዛሬ የሚያስብ ትውልድ የሱን ደስታ እንጂ ስለሌላው የማያስብ ባሕሪያዊ አሳማ አስተሳሰባዊ ደካማ ከተማረው እስከ አልተማረው
  እለታዊ እይታ እንጅ እልታዊ እራይ የለው ትውልድ ተፈጥሮም እየተፈጠረም ነው አረ ጎበዝ የጊዜ ጀግና አጣን በውነት ያ አርበጛ በላይ ዘለቅ ከመስቀሉ በፊት የትናገረው «በውነት አንች አገር ጀግና አይወለድብሽ» ያለው መሪር ቃል በውን በዚሕ ትውልድ ደረሰ ...ኦ አምላኬ አታድርገው አረወገን ስለ ዛሬ ሳይሆን ስለ ነገ ኢትዮጵያ እናስብ ከመለያየት መቀራረብ ካኩራፊነት ይቅር ባይነት ተቻችለን አገራችንን እንገባ !!!

  ReplyDelete
 11. It is nice article Dn Daniel. I have one comment for you. Most of the time when you mentioned Ethiopian Kings, you jump from King Tewodros to King Minilik but it is good also to mention the name of King 4th Yohannes because he ruled Ethiopia as well for 17 years.

  ReplyDelete
 12. This is how real human being supposed to think but we are losing our identity, so we need someone to remind us....thxs D.Danial

  ReplyDelete
 13. Dani yihe tshuf Mesqel Adebabay betiliqu tetsifo hulu bianebew des balegn.
  Egzyabher yistilin.Endezih yemiasib betefabet le hodu bilo wendimun telfo lemetal enqilf yata sew bemolabet gize ye ezih aynet tshuf manbeb nefs yizeral.

  ReplyDelete
 14. Gerum tsehuf new Dany.Ahunem Egeziabher aemerohen yigeletseleh.yenenem endehu. Amen.

  ReplyDelete
 15. This is really great way of thinking. Ketesfa mekuret yemimelis tsihuf new. Egziabher kenawin yasasben antenim yibarkih!!!

  ReplyDelete
 16. Dn.Daniel, let the Almighty God bless you 'Iske sebat bet!!!! kezema belay kale!!' 'tsegawin yabizalih!!!!!' Dingil Titebikih, zerih tibarkilih...no words for you!!!'

  Let God bless the world!!!

  Thanks,
  Hailemariyam

  ReplyDelete
 17. Thanks dear dani! As u said our leaders so far are shortsighted and those who commented said all of us are shortsighted too. I completely agree; but what we must know leaders are few but their impact is far reaching if they have followers for z good or z bad. I think what we don have is WE DON APPRECIATE THOSE WHO DIE, WRITE, CRY, LIVE FOR US. Even we don know them. We listen to those who just brag and destroy us! What a curse!

  ReplyDelete
 18. Dear Dn.Dani
  A perfect article as usual if it gets a reader who can contemplet and act upon it.
  But Dani I am afraid because we Ethiopians are not currently thinking for our brothers and sisters living besides us leave alone thinking for the future; it is really gloomy.
  So what I suggest is let us first think about each other and then the rest will come.....

  ReplyDelete
 19. ዛሬ ወያኔ እየተከለው ያለው የዘረኝነትና የብድር ነቀርሳ በ7 ትውልድስ ይነቀላል ብለህ ነው ዳኒ? አንዱ ብሄረሰብ ሌላው ብሄረሰብ አካባቢ ሄዶ መስራት የማይችልበት የብሄርተኝነት ደረጃ ላይ ደርሰናል እኮ። በየቢሮው በየንግድ ቦታው ሁሉ ጨዋታው በብሄር ከሆነ ዋል አደር ብሎ የለም። በየቢሮው ውጤት ተኮር የሚሰጠው፤ ፊልድ የሚላከው፤ እንደፈለገው ለመሆን ፈቃድ የሚያገኘው በዘር ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። ብቻ ይህች የድንግል ማርያም ሀገር እግ/ር ይታደጋት እንጂ ምን እንላለን።
  የስልጣን ዘመኑን ማራዘም እንጂ የህዝብ ጉዳይ የማይገደው መንግስት አምላክ ይብቃህ ይበለው።

  ReplyDelete
 20. Dear Daniel
  አሜሪካ ዛሬ የምትቸገርበትን የኢራን የኒኩልየር መሣርያ ለኢራን ያመጣችላት ራሷ ናት፡፡ ኢራናውያን ኒኩልየር እንኳን መኖሩን በማያውቁበት ዘመን በራቸውን አንኳኩታ ኑክልየርኮ ለኃይል ምንጭ ይጠቅማል ግዙኝ ብላ የሄደችው ራሷ ነበረች፡፡ ይኼው አሁን ማጣፊያው አጠራት እንጂ፡፡
  እናም ከመወሰናችን፣ ከመገንባታችን፣ ከመሸጣችን እና ከመግዛታችን፣ ከመጻፋችን እና ከመዝፈናችን፣ ከማስተማራችን እና ከመግለጣችን፣ ከማደራጀታችን እና ከማዋቀራችን፣ ከማወጃችን እና ከመፍረዳችን በፊት ይህ ጉዳይ እስከ ስንት ትውልድ ሊጠቅም እንደሚችል ለአፍታ እናስብ፡፡ ለልጆቻችን ውቃቤ እንዳናወርሳቸው፡፡

  You just wrote what was in my heart. Egziabhere Kale Hiywotin Yasemalin, yetebkih, yageliglot zemenihin yarzimilin

  ReplyDelete
 21. ውድ ዲ. ዳንኤል

  እኛ ስንሞት ሰርዶ ሳይሆን ሀገር ናት መብቀል ያለባት፡፡ ስለ ሰባት ትውልድ የማናስብ ከሆነ ኢትዮጵያ ማለት እያንዳንዱ ትውልድ እንደገና እያፈረሰ የሚሠራት ሀገር ትሆናለች፡፡
  ብትል
  በቅርቡ በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የተጻፈ Pioneers of change in Ethiopia የተሰኘ መፅሃፍ ላይ ያነበብኩት የሚከተለው ትዝ አልኝ፡ (ንግግሩ በ ቀ. ኃ/ስላሴ ና በበጅሮንድ ተ/ሓዋርያት ኃ/ማርያም መካክል ይተደረገ ቃለ ልውውጥ ነው፡

  አፄ ኃይለ ሥላሴ፡ አንተ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የምትለው ኢትዮጵያ ያለ እኔ ምንም አይደለችም እድልዋ ክኔ ጋር የተሳሰረ ነው።እኔ ነኝ የማደርሳት ካለኔ ትኖራልች ብለህ አታስብ።

  ተክለ ሃዋርያት፡ እንዴት እንደዚህ ያስባሉ? ኢትዮጵያኮ ሕያው ነች! እኛ ሁላችን አላፈዎች ነን። እስቲ ይመልከቱ! አፄ ምኒልክ ዛሬ የት ናቸው? አባትዎ ራስ መኮንን የት አሉ? ሌሎቹስ ታላላቆችና ገናናዎች የነበሩት ሁሉ የት ናቸው? ኢትዮጵያ ግን አለች ወደፊትም ትኖራለች።

  እንዲሁም እነ አቶ መለስና ጉዋደኞችዎ ኢትዮጵያን መገነጣጠልና እርስ በርሳችን ተናክሰን የምናልቀበትን የማይጠቅም ብሎም ብዙው ሃሰት የሆን ራሳችሁ የፈጠራችሁትን የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ተገንብቶ ሳያልቅ ብትንትኑ እየወጣ ያለውን የማይረባ ይህውም በሚመጣው ትውልድ ጊዜ እንኩዋን ትክፍሎ የማያልቅ እዳ የሚሰራውን ግንባታችሁን ትታችሁ መስርታዊ ከሆነው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ከሰጠው ነጻነትና ፍትሕ ብትጀምሩ እንዲሁም የቀደሙ አባቶቻችንም በደምና በአጥንታቸው አስከብረውት ያለፉትን ኢትዮጵያዊ ብለን ራሳችንን የምንጠራበትን ኩራታችንን ብትመልሱልን መልካም በሆነ ነበር። ነገር ግን ማንን እንዴት እንዳወረዳችሁ እንኩዋን የዘነጋችሁ በሚመስል ሁኔታ ህዝቡ ትከሻ ላይ ተዝናንታችሁ የተቀመጣችሁ ይመስላል። የሚመክራችሁ አጥታችሁ ካልሆነ በቀር የተጸየፋችሁት የኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ባስተማራችሁ ነበር። ለአሁኑ እንዲሁ እንደናንተ ያለ ዝንጉ ይስጨነቀው ዮፍታሄ ንጉሴ የሚባል ጸሃፊ ያለውን ብዬ ላብቃ፡
  ዝም ብዬ ቢያየኝ ዝም ያልኩ ምስሎታል፤
  ሲታሰብ ነው እንጂ ዝም ማለት የታል።

  ሰላም
  ሙሉጌታ ሙላቱ ነኝ
  ክቫንኩቭር ደሴት

  ReplyDelete
 22. kale hiwot yasemalin dn danielእኔ ለልጆቼ ቆሎው ያርብኛል
  ያባቴ ውቃቤ ያስገፈግፈኛል. betam tiru eyita new especially for this generation and EPRDF thought

  ReplyDelete
 23. "ወደድንም ጠላንም ይህ ትውልድ የዐፄ ቴዎድሮስ፣ የዐፄ ምኒሊክ፣ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ እና የደርግ ፖሊሲዎች፣ አሠራሮች፣ አስተሳሰቦች፣ ውሳኔዎች እና ሥራዎች ውጤት ነው፡፡ ቢፈልገውም ባይፈልገውም የእነርሱ ተጽዕኖ እንዲህ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ በጎ ተግባራቸው ጠቅሞታል፡፡ ስሕተታቸውም ጎድቶታል፡፡ ወይ ሥራ ቀንሶለታል፤ ወይ ሥራ ጨምሮበታል፡፡ የኢሕአዴግም አመራር፣ አሠራር እና አስተሳሰብ እንደዚሁ በቀጣይ ትውልድ ላይ መንፀባረቁ የማይቀር ነው፡፡" I invite this quote for EPRDF have who extremely hate to the previous gov't

  ReplyDelete
 24. ባለፈው ጊዜ ውሾቹን ተው በላቸው በሚለው ፅሁፍህ ላይ የቤተ-ክርስቲያን መቃጠል እና የኢትዮጵያ ሰራውት ሱማሊያ መግባት ጋር የተያያዘ ነገር ስለመኖሩ አስተያየት ልፅፍልህ ስል የግንኙነት ችግር አጋጥሞኘ ትቼው ነበር አሁን አንተ እራስህ ርዕሱን በማነሳትህ ደስ ብሎኛል ፤፤የሶማሊያ አማጺ ሃይል ሆነ የሽግግሩ መንግስት ለኔ ሁለቱም አንድ ናቸው የኢትዮጵያ መንግስት ማንንም አምኖ ሆነ ጥቃትን ፈርቶ መዋጋት አልነበረበትም አለበለዚያ ደግሞ እንደ ደቡብ ኮሪያ ሁሉም ሀገራት የዘመቱ ለት መግባት ይሻላል በእርግጥ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች በውስጡ እንዳሉ እገምታለሁ ቢሆንም ግን በምእራባውያን ተፅዕኖ ምክንያት ወታደሮቻችን እንዲያልቁብን አንፈልግም ፤፤ ከአጼ ኀይለ ስላሴ ጀምሮ የሶማሌ ጉዳይ ያለምንም መፍትሄ እዚህ ደርሶል፤፤በተረፈ ለነዚህ ሱማሌዎች የምመኝላቸው እነሱን ወደ ህንድ ውቅያኖስ ገፍቶ መክተትና እፎይ ማለት ሣይሻል አይቀርም

  ReplyDelete
 25. You just wrote what was in my heart keep it up!!

  ReplyDelete
 26. yes we all have some sort of shortage to see a bit far... thanks for you. as usual the great man kebede Michal said "LE SERA LE EWUKET GILO LEMENESAT QOSQUASH YEFELIGAL YESEW LIJ ENDE ESAT!!!" so keep writting it is wonderful task... we including any of us has to be a part of the solution rather than complaining on the past...those butifuls were done by the former generation... the future yes always the future of at least our family is in our hand!!!

  ReplyDelete
 27. ሰላም ብያለሁ ዳኒ!
  ሰዎች አንድ አንዴ ግን ስንናገር በስሜት ፈረስ እየጋለብን ባይሆን መልካም ይመስለኛል። አስተዋይ ሰው ካለ ይህ ፅሁፍ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ይመስለኛል።"ተወደደም ተጠላም ሰው የራሱ ዘመን ብቻ ውጤት አይደለም ያለፉት ትውልዶች ውሳኔና ተግባር ጭምር እንጂ" እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እየተነሳን ያለንበትን ዘመን እና እስተዳደር ስነወቅስ ስናቀላብስ እንኖራለን ነገር ግን አይደልም ሀገር አንድ ቤተሰብ ለመምራት ቀጥ ብሎ የሚሄድ ስርአት ወይም መዋቅር(system) ያስፈልጋል። አንድ ጊዜ ቀጥ ብሎ መሄድ የጀመረን ስርአት ወይም መወቅር(system) ደግሞ ተፈፃሚነቱን መከታተል እንጂ መሪ ሁሉ ላያስፈልገው ይችላል:: ታዴያ ከዚህ በፊት ያልነበረን አሰራርና መዋቅር ወያኔ ፣ ኢሀዲግ እያልን የምንጮህበት መንግስት ከየት ያመጣዋል። እንደኔ እንደኔ ብዙ መስራት የሚጠበቅበት ነገር ቢኖርም ከዚህ በፊት ያልነበረውን system ለመዘርጋት የጀመረው መውተርተር ግን ይበል የሚያስብል ይመስለኛል። ለኢትዮጽያ ተስፋን ፈንጥቆላት የነበረው ብርሀን የጠፋው ድሮ የአክሱምና የዛግዊ ስርዎ መንግስት ማክተም ጋር ተያይዞ ነው። የመጀመሪያው ወይም ሁለተኛው ትውልድ ምን ንቁ ቢሆን ያ ንቃት ተወራርሶ እስከ ሰባተኛው ትውልድ ካልደረሰ ታሪክ ማጌጫ እንደማይሆን በአይናችን እያየን በጆሮችን እየሰማን ነው። ላሊበላን ኢትዮጽያውያን አልገነቡትም እሰከመባል ያደረሰን በወቅቱ የነበረው ተተኪ ትውልድ እንቅልፍ ወስዶት ስለነበር ነው። አንድን ሀገር ለማሳደግ የዛችው ሀገር ያንድ ዘመን ትውልድ መጥፋት ወይም ማለቅ አለበት። ቻይናን እዚህ ቦታ ያደረሳት ይኖሩባት የነበሩ ያንድ ዘመን ሰዎች የጀመሩት የሀገር ዘመቻ ስራ እስኪያልቅ የዘሩት እህል እስኪደርስ እርዳታ ቻይና እንዳይደርስ ከልክለው በርሀብ እያለቁ የቀሩት ጫማቸውን ቀቅለው እየበሉ ከፍተኛ መስዋትነት ከፍለው ለሀገራቸውና ነገ በውስጧ ለሚኖሩ ፍጡራን ለእድገት፣ ለሰላም፣ ለጥበብ፣ የሚፋጀውን የሰው ፊት እናዳያዩ
  ሞተውላቸው ስለነበር እንደሆነ አለም የሚያውቀው እውነት ነው። አኛ ኢትዮጽያውያን አደለም ለነገ ትውልድ ማሰብ ቀርቶ ደማችን የወለድነው ልጂ እኛን ኩራዝ አብርቶ አብልቶ ሲጨርስ የተረፈንን ይበላል፡ እኛ ሲጠበን ወይ ልብሱ ሲያረጂ ልጅ እንዲለብሰው ይደረጋል ከስምንት ልጂ በላይ ወልደን ነገ ሲደርስ እንዲጦረን እንዲከባከበን እናስባለን ባጠቃላይ ልጂ መፈጠሩ ራሱ የኛ አገልጋይ ባርያ እንዲሆን እንጂ ሌላ አላማ ያለው መስሎ አይሰማንም። እድገቱ በራስ ወዳድነት፣ በስግብግብነት፣ በዘረኝነት፣ በጠባብነት፣ በጉበኝነት፣ በተራ ስነ ቃልና ወሬ በታጠረ ማህበረሰብ ውስጥ የሆነ ትውልድ ደግሞ አብሮ ስለመኖር፡ አብሮ ስለማደግ ተግባብቶ አገር ስለማቆየት እንዴት ሊማርና ሊያስብ ይችላል። እንደኔ እንደኔ ይህ በአጭር ጊዜ የማደግ ምኞት ዛር የተጠናወተን አለም አንድ መንደር መሆኖና የምእራባውያንን እድገት ከማየት የመጣ መቋመጥ ይመስለኛል:: ይህ ደግሞ የትም አያደርሰንም ለሀገርና ለነገው ትውልድ ካሰብን መስዋትነት መክፈል መቻል እንጂ። እኔ ማን ነኝ ትናንት የት ነበርኩ ዛሬ ምን ላይ ነኝ ለሚለው ጥያቄ የእኔ ድርሻ ትንሽ ሊሆን ይችላል ነውም ነገ የት መድረስ አለብኝ የሚለው ጥያቄ ግን ለኔም ለሀገርም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ይመስለኛል። እስኪ ትችቱን ስድቡን ማንጎጠጡን ወሬውን ትተን እንደዜጋ ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል ብለን እንነሳ፣ በየመስሪያ ቤታችን ያሉትን ብልሹ አሰራር እንዲስተካከሉ እስከመባረር እንፋለማቸው እኛ ብንባረር እንኳ ነገ የኛ ልጂ ሲተካ እፎይ ብሎ እንዲሰራ አመቻችተንለት ይሆናል...!!

  ReplyDelete
 28. ውቃቢ የሚለው ትርጉም በትክክለኛው ቦታ የገባ አይመስለኝም፡፡

  አንተም ስትፅፍ ስንት ትውልድ እንደሚያነበው አስበህ ብትፅፍ ፡፡
  ወንድሜ አንባቢ እባክህን ከመተቸትህ በፊት ግዚ ወስደህ ደጋግመህ አንበው::ለመተቸት አንቸኩል ለማለት ነው::

  ReplyDelete
  Replies
  1. Ok! men are you from the reign of RAS ALI?

   Delete
 29. መጀመሪያ አካባቢ አስተያየት የሰጠኸው ፊልድ የሚላከው እድገት የሚሰጠው በዘር ሆኗል ብለሃል ይህ ምንም አይደንቅም ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በሚመራት ቤ/ክ እንኳን በስብከተ ወንጌል ሃላፊነት ወይም በአለቃነት ለመመደብ በዘርና በገንዘብ ሆኖ የለ እንዴ?
  ታዲያ ቤ/ክ ያላገኘነውን ታማኝነት እንዴት ከአለም እንጠብቃለን?

  በዚህ ዘመን ወደ ፈጣሪ መጮህ ብቻ እንጂ በሰው ጥረት የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡

  ዘመኑ አለቀ ብቻ ሳይሆን ተሟጠጠ፡፡

  ReplyDelete
 30. ውድ አቶ አክሊሉ፤
  በመልዕክትዎ ከሞላ ጎደል ብስማማም በመደምደሚያዎ ላይ ባቀረቡት በሚከተሉት ሃሳቦች ግን አልስማማም፤
  “….እንደኔ እንደኔ ይህ በአጭር ጊዜ የማደግ ምኞት ዛር የተጠናወተን አለም አንድ መንደር መሆኖና የምእራባውያንን እድገት ከማየት የመጣ መቋመጥ ይመስለኛል:: ይህ ደግሞ የትም አያደርሰንም ለሀገርና ለነገው ትውልድ ካሰብን መስዋትነት መክፈል መቻል እንጂ።….”
  እንደ እኔ እንደ እኔ… ያሉት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ምናልባት ተዘንግትዎ ይሆናል እንጂ በ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ የነበሩ እንደነ ሃኪም ወርቅነህ እሸቴ ፤ከንቲባ ገብሩ ደስታ፤ ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ፤በጅሮንድ ተ/ሃዋርያት ኃ/ማርያም አለቃ ታዬ ገ/ማርያም ወዘተ ኢትዮጵያውያን ምሁራን አሁን ስናየው ባይሳካም ለሃገራቸው ይመኙላት የነበረው እንደ ጃፓን ያለ በአጭር ጊዜ እመርታ ላይ የደረሰ ስልጣኔ እንጂ የግድ እንደ ምዕራባውያኑ ብዙ መቶ አምታት የፈጀን አልነበረም። እራስዎ እንደ ምሳሌ የተጠቀሙባት ቻይናም የዚሁ ፈጣን እደገት ማሰረጃም ነች። በእርግጥም ቻይና ምዕራባውያን ለሚሉን የኢኮኖሚ ልዕልና ከዴሞክራሲ ልዕልና ጋር የተቆራኘ ነው ለሚለው ፍልስፍናቸው ስህተት እንደ ማረጋገጫ ከመሆን በላይ ካፒታሊዝም የዲሞክራሲ ማረጋገጫ እንዳልሆነና በሃገራችን እይተደረገ እንዳለው የኢኮኖሚ እድገት አለ ብሎ መለፈፍ የዲሞክራሲ ማረጋገጫ እንደማይሆን ጉልህ ማስረጃ ነው።በእርግጥም የምዕራባውያንን እድገት አይተን ሀገራችን እንዲህ ብትሆን ብለን መቓመጥ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ መሆን አይገባውም። በእርግጥ ስልጣኔ የሚመስሉ ግን ያልሆኑ ርካሽ ለነሱም ያልበጁ በዕውቀት፤ በመረዳትና፤ በጥበብ ሳይሆን በመመልከት፤ መዝናናት፤የነገን በዛው ማቆየት ይቻል ይመስል በራሳችን ምዕናብ ውስጥ በፈጠርነው ምናባዊ ዓለም ውስጥ ስንኖር ነው። (a world of illusion and spectacle)

  “…. እንደዜጋ ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል ብለን እንነሳ፣ በየመስሪያ ቤታችን ያሉትን ብልሹ አሰራር እንዲስተካከሉ እስከመባረር እንፋለማቸው እኛ ብንባረር እንኳ ነገ የኛ ልጂ ሲተካ እፎይ ብሎ እንዲሰራ ይሆናል...!!”
  የመንግስት ምስሪያ ቤት ለመስራት ፤ ስርቶም እድገት ለማግኘት ፤ ሀገር ውስጥ ተዘዋውሮ ለመስራት፤ ትምህርት ለመማር የፖለቲካ አመራሩ ደጋፊነት፤ የዘርና የጎሳ ማንነት በሚጠይቀበት ሀገር የመስሪያ ቤቶችን የውስጥ አሰራር እንከል የማይወጣለት ብናደረገው እዚህጋ የዳንኤልን “ድንጋይ ፈላጮች” ከሚለው መጣጥፍ ልዋስና፤ ድንጋይ ፈላጭ እንጂ ሌላ አይደለንም።እታች ለሚሰሩና 7 ትውልድ ሊደርሱ ለሚችሉ መሰረቶትችን ለመገንባት አመራሩ ላይ ያለው የጊዜው መንግስት የሚቀይሳቸው ፖሊሲዎችና መመሪያዎች እጅግ ወሳኝ ናቸው።ብዙ ሳልርቅ በሰበብ ባስባቡ በገፍ የሚታሰሩትን የሃገሪቱ ዜጎች፤ ጋዜጠኞች፤ምሁራንና፤የፖለቲካ ተቃዋሚዎች መጥቀስ ለዚህ በቂ ማስረጃ ይመስለኛል።እነዚህን ዜጎች ከማዳምጥ ይልቅ ማግለልና ሲብስም ያማይገባ ቅጣትን መቅጣት ካለፈው የራሳችን ታሪክ አለመማር ነው።ይህም ይህን የሚተካው ደግሞ ከእንደገና ጀምርኩ ለማለት ጥሩ ማመካኛ ያገኛል።
  እኔን የሚያሳዝነኝና የምሰጋው እኛ ለልጆቻችን የምንተዋት ኢትዮጵያ ከዚሕ በፊት ከነበሩ የከፉ ያልናቸው ስርዐቶች እንኩዋን ካስረከቡን ያነሰ ግዛት፤ ስልጣኔና፤ መልካም ማሕበራዊ እሴት የመነመነባት ኮሳሳ ሀገርን እንደሆነ ነው። እንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ለኢትዮጵያውያን “እናትህን ያገባ ሁሉ አባትህ ነው” የሚለው ብኂል እንደማይሰራ ነው።
  ሰላም!
  ሙሉጌታ ሙላቱ
  ከቫንኩቭር ደሴት

  ReplyDelete
 31. A nation, which fails to learn from history, is destined to repeat is mistakes.
  This contrary, especially this regime is very famous for its shortsightedness.
  From the very beginning EPRDF, has been engaged in self-destruction scenarios.
  They never listen others whatsoever.
  Ethiopia is a very big country with rich patriotic history. However, soon or latter, the present selfishness & shortsightedness’ will let this country down,
  For those who are willing to learn at least from recent history, there is still time to rectify the present ill. Otherwise, no body will be emerged as a winner when the
  Doomsday comes.

  Thanks Dani &
  God bless Ethiopia!!

  ReplyDelete
 32. yemitsfachew wegoch ke haymanot sirhet gar endaytala

  ReplyDelete
 33. እስከ ሰባት ትውልድ!!!

  አንድ ስራ ሁላችሁንም እንዳዝ ይፈቀድልኝ... ሁላችንም ይህን ጽሁፍ ባነበብንበት መንፈስ በኑራችን(በሁሉም አቅጣጫ) እያደረግን ስላለው ነገር ማድረግ ስላሰብነው ነገር በደንብ እናስብ በመቀጠል እንጻፈው ከዚያ ለሰባቱ ትውልድ ምን እያደረግን እንደሆነ... በትክክለኛው መንገድ ላይ ነን? ማድረግ ያለብንን እያደረግን ነው? መልሱን ለራሳችሁ። ይህም አሳቤ የትውልዱ ውጤት ነው።

  ዳኒ እናመሰግናለን።

  ReplyDelete
 34. Selam Dn. Daniel
  I like your article. This is how real human being supposed to think. What can we do? God bless Ethiopia.
  Makusha

  ReplyDelete
 35. እናም ከመወሰናችን፣ ከመገንባታችን፣ ከመሸጣችን እና ከመግዛታችን፣ ከመጻፋችን እና ከመዝፈናችን፣ ከማስተማራችን እና ከመግለጣችን፣ ከማደራጀታችን እና ከማዋቀራችን፣ ከማወጃችን እና ከመፍረዳችን በፊት ይህ ጉዳይ እስከ ስንት ትውልድ ሊጠቅም እንደሚችል ለአፍታ እናስብ፡፡ ለልጆቻችን ውቃቤ እንዳናወርሳቸው፡፡

  ReplyDelete
 36. እናም ከመወሰናችን፣ ከመገንባታችን፣ ከመሸጣችን እና ከመግዛታችን፣ ከመጻፋችን እና ከመዝፈናችን፣ ከማስተማራችን እና ከመግለጣችን፣ ከማደራጀታችን እና ከማዋቀራችን፣ ከማወጃችን እና ከመፍረዳችን በፊት ይህ ጉዳይ እስከ ስንት ትውልድ ሊጠቅም እንደሚችል ለአፍታ እናስብ፡፡ ለልጆቻችን ውቃቤ እንዳናወርሳቸው፡፡
  Mamush,MN

  ReplyDelete
 37. Well said Dani,bertalin

  ReplyDelete
 38. 10Q Dani&Sheger fm 102.1
  mule

  ReplyDelete
 39. o my God d. gieta kekifu yitebikih

  ReplyDelete
 40. kale heywot yasemalin

  ReplyDelete
 41. good article. but every one don't understand as you did that's why different comment.

  ReplyDelete
 42. Dear Brother, Daniel,

  God bless you for writing this excellent message. Really, you are doing great for your country. Be sure that there are lots of people who are following your idea. What we lack is how to integrate the efforts of those interested and committed people to the advancement of our country. Thank you for your countinuous writing that gives hope and motivation for those positive thinkers to Ethiopia.

  ReplyDelete
 43. minewu tefah wude Daniel, please tell us your reason it is long to write

  thank you

  ReplyDelete
 44. እኔ ለልጆቼ ቆሎው ያርብኛል
  ያባቴ ውቃቤ ያስገፈግፈኛል
  አለች አሉ ሴትዮዋ፡፡ እርሷ በድህነት ጉልት ሽጣ የምትኖር ነበረች አሉ፡፡ ለልጆቿ የላመ የጣመ መብላት ቀርቶ ቆሎ ቆርጥመው ለማደር እንኳን ይቸገሩ ነበር፡፡ በየዓመቱ ግን «የአባቷ ውቃቤ» እያስጓራ ሲያንዘፈዝፋት ለፍታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ወሰራ ዶሮ አርዳ ትለማመነው ነበር፡፡ የውቃቤ ዶሮ ሦስት ጊዜ በጭንቅላት ላይ ዙሮ መንገድ ይጣላል እንጂ ሰው አይበላውም፡፡ እነዚያ ድኾች ልጆቿ የዶሮን ድምፅ ሰምተው እንጂ በልተው አያውቁም፡፡ ከአያት ከቅድመ አያቶቿ የተቀበለችው ውቃቤ ግን ዶሮ እያረደች እንድትበላ ሳይሆን ዶሮ እየወረወረች እንድትኖር ያደርጋታል፡፡
  እንዴው ግን እኛም ውቃቤ ይኖርብን ይሆን እንዴ? ለልጆቻችን የሚያስፈልገውን፣ ለሀገር የሚጠቅመውን አስትቶ ለዕለት ዛር መወጫ ሲያስደገድገን የሚኖር፡፡

  ReplyDelete
 45. እኔ ለልጆቼ ቆሎው ያርብኛል
  ያባቴ ውቃቤ ያስገፈግፈኛል
  አለች አሉ ሴትዮዋ፡፡ እርሷ በድህነት ጉልት ሽጣ የምትኖር ነበረች አሉ፡፡ ለልጆቿ የላመ የጣመ መብላት ቀርቶ ቆሎ ቆርጥመው ለማደር እንኳን ይቸገሩ ነበር፡፡ በየዓመቱ ግን «የአባቷ ውቃቤ» እያስጓራ ሲያንዘፈዝፋት ለፍታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ወሰራ ዶሮ አርዳ ትለማመነው ነበር፡፡ የውቃቤ ዶሮ ሦስት ጊዜ በጭንቅላት ላይ ዙሮ መንገድ ይጣላል እንጂ ሰው አይበላውም፡፡ እነዚያ ድኾች ልጆቿ የዶሮን ድምፅ ሰምተው እንጂ በልተው አያውቁም፡፡ ከአያት ከቅድመ አያቶቿ የተቀበለችው ውቃቤ ግን ዶሮ እያረደች እንድትበላ ሳይሆን ዶሮ እየወረወረች እንድትኖር ያደርጋታል፡፡
  እንዴው ግን እኛም ውቃቤ ይኖርብን ይሆን እንዴ? ለልጆቻችን የሚያስፈልገውን፣ ለሀገር የሚጠቅመውን አስትቶ ለዕለት ዛር መወጫ ሲያስደገድገን የሚኖር፡፡

  ReplyDelete
 46. ¨ስለ ሰባት ትውልድ የማናስብ ከሆነ ኢትዮጵያ ማለት እያንዳንዱ ትውልድ እንደገና እያፈረሰ የሚሠራት ሀገር ትሆናለች¨

  ReplyDelete