Friday, December 28, 2012

ሥጋ፣ ኅሊናና ልቡና


በአሜሪካዋ ኮኔክቲከት ግዛት በሳንዲ ሁክ ትምህርት ቤት ሕጻናትና መምህራን ላይ የተፈጸመው ኢ ሰብአዊ ግድያ ሰሞኑን የዓለም መነጋገርያ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ጉዳዩን አሳዛኝና አሰቃቂ ያደረገው ደግሞ ምንም በማያውቁ ሕጻናትና በሥራ ላይ በነበሩ መምህራን ላይ የተፈጸመ መሆኑ ነበር፡፡ እነዚህ አካላት ከገዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ‹ጠብ ወይም ዝምድና› የሌላቸው፣ ለዚህ ቀርቶ ለቁጣ እንኳን የሚያበቃ ጥፋት በአጥፊው ላይ ያልፈጸሙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሕይወታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከማጣት አልታደጋቸውም፡፡
ምንም በማያውቁና በራሳቸው ዓላማ ምክንያት ተሰባስበው በሚገኙ ወገኖች ላይ የተኩስ እሩምታ እየከፈቱ ሕይወትን መቅጠፍ አሁን አሁን በዓለማችን እየተለመደ የመጣ ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኖርዌይ ሀገሪቱን ጸጥ ያሰኘ ግድያ በአንዲት ደሴት ተሰባስበው በነበሩ ተማሪዎች ላይ ተፈጽሞ ነበር፡፡ እምብዛም ይህን መሰል ወንጀል በማይሰማባት ቻይና እንኳን ሳይቀር በትምህርት ቤት ሕጻናት ላይ እሩምታ መክፈት እየተለመደ መምጣቱን የሚያሳዩ ድርጊቶች ብቅ እያሉ ነው፡፡ 

Thursday, December 27, 2012

‹ሁሉም ወደየበኣቱ ይመለስ›


click here for pdf
በአንድ ገዳም የነበሩ አበው አንድ ጉዳይ ይገጥማቸውና ከየበኣታቸው ወጥተው በገዳሙ ዐውደ ምሕረት ላይ ይከራከራሉ፡፡ ክርክሩ ወደ መጋጋል ይሄድና ኃይለ ቃል መውጣት ይጀምራል፡፡ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ አረጋውያን አባቶች ወጡና በየወገኑ የነበሩ ተከራካሪዎችን ሊያስማሟቸው ሞከሩ፡፡ ነገር ግን የሚያስማማ ሃሳብ ማምጣት አልቻሉም፡፡ በዚህ ጊዜ በገዳማውያኑ ዘንድ በብቃታቸው የሚታወቁ አንድ አባት ከበኣታቸው በር ላይ ቆሙና ‹በሉ ሁላችሁም ወደየበኣታችሁ ግቡ፤ ከዚያ በኋላ ለክርክራችሁ መፍትሔ ታገኛላችሁ› ሲሉ ተናገሩ፡፡
እርሳቸው እንዳሉትም ሁሉም ገዳማውያን ወደየበኣታቸው ገቡ፡፡ ወደ ዋሻው የሚገባም ገባ፤ ወደ መቅደስ የሚሄድም ሄደ፤ ወደ ምርፋቅ የሚሄድም ሄደ፤ ወደ ተግባር ቤት የሚሠማራም ተሠማራ፤ ወደ እርሻም የሚሄድ ሄደ፡፡ ያን ጊዜም ማዕበሉ ጸጥ አለ፡፡ ዐውደ ምሕረቱም ዐውደ ምሕረት ሆነ፡፡ ሁሉም ገዳማዊ ወደ በኣቱ ተመልሶ በረጋ ኅሊናና ነገሩን ማሰላሰል ጀመረ፡፡ አንዳንዱ በማያውቀው፣ አንዳንዱ በማያገባው፣ አንዳንዱ መልካም የሠራ መስሎት፣ አንዳንዱ ለሌላው ሰው ደጋፊ በመሆን፣ አንዳንዱ ያለ ችሎታው ነበር በነገሩ የገባው፡፡ 

Monday, December 24, 2012

አጣብቂኝ


በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት በየገዳማቱ ‹አጣብቂኝ› የሚባሉ ቦታዎች አሉ፡፡ በዚህ ትውፊት መሠረት ወደነዚህ አጣብቂኞች የሚገባ ሰው ከአጣብቂኙ መውጣት የሚችለው ‹ንጽሕና› ካለው ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ አጣብቂኙ ሰውዬውን ይዞ ያስቀረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያናችን ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ያለችበት ጊዜ ነው፡፡ በአንድ በኩል በውጭ ሀገር ከሚኖሩ አባቶች ጋር ያለው የዕርቀ ሰላም ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ? እንዴትስ እንደሚቀጥል? በውል አልታወቀም፡፡ ለዕርቁ  የተላኩት አባቶችም የዕርቁ ስብሰባ ከተከናወነ ከሳምንታት በኋላ እንኳን ወደ ሀገር ቤት አልመጡም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በዕርቁ ሂደትና በቀጣይ ተግባራት ላይ እንዲወያይ አላደረጉም፡፡ ከዚያ ይልቅ በአሜሪካ ያለውን አስተዳደራዊ ችግር በመፍታትና በሌሎች ግላዊ ነገሮች ላይ ተይዘው ከዚያው ከአሜሪካ ሳይወጡ በጥር ወር ይካሄዳል የሚባለው ቀጣዩ ስብሰባ እየደረሰ ነው፡፡

Wednesday, December 19, 2012

ከጣራ እስከ ጉዛራ

(የመጨረሻው ክፍል)
የኢፋግ የባርያ ንግድ ገበያ ዋርካ
‹ላላዋቂ ፎገራ ዱሩ ነው› ሲባል ሰምታችሁ ከሆነ አሁን ስላለሁበት ቦታ እየተነገራችሁ ነው ማለት ነው፡፡ ፎገራ በደቡብ ጎንደር፣ ዓባይን ከተሻገራችሁ በኋላ ጣናን ባሻገር እያየ የሚገኝ ሰፊ ሜዳ ነው፡፡ ለዚህ ነው ‹ላላዋቂ ፎገራ ዱሩ ነው› የሚባለው፡፡ ፎገራ አለቃ ገብረ ሐናን የመሰሉ ሊቃውንትን ያፈራ ታዋቂ ቦታ ነው፡፡ እዚህ ናበጋ ጊዮርጊስ ነው አለቃ ትውልዳቸውም፣ ዕረፍታቸውም፡፡
ፎገራ ውኃ ገብ ረግረግ መሬት በመሆኑ ከአፍ እስከ ገደፉ በሩዝ ምርት ተሸፍኗል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ‹ሕንድ በኢትዮጵያ› እያሉ ይጠሯታል ፎገራን፡፡ የፎገራ ገበሬ የነቃ የበቃ ገበሬ ነው፡፡ ፎገራ መንደር ውስጥ ስትገቡ የምታገኟቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች ገጠር መሆናችሁን ያስረሷችኋል፡፡ ንግግራቸው አማርኛ፣ አለባበሳቸው ወደ ኦሮምኛ ይጠጋል፣ ፎገራዎች፡፡ በመንደሩ ውስጥ ትግርኛ፣ አማርኛና ኦሮምኛ ተቀላቅሎ ሲነገር ትሰማላችሁ፡፡

Wednesday, December 12, 2012

ከጣራ እስከ ጉዛራ (ክፍል ሁለት)


 click here for pdf

ዋሻ ተክለ ሃይማኖት
ያለነው ደቡብ ጎንደር ጣራ ገዳም አካባቢ መሆኑን አስታውሰን እንጓዝ፡፡
ከዋሻ እንድያስ ወጣንና ወደ ግራ በኩል ታጥፈን መጓዝ ጀመርን፡፡ አሁንም እየተንደረደርን ነው ወደ ታች የምንወርደው፡፡ ግራና ቀኛችን በልምላሜ የታጠረ ነው፡፡ በአካባቢው ምንነቱን ለመለየት የሚያስቸግር በጎ መዓዛ ያውዳል፡፡ ወፎች ሲዘምሩ፣ ዛፎችም ሲያሸበሽቡ ለማየት የሚመኝ ሰው ካለ ወደ ዋሻ ተክለ ሃይማኖት መውረድ ነው፡፡ 

Saturday, December 8, 2012

ከጣራ እስከ ጉዛራ (ክፍል አንድ)እነሆ ከጎንደር ከተማ ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ተነሣን፡፡ የምናመራው በአዲሱ የጎንደር ባሕር ዳር መንገድ ወደ አዲስ ዘመን አቅጣጫ ነው፡፡ ይህ አዲሱ የአስፓልት መንገድ የገበሬዎችን እርሻና አስደናቂ የሆኑትን የሰሜንና ደቡብ ጎንደር ተራራማ ቦታዎች እያቋረጠ የሚጓዝ በመሆኑ ዓይናችሁን ከግራና ቀኝ የተፈጥሮ ትርዒት አትነቅሉም፡፡
በመንገድ ላይ በኩራት ከቆሙት ዐለቶች አንዱ
የሩቅ ምሥራቅ ምንጣፍ የመሰሉ እርሻዎች፣ እንደ ሞዴሊስት ወገባቸውን ይዘው የልብስ ትርዒት የሚያሳዩ የሚመስሉ ወጥ ድንጋዮች፣ በዛፎችና ቁጥቋጦዎች የተሞሉ ተራሮች በመንገዱ ግራና ቀኝ እየተሰናበቷችሁ ያልፋሉ፡፡ ሾፌራችን ሞላ ረጋ ብሎ ለጎብኝ በሚያመች መንገድ ይነዳል፡፡ የጎንደር ልደታው ሙሉቀን ደግሞ እያንዳንዷን መሬት ልቅም አድርጎ ያውቃታል፡፡
ምዕራፋችን የሆነው ሦስቱ ታላላቅ ገዳማት የሚገኙባት የጣራ ገዳም አካባቢ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ጣራ ገዳም፣ ዋሻ እንድርያስና ዋሻ ተክለ ሃይማት የተባሉ ገዳማት ይገኛሉ፡፡ የመጀመርያ ጉዟችን ወደ ዋሻ እንድርያስ ነው፡፡ 

Monday, December 3, 2012

ወርቅ እንዲህ ሲገዛባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ ወደ ጆሃንስበርግ በሚሄደው ኢትዮጵያ አየር መንገድ የደረሰብኝን መጉላላት ዘርዝሬ በዚህ ጦማር ላይ ጽፌ ነበር፡፡ ያንን ሳደርግ ዋናው ዓላማዬ የኢትዮጵያ አንዱ መለያ የሆነው አየር  መንገዳችን እንዲሻሻል በማሰብ ነው፡፡ ‹ጠላት ያማል ወዳጅ ይወቅሳል› እንዲሉ፡፡ ታላቁን መርከብ የአንዲት ብሎን መውለቅ ለአደጋ እንደሚ ዳርገው ሁሉ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ታላላቅ ተቋማትንም በየአካባቢው የሚፈጠሩ ትናንሽ የሚመስሉ ስሕተቶች ዋጋ ያስከፍሏቸዋል፡፡   
ዛሬ ከጆሃንስበርግ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ በደቡብ አፍሪካ የኢትጵያ አየር መንገድ የአካባቢ ሥራ አስኪያጅ በተፈጠረው ጉዳይ ላይ አነጋግረውን ነበር፡፡ ባለፈው ለተፈጠረው መጉላላት ይቅርታ ጠይቀው፣ በቀጣይ ተመሳሳይ ስሕተቶች እንዳይፈጠሩ አሠራራቸውን ማረማቸውን ገልጠውልናል፡፡ ያለፈውንምንም ለመካስ በቢዝነስ ክላስ ወደ አዲስ አበባ እንድንመለስ አድርገዋል፡፡
በመጀመርያ ቅሬታችንን በመስማታቸው፤ ቆይቶም ቢሆን ይቅርታ በመጠየቃቸውና ስሕተቱን ለማረም አሠራር መዘርጋታቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ ችግሮች መቼምና የትም ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ሁለት ነገሮችን ግን ይፈልጋሉ፡፤ አንድ ሲፈጠሩ በቅርብ ተገኝቶ ሳይብሱ የሚፈታ አመራርና፣ ችግሮቹ ዘላቂ ሆነው እንዳይቀጥሉ የሚያደርግ አሠራር ናቸው፡፡ ያኔ ያጣነው ይሄንን ነበር፡፡
ደንበኞች ቅሬታቸውን የሚሰማና የሚፈታ ካገኙ ከአየር መንገዱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይቀጥላሉ፡፡ ቅሬታቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ከተደረገ ግን በዚህ የውድድር ዘመን ፊታቸውን ወደ ሌሎች ያዞራሉ፡፡
በመሆኑም አየር መንገዳችን ቅሬታውን ተቀብሎ ለማረምና ይቅርታ ለመጠየቅ ያደረገው አሠራር አስደስቶኛል፡፡ ወርቅ እንዲህ ሲገዛ ያምርበታል፡፡ ነገም እንዲሁ እየተሰማማን እንደምንቀጥልም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጥበቡን በልቡናችሁ፣ መልካሙን መስተንግዶ በአውሮፕላናችን ላይ ያሳድርብን፡፡ አሜን፡፡
ከጆሃንስበርግ ወደ አዲስ አበባ በረራ ላይ

Thursday, November 29, 2012

ዶሮና የሁለት ልጆች ፈተና


ሁለት ተማሪዎች አንድ የቤት ሥራ ተሰጣቸው፡፡ የቤት ሥራው የተማሪዎችን ችሎታ ለመፈተን በከተማ ደረጃ የተዘጋጀ የዕውቀት መለኪያ ፈተና ነበር፡፡ ይህ ፈተና በሁለት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ አንደኛው ተማሪ አባቱ የናጠጡ ነጋዴ ሲሆኑ እናቱም አሜሪካ ተወልደው አድገው በአንድ የውጭ ድርጅት ለመሥራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው፡፡ እርሱም የሚማረው ‹‹አበባ የቀጠፈና አማርኛ የተናገረ ይቀጣል›› የሚል ማስታወቂያ በተለጠፈበት አንድ የግል ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሁለተኛው ተማሪ አባቱ የቀን ሥራ በመሥራት የሚተዳደሩ እናቱም ዶሮ የሚያረቡ ናቸው፡፡ ልጁም የሚማረው ከተቋቋመ ከሦስት ዓመቱ ጀምሮ መስኮቱ ተዘግቶ በማያውቅ አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡
የቤት ሥራው እንዲህ ይላል ‹‹ዶሮን በተመለከተ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናንተ ከምታውቁትና ከወላጆቻችሁ ጠይቃችሁ መልሱ›› 

Tuesday, November 27, 2012

ለቤተ መጻሕፍትዎ


የኢትዮጵያ ታሪክ
(፲፭፭፭፻፺፯–፲፮፻፳፭)
የዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል
ትርጉም፡- በዓለሙ ኃይሌ (2005ዓም)
ዋጋ፡- 45 ብር
ይህ የዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል ለብዙ ዘመናት በግእዝ ተጽፎ የኖረ ነው፡፡ በርግጥ የውጭ ሰዎች በተለይም አውሮፓውያን በየቋንቋቸው ሲተረጉሙት ኖረዋል፡፡ ‹በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት› ሆነና አማርኛ አንባቢዎች ግን አሁን ማግኘታቸው ነው፡፡ በዚህም አቶ ዓለሙ ኃይሌ ይመሰገናሉ፡፡ ከዚህ በፊት ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ተርጉመዋቸው በመሥሪያ ቤቱ በኩል የታተሙላቸው ሁለት ዜና መዋዕሎች አሏቸው፡፡ የዐፄ ሠርጸ ድንግል እና የዐፄ ገላውዴዎስ ዜና መዋዕሎች፡፡ በእነዚህ ቀደምት ሁለት መጽሐፎቻቸውም ሆኑ በሚገኙባቸው መድረኮች ሁሉ ስለ ግእዝ ሥነ ጽሑፍና ስለ ጥንታውያን ዕውቀቶች በተቆርቋሪነት መንፈስ ሲገልጡ ታገኟቸዋላችሁ፡፡ ይህ ቁጭታቸውም ሳይሆን አይቀርም ይህንን የሱስንዮስን ዜና መዋዕል ያስገኘው፡፡
የሱስንዮስ ዜና መዋዕል በዋናነት አራት ነገሮችን የያዘ ነው፡፡

Monday, November 26, 2012

ወርቅ የማይገዛው አገልግሎት

photo from (http://www.africaboundadventures.com)

እነሆ ሻንጣዬን እየገፋሁ ወደ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመጓዝ ላይ ነኝ፡፡ ለመንገደኛ መግቢያ ከተዘጋጁት በሮች ሁለቱ ብቻ ይሠሩ ስለነበር የገቢ መንገደኛው ሰልፍ አስፓልቱን አቋርጦ ወደ ሣሩ ደርሷል፡፡ ምስጋና በፍተሻው ላይ ለተሠማሩት ባለሞያዎች ይድረሳቸውና ጥንቃቄው እንደተጠበቀ ሆኖ እንግዶችን በፍጥነት ለማስተናገድ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር፡፡
ተፈተሽንና ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መስኮት ደረስን፡፡ ትኬታችንን አሳየንና ሻንጣዎቻችን አስረከብን፡፡ በመስኮቱ ጀርባ ለምታገለግለው የአየር መንገዱ ባለሞያ ወቅቱ የገና ጾም ወቅት ስለሆነ የጾም ምግብ ማስመዝገባችንን ገለጽንላት፡፡ እርሷም መልከት አለችና ‹‹ምንም ችግር የለውም›› አለችን፡፡ ‹‹የጾም ምግብ አለ ማለትሽ ነው›› ስንል የማረጋገጫ ጥያቄ አቀረብን፡፡ ‹‹ችግር የለውም አታስቡ›› አለችን ፈገግ ብላ፡፡
አንድ የስድስት ኪሎ ወዳጄ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያለን እንዲህ የሚል ግጥም አቅርቦ ነበር
አንድ ችግር አለ የችግር ካንሠር
‹ምንም ችግር የለም› የሚሉት ችግር
አንድ ሌላ ወዳጄም ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ‹ምንም ችግር የለም› በሚለውና ‹ችግር አለ› በሚለው መካከል ያለው ልዩነት የቃላት ብቻ ነው›› ብሎኝ ነበር፡፡ 

የሁለት ሐውልቶች ዕጣ 3

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ እንዲያስችል በሚዘረጋው የቀላል ባቡር መሥመር ዝርጋታ ምክንያት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት እንደሚነሳ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡ 

አቶ አበበ ምህረቱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮምኒኬሽን አገልግሎት ክፍል ኀላፊ የሐውልቱ መነሳት ያሰፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጹ “በቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ምክንያት መንገዱ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ጀምሮ ወደ አውቶቡስ ተራ የሚወስደው መንገድ አትክልት ተራ ድረስ ባቡሩ በዋሻ ውስጥ ነው የሚያልፈው፡፡ በተጨማሪም የባቡሩ መስመር ከምኒልክ አደባባይ ወደ ሽሮ ሜዳ ይዘረጋል፡፡ እንደሁም ከአውቶቡስ ተራ ወደ ቅድስት ልደታ ለማርያም የሚታጠፈው መስመር መነሻም ነው፡፡ 

ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ከማዘጋጃ ቤት አጥር ጀምሮ ወደ ትግበራ የተገባበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ሥራው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ሲደርስ ስዊድን አገር የሚገኘውና ከፍተኛ ልምድ ያለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ሥራውን በበላይነት የሚቆጣጠረው ሲሆን በሚያስመጣቸው ባለሙያዎች አማካይነት በክብርና በጥንቃቄ ሐውልቱን አንሰቶ የዋሻው ግንባታ እንደተጠናቀቀ አንዲትም ሣ/ሜትር ሳይዛነፍ እንደነበረ በቦታው ላይ በክብር እንዲያስቀምጥ ይደረጋል፡፡ ሐውልቱ የሀገር ቅርስና ሀብት ነው፤ ለዚህም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ይሰራል፡፡” ብለዋል፡፡

Saturday, November 24, 2012

የሁለቱ ሐውልቶች ዕጣ 2

click here for pdf 
ዛሬ ጠዋት በተሰጠ መግለጫ የዐፄ ምኒሊክ ሐውልት አሁን ባለበት እንደሚቀጥል፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ግን ተነሥቶ ከግንባታው በኋላ እንደሚመለስ ተነግሯል፡፡ ዘግይቶም ቢሆን መግለጫው መሰጠቱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ዝርዝር የሚፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡
  • የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ተነሥቶ የት ነው የሚቀመጠው?
  • ማን ነው የሚያነሣው?
  • የቅርስ ባለሞያዎች ተሳትፎ ምን ያህል ነው?
  • በቆይታው ጊዜ የሚደረግለት ጥንቃቄስ?
  • ሲመለስስ የት ነው የሚቆመው? አሁን ከሚሠራው የባቡር መሥመር ጋር ባለው ተዛምዶ የወደፊት አቋቋሙ ምን ይመስላል?
ለወደፊቱ እንደዚህ ዓይነት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አስቀድሞ ዝርዝርናሉ መረጃ መስጠት ሊለመድ ይገባል፡፡

Friday, November 23, 2012

የሁለት ሐውልቶች ዕጣclick here for pdf
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ የመነጋገርያ አጀንዳ የሆነ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ የአቡነ ጴጥሮስና የምኒሊክ ሐውልትና የባቡሩ መሥመር ያላቸው ዝምድና፡፡ ስለ ባቡር በመዝፈን ከመቶ ዓመት በላይ ያሳለፍን ሕዝቦች የከተማ ባቡር ማግኘታችንን በዕልልታ የምንቀበለው ነገር ነው፡፡ ዘግይተን ይሆናል እንጂ አልቸኮልንም፡፡ ሥራው በቁርጠኝነት መጀመሩና ከወሬ አልፎ ሲተገበር ማየታችንም እሰዬው የሚያሰኝ ሆኗል፡፡
ግን ደግሞ  ጥያቄ አለን፡፡

Thursday, November 22, 2012

ዝኆኑም ትንኙም

click here for pdf
አንበሳ በሚገዛው አንድ ጫካ ውስጥ አያሌ እንስሳት ይኖሩ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንበሳ ለአንድ የሥራ ጉዳይ ወደ ሌላ ሀገር ለመሄድ ተነሣ፡፡ የእርሱ መሄድ በእንስሳቱ ዘንድ በተሰማ ጊዜ የጫካውን ሕልውና በተመለከተ ጥያቄ ተነሣ፡፡ ጦሩን ማን ይመራል? ገንዘብ ማን ይይዛል? ምግብ ማን ያከፋፍላል? መልእክት ማን ይቀበላል? ዳኝነት ማን ይሰጣል? ሠራተኛ ማን ያሠማራል? ሹመት ማን ይሰጣል? እያሉ እንስሳቱ መጠያየቅ ጀመሩ፡፡ በዚያ ጊዜ አንበሳ ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ይዞት ስለነበር አሁን እርሱ ሲሄድ ነገር ዓለሙ ሁሉ ሊዛባ ደረሰ፡፡
አንበሳ ችግሩን ቢረዳውም ነገር ግን ለአንዱ እንስሳ ብቻ ሥልጣኑን ሰጥቶ መሄዱ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ በታች እኩል ሆነው የኖሩትን ታማኞቹን ማባላት መስሎ ታየው፡፡ ስለዚህም ‹ሥልጣን በተርታ ሥጋ በገበታ› ብሎ ሥልጣኑን ቆራርሶ ለሁሉም በየዐቅማቸው ለማካፈል ወሰነ፡፡ በዚህም መሠረት ነበርን የጦር ሚኒስትር፣ ዝንጀሮን ዋና ዳኛ፣ ጦጣን የገንዘብ ተቆጣጣሪ፣ ቀበሮን የሥጋ ኃላፊ፣ ዝሆንን ምግብ አከፋፋይ፣ አጋዘንን የሠራተኞች ተቆጣጣሪ፣ ተኩላን ፖሊስ አድርጎ ሰየማቸው፡፡ 

Tuesday, November 13, 2012

እኛ፣ የመጨረሻዎቹበፌስ ቡክ የተለቀቀ አንድ ጽሑፍ በምዕራቡ ዓለም የ1950ዎቹን፣60ዎቹን፣ 70ዎቹንና 80ዎቹን ትውልዶች በተመለከተ ‹‹እኛኮ በቶምና ጄሪ ፊልም ያደግን፣ በመንገድ ላይ የተጫወትን፣ በሬድዮ ካሴት ሙዚቃ ያዳመጥን የመጨረሻዎቹ ትውልዶች ነን፡፡›› ይላል፡፡
እኔም ይህንን ሳይ የራሴ ትውልድ ትዝ አለኝ፡፡
እውነትም እኮ እኛ የ1940ዎቹ፣ 50ዎቹና 60 ዎቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች ጠቅላይ ግዛት የሚባል አከላለል ክፍለ ሀገርም የሚባል አካባቢ፣ አውራጃ የሚባል ቦታ፣ ምክትል ወረዳ የምትባል ጎጥ ያየን፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ በምድር ላይ ሲጓዝ የተመለከትን፣ የንጉሥ ግብር የበላን ወይም ሲበሉ ያየን፣ ንጉሥ ሲወርድ፣ መሪም ሲኮበልል ለመታዘብ የቻልን፣ ደጃዝማችነት፣ ቀኝ አዝማችነት፣ ራስነት፣ ባላምባራስነት፣ ፊታውራሪነት፣ ነጋድራስነት፣ ጸሐፌ ትእዛዝነት፣ አጋፋሪነት፣ እልፍኝ አስከልካይነት ዓይናችን እያየ ታሪክ ብቻ ሆነው ሲቀሩ ምስክር የሆንን የመጨረሻዎቹ ትውልዶች ነን እኛ፡፡ 

Thursday, November 8, 2012

ከተራራው ጀርባ ያለው ሰው

እስኪ ታላቅ ነው በምንለው ቦታ ደርሰናል ብለን የምናስብ ሰዎች ለአፍታ ዘወር ብለን ተንጠላጥለንባቸው የተሻገርንባቸውን አያሌ ሰዎች ለማስታወስ እንሞክር፡፡ እዚህ ለመድረሳችን የምናውቀውንም የማናውቀውንም ድርሻ የተወጡ፣ እነርሱነታቸው እኛነታችን ውስጥ ያለ፡፡ አሁን የተቀመጥንበት ወንበር፣ የምንተኛበትም አልጋ፣ የምንኖርበትም ቤት፣ የምንቆጥረውም ብር፣ የወጣንበትም ከፍታ የእነርሱ ጭምር የሆነ፡፡ እነርሱ ባይኖሩ ኖሮ እዚህ ቦታ ለመድረስ ቀርቶ ወደዚህ አቅጣጫ እንኳን ለማየት የማይቻለን፡፡ እስኪ የሚቀጥለውን ታሪክ እየተከታተላችሁ እነዚህን አስቧቸው፡፡
መምህራን፣ የቤት ሠራተኞች፣ ሞግዚቶች፣ የሠፈር ሽማግሌዎች፣ አያት፣ አጎት፣ አክስት፣ የጥበቃ ሠራተኞች፣ ሾፌሮች፣ ጓደኞች፣ ሐኪሞች፣ ፖሊሶች፣ አንድ መሥሪያ ቤት ሄደን በጎ ያደረጉልን ሰዎች፣ ሳያስቡትም ሳናስበውም ዕድል የከፈቱልን ሰዎች፣ ሕይወታችንን የቀየረችውን አንዷን ብር የሰጡን ሰዎች፣ ከሞት ያተረፉን፣ ከመከራ የታደጉን ሰዎች፤ ያበረታቱን፣ ያጨበጨቡልን፣ የመረቁን፣ መንገድ ያሳዩን፣ በልብሳቸው አጊጠን፣ በምግባቸው ጠግበን እንድንጓዝ የረዱን፤ ከኛ በፊት ሕይወታቸውን ሰጥተው፣ ለኛ ሲሉ ተሠውተው ያለፉልን ጀግኖች፤ እነማን ነበሩ? እስኪ ይህንን ታሪክ እያነበባችሁ አስቧቸው፡፡

Tuesday, November 6, 2012

ሞያ ከጎረቤት


ባለፈው እሑድ ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓም አዋሳ ላይ ሆኜ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን 118ኛ ፓትርያርኳን ስትመርጥ እያየሁ ነበር፡፡ እጅግ ደስ የሚለው ሥነ ሥርዓቱን ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሽፋን ሰጥተውት ነበር፡፡ በረከታቸው ይደርብንና ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ በዘመናቸው ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከሠሯቸው ሥራዎች አንዱ ዘመናዊ የሆነ የኦዲዮ ቪዡዋል ማዕከል ባለቤት ማድረጋቸው ነው፡፡ በእርሳቸው ዘመን ታላቅ የሆነ የቴሌቭዥን ስቱዲዮ ተገንብቷል፡፡ ኮፕቲክ ቴሌቭዥን፣ አጋፒያና ክርስቲያን ቲቪ የተሰኙ የቤተ ክርስቲያኒቱን የዕለት ተዕለት ጉዳዮች የሚዘግቡ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተቋቁመዋል፡፡
በዕለቱ የነበረውን ዝግጅት ከዋዜማው ጀምሮ ታላላቅ ባለ ክሬን ካሜራዎችን በመትከልና የትኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መቀረጽ እንዳለበት በመለየት የኮፕቲክ ቴሌቭዥን ጣቢያ ከኮፕቲክ የኦዲዮቪዡዋል ማዕከል ጋር በመሆን ተዘጋጁ፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥና ውጭ ከ16 በላይ ባለ ክሬን ካሜራዎች ተተክለው ነበር፡፡
ከመላው ዓለም የተገኙ ከ230 በላይ ጋዜጠኞች በተዘጋጀላቸው ልዩ ቦታ ላይ ሆነው ከጠዋቱ ጸሎት አንሥቶ እስከ ምርጫው ፍጻሜ የነበረውን ሥነ ሥርዓት ለመላው ዓለም በቴሌ ቭዥን፣ በሬዲዮ፣ በዌብ ሳይትና በብሎግ ያስተላልፉ ነበር፡፡ ከአሥር ሺ ሕዝብ በላይ የሚይዘው የአባስያ የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በተመረጡ ገዳማውያን፣ ካህናት፣ ምእመናን እና ተጋባዥ እንግዶች መሞላት የጀመረው ገና ከጠዋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነበር፡፡ 

Friday, November 2, 2012

ፓርኪንግ


አሜሪካን ሀገር ወደሚኖሩ ወዳጆቼ ቤት ሄጄ ነበር፡፡ ከተጋቡ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ቤታቸው ስገባ የቤቱም ዕቃ የቤቱም ሰዎች ዝምታ ውጧቸዋል፡፡ አባ አጋቶን ቤት የገባሁ ነው የመሰለኝ፡፡ እርሱ ክፉ ላለመናገር ሰባት ዓመት ድንጋይ በአፉ ጎርሶ በአርምሞ ተቀምጧል፡፡ ነገር ዓለሙ አላምር ሲለኝ ‹ምነው ያለ ወትሯችሁ ዝምታ ዋጣችሁ› ብዬ ተነፈስኩ፡፡ እዚህ ቤት የነበረውን ሳቅና ጨዋታ ስለማውቀው፡፡ ‹ሳቅና ጨዋታ ዝና ካማራችሁ› ሲባል አልሰማችሁም፡፡
የመለሰልኝም የለ፡፡
በኋላ ነገሩን ሳጠናው ሁለቱም ተኳርፈዋል ለካ፡፡ ‹‹ለመሆኑ እንዲህ ሳትነጋገሩ ስንት ጊዜ ተቀመጣችሁ› ብዬ ስጠይቅ ስድስት ወር ሆኗቸዋል፡፡ ሁሉም በየሥራው ይውላል፤ ማታ ይመጣል፤ ኪችን ገብቶ ያበስላል፤ በልቶ ቴሌ ቭዥን ያያል፤ ከዚያም ይተኛል፡፡ ቢል ሲመጣ ይህንን እኔ ከፍያለሁ ብሎ አንዱ ወረቀት ጽፎ ይሄዳል፤ ሌላው በተራው ይከፍላል፡፡ ይቺ ናት ትዳር፡፡
ድሮ የሰማሁትን ቀልድ ነበር ትዝ ያሰኙኝ፤ ባልና ሚስቱ ተኳርፋው አይነጋገሩም አሉ፡፡ ቤቱ እንደ መቃብር በጸጥታ ተውጦ ከርሟል፡፡ አንድ ቀን ባል ሌሊት አሥር ሰዓት የሚነሣበት ጉዳይ ገጠመው፡፡ ከተኛ መነሣት የሚከብደው ቢጤ ነበርና የመቀስቀሻውን ሰዓት ሊሞላ ሲስበው ተበላሽቷል፡፡ አዘነም፤ ተናደደም፡፡ ምን ያድርግ፡፡ ባለቤቱ ገና ከሥራ አልገባችም፡፡ ‹የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይመርጡ› ነውና፡፡ በቁራጭ ወረቀት ላይ ‹አሥር ሰዓት ላይ ቀስቅሽኝ› ብሎ ጽፎ በራስጌው ባለው ኮመዲኖ ላይ አስቀመጠና ተኛ፡፡
ሚስቱ ስትመጣ አየችውና ስቃ ተኛች፡፡ ልክ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ነቃችና በዚያው በቁራጭ ወረቀት ላይ ‹አሥር ሰዓት ሆኗልና ተነሣ› ብላ ጽፋለት ተኛች፡፡ እርሱ ዕንቅልፉን ለጥጦ ለጥጦ ሲነሣ ነግቷል፡፡ ተናደደ፤ ግን እንዳይናገራት ለካስ ተኳርፈዋል፡፡ እዚያው ወረቀት ላይ ‹በጣም ታሳዥኛለሽ› ብሎ ጻፈላት፡፡
እነዚህ ወዳጆቼ ይህን ነበር ያስታወሱኝ፡፡ አሁን እንዲህ ያለው ኑሮ ምን ዓይነት ኑሮ ይባላል? ብዬ ስም ፍለጋ ብዙ ጊዜ አሰብኩ፡፡ 

Tuesday, October 30, 2012

118ኛው ፓትርያርክ መንገድ ላይ ናቸው

ዐቃቤ መንበር አቡነ ጳኩሚስ ድምጽ ሲሰጡ
የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 118ኛውን ፓትርያርክ የመምረጡ ሂደት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሻግሯል፡፡  በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ አራት ሂደቶችን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ የጥቆማና ማጣራት፣ የመጨረሻዎቹን አምስት ዕጩዎች የመወሰን፣ ለዕጣ የሚቀርቡትን ሦስት አባቶችን መምረጥና የመጨረሻውን አባት በዕጣ መምረጥ ናቸው፡፡
በዚሁ መሠረት ከተጠቆሙት ወደ አሥራ ሰባት አባቶች መካከል የማጣራቱና አምስቱን የመወሰኑ ሂደት እጅግ ረዥም ጊዜ የወሰደ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ ሂደት ሁለት ከባባድ ችግሮች ተጋርጠውበት ነበር፡፡ የመጀመርያው ፈተና በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ከተጻፈውና የግብጽ ቤተ ክርስቲያንም ሕግ ከሚደነግገው ውጭ ሀገረ ስብከት ያላቸው አባቶች ራሳቸውን ሳይቀር ለዕጩነት መምረጣቸው፣ ከዚህ በፊት አንዳንድ ችግሮች ተከስተውባቸው የነበሩ አባቶችም በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ መግባታቸው ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ሕግ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ራሳቸውን ከዕጩነት እንዲያገልሉ በአስመራጭ ኮሚቴውና በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ አባቶችና ሽማግሌዎች የማግባባትና የማረም ሥራ ሲሠራ ነበር፡፡ ለሁለት ጊዜ ያህል ሱባኤ ታውጆ፣ ጳጳሳቱም ሁሉ ወደ አባ ብሶይ ገዳም ገብተው በጸሎትና በውይይት ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የተወሰኑት አባቶች ‹እኔ በሺኖዳ መንበር መቀመጥ የለብኝም› እያሉ ራሳቸውን ከዕጩነት አግልለዋል፡፡ 

Thursday, October 25, 2012

በታሪክ መርካት

click here for pdf
(ፎቶ -በአሜሪካ የኢትዮጵያ  ኢምባሲ ድረ ገጽ)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመመለሱ ፌሽታ ሕዝቡን አልለቀቀውም፡፡ ተጨዋቾቹና ፌዴሬሽኑም በዚሁ ደስታ ውስጥ ናቸው፡፡ ስለ እሑዱ ድል እንጂ ስለ ቀጣዩ ውድድር የሚያስብ ግን ያለ አይመስልም፡፡ ሌሎቹ ቡድኖች እስከ ጥር ወር ድረስ ምን እንደሚሠሩ በሚናገሩበት ጊዜ እንኳን የኛው ቡድን እስከ ጥር ወር ድረስ ምን እየሠራ እንደሚቆይ አይታወቅም፡፡
እንዴውም እንደምንሰማው ከሆነ አንዳንድ ተጫዋቾቻችን በየመጠጥ ቤቱ እየተጋበዙ በሸክም ሆኗል አሉ የሚወጡት፡፡ ምነው ሲባሉ ‹ድል አድርገናልኮ› ነው መልሱ፡፡
ይኼ በትናንት ድል እየረኩ ነገን የመርሳት አባዜ የቆየ በሽታችን ነው፡፡ በአድዋ ጦርነት ጣልያንን ወኔያችንን ተጠቅመን፣ ጀግንነታችንን ተኩሰን ፈጣሪም ረድቶን ድል አደረግናት፡፡ በጥቁር አፍሪካ ምድር ቅኝ ገዥዎችን ድል ያደረገ ጥቁር ሕዝብ መሆናችንን አስመሰከርን፡፡ ታሪክ ሠርተን ታሪክ አየን፡፡

Tuesday, October 23, 2012

‹ሲኖዶስ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም›

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣይ ዘመናት የሚመራውን አባት የመምረጡ ታላቅ ሥራ ቅዱስ ሲኖዶሱን ከገጠሙት የዘመናችን ተግዳሮቶች ዋናው ነው፡፡ ይህንን ተልዕኮ ከተግዳሮቶቹ ሁሉ ዋናው የሚያደርጉት አራት ምክንያቶች ናቸው፡፡
የመጀመርያው በአራተኛውና በአምስተኛው ፓትርያርኮች መካከል በተደረገው ሽግግር በተፈጠሩ ወቅታዊና ቀኖናዊ ጉዳዮች ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት ‹ሲኖዶሶችን› ያስተናገደችበት ዘመን ላይ የሚደረግ ምርጫ መሆኑ ነው፡፡ በሀገር ቤትና በውጭ ባሉት አባቶች መካከል እየተከናወነ ባለው የዕርቀ ሰላም ሂደት ውስጥ ዛሬም በሕይወት ያሉት የአራተኛው ፓትርያርክ ዕጣ ፈንታ ቀጣዩን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰላማዊና መንፈሳዊ ብሎም ቀኖናዊ ጉዞ የሚወስነው ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድም አራተኛውን ፓትርያርክ ወደ መንበር ትመልሳለች፣ ያለበለዚያም አራተኛውን በጸሎት ወስና በእንደራሴ ትቀጥላለች፣ ያለበለዚያም ስድስተኛውን ትመርጣለች፡፡ 

Wednesday, October 17, 2012

እስከ መቼ ?


ይህንን ስጽፍላችሁ እጅግ አዝኜ፣ እጅግም ተናድጃለሁ፤ ወንድ መሆኔን ከጠላሁባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች አንዱ  የዛሬው ገጠመኝ ነው፡፡
ቢሮዬ ውስጥ ቁጭ ብዬ እየሠራሁ እያለ ድንገት የጫጫታ ድምጽ ከውጭ ሰማሁ፤ መጀመርያ የሰዎች የጨዋታ ድምፅ መስሎኝ ዝም አልኩ፡፡ እየቆየ ግን ‹ጩኸት በረከተ› እኔም ነገሩ ግራ ገብቶኝ ወጣሁ፡፡ ይህ አካባቢ የወፍ ድምጽ እንኳን የማይሰማበት ጸጥታ የሞላው አካባቢ ነበርና ነገሩ እንግዳ ነው የሆነብኝ፡፡
ከወጣሁ በኋላ ያየሁትንና የሰማሁትን ግን ለማመን አልቻልኩም፡፡
እኅትና ወንድም በአንድ ድርጅት ውስጥ ይሠራሉ፤ ብዙ ጊዜ በመግባባት መንፈስ መሥራታቸው ይደንቀኝ ነበር፡፡ ሲሳሳቁና ሲጫወቱ እንጂ ሲከራከሩ እንኳን ሰምቼ አላውቅም፡፡ አሁን ያየሁት ግን በእውኔ ነው፣ በሕልሜ፣ ወይስ በፊልም የሚያሰኝ ነው፡፡

Tuesday, October 16, 2012

ገናዧ


ከላስ ቬጋስ ወደ ፊኒክስ አሪዞና በዩ. ኤስ. አየር መንገድ በመጓዝ ላይ ነበርኩ፡፡ የተቀመጥኩት በአውሮፕላኑ ወገብ ላይ ነው፡፡ ከእኔ ቀጥሎ አንዲት ወጣት ሴት፣ ከእርሷም ቀጥሎ አንድ ሽማግሌ በመስኮቱ በኩል ተቀምጧል፡፡ አውሮፕላኑ ተነሥቶ ጥቂት እንደተጓዘ የበረራ አስተናጋጇ ‹አሁን የኤሌክትሮኒክስ መሣርያዎቻችሁን መጠቀም ትችላላችሁ፣ ከስልክ በቀር› ስትል ሁሉም ኮምፒውተሩንና አይ ፓዱን መመዥለጥ ጀመረ፡፡
‹እኔስ የአበሻው ልጅ እንደ አባቶቼ ጎራዴ መመዥለጥ ቢያቅተኝ እንዴት አንድ አሮጌ ላፕ ቶፕ መመዥለጥ ያቅተኛል› ብዬ መዠለጥኩ፡፡ አንድ የማርመው ጽሑፍ ነበርና ያንን ከፍቼ ስሠራ ድንገት ከቀኝ ጎኔ ‹‹ይቅርታ›› የሚል ድምፅ ሰማሁና ዞር አልኩ፡፡ ልጅቱ ናት፡፡ ‹‹የምታነብበት ቋንቋ ምንድን ነው?›› ብላ ጠየቀችኝ፡፡ አማርኛ መሆኑንና የኢትዮጵያ ቋንቋ መሆኑን ነገርኳት፡ ያው እነርሱ ማድነቅ ልማዳቸው ነው ‹‹ዋ......ው›› ብላ አደነቀች፡፡ ከዚያ ደግሞ ስለምጽፈው ነገር ጠየቀችኝ፡፡ እርሱንም ነገርኳት፡፡ 

Thursday, October 11, 2012

አንድ ገመድ አለኝ

ሁለት ወንድማማቾች እናታቸው ስታርፍ በቤት ውስጥ ያገኙት አንድ ትልቅ ገመድ ብቻ ነበር፡፡ ታላቁ ልጅ እጅግ በመበሳጨቱ ገመዱን ጠቅልሎ ጣራ ላይ ወረወረውና ከቤት ወጥቶ ሄደ፡፡ ታናሹ ግን ምንም ቢሆን ገመዱ የእናቱ ቅርስ ነውና እንደምንም ብሎ ጣራ ላይ ወጥቶ አወረደው፡፡
ከባዱ ጥያቄ ግን ከዚህ በኋላ ያለውን ኑሮ እንዴት መግፋት ይችላል? የሚለው ነበር፡፡ ለብዙ ሰዓታት ተቀምጦ አሰበበት፡፡ ምንም ነገር ሊታየው ግን አልቻለም፡፡ መንገዱ ሁሉ በግንብ የታጠረ ነው፡፡ አስቦ አስቦ ወደ አንድ ጠቢብ ዘንድ ሄደ፡፡
ጠቢቡ ሰው እንዳገኘው የጠየቀው ጥያቄ ‹‹ምን አለህ›› የሚል ነበር፡፡
 መልሱም ቀላል ሆነ ‹‹ ምንም››
ጠቢቡ ሰውም ‹‹በዓለም ላይ ምንም የሌለው ሰው የለም፡፡ ምናልባት ግን ጥቂት ብቻ ያለው ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ከለምሳሌ አንተ ከወንድምህ በተለየ ጥበብ አለህ፤ ይህ ጥበብህም ነው ወደ ጠቢብ ያመጣህ›› አለው፡፡ ልጁ ግን በርግጠኛነት እየማለ ምንም እንደሌለው ተናገረ፡፡ 

Tuesday, October 9, 2012

የአሸዋና የድንጋይ ጽሑፍ


አንድ ወዳጄ ከላከልኝ መጽሐፍ ላይ ይህንን አነበብኩ፡፡
ሁለት እጅግ የሚዋደዱ ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ የትም ቦታ ሲሄዱ አይለያዩም ነበር፡፡ እንደለመዱትም አብረው ወደ አንድ ሀገር በእግራቸው ይጓዙ ነበር፡፡ መንገድ በዝምታ ይረዝማልና እየተጨዋወቱ ነበር የሚጓዙት፡፡ አንዳንድ ጨዋታ በድካም መንፈስ ከተጫወቱት ለጠብ ይዳርጋል፡፡ ድካም የትዕግሥትን ዐቅም ይፈታተናልና፡፡ ለዚህ ነው የሀገሬ ሰው የድካም ና የዕረፍት ጨዋታ ለየቅል ነው የሚለው፡፡
እነዚህም ወዳጆች የዕረፍቱን ጨዋታ ለድካም አምጥተውት ኖሮ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ አንደኛው ታድያ ብልጭ ሲልበት በቦክስ ድንፉጭ የማድረግ ልማድ ነበረበትና በጓደኛው ላይ ታይሰን የማይችለው ቡጢ ሠነዘረበት፡፡ ቡጢውን የቀመሰው ጓደኛም የፊቱን ደም ጠርጎ፣ እያበጠ የሄደውን ግንባሩን ዳሰሰው፡፡ እጅግም አዘነና መንገዱን አቋርጦ በበረሃው አሸዋ ላይ ተቀመጠ፡፡ አንገቱን ግራና ቀኝ እያወዛወዘ ኀዘኑን ገለጠ፡፡ ንዴቱ ከውስጥ እንደ ልቅሶ ቤት ሽሮ ቡልቅ ቡልቅ ይልበት ጀመር፡፡ መልሰህ ‹በለው፣ በለው› እያለ ወንድነቱ ያስቸግረው ነበር፡፡

Tuesday, October 2, 2012

የተሰደዱ ስድቦች

በአንድ ወቅት ነፍሷን ይማረውና ፊርማዬ ዓለሙ አንድ ገጠመኟን በኢትዮጵያ ሬዲዮ አስደምጣን ነበር፡፡ ፊርማዬ በመንገድ ላይ ስትጓዝ ከአንድ ጎረምሳ ጋር ትጋጫለች፡፡ ጎረምሳውም በለመደ አፉ በእናቷ ይሰድባታል፡፡ ፊርማዬ ነገሩን በስድብ ብቻ አላየችውም ነበርና ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ትወስደዋለች፡፡ ፖሊስም ልጁን ሕግ ፊት አቅርቦ ያስቀጣዋል፡፡ ይህንን ነበር ፊርማዬ የነገረችን ‹ስድብን ዝም አትበሉ› ብላ፡፡
ይህንን ፊርማዬን እስከ ክስ የወሰዳትን ስድብ ዛሬ ዛሬ በአዲስ አበባ መንገዶች አልሰማውም፡፡ እኔ ስድብ የመስማት ችሎታ ቀንሷል ወይስ ስድቡ ራሱ ሰው ዘንድ የመድረስ ዐቅሙ ተዳክሟል? አንዳንድ ጊዜም ‹ስድቦቻችን የት ሄዱ?› እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ መቼም ነገሮች ከዘመኑና ከቴክኖሎጂው ጋር ይቀየራሉና ስድቦችም መልካቸውን ቀይረው ሊሆን ይችላል፤ አለያም ደግሞ የመሳደብ ፋሽኑ አልፎበት ይሆናል እያልኩ ነበር የማስበው፡፡

Friday, September 28, 2012

አንድ ምሁር በገበሬው ፊትአንድ በእርሻ ላይ የሚሠራ ዪኒቨርሲቲ መምህር በገበሬው ዙርያ ጥናት ለመሥራት ወደ ገጠር ወጡ፡፡ የአካባቢው የገበሬዎች ማኅበርም በአካባቢው የሚኖሩትን ገበሬዎች ለጥናቱ እንዲተባበሩ ለማድረግ ስብሰባ ጠራ፡፡ ምሁሩም ከገበሬዎቹ ፊት ለፊት ተቀመጡና ስለመጡበት ሥራና ከገበሬዎቹ ስለሚጠበቁ ነገሮችም ማብራራት ጀመሩ፡፡
‹‹ጉድ አፍተርኑን፤ እዚህ የመጣነው ፍሮም ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ከእናንተ ጋር ሚት ማድረጋችን ጉድ ኦፖርቹኒቲ ነው፡፡ ኦፍ ኮርስ እዚህ ለመምጣት ያሰብነው ቢፎር ኤ ይር ነበር፡፡ በት አንዳንድ ፕሮሲጀሮችን ለማሟላት ሃርድ ስለሆነብን ትንሽ ሌት ሆነናል፡፡ ሶሪ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሜይን ኢንካሟ አግሪካልቸር መሆኑን አንደርስታንድ ታደርጋላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ አግሪካልቸር ዋን ኦፍ ዘ ሜይን የሰው ልጆች አንሸንት አክቲቪቲዎች ነው፡፡ ኢን ኢትዮጵያ ደግሞ ሎንግ ሂስትሪ አለው፡፡ በት አግሪካልቸራችን አንደር ደቨሎፕ ሆኗል፡፡ ፋርሚንጋችን ፑር ነው፡፡ አክቲቪቴያችን ሌበረስ ነው፡፡ ገበሬው ሳይንቲፊክ ዌይ አይጠቀምም፡፡ ፋርሚንጋችን ሜካናይዝድ አይደለም፡፡ ገበሬው ኢንፎርሜሽን እንደልቡ አያገኝም፡፡ 

Thursday, September 27, 2012

የምታይበት መንገድ

click here for pdf
አንድን የናጠጠ ሀብታም ቤተሰብ የሚያስተዳድር አባት ልጁ ስለ ድኽነት እንዲያውቅ ስለፈለገ በከተማው ጥግ ወዳለው የድኾች መንደር ልጁን ይዞት ይሄዳል፡፡ እዚያም ወደ አንድ ድኻ ቤት ይገባና ለልጁ ሁሉንም ነገር ያሳየዋል፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባትና ልጅ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ቤታቸው በመኪናቸው ይመለሳሉ፡፡ አባትም ልጁን ‹‹ጉዞው እንዴት ነበር?›› ይለዋል፡፡
ልጁም ‹በጣም ጥሩ ነበር›› ብሎ ይመልስለታል
አባትዬውም ‹‹ድኾች ምን ዓይነት እንደሆኑ አየህን?›› ይለዋል፡፡
ልጁም ‹‹በርግጠኛነት አይቻለሁ›› ሲል መለሰለት፡፡
‹‹ታድያ ምን ተማርክ?›› አለው አባት፡፡

Tuesday, September 25, 2012

በመጥፋት ላይ ያለው ዝርያ


አደንን በመሰሉ ሰው ሠራሽ ችግሮችና በተፈጥሮ ላይ በሚደርሱ አደጋዎች የተነሣ በዓለማችን ላይ የነበሩ አያሌ እንስሳትና ዕጽዋት ጠፍተዋል፡፡
ለእነዚህ ዝርያዎች መጥፋት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው የሚባሉት አራት ናቸው፡፡ የመጀመርያው የሚኖሩበት የአየር ንብረት መለወጥ ነው፡፡ ለኑሯቸው ተስማሚ የሆነውና የሚያስፈልጋቸው የአየር ንብረት መለወጥ ሲጀምር እነርሱም ቀስ በቀስ ቁጥራቸው እየቀነሰ መጥፋት ይጀምራሉ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ልቅ የሆነ አጠቃቀም ነው፡፡ የእነርሱን መብት ሊያስከብር፣ ዝርያቸውንም ከመጥፋት ሊያስጠብቅ የሚችል ኃላፊነት የተሞላው አጠቃቀም ከሌለ እነዚህን ዝርያዎች ማንም እንደፈለገ በማድረግ እስከመጥፋት ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡ 

Tuesday, September 18, 2012

የደብረ ምጥማቅ መግባቢያ


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆነች ትልቋ ተቋም ናት፡፡ በሕዝቡ ሃይማታኖዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ የማይተካና ወሳኝ የሆነ ሚናም አላት፡፡ ዕድገቷ ለሀገሪቱ ዕድገት፣ ሥልጣኔዋ ለሀገሪቱ ሥልጣኔ፣ አሠራርዋ ለሀገሪቱ አሠራር፣ የችግር አፈታቷም ለሀገሪቱ የችግር አፈታት ወሳኝ ነው፡፡
በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ለመፍታትና አንዲት፣ ጠንካራ፣ በአሠራርዋ ዘመናዊ፣ በእምነቷ ጥንታዊ፣ በሀገሪቱ ጉዞ ውስጥ ተደማጭና ወሳኝ የሆነ ሚና ያላት፣ ሌሎች ችግሮቻችንን በመፍታት ረገድ ሀገራዊ መንፈሳዊና ተልእኮዋን የምትወጣ ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን በማድረጉ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ይመለከተናል፡፡
በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከገጠሟት ፈተናዎች አንዱ የመለያየት ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ይህ ዕጣ በተለይም በሀገር ቤትና በውጭ በሚባል ሲኖዶስ፣ በማይግባቡና በማይቀራረቡ አባቶች እነርሱም በተከተሉት ሁለት ዓይነት የችግር አፈታት ምክንያት የተከሰተ ነው፡፡ 

Saturday, September 15, 2012

ገለልተኞች ሆይ የት ናችሁ?


click here for pdf
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቅርብ ዘመን ታሪክ ከተፈጠሩት ገጽታዎች አንዱ ‹‹የገለልተኛነት›› አቅጣጫ ነው፡፡ ገለልተኛነት በተግባር የታየው በ1970ዎቹ አጋማሽ በአሜሪካን ሀገር ከቅዱስ ሲኖዶስ ተለይተው የቀሩትን ሁለት ጳጳሳት ተከትሎ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጳጳሳት በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ራሳቸውን በማግለል በቅዱስ ሲኖዶስ የማይመሩ አብያተ ክርስቲያናትን መመሥረት ጀመሩ፡፡
በወቅቱ ይህንን ተግባር የተቃወሙት በምዕራብ ንፍቀ ክበብ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ይስሐቅ ነበሩ፡፡ አቡነ ይስሐቅ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አድርሰው እስከ ማስወሰን በመድረሳቸው ሁለቱ ጳጳሳት ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን›› የሚለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም በመተው ‹‹የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን›› በማለት እስከ ማቋቋም ተደርሶ ነበር፡፡ በርግጥ ታሪክ ራሱን ስለ ሚደግም አቡነ ይስሐቅም በተራቸው ሌሎችን ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት አቋቁመው ነበር፡፡

Thursday, September 13, 2012

4 ሚሊዮን


የጡመራችን ተከታታይ 4 ሚሊዮን መድረሱን መረጃችን ገልጦልናል፡፡ ይህ በሁለት ዓመት ከአምስት ወር የተገኘ ስኬት በብዙዎች ጸሎት፣ እገዛና አስተያየት የተገኘ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ በጽሑፎቹ ሃሳቦች ተስማምተው የሚያነቡም ሆኑ ተቃውመው የሚያነቡ፤ የሚያመሰግኑም ሆኑ የሚሳደቡ፣ ለራሳቸው የሚያስቀሩም ሆኑ ለሌሎች የሚያዳርሱ ሁሉ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡
ለጽሑፍ መነሻ የሚሆኑ ነገሮች የሚልኩ፣ ጊዜ ወስደው ከሀገርም ሆነ ከውጭ ደውለውና ጽፈው ሃሳብ የሚሰጡ፤ ያልጣማቸውን ነገር የሚተቹ፤ ለቀጣይ ሥራ ብርታት የሚሆን ድጋፍ የሚሠጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚህ የጡመራ መድረክ የሚወጡ ጽሑፎች በሀገር ውስጥ ከስድስት ከሀገር ውጭ ደግሞ ከአምስት በሚበልጡ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ይወጣሉ፡፡ በልዩ ልዩ ሬዲዮዎችም ይቀርባሉ፡፡ በተለይም አንዱ ዓለም በፋና ሬዲዮ የሚያቀርባቸውን ትረካዎች ብዙዎች እንደሚከታተሉት ነግረውኛል፡፡ 

Wednesday, September 12, 2012

እናቁም?


አንዳንዴ የትግላችን፣የጥረታችን፣የልፋታችን ውጤት መና የቀረ የሚመስልበት ጊዜ አለ፡፡ ውኃ አልቋጥር፣ ጠብ አልል ሲልብን፤ መንገዱ ሁሉ ረዥም፣ በሮቹ ሁሉ ዝግ፣ ጩኸቱ ሁሉ ሰሚ አልባ ሲመስለን፣ በመጨረሻ የምንወሰደው መፍትሔ ነገር ዓለሙን ሁሉ መተውና መሸነፍ ይሆናል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ አበቃ›› ማለት እንጀምራለን፡፡ እንኳን እኛ ቀርቶ ሌሎች እንኳን እንዳይበረቱ ‹‹ባክህ እኛም ብለነው ብለነው አቅቶን ነው›› እያልን ተስፋ እናስቆርጣቸዋለን፡፡
ግን ሰው መልፋት ያለበት፣ መትጋትስ ያለበት፣ መታገልስ ያለበት፣ መሮጥስ ያለበት እስከ የት ነው? ሰው ተስፋ መቁረጥ ያለበት የት ደረጃ ሲደርስ ነው? የመንገድ ማለቂያው የት ነው? ውጤቱን ዛሬ ያላየነው ነገር ሁሉ ውጤት አልባ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላልን? በታሰበው ጊዜ ያልተደረሰበት ነገር ሁሉ ሊደረስበት የማይችል ነገር ነው ማለት ነው? መንገዱስ ይሄ እኛ የያዝነው መንገድ ብቻ ነውን? በሌላ መንገድስ ሊሞከር አይቻልምን?

Thursday, September 6, 2012

የአውጫጭኝ ወጥ


click here for pdf
ሴትዮዋ እርሟን አንድ ቀን ወጥ ሠራች አሉ፡፡ ገና ወጡ ከድስቱ ሳይወጣ ጎረቤቱን ሁሉ በነቂስ ጠራችና ወጥ ቅመሱ አለች አሉ፡፡ ሰውም ምን አዲስ ነገር ልታሳየን ይሆን? እያለ ግልብጥ ብሎ ወደ ቤቷ መጣ፡፡ ሴትዮዋም እንጀራውን እያጠፈች ከድስቱ ወጥ እየጨለፈች አቀረበች፡፡
በላተኛውም ግምሹ እያዳነቀ፣ ግማሹም እየሳቀ፣ ግማሹም እየተሳቀቀ፣ ሌላውም በቸርነቷ እያመሰገነ በላ፡፡ እርሷም ከምግቡ በኋላ ቡና አፍልታ የተጋባዦችን አስተያየት ትቀበል ጀመር፡፡ አንዳንዱ በወጡ አሠራር መደነቁን፤ ሌላው በተጠቀመችው ቅመም መማረኩን፤ ሌላውም የጨመረችው ቅቤ ልዩ መሆኑን፤ የቀረውም ሰው በሠራችበት ድስት የተደነቀ መሆኑን ነገራት፡፡ እርሷም ‹‹እርሟን ጠምቃ ሰጠች ጠልቃ›› ሳይሏት ይህ ሁሉ ጎረቤት ተገኝቶ ይህንን  የርሷን ግብዣ ማድነቁ አስደስቷታል፡፡ ከዚህ በፊት በሠፈሩ ያልተደረገ፤ አዲስ ነገር መሆኑንም ጎረቤቶቿ አድንቀውላታል፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ እኔ ነኝ ያሉ አያሌ የወጥ ባለሞያዎች በመንደርዋ ተሠርተዋል፤ እንዲህ እንደርሷ ሰው ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ወጡን የቀመሰለት፤ እንዲህ እንደርሷም ወጡን ለሕዝብ ክፍት ያደረገ ባለሞያም ታይቶ ተሰምቶ እንደማይታወቅ የተናገሩም ነበሩ፡፡

Monday, September 3, 2012

የተማርንበትም የተማረርንበትም ሰሞን(ፎቶው የቢቢሲ ነው)
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ከተረዳበት ሰዓት ጀምሮ ሀገራችን አዲስ መልክ ይዛለች፡፡ ያለፉት ቀናት ስለራሳችን የተማርንባቸው፤ በራሳችንም የተማረርንባቸው ቀናት ነበሩ፡፡ እስኪ ከተማርንባቸው ልጀምር፡፡
ትዝ ይለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከውጭ ሀገር ወደ አዲስ አበባ የሚገቡበት ጊዜ ነበር፡፡ በቦሌ ጎዳና ፖሊሶች አዚህም እዚያም በዛ ብለዋል፡፡ እኔ ደግሞ አልሰማሁም ነበርና እዚያ አካባቢ ለሥራ መሄድ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መንገዱ ጭር አለ፡፡ ፖሊሶችም መጡና ከአካባቢው ዘወር እንድንል ነገሩን፡፡ የሚገርመው ነገር ግን አካባቢው በአፓርታማዎች የተጠቀጠቀ ነበርና ዘወር የምንልበት ቦታ ጠፋን፡፡ ፖሊሱ ግን አሁንም አሁንም ከአካባቢው ዘወር እንል ዘንድ ያዝዛል፡፡ ግን የት ዘወር እንበል? በመጨረሻ መጣና በአፓርታማው የታችኛው ክፍል ካሉት ቤቶች አንዱን አንኳኳ፡፡ አንዲት በእድሜ ጠና ያሉ ሴት ከፈቱ፡፡ ‹‹ግቡ›› አለን ፖሊሱ፡፡ አንድ ሰባት እንሆናለን፡፡ ግራ ገብቶን ተያየን፡፡ ከጀርባችን ገፋ ገፋ እያደረገ ሰው ቤት ውስጥ አስገባን፡፡ ስለ ቻይና ባቡርና ፖሊስ ያየሁት ፊልም ነው ትዝ ያለኝ፡፡ ሴትዮዋ በሩን እንዲዘጉ ተነገራቸው፡፡ ተዘጋ፡፡
አሁንም ሰው ቤት ገብተን ተያየን፡፡ ደግነቱ ሴትዮዋ ተግባቢ ናቸውና ‹‹በሉ እንግዲህ መንግሥት ካዛመደን ዐረፍ በሉና ሻሂ ጠጡ›› አሉን፡፡ እኛም ሳቅ እያልን ባገኘነው ወንበር ተቀመጥን፡፡ እዚያ ተቀምጠንም በባለ ሥልጣኖቻችንና በሕዝባቸው መካከል ስላለው ግንኙነት ተቸን፤ አማን፤ ሃሳብም ሰነዘርን፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠመንንም ተጨዋወትን፡፡

Wednesday, August 29, 2012

ፓትርያርክና ፕትርክና


ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር፤ ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቃለ መጠይቅ ማድረግ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ በሚገኘው ቢሯቸው ወደ አሥር ሰዓት አካባቢ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር ተገኝቼ ነበር፡፡ ያ ቃለ መጠይቅ ወደ አራት ሰዓታት ያህል የፈጀና በሐመር መጽሔት ላይ በተከታታይ የወጣ ነበር፡፡
በመካከል ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በወቅቱ የነበረችበትን ሁኔታ የሚያነሣ አንድ ጥያቄ ተሰነዘረላቸው፡፡ መጀመርያ በመዳፋቸው አገጫቸውን ያዙና ወደ ጠረጲዛቸው አንገታቸውን ደፉ፡፡ በዚያም ለረጅም ሰዓት አቀርቅረው ቆዩ፡፡ ምን እያሰቡ ይሆን ብለን እናስብ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ቀና ሲሉ ዕንባዎቻቸው በሁለቱም ጉንጮቻቸው ላይ መንታ ሆነው ይፈሱ ነበር፡፡ ምንም አላሉንም፡፡ ዝም ብለው አዩን፡፡ ከዚያም ይቀረጹበት የነበረውን ቪዲዮ እንዲጠፋ አዘዙ፡፡ እኛንም ተቀመጡ አሉን፡፡ ግራ ገብቶን ተቀመጥን፡፡
ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያን ዕለት ሲናገሩት የነበረውን ነገር ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ሲናገሩት ሰምቼ አላውቅም፡፡ ሲነግሩን ያለቅሱ ነበር፡፡ እኛም ብንሆን በኀዘን ድባብ ውስጥ ነበርን፡፡

Thursday, August 23, 2012

ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት


click here for pdf
ብዙ ጊዜ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ሲባል፤ ለዚህም ሕግ ሲጠቀስ እሰማለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን የሚናገረው ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት አንድ መሆናቸውን፡፡ እንኳን በደስታ በኀዘን እንደ ማይለያዩ፡፡
ንግሥት ዘውዲቱና አቡነ ማቴዎስ ሁለቱም የተወደዱ ነበሩ፡፡ ሁለቱም ሞተው ተለቅሶላቸው ተቀበሩ፡፡ ሁለቱም ሲሞቱ የሰው እጅ አለበት ተብሎ ታምቷል፡፡ ሁለቱም በኣታ ተቀበሩ፡፡
ዐፄ ኃይለ ሥላሴና አቡነ ቴዎፍሎስ ሁለቱም የለውጥ አራማጆች ተብለው በአዲሱ ትውልድ መጀመርያ ተመሰገኑ፡፡ ሁለቱም በኋላ ላይ ከደርግ ጋር ተጣሉ፡፡ ሁለቱም ታሠሩ፡፡ ሁለቱም ባልታወቀ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ የሁለቱም መቃብር ለ17 ዓመታት ሳይታወቅ ኖረ፡፡ ሁለቱም ኢሕአዴግ ከገባ በኋላ ዐፅማቸው ወጥቶ ተቀበረ፡፡
መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና አቡነ መርቆሬዎስ ሁለቱም የብሔራዊ ሸንጎ አባላት ነበሩ፡፡ ሁለቱም ኢሕአዴግ ሲገባ ከሥልጣን ‹‹ወረዱ››፡፡ ሁለቱም ከሀገር ወጡ፡፡ ሁለቱም በሕይወት ኖረው በቦታቸው የተተኩት ሲሞቱ አዩ፡፡
መለስ ዜናዊና አቡነ ጳውሎስ ሁለቱም ከ1983 ዓም በኋላ ወደ ሥልጣን መጡ፡፡ ሁለቱም በአንድ ሰሞን በሆስፒታል ዐረፉ፡፡ ሁለቱም ከእነርሱ በፊት የነበሩት መሪዎች ሳይሞቱ ቀድመው ሞቱ፡፡ በአቡነ ጳውሎስ ቀብር ላይ ጊዜያዊው ጠቅላይ ሚኒስትር ተገኙ፤ በመለስ ዜናዊም ቀብር ላይ ጊዜያዊው ፓትርያርክ ይገኛሉ፡፡
እና ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት የተለያዩ ናቸው ያለው ማነው?

Tuesday, August 21, 2012

አሳዛኙ ዜና


እየሰማሁት ያለሁትን ነገር ለማመን ረዥም ሰዓት ፈጅቶብኛል፡፡ ቆይቼ ደግሞ ምናለ ውሸት በሆነ እላለሁ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን በዚህ ሁኔታ ማጣት አልነበረብንም፡፡ እንደ ሰው የተሳሳቷቸውን ራሳቸው አርመዋቸው፤ የጀመሯቸውን ነገሮች ውጤታቸውን አይተው፡፡ በሕይወት እያሉ ሌላ ሰው በሥልጣናቸው ተቀመምጦ፤ እርሳቸው እንደማንኛውም ሰው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሲራመዱ ለማየት ነበር ምኞቴ፡፡
በተለያዩ ሚዲያዎች ስለ ሕመማቸው፣ ከዚያም ዐልፎ ስለ መሞታቸው አስቀድሞ ሲነገር ነገሩ እጅግ ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ ከሕመማቸው ተሽሏቸው ያለፉትን ሃያ ዓመታት ስሕተቶችን ራሳቸው ያርሙታል፤ ያለፉትን ሃያ ዓመታት ጥንካሬዎችም በግለሰብ ላይ ሳይሆን በሥርዓት ላይ ይስኬዱታል ብዬ አምን ነበር፡፡
ግን አልሆነም፡፡ ሰው መሆን አይቀርም፡፡ አሁን ራሱ ለማመን እየከበደኝም ቢሆን አቶ መለስ ዜናዊ ዐርፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ መሪዎቿ በሕይወት እያሉ ሥልጣን ሲቀያየሩ ሳያይ፣ የመሪዎች ለውጥ የሚመጣው አንድም በሞት አንድም በስደት ብቻ እንደሆነ ልንቀጥል ነው ማለት ነው፡፡
በአንድ ሰሞን ፓትርያርኩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያጣንበት ምክንያት ምን ይሆን? የእግዚአብሔርስ መልእክቱ ምንድን ነው? ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኀዘን ቦታ ላይ ‹‹ሞት ታላቅ መጽሐፍ ነው፤ ነገርግን የሚያነበው የለም›› እንዳሉት ከሰሞኑ ሁኔታ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ሌሎቻችንስ ምን እንማራለን?
ለሁላችንም መጽናናቱን ይስጠን፡፡


እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር

Thursday, August 16, 2012

ከፊታችን ያለው መንገድ


click here for pdf
በትግራይ ክልል ዐድዋ ውስጥ ልዩ ስሙ እንዳ አቡነ ገሪማ በተባለው ቦታ ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓም የተወለዱት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማረፋቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱ በይፋ ገልጣለች፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ከተሰየሙት ፓትርያርኮች መካከል በመንበራቸው ላይ ብዙ ጊዜ የቆዩት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡ ለሃያ ዓመታት፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ውስጥ ካለፉት አምስት ፓትርያርኮች መካከል አንደኛው በደርግ ተገድለዋል፤ አንደኛው ተሰድደው ወጥተዋል፤ ሦስቱ ደግሞ በአገልግሎት እያሉ ዐርፈዋል፡፡ ምንጊዜም ቢሆን አንዲትን ቤተ ክርስቲያን ይመራ የነበረ አባት ሲያርፍ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ዘንድ በአንድ በኩል ያረፉት አባት እንዴት ነበር ያገለገሉት የሚል ጥያቄ ሲነሣ በሌላ በኩል ደግሞ ቀጣዩስ ማን ይሆናሉ የሚል ጥያቄ ይፈጠራል፡፡
በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቀኖናና ትውፊት መሠረት አንድ ፓትርያርክ ሲያርፉ የሚከናወኑ ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህም በስድስት ይከፈላሉ፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዛሬ ሌሊት ዐረፉ

                            ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ዐርፈዋል፡፡
እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር
ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያልታሰበ አደጋ እንዳያመጣ ጥንቃቄ የተሞላ ሃይማኖታዊና ጥበባዊ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አራት ነገሮች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል
  1. የእርሳቸው ደጋፊና ተቃዋሚ በሆኑ አካላት መካከል በሚፈጠር ግጭት ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትታወክ
  2. ሀብት እና ቅርስን የማሸሽ አዝማሚያ እንዳይከሰት
  3. ቤተ ክርስቲያኒቱን ማን ለጊዜው ይምራት በሚለው ዙርያ በሚፈጠረው ልዩነት አደጋ እንዳይከሰት
  4. በቀጣይስ ማን በወንበሩ መቀመጥ አለበት በሚለው ዙርያ ችግር እንዳይከሰት
አሁን የመረጋጊያ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ለፓትርያርኩ የኀዘን ጊዜ ያውጅ፡፡ ጊዜያዊ ኮሚቴ ያቋቁም፡፡ ነገሮችን በግልጽነት ለሕዝቡ ይፋ ያድርግ፡፡ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ልምድ ይውሰድ፡፡ ማንኛውም የፓትርያርኩ ንብረቶች ወደ ሌሎች ከመጓዛቸው በፊት በጥብቅ ይቀመጡ፡፡ የባንክ ሂሳቦች ይዘጉ፡፡
አሁን የመረጋጊያ ጊዜ ነው፡፡ ለሀገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲባል ቤተ ክርስቲያኒቱን በዚህ ሁኔታ ወደ ጸጥታ ወደብ የሚመራ አመራር ያስፈልጋል፡፡
ዝርዝሩን እንመለስበታለን፡፡

ኢምፓላ

እነሆ አሁን በደቡባዊ አፍሪካ በምትገኘው ዚምባቡዌ ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ዋና ከተማዋን ሐራሬን በአውሮፕላን ማረፊያው በኩል ለቅቀን እየወጣን ነው፡፡ የሐራሬ አውሮፕላን ማረፊያ ሲባል እንዲህ እንደ አዲስ አበባው እንዳትጠብቁት፡፡ የጥንቷ የአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያን አስቡና፣ ሩብ ጨምሩባት፡፡ ሀገሪቱ በገጠማት የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት አየር መንገዳቸው ዓለም አቀፍ በረራውን ማቆሙን ሰምቻለሁ፡፡
የዛሬን አያርገውና ሀገሪቱ ፓሪስን በውበቷ፣ አየር ላንድን በእርሻዋ፣ ቺካጎን በከተማ ቅርጽዋ፣ ካናዳን በኢኮኖሚዋ፣ ትጣቀሳቸው እንደነበረች ዛሬም እንኳን መከራውን ተቋቁሞ የሚገኘው ማንነቷ ይናገርላታል፡፡
ከሐራሬ ወጣ ስትሉ ትናንት ሰፋፊ እርሻዎች የነበሩ ሜዳዎች ጦርነት የተካሄደባቸው የአፍጋኒስታን መንደሮች መስለው ይታያሉ፡፡ በእርሻው መካከል እዚህም እዚያም የቆሙ ትራክተሮችን ታያላችሁ፡፡ በላያቸው ላይ ሣር በቅሏል፡፡ የሳቫና የሜዳ ሣር  እንኳን ርግፍ አድርጎ የሚተወው አግኝቶና እንዲያውም እደግ እደግ ይለዋል፡፡ የእርሻ ምርቶች ሲቀነባበሩባቸውና እስከ አሜሪካና ካናዳ ሲላክባቸው የነበሩት የእርሻ ፋብሪካዎች ተገትረው ቀርተዋል፡፡ 

Wednesday, August 1, 2012

ማጣት እንደ ማግኘት

I couldn't post the word document as usual because of some technical difficulties of my Amharic software. For the time being please read the article in PDF. Sorry for the inconveniences.


Tuesday, July 24, 2012

ፈረንጅ ነውኮ


click here for pdf 
ማክሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2004 ዓም የተዘጋውን የኢንተርኔት መሥመር ለማስከፈት እዚህ አያት መንገድ ጉርድ ሾላ ያለው የቴሌኮሙኒኬሽን ቅርንጫፍ ሄድኩላችሁ፡፡ በጠዋቱ ሠልፉ ለጉድ ነው፡፡ ምናለ የቀበሌ መስተዳድሮች ለአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሥልጠና ቢሰጡ? ቀበሌ እንኳን የጠፋው ሰልፍ እዚህ ከነ ሙሉ ክብሩ ይንጎማለላል፡፡ አዛውንትና አሮጊቶች እግራቸው እየተንቀጠቀጠ ውጭ በብርድ ቆመዋል፡፡ ያውም ከሠላሳ ደቂቃ በላይ፡፡
እንደምንም ተራ ደርሶኝ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ እዚያም ለካስ ሌላ ሰልፍ አለ፡፡ ደግነቱ እዚህ የምትሰ ለፉት ተቀምጣችሁ ነው፡፡ ፊት ለፊታችን የተገተሩት ኮምፒውተሮች ብዙዎች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ሰዎች ግን ሦስት ኮምፒውተር ለአንድ ሠተራኛ እንዲደርሳቸው ሆነው ነው፡፡ አሁን እነዚህ ሁሉ ኮምፒውተሮች የሚሠራባቸው ከሌለ ለምን ተገዙ? ከተገዙስ ለምን አይሠሩም? ማን መልስ ይሰጣችኋል? ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ አለ ያገሬ ሰው፡፡