Wednesday, December 14, 2011

እንድንሟላ እንተጋገዝ

(click here for pdf) አንድ ቀበጥ ልጅ የነበራት አንዲት እናት ነበረች፡፡ ገጽታዋ ሁሉ በእሳት የተለበለበ ነበር፡፡ ያያት ሁሉ ይገረማል፡፡ አንዳንዱም ደንግጦ ይሸሻል፡፡ በተለይ ልጇ በእናቱ ገጽታ ስለሚያፍር አብሯት መታየትም ሆነ ትምህርት ቤት አብራው እንድትሄድ አይፈልግም ነበር፡፡ ለአንዳንድ ጓደኞቹ እናቴ ሞታለች፣ ለሌሎቹም እናቴ ውጭ ሀገር ሄዳለች እያለ ነበር የሚነግራቸው፡፡
ከፍ አለ፡፡ ከኮሌጅም ወጣ፡፡ ትልቅ ባለ ሥልጣን ሆነ፡፡ በየሚዲያውም ስሙ ይጠራ ነበር፡፡ ሰዎችም ከእርሱ ጋር መገናኘትን እንደ ብርቅ ያዩት ነበር፡፡ መቼም ቢሆን ግን ጓደኞቹንም ሆነ ሌሎች ወዳጆቹን ወደ ቤቱ ለማምጣት አይደፍርም ነበር፡፡ በድንገት ወደ ቤቱ ለመጡትም ቢሆን ያቺን ምስኪን እናቱን የቤት ሠራተኛዬ ናት እያለ ነበር የሚያስተዋውቃቸው፡፡
 አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡
እናቱ ጠራቺው፡፡ እያንጎራጎረ መጣ፡፡ ፊት ለፊቱ ተቀመጠች፡፡
«ለመሆኑ ለምን እነደዚህ እንደሆንክ ታውቃለህ?» አለቺው
«ስትፈጠሪ እንደዚህ የሆንሽ ይመስለኛል» አላት፡፡
«አይደለም፡፡»
አንድ ፎቶ ግራፍ አወጣችና አሳየቺው፡፡ እጅግ በውበት የተጥለቀለቀች ለግላጋ ወጣት ሴት፡፡
«ማናት?» አላት፡፡
«ከጀርባው ተመልከተው» አለቺው፡፡
ጀርባውን ገልብጦ አየው፡፡ የእናቱ ስም ተጽፏል፡፡ ከሠላሳ ዓመታት በፊት የተነሣ ፎቶ ነው፡፡
«አላምንም» አለ ደንግጦ፡፡
«ታምናለህ» አለቺውና ሌላም ሰጠቺው፡፡
ትምህርት ቤት ከጓደኞቿ ጋር የተነሣቺው ፎቶ ግራፍ ነበር፡፡ ሌላም ሠለሠችለት፡፡
ታድያ ለምን እንደዚህ ሆንሽ አላት አፍጥጦ፡፡
«ታሪኩ እንዲህ ነው» አለቺው፡፡
«አንድ ቀን አንተ የአሥር ወር ሕፃን እያለህ ዕንቅልፍ ወስዶህ አልጋ ላይ ተኝተህ ነበር፡፡ እኔ እህል ላሰጣ ውጭ ነበርኩ፡፡ እህሉን አስጥቼ ዘወር ስል ቤቱ በእሳት ተያይዟል፡፡ ለካስ ቡታ ጋዙ አጋድሎ ቤቱ በእሳት ተያይዟል፡፡ ኡኡ ብዬ ጮኽኩ፡፡ ሠፈሩም ተሰባሰበ፡፡ ሁሉም እሳቱን ለማጥፋት እንጂ አንተን ለማውጣት አላሰቡም ነበር፡፡
«በእሳቱ መካከል እንደ ቅዱስ ገብርኤል ገባሁበት፡፡ አንተን በብርድ ልብሱ ሸፍኜ አምላኬን እየተማጸንኩ በፍጥነት ይዤህ ወጣሁ፡፡ ያኔ የኔ ልብስ በእሳት ተያይዞ ነበር፡፡ ከፊሉ አካሌም በእሳቱ ተጎድቶ ነበር፡፡ አንተን ከሠለስቱ ደቂቅ የለየህ እነርሱ ጢስ ሳይነካቸው መውጣታቸው ነው፡፡ አንተን ግን ጢሱ ቢያፍንህም እሳቱ ግን አልነካህም፡፡ የአንተን እሳት እኔ ተቃጠልኩልህ፡፡
«አየህ ልጄ፡፡ ያንተ ቃጠሎ እና ጉዳት እኔ ላይ ነው፡፡ የእኔ ጤና እና ውበት ደግሞ አንተ ላይ ነው፡፡
«ያን ጊዜ ለራሴ አድልቼ ብተውህ እኔ በጤና መኖር እችል ነበር፡፡ አንተ ግን ዛሬ በሕይወት አትኖርም ነበር፡፡»
ልጁ ራሱን ይዞ ጮኸ፡፡ እንደ ዕብድ እየጮኸም እናቱ እግር ሥር ተደፋ፡፡
በሦስተኛው ቀን ጓደኞቹን ሰበሰበ፡፡ እናም እንዲህ አላቸው፡፡
«እናቴ ይህቺ ናት፡፡ የርሷ ውበት እኔ ጋር ነው፡፡ ይእኔ መከራ እና ጉዳት ግን እርሷ ላይ ነው፡፡» አላቸው ይባላል፡፡
ለመሆኑ አካል ጉዳተኞች የማንን ጉዳት ነው የተጎዱት?
እንደ እኔ እምነት የሁላችንን ጉዳት ነው የተጎዱት፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ሁሉም ጤነኛ፣ ሁሉም አካል ጉዳተኛ ሊሆን አይችልም፡፡ የኛ ጤንነት የኛ ብቻ አይደለም የእነርሱም ነው፡፡ የእነርሱ ጉዳትም የኛ ጭምር ነው፡፡ ስለ አካል ጉዳተኞች ስናስብ ስለ ተጎዱ ስለ ሌሎች ሰዎች አይደለም የምናስበው፡፡ ስለተጎዳነው ስለ እኛ ነው የምናስበው፡፡ የተጎዱት የማኅበረሰቡን ጉዳት ነው፡፡ የተሸከሙትም የማኅበረሰቡን ሸክም ነው፡፡ የሚቀበሉት ፈተና የማኅበረሰቡን ፈተና ነው፡፡
ለአካል ጉዳተኞች የምናደርጋቸው ነገሮች የቸርነታችን፣ የደግነታችን፣ የችሮታችን፣ የአዛኝነታችን ውጤቶች አይደሉም፡፡ እኛ ለእኛ የምናደርጋቸው የሰውነት ግዴታዎቻችን ናቸው፡፡ የእኛ መከራ እነርሱ ላይ የእነርሱም ጤና እኛ ላይ ነው፡፡
ማኅበረሰብ አንዱ ያለ አንዱ ሊኖር አይችልም፡፡ የማያስፈልጉ ዜጎች የሉም፡፡ እጅግ የሚያስፈልጉ ዜጎችም የሉም፡፡ አንዱ የሌላው ጥገኛ መሆኑ የሰውነት ግዴታ እንጂ የአካል ጉዳተኛነት ውጤት አይደለም፡፡
አካል ጉዳተኛነት ከሰዎች ጋር የሚኖር ነው፡፡ አንዳንዶች አጋጥሟቸው ተጋፍጠውታል፡፡ ሌሎቻችን ሰምተነው እና አይተነው ብቻ እናውቀዋለን፡፡ ዛሬ አካል ጉዳተኞች ብለን የምንጠራቸው ወገኖቻችን ግን የኛን ችግር ተጋፍጠው፣ የኛን ሕመም ታምመው፣ የኛንም ገፈት ቀምሰውልናል፡፡
ለእነዚህ ወገኖች ክብር መስጠት፣ ክብካቤ ማድረግ እና መብቶቻቸውን መጠበቅ ለማንም የሚደረግ ተግባር አይደለም ለእኔ የሚደረግ ነው፡፡ ለራሴ፡፡
ሰው በራሱ ሙሉ አይሆንም፡፡ አንዳችን የሌላችን ማሟያ ነን፡፡ አንዳችንም ያለ ሌላችን ሙሉ አንሆንም፡፡
በሀገራችን እንዲህ የሚባል ነገር አለ፡፡ አንድ ማየት የተሳነው እና መራመድ የተሳነው ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ በዚያው መንደር ደግሞ የአንድ የወይን እርሻ ባለቤት ነበር፡፡ ሰው ሁሉ ከዚያ የወይን ማሳ ገብቶ የፈለገውን ይወስድ ዘንድ ተፈቅዶለት ነበር፡፡ ሁለቱ ግን ተከለከሉ፡፡
ምክንያት? ሲባል
ይህም አያይም ያም እንደ ሌላው ሆኖ አይራመድም ተብሎ፡፡ እነዚህ ሁለቱም ለየራሳቸው ጉዳታቸውን እንጂ ጥንካሬያቸውን አስበውት አያውቁም ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ተማከሩ፡፡ አንተ በእኔ እግር ሂድ፣ እኔም በአንተ ዓይን ልይ ተባባሉ፡፡ እናም ወደ ወይኑ ሥፍራ ሄዱ፡፡ ባለቤቱም ምንም ኣያመጡም ብሎ ትቷቸው ሄደ፡፡
ማየት የተሳነው እግሩ የተጎዳውን ጓደኛውን ትከሻው ላይ ሽኮኮ አለው፡፡ ያም በጓደኛው ትከሻ ላይ ሆኖ ባለቤቱ መምጣት አለመምጣቱን መጠበቅ ጀመረ፡፡ ማየት የተሳነውም በእጆቹ እስኪበቃው ወይኑን ሸመጠጠ፡፡ በኋላም ባለቤቱ ሲመጣ ማየት በተሳነው እግር እየሮጡ፣ እግሩ በተጎዳው ዓይን እያዩ አመለጡ፡፡
ይህንን ያየ ባለቤቱም
      ሐንካስ በእግረ ዕውር ሖረ፣
      ዕውርኒ በዓይነ ሐንካስ ነጸረ፣
      ወበክልኤሆሙ ወይንየ ተመዝበረ፣ አለ ይባላል፡፡
               ከተባበርን የማንወጣው ችግር የለም፡፡      
በዓለም ዐቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን
በኢትዮጵያ የስብሰባ ማዕከል የቀረበ                                                                            ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓም

13 comments:

 1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

  ‹‹ ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፡፡››

  እኔ እንዴው አካል ጉዳተኛ ከሚባል በደፈናው ጉታተኛ ቢባል የሚመረጥ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቻችን አይን ወይንም እግር ስላላጣን በሌሎቹ ላይ ስንመፃደቅ እንኖራለን፡፡ አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች ከማንኛውም ሰው ባላነሰ መልኩ ማሰብ መማር መስራት ይችላሉ፡፡
  በእርግጥ የቤተሰብ ሁኔታ ወይም የችግር ሁኔታ እየያዛቸው አብዛኞቹ በልመና ሲሰማሩ ይስተዋላል፡፡ ምክንያቱም ወላጆች ተምሮ ይጦረኛል የሚለው ተስፋ ስለሌላቸው ነው፡፡ እና ለቤተሰብም ግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠት አለበት፡፡
  አካል ጉዳተኞችም ቢሆኑ ለመማርና ለመስራት ፅኑ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህ ደግሞ ብዙ አርአያ የሚሆኑ አሉ፡፡ በሌላ በኩል አንድ አይኑን ትራኮማ ከተያዘ ጥቁር መነፅር አድርጎ አይን የሌለኝ እያለ በሰው ላይ ይረማመዳል ወይም አውራ ጣቱ ከቆሰለ መላ እግሩን ጠቅልሎ ክራንች ይዞ ሲለምን የሚታየው ቀላል አይደለም፡፡

  ለመሆኑ እንዴው የልመና ነገር ከተነሳ ላይቀር የኛ ቤ/ክ ማየት የተሳናቸው መዝሙር እንዴት ሆነ? አሁንማ በእንጨትም ማጨብጨብ ጀምረዋል፡፡ ሰው ራሱ ራርቶ ሊመፀውታቸው ይገባል እንጂ የመላእክት ምስጋና እንዴት መለመኛ ይሆናል?

  ለማንኛውም አካል ጉዳተኞችን በማስተማር በመርዳት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ እላለሁ፡፡ለዚህም እግዚአብሔር ሃይልና ብርታት ይስጠን፡፡ አሜን፡፡

  ReplyDelete
 2. ቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡ የሰማነውን ለመተግበር ያብቃን፡፡

  ReplyDelete
 3. masetawale yesetana...tabarake dn daniel

  ReplyDelete
 4. Dear Daniel,

  You teach and preach us to think rationally. We should underline that the disabled people are not disabled by their will. It is better to see things if we are in their foot.

  ለመሆኑ አካል ጉዳተኞች የማንን ጉዳት ነው የተጎዱት?
  እንደ እኔ እምነት የሁላችንን ጉዳት ነው የተጎዱት፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ሁሉም ጤነኛ፣ ሁሉም አካል ጉዳተኛ ሊሆን አይችልም፡፡ የኛ ጤንነት የኛ ብቻ አይደለም የእነርሱም ነው፡፡ የእነርሱ ጉዳትም የኛ ጭምር ነው፡፡ ስለ አካል ጉዳተኞች ስናስብ ስለ ተጎዱ ስለ ሌሎች ሰዎች አይደለም የምናስበው፡፡ ስለተጎዳነው ስለ እኛ ነው የምናስበው፡፡ የተጎዱት የማኅበረሰቡን ጉዳት ነው፡፡ የተሸከሙትም የማኅበረሰቡን ሸክም ነው፡፡ የሚቀበሉት ፈተና የማኅበረሰቡን ፈተና ነው፡፡

  ለአካል ጉዳተኞች የምናደርጋቸው ነገሮች የቸርነታችን፣ የደግነታችን፣ የችሮታችን፣ የአዛኝነታችን ውጤቶች አይደሉም፡፡ እኛ ለእኛ የምናደርጋቸው የሰውነት ግዴታዎቻችን ናቸው፡፡ የእኛ መከራ እነርሱ ላይ የእነርሱም ጤና እኛ ላይ ነው፡፡

  ReplyDelete
 5. ዲ.ን ዳንኤል፤ዛሬ ሁሌ እየቆጨኝ ያለ ነገር አነሳህልኝ!
  በርካታ አካል ጉዳተኞቻችን ወደ ነደያንነት ተሸጋግረዋል!ለምን ይሆን?
  አገራችን ውስጥ ስንቶች በጦርነት አካል ጉዳተኛ እንደሆኑ ቤቱ ይቁጠረው፡፡የህዝብ እና ቤት ቆጠራ መ/ቤት!እጅግ በርካታ እንደሚሆኑ እገምታለሁኝ፡፡እንደውም በአይነት ይኽኛው ምክንያት ሳይበልጥ አይቀርም እንደ እኔ ግምት፡፡በተጨማሪም በተፈጥሮ አደጋ፤በመኪና አደጋ፤በኬሚካል፤በረሀብ፤---በርካቶች አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፤እየሆኑም ይገኛሉ፡፡በኬሚካል ስል አሁን አሁን በእህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ አንድ ካልተባለ አሁን በአንድ ድጅት ውስጥ ያለው ዳታ ነገ ወደ ሁለት ድጅት መግባቱ አይቀሬ ነው የሚሆንብን፡፡ለነገሩ እድገት እንጂ መከራ እንኳንስ በሁለት ድጅት አይደለም በአንድም ይመራል፡፡
  ኢትዮጲያ ውስጥ ያሉት አካል ጉዳተኞችን ለመንከባከብ የምንሰራው ስራ ስንመለከተው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ዳር ድንበርን ለማስከበር ብለው ለተጎዱ፤የጠራ መኪና ፣ሹፊር እና መንገድ ባለመኖሩ ለጎዳናቸው፤አሲድ ለደፋንባቸው፤የቅድመ ማስጠንቀቂያ አዋጅ ሳንናገር በተፈጥሮ አደጋ አካላቸውን ላጡ፤በቂ ህክምና ሳናደርግላቸው ቀርተን አይናቸው ለጠፋ፣እጃቸው ለተቆረጠ-- ያደረግንላቸውን ድጋፍ እና እንክብካቤ እንየው እስኪ፡፡እንደ እኔ ምንም አላደረግንላቸው ባይ ነኝ፡፡በዚህም የተነሳ በአብዘሃኛው እኛ አገር ያሉ አካል ጉዳተኞች የት ወደቃችሁ ባለመባላቸው ምክንያት ወደ ነዳያንነት ተሸጋግረዋል፤እየተሸጋገሩም ነው፡፡ ስለሆነም፤
  1.የአካል ጉዳተኞቻችን መረጃ በአግባቡ መያዝ አለበት፡፡አካል ጉዳተኛ ሳይሆኑ አስመስለው ድጋፍ የሚጠይቁ፤ምጽዋት የሚሻሙ፤እርዳት መዝገብ ላይ ስማቸው ዘወትር የማይጠፋ በርካቶች አሉ፡፡ሌሎች ደግሞ በገንዘብ ሳይሆን በተለያየ ነገር እንዲንደግፋቸው ይፈልጋሉ እና መረጃቸውን መያዝ ተገቢ ነው፡፡
  2. በእነርሱ ስም መነገድ ሳይሆን እንዲነግዱ፤ስራ እንዲፈጥሩ በስማቸው የተቋቋሙ ማህበራት ከህዝቡ ጋር በመተባበር መስራት አለባቸው፡፡አለብን፡፡አካል ጉዳተኞች ያጡት የአካል ክፍላቸውን እንጂ አዕምሮን ባለመሆኑ መስራት፤ራስን መምራት፤ቤተሰብ ማስተዳደር ይችላሉ፡፡ ለዚህም ህብረተሰቡ በዘላቂ ሁኔታ እንዲረዳቸው የሚያስችል ስልት በየሰፈሩ፤በየቀበሌው መዘርጋት አለበት፡፡ዘለቄታዊ እርዳታ ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡በየአመቱ የፋሲካ፤የገና፤የሰኔ ጾም --- በየሰንበት ት/ቤቶች ነደያንን ለማስፈሰክ ተብሎ የሚሰበሰብ ብር፡፡ተማሪዎቹ ይሰበስባሉ፣ከዚያም ነዳያንንም ያስፈስካሉ፡፡በቀጣይ አመት ደግሞ እንዲሁ ይደረጋል፡፡በቃ አንድ ሰንበት ት/ቤ/ት ጎበዘ ከተባለ 2 እና ሶስቴ በአመት ለነዳያን እንጀራ በስጋ ማብላት የእቅዱ ታላቅ ግብ ነው፡፡ምን ሰ/ት/ቤት ብቻ?በየማህበራቱስ ቢሆን የተረፈን እንጀራ ሰጥቶ ድጋፍ አደረኩኝ ፣ምጽዋት ሰጠሁኝ ማለቱ ምን ቁም ነገር አለው፡፡ምሳ አብልቶ እራት የማያስደግም ድጋፍ ድጋፍ ይባላል እንዴ?መንግስት ቢሆን የአካል ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ ነጭ ቲሸርት አልብሶ ስላስሮጠን፣ለስላሳ ስለጋበዘን ስራ ሰራ ሊባል ይችላል እንደ?
  ሰ/ት/ቤቶች ገንዘብ ካላቸው፣ካሰባሰቡ ከሰበካ ጉባኤው ጋር ሆነው ለምን ዘለቄታዊ ድጋፍ አያደርጉም፡፡እንደ አንድ ቤተክርስቲያን በር ላይ እኮ ከ10 እስከ 15 አመት የሚቀመጡ ነደያንን በርካቶች አካል ጉዳተኞቻችን እኮ ሰ/ት/ቤቱ 5 እና 10 ችግኞች እንዲተክሉ ቢያደርጋቸው እኮ ከእነርሱ አልፈው ሌላም ይጠቅማሉ፡፡ግፍትርትራቸውን አውጥቶ ለራሱ የመኪና ወንበር የሚይዘው እኮ ያ በበአል እለት ሳንቲም የሚወረውረው ህዝብ አይደለም እንዴ?እናም ዘላቂ እርዳታ መፈለግ አለበት፡፡እስኪ አስቡት እኛ ለጽድቅ ብለን ማለዳ ተነስተን ቤተክርስቲያን ለመሄድ ብርድ ምናምን የምንል ሰዎች እነርሱ እኮ ሌሊቱን ሙሉ ብርድ እና ውርጭ ወርዶባቸው ማለዳ ላይ ግን ለመለመን አይቦዝኑም፡፡እንግድህ ያን ያህል ችግርን መቋቋም ልምድ ካላቸው ለምን ስራ እንዲፈጥሩ አናደርጋቸውም፡፡በርካታ ቤተክርስቲያናት ሰፋፊ ቦታ አላቸው፤የከተማ አስተዳደርስ ቢሆን ከሊዝ የተረፈው ቦታ ያጣል እንዴ ለዚህ የተቀደሰ ሃሳብ!?
  3. በስነ ምግባር የታነጹ ለማድረግም ስራ መሰራት አለበት፡፡ቤተክርስቲያን አካባቢ ጧት ምጽዋት ሲጠይቅ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የምታዩት ሰው ከሰዓት ጠጅ ቤት ገብቶ እንቧ ከረዩ ይላል፡፡ሰው እንዴት ለምኖ ጠጅ ይጠጣል?ለነገሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ብር እየለመነ ቢራ የሚጠጣ አካል ባለበት አገር እነርሱ ቢጠጡ ላይገርም ይችላል፡፡ሆኖም ዝንጀሮ መጀመሪያ የመቀመጫየ እንዳለችው እነዚህ ከአካል ጉዳተኝነት ወደ ነደያንነት የተላለፉ ወገኖቻችን ማስቀደም ያለባቸው መጠጥ ሳይሆን እራስን መቻልን መሆኑን በማስተማር በስነ-ምግባር እንዲታነጹ ስራ መስራት አለብን፡፡
  እኔ በመንፈሳዊ ወንድሜ ሃሳብ ተነሽቸ የታየኝን እና የተሰማኝን ብያለሁ!እናንተ ደግሞ ጨምሩበት እና በየአካባቢያችን ድጋፍ ለማድረግ ሃሳቡን እንቀምረው፡፡ቅመራ እውነትነት ካለው ጠቃሚ ነው፡፡
  ውብሸት ከባህር ዳር!

  ReplyDelete
 6. ጤና ይስጥልኝ ዳኒ! ይችን መጣጥፍህን እያነበብኩ ሳለ
  ሰሞኑን በ EBS TV ተጋባዢ የነበረ ብሩክ የሚባል ሰአሊ ልጂ አስታወስኩ ልጂ በእኛ አጠራር አካል ጉዳተኛ ይባል እንጂ እሱ የያዘውን ጥበብ ከጥቂቶች ውጭ ማንም
  አልያዘው እሱ የሚያስበውን እሳቤ እሱ ያለውን እራእይ ጥልቀት ጤነኛ ነኝ ያለ አስቦት አያውቅም:: እንዴት ወደዚህ ጥበብ ልትገባ ቻልክ ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ብሩክ ሲመልስ "እኛ ኢትዮጽያውያን ከልጂነታችን ጀምሮ እየሰማን ያደግነው የ አካልን ሀይል እንጂ የአዕምሮን ሀይል አይደለም ልጂ ሆነን ከወላጆቻችን ጋር የሆነ ቦታ ስንሄድ በየመንገዱ ከሚለምኑት ውስጥ እጂ እግር ያለው ካለ ጤነኛ ሆኖ እንዴት ይለምናል እያሉ ነው የሰማነው ማህበረሰቡ የ አካል ሀይል ከ አዕምሮ ሀይል እንደሚበልጥ እንጂ የአዕምሮ ሀይል ከአካል ሀይል እነደሚበልጥ አልሰበከልንም እና እኔ የመጣልኝ ነገር አዕምሮ የሁሉም የበላይ መሆኑ ነው " ነበር ያለው እኔም ልጁ የተናገረውን ነገር ሳብሰለስለው አፈርኩ ምክንያቱም ወላጆቻችንስ አነደዚህ ቢያስቡ ብዙ አልተማሩም ማለት አያውቁም ማለት ሳይሆን ብዙ አልተመራመሩም ወይም አላነበቡም ነገር ግን ወላጆቻችን ሳይማሩ ያስተማሩን እኛ አካል አይተን በጭፍን የምነበይነው ነገር ትዝ አለኝ ጤነኛ ነን የምንለው እኛ ላይ ያለው በ አይን የማይታየው የ አካል ጉዳታችን ገዝፎ ታየኝ መቶ በመቶ ጤነኛ መቶ በመቶ ጉዳተኛ ወይም በሽተኛ የሚባል ነገር እንደሌለም አስተዋልኩኝ ምክንያቱም አሁን ከ እኛ ጋር ከጎናችን ሲስቅ ሲጫውት የነበረ ጤነኛ ሰው በ እግሩ መቆም አቅቶት ተዝለፍልፎ ሲወድቅ ወይም ሌላ ነገር ሲሆን እያየን ነው በእኛም ላይ እየደረሰ ነው የሚገርመው ብሩክም እሰከ ሰባት አመቱ ድረስ ሙሉ ጤነኛ ነበር ::ችግሩ እኛ ያጣነው ማስተዋሉን ነውና አርስበርስ ተደጋግፈን እንኖር ዘንድ እግዚአብሄር ልቦናችንን ይክፈትልን::

  ReplyDelete
 7. Hi danie
  it is great work, keep it up
  people have their spacial gift
  the difference is to act by their skill and knowledge,it is not our perception on disable that govern but the act of their perception on their body,it is not the human body went first to space but its mind.

  ReplyDelete
 8. ውድ ዳኒ ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ የሚል ብሂል ወደ አእምሮዬ መጣ

  ReplyDelete
 9. If we live long enough, every one of us will experience some form of disability in our own life times.We shouldn't make disability something very remote.As the above article articulates it's a human condition.A given society's moral standard and civility can be judged based on how it treats its less fortunate among its members like the elderly,the disabled,the poor etc.In different countries across the world its the law of the land to make sure that the disabled are accomodated and given priorities in the public transportation, acess to buildings, parks,recrational facilities and educational institutions to list the few.It's a very good start that the new building codes in Ethiopia include acess to the disabled.I hope we can see this extended to other services.
  Selam!
  Mulugeta Mulatu
  Vancouver Island

  ReplyDelete
 10. Thanks Danny,Ya realty ,we have to think about them,care and understand their feelings,needs.."it could be me-it all about mine",,,that was u said --yes,caring as if it was caring for your self will pay the debt.we didn't know..but,Let help them as possible as we can! despite,this i have one message..for handicapped peoples,"Belive in Your Self! you can do this!"....

  ReplyDelete
 11. ለአካል ጉዳተኛ ወገኖቻችን ማዘን አለብን፡፡ እንዲያውም በኢኮኖሚ የሚቋቋሙበት የተለያዩ ዘዴዎችን መፈለግ አለብን ቤዬ አስባለሁ እግዚአብሄር ልቦና ይስጠን እስቲ-----

  ReplyDelete
 12. thank you daniel for taking this issue to the world.my father is a disabled person with a lot of success he helps a lot of people with no disability what i mean is being phisically disabled is not a problem at all the problem is to think that it is aproblem.if some one believe that he/she can do what ever they want they can do it with the help of God.b/c he has always a purpose to creat us & he doesn't want us to falldown.

  ReplyDelete