Friday, October 28, 2011

ኢትዮጵያ፡- ነጠላ እና ጋቢ


 click here for pdf
 ከሁለት ዓመታት በፊት ለአንድ ጉዳይ አኩስም ሄጄ ነበር፡፡ አንድ የሰባ ሁለት ዓመት ሽማግሌ አገኘሁ፡፡ እናም ስለ አኩስም እና አኩስማውያን እናወራ ጀመር፡፡
«አኩስም ማለትኮ ትንሿ ኢትዮጵያ ናት፡፡ እዚህ ያልኖረ፣ ያልሠራ፣ ያልተቀበረ የሰው ዓይነት የለም፡፡ እስኪ የአኩስም ነገሥታትን ስም ተመልከት የትግሬ ይሁን የአማራ፣ የኦሮሞ ይሁን የአገው በምን ታውቃለህ? እዚህኮ አይደለም ኢትዮጵያዊ ግሪኩ፣ አርመኑ፣ ጣልያኑ፣ ዓረቡ፣ አይሁዱ፣ ግብጹ፣ ሕንዱ፣ ምን ያልኖረና ያልተቀበረ አለ? አኩስም የሁላችሁ ናት፡፡ አኩስም በመወለድ አይደለም በመሆን ነው» አሉኝ፡፡ ገርሞኝ ነበር የማዳምጣቸው፡፡

በተለይ ደግሞ «አኩስም በመወለድ ሳይሆን በመሆን ነው» ያሉት ነገር ለእኔ ትልቅ ፍልስፍና ሆነብኝ፡፡ እንዴት? አልኳቸው፡፡ «አኩስማዊ የምትሆነው አኩስም ስለተወለድክ አይደለም፡፡ አኩስም ተወልደው እንደ ዮዲት ጉዲት አኩስምን ያጠፉ ሞልተዋል፡፡ እነዚህ አኩስማውያን አይደሉም፡፡ አኩስማውያን ማለት በአኩስም ሥልጣኔ የሚሄዱ፣ ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ፣ ለታሪክ እና ሃይማኖት ክብር የሞቱ ናቸው፡፡ የትም ተወለድ፤ ይህንን ካደረግክ አንተ አኩስማዊ ነህ፡፡
«እኛ አኩስሞች ዘረኛነት አናውቅም፡፡ (እንዲህ ሲሉኝ እጃቸውን ወደዚያ እያወራጩ ነው፡፡) እዚህ ዋናው ሥራህ ነው ትውልድህ አይደለም፡፡ እስኪ እነዚህን የአኩስም ቤተ ክርስቲያኖች ተመልከት፡፡ (ጣታቸውን ወደ አሮጌው እና አዲሱ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አመለከቱኝ) ያንን የጥንቱን ያነፀው ፋሲል ነው፡፡ ከየት እንደመጣ ታውቃለህ? ከጎንደር ነው፡፡ ይህንን ያነፀው ተፈሪ ነው፡፡ እርሱም ከሸዋ ነው የመጣው፡፡ ለኛ ግን እነዚህ ሁሉ አኩስማውያን ናቸው፡፡
ታቦቷ ያለቺበትን መቅደስ ማነው ያነፀው? መነን ናት እርሷም ከሸዋ መጥታ ነው፡፡ በዮዲት የመከራ ጊዜ ሸዋ፣ በግራኝ ወረራ ዘመን ኤርትራ ሄዳ ነው ታቦቷ የቆየቺው፡፡ አሁን ይህንን ሐውልት ማን እንደሠራው በምን ታውቃለህ? ትግሬ ነው? አማራ ነው? ኦሮሞ ነው? አገው ነው? ወላይታ ነው? ሶማሌ ነው? ለመሆኑ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ዘሩ ምን ነበር? አማራ ነው? ኦሮሞ ነው? ትግሬ ነው? ምንድን ነው? ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
ስንቶቹ የጎንደር እና የሸዋ ነገሥታትኮ ሥልጣን እጅ ካደረጉ በኋላ እዚህ አኩስም መጥተው ነበር ዘውድ የሚጭኑት፡፡ በዚያኛው በር በኩል አላየኸውም? (በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር በኩል ነገሥታቱ ሲመጡ የሚቆሙበት፣ የሚቀመጡበት እና በትረ ሥልጣን የሚጨብጡበትን ትውፊታዊ ቦታ ማለታቸው ነው) እዚያ ሳይደርስ ማን ይነግሥ ነበር? ለምን ይመስልሃል? ሁሉም አኩስማውያን ናቸዋ፡፡ አኩስማዊነት ማለትኮ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ሌላ ነገር የለውም፡፡ እናንተ ባለፈው ጋቢ አልሰጧችሁም? (የአኩስም የቅዱስ ያሬድን ትምህርት ቤት ለማሳደስ በተቋቋመው ኮሚቴ ለሠሩ አባላት እናንተ አኩስማውያን ናቸሁ፣ ታሪክ ጠብቃችኋልና ብሎ ሕዝቡ ባህላዊ ጋቢ ሸልሞን ነበር) አየህ አሁን አንተ እዚህ አልተወለድክም፤ አላደግክም፤ አልኖርክም፤ ቋንቋ አታውቅም፤ ግን አኩስማዊ ነህ፡፡ የያሬድ ታሪክ እንዳይጠፋ ብላችሁ አይደለም የሠራችሁት፤ ታሪክ ጠባቂ ከሆንክ አኩስማዊ ነህ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ጋቢ የሰጠናችሁ፡፡ እዚሁ ተወልዶ ደግሞ አኩስማዊ ያልሆነ ብዙ አለ፡፡ መወለድ ምን ቁም ነገር አለው፡፡
«አባ ጉራጌን ታውቃቸዋለህ? ከዐፄ ዮሐንስ ሠራዊት ጋር አብረው እየዘመቱ ወታደሩን በርታ ጠንክር እያሉ ለሀገሩ እንዲዋጋ ያደፋፈሩት አባ ጉራጌ እዚህ አኩስምኮ ነው የኖሩት፡፡ በጉራዕ እና በጉንዳጉንዲ ጦርነት ንጉሡን ተከትለው ስንት ውለታ ሠርተዋል መሰለህ፤ አኩስማዊ እኮ ናቸው፡፡ ትውልዳቸው ጉራጌ በመሆኑ ግን ሕዝቡ አባ ጉራጌ ይላቸዋል፡፡
ይህ የአረጋዊው ትምህርት ትዝ ያለኝ አንዳንድ መጽሐፎቻችን እና ጽሑፎቻችን አኩስምን ከአካባቢ፣ ከቋንቋ እና ከአንድ ወገን ጋር ማያያዝ እንደ ጀመሩ ሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መገለጫዎች የሆኑ ምእራፎች እና ቦታዎች አሉ፡፡ አኩስም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ሐረር፣ አዲስ አበባ፣ ሌሎችም፡፡ እነዚህ ቦታዎች እና ሥልጣኔዎች በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን የቱን ቦታ እና ሥልጣኔ ማዕከል አድርገው እንደነበሩ የሚያሳዩ እንጂ ዛሬ በአካባቢው ያሉትን ሕዝቦች ታሪክ እና ሥልጣኔ ብቻ የሚያሳዩ አይደሉም፡፡
አኩስምን ከትግራይ፣ ላሊበላን ከአገው፣ ጎንደርን ከአምሐራ፣ ሐረርን ከሐረሪ፣ አዲስ አበባን ከኦሮሞ እና አምሐራ ጋር ብቻ እያያያዝን የምናያቸው ከሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ እና ጉዞ ውስጥ ይቅር የማይባል ስሕተት እንሠራለን፡፡
ለመሆኑ ጎንደር ላይ ስንቱ አልፏል? እነ ራስ ሚካኤል ስሑል ጎንደር ተወልደው ጎንደር ነበር እንዴ ያደጉት? ከትግራይ የመጡ መሳፍንት አልነበሩምን? ደረስጌን ያሳመሯት ራስ ውቤ የትግራይ ሰው አልነበሩምን? እነ ራስ ጉግሳ እነ ራስ ዓሊ፣ ኦሮሞዎች አልነበሩም?
ጎንደር የሀገሪቱ የትምህርት፣ የአስተዳደር እና የሥልጣኔ ማዕከል በመሆንዋ ወደ እርሷ የማይጎርፍ አልነበረም፡፡ እንኳንና ኢትዮጰያውያኑ ቀርተው የውጮቹ ሰዎችም እዚያው ኖረው እዚያው ተጋብተው እዚያው ቀርተዋል፡፡ የእንግሊዛዊው የፕላውዴን መቃብርኮ ጎንደር ግምጃ ቤት ማርያም ነው ያለው፡፡ ጎንደሬው፡፡
ጎንደር መላው ኢትዮጵያ አንድ ሆኖ ላቡን እና ደሙን አዋጥቶ የሠራት የሥልጣኔ ማዕከል ናት፡፡ በግራኝ ወረራ ጎንደር እና አካባቢዋ ከጠፋ በኋላ በዐፄ ሠርፀ ድንግል ጊዜ እንደገና ስታንሠራ ጎንደር ሊቃውንትን ያስመጣቺው ከጉራጌ ነበርኮ፡፡ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ላይ ጋይንት ወረዳ በደራ ቀፎዬ ገበሬ ማኅበር የምትገኘው የደብረ ማርያም ገዳም ታሪክ እንደሚገልጠው አባ መሰንቆ ድንግል፣ አባ ለባዌ፣ አባ ብእሴ ሰላም እና መምህር ተክለ ወልድ የተባሉ ሊቃውንትን ከጉራጌ ምሁር ኢየሱስ አምጥተው በጎንደር አድባራት መደቧቸው፡፡
ጎንደርን የትምህርት ማዕከል ያደረጓት እነዚህ አራት የጉራጌ ሊቃውንት ናቸው፡፡ የእነርሱ ደቀ መጻሙርት ነበሩ በመላዋ ጎንደር እና በመላዋ ኢትዮጵያ ተሠማርተው ሀገራዊውን ዕውቀት ከሞተበት ያሥነሡት፡፡ አሁን ጉራጌን ጎንደር ላይ ማን ያስበዋል?
የይምርሃነ ክርስቶስን እና የደብረ ብርሃን ሥላሴን አሠራር ያየ ወሎዬ እና ጎንደሬ አንድ ላይ ሆነው የሠሩት እንደሆነ ይመሰክራል፡፡ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ታቦት እና ስም ከሸዋው ደብረ ብርሃን ሥላሴ ሲወሰድኮ ታላቁ ኢያሱ ሁለት መክሊት ወርቅ ለደብረ ብርሃን ሥላሴ ከፍለው ነው፡፡
ጎንደርን ጎንደር ካሰኟት ሊቃውንት አንዱ የሆነው የቅኔው ባላባት ክፍለ ዮሐንስኮ የአገዎች ምድር ከነበረቺው ከመተከሏ ጋፍኒ ልደታ የተገኘ «ጎንደሬ» ነው፡፡ የአባቱም ስም ቹሐይ ነው፡፡ ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ ከብቃቱ የተነሣ የሥላሴን በዓል በጎንደሩ እና በሸዋው ደብረ ብርሃን ሥላሴ እየተገኘ በአንድ ቀን ያከብር ነበር ይባላል፡፡ ለዚህም ነው
እነሂ ወግብረ ቅኔ ዘበሆሳዕና
እም ዕደ ገፋዒ ወተገፋዒ ንትመሰጥ በደመና
ያለው እያሉ ሊቃውንቱ ይተርኩለታል፡፡
እንኳን እና ሰው የጎንደር ታቦታት እንኳን ከመላዋ ኢትዮጵያ ተሰብስበው ጎንደር የከተሙ ናቸው፡፡ የጎንደሩ አደባባይ ኢየሱስ በዐፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን ወደ ጎንደር ተሻግሮ የተተከለ የወላይታ ታቦት ነው፡፡ የአዞዞ ተክለ ሃይማኖት ታቦታት ከሸዋ ደብረ ሊባኖስ የሄዱ ናቸው፡፡ ኤርትራዊው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ አርመን ተጉዘው ካረፉ በኋላ ዐፅማቸው መጥቶ ያረፈው ጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ነው፡፡   
በጎንደር አድባራት እየዞርን የሊቃውንቱን እና የመምህራኑን ስም እና የዘር ሐረግ ብናጠና በከተማዋ እና በአካባቢዋ ተወልደው ካደጉት ይልቅ ከጎጃም፣ ከሸዋ፣ ከትግራይ፣ ከወሎ፣ ከሐረር፣ ከኤርትራ፣ ለትምህርት መጥተው እዚያው ለምደው እዚያው የቀሩት ይበልጣሉ፡፡ ሀገሬው ትምህርታቸውን እና ደግነታቸውን ተመልክቶ ልጁን ድሮ በዚያው ርስት እያሰጠ ያስቀራቸዋል፡፡ ጎንደር ላይ አገልግለው ጎንደሬ ይባላሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ የሀገሪቱ ልጆች ጎንደር ላይ ሲያንጹ፣ ጎንደር ላይ ሲጽፉ፣ ጎንደር ላይ ሲቀኙ፣ ጎንደር ላይ ሲያዜሙ፣ ጎንደር ላይ ሲነግሡ፣ ጎንደር ላይ ሲሾሙ ለሀገራቸው እና ለወገናቸው አንዳች ነገር ስለማድረግ ያስቡ ነበር እንጂ ለጎንደር ወይንም ለአማራ ብለው የሠሩት አልነበረም፡፡
ሸዋ እንውረድ እስኪ፤ አዲስ አበባ የማናት? የአዲስ አበባ ሥልጣኔስ የማነው? አዲስ አበባ ላይ ወዝ እና ደሙ ያልፈሰሰ ኢትዮጵያዊስ አለ? የአዲስ አበባውን የእንጦጦ ራጉኤል ንድፍ ያወጡት «ዘጠኙ ጎንደሬዎች» የሚባሉት ከጎንደር የመጡት አርክቴክቶች አልነበሩም እንዴ? የድንጋይ ባለሞያዎቹ አንኮበሬዎች ሲሆኑ እነ አፔንዚለር እና አልፍሬግ ኢልግ የተባሉት ስዊድናውያን እነፃውን አብረው ሠርተዋል፡፡
እነ ሐጂ ቀዋስን የመሰሉ ሕንዳውያን ደግሞ በዋና አርክቴክትነት ከጎንደሬዎቹ ጋር ሠርተዋል፡፡ እንጨቱ ከመናገሻ፣ ቆርቆሮው ከፈረንሳይ፣ የጣርያው ርብራብ ከካይሮ መጣ፡፡ ታቦቱስ ቢሆን የጎንደር ታቦት አይደለም እንዴ? ሰዓሊዎቹ አለቃ ዮሐንስ ዘጎንደር ማኅደረ ማርያም፣ አለቃ ሉቃስ ዘጎጃም፣ አለቃ ሣህሉ ዘጎጃም ነበሩ፡፡ እስኪ እንዴት ሀገር አንድ ሆኖ እንደተባበረ ተመልከቱ፡፡
 ታላቁ ካቴድራል ቅድስት ሥላሴ ታቦቱ የመጣው በግራኝ ጊዜ ከፈረሰው ከወሎው መካነ ሥላሴ ነው፡፡ ከዚያ ተወስዶ ወግዳ ኖረ፣ ከወግዳ ራስ ጎበና አምጥተው ሸዋ አዲስ ዓለም ፍየታ አኖሩት፡፡ ምኒሊክ ደግሞ አዲስ አበባ አራት ኪሎ አመጡት፡፡
አዲስ አበቤ ማለት ምን ማለት ነው? አዲስ አበባ የኖረ ማለት እንጂ የተወለደ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባን አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች፣ መንገዶች፣ አብያተ መንግሥት፣ ሕንፃዎች፣ /ቤቶች የሠሩት የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ ያንን ሲሠሩ ለሀገራቸው አንዳች ነገር እንደሠሩ ያስቡ ነበር እንጂ ለሸዋ ወይንም ለኦሮሞ ሲሉ አልሠሩትም፡፡
 ዛሬ የሐረሩ ቁልቢ ገብርኤል ታቦት የጥንቱ ከአኩስም ትግራይ የዛሬው ከሸዋ ቡልጋ የመጣ ነው ቢባል ማን የሐረር ሰው ያምናል? ልክ ደቡብ ሸዋን እና ወለጋን የሰበኩት አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ከሐረር ነው የመጡት ቢባል ወለጌ እና ሸዬ እንደማያምነው ማለት ነው፡፡ የመጀመርያው የቁልቢ ታቦት መነሻውን አኩስም አድርጎ ከታቦተ ጽዮን ጋር ዝዋይ መጣ፡፡ ታቦተ ጽዮን ስትመለስ እርሱ ዝዋይ ቀረ፡፡ አባ ሌዊ አምጥተው ቁልቢ ዋሻ ውስጥ አስቀመጡት፡፡
ሌላም የሚገርም ይህቺ ሀገር እንደ ዘሐ ዘጊ የተያያዘች መሆንዋን የሚያሳይ ታሪክ ልጨምር፡፡ በግራኝ አሕመድ ወረራ ዘመን መልአከ ገነት መብረቁ፣ መምህር የማነ አብ፣ አባ ተከሥተ ሥሉስ የተባሉ አበው ወደ ቁልቢ ይሄዳሉ፡፡ በዚያም በድንጋይ ላይ አባ ሌዊ የጻፉትን የቁልቢ ታሪክ ያገኛሉ፡፡ ከቁልቢ ሲመለሱ ያንን በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ ኅዳግ ላይ ገልብጠው በደሴተ ዝዋይ አስቀመጡት፡፡ ራስ መኮንን ከዝዋይ ደሴት መጽሐፈ ቀሌምንጦስን አስመጥተው ሲያነቡ ታሪኩን አገኙ፡፡
በቦታው ላይ ሌላ የገብርኤል ታቦት ለማስገባት ፈልገው ሲያፈላልጉ ቡልጋ ላይ ያገኙታል፡፡ እነሆ ዛሬ የሐረርጌ አንዱ መታወቂያ ሆነ፡፡
ኢትዮጵያን ዛሬ ዘመናችን ባመጣብን ጎጠኛ አስተሳሰብ ማየት የለብንም፡፡ ኢትዮጰያ ከዚህም የሰፋች የተለየቺም ናት፡፡ ሰሎሞን ደሬሳ «በጥንት ሴት አያቶቼ በር ማን እንዳለፈ አላውቅም» እንዳለው ከዚህኛው ዘር ብቻ እወለዳለሁ ብሎ መናገር የዋሕነት ሳይሆን አላዋቂነት ነው፡፡ ይህኛው ወይንም ያኛው ሥልጣኔ እና ታሪክ፣ ገድል እና ተአምር የዚህ ወገን ብቻ ነው ብሎ መጻፍም ኢትዮጵያን አለመረዳት ነው፡፡
ኢትዮጵያኮ እነ አቡነ አረጋዊ ከአውሮፓ፣ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከግብጽ፣ እነ እጨጌ ዕንባቆም ከየመን መጥተው ኢትዮጵያዊ የሆኑባት ሀገር ናት፡፡ እንዴት ነው አንድን አካባቢ ዛሬ በቦታው ለሚኖረው ሕዝብ ብቻ መስጠት የምንችለው? ተዋግተንም፣ ተፋቅረንም፣ ተጣልተንም፣ ተዋልደንም፣ ተጋፍተንም፣ ተሳስበንም አሁን ያለውን መልክ ይዘናል፡፡ ዛሬ ያለው መልክዐ ምድር ጦርነት የፈጠረው መልክዐ ምድራችን ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ጦርነት እና የሃይማኖት ንቅናቄ አንድ ያደረጋት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አንዳችን ማግ ሌላችን ዝሐ ሆነን አሁንማ ነጠላ እና ጋቢ ሆነናል፡፡

74 comments:

 1. tiru tariki new beatekalayi zeregninet yibika new.

  ReplyDelete
 2. ቃለሕይወት ያሰማልን፡፡ ለሁላችንም ልቦና ይስጠን!

  ReplyDelete
 3. ሰው ዛሬ በጎጠኝነት አእምሮው ስለታወረ ብቻ ይህ የኔ ብቻ ነው ያ ደግሞ የሌላ ነው በማለት እውነትን ለመካድ የሚደረግ ጥረት ከማሳዘንም አልፎ እጅጉን ያንገበግባል፡፡ ለመሆኑ ግን ከ3000 ዓመት በፊት የነበሩት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ከ እኛ ምን ያህል በአስተሳስብ ይበልጡ እንደነበር አስተውለናል? ያስተዋልን አይመስለኝም፡፡

  AA FROM Addis Ababa

  ReplyDelete
 4. እጅግ ወቅታዊ ጽሑፍ ፡፡ አንባቢ ካለመሆኔ የተነሳ አጠገቤ ያለውን ይህንን ታሪክ አጉልቼ ኢትዮያውያን አንድ እንደሆንን መግለጽ ስችል ላም አለኝ በሰማይ አንድ የምንሆነው በዴርቶጋዳ የተጻፈው ሐዲድ ሲሰራ ነው የሚል ሀሳብ ነበረኝ፡፡ይ ህ አንተ ዛሬ የለቀቅከው ጽሑፍ በጣም ከባልንጀሮቼ ጋር ልወያይበትና በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ መናገር እንዳለብን አምናለሁ፡፡ ግን የአክሱሙ ሰው የተናገሩትን የአገሬው ሰው ይቀበለዋል ወይንስ በዘመኑ ጎርፍ ተወስዷል?

  ReplyDelete
 5. Dear Daniel,

  I had red the book you referred. I was shocked while I red it. Your analysis on this article heals me. Kale Hiwot Yasemalin. Your analysis and historical view is too wonderful. Stay blessed.

  ReplyDelete
 6. we all are Ethiopians. The more we come to unity, the more powerful nation in the region we become. God Bless Ethiopia! Amen!

  ReplyDelete
 7. ደስ የሚል መልክት ነው:: ሁሉ ሰው እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሊል ይገባል:: የዘር መቁጠር በሽታ ሊቀር ይገባል:: ዳንኤል በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ላስታውስህ ከብዙ አመት በአንዱ እኛ ሰንበት ት/ቤት መጣህ:: ምክንያቱ ዘማሪያኑና የመዝሙር ኮሚቴው በመጋጨታቸው ለሁለቱም አካል ትምህርት በመስጠት አገልግሎቱን ቀና ለማድረግ ነበር:: ከዚያ ደስ የሚል ትምህርት ሰጠህ:: ሁለቱንም አካል በመውቀስ:: ያን ጊዜ ደስ የሚል መልክት ነበር:: ግን ስንወጣ መዝሙር ኮሚቴዎቹ ለመዘምራኑ ነገረልን ልክ ልካቸውን አሉ:: መዘምራኑ ደሞ ለመዝሙር ኮሚቴዎቹ ነገረልን ልክ ልካቸውን አልን:: ስለዚህ ሁለታችንም ሳንማር ቀረን:: አሁንም እንዲህ አይነትን መልክት ለእኔ ብለን መስማታ ካልቻልን ሜዳ ላይ ይቀራል ለማለት ነው::
  አክባሪህ

  ReplyDelete
 8. AY DAN ahun ahun ema keftagna tmhrt tekumat eko kewanaw tmhrt belay zeregvnet aby guday adrgew yzewta .aau 6kilo leyebharu mahiber mesrto eyasfafa newko menendasebem enja....

  ReplyDelete
 9. this is a good saying but way Aba Paulos does not understand it..............????????

  ReplyDelete
 10. መሰረት ነኝ (ከአፋር ጭፍራ)
  እግዚአብሄር ይባርክህ ዳኒ. ህሊና ያለዉ ሰዉ ይህን ያስተዉል፡፡

  ReplyDelete
 11. thank you for your observation.

  ReplyDelete
 12. Betam des yemil Tsihuf des yemil Tarik new, God bless you!Ethiopiachin kedar eskedar yehulachin nech hulachin ye Ethiopiachin nen, Selam ena Fikir amilak yisten

  ReplyDelete
 13. አኩስም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ሐረር፣ አዲስ አበባ፣ ሌሎችም፡፡ እነዚህ ቦታዎች እና ሥልጣኔዎች በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን የቱን ቦታ እና ሥልጣኔ ማዕከል አድርገው እንደነበሩ የሚያሳዩ እንጂ ዛሬ በአካባቢው ያሉትን ሕዝቦች ታሪክ እና ሥልጣኔ ብቻ የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ TRUE!

  ReplyDelete
 14. KALEHIWOT YASEMALIN

  ReplyDelete
 15. WOW... VERY nice article. It teachs a lot.. Lib Yalew Lib Yibelllllll

  ReplyDelete
 16. Dani it is so interesting!!!
  Dani can you write some thing about Sadam Hussien and Gadaffi,like << yehuletu hawltoch wog>> <>. Because Sadam and Gadaffi have the same story from the begning tothe end.pleasesssssssssss!
  God bless you!!

  ReplyDelete
 17. Thanks and God bless u Dan! I wish if you write it in parts like 1,2,3--- since you can share us a lot with this vast topic. We,the generation thiristy of our country's history, need to know more as it is a base for out political and historical integrity. God bless the eye of the 'eagle'-Dan!!

  ReplyDelete
 18. Dani betam yigermal hulum neger egeziabeher yitebekih

  ReplyDelete
 19. man yisemahal Dani. Merz gebtobinal be hilinachin. Esti kechalk be metsaf melik asatim endih ayinetochin tarokoch asebasibeh. Le mafres letenesut sayihon be Ethiopiawinet leminaminina leminasb yihonenal. Ahun ahun le lijochachin mechenek jemireyialehu. Egnas ande leyitolinal. Egzerum eresan meselegn.

  ReplyDelete
 20. Thanks Dani
  your express my feeling in Linguistic quality.
  God bless.
  leb yalew leb yebel

  ReplyDelete
 21. "ye Aksum hawlt lewelaytaw minu new?!" PM Meles,

  I wish he would read this.

  ReplyDelete
 22. ኢትዮጵያን ዛሬ ዘመናችን ባመጣብን ጎጠኛ አስተሳሰብ ማየት የለብንም፡፡ ኢትዮጰያ ከዚህም የሰፋች የተለየቺም ናት፡፡
  SOFONIYAS.

  ReplyDelete
 23. What an incredible article. Thanks Dani. i wish prime minister Melese and Abune Paulos read this.
  be blessed.

  ReplyDelete
 24. ቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡

  እንዲህ የሚያንጹ ጽሑፎችህ ምን ያህል ያረሰርሳሉ፡፡

  ዳኒ እባክህን ፖለቲካ ነክ ነገር ስጦታህ አይመስለኝም ፡፡ በእውቀት ታስተላልፈዋለህ ግን እኔንጃ በግድ ዋጡት አይነት መልእክቶች ናቸው፡፡ የአገርን የትውልድን ታሪክ ፣የታላላቅ ሰዎችንና የታሪካዊ ቦታዎችን ዝርዝር ሁኔታ ስትጽፍ እንኳን ሃይማኖት ያለው አሕዛቡም ይደመማል፡፡

  ለማንኛውም ከመጻፍህ በፊት ጸልይበት፡፡

  ከእውቀትህ ጋር ብቻ ሳይሆን ከነፍስህም ጋር ተነጋገር፡፡

  አድናቂህም አክባሪህም፡፡

  ReplyDelete
 25. u ....... remined me some extra few things which i was able to know Tx Dn.Daniel...my friend who is muslim n owner of small company let me to lesson what z popular 'young' muslim preacher Sadik talked on phone with z Tewahido young preacher Tesfaye!!! my friend was a bit nervous n changed at least from his former good ethiopian muslim nature similarly to other few changed youth agressive protestant friends nature who believe what zy r saing is only true n our right as human is to lesson them as we don't have z right at least to reflect our opinion....!!!from both my muslim n protestan friends what i understand is if among them or zy have got a chance to be a ruler zy will destroy or revange on z orthodox history, asset & belivers not only to me but to their families... even don't hesitate to zr sister n brother... i am sure if not corrected as some leaders or 'power full' persons r trying zr best.....(((sory i will continue z second.

  ReplyDelete
 26. Inehoo yihen ketiwlidu man astewale?

  ReplyDelete
 27. (((z second part...
  as it is said Ewer Ewerin bimeraw... most youthes in most religion r driven wrongly to other extriem like an item by z 'preacher' whom zy admire...!!! we z orthodox belivers especially youthes may not understand our potential n doing z right thing today as our fair gentle parents...if we go back almost every thing is written as a model for our way of life in any century as u Daniel brought many examples n said then to correct our selfs yes our selfs n our mistakinly wronged muslim n protestant friends n families we will use it...i have seen in aau 6 yrs back z raciest n worest religious grouping which simply which seems correct to confirm z saing man is social animal...we have plenty of facts to learn from if we will from former generation but we have to be strong...all our grand parents first were mistakin. yes u or any one can begin from Eve or Adam....then many n zr king ...Jesus came.. n our parents accepted being among z first going there while zy here z news...zn mohamed came...then his famillies came with their teaching to our parents land n our commen parents give them place, time n power some of our parents changed to z new religion that was came...so as every thing even today is enough zy lived in peace with no force to chrisianize but z saudi nature of islam was not applied or rejected not from Quran but from day to day life here as Jerusalem nature of christianity was not applied too here before islam...THIS MEANS OUR PARENTS WERE CORRECT. Ethiopic type of respect for Islam n for Christian were present....Gragne mohamed destroyed n make islam most by force...but zr was no revange even by Aste Yohanes whom most of my muslim friends hate!!!HERE ALSO OUR COMMEN ETHIOPIAN PARENTS WERE CORRECT TOO!!!...
  (((see z last next sory people for stoping

  ReplyDelete
 28. the last part
  Ethiopia n Ethiopians formerly were correct for JUDAISM,ORTHODOXY ND CHRISTIANITY and even for z poletics but then also... protestant teaching came n our brothers changed n for example zy took z name MEKANE EYESUS from z 400 yr old GONDER MEKANE EYESUS church & used for z last 40/50 yrs with almost 'cheating' unlike z Debrebrhan church very wonderful history that u Daniel mantioned... and zy r trying to take many of ours even z catholics with WUSTE Z methods...we r patient like our commen correct parents we r still good tewahido belivers though we r not like our LIBE SEFE NEGER ALAFI YEMICHELUTEN TESATAFI parents... look z modern education system, z last '40' yrs poletics, unfair businesses n distribution of welth including becoming of diaspora in US & Arab world commenly...is a challenge for us especially for z orthodox but we r z one who r almost correct than our mulim n protestant friends n brothers...being honest especially we z youthes for z confused poletics, concept of BEHERE or race, education process,business,jobs ....if we r wrong not z Bible or Quran first.Yes Yeneta z famous Bible scholar said we do not axcept z bible b/c we understand it!!! Never we may understand few topics as I do he said... so wow we have to refer how our grand parents were living together...z gentle smart our commen ones use z books effectivly not only in z eyes of God but also befor z very respected our their childrens eye even...like yesterday z world is not narrow, z time is not short, ...if we want to live our Ethiopia is enough even today but respect urself then u can respect m then...let me finish by reminding what profesor Efrem Yshak answered 7/8 monthes befor z 97 confusion ...my mother was born in oromia n knows how to speak only of it. i came to addis for education n speak amharic...so based on z 'dirty' BHERE POLETICS WHO AM I WHILE MY GRANDPARENTS FROM gOJJAM...Tigry? do u think that he is born today to be amhara, oromo, Gojam, tigre...
  our generation must do our own homwork without destroying such beuty constructive works of our common former parents work wheather we r or wish to be Orthodox, Islam, protestant....RESPECT WHAT U HAVE TO RESPECT, BE JENTLE AS U R TALKING, CORRECT Z WRONG THINKING,ACTION,LIFE OF UR SELF & learn z truthe including what u don't have but that our parents had......uuuuuuuuuuu i said too much....Dn.Daniel Tx God of z fathers be with u!!!

  ReplyDelete
 29. Dn. Dani,

  Majority of we fill the same. The minority too taken since they didn't internalize what they did. Some individuals take the seat & drive all of us. please there too many others who knows many history relate with it/even more pain full like 'Sekoka wemehabuba'. let us write & forward it to dani he can post it and complement. All of us have the same responsibility & we have to share z pain...AHhhh..Ehhhh

  ReplyDelete
 30. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 31. ጎጠኛ አስተሳሰብንና አሰራርን ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል፡፡
  ከተማሪዎቸህ፡፡

  ReplyDelete
 32. Dn.Daniel let the Almighty God bless you. It is really a timely article which has to be published in different communication medias. We are really going backward/negative progress/. Plz guys let we Ethiopians start to think for those by our side,but also for other Africans,...human being. It is really a shame to fight with our brothers. We all, Amhara,orormo, gurage...may have different language and culture but we all want peace and growth. Please let we focus on those we want them to achieve.

  Dn.Daniel Aksum is more than even what you mentioned on your article,it is a place where one of the world,miracle, precious thing exist...'TABOTE TSION'/The Arc of The Covenant/.Do you know how aggressively others try to get 'tabote tsionen?. But God has given for Ethiopians,cuz of his 'cherinet' not our work.

  Finally, plz let us all pray to unit us,to make us to think like normal human being. This days we are not 'normal'.Some times i doubt we might be getting punishment from the 'Tabote tsion' cuz we are not behaving as people having it,even not as people who knows abt that.

  God bless the world,God bless Ethiopia!!

  Thanks,
  Hailemariam
  Villa Park,Chicago

  ReplyDelete
 33. zares garamage eskei enesaley holachenem AXUMAYE enedenehone.yaanabarabegen zaragenate tawekote.gene astamerone balamawake nawe.dn dani meseganawe enedayeteleh zeme alkoo

  ReplyDelete
 34. ግን የአክሱሙ ሰው የተናገሩትን የአገሬው ሰው ይቀበለዋል ወይንስ በዘመኑ ጎርፍ ተወስዷል?

  this is a good saying but way Aba Paulos does not understand it..............????????

  አኩስም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ሐረር፣ አዲስ አበባ፣ ሌሎችም፡፡ እነዚህ ቦታዎች እና ሥልጣኔዎች በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን የቱን ቦታ እና ሥልጣኔ ማዕከል አድርገው እንደነበሩ የሚያሳዩ እንጂ ዛሬ በአካባቢው ያሉትን ሕዝቦች ታሪክ እና ሥልጣኔ ብቻ የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ TRUE!

  Thanks and God bless u Dan! I wish if you write it in parts like 1,2,3---

  i wish prime minister Melese and Abune Paulos read this.

  Inehoo yihen ketiwlidu man astewale?

  We are really going backward/negative progress/. Plz guys let we Ethiopians start to think for those by our side,but also for other Africans,...human being. It is really a shame to fight with our brothers. We all, Amhara,orormo, gurage...may have different language and culture but we all want peace and growth.

  thank you

  ReplyDelete
 35. Deakon Daniel Egziabhere yeagelgilot zemenihen Yibark! Kalehiwoten yasemalen! Amen
  Egziabhere Yehulachenenem Ayne Libona Yikfetlin.
  Bertalen

  ReplyDelete
 36. Dani u hv abrave mind God bless u! God protect our united Ethiopia, i wish all Ethiopians think like dani...

  ReplyDelete
 37. ohhhhhhhhhhhhh!rt dany!

  ReplyDelete
 38. በእውነት ዳንኤል እድሜ ይስጥህ! እግዚአብሔር ይመስገን ኢትዮጵያ ጥቂቶች እንደሚያስቡት አይደለችም እንዲህ እኝህ አባት እንደተረኩት እንጂ፡፡ ቃለህይወት ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete
 39. Dn. Daniel keteleyaye akitachaya eyayeh bititsif tiru new. It seems to me you have sided.....

  ReplyDelete
 40. “ኢትዮጵያኮ እነ አቡነ አረጋዊ ከአውሮፓ፣ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከግብጽ፣ እነ እጨጌ ዕንባቆም ከየመን መጥተው ኢትዮጵያዊ የሆኑባት ሀገር ናት፡፡ እንዴት ነው አንድን አካባቢ ዛሬ በቦታው ለሚኖረው ሕዝብ ብቻ መስጠት የምንችለው? ተዋግተንም፣ ተፋቅረንም፣ ተጣልተንም፣ ተዋልደንም፣ ተጋፍተንም፣ ተሳስበንም አሁን ያለውን መልክ ይዘናል፡፡ ዛሬ ያለው መልክዐ ምድር ጦርነት የፈጠረው መልክዐ ምድራችን ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ጦርነት እና የሃይማኖት ንቅናቄ አንድ ያደረጋት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አንዳችን ማግ ሌላችን ዝሐ ሆነን አሁንማ ነጠላ እና ጋቢ ሆነናል፡፡”


  እጅግ ውብ፣ የሚያስተምር፣ የማንነታችንን አሻራ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ፣ አሁን ያለንበትንም ሁኔታ ቆም ብለን እንድንመረምር የሚያስችል ድንቅ አቀራረብ ነው፡፡
  ዲ/ን ዳንኤል እግዚአብሔር ረዥም እድሜና ሙሉ ጤናን ይስጥልን፤ በሕይወት ይጠብቅልን፡፡ ታሪክ ነጋሪና አስተማሪ ያላሳጣን እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

  ReplyDelete
 41. ዳኒዬዬዬዬዬ ኑርልን ፣ ተባረክ

  ReplyDelete
 42. የታሪክ አወቃቀርህ ምንጊዜም ቢሆን የማደንቀው ነው፡፡አዲስ አበባው ነኝ እያልክ አስተያየት የምትሰጠው ሰው በይበልጥ ልቦናህን ከፍተህ ልትረዳዉ ይገባሀል ፅሁፉን፡፡ አሁን አንተ ከአዲስ አበባ ነኝ ጠበብ ስታደርገው ደግሞ ከቄራ ነኝ ይሄ ሁሉ ለምን አስፈለገ ፡፡አንዳንድ አስተያየት የምትሰጡትም ሰዎች ለመንቃት ጊዜ እየወሰደባችሁ ያለ ይመስለኛል፡፡

  ReplyDelete
 43. i read the preview of a book on Axumawinet from Fiteh gazeta. I was shocked. Is the writer crazy? Kezih belay endenetelala yemiadergun gen lemendenew.Dani Egzer yesteh hasaben asamero meglets tadelehal...esti enante Enkuwan sele andenet sebeku man yawkal yehe geze yalfena....a better day may come.

  ReplyDelete
 44. ዳኒዬዬዬዬዬ ኑርልን ፣ ተባረክ

  ReplyDelete
 45. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!

  ReplyDelete
 46. To my brother/sister who requested "Dani can you write some thing about Sadam Hussien and Gadaffi,like << yehuletu hawltoch wog>> <>. Because Sadam and Gadaffi have the same story from the begning tothe end.pleasesssssssssss!"
  Seriously???? why don't u ask him to write about your own "negestat"? what do u benefit from their story?

  ReplyDelete
 47. Natey Restey

  Selam Diaqon,

  Just for the record,Ras Wube Hailemariam is not from Tigrai but rather from Semein province of Gonder.As a powerful ruler of his time,his teritory was not limited to the west side of Tekezze but ruled Tigrai (then known as Tigre) including the highlands and parts of the lowlands of Mereb-Melash,what is now called Eritrea.He is the paternal uncle of Itege Taitu Betul as Ras Betul Hailemariam is his brother.His era was ended after the defeat in the hands of his rival Kassa of Quara.The magnificent and historical church,Deresge Mariam was built by him in his home land of Semein Janamora some 200 km from Gonder town in close range to Ras Dashen.It was here in Deresge that Kassa of Quara crowned as Emperor Tewodros of Ethiopia.

  ReplyDelete
 48. በጣም ትክክልና ደስ የሚል ጽሁፍ ነው። ኢትዮጵያ ሰፊ ናት። ሕዝቦቿም እንደዛው እንደተማሪ ጥሬ ከዚህም ከዚያም የተውጣጡ ናቸው። ለምሳሌ እኔ አባቴ ከመንዝ-አማራ፡ እናቴ ከሸዋ ኦሮሞ፡ አክስቴ ከጉራጌ፡ አጎቴ ከወላይታ ነን እኔ የተወለድኩት ደግሞ ትግሬ ውስጥ ነው እና ኦሮሞ ነኝ እንዳልል ብቻ አይደለሁም፡ አማራ ነኝ እንዳልል አሁንም አማራ ብቻ አይደለሁም፡ ትግሬ ነኝ እንዳልል ብቻም አይደለሁም፡ ጉራጌም ለብቻውን አይገልጠኝም፡ ወላይታም ለብቻው አይደለም። ግን እኔ የእነዚህ ሁሉ ቅይጥ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ይህንን ነው የማምነው። ኦሮሞ ሀገር ብኖርም ከጉራጌውም ከአማራውም ከወላይታውም ከኤርትራውም ከትግራዩም ከሌሎቹም የሚመዘዝ ዘር አለኝ እና የአንዱ ጉዳት የእኔም ጉዳት ነው። አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል እንዲሉ እኔም የአንዱ ጉዳት ጉዳቴ የአንዱ ጥቅም ጥቅሜ የአንዱ ሀሴት ሀሴቴ መሆኑን አውቃለሁ። ሁላችንም ብናስበው ደግሞ እንዲሁ ከዚህም ከዚያም የተውጣጣን እንጂ ከአንድ ነገድ ብቻ የተገኘን ባለመሆኑ የዘውገኝነትንና የጎጠኝነትን ጉዳይ ከኅሊናችን ሊናጠፋው (ልንደልተው) የሚገባን መርዝ ነው።

  ስለ አስተማሪ ጽሁፉ ምስጋናዬ ልክ የለውም።

  እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

  ReplyDelete
 49. ቢዘገይም ጥሩ ነው
  ቢያንስ ቢያንስ የዳንዔል እይታ ሊባል ይችላል::

  ReplyDelete
 50. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
  ለሁላችንም ልቦና ይስጠን!

  ReplyDelete
 51. መልካም ነው፡፡ ሁላችን እንዲህ ብናስብ ፍቅር በላያችን ቤቱን በሰራ እግዚአብሔርም በታረቀን ነበር፡፡ ግን ሕገመንግስቱ እንዲህ እንድናስብ ይፈቅድልን ይመስልሃል?

  ReplyDelete
 52. ዲያቆን እግዚአብሄር ዕውቀቱን ያብዛልህ።
  ረዥም ዕድሜ ከሙሉ ጤንነት ጋር ያድልህ።
  ለሁላችንም ዐይነ ልቦናችንን ያብራልን።
  በፍቅር በአንድነት እንድንኖር የበቃን
  እንሆን ዘንድ ፈጣሪያችን ይርዳን።
  አሜን።

  ReplyDelete
 53. ዳኒ ቃለ ህይወት ያሰማልን
  እግዚያብሄር ስለ ኢትዮጵያ እንድናስብ ይርዳን

  ReplyDelete
 54. ወንድም ዳንኤል እንዴት አይነት ድንቅ ነገር ነው እየነገርከን ያለኸው፡፡
  እጅግ በጣም የሚገርመው ነገር ሰዎችን በዘር በቋንቋና በመደብ በተመሰረተ ካለ ጊዜያዊ ነገር በጠለቀና በሰፋ መልክ የአለማ የአስተሳሰብ የአመለካከትና የስሜት መመሳሰል መግባባትና አንድ መሆን የበለጠ ያቀራርባቸዋል አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ወይንም በአጭር አነጋገር ሰው ሆነው መፈጠራቸው ማለት ነው፡፡
  ሰው ሆነን ከመፈጠራችን በዘለለ ያለው ሌላው በዘር በቋንቋ በመደብና ወይንም በሌላ ያለው ተቀጥላ ነገር ሁሉ ዘለቄታዊነት ያለው ነገር አይደለም፡፡ይህ ተቀጥላ ነገር ሁሉ ሰው ሆነን ከመፈጠራችን ምስጢር ትርጉምና አላማ በታች ባለ ዘቅጠን ከሙሉ የሰውነት ተራ ስንወረድ ለጊዜው የምንደበቅበት መሸሸጊያ ዋሻችን ነው፡፡ዛሬም ገዢዎቻችን እያደረጉ ያሉት ከዚህ የሙሉ የሰውነት ተራ ወርደንና ዘቅጠን በብሄርና በቋንቋ ዋሻ ውስጥ ዘላለም እንድንደበቅና እራሳችንን ቀና አድርገን በድፍረትና በቀናነት እርስ በርሳችን እንዳንቀራረብ እንዳንተዋወቅና ህብረት እንዳይኖረን እያደረጉን ነው፡፡
  የኢትዮጵያዊነትን ሀሁ ፊደል ምን ብለን ብናስቆጥራቸው ይገባቸው ይሆን አሉ እንደተባሉት አፄ ቴዎድሮስ ይህንን ጥልቅና ሰፊ ሚስጥር አንተም በአደባባይ እየተናገርከው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
  ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቢናገሩ ቢፅፉ ቢማሩ እኔ ቅሬታ የለኝም፡፡ነገር ግን በዚህ ትንሽ ጎጆ ወይንም ዋሻ ውስጥ ብቻ ተወስነውና ተደብቀው እራሳቸውን አግልለው ሌላውንም እንደዚሁ አግልለው ኢትዮጵያዊነትንና መላውን አለምን በዚህ የተወሰነ ጠባብ መነፅር ብቻ እንዲያዩ ሲደረግ ግን አሳዛኝም ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ጭምር ነው፡፡እንግሊዘኛ ዛሬ አለም አቀፍ መግባቢያ ቋንቋ የሆነው ተስማምተንበትና ፈልገነው ብቻ አይደለም፡፡ፀሀይ በእንግሊዝ ግዛት አትጠልቅም የተባለላት ታላቋ ብሪታንያ ወይንም እንግሊዝ መላው አለምን በቅኝ ግዛት በሃይል በአንድ ላይ ስትገዛና ስታስተዳድር በዚያውም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተስፋፋና እነሆ ዛሬ የአለም ህዝብ ቁጥር አንድ መግባቢያ ሆነ፡፡ስለዚህም ዛሬ መሪዎቻችን በየአደባባዩ ያለ አስተርጓሚ አቀላጥፈው ይናገሩታል፡፡እንደዚሁም አማርኛ በተመሳሳይ መልክ የሀገራችን ብሄራዊ መግባቢያ ቋንቋ ለመሆን በቃ፡፡ይህ በመሆኑም አንድ የሚያደርገን የሚያግባባን ነገር ነው ማለት ነው፡፡ነገር ግን እንግሊዘኛን እንደ አለም አቀፍ ቋንቋነት መናገርን ያልነቀፉና ያላፈሩ ሰዎች አማርኛ ብሄራዊ ቋንቋ ሆኖ ሲነገር ግን አላስፈላጊ አቃቂር እያወጡና ነገር እየሰረሰሩ የሚተቹ አሉ፡፡እንዲያውም አንዳንዶች የነፍጠኛ ቋንቋ እያሉ ለማጥላላት ለማዳከምና ለማጥፋት የሚፈልጉና የሚጥሩ ሰዎች አሉ፡፡የጋራ እሴቶቻችንንም ሆነ የየግል እሴቶቻችን በአንድ ላይ በጋራ የመጠበቅ የመንከባከብ ግዴታና ሃላፊነት አለብን፡፡ለምሳሌ ትግሪኛ ቋንቋ የትግሬዎች ብቻ የግል ንብረት አይደለም፡፡ኦሮሚኛም ጉራጌኛም ወላይትኛም ወዘተ፡፡ሁላችንም ለእያንዳንዱ ቋንቋ ህልውናና ደህንነት ተቆርቋሪ መሆን አለብን፡፡ምክንያቱም ለመላው የሰው ልጅ ባጋራ ሊጠቅሙ የሚችሉ በዚያ ቋንቋ የተፃፉና ያልተፃፉ ብዙ የጋራ እሴቶች አሉና ማለት ነው፡፡ለምሳሌ ግእዝ በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ እንደሚሰጥ ሰምቻለሁኝ፡፡ፈረንጆች ይህንን የሚያደርጉት ለምንድን ነው፡፡ምክንያቱም ለመላው የሰው ልጅ ባጋራ ሊጠቅሙ የሚችሉ በግእዝ ቋንቋ የተፃፉና ያልተፃፉ ብዙ የጋራ እሴቶች አሉና ማለት ነው፡፡ስለዚህም እይታችንን ጠለቅና ሰፋ ማድረግ ስንችል አንድነታችንን ብቻ ሳይሆን ልዩነቶቻችንንም ጭምር እናዳንቃለን እናከብራለን ከዚህም አልፎ ለህልውናቸውና ለደህንነታቸው በጋራ ተቆርቋሪ በመሆን አብረን እንንከባከባለን እንጠብቃለን ማለት ነው፡፡
  የሰው ልጅ በዘር በቋንቋ በሃይማኖት ወዘተ የጠበበ እይታ ውስጥ ተደብቆ ለዘላለም የሚኖር ቢሆንማ ኖሮ ይህ ሁሉ የጋራ የሆነ የአለም ስልጣኔ ባልታየ ነበር፡፡ዳንኤል ጥሩ ነገር ነው ያነሳኸው ቀጥልበት፡፡
  ጥሩ የሚያኮራ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ እንዳለን ሁሉ በጥፎም አሳፋሪ ታሪክ አለን፡፡ዞሮ ዞሮ ግን ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን አምነን ከመቀበል ውጪ ልንክድና ሌላ አይነት አዲስ የማናውቀው ባእድ የሆነ ማንነት ልንፈጥር ግን ከቶ አይቻለንም፡፡ከፋም ለማም ብንወድቅም ብንነሳም እራሳችንን ሆነን ነው እራሳችንን ማሻሻልና ማሳደግና መቀየር ያለብን፡፡ስለዚህም ያን ያህል የተለየ የሆነ አዲስቷ ኢትዮጵያ ወይንም አሮጊቷ ኢትዮጵያ የሚባል ክፍፍል መኖር የለበትም፡፡አሮጌውም ሆነ አዲሱ የማንነታችን የጋራ መገለጫ አሻራችን ነውና፡፡ብንደኸይም ሆነ ብንከብርም፣ቢመቸንም ሆነ ባይመቸን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ወደ ኋላ ብንቀርም ሆነ ወደ ፊት ብንመጥቅም፣ ብንሰለጥንም ሆነ ብንሰየጥን ኢትዮጵያዊነታችን የማንነታችን መገለጫ ከመሆን ሊቀየር አይገባውም፡፡የኢትዮጵያዊነት ማንነታችንን ስፋትና ጥልቀት ደግሞ ዳናኤል በደንብ በሚማርክ አቀራረብ እየነገረን ነው፡፡እግዚአብሄር ይባርክህ ይጠብቅህ፡፡
  እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ ይባርክ !!!

  ReplyDelete
 55. tiru ne wgin ehadeg eskale yihe mech yikerefal kefafileh giza

  ReplyDelete
 56. እባካችሁ ከአቶ መለሰ ዜናዊ ጋር ግንኙነት ያላችሁ ሰወች ይህን የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲያነብ ብታደርጉልን ለ20 አመታት የገዟትን ኢትዮጵያን እንዲያውቌት እረዳችሁት ማለት ነው ::

  ReplyDelete
 57. beereta,hulachinem anebebne lsera mezegajete yetbekibenale. worie becha ayetekimeme, bsmanwe leke benesra lwete enametalne.

  ReplyDelete
 58. ስለ ማንነት ጉዳይ ምነው ምነው ኣሳሰባችሁ? በኢትዮፕያዊነት የሚያምን ሰው ኣክሱማውያን እንዲህ ሰሩ እንዲህ ኣደረጉ ብሔረ ናግራን ዘመቱ ታሪክ ሰሩ ሓወልት ኣቆሙ ዘመናዊ ስልጣኔ ነበራቸው ቢባል ምን ያስቆጣል??
  እንደሚታወቀው ኣገራችን የብዙ ብሔረ ሰዎችና ሕዝቦች ኣገር ነች እነዚህ ደግሞ ኢትዮፕያውን ናቸው ስለዚህ ምን ያስኮርፋቸዋል ይህ የሚያሳየው የየኣካባቢው ያለውን ታሪክ ለመሻማት ያላችሁ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳያል ከዚህ በተጨማሪ ለ ኣገሪቱ ሕዝቦች ያላችሁን ዝቅተኛ ኣመለካከት ያሳያል
  ብታስቡበት ይሻላል

  ReplyDelete
 59. ዳንኤል፣ ቃለ ሕይወት ያሰማልን! ግሩም ድንቅ ጽሑፍ ነው። ሰዎቹ ይህን ታሪክ ሳያውቁት ቀርተው ሳይሆን የሚደረገው ሁሉ የሚመጣውን ባለማሰብ (ራዕይ በማጣት) በእንዲህ ዓይነት መንገድ የነበረውን ታሪክ (አይቻልም እንጅ) ቢቻል ሙልጭ አድርጎ አጥቦ፣ ካልሆነም ከላዩ ላይ ሌላ ቀለም ቀብቶ ሌላ ለእኛ የሚመች "ታሪክ" መጻፍ ይቻላል ከሚል ጭፍን እብሪትና፣ ይህን ለማድረግ ከዚህ የተመቸ ጊዜ አይገኝም ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው። እግዚአብሔር ግን በጊዜው ሁሉንም ያደርጋል። "እግዚአብሔር ይዘገይ ይሆናል ነገር ግን የሚቀድመው የለም" ብለህ እኮ አስተምረህ ታውቃለህ።

  ReplyDelete
 60. i think you read the book titled ፍኖተ ገድል don't you and i dont agree upon what you say because finfine is for oromos minilik came and colonize us

  ReplyDelete
 61. i think you read the book titled ፍኖተ ገድል don't you and i dont agree upon what you say because finfine is for oromos minilik came and colonize us

  ReplyDelete
 62. This is True Histrory. Always write like this.Everything will pass, but truth. I want you to be remembered like Tsegaye Gebremedihin or Abe Gubegaw.

  ReplyDelete
 63. wede abatoch ketetegah kezih yebelete buzu kumneger tagengalehu,keza ante degimo tasefawaleh,God Bless you

  ReplyDelete
 64. እባካችሁ ከአቶ መለሰ ዜናዊ ጋር ግንኙነት ያላችሁ ሰወች ይህን የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲያነብ ብታደርጉልን ለ20 አመታት የገዟትን ኢትዮጵያን እንዲያውቌት እረዳችሁት ማለት ነው ::ስለአገር ምንነት በደንብ እንዲያውቅ አድርጉት፡፡ በተለይ ስለወደባችን ጊዜ ስጡትና ያስብበት፡፡

  ReplyDelete
 65. Dear Daniel,

  God bless you for your fantastic explanation on the link of Ethiopians starting from the ancient time. Sorry for todays, some individuals, who try to associate the common feature of Ethiopians only to the to be established Dam and the flag. We Ethiopians are one people by blood. All we are the combination Tigrian, amhara, oromo, gurage, sidama, ....... genetically. If we could reach a technology level that can isolate the different genes of the Ethnic groups and individuals, no Ethiopian would have pure blood that is not mixed. So, can we say that, this Ethnic group has this history and that Ethinic group has that history? No, no way to say like that. The yound generation is better follow the great thinkers of Ethiopians like Daniel Kibret. Thank you dear Daniel.

  ReplyDelete
 66. i was born in axum and this is true history,,,,most people in axum believe we all ethiopia.......

  ReplyDelete
 67. ደን ደንኤል ድካምህ ይገባኛል የምትሰጠዉን ቦታ እንድንረዳ ለማድረግ ነዉ ቀጥልበት ዉጤት አያመጣህ ይመስለኛል ደሞ አንደሰዉም ቤሆን መለዎጥ ቀላል አደለም አለማወቀን መወቅ ጥሩ ነገር ነዉ!

  ReplyDelete
 68. ውድ ዳንኤል

  ያንተን እይታወች በጣም እስማማባቸዋለሁ። በዚች ምድር ላይ ሰው ያመነበትን፣ የመሰለውን ያደርጋል። በዚያም ድርጊት ግማሹ ሲደሰት ግማሹ ያዝናል። የጠቅላይ ሚኒስተር መለስም የመሪነትና የትግል ዘመን በዚሁ አይነት የሚታይ ነው። ሚሊየኖች በስራዎቹ ተደስተዋል፤ ሚሊየኖች አዝነዋል። ባጠቃላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሞታቸው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አሳዝኖአል። የይቅርታና የፍቅር መንገድ ብንከተል ለሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ይበጃል። እናም ወገኖቸ ከንግድህ የቂምና የበቀል ነገር ይብቃ። በአድስ የልማትና የብልጽግና መንፈስ እንነሳ። የሞቱትን ነብስ ይማር። ለመላው ህዝብ መጽናናትን ይስጥልን። አሜን።

  ReplyDelete
 69. hagerag awekayte endewedat aderakege memher kalee heyewete yasemaleg megsetea semayate yawareselege.
  bety dallas

  ReplyDelete
 70. The Word 'Axum' is an Agew word. its meaning is chief of water(AK: water and sum: cheif). the Axumite civilisation belongs to Agews. however, the TPLF writers try to deny this history. they have altered ethiopian history. they are ignorant of ancient ethiopian ethnic structure and compostion. before thousand years, the present day tigray was inhabited by Agews. They were the ruling elites and founders. Queen Sheba was an Agew queen. As far as Axum is concerned Amhara and Tigre are secondary. they should know these. Eventhough Amharic is said to be started as a secret language by the royal family of axumites and soldiers according to some writers, this does not make difference. the present day Amharas are Agews because the Agew people of Begemedr, Gondar, Wollo became Amharic speakers as the language was imposed from above by King Lalibela of Zagwe daynaty and by successive solominic dyansty rulers such as Amdetsion, Yekuno-amlak, Zeraycob , Dawit, Gelawdios and many others.

  ReplyDelete
 71. Anonymous said...
  The Word 'Axum' is an Agew word. its meaning is chief of water(AK: water and sum: cheif). the Axumite civilisation belongs to Agews. however, the TPLF writers try to deny this history. they have altered ethiopian history. they are ignorant of ancient ethiopian ethnic structure and compostion. before thousand years, the present day tigray was inhabited by Agews. They were the ruling elites and founders. Queen Sheba was an Agew queen. As far as Axum is concerned Amhara and Tigre are secondary. they should know these. Eventhough Amharic is said to be started as a secret language by the royal family of axumites and soldiers according to some writers, this does not make difference. the present day Amharas are Agews because the Agew people of Begemedr, Gondar, Wollo became Amharic speakers as the language was imposed from above by King Lalibela of Zagwe daynaty and by successive solominic dyansty rulers such as Amdetsion, Yekuno-amlak, Zeraycob , Dawit, Gelawdios and many others.

  ReplyDelete
 72. ተካልኝ ከጂማ ዩን.December 23, 2012 at 11:26 PM

  ዘረኞችና ጎጠኞች ራሳችሁን መርምሩ።ታሪክን ከስሩ ለማወቅ ሞክሩ።

  ReplyDelete
 73. እግዜር ይስጥልኝ።

  ReplyDelete