Tuesday, October 25, 2011

ቻይንዬ


ሴትዮዋ ልጃቸው ከቻይና ትወልዳለች አሉ፡፡ አንድ ወር እንደሞላት ልጂቱ ትሞትና ልቅሶ ይጠራሉ፡፡ ታድያ እያለቀሱ ወደ ድንኳኑ ሲገቡ ምን አሉ መሰላችሁ «እኔ ድሮም ጠርጥሬ ነበር፣ ጠርጥሬ ነበር፤ የቻይና ነገር ይኼው ነው አይበረክትም» አሉ ይባላል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሚዲያ ስማቸው ከሚነሣ ሀገሮች እና ሕዝቦች መካከል የቻይናን እና የቻይኖችን ያህል ቦታ ያለው የለም፡፡
በመንገድ ሥራ፣ በግድብ፣ በማዕድን ማውጣት፣ በቴሌ ኮሙኒኬሽን፣ በሸቀጣ ሸቀጥ፣ በፖለቲካ፣ ባህል ሁለ ነገራችን ቻይና ቻይና ይላል፡፡ የኢትዮጰያ ቴሌቭዥን እንኳን በቀን ውስጥ ቢያንስ አንድ የቻይና ዜና ሳያሳየን አይውልም፡፡ ጠላ ቤት፣ ጠጅ ቤት፣ ሥጋ ቤት፣ ጉልት ገበያ፣ መርካቶ፣ አትክልት ተራ፣ አጠና ተራ፣ በግ ተራ፣ ካዛንቺስ፣ ቺቺንያ ዘወር ዘወር ብትሉ ከአሥሩ ሰው አንድ ሦስቱ ቻይና ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡
እንዲያውም ከመብዛታቸው የተነሣ እንደ አንድ ብሔረሰብ ተቆጥረን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ወንበር ይሰጠን ብለዋል እየተባለ ይቀለድም ነበር፡፡
በዚህች ሀገር ታሪክ ውስጥ ዑቃቤ እየሆኑ በየዘመናቱ የሚመጡ ሕዝቦች አሉ፡፡ ከግራኝ አሕመድ ጦርነት በኋላ ፖርቱጋሎች መጥተው ነበር፡፡ በሀገሪቱ በነበሩ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ብጥብጦች ውስጥ እጃቸውን ነክረው፣ በሌላም በኩል ቤተ ክርስቲያን እና ድልድይ ሠርተው ሄደዋል፡፡ በእነርሱ ዘመን የተሠሩ ድልድዮች ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ተሻግረው ዛሬም ለታሪክ ተቀምጠዋል፡፡
ከፖርቱጋሎች ጋር ተዋልደው የቀሩ አያሌ ኢትዮጵያውያንም አሉ፡፡ በምዕራቡ የጎንደር ክፍል ራሳቸውን የፖርቹጋል ዝርያ አድርገው የሚቆጥሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ሰምቻለሁ፡፡
በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መጀመርያ ላይ ኢትዮጰያ ፈረንሳይ ፈረንሳይ ትሸት ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ አሜሪካኖች የሀገሪቱ ውቃቤዎች ሆኑ፡፡ አሥመራ ላይ ቃኘው ጣቢያን ተክለው ፖለቲካውንም ወታደራዊው ተቋሙንም የበላይ ጠባቂነት ተሾሙበት፡፡
1966 አብዮት ደግሞ ኩባ እና ራሽያ የሚባሉ የበላይ ጠባቂዎችን ይዞ መጣ፡፡ ኩባዎች ኢትዮጵያን ተምነሸነሹባት፤ ኢትዮጵያውያንም ኩባ ሄደው ኖሩ፤ ተማሩ፡፡ እነ ፊደል ካስትሮን የአያቶቻችን ያህል አወቅናቸው፡፡ የአራት ሰዓታት ንግግራቸውንም የቅዳሴ ያህል ቆመን አዳመጠን፡፡ ኩባ ከቆዳ ስፋቷ በላይ በኛ ልብ ውስጥ ቦታ አገኘች፡፡
ኢትዮጵያ የሶቪየት አንዷ ክፍለ ሀገር እስክትመስል ድረስ የሶቭየቶች መንፈስ ወረረን፡፡ በወታደር ቤት የነበሩት ቁምጣዎችም ብሬዥኔቭ ተባሉ፡፡ ሥነ ጽሑፋችንም ከግእዝ ወጥቶ ወደ ራሽያ አቀና፡፡ እንደ ሰው በምድር እንደ ዓሳ በባሕር፣ የምንጮች መፍለቂያ ተራሮች ናቸው፤ ልጅነት፣ የሚባሉ መጻሕፍትን ኩራዝ አከፋፈለን፡፡ እነ ማክሲም ጎርኪይን ከነሐዲስ ዓለማየሁ በላይ አደነቅናቸው፡፡ እነ ቀስተ ደመና መጽሔቶችን አነበብን፡፡ የሞስኮ ራዲዮም አዳመጥን፡፡ ሌኒን የሚባል ሰው በአካል ባናገኘውም በመንፈስ ከኛ ጋር ለአሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፡፡
ያም ደግሞ አለፈና የቻይና ዘመን መጣ፡፡
ነገሩ ቻይኖች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም፡፡ እኛም ስንጓዝ እነርሱም ሲመጡ መክረማችንን የሚያስረዱ ድርሳናት አሉ፡፡ ፒንግ የተባለው የቻይና ንጉሥ ነግሦ በነበረ ጊዜ (1 እስከ 6 ዓም) አውራሪሶች በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኝ «አግአዚ» ከሚባል ሀገር ይገቡ እንደነበር የሚገልጡ የቻይና መዛግብት አሉ፡፡ ይህ አግአዚ የተባለው ሀገርም ኢትዮጵያ ሳትሆን እንደማትቀር ይታመናል፡፡
በታግ ሥርወ መንግሥት ጊዜ (618 - 907 ዓም) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ግንኙነት ነበራት፡፡ በዚያም ባሮችን፣ ዝሆኖችን፣ አውራሪሶችን፣ የከበሩ ድንጋዮችን እና ሌሎችንም ታስገባ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአርኬዎሎጂ የተገኙ የቻይና ሳንቲሞች የዚህ የንግድ ግንኙነት ውጤቶች መሆናቸው ይታመናል፡፡
በዘመናዊው ታሪካችንም በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ውስጥ ኢጣልያን ኢትዮጵያን መውረሯን ከተቃወሙት አምስት ሀገሮች አንዷ ቻይና ነበረች፡፡ ሁለቱ ሀገሮች የመጀመርያውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት እኤአ በዲሴምበር 1 ቀን 1970 ዓም ነበር፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለች ቻይና እዚህ ደርሳለች፡፡
ኢትዮጵያውያን ቻይናን የሚያውቋት በብዙ ጠባይዋ ነው፡፡ አብዛኞቹ የመርካቶ ሰዎች የቻይኖች ደንበኞች ናቸው፡፡ ሁለመናችን ከቻይና ሆኗል የሚመጣው፡፡ እንዲያውም ባለፈው ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎችም ቻይና ተመርተው እንደሚገቡ ሰምቻለሁ፡፡ ነገ ንዋያተ ቅድሳትም ከቻይና ማስመጣታችን የማይቀር ነው ማለት ነው፡፡
የቻይና ዕቃዎች ርካሾች ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ ለገሐር ላይ አንድ የቻይና ሙሉ ልብስ በአሥራ አምስት ብር ሲሸጥ አይቻለሁ፡፡ እውነት ስላልመሰለኝ ጠጋ ብዬ አየሁት ልብስ ነው፡፡ ታድያ አንዱ ተረበኛ «ለመሆኑ ይታጠባል ብሎ ጠየቀ፡፡ ሻጩ ምን እንዳለው ታውቃላችሁ «በአሥራ አምስት ብር የሚታጠብ ሱፍ ያምርሃል? ባክህ ዩዝ ኤንድ ስሮው ነው»፡፡
ይህን ስሰማ አንድ የድሮ ቀልድ ትዝ አለኝ በድሮ ዘመን መንግሥት የመምህራን እጥረት ስለነበረበት አሥራ ሁለተኛ ክፍል ያጠናቀቁትን መጠነኛ ሥልጠና ሰጥቶ ያሠማራ ነበር አሉ፡፡ እነዚህም «የድጎማ መምህራን» ይባሉ ነበር፡፡ ደሞዛቸውም መቶ ሰማንያ አምስት ብር ነበር ይባላል፡፡ ታድያ አንዱ የድጎማ መምህር የእንግሊዝኛ ክፍል ውስጥ ገብቶ ክኖው፣ ክናይፍ፣ ክኖውሌጅ፣ እያለ ያስተምራል፡፡ እንዳጋጣሚ በዚያ ጊዜ ተቆጣጣሪ ይገባና የሚያስተምረውን ይሰማዋል፡፡ በኋላ ታድያ ቢሮው ጠርቶ «እንዴት ክናይፍ፣ ክኖው፣ ክኖውሌጅ እያልክ ታስተምራለህ ይለዋል፡፡ የድጎማ መምህርም «ታድያ 185 ብር ደሞዝ ናይፍ፣ ኖው፣ ኖውሌጅ እያልኩ እንዳስተምርልህ ትፈልጋለህ አለው አሉ፡፡ በአሥራ አምስት ብር የሚታጠብ ሱፍ ትፈልጋለህ» ያለውን እንዳትረሱ፡፡
ሌላኛው ቀበል አድርጎ «በተለይ ዝናብ ከመጣ ከቤትህ መውጣት የለብህም፡፡ ውጭ ከሆንክም ሮጠህ አንድ ቤት መግባት አለብህ፡፡ ያለበለዚያ ዝናቡ ልበሱን አጥቦ ይወስደውና ራቁትህን ትቀራለህ» አለና ሁኔታውን አሟሟቀው፡፡ « እንደርሱ አይደለም» አለ ደግሞ ሌላው፡፡ «ዝናብ ከመታህማ ራስህን ታጣዋለህ፤ ምክንያቱም የልብሱ ቀለም ይቀየርና ሌላ ልብስ ነው የሚሆነው፡፡»
ቻይና ለአፍሪካ እና ለአሜሪካ ገበያ የምትሠራው ይለያያል፡፡ አሜሪካኖችም ቢሆኑ በቻይና ምርቶች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ እዚያ ግን ደረጃቸውን እና ጥራታቸውን የጠበቁ የቻይና ምርቶችን ነው የምታ ገኙት፡፡ አንድ ቻይና የሚገኝ ወዳጄ እንዳለው ቻይና አንድን ምርት በምን ያህል ጥራት ልስራልህ? ብሎ አይጠይቅም፡፡ በምን ያህል ወጭ ልሥራልህ? እንጂ፡፡ አንድን የጫማ ዓይነት መልኩ እና ቅርጹ ተመሳሳይ ሆኖ የመቶም የአንድም ብር አድርጎ ማምረት ይቻላል፡፡ በቻይና፡፡
ቻይኖች መንገድ ሲሠሩ አንድ መንደር ይደርሳሉ፡፡ የመንደሩ ሰዎች ይጠመቁበት የነበረው ጠበል በመንገዱ ሥራ ምክንያት ይቋረጥባቸዋል፡፡ ታድያ መንደርተኞቹ አንድ ሆነው ቻይኖቹ ይሄዳሉ፡፡ «ጠበላችን እንዲቋረጥ አድርጋችሁታል» ይሏቸዋል ቻይኖቹን፡፡ «ችግር የለም» አሉ ቻይኖቹ፡፡ «ሳምፕሉን ስጡን እና አምርተን እናመጣላችኋለን»
አንዳንድ ነጋዴዎች የአሜሪካን ወይንም የአውሮፓን ሞዴል ይገዙና ወደ ቻይና ይሮጣሉ፡፡ እዚያም በአነስተኛ ዋጋ እና በመናኛ ጥራት ያስመርቱታል፡፡ ከዚያም ለእነርሱ በመቶ ፐርሰንት ትርፍ፣ ለእኛ ደግሞ በርካሽ ይሸጡልናል፡፡
ቻይኖች ጠንካራ ሠራተኞች መሆናቸውን አበሻ በሙሉ መስክሮላቸዋል፡፡ ሥራ አይንቁም፣ በሥራም አያለግሙም፡፡ እንዲያውም «በሥራ መለገምን ኢትዮጵያ መጥተን ነው የተማርነው» ይላሉ አሉ፡፡ እነርሱ የሠሩትን የመንገድ ዳር ብረት አበሻ ነቅሎ ሲወስድባቸው «እነዚህ ሰዎች ሌላ ሀገር አላቸው ወይ ብለው የጠየቁትም ወደው አይደለም፡፡
የቻይኖች የሀገር ፍቅር በመፈክር እና ባንዴራ በመልበስ ብቻ የሚገለጥ አይደለም፡፡ ለሀገራቸው የማይሆኑላት ነገር የለም፡፡ አሜሪካ ያሉ ቻይኖች አንድ የሚጠረጠሩበት ነገር ማንኛውንም ለሀገራቸው የሚጠቅም ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ወደ ቻይና በማሸጋገራቸው ነው፡፡ ለቻይኖች ቻይናም ተወለዱ አሜሪካ ሀገራቸው ቻይና ናት፡፡ እንኳን በቀላሉ የሚገኘውን ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ቀርቶ በድብቅ እና በስለላ የሚገኘውን ወታደራዊ ምሥጢር እንኳን እየፈለፈሉ ወደ ሀገራቸው ይልካሉ ተብለው ይታማሉ፡፡ ይህንን ያህል የሀገራቸው ፍቅር ዘልቆ የገባቸው ቻይኖች እኛን «ሌላ ሀገር አላቸው ወይ ብለው ቢጠይቁ አይፈረድባቸውም፡፡
ቻይኖች ያኙትን ሁሉ የሚበሉ ናቸው እየተባለ ተመርጦ በሚበላበት በሐበሻ ምድር ይታማሉ፡፡ ታድያ 1.5 ቢሊዮን ሕዝብ ያገኘውን ካልበላ እንዴት ሆኖ ሊኖር ኖሯል? ገበሬው ቻይኖች መንገድ ከሚሠሩበት ቦታ አጠገብ ነበር አሉ ቤቱ፡፡ ለመኪኖቻቸው እና ለራሳቸው የሚሆን ውኃ የሚያመላል ስላቸው አህያ ይፈልጉና ቻይኖቹ ያነጋግሩታል፡፡ ሰውዬውም በዋጋ ይስማማል፡፡ «ነገር በአህያዬ ፋንታ እኔ ነኝ ውኃውን የማመላልሰው» ብሎ ታድያ በየቀኑ ውኃ የሚያመላልሰው ራሱ ነበረ፡፡ ቻይኖቹ ገረማቸውና ጠየቁት፡፡ «አንተ ከምታመላልስ ለምን አህያህን አታከራየንም ሰውዬውም መለሰ «አህያዬ እንደወጣች ባትመለስስ ቻይና ያገኘውን ነው የሚበላው ሲባል ሰምቶ ነዋ፡፡
ቻይኖችን እንደ ሌሎች የውጭ ዜጎች በውድ እና በተለዩ የሥራ ቦታዎች ላይ አታዩዋቸውም፡፡ ከትናንሽ እስከ ግዙፍ ሥራዎች ላይ ተሠማርተዋል፡፡ ከከተማ እስከ ገጠር ገብተዋል፡፡ እንዲያውም አንድ ቦታ የሰማሁት ቀልድ አለ፡፡ አንድ የገጠር መንገድ ቻይኖች ያሸንፉና ሠርተው ያስረክባሉ፡፡ እነርሱ ፕሮጀክቱን በጨረሱ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በመንደሩ የሚወለዱት ሁሉ ዓይናቸው ሞጭሟጮች ቁመታቸው አጫጭሮች ሆኑ አሉ፡፡ ደግሞ የሚገርመው የአብዛኞቹ ልጆች ስሞች «ቻይና» ነው የሚባለው፡፡
እና በዚህ የተነሣ ቻይኖች ኮንትራት በወሰዱባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ዳር እና ዳር ያሉ መንደሮች ወንዶቹ እርሻ እና ከብት ጥበቃ መሄድ እያቆሙ ነው ይባላል፡፡ አንድ አባ ወራ ሲወጣ አንድ ቻይና እየገባ ተቸግረው ነው አሉ፡፡
ቻይኖች ማኅበራውያን ናቸው፡፡ ለጠጥ ያለ ሆቴል፣ ቀብረር ያለ ቡና ቤት አታገኟቸውም፡፡ ጠጅ ቤት፣ አረቂ ቤት፣ ሥጋ ቤት፣ ሽሮ ቤት፣ እማማ ቤት፣ ብትገቡ ቢያንስ አንድ ቻይና አታጡም፡፡ እያቃጠ ላቸውም ሆነ እያንገበገባቸው ከቃርያ እና ሚጥሚጣ ጋር ሲታገሉ ታገኟቸዋላችሁ፡፡ ድሬዳዋ በሄድኩ ጊዜ ቻይኖች መንገድ ዳር አንጥፈው ጫት ሲቅሙ አይቼ ገርሞኝ ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን ሌሎችን ማስመጥ የምንችል ሕዝቦች መሆችንን ያየሁት በቻይኖች ነው፡፡ ቻይና አሜሪካ መጥቶ ራሱንም ባሕሉንም ጠብቆ ይኖራል፡፡ አንድ ቻይና ዛሬ ከታየ ከዓመት በኋላ «ቻይና ታውን» ይመሠረታል ተብሎ የሚነገርላቸው ቻይኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሰምጠው ቀርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘፈንለት፣ የሚለፈፍለት እና ቅኔ የሚወርድለት ዓባይ ካይሮ ላይ ስታዩት ያናድዳችኋል፡፡ ማንም እንደ ፈለገ በየመንደሩ ሲጎትተው ታያላችሁ፡፡ አንዱ ከብት ያጠጣበታል፤ አንዱ ይዋኝበታል፣ አንዱ ልብስ ያጥበበታል፣ አንዱ ቆሻሻ ይደፋበታል፣ አንዱ መንገድ ያጥብበታል፣ አንዱ ጀልባ ይቀዝፍበታል፡፡ ጎጥ ለጎጥ፣ መንደር ለመንደር፣ ቱቦ ለቱቦ፣ ስርቻ ለስርቻ ያንከራትቱታል፡፡
ቻይናም ኢትዮጵያ እንዲሁ ነው የሆነው፡፡ አረቂ ጠጭ፣ ጫት ቃሚ፣ ጥሬ ሥጋ ቆራጭ ሆኖ ቀርቷል ቻይና፡፡ ካዛንቺስ እና ቺቺንያ ያመሻል ቻይና፡፡ «ከተቀላቀልክ ማን ይለይሃል» አለ የወሎ ገበሬ እውነቱንኮ ነው፡፡ መንገድ የሚሠራ ቻይና አህያውን ይገጭበታል፡፡ ገበሬው ዘራፍ ብሎ አንገቱን ይጨመድዳል፡፡ «ክፈል» ይላል ገበሬው፡፡ ቻይና ሆዬ «ገንዘብ አልያዝኩም ካምፕ እንሂድና ልስጥህ» ይላል፡፡ «አይሆንም» አለ ገበሬ፡፡ «እዚያ ከዘመዶችህ ጋር ከተቀላቀልክ ማን ይለይሃል? ሁልህም ተመሳሳይ ነህ» አለ አሉ፡፡ ቻይና ተቀላቅሏል፡፡
የዓለምን ኢኮኖሚ እያስጠነገሩ፣ ለአሜሪካ እያበደሩ፣ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው በሚለው የዲፕሎማሲ መርሐቸው እየተመሩ ቻይኖች አዲሶቹ ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ ቢያንስ ሌላ የሚተካቸው እስኪመጣ ድረስ፡፡ ይቺን ፎርጅድ ምርታቸውን ቢተውን ግን እንዴት በወደድናቸው ነበር፡፡
አሌክሳንድርያ፣ ቨርጂንያ
© ህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።

40 comments:

 1. "ከዘመዶችህ ጋር ከተቀላቀልክ ማን ይለይሃል?" dani u are the best

  ReplyDelete
 2. endemen alehe dane belelaw senenaded ante bezehe tazennalehe edemana tenawen yestehe

  ReplyDelete
 3. I do not want them.When i see them what i feel is that drainage of our wealth. Let we keep/maintain our wealth so that the next generation will use it properly(If we are unable to use it today). China, India, Pakistan, Arab,...i feel as if we are colonized by these people.

  ReplyDelete
 4. ይቺን ፎርጅድ ምርታቸውን ቢተውን ግን እንዴት በወደድናቸው ነበር፡፡
  SOFONIYAS.

  ReplyDelete
 5. D. Daniel, It has been such a long time since i laughed this hard...Egziabhair Yisttlin, i needed it with all the depressing news i have been hearing.

  Ameha Giyorgis
  DC Metropolitan Area

  ReplyDelete
 6. nice article & view I like it...it shows there is a lot to be thinked & to be done. z task is not only given to z government...i have seen them when zy participate n being impresed by z activity of church. with regard to it, like any other task it is also z task of preachers n church men...where r u z childrens of z fathers...u have wonderful fathers who made & even r doing a history but u r not working, doing, thinking, teaching... like ur fathers... oh i am sorry me too...we have been z one to awaken...as Kebede mikael said LESRA LE EWKET GILO LEMENESATE KOSQUASH YEFELEGAL YESEW LEJ ENDE ESATE!!! Dani keep writting, we will read, who is able to pray will pray, z others will do...thanks & blessings of fathers be up on u!

  ReplyDelete
 7. Girum, new balehubet be medere america bezu chaina ale yaw globalization aydel yembalew

  ReplyDelete
 8. Thank you Dn. Daniel
  Did you know the Chinese who go to Ethiopia are criminals and prisoners? I bet you didn't know that. The chinese who come to America are those with class. Well at least most of them. But the chinese people in Ethiopia right now are a concern to most Ethiopians because they are criminals and were sent to Ethiopia to work and live there for the rest of their lives. That's the reason why you see them Tej Bet.

  ReplyDelete
 9. ውድ ዳኒ አንድ ልጨምርልህ

  አንድ ቻይና ምግብ ቤት ገብቶ እያቃጠለው ይበላል፡፡ ከዚያ የእኛ ሰው ተመልክቶ የታባክ ተቃጠል የእናንተ ጫማ እንዲህ ነው የሚያቃጥለን አለ ይባላል!!
  ደህና ሰንብት

  ReplyDelete
 10. Dear Daniel,

  I agree with you; China produces an item according to your payment to the item. In this sense, our merchants are subject to low quality item they imported.Their selfishness cost the total people in our country. You know it very well many quality goods in America is produced in China. Even the statute of Martin Luther King in Washington DC is produced by China. Thus, we can not accuse them or finger on them. When someone finger to someone, it is clear that three of the fingers directed to the one who is fingered. In line with this, we should look inward.

  ReplyDelete
 11. ይቺን ፎርጅድ ምርታቸውን ቢተውን ግን እንዴት በወደድናቸው ነበር !!!

  ReplyDelete
 12. ወይ ቻና እኔነኝ የሠራሁ አለች እንደዚህ አንደምታደርግ የተባበሩት መንግስታት ሰምቷል

  ReplyDelete
 13. ቻይናዎች ለእኛ ለዘመኑ ወጣት ትውልድ ርካሽ ብልጭልጭ ፋሽኖችን ኮስሞቲኮችንና አልባሳትንና ሌሎችንም ነገሮች በገፍ ላኩልን እኛም ሳንመርጥ እያግበሰበስን አስገባን፡፡ዛሬ በየአደባባዩ በየመንገዱና በየሱቁ ለአይን የሚታክቱና የሚያማልሉ ርካሽ ብልጭልጭ ፋሽኖችን ኮስሞቲኮችንና አልባሳት ነገሮችን በገፍ እናያል፡፡ወጣቱ ትውልድ በተለይም ሴቱ በዚህ ደንዝዞና ማሎ ሲደናበርና በየካፊቴሪያውና በየመዝናኛው በእነዚህ ፋሽኖች አማካኝነት እየተኳኳለ እየተሸቀረቀረ ውድ ጊዜውን በከንቱ እያባከነና ሌላውንም እንዲሁ በተመሳሳይ እንዲያባክን እያዘናጋ ስለሆነ የስራ ፍቅርና የታታሪነት ባህል እየጠፋ ስለመጣ እነዘሆ ዛሬ ቻይና ሀገራችንን እንድትወረው ሆነ፡፡አዎ ልክነው ቻይናዎች እኛን ኢትዮጵያኖችን ሌላ ሀገር አላቸዎይ ያሉት፡፡ትክክል ብለዋል አዎ ዛሬ ትውልዱ ሁሉ በየራሱ ጠባብና እረስ ወዳድ በሆነ መንገድ በራሱ አለም ከመክነፍ ውጪ ለሀገሬ ለወገኔ ብሎ በጋራ ስለጋራ መፃኢ ህይወት ጉዳይና አጀንዳ ማሰብና መጨነቅ ቀርቷል፡፡ጠቀም ያለ ትርፍ እስካስገኘ ድረስ ዛሬ ነጋዴው ከቻይና የሚያስመጣው ጥራቱን ያልጠበቀ ጋርቤጅ ውዳቂ ምርት ጭምርም ቢሆን ሀገርንና ወገንን ይጥቀም ይጉዳ ግድ አይሰጠውም፡፡ዛሬ እኛ ብዙሀኑ ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በላይ እንደ ሀገር እንደ ህዝብና እንደ ዜጋ በንቃት በቀናኢኒነትና በፍቅር ለሀገርና ለወገን በዘላቂነት በሚጠቅም መልኩ ማሰብ አቁመን በደመ-ነፍስ የምንንቀሳቀስ ፍጡራን ሆነናል፡፡በምክንያታዊነትና በእውነት የምንመራ ህዝቦችና ዜጎች መሆናችንን አቁመን በስሜታዊነት በውዥንብርና በሀሰት የምንመራና የቻይናና የሌላም ሀገር ርካሽ ሸቀጥ አግበስባሽና ማራገፊያ ሆነናል፡፡ለዘላቂ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም ከመሯሯጥና ከመታገል ይልቅ በራስ ወዳድነትና ስግብግነት ስሜት በጊዚያዊ ብልጭልጭ ነገር በቀላሉ የምንማልልና የምንታለል ሆነናል፡፡እጅግ የሚገርመው ነገርና መረዳት ያለብን ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ከቻይና የሚመጡ እቃዎች የሚሰሩባቸው ጥሬ እቃዎች አካባቢን የሚበክሉና እጅግ አደገኛ የሆኑ መርዛማ ነገሮች ጭምር መሆናቸው ነው፡፡ለምሳሌ ብዙ የጫማ መረገጫ ዋና ሶል የሬንጅነት ፀባይ ካላቸውና መወገድ ካለባቸው ጥሬ እቃዎች እየተሰራ እየተላከ ነው፡፡እጅግ በጣም በማይታመን ዋጋ እየተሸጠልን ያለውም አንዱ ምክንያት በተዘዋሪ መወገድ ያለበትን ዝቃጭና በካይ ማቴሪያሎችን ቻይና በተዘዋዋሪ ወደ መጠቀሚያ ምርትነት በመቀየር ዳምፕ በማድረግ እኛን የቆሻሻ ማስወገጃና ማጠራቀሚያና ቅርጫት ጭምር እያደረገችን ነው ማለት ነው፡፡አዎ ልክነው ይህንን ነገር ሁሉ የማይረባና እጅግ ጎጂ የሆነ ነገር ጭምር አሜን ብለን ሳንመረምርና ሳንመርጥ ዝም ብለን ስናስመጣና ስንቀበል ኢትዮጵያውያን ሌላ ሀገር አላቸዎይ ያስብላል፡፡ለዚህ ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ስግብግብና ራስ ወዳድ የሀገራችን ነጋዴዎች ተጠያቂዎች ናቸው፡፡በወገናቸውና በሀገራቸው ጉድለት ስቃይና ጉዳት ከልክ መጠን ያለፈ ትርፍ ለማግበስበስ ሲሉ ሀገራቸውን ጭምር ከመሸጥ ወደኋላ የማይሉ በታሪክ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ለዚህ አይነት ከፍተኛ ሃላፊነት የጎደለው የሀገርና የህዝብ ጥፋትና ጉዳት ደግሞ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ጭመር በዋናነት ተጠያቂ ነው፡፡ምክንያቱም እራሱ መንግስትም ጭምር በዋናነት እሁን ቢዝነስና ንግድ ውስጥ በስፋትና በጥልቀት እጁን አስገብቷልና፡፡የሀገሪቱ አንጡራ ነፁህ ጥሬ ሀብትና የግብርና ወጤቶች የህዝብ ጉሮሮ እየተዘጋና ህዝብ እየተራበና እየተቸገረ ኤክስፖርት መር በሚል ጭፍንና መሰሪ የሆነ ስግብግብ አስተሳሰብ ብቻ በመመራት የጥቂት ግለሰቦችን ኪስ ለመሙላትና ለማጎልበት ሲባል ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡በምትኩና ደግሞ ለብዙሀኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚቀርብለት ከውጪ የሚገባ ምርት በተቃራኒው ጥራቱን ያልጠበቀና እጅግ ጎጂና አደገኛ የሆነ ምርት ነው፡፡እንግዲህ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት ይህ ነው፡፡ህዝብንና ዜጋን በዚህ አይነት አደገኛ ሁኔታ እየጎዱ እንግዲህ ምን አይነት ልማት ነው ትርጉም ያለው ልማት የሚሆነው፡፡በአጠቃላይ ሀገሪቷ በዋናነት ትክክለኛ ማህበረሰባዊ ልማት እድገትና ስልጣኔ የሚካሄድባት ሳትሆን በተቃራኒው በነፃ-ገበያ ሽፋን ጥቂቶችን በሚጠቅም መልክ በዋናነት ተራ የውንብድናና የዝርፊያ ባህሪ ያለው የማፍያ ስራ አይነት የቢዝነስ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት አውድማ ነው እየሆነች ያለችው፡፡
  ለዚህ ነገር ደግሞ ዋናው ችግሩ የቻይናዎቹ ወይንም የህንዶቹ አይደለም በዋናነት የእኛው የራሳችን ነው፡፡ችግሩ ደግሞ በቻይናዎቹ እንደተባለው ኢትዮጵያኖች ሌላ ሀገር አላቸዎይ ከተባለው መሰረታዊ ጥልቅ እውነታ ባለው አነጋገር የሚገለፅ ነው፡፡ቻይናዎቹ ይህንን አሉ ተባለ እንጂ አንዳንድ ቀናኢ ኢትዮጵያንም የሀገሪቱና የትውልዱ አጠቃላይ መፃኢ ሁኔታ በጣም ያሳሰባቸው ደግሞ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ይህ ትውልድ ይህቺን ሀገር እንደ ሀገር በቀጣይነት ለመረከብ ለማስተዳደርና ለማስቀጠል ስለማይችል ሀገሪቷን ቻይናውያን ቢረከቧት ይሻላል በማለት ተናግረዋል፡፡አሜሪካኖችም መጡ ፈረንሳዮችም መጡ ራሽያውያንም መጡ ቻይናውያንም መጡ ወይንም ሌላ ሁሉም በቅድሚያ በዋናነት የሚያስጠብቀው የራሱን አላማና ጥቅም ብቻ ነው፡፡እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን ሀገራዊ የሆነ የዜግነት ግዴታችንን እንደ ሌሎቹ ለመወጣት አቅቶናል፡፡ሌሎች የኋላ ቀርነት ችግሮቻችን እንዳሉ ሆነው ለዚህ አሳፋሪና አሳዛኝ ክስተት ደግሞ አንዱ ዋነኛ መሰረታዊ ምክንያት ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የራሱን ድብቅና ጠባብ የሆነ ስልጣኑንና ጥቅሙና ለማስጠበቅ ሲል ላለፉት 20 ዓመታትና አሁንም እየተከተለው ያለው የከፋፍለህ ግዛው መሰሪ አካሄድ የፈጠረው አጠቃላይ የመግባባት የመተሳሰብ የአንድነትና የብሄራዊ ስሜትና መንፈስ መላሸቅና መመናመን ውጤት ነው፡፡ነገር ግን ፍላጎቱ ማስተዋሉና ቁርጠኝነቱ ካለን ግን ቢረፍድም ቅሉ ገና አልመሸምና ዛሬም ይህንን ስሜትና መንፈስ በስተመጨረሻ ሳይሞት የሀገራችንና የራሳችንን መፃኢ እድል መታደግ እንችላለን፡፡

  ReplyDelete
 14. ስራቸውን ሁሉ የተከታተለ አንድ የገጠር ሰው ቻይኖችን ጥልያን አይንሽን አጥብበሽ መጣሽ ብሎአቸዋል

  ReplyDelete
 15. «ታድያ በ185 ብር ደሞዝ ናይፍ፣ ኖው፣ ኖውሌጅ እያልኩ እንዳስተምርልህ ትፈልጋለህ?»

  ReplyDelete
 16. የሆድ የሆዳችንን፣ ብሶት ብሶታችንን በጨዋታ በጨዋታ ስትገልጠው አቤት ደስ ሲል፣ እያረርክ መሳቅ በችግርህ መቀለድ ደስ ይላል፣ ይህቺን ጽሑፍ ደግሞ ቻይናዎች ቢያነቧት ወይ ባስተርጓሚ ቢሰሟት ደግሞ አንጀታችን ፓልም ዘይት በጠጣ ነበር፡፡

  ReplyDelete
 17. ቻይኖች ይህችን ጽሑፍ ባነበቡልን አንጀታችን ፓልም ዘይት በጠጣ፡፡ ቅቤ ድሮ ቀረ ብዬነው፡፡

  ReplyDelete
 18. እኛን በተረት የሚችለን የለም በስራ ግን ባዶ ነን!!!

  ReplyDelete
 19. ምንተስኖት ዘፍኖተ ሎዛ
  የዓለምን ኢኮኖሚ እያስጠነገሩ፣ ለአሜሪካ እያበደሩ፣ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው በሚለው የዲፕሎማሲ መርሐቸው እየተመሩ ቻይኖች አዲሶቹ ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ ቢያንስ ሌላ የሚተካቸው እስኪመጣ ድረስ፡፡ ይቺን ፎርጅድ ምርታቸውን ቢተውን ግን እንዴት በወደድናቸው ነበር፡፡

  ReplyDelete
 20. ከሁሉ የሚያሰጋው ምርቶቻቸው ካንሰር የማስያዝ እድሉ ብዙ ነው።ስለዚህ በጊዜ ቢታሰብበት መልካም ነው።

  ReplyDelete
 21. የዛሬ ጽሁፍህ ተመችቶኛል ከታሪክ አወቃቀሩ ጭምር፡በተለይ ደግሞ ያሳረግክበት አባባል ወድጄዋለሁ ፡፡እኔ ግን ግራ እየገባኝ ያለው የሴቱ ነገር ነው ከዘር ሁሉ ድብልቅ ዘር ምርጥ ነው ቢባልም ዝም ብሎ አይነት በመሆን ግን አይደለም እኔም ሴት ብሆንም በአሁን ጊዜ ባሉት ጥቂት በማይባሉ ሴቶች ባህሪ በጣም ነዉ የምሸመመው በይበልጥ አስተሳሰባቸውና ንግግራቸው እስከ ድርጊታቻው ተመመሳሳይ መሆኑና ምክንያታዊነትም ሆነ ግላዊ አስተሳሰብ የማይታይባቸው በህብረተሰብ ጫና ስር የወደቁ መሆናቸው ያያሳስበኛል፡፡ብሎግህ በይበልጥ ሶሻላይዜሽን ላይ ስለሚያተኩር ይሄኛውን ፅሁፍህን ብታሰፋው ጥሩ ይመስለኛል አመሰግናለሁ፡፡

  ReplyDelete
 22. yegermal betam tru neger anbebku.

  ReplyDelete
 23. betam yegermal yalawekuten bezu neger terdahu bezihu ketel.

  ReplyDelete
 24. It is amazing . I have finished it with a single breath. Your pen is so blessed . I wished i would be like you and vomit what is going on with my simple mind. It gives us big lessons . we should not import only technologies , we must develop our sight and import institutions and working cultures from China. I am afraid to say that We ethiopians have an artficial love for Ethiopia. we must have a real love and we should dedicate our time , our energy , our money for this poor and higgly impoversihed people. Of course chinese were singing the song of unity for centuries . The chinese rulers were disciples of UNITY and Hard work . Our rulers were devils and are devils.

  ReplyDelete
 25. eskei kaega enegamer bahager bahel lebse mawabe.batalaye lalejochachen eyayone enedadego

  ReplyDelete
 26. UNLIMITED TALK + LIMITED WORK = POVERTY
  UNLIMITED NEED + UNLIMITED WORK = CHINA

  ReplyDelete
 27. betam yegermal yalawokuten bizu neger awkiyalw.

  ReplyDelete
 28. ይመሳሰላል፡፡

  http://www.diretube.com/a-bright-chinese-young-man/wey-china-gud-eko-new-video_1c8bcdb7c.html

  ReplyDelete
 29. THAT IS GOOD,I WILL SHARE

  ReplyDelete
 30. Thank you Danie ..KUM NEGER ENA QELD BE-AND LAY SELAM ALEWU

  ReplyDelete
 31. ይህ እኮ ግልጽ ነው ለህዝቡ የቆመ መንግስት ቢኖር ኖሮ ህዝቡን አሳምኖ አስተባብሮ አደጋግፎ ጠንካራ ታታሪና ልክ እንደ ቻይኖቹ ለሃገራቸው ሟች ያደርግ ነበረ:: ነገር ግን የስልጣንን ወንበር ልክ በስፌት መኪና እነደተሰፉበት ተወዝተው በ20 ዓመት ግዛት ለቻይና ቅኝ ግዛት ዳረጉን:: የቻይና እናት ያደረገችውን ኮንጎ ጫማ በልታ ነው ልጇን ዛሬ ጠንካራ ያደረገችው::

  ReplyDelete
 32. በዘላቂነት በሚጠቅም መልኩ ማሰብ አቁመን በደመ-ነፍስ የምንንቀሳቀስ ፍጡራን ሆነናል፡፡በምክንያታዊነትና በእውነት የምንመራ ህዝቦችና ዜጎች መሆናችንን አቁመን በስሜታዊነት በውዥንብርና በሀሰት የምንመራና የቻይናና የሌላም ሀገር ርካሽ ሸቀጥ አግበስባሽና ማራገፊያ ሆነናል፡፡

  ReplyDelete
 33. አሁንማ እኔ እነሱ አገር የምኖር ያክል ነው የሚሰማኝ እኮ::

  ReplyDelete
 34. We have great appreciation for Peoples and Governments who had given us help through centuries. This is history; no one can change it.
  From Ethiopia, Addis Abeba.

  ReplyDelete