Thursday, October 20, 2011

ለምን እጮኻለሁ?


 ሰሞኑን አንድ መልዕክት በኢሜይል ደረሰኝ፡፡ ካገባሁ ሁለት ዓመቴ ነው ትላለች እኅታችን፡፡ ገና ልጅ አልወለድንም፡፡ እኔ የሚያስጨንቀኝ ልጅ አለመውለዴ አይደለም፡፡ የባለቤቴ ጩኸት ነው፡፡ ምንም ነገር ቀስ ብሎ መናገር አይሆንለትም፡፡ ቁጣ እና ጩኸት የቀን ቀለቤ ሆኗል፡፡ አሁን አሁንማ ካልጮኸ የተናገረ አልመስልሽ እያለኝ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቴ ውስጥ ወንዶች ሲያወሩኝ የጮኹብኝ እየመሰለኝ እሰቀቃለሁ፡፡ አሁን እየፈራሁ የመጣሁት እኔም የርሱ ጠባይ ተጋብቶብኝ ጩኸቱን በጩኸት መመለስ ስለጀመርኩ ነው፡፡ ታድያ እንዴት ብዬ ልዝለቀው? ይላል ጥያቄዋ፡፡

 ባል እና ሚስት በተጋቡ በመጀመርያዎቹ አምስት ዓመታት ሚስት ትጮኻለች ባል ያዳምጣል፡፡ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ደግሞ ባል ይጮኻል ሚስት ታዳምጣለች፡፡ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ግን ሁለቱም ይጮኻሉ ጎረቤት ያዳምጣል የሚል ቀልድ ድሮ ሰምቻለሁ፡፡
ጩኸት የአንድ ወቅት ስሜትን ለመግለጥ ከሆነ ተገቢ ነው፡፡ አንዱ የመግባቢያ መንገድ ነውና፡፡ በጉዳዩ ላይ የሰውዬውን የስሜት ደረጃ እና ውሳጣዊ ሁኔታውን ለመረዳት ያስችላል፡፡ ትኩረት ለመሳብም ይረዳል፡፡ ጩኸት የዘወትር አመል ከሆነ ግን እጅግ በጣም አደገኛ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ጩኸት ከማሳመን ድክመት ሊመነጭ ይችላል፡፡ ሰው የያዘውን አቋም ወይንም ሃሳብ አስረድቶ፣ ተንትኖ እና አብራርቶ ማቅረብ ሲያቅተው መጮኽ ይቀናዋል፡፡ ሰው ሲጮኽ ድምፁ እንጂ ሃሳቡ አይሰማም፡፡ የጡንቻዎቹን ጉልበት እንጂ የሃሳቡን ዐቅም አያሳይም፡፡ ስሜቱን እንጂ ነጥቡን አያመለክትም፡፡ በተለይም ሃሳቡን በትክክል መግለጥ የማይችል ሰው ከመናገሩ በፊት የቁጣ ጥይት አቀባብሎ ነው የሚቀመጠው፡፡ ብዙ ጊዜ ጭንቅላት ባዶ ሲሆን አፍ ይጮኻል፡፡ ከበሮ ለምን ይጮኻል? ቢሉ ውስጡ ባዶ ስለሆነ ነው አይደል የተባለው፡፡
ቁጣ የተቀላቀለበት ጩኸት በበታችነት ስሜት የተነሣ የሚከሰትበት ጊዜም አለ፡፡ ራሱን ከሌሎቹ በታች አድርጎ የሚገምት፣ ማንም አይሰማኝም፣ ይስቁብኛል፣ ያሾፉብኛል፣ ይንቁኛል፣ ሃሳቤን አይቀበሉትም፣ ውድቅ ያደርጉብኛል ብሎ የሚፈራ ሰው ከሃሳብ ልዕልና ይልቅ በቁጣ እና በጩኸት የበላይነቱን ማስመስከር ይፈልጋል፡፡ በተለይም በየቢሮው የሚገኙ እና ከበታች ሠራተኞቻቸው በልምድ፣ በትምህርት ደረጃ እና በእድሜ እናንሳለን ብለው የሚሰጉ አለቆች ይህ ጠባይ ይታይባቸዋል፡፡ ሠራተኞቻቸው ላይ እየጮኹ በማሸማቀቅ ተፈርተው እንዲኖሩ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ገብቶት እና አምኖበት ከሚሠራ ሠራተኛ ይልቅ ፈርቶ እና ተሸማቅቆ፣ ደንግጦ እና በርግጎ የሚሠራ ሠራተኛ ያስደስታቸዋል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ሥልጣናቸውን ማሳየት የሚችሉት በቁጣ እና ጩኸት ይመስላቸዋል፡፡ ልጆቻቸውን ማስበርገግ፣ ሠራተኞቻቸውን ማስበርገግ፣ የትዳር አጋሮቻቸውን ማስበርገግ፣ የሠፈር ልጆችን ማስበርገግ፣ ዓመላቸው ነው፡፡ ገና ከበር ጀምረው መቆጣት ሲጀምሩ «መጡ፣ መጡ» ይባልላቸዋል፡፡ በየቆሙበት እና በየተቀመጡበት ይህንንም ያንንም በቁጣ ሲጮኹበት ያን ጊዜ ሥልጣናቸው አየረ አየራቱን አልፎ የተጓዘ ይመስላቸዋል፡፡ በተለይማ እነርሱ ለተናገሩት ነገር መልስ የሚሰጣቸው ሰው ካጋጠማቸው «ደግሞ ይመልስልኛል/ ትመልስልኛለች» ብለው በረዶ ቀላቅሎ የሚጥለውን ዝናብ ያወርዱበታል፡፡ የተደፈሩ፣ የተዋረዱ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡  
አርድ አንቀጥቅጥ እንደ ለበሱ የአይሁድ ሊቃነ ካህናት ማሸበር እና ማስደንገጥ ይወዳሉ፡፡ ሠራተኛው ሁሉ እንደ ዓባይ ዳር ቄጤማ በፊታቸው ሲብረከረክ ሲያዩት መንበራቸው የጸናላቸው፣ ክብራቸው የተጠበቀላቸው፣ ሥልጣናቸው ከፍ ከፍ ያለላቸው ይመስላቸዋል፡፡
በውስጣቸው ሊደብቁት የሚፈልጉት፣ የሚሸሹት ነገር ያላቸው ሰዎች ከሚደበቁባቸው ምሽጎች አንዱ መጮኽ ነው፡፡ ረጋ ካሉ፣ መወያየት ከጀመሩ፣ ሃሳብ መቀበል ከጀመሩ በውስጣቸው ያለው ነገር የሚታይ ስለሚመስላቸው ይጮኻሉ፡፡ በውስጣቸው ያለው ነገር ኅሊናቸውን ይቆረቁረዋል፡፡ አዘውትሮ ስለሚሟገታቸው ሰው ሁሉ የእነርሱን ያህል ያወቀባቸው ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህም ማናቸውንም ነገር በቁጣ ይዘጉታል፡፡ ከሚቆጣ እና ከሚጮኽ ሰው ጋር መነጋገር የሚወድ የለም፡፡ ቁጣቸው እየተፈራ ዝም ይባላሉ፡፡ እናም ምሥጢራቸው ተደብቆ የሚቀር ይመስላቸዋል፡፡
በጮኹ ጊዜ ሃሳባቸውን በደንብ የገለጡ፣ የተሰሙ እና ነገሩን ያጸኑ የሚመስላቸው ወገኖችም አሉ፡፡ ለእነርሱ በደንብ መንገር ማለት እየጮኹ መንገር ማለት ነው፡፡ ቀስ ተብሎ የተነገረ ነገር እንደ ዋዛ ፈዛዛ የሚታይ ይመስላቸዋል፡፡ ሰው ቁጣቸውን እና ጩኸታቸውን ፈርቶ እሺ እሺ ስለሚላቸው በደንብ የገለጡ እና ያሳመኑ መስሎ ይሰማቸዋል፡፡
ጩኸት ይጋባል፡፡ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከመምህር፣ ከትዳር አጋር፣ ከቤት ሠራተኛ፣ ከሥራ ባልደረባ፣ ከአለቃ፣ ወዘተ ሊጋባ ይችላል፡፡ በሚጮኽበት ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ልጅ መጮኽን የቤተሰብ የመግባቢያ ቋንቋ አድርጎ ይወርሳል፡፡ እንደተጮኸበት ሁሉ እርሱም በተራው ይጮኻል፡፡ ምክንያቱም በቤቱ ውስጥ የመግባቢያው ቋንቋ ጩኸት ሆኖ ኖሯልና፡፡ ከጓደኞቹ ጋር እየተጯጯኹ ማውራትን የለመደ ሰው ያንን ጠባይ ወደ ቤተሰቡ እና የሥራ ቦታው ሊያመጣው ይችላል፡፡ ከትዳር ጓደኞች አንዱ መጮኽ ከጀመረ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሌላኛውም ለተመጣጣኝ ምላሽ ሲል መጮኽ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ግንባርን በግንባር እንደተባለው ጩኸትን በጩኸት መመለስ ይጀመራል፡፡
ለመሆኑ አስረድተነው፣ ነግረነው፣ አሳይተነው፣ አብረነው ሠርተን የማይገባው ሠራተኛ፣ ተማሪ፣ ልጅ፣ ቢያጋጥመን መፍትሔው መጮኽ ነውን? ለአንዳንዶቻችን መጮኽን እንደመፍትሔ እንወስደዋለን፡፡ በጩኸት ሃሳብን መግለጥ እንደ አንድ ዓይነት ሊቀርብ ይችል ይሆናል፡፡ እንደ ብቸኛ የማስረጃ መንገድ ከተወሰደና ያለማቋረጥ ከተደጋገመ ግን ዒላማውን ይስታል፡፡ ያሳየነው ሰው ያናድዳል? አዎ፡፡ ያበሳጫል? አዎ፤ አይገባውም? አዎ፤ አድርቅ ነው? ሊሆን ይችላል፡፡ ታድያ ከዚህ በኋላ በጠብጠን አንግተው፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ በሰውዬው ላይ መጮኽ ግን ሁለት ችግር ያመጣል፡፡
የመጀመርያው ቸግር ሰውዬው መጮኻችንን እየለመደው ሲመጣ ልማዱ ነው ብሎ ይተወናል፡፡ ለጊዜው የሰማን፣ የታዘዘን፣ የገባው መስሎ ከኛ ጩኸት ለመላቀቅ እሺ እሺ፣ ገባኝ ገባኝ ብሎ ከፊታችን ይሄዳል፡፡ በኋላ በልቡ ለብቻው የሚለውን ግን አለመስማት ነው፡፡ የሰጠነውን ሥራም ከመጮኻችን በፊት በሚያውቀው መንገድ ብቻ ነው የሚሠራልን፡፡
ሁለተኛው ችግር ደግሞ እኛን ጯኺ አድርጎ ያስቀረናል፡፡ ውኃን ምን ያናግረዋል ቢሉ ውኃ የማይገባው ድንጋይ አሉ አሉ፡፡ አንዳንዴ የማይገባው እና የማይረዳን ሰው ስናገኝ የማስተማርያ መንገዳችንን ወይንም ራሱን ሰውዬውን መቀየር ይሻላል፡፡ እኛ እየተናደድን በጮኽን ቁጥር የኛ ጠባይ እየተቀየረ ዝምተኞቹ ጯኺዎች ትእግሥተኞቹ ቁጡዎች እንሆናለን፡፡ ሰው ባንድም በሌላም መንገድ መሄዱ ላይቀር ለኛ ግን የማይሄድ ጠባይ ይሰጠናል፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ጩኸትን እንደ ሴፍቲ ቫልቭ የብሶት እና ድካም መተንፋሻ እናደርገዋለን፡፡ ጓደኛው ቢያጠቃው ወደ ሚስቱ ዞረ እንደተባለው በመሥሪያ ቤት፣ በንግድ ሥፍራ፣ በጓደኞቻችን ዘንድ፣ በትምህርት ቤት፣ በስብሰባ፣ በውድድር ወዘተ ላይ ያጋጠመንን ችግር በምንቀርባቸው ሰዎች ላይ በመጮኽ ልንወጣው እንሞክራለን፡፡ አለቃው ሲጮኽበት በበታቾቹ ላይ እርሱም እንደሚጮኽ ባለ ሥልጣን ማለት ነው፡፡ በትዳር ውስጥ ሊወጡት ያልቻሉ እንከን የገጠማቸው አለቆች በሠራተኞቻቸው ላይ በመጮኽ እፎይ ይላሉ፡፡
ያለ ዕረፍት የሚሠራ፣ ከባድ ጫና ያለበት፣ ከብዙ ባለ ጉዳዮች ጋር የሚያገናኝ፣ ጭንቀት የተሞላበት፣ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች አእምሯቸውም ሆነ አካላቸው ድካም ይሰማዋል፡፡ ሰው አእምሮው እና አካሉ በጣም ሲደከም የትዕግሥት መጠኑ ይቀንሳል፡፡ እንዲህ ባለ ሰዓት ማንም እንዲናገረው፣ ማንም እንዲነካው፣ ማንም እንዲተቸው፣ ማንም እንዲሟገተው አይፈልግም፡፡ ያሰበው በፍጥነት፣ የፈለገው ቶሎ፣ የጠየቀው ወዲያው መምጣት ካልቻለ፣ መንገድ ላይ ትዕግሥቱን የሚፈታተን አንዳች ካጋጠመው ድካሙን የሚገልጠው በጩኸት ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለውን ሰው ዕረፍት አግኝቶ በጤናው ሲያዩት እንዴት አመለ ሸጋ መሰላችሁ፡፡
በበሽታቸው ምክንያት ጩኸትን ገንዘብ ያደረጉም አሉ፡፡ ዕረፍት የማይሰጥ፣ ኅሊናቸውን የሚረብሽ፣ ተስፋ የሚያስቆርጥ እና ሰላማቸውን የሚነሣ ሕመም ያለባቸው አንዳንድ ወገኖች የውስጣቸውን ችግር የሚያስታግሡት ሰው ላይ በመጮኽ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ሰው ሁሉ የእነርሱን ችግር መገንዘብ እንዳለበት አድርገው ያስባሉ፡፡ በሕመማቸው ምክንያት ከሁሉም ሰው፣ ርዳታ፣ ቅድሚያ፣ ክብካቤ፣ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ያንን ያጡ ከመሰላቸው በሆነው ባልሆነው ይጮኻሉ፡፡
የቁጣ እና ጩኸት አመል በምንም መንገድ ይምጣ በምንም መንገድ በዋናነት የሚጎዳው ጯኺውን ሰው ራሱን ነው፡፡ ሃይማኖታዊ፣ አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን በራሱ ላይ ያስከትላል፡፡ ጩኸት የትዕግሥትን ማለቅ እና የስሜትን ማየል ስለሚያሳይ ሃይማኖት ከሚጠይቀው ታጋሽነት እና መንፈሳዊ ርጋታ ጋር አይሄድም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ሆኑ የሃይማኖት ትምህርቶች ቁጣን እና ጩኸትን የሥጋዊ ጠባይ ማየል ውጤት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያለ ጠባይ ያለው ሰው ትምህርቱን በሰማ ቁጥር የኅሊና ፀፀት ያድርበታል፡፡ ራሱንም እስከ መጥላት ሊያደርሰውም ይችላል፡፡
ቁጣ እና ጩኸት አመሉ የሆነ ሰው ለጨጓራ እና ለአእምሮ በሽታ የተጋለጠ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም የደም ብዛት በሽታን በማባባስ ራስን እስከማጥፋት ያደርሳል፡፡ ጩኸቱ ቁጣ እየቀላቀለ ያለማቋረጥ ሲሆን ደግሞ ራስን አስቶ አጉል ቦታ ላይ ይጥላል፡፡
ሰው ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት ጩኸቱን እየጨመረ ሲሄድ የትዕግሥቱን ልጓም ይበጥሰዋል፡፡ ያን ጊዜ የሚያደርገውን አያውቀውም፡፡ በጤናው ሊናገረው ቀርቶ ሊሰማው የማይፈልገውን ቃል ከአፉ ያወጣል፤ ሰው ያስቀይማል፤ ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ነገር ይናገራል፤ አንዳንዱ ደግሞ ስሜታዊ ውሳኔ ይወስናል፡፡ ውል ያቋርጣል፤ ትዳሩን ይፈታል፤ ሠራተኛውን ያባርራል፤ ንብረቱን ይሸጣል፤ አንዳንዴም ምሥጢሩን ሳያስበው ያወጣል፡፡
የሚጮኽ ሰው በስሜቱ ቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡ ምክንያቱን ጩኸት ብቻውን አይመጣምና፡፡ ንዴትን እና ጉልበትን አስከትሎ እንጂ፡፡ ጩኸት እነዚህን አስከትሎ ሲመጣ ደግሞ ሰውዬው ሳያስበው ይማታል፤ ዕቃ ይወረውራል፤ ስለት ባላቸው ነገሮች አደጋ ያደርሳል፤ ራሱን ይጎዳል፤ መሣርያ ይተኩሳል፤ እሳት ላይ ይጥላል ወይንም ይወድቃል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ወደ ከባድ ወንጀል ሊያመሩ ይችላሉ፡፡
የሚጮኽ ሰው ማኅበራዊ ከበሬታው እየቀነሰ ነው የሚሄደው፡፡ በጯኺነቱ ቅጽል ስም ይወጣለታል፡፡ ሰዎች እርሱ የሚናገረውን መስማት ሳይሆን ከጩኸቱ መገላገል ነው የሚፈልጉት፡፡ ልጆቹ ይፈሩታል እንጂ አያከብሩትም፡፡ ከእርሱ ጋር መነጋገር ይፈራሉ፤ ሃሳባቸውን አይገልጡለትም፡፡ ይታዘዙታል እንጂ አያፈቅሩትም፡፡ እየባሰ ሲመጣ ደግሞ ቤተሰቦቹ ልባቸው ይደነድናል፡፡ እናም በአንዱ ጆሯቸው ሰምተው በሌላው ያፈሱታል፡፡ ጩኸት ጠባይ ሲሆን ለሰሚው እንደ ሙዚቃ ይቆጠራል፡፡
በተለይ በልጆቻቸው ላይ የሚጮኹ ወላጆች ልጆቻቸውን ድንዝዞች ያደርጓቸዋል፡፡ በመጀመርያዎቹ ወቅቶች ልጆቹ ይደነግጣሉ፤ ቀጥለው ይሸበራሉ፤ ከዚያ ይለምዱትና ይደነዝዛሉ፡፡ ከዚያ በኋላማ እንኳን ጩኸት ድማሚት የማይመልሳቸው ይሆናሉ፡፡
የሚጮኽ ሰው የተሳደበ፣ ያቃለለ፣ ክብር የነካ፣ ሰውንም ያስቀየመ፣ ተደርጎ ስለሚቆጠር ከሰዎች ጋር የመጣላት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምንም እውነት ቢኖረው ጥፋተኛ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እንዲያውም ተንኮለኛ ሰዎች በጯኺነታቸው የታወቁ ሰዎችን ይተነኩሱና እነርሱ ዝም ይላሉ፡፡ እነዚህ በንዴት ሲጮኹ ተመልካች በእነርሱ ላይ ይፈርዳል፡፡ በሕግ ፊትም የሚመሰክርባቸው እንጂ የሚመሰክርላቸው አያገኙም፡፡
ከሚጮኽ ሰው ጋር አብሮ መጫወት፣ አብሮ መሥራት እና አብሮ መኖር የሚፈልግ ሰው ጥቂት ነው፡፡ «ባክህ እርሱ በትንሹም በትልቁም እንደ ቁራ ይጮኻል» እየተባለ ስለሚነገር ሁኔታው ማኅበራዊ መገለልን ያስከትላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ፣ ሰው በአንድ መንደር ውስጥ ተጨናንቆ በሚኖርበት ሀገር፣የጯኺ ጎረቤቱን ቅኝቱ የተበላሸ ዜማ እየሰማ ለመኖር ትዕግሥት ያለው ጥቂት ነው፡፡ የቤት ሠራተኛ አይበረክትለም፤ ቢጤውን፣ ወይንም አምላክ የመረቀውን ካላገኘ በቀር፣ ጯኺ ጓደኛ የለውም፡፡
ታድያ ምን ማድረግ ይሻላል? በቀጣይ እንመለስበታለን፡፡
አሌክሳንድርያ፣ቨርጂንያ

19 comments:

 1. ከሁሉም ነገር ጮሂ ሰዎች አመላቸው ከመጋባቱ በላይ በጣም የሚያስጠላው የመጨረሻው የአመላቸው እድገት ላይ ሲደርሱ ባለጌና ቀወስ መሆናቸው ላይ ነው፡፡

  The danger of single story የሚለው ለምን ተዘጋ እኔ አሁንአላነበብኩትም፡፡

  ReplyDelete
 2. Very important issue which has so many implications on psychology,social interaction and personality. It teaches a lot specially to those Ethiopians who do believe in shouting than convincing.

  ReplyDelete
 3. ቁጣ እና ጩኸት አመሉ የሆነ ሰው ለጨጓራ እና ለአእምሮ በሽታ የተጋለጠ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም የደም ብዛት በሽታን በማባባስ ራስን እስከማጥፋት ያደርሳል፡፡ ጩኸቱ ቁጣ እየቀላቀለ ያለማቋረጥ ሲሆን ደግሞ ራስን አስቶ አጉል ቦታ ላይ ይጥላል፡፡

  ጩኸት ይጋባል፡፡ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከመምህር፣ ከትዳር አጋር፣ ከቤት ሠራተኛ፣ ከሥራ ባልደረባ፣ ከአለቃ፣ ወዘተ ሊጋባ ይችላል፡

  ይሄን ፅሁፍ ሳነብ የራሴ ታሪክ ትዝ ብሎኝ ነው ባንድ ወቅት በዙሪያዬ የነበሩ ሰዎች ዝምታ ወርቅ እያሉ የጠሩኝ ነበር፤ በአግባቡ ምናገር ና ድምፄም ለስለስ ያለ ስለነበር እና እኔ የተናገርኩት ታላላቆቼ ከሚናገሩት የበለጠ የመሰማት ዕድል ነበረው ፤ በቤተሰቤም ትልቅ ክብር ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ከአንድ አብዝታ ከምትጮህ ጓደኛዬ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ከጀመርኩ ወዲህ ሳላስበው ጯሂ ሆንኩ ክብሬን አጣሁ . ድህና ሰው ሲበላሽ ….. ተብሎም ተተረተብኝ ከሁሉም ግን የባሰው ብዙ ጊዜ እራሴን ያመኛል ውስጤ ሰላም ያጣል ፤ እራስ ምታቱ ቋሚ እየሆነ መጣ እና ግራ ገባኝ paracetamol መጠቀም መረረኝ እና አንድ ቀን አባቴ እስኪ ልጄ ስሚኝ ያንቺ እራስ ምታት ሌላ አይደለም የገዛ ጩኸትሽ ነው እሱን ቀንሺና ሞክሪው አለኝ አልታወቀሽም እንጂ መጮህ ከጀመርሽ በኋላ ነው እራስሽን ያመመሽ አለኝ ወዲያው አልተቀበልኩተም ምክኒያቱም ጩኸቴን ተለማመጄው የምጮህ ስለማይመስለኝ ነገር ግን ትንሽ ቆይቼ እስኪ ፀጥታ ያለበት ቦታ እና እኔም ያለልክ የማለወራበት ቦታ ልሂድ ብዬ ወደገዳም ሄድኩ የተወሰነ ጊዜ ተቀመጥኩ በጣም የሚገርመው መጮህና ያለልክ ማውራት ስላቆምኩ ለውጥ ማየት ጀመርኩ ሰላሜን አገኘሁ ከዛ አባቴን እየመረቅሁ ተመለስኩ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ችግሬን ስላወቅሁ ወሬም አላበዛም አልጮህምም እራስ ምታት ቀረ ፡፡ እና ዳኒ እንዳልከው መጮህ የሚጎዳው በመጀመሪያ ባለቤቱን እራሱን ነው ፤ እንደኔ አባት ችግሩን አውቆ የሚመክር ካልተገኘ በስተቀር ጯሂውማ ለምዶት አይታወቀውም እና የሚነገር ሰው ንግግራችንን የሚያርቅ ሰው ቢገኝ መልካም ነው እላለሁ ፡፡ ተባረክ ዲ.ን ዳኒ.

  ReplyDelete
 4. Dear Daniel,

  it is an interesting view:

  ከሚጮኽ ሰው ጋር አብሮ መጫወት፣ አብሮ መሥራት እና አብሮ መኖር የሚፈልግ ሰው ጥቂት ነው፡፡
  «ባክህ እርሱ በትንሹም በትልቁም እንደ ቁራ ይጮኻል» እየተባለ ስለሚነገር ሁኔታው ማኅበራዊ
  መገለልን ያስከትላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ፣ ሰው በአንድ መንደር ውስጥ ተጨናንቆ በሚኖርበት ሀገር፣
  የጯኺ ጎረቤቱን ቅኝቱ የተበላሸ ዜማ እየሰማ ለመኖር ትዕግሥት ያለው ጥቂት ነው፡፡ የቤት ሠራተኛ
  አይበረክትለም፤ ቢጤውን፣ ወይንም አምላክ የመረቀውን ካላገኘ በቀር፣ ጯኺ ጓደኛ የለውም፡፡

  ReplyDelete
 5. Thanks Dani this reality Specail in my office.

  ReplyDelete
 6. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ጥሩ እይታ ነው ነገር ግን ሀሳብን ለመግለጥ ይረዳሉ ብለህ ካሰብካቸው ስዕላት ውስጥ ጸያፍ ስዕሎች አሉ(3ኛው ስዕል) ብታወጣቸው ህጻናት፣ የሃይማኖት አባቶች አና ሎሎችም ሊያነቡች ስለሚችሉ ቢስተካከል ተመሳሳይ ሐሳብን ለመግለጥ የሚረዳ ስዕል አይጠፋምና።

  ኪዳነማርያም ዘደብረ ይድራስ
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  ReplyDelete
 7. ማን ነበር ዝምታ ከጩኸት በላይ ይሰማል ያለው!!!

  ReplyDelete
 8. Dear Dani,
  1. You should have indicated the source of the pictures you posted. That is a copyright issue.
  2. The picture of the insulting mother and kids is not worth posting here.

  With all due respect

  ReplyDelete
 9. አንዳንድ ጊዜ ጩኸት ከማሳመን ድክመት ሊመነጭ ይችላል፡፡ ሰው የያዘውን አቋም ወይንም ሃሳብ አስረድቶ፣ ተንትኖ እና አብራርቶ ማቅረብ ሲያቅተው መጮኽ ይቀናዋል፡፡ ሰው ሲጮኽ ድምፁ እንጂ ሃሳቡ አይሰማም፡፡ የጡንቻዎቹን ጉልበት እንጂ የሃሳቡን ዐቅም አያሳይም፡፡ ስሜቱን እንጂ ነጥቡን አያመለክትም፡፡ በተለይም ሃሳቡን በትክክል መግለጥ የማይችል ሰው ከመናገሩ በፊት የቁጣ ጥይት አቀባብሎ ነው የሚቀመጠው፡፡ ብዙ ጊዜ ጭንቅላት ባዶ ሲሆን አፍ ይጮኻል፡፡ ከበሮ ለምን ይጮኻል? ቢሉ ውስጡ ባዶ ስለሆነ ነው አይደል የተባለው፡፡

  ReplyDelete
 10. THis NOT FOR SELL...BUT..I DON'T SEE ANY COPYRIGHT ISSUE...THEN U GOING TO SAY DON'T SHARE FORM GOOGLE AND POST IT TO A FACEBOOK..AND WRITE A "COPYRIGHT(c)"...

  ReplyDelete
 11. ሰላም ዳኒ አንዳድ መምህራን በትምህርታቸው ጣልቃ ጩኸት ባንለውም የጎላ loud ድምጽ ያስተጋባሉ. በተለይ በመንፈሳዊ ትምህርት. ይህ ከምን የሚመነጭ የመስልሃል? እውን አግባብ ነውን? የድምጽ ማጉያው መሸከም እስኪያቅተው ድረስ የሚጮሁም አይጠፉም ምን አለ ቀስ ብላችሁ ብትመክሩን ......
  ReplyDelete
 12. ባል እና ሚስት በተጋቡ በመጀመርያዎቹ አምስት ዓመታት ሚስት ትጮኻለች ባል ያዳምጣል፡፡ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ደግሞ ባል ይጮኻል ሚስት ታዳምጣለች፡፡ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ግን ሁለቱም ይጮኻሉ ጎረቤት ያዳምጣል

  ReplyDelete
 13. It is an interesting expression.God bless you!!

  ReplyDelete
 14. tilik tmhirt new ....

  ReplyDelete
 15. ''ውኃን ምን ያናግረዋል ቢሉ ውኃ የማይገባው ድንጋይ አ አሉ

  ReplyDelete
 16. may THE WHOLLY TRINITY BLESS YOU WITH MORE WISDOM. it is a good lesson. this story has a big relation with my family my mother shouts almost every time. and sometimes i worry that all children's might become like her. now i got a big lesson how to avoid that. thank you!!1

  ReplyDelete
 17. Dear Dani... oh i dont really know what i should say and i know no one is perfect but ur very close to that, how do you see the angles? where are u standing to see? am just crazy how u see things...wow please go go go ...ur so Ethiopian and real picture of what we should be as human and ethiopian...thankx

  ReplyDelete