Monday, October 17, 2011

የዘረኛነት ወረርሽኝ

to read in pdf click here 
ሰሞኑን አንድ የንግድ ተቋማት ማስተዋወቂያ ቡክሌት ደርሶኝ ተገርሜ እያየሁት ነው፡፡ መጽሔቱ ክርስቲያን ነጋዴዎችን የያዘ መሆኑን ገና ከመግቢያው ል፡፡ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ሊረዳዱ እንደሚገባ፣ የጌታ ልጆች በአንድነት መኖር እንዳለባቸው፣ ከዚያም አልፎ አንዱ ከሌላው በመግዛት ወይንም በመጠቀም ወንድማማችነትን እንዲያሰፍኑ፣ ያም ለምድሪቱ በረከት መሆኑን በጥቅስ እያዋዛ ይገልጣል፡፡
እየገረመኝም እየደነገጥኩም ነበር ያነበብኩት፡፡ በኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዘረኛነት ይህንን ያህል ሥር ሰድዷል ማለት ነው? አልኩ ለራሴ፡፡ ለመሆኑ ይህቺ ሀገር በስንት ዓይነት ዘረኛነት እንድትሰቃይ ይሆን የተፈረደባት? ስልም ጠየቅኩ፡፡ ዛሬ በዚያች ሀገር «ገንዘባችን በየክልላችን» ብቻ ሳይሆን በየቋንቋችንም በመግባት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሚለው እየቀረ የኦሮምያ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የትግራይ፣ የሶማልያ ባንኮች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ደግሞ በይፋ ስማቸውን ባይገልጡም በአንድ እምነት ሥር ያሉ ሰዎችን ብቻ በአክስዮን የሚያሰባስቡ ባንኮችም እየታዩ ነው፡፡

 ዘረኛነት ማለት እንዴው በቀላሉ ሲገለጥ አንድን ሰው በዕውቀቱ፣ በችሎታው፣ በዐቅሙ፣ በትምህርት ደረጃው ወይንም በሌላ መለኪያ ሳይሆን በወገንተኛነቱ ብቻ መመዘን ማለት ነው፡፡ ወይንም ደግሞ ወገንተኛነትን ከሌሎች መለኪያዎች ሁሉ አልቆ መመልከት ማለትም ይሆናል፡፡
ሀገርሽ ወዴት ነው ብዬ ብጠይቃት
ከም ከም ብላ ሳቀች ነገሩ ቢደንቃት አይደለ ብሂሉ
ዘረኛነት ለአንዲት ሀገር በሽታዋ ሲሆን ነገሮችን ሁሉ በግለሰባዊነት ወይንም ደግሞ በጋራ ጥቅሞች እና አስተሳሰቦች ሳይሆን በአንዳች የቡድን መልክ ብቻ ማየት ይጀመራል፡፡ ዘረኛነት በመወለድ እና በክልል፣ በጎሳ እና በሀገር ልጅነት ብቻ የሚከሰት አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ መልከ ብዙ ገጽታ ነው ያለው፡፡ የጎሳ፣ የፓርቲ፣ የሃይማኖት፣ የማኅበር፣ የሠፈር፣ ወዘተ ዓይነት ዘረኛነቶች አሉ፡፡
የጎሳውን ዓይነት ዘረኛነት በውጭም በውስጥም ያለን የዚህች ሀገር ሰዎች ጠግበነዋል፡፡ የት ተማርክ? ከሚለው ይልቅ የት ተወለድክ? የሚለው ጥያቄ አሰልችቶናል፡፡ ምን ትችላለህ ሳይሆን ምን ትናገራለህ? ሆኗል መመዘኛችን፡፡ አንድ ሰው የእገሌ ጎሳ አባል በመሆኑ ምክንያት ይወደዳል፣ ይጠላል፡፡ ይከበራል፣ ይናቃል፡፡ ሥራ ያገኛል፣ ሥራ ያጣል፡፡ ይኮራል፣ አንገት ይደፋል፡፡ ዕድል ይከፈትለታል፣ ዕድል ይዘጋበታል፡፡ ይሾማል፣ ይሻራል፡፡
ሳቅና ጨዋታ ዝና ካማራችሁ
እንደኛ እንትን ላይ በተወለዳችሁ
የሚለው ዘፈናችንኮ ጤነኛ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሳቅ፣ ጨዋታ እና ዝናን ለማግኘት አትችሉም እያለን ነው፡፡ ለምን ብንለው ከኛ ሀገር አልተወለዳችሁማ፤ ምን አማራጭ አለን፡፡ መልሰን አንወለድ፡፡
ሌላ ቋንቋ ሲሰሙ ጆሯቸውን የሚያሳክካቸው፤ ፊታቸው የሚለዋወጥ፣ ንዴት ንዴት የሚላቸው እንዳሉ ሁሉ፤ ያንን ቋንቋ ሲሰሙ ቸርነታቸው ሁሉ የሚከፈት፣ መስተንግዷቸው የሚሟሟቅ፣ አድሏዊነታቸው የሚጨምርም አሉ፡፡
የጎሳ ዘረኛነት ሥር ከመስደዱ የተነሣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ እና ለማግባባት ከምንሠራው ሥራ ይልቅ ልዩነታቸው እንዲገባቸው የምንሠራው ሥራ ይበልጣል፡፡ እንደ ኢትዮጵያን በመሰለች ብዙ ቋንቋዎች በሚነገርባት ሀገር አንድ ተማሪ ከሥራ ቋንቋ ውጭ የራሱን አካባቢ ቋንቋ ብቻ ነው የሚማረው፡፡ ከዚያ ውጭ የሚማረው እንግሊዝኛ ነው፡፡ ከአካባቢው ቋንቋ ውጭ ያለውን የሚያስተምሩት መምህራንም አንዳንድ ጊዜ የጠላት ሀገር ቋንቋ የሚያስተምሩ ይመስል ወይ  እነርሱ በግዴለሽነት  ያስተምራሉ አለያም አካባቢያቸው በንቀት ያያቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሕዝብ የሚናገራቸው ቋንቋዎች አሉ፡፡ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛን የመሰሉ፡፡ አንድ ተማሪ ከአካባቢው ቋንቋ በተጨማሪ ቢቻል ሌሎች ሁለት ካልተቻለም አንድ የሌላ አካባቢ ቋንቋ መርጦ እንዲማር ቢደረግ እንዴት መልካም ነበር፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ጥላቻውን ያስቀረዋል፡፡ ሰው የሚያውቀውን ነገር የመጥላት ሁኔታው ዝቅተኛ ነውና፡፡ በሁለተኛ ደረጃም ያግባባናል፡፡ አንዳንዴኮ ከተወለድንበት እና ካደግንበት ክልል ውጭ መሄድ ውጭ ሀገር እንደመሄድ እየሆነብን ነው?
አንድ የሶማሌ ሰው (6.0% ተናጋሪ አለው) አማርኛ (32.7% ተናጋሪ አለው) እና ኦሮምኛ (31.6% ተናጋሪ አለው) ቢችል ከስድሳ በመቶ በላይ ከሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ይግባባል ማለት ነው፡፡ ይህም አንዱ ወደ ሌላው ሄዶ የመሥራት፣ ተጋብቶ እና ተዋልዶ የመኖር ብሎም ከሌላው ወገኑ ጋር ልብ ለልብ የመግባባት ዕድሉን ይጨምረዋል፡፡ እንግሊዝኛ በትምህርት ቤቶቻችን ያለውን ክብር ግማሽ ያህል የሀገራችን ሌሎች ቋንቋዎች የላቸውም፡፡
ይህንን አመለካከት ቀርፈው ሕዝቡን ልዩነት ወደሚከበርበት አንድነት ያመጡታል የሚባሉት የፖለቲካ ልሂቃንም ራሳቸው ዘውገኞች ሆነዋል፡፡ አብዛኞቹ ፓርቲዎቻችን ጎሳን ወይንም አካባቢን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ያንን ፓርቲ በአሠራሩ፣ በአመለካከቱ እና በፖለቲካ ፕሮግራሙ ብትወዱት እንኳን እንደገና እዚያ ክልል ገብታችሁ ለመወለድ ባለመቻላችሁ ብቻ ከአባልነት ትታቀባላችሁ፡፡
የሀገሬ ሰው «መወለድ ቋንቋ ነው» የሚለው እዚህ ላይ አይሠራም፡፡ መወለድ እኛ ሀገር ቋንቋ ብቻ አይደለም፡፡ ፓርቲም፣ ሥራም፣ ሹመትም፣ ገንዘብም፣ መሬትም፣ ርእዮተ ዓለምም ጭምር ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አንድን ወገን ነጻ የሚያወጡ አያሌ ድርጅቶች አሉን በሀገራችን፡፡ ማን ማንን ከማን ይሆን ነጻ የሚያወጣው? አማራው ከትግሬው፣ ትግሬው ከአማራው፣ ኦሮሞው ከአማራው፣ አማራው ከኦሮሞው ነው ነጻ የሚወጣው? እየተጨቋቆንን ነው የምንኖረው ማለት ነው?
አንዳንዶቹ ፓርቲዎች እኛ ሕዝቡን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነው ነጻ የምናወጣው ይላሉ፡፡ መቼም ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነጻ መውጣትን የሚጠላ የለም፡፡ ግን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነጻ ለመውጣት የግድ ነጻ አውጭ ፓርቲ ያስፈልገናል? በዓለም ላይ ራሳቸውን ከድህነት አረንቋ ያወጡ ሕዝቦች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በነጻ አውጭ ፓርቲዎች ነው እንዴ ነጻ የወጡት?
ፓርቲዎቻችን የጎሳ ዘረኛነትን ብቻ አይደለም የፓርቲ ዘረኛነትንም መላቀቅ አልቻሉም፡፡ ከራሴ ፓርቲ አባል ውጭ ያለው ሁሉ ስሑት፣ ፀረ ልማት፣ ጨቋኝ፣ አንድነትን የሚያናጋ፣ አገር አጥፊ፣ ጠላት፣ ከሀዲ፣ ለሀገር የማይጠቅም ነው ብሎ ማሰብ ነው የፓርቲ ዘረኛነት፡፡ ሰውን በፓርቲ አባልነቱ ብቻ ማድነቅ፣ መውደድ፣ መሾም እና ማግነን ነው የፓርቲ ዘረኛነት፡፡ ሰውን በፓርቲ አባልነቱ መጥላት፣ ማነወር፣ ማራቅ እና ማግለል ነው የፓርቲ ዘረኛነት፡፡
በርግጥ በአሁኑ ጊዜ በሕዝባችን ዘንድ ሰውን ብቻውን ማየት ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰው በቡድን ውስጥ ነው የሚታሰበው፡፡ በፓርቲው፣ በጎሳው፣ በእምነቱ፣ በክልሉ፣ በሚኖርበት አካባቢ፣ በሥራ ዓይነቱ፣ ነው የሚታየው፡፡ እገሌ ሳይሆን እነ እገሌ የሚለው ድምፅ ነው የሚሰማው፡፡
ከምድራዊ ነገር ይልቅ ሰማያዊውን የሚሰብኩት፣ ፍቅር እና ሰላም ዋና አጀንዳዎቻቸው የሆኑት የእምነት ተቋማት እንኳን ሳይቀሩ በዘረኛነት አረንቋ ውስጥ ሰምጠውበታል፡፡ በአንድ በኩል የእምነት ዘረኛነት በሌላ በኩል ደግሞ የጎሳ ዘረኛነት እያላጋቸው ነው፡፡
አንድ ሰው በንግዱ፣ በአገልግሎቱ እና በሞያው መመረጥ ያለበት ባለው ችሎታ፣ ዐቅም እና ጥራት መሆን ነበረበት፡፡ አሁን አሁን ግን የኛው እምነት ሰው መሆኑ የበለጠ ቦታ እየተሰጠው መጥቷል፡፡ ሙስሊሙ ሙስሊሙን ነጋዴ፣ ክርስቲያኑም ክርስቲያኑን ነጋዴ እንዲመርጡ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎች እየወጡ ነው፡፡ ከዚያም አልፈው የንግድ እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በሃይማኖታቸው ዘውግ ብቻ ከፍለው ከእነዚህ ብትገዛ ይመረጣል እያሉን ነው፡፡ ገንዘባችን በየእምነታችን እንዲሆን እየተሰበክን ነው፡፡
ትምህርት ቤቱ ጥራቱ እንዴት ነው? የሚለው ቀርቶ ሙስሊም ነው የከፈተው ወይስ ክርስቲያን? ኦርቶዶክስ ነው የከፈተው ወይስ ፕሮቴስታንት ሆኗል ጥያቄው፡፡ መርፌውን በየእምነታችን ሊወጉን የተዘጋጁ የሕክምና ተቋማትም ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ለመቀጠር የአንድ እምነት ተከታይ መሆን ብቻ ከትምህርትም፣ ከልምድም በላይ ዋጋ ሲኖረው እያየን ከመገረም አልፈን ለምደነዋል፡፡
የእምነት ተቋማቱ ከዚህም አልፈው የጎሳውን ዘረኛነት የሚያባብሱ ተቋማትም ሆነዋል፡፡ ጎጃሜ ጎጃሜውን፣ ጎንደሬ ጎንደሬውን፣ ትግሬ፣ ትግሬውን፤ ኦሮሞ ኦሮሞውን፣ ወሎ ወሎዬውን ሲስበው ማየት ለተቋማቱ ቅርብ ለሆነው ብቻ ሳይሆን ርቆ ላለው ምእመናቸውም የዕለት ዜና ሆኖለታል፡፡ የአንደኛው ወገን በእምነት ተቋማቱ የሥልጣን እርከን በወጣ ቁጥር፣ የእምነቱን ተከታዮች ከማብዛት ይልቅ የወንዙን ልጆች ማብዛት ዋናው ተልዕኮው እየሆነ ነው፡፡
መካ ላይ አላሁ አኩበር ያለው ቢላል ኢትዮጵያዊ እንጂ ሳዑዲያዊ አለመሆኑ ተረስቷል፡፡ ደብረ ዳሞ ላይ የሚከብሩት አቡነ አረጋዊ የአውሮፓ ሰው እንጂ ኢትዮጵያዊ እንዳልነበሩ ተዘንግተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሰውን በሰውነቱ ብቻ ተቀብለው የሚያስተናግዱበት፣ በእምነቱ ከመሰላቸው ሀገራቸውን ሀገሩ አድርገው የሚሰጡበት ዘመን እንዳይቀር ያሰጋል፡፡
ስንቶች ከሌላ ክልል ብቻ ሳይሆን ከሌላ ሀገር መጥተው፣ ትውልዳቸውንም ረስተው ኢትዮጵያውያን ሆነው ቀርተዋል፡፡ «እኔስ በሀገሬ እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ» ነበር የምንለው፡፡ ዛሬ ይሄ ተረት ሊሆን ነው መሰለኝ፡፡ አቡነ አረጋዊን ትግሬ፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስንም አማራ አድርጎ የሚያይ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ሁለቱም ግን እንኳን እና ትግሬ እና አማራ ኢትዮጵያዊም አይደሉ፡፡
ልጁ ሊቀጠር ወደ አዲስ አበባ ይመጣል፡፡ ታድያ መካሪዎች «ስትሄድ ጳጳሱ የሀገራቸውን ሰው ይቀጥራሉና ሀገርህ የት ነው ካሉህ ያንተን አትናገር የርሳቸውን ሀገር ተናገር» ብለው ይነግሩታል፡፡ ታድያ ጳጳሱ ፊት ሲቀርብ የሀገራቸው ስም ጠፋው አሉ፡፡
እንደገባ የተነገረው አልቀረም
«ሀገርህ የት ነው አሉት
«የርስዎ ሀገር» አላቸው፡፡
«የኔ ሀገር የት ነው አሉት
«ከኔ ሀገር» አላቸው አሉ፡፡ ምን ያድርገው፡፡
አንዳንዶችማ ከዚህም ወርደው ወርደው የቆብ ዘረኛነትም ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሕጋውያን ካህናት ከታላላቅ አድባራት አስተዳዳሪነት እንዲወገዱ ዐዋጅ ያወጣው ማን ይሆን? ዛሬ ለሹመት ዋና መመዘኛው መመንኮስ ሆነና «መነኮሰ ሞተ» የሚለው ትርጓሜ «መነኮሰ በላ» ወደሚለው ዞረ፡፡ በዚህ የቆብ ዘረኛነት ምክንያትም መመንኮስ የሌለባቸው ለሥራ እና ለሹመት ሲሉ እንዲመነኩሱ አንዳንዶችም ሚስቶቻቸውን ደብቀው እንዲመነኩሱ አደረግናቸው፡፡ በተለይም የውጩ ሀገር ዕድል ሁሉ ከሕጋውያን ይልቅ ለመነኮሳቱ እጅግ ክፍት እየሆነ ሲመጣ፣ ያልገባቸው እና ያልተገባቸው መነኮሳት እየበዙ መጡ፡፡
ከዚህም አልፎ ምንኩስናዊ ሕይወቱ ሳይሆን የት መነኮሰ? የሚለው የዘረኛነት መለኪያ እየሆነ ነው፡፡ እናም የት ብመነኩስ የምንኩስናን ተጋድሎ እፈጽማለሁ? መባሉ ቀርቶ የት ብመነኩስ ቶሎ ሹመት አገኛለሁ? ሆነ ጥያቄው፡፡
«የኛ ልጆች» የሚሉ የማኅበርተኞችን የዘረኛነት ቋንቋስ ሰምታችሁ አታውቁም፡፡ ዛሬ ዛሬ አያሌ ማኅበራት እየተፈጠሩ ነው፡፡ የሃይማኖት፣ የጉዞ፣ የሞያ፣ የበጎ አድራጎት፣ የክብካቤ፣ የሌሎችም ማኅበራት፡፡ አንድን ሥራ ለማከናወን አንድነት መፍጠሩ መልካም ሆኖ ሳለ ዘረኛነቱ ግን ከፋ፡፡ «እንዲህ ሲል ያውካል» አለ ተርጓሚ፡፡ የሰውን ስሕተተኛነት እና ትክክለኛነት ከማኅበራቸው አባልነት አንፃር ብቻ የሚተነትኑ ማኅበርተኞች አሉ፡፡
ይህን የመሰለ ቁመና ይዘሽ
ምናለ ፈጣሪ የኛ ባረገሽ
የሚለው ሀገርኛ ዘፈን ትርጉሙ የገባኝ አሁን ነው፡፡
ምን መልካም ብትሠሩ፣ ምን ተአምር ብትፈጽሙ እነርሱ ከገቡበት ካልገባችሁ ሥራችሁ ሁሉ የመርገም ጨርቅ ይሆናል፡፡ ምን ተሠራ? ሳይሆን ማን ሠራው? ነው ለእነርሱ ቁም ነገሩ፡፡ በማኅበር ይወዳሉ፣ በማኅበር ይጠላሉ፣ በማኅበር ያቀርባሉ፣ በማኅበር ያገላሉ፣ በማኅበር ያጸድቃሉ፣ በማኅበር ይኮንናሉ፣ በማኅበር ይረዳሉ፣ በማኅበር ይነፍጋሉ፡፡ አባል ከሆናችሁ ሁለት እና ሁለት አምስት ይሆንላችኋል፤ አባል ካልሆናችሁ ግን እንኳን አምስት አራት አይሆንላችሁም፡፡
በጎ ነገር ስትሠሩ ካዩዋችሁ ሊያበረታቷችሁ እና ሊያግዟችሁ አይደለም የሚፈልጉት፤ ሊያደንቋችሁ እና ሊያመሰግኗችሁ አይደለም የሚተጉት፤ አባል ሊያደርጓችሁ እንጂ፡፡ ምክንያቱም ከማኅበራቸው ውጭ በጎ ነገር ሲሠራ ማየት ስለማይፈልጉ፡፡
ዘረኛነት የሁላችንም ጠባይ እየሆነ ነው፡፡ ከጎሳው ብናመልጥ፣ ከፓርቲው፣ ከፓርቲው ብናመልጥ ከእምነቱ፣ ከእምነቱ ብናመልጥ ከማኅበሩ ጎጠኛነት ውስጥ መገኘታችን አልቀረም፡፡ ይህ ሁሉ ሰዎች በሥራቸው፣ በሞያቸው፣ በልምዳቸው፣ በችሎታቸው፣ በዐቅማቸው፣ በጥንካሬያቸው፣ በትጋታቸው እና በጥረታቸው ሳይሆን በአንዳች ወገንተኛነታቸው እንዲመዘኑ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ወልጋዳ ሚዛን ደግሞ ወዳጆችን እንጂ ጎበዞችን፣ ወገንተኞችን እንጂ ሊቆችን ዕድል አይሰጥም፡፡
አገር የምታድገው በብርቱ ባለ ሞያዎች፣ በተመራማሪ ወጣቶች፣ በለውጥ አምጭ ምሁራን፣ በችግር ፈቺ የፈጠራ ሰዎች፣ በሥጋት ሰባሪ ነጋድያን፣ በሃሳብ አመንጭ ሊቆች እንጂ በተሰባሰቡ ወገንተኞች አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን በየወገናችን ለሺ ዓመታት ያህል ተሰባስበን አልነበር?
አሌክሳንድርያ፣ ቨርጂንያ

64 comments:

 1. አንዳንዶቹ ፓርቲዎች እኛ ሕዝቡን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነው ነጻ የምናወጣው ይላሉ፡፡ መቼም ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነጻ መውጣትን የሚጠላ የለም፡፡ ግን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነጻ ለመውጣት የግድ ነጻ አውጭ ፓርቲ ያስፈልገናል? በዓለም ላይ ራሳቸውን ከድህነት አረንቋ ያወጡ ሕዝቦች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በነጻ አውጭ ፓርቲዎች ነው እንዴ ነጻ የወጡት?

  . . . አገር የምታድገው በብርቱ ባለ ሞያዎች፣ በተመራማሪ ወጣቶች፣ በለውጥ አምጭ ምሁራን፣ በችግር ፈቺ የፈጠራ ሰዎች፣ በሥጋት ሰባሪ ነጋድያን፣ በሃሳብ አመንጭ ሊቆች እንጂ በተሰባሰቡ ወገንተኞች አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን በየወገናችን ለሺ ዓመታት ያህል ተሰባስበን አልነበር?

  D/n Daniel Egziabiher Yistlin. Girum Eyita new. Lemiyastewul Ejig betam astemarina mekari Lehager ediget amelakach meftihem new.

  ReplyDelete
 2. Daniye
  Is this problem in Ethiopia only or where ever the world?
  yours

  ReplyDelete
 3. ዑዑዑዑ…. እነዚህንም እቃወማለሁ/እንቃዋማለን ለሀገራችንም፤ ለእምነታችንም፤ ለነፍሳችንም፤ ለስጋችንም አይጠቅምምና፡፡ ዳኒ አመሰግንሀልሁ ፤ ዑዑዑ…ማን ይሆን ሳንጠፋፋ ይህችን ሀገር የሚታደጋት፡፡ ምንስ ብናደርግ ይሻል ይሆን…

  ሐብታሙ ከ አዋሳ

  ReplyDelete
 4. ሰሚ ጆሮ ካለ ዳኒ!መልእክትህ ያስደስታል፡፡ ነገር ግን በእንደዚህ ዓይነት ልክፍት ውስጥ ያለ ሰው ይህንን የሚያዳምጥበት ጆሮ፣ የሚያስተውልበት አዕምሮ የለውም፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ይህ ወረርሽኝ ህዝብና አህዛብን አንድ ያደረገውን ክርስቶስን እንሰብካለን በሚሉት የሃይማኖት ተቋማትም ጎልቶ መታዬቱ ነው፡፡ ለማንኛውም የሚያስተውል ልቡና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲሰጥ ብርቱ ልመና ይጠይቃል፡፡ ይህ ወረርሽኝ የተማረ ወጣት፣ የሰለጠነ ጣት አለባቸው በሚባሉት የክፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይም ጥላውን አጥልቷል፡፡ መምህራኑ በአብዛሐኛው ወደ ተወለዱበት አካባቢ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በቅጥር፣ በዝውውር ይጎርፋሉ፣ተማሪውም እንዲሁ...
  ዘረኝነት ቀርቶ ከዚህ በኋላ አንድነት ይመጣ ይሆን?...
  ደብረ ማርቆስ

  ReplyDelete
 5. በስንቱ ልበጥበጥ አለች በሶ!!!!

  ReplyDelete
 6. ዘረኛነት የሁላችንም ጠባይ እየሆነ ነው፡፡ ከጎሳው ብናመልጥ፣ ከፓርቲው፣ ከፓርቲው ብናመልጥ ከእምነቱ፣ ከእምነቱ ብናመልጥ ከማኅበሩ ጎጠኛነት ውስጥ መገኘታችን አልቀረም፡፡ ይህ ሁሉ ሰዎች በሥራቸው፣ በሞያቸው፣ በልምዳቸው፣ በችሎታቸው፣ በዐቅማቸው፣ በጥንካሬያቸው፣ በትጋታቸው እና በጥረታቸው ሳይሆን በአንዳች ወገንተኛነታቸው እንዲመዘኑ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ወልጋዳ ሚዛን ደግሞ ወዳጆችን እንጂ ጎበዞችን፣ ወገንተኞችን እንጂ ሊቆችን ዕድል አይሰጥም፡፡

  Well said, ዘረኛነት የሁላችንም ጠባይ ስለሆነ, change has to start from us, me; not from that party or from somebody else.

  Thanks dani, tebarek.
  May GOD be with us.

  ReplyDelete
 7. egzer yerdan new lela men yebalal.

  ReplyDelete
 8. I hate ..ዘረኛነት!.."Erse beraschu Betnekakesu,Ere beraschu Endatetefaffu Tetenkeku.."..bible

  ReplyDelete
 9. by this problem many our peoples are affected
  thank you brother

  ReplyDelete
 10. Amazing analysis of the "reality".

  I am afraid there is a bit of "generalization with the danger of single story" in your write-up. For example, if I decline to put my child in a protestant school , am I being racist ? To answer this question, you have to first agree with me that schools run by religious organizations will have additional time (subject)for religious teaching that I may not want to expose my child to. Are they also racist for doing this? Is that not what they exist for as a religion? Do they have to teach about other religions to be non-racist?

  What about the saying that goes, " tell me who your companion is and then I will tell you who you are" ? Is that being racist? What does the bible say about this?

  Do I have to disclose to everyone everything that I share with my members ? Then I shouldn't have in the first place be a member of an organization or a cause. I know your point is not against having common visions as groups but not to discriminate people in joining such a group based on racial status. But still your article have incorporated certain issues that could be interpreted in more of "the danger of a single story" ways.

  The overall message of your article is quite inspirational. Unfortunately, I doubt if it can be achieved in ideal ways you tried to portray. I don't think it is a problem of Ethiopia only as such problems arise because of people's differing worldviews. But I hope your message will help ameliorate those issues grossly unacceptable to the nation as a whole such as promoting trading among religious groups only. Such things have to be condemned with the strongest possible words and actions.

  Remain blessed!

  ReplyDelete
 11. ዲያቆን ዳንኤል እግዚአብሔር ይስጥልን የአገልግሎት ዘመንህን ያብዛልን
  በእውነት ትልቅ ነገር አልክ በጣም እውነት እና እውነት የሆነ ነገር እስቲ ለሁላችንም በብሔር፣ በጎሳ፣ በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ የማይከፋፍለው ሁሉን ቻይ አምላክ ልቦና ይስጠን አሜን
  በ. . . አገር የምታድገው በብርቱ ባለ ሞያዎች፣ በተመራማሪ ወጣቶች፣ በለውጥ አምጭ ምሁራን፣ በችግር ፈቺ የፈጠራ ሰዎች፣ በሥጋት ሰባሪ ነጋድያን፣ በሃሳብ አመንጭ ሊቆች እንጂ በተሰባሰቡ ወገንተኞች አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን በየወገናችን ለሺ ዓመታት ያህል ተሰባስበን አልነበር? ይህች ፅሁፍ ለሚገባው እውነትና ሐቅ ናት፡፡

  ReplyDelete
 12. woyanie yametaw tata new

  ReplyDelete
 13. እሺ መፍትሄው ምንድን ነው ዲ/ን ዳንኤል? ምን ብናደርግ ነው ይህንን የዘረኝነት አባዜ የምገድበው? ዛሬ ይህን ሰማን ነገ ደግሞ ውጤቱን እናያለን:: ብለን ነበር ተናግራን ነበር ለማለት ነው ውይስ ምንድነው? የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት ልባቸውን የሰበራቸው ቀራጮች እሺ ምን እናድርግ አሉት ይላል መፀሀፍ ቅድስ:: እሺ ምን እናድርግ? የዚህ ትውልድ ድርሻ ምንድነው? የእኔስ ድርሻ ምንድነው ? ምን ላድርግ? ዛሬም በተረትና በምሳሌ ነው ሊነገረን የሚገባው? መቼ ነው ድርጊት የሚጀመረው? ማወቅ ከሁሉም በፊት መልካም ነው :: እሺ አወቅን ከዚያስ ማወቅ ብቻውን እኮ አያድንም? ስለዚህ ምን እናድርግ? ለውጥ የሚመጣው እንዴት ነው? እንደ ሜትሮ ሎጂ ነገ ጎርፍ ሊሆን ይችላል እያልከን ነው? ስለዚህ መርከብ ስሩ አትለንም? የጥፋት ውሃ ይመጣል ማለት ብቻ ምን ዋጋ አለው:: እንዴት ነው መርከቡን የምንሰራው? ስፋቱ ርቀቱ ቁመቱ ስንት ነው? ስንት ሰው ሊይዝ ይችላል? አትነግረንም? መርከቡ ከምን ይሰራል? ስንት ክፍል ይኖረዋል? አዎ ጥፋት ሊመጣ ይችላል:: ስለዚህ ምን እናድርግ? ስለዛች ሀገርና ህዝብ ስናስብ እና የምትፅፈው ፅሁፍ ስናነብ እንዲሁም እየሆን ያለው ሁናቴ ስናይ እኮ እንረበሻለን:: ስለዚህ እኛ ምን እናድርግ? መንግስት ምን ያድርግ? የተቃዋሚ ፖርቲዎች ምን ያድርጉ? የሀይማኖት አባቶች ምን ያድርጉ? ቤተ ክርስቲያን ምን ታድርግ? ምዕመናን ምን ያድርጉ? ይህን ለማድረግ መሰባሰብ ነው ያለብን? ፓርቲ ነው ማቋቋም ያለብን? ደመናን አይቶ ዝናብ ሊዘንብ ይችላል ማለት እኮ ይቻላል:: ግን የተሰጣ ነገር አስገቡ:: እንዲህ አድርጉ ወይንም እንዲህ እናድርግ:: በጋር እንዲህ እናድርግ በተናጥል ደሞ ያንን እናድርግ የሚለን ማን ነው? ማንን እንጠብቅ?

  ReplyDelete
 14. So nice article as usual. Keep up bringing light to this blind world. We often see and live in a limited distance and circle.
  «ሀገርህ የት ነው?» አሉት
  «የርስዎ ሀገር» አላቸው፡፡
  «የኔ ሀገር የት ነው?» አሉት
  «ከኔ ሀገር» አላቸው አሉ፡፡ This one made me laugh loud.

  Thank you and May God Bless You more.
  Yours

  ReplyDelete
 15. Dear Daniel,

  I believe in the unity in diversity mind set up. No one can deny that we come from different background. One thing that I agree with you we should work hard to narrow our difference and brought a national thinking.

  ReplyDelete
 16. ወንድም ዳንኤል ዘረኝነትና ወገንተኝነት ጤናማ በሆነ መልኩ ሲታይ ከራሱ የሆነ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ህግጋት አንፃር የራሱ የሆነ ጥቅም እንዳለው አንተም በደንብ ይገባሃል፡፡
  ማለትም በአላማና በአስተሳሳብ መቀራራብ ህይወትን በመልካም መስመር ለመምራትና ለመኖር ማለት ነው፡፡ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን ከሌላው ክርስቲያን ጋር በአንድ የተወሰነ አጀንዳና እንቅስቃሴ ላይ የበለጠ እንዲቀራረብና እንዲሰራ የሚያደርጉት ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ለሙስሊሙም እንደዚሁ፡፡በቋንቋም ሆነ በሌላ የተለለያየ አስተሳሰብ ላይ በተመሰረተ መቀራረብ የሚፈጠር ነገርም እንደዚሁ ማለት ነው፡፡
  ነገር ግን ሁለት ሰዎች በሃይማኖት አንድ ሆነው በዘር ግን ሊለያዩ ይችላሉ፡፡በዘር አንድ ሆነው በሃይማኖት ደግሞ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡በሁሉም ነገር አንድ ሆነው በፆታ ግን በስተመጨረሻ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ነገር ግን በሁሉ አንድ ሆነው በስተመጨረሻ በጾታ አንድ ቢሆኑ ግን አንድ ላይ ሊጋቡና በአንድ ጎጆ ውስጥ የጋራ ህይወት ሊኖሩ አይችሉም፡፡ይህ በስተመጨረሻ በጾታ መለያየታቸው ግን የበለጠ ባልና ሚስት ሆነው በፍቅር እንዲቀራረቡና አንድ እዲሆኑ አደረጋቸው እንጂ እንዲለያዩ ከቶ አላደረጋቸውም፡፡አስቲ አንድን ወንድ በጣም ልታስደሰትውና በተቃራኒው ደግሞ እጅግ በጣም ልታበሳጨው የምትችለው ፍጡር ከሚስቱ ወዲያ ማን ልትኖር ትችላለች?እንግዲህ ጥላቻና ፍቅር መለያየትና መስማማት እንኳን ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ አጠገባችን ቤታችን ውስጥና አልጋችን ላይ አይደለምን?እሩቅ ሳንሄድ እንኳን ሰው የተለያዬ የስሜት ህዋሳትና አካላት አሉት፡፡አፍንጫ፣ ጆሮ ፣አፍ/ምላስ፣አይን፣እጅ፣ እግር፣ልብ፣ ኩላሊት፣ሳንባ ወዘተ፡፡ሁሉም የተለያየ ተግባራት አላቸው፡፡የሰው አካል ሁሉ ጆሮ ወይንም አፍንጫ ወይንም አይን ቢሆን ትርጉሙና ጥቅሙ ምንድን ነው?አይን የአይንን ስራ ይሰራል ጆሮም እንደዚሁ የጆሮን ስራ ይሰራል፡፡አይን ለጆሮ ጆሮም ለአይን ያስፈልገዋል ይጠቅመዋል፡፡እኔ እንተረዳሁት ከሆነ በአንድ ነገር ላይ መሰባሰብ መግባባትና መቀራረብ ለአንድ ለተወሰነ ተግባርና አላማ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ያንን መሰባሰብ መግባባትና መቀራረብ ግን ለማንኛወም ነገር በማንኛውም ቦታና በማንኛውም ጊዜ ሁል ጊዜ እየመነዘርን በተመሳሳይ መልክ ለመጠቀም ስንፈልግ ነው ትልቁ ችግር እየተፈጠረ ያለው፡፡አንድነትና ልዩነት እጅግ የተምታታብን ይመስለኛል፡፡በአንድነት ውስጥ ልዩነት እንዳለ በልዩነትም ውስጥ አንድነት እንዳለ በደንብ የገባን አይመስለኝም፡፡በጣም የምንቀርበው የምንወደውና የሚጠቅመን ነገር የዚያኑ ያህል በተቃራኒው ደግሞ በጣም ልንጠላው ልንርቀውና ሊጎዳን የሚችል እንደሆነ አልገባንም ይመስለኛል፡፡
  ለምሳሌ ለህጻናት ጥላቻና ፍቅር ሀ ተብሎ የሚጀምረውና የሚመሰረተው ከዚያው ከቤተሰቦቻቸውና ከወላጆቻቸው ነው ይባላል፡፡ህፃናት ቤተሰቦቻቸውን እንደ ፈጣሪ ነው የሚቆጥሩት ይባላል፡፡በተቃራኒው ደግሞ መጥፎና ክፉ ከሆኑባቸው እንደ እኩይ ሰይጣን የሚቆጥሩት እነሱኑ ነው ማለት ነው፡፡እንግዲህ ጥላቻም ሆነ ፍቅር እጅግ ከመቀራረብ የመነጩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ማለት ነው፡፡
  በጠባብ አስተሳሰብ ውስጥ ያለ ወገናዊነትና ቡድነኝነት ወይንም ጥላቻና ፍቀርም በዋነኝነት እራስን ከመፍራትና ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ብዙዎቹ ወገናዊነትና ቡድነኝነትም ከሃይማኖታዊ ከፖለቲካዊና ከኢኮኖሚያዊ መንስኤዎቻቸው ይልቅ ውስጣዊ የሆነ የስነ-ልቦና መንስኤዎቻቸው የበለጠ ያመዝናሉ፡፡በሰዎች ዙሪያ የሚሽከረከር ማንኛውም ነገር በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ስለዚህም አስቀድሞ እራሱን ሰብዓዊነትን የካደና ያልተቀበለ ማንኛውም ሃይማኖት አይዲኦሎጂ ፖለቲካ ወዘተ በስተመጨረሻ ትርጉመ ቢስ ነው፡፡ምክንያቱም እነዚህ ወገንተኝነቶችና ቡድናዊነቶች እራሳቸው የሚመሰረቱት በዋነኝነት ሰብዓዊነትን መሰረት አድርገው ስለሆነ ማለት ነው፡፡ለምሳሌ ማነው አንድ የሆነ ሰው ከሌላ እንስሳ ወይንም ከሌላ ፕላኔት ከመጣ ከማውቀው ፍጡር ጋር ወገንተኝነቶችና ቡድናዊነቶች ያሉበትን መቀራረብን ሊፈጥር የሚችለው፡፡ስለዚህም በዋነኝነት ሰብዓዊነትን ያልተቀበለና ያላከበረ ይህ አይነቱ ዳንኤል በፅሁፍህ የገለፅከው አጠቃላይ አካሄድ መስመሩን የለቀቀ ጤናማ ያልሆነ የቡድናዊነት አስተሳሰብና ስሜት እራስን ከመፍራትና እራስን ጠንቅቆ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡
  ጤናማ የሆነ መቀራረብና ወገንተኝነት አለ ጤናማ ያልሆነ መቀራረብና ወገንተኝነት አለ፡፡ለምሳሌ አንድ ሰው በደንብ በስርዓት ሊቀርብ ሊንከባከብና ሊያፈቅርና ትርጉም ያለው ግንኙነት ሊፈጥር የሚችልው የተወሰኑ ሰዎችን ነው፡፡ስለዚህም ሰው ፍቅረኛንና ቤተሰብን መሰረት አድርጎ የራሱ የሆነ ወገንተኝነትንና መቀራረብን ሊፈጥር ይችላል ማለት ነው፡፡ይህ ማለት ግን ሌሎችን ይጠላል ወይንም ያገላል ማለት አይደለም፡፡በዘር በሃይማኖት በቋንቋ በፖለቲካ አስተሳሰብ በሙያ በእውቀት ወዘተ በተለያየ አካሄድ ቅርርብና ለአንድ የተወሰነ ተግባርና አላማ ሲባል ቡድነኝነት ይኖራል፡፡ነገር ግን ይህንን መቀራረብ ሌሎችን ለማግለልና ለመጉዳት መጠቀም አግባብ አይደለም፡፡አንድ ባለሙያ በተማረው ትምህርት በቀናነት ለማገልገል የፈለገውን አመለካከትና አስተሳሰብ ሊከተል ቢችልም ያንን ሙያውን ለመተግበር ግን የያዘው የግል አመለካከትና አስተሳሰብ እንቅፋት ሊሆንበት አይገባም፡፡
  ለምሳሌ ሁሉም የህክምና ባለሙያዎች ስለ አንድ የተወሰነ በሽታ ለመነጋገር ለመግባባትና በአንድ ላይ ለመስራት የግድ አንድ አይነት ሃይማኖት የፖለቲካ አስተሳሰብ ወይንም ዘርና ቀለም የግድ አንድ እነዲያደርጋቸው አያስፈልግም፡፡በአንድ ነገር ላይ አንድ ለተወሰነ አላማና ተግባር ሲባል አንድ የተወሰነ አይነት መቀራራብና መግባባት እንዳለን ሁሉ በሌላው ላይ ደግሞ እንደዚሁ እንለያያለን ማለት ነው፡፡
  ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል የተባለው የጥንት የሀገራችን አባባልም ለዚህ አይደለምን፡፡
  ብቻ ዳንኤል አሁን የገለፅከው አይነት ጎጂ የሆነ አላስፈላጊ ቡድንኝነትና መቀራረብ ግን የስልጣኔና የእድገት ምልክት መልካም ተግባር ሳይሆን እንዲያውም በተቃራኒው ያለ የእውቀት ማጣትና የትውልድ ዝቅጠት መገለጫ ነው፡፡ለዚህም አይደል በቅዱስ መፅሀፍ ህዝቤ እውቀት ከማጣት የተነሳ ጠፋ የተባለው፡፡የሚገርመው ግን አንዳንድ ጊዜ ይጠቅመናል ብለን አብዝተን ካቀረብነው ወገናችን ከምንለው ይልቅ አይጠቅመንም ብለን አብዝተን የራቅነውና ያገለልነው የሩቅ ሰው ባእድ በተቃራኒው የሚበጀን ሆኖ ይገኛል፡፡ስለዚህም ከመጥፎና አላስፈላጊ ዘረኝነት እንጠበቅ፡፡

  ReplyDelete
 17. ጥሩ እይታ; ጆሮ ያለው ይስማ::

  ReplyDelete
 18. በጣም ይገርማል በዚህ ጽሁፍ ራሴን አየሁት የመስተካከል አቅሙን ይስጠኝ አመሰግናለሁ ዳኒ! መልካም ነገሮች ሁሉ ይብዙልህ!

  ReplyDelete
 19. Daniel,

  Many thanks for your wonderful article.

  I really appreciate your courage and literal quality to produce such current but burning issue of the nation (Ethiopia) although it does have generalization at some points that should be taken in to consideration seriously.

  I don't have problem and even see any defect of the article as regards the socio-political aspects. We have to stand together firmly up to say "NO'' for racial and ethnic based system of politics, common social values and economic activities.

  During the news conference of the PM with local journalists a question was raised about the danger of the emerging ethnocentric, religion and region-based banking share companies. The PM's response was that I felt that it was not worth recommending, it was not good to go likewise but he further countinued that he didn't have the power to deprive them of from that kind of organization.

  For me this was totally unacceptable and shouldn't be a word from The PM for the practice will have a very negative consequences in the days to come. And that is what we are feeling today, to mention some Hawassa Bank, Debub Global Bank, Zemzem Bank, Ormiya Int'l Bank, Noah Bank.

  My reservation on the article is that you can't generalize the contents of Religion. We can't show up oneness in Religion for each of us is based on different Dogma.

  It is not bad, at least, for me that Christians foster their values through healthy teachings of their religion that make up themselves more coordinated, sympathetic and passionate towards the good of others and so does the Muslims. You can't put make or break kind of coercive action to get people united in religion. Religion is a very sensitive part , even more sensitive than our body, that should be handled with due care.

  For me the article has proved me of how we are making apart from the wonderful culture of our forefathers. Let us do our best to reinstate the lost one (our golden tradition)

  May God bless EThiopia

  ReplyDelete
 20. wey gud! lik likachinn negerken!EgziAbher yistlin! ahunm yihn astesasebachinin lemekeyer parti ayasfelgenm eyandandachin astesasebachinin mastekakel alebn! lib yisten!
  Tsion

  ReplyDelete
 21. It is very true especially property ownership as christian as a group is the core problem of spirituality.

  ReplyDelete
 22. እርስ በእርሳችሁ ብትለያዩ እርስ በአርሳችሁ ትጠፋላችሀ እባካችሁ ለዚህ አጭር ህይወት ብለን እንዲህ አንሁን እንለወጥ አምላክን የሚያስደስተውን ሥራ ሠርተን እንለፍ የዘላለም ህይወት ይበልጣል

  ReplyDelete
 23. Dani, as always, you brought up a very interesting point. This morning I was listening to a talk by one of the Ethiopian politicians, Andargachew Tsige, about similar issue in our country. He came up with very interesting idea of recognizing the causes of our ethnicity. As he said, we should never deny the facts in the ground. It is hardly possible to find a SINGLE individual among Ethiopians who is not at least psychologically a victim of the ethnicity issue. No need to politicize this issue. This is not started by EPRDF. Weyane just used the fertile ground in our society, which is what any politician do. It is a real problem of our country in particular and the world at large. That is why I agree with the speaker’s solution of recognizing the dark side of our history as a nation and agree to go forward. In order to do this we need to understand what other people feel and we should never blame them for what they felt. Rather let us try to understand them and sympathize with those who feel were victims and tell them we can work together not to victimize the coming generation. Unfortunately, we don’t have intellectuals or preachers who want to dig to this issue from the right direction. I found Andargachew’s idea the most interesting so far. I hate when everyone talks and writes about this issue as if he/she is not part of the problem. I wish you have the courage to discuss historical background of the issue and show us how we can get out of the vicious circle in which all of us are swaying in.

  http://www.ethiotube.net/video/16022/ESAT-Special--Andargachew-Tsige-of-Ginbot-7-speaking-in-Dallas--September-2011--Part-2-of-2

  ReplyDelete
 24. Dani, as usual a very interesting article. I have a reservation on one paragraph that I qoute below.

  በጎ ነገር ስትሠሩ ካዩዋችሁ ሊያበረታቷችሁ እና ሊያግዟችሁ አይደለም የሚፈልጉት፤ ሊያደንቋችሁ እና ሊያመሰግኗችሁ አይደለም የሚተጉት፤ አባል ሊያደርጓችሁ እንጂ፡፡ ምክንያቱም ከማኅበራቸው ውጭ በጎ ነገር ሲሠራ ማየት ስለማይፈልጉ፡፡

  I find this paragraph not well thought out. I think once you start seeing things through the lens of ethinicity, you are seeing everything through this lens ONLY.

  Be it in the acadamic or corporate world, whenever there is a human resource need, those that are tasked with it will try to find the best that they can get. One way of doing this may be from the list of people that you appreciate for their outstanding achievement.

  So inviting someone to join your ship and entrusting the person with more responsibility than what he has been entrusted so far is the ultimate recognition you can give as long as it is done based on merit.

  So while seeing/acting through ethinicity lens is dangerous, trying to explain everything through that lens is equally dangerous too.

  So long my friend and thanks for your continued reflection...

  ReplyDelete
 25. "በጎ ነገር ስትሠሩ ካዩዋችሁ ሊያበረታቷችሁ እና ሊያግዟችሁ አይደለም የሚፈልጉት፤ ሊያደንቋችሁ እና ሊያመሰግኗችሁ አይደለም የሚተጉት፤ አባል ሊያደርጓችሁ እንጂ፡፡ ምክንያቱም ከማኅበራቸው ውጭ በጎ ነገር ሲሠራ ማየት ስለማይፈልጉ፡፡"
  that is a true statement Dani i appreciate your observation!

  ReplyDelete
 26. ውድ ዳንኤል :-ዘረኝነትን ለማንም አይጠቅምም?? ጽሁፍህን የጀመርክበትን የ ድርጅቱ ጉዳይ ግን ከዘረኝነት መቁጠርህ ገርሞኛል:: እንደገና ብታስብበት መልካም ነው:: በዚህ አይነት እማ አንድ እምነት ይዘው በጋራ የሚያመልኩ ወገኖች ሁሉ ዘረኛ ናቸው:: እነዚህ ሰዎች "የዚህ እምነት ተከታዬች ቢገበያዩና ገንዘቡ በነሱ እጅ ውስጥ ቢሆን ሀገሪቱን የበለጠ ይጠቅማል::የረባ ነገር ላይ ይውላል" ቢሉ ምኑ ላይ ነው ዘረኝነቱ??መቸም ሁሉም እምነትና ሁሉም ሰው ገንዘቡን ለተመሳሳይ አላማ አያውለውም አይደል??

  ReplyDelete
 27. mahibertegnet tilku yebetecristian fetena homwal.

  ReplyDelete
 28. በኢትዮጵያ ዉስጥ ዘረኝነትን ማን ጀመረዉ ብንል ሁላችንም በዚህኛዉ መንግስት ላይ ጣታችንን ልንቀስር እንችል ይሆናል ሆኖም ግን ትክክለኛዉን መንገድ ለመያዝ 100 አመት ወደ ሃላ ማሰብን ይጠይቃል ምናልባት የአሁኑ መንግስት ችግር መስሎ የታየኝ ትልቅን ስህተት በትንሽ ስህተት መመለሱ ላይ ነው የቀደምት አፄዎች ስህተትን መልካም በሆነ መልኩ አለመመለስ ላይ ነው፡፡እንደገባ ከሆነ ይሄ ቡድነኝነት ከዘረኝነት የመነጨ ነው ለምትለው አንጻራዊ ይመስለል ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዉስጥ እኮ ዘረኝነት ዛሬ አልተጀመረም ቡድነኝነታችን ከድህነት እና ከድንቁርነታችን ጋር አብሮ እያደገ የመጣ ነው እን ቡድነኝነትን የምመለከተው ከእንስሳት ባህሪያችን ጋር ነው ምክንያቱም እንስሳት ቡድን መስርተው የሚንቀሳቀሱት የሚፈልጉትን ለማግኘት ጉልበት ብቻ አማራጫቸው በመሆኑ ነው ሰው ግን ከዛ በተለየ መልኩ ማሰብ የሚችል ፍጡር በመሆኑ ሰርቶ ወይም ተካፍሎ የሚኖር ነው፡፡ግን እኛከዛ እየወጣን ነው ያለነው በሌላ መልኩ ግን አንተ ባቀረብከውም መልክ ቡድንኝነት ሊፈጠር ይችላል፡፡
  ዘርመጠየቅም ዛሬ አለተጀመረም ጌታ ኢየሱስም ባንድ ወቅት ዘሩ ተጠይቆል ሳምራዊ ነህ ወይስ ናዝራዊ ጌታ ኢየሱስም ከዳዊት ዘር መፈጠሩ ዘርን ከአንድ አቅጣጫ ዕንዳናይ ያደርገናል፡፤ትልቁ ችግር ቡድነኝነትን ዘርን ለእኩይ ምግባር ማዋላችን ላይ ነው፡፤

  ReplyDelete
 29. እንኳን የኛ ሆንክ እንዳልልህ፣ አይባል፤ … ብቻ … እናመሰግናለን ዳኒ፡፡

  ReplyDelete
 30. አገር የምታድገው በብርቱ ባለ ሞያዎች፣ በተመራማሪ ወጣቶች፣ በለውጥ አምጭ ምሁራን፣ በችግር ፈቺ የፈጠራ ሰዎች፣ በሥጋት ሰባሪ ነጋድያን፣ በሃሳብ አመንጭ ሊቆች እንጂ በተሰባሰቡ ወገንተኞች አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን በየወገናችን ለሺ ዓመታት ያህል ተሰባስበን አልነበር?

  ReplyDelete
 31. Who is responsible for these evilish work? Definenatlly, Eprdf!! They had been saw the seed of ethnicity and division on Ethio.since they took the the power. Now they start harvest their fruit. I think they got ''bizu enkirdad''. Congratulation!! EPRDF!! Now we r divided in to different groups! Great job! Mr pm! Ur dreams have come true!

  ReplyDelete
 32. ዲ.ን ዳንኤል ምላሴ ቁርጥ ይበልልህ የሚባለው ለዚህ ዓይነት አገላለጽ ነው፡፡ ምላሴ ቢቆረጥ ግድ የለኝም መናገር የምፈልገውን ተናግረህልኛል ለማለት ይመስለኛል….ምን እናድርግ እህህህህህ ነው እንጅ! በየጓዳችን ያለውን ከልክ ያለፈ ዘረኝነት መሸከም ሰልችቶናል….የሚያሳዝነው ይህ ገዳይ አስተሳሰብ በእኛ ሀገር የህግና የአሰራር ድጋፍ አለው…የሚያውቁትን እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን አለ ያገሬ ሰው….

  ሕሩይ ከጎንደር

  ReplyDelete
 33. ለእግዚአብሄር የሚያደላስ ዘረኛ ይባላል? ስለ ሃይማኖት መግደል ወይስ መገደል ይሻላል? የትኛው ፍቅር አዝላአል? እግዚአብሄር ይባርክህ ዳኒ...

  ReplyDelete
 34. You post only the comments of your friends and supporters like ETV.sorry for my visiting the wrong blog.To tell you the truth you are not morally capable to raise any issue concerning ETHIOPIAN PEOPLE.YOU ARE SUCCESSFUL WHEN YOU RAISE TOPIC RELATED TO TPLF.

  ReplyDelete
 35. ዳንኤል መግቢያው ላይ ሊያሳይ የሞከረው ነገር ይህ የሀይማኖት ተከታይ በዚሁ የሀይማኖት ተከታይ ቤት ውስጥ የሚመረተውን ምርት ብቻ ይግዛ የሚለው ነገር በተከታይ የሚያመጣውነ ጦስ ነው ይህ ጉዳይ ደግሞ በየቤተአምልኮዎች ሳይቀር ከዚህ ውጭ ከገዛችሁ እንዲህ ሊሆን ይችላል የሚሉት የጥንቆላ አይነት አስተሳሰበ እየተረጨ ነው እኔ ግራ የሚገባኝ ጠበን ጠበን ጠበን የት እንደምንደርስ ብቻ ነው

  ReplyDelete
 36. ትንሹ ለጄ እንዲህ ሲል ጠየቀኝ በሶና ሙቅ ልዩነታቸው ምንድ ነወ እኔም እንዳሀ ስል መለስኩለተ በሱ ይበጠበጣለ ሙቅ ደግሞ በእሳት ይበስላል አልኩት ምኑ ነው የሚበጠበጠውና የሚበስለው አለኝ ገብሱ አልኩት ገብሱን ግን ከመበጥበጥና ከመብሰል የትኛው ነው የሚያሳምመው አለኝ ገብስ ስለሆነ አይሰማውም አልኩት ሰው ቢሆንስ አለኝ ከዚህ በሃላ ግነ መመለስ አልቻልኩም ነገሩ ከርእሱ ጋረ ባይገናኝም ከምረሳው ብየ ጻፈኩት እስቲ አንድ ቀን ስለመበጥበጥና መብሰል ጻፍልን ዲን ዳንኤል

  ReplyDelete
 37. This is one of our problem, but we didn't know that.

  ReplyDelete
 38. In my way of thinking, Racism has both good and bad aspects.What matters is the result.

  ReplyDelete
 39. Dn. Dani really it is perfect look.

  ReplyDelete
 40. yihe siltan lay yalew mengist yemifetrew guday. hizb yihen yikebelal hiwot yadergewal.lemsale dergn yetalew endziz yetebaln biheroch nen yluhal.endet biher yiwagal? gileseboch bedirjit le alama tesebasbew dil madregachewn ayamnum.yihe lemn meseleh

  mashenef kamarachhu ke egna beteweledachiw hahah

  sew besiraw bicha yimikeberbet,yimikonenbet,.yemishombet,yemisharbet zemen yamtalin,
  mignote new enji ahun balew akahed endemaysaka gilts new

  ReplyDelete
 41. i read z same type of add at z notice board in a mahibere that i offer ma service.so i guess if u were member of a board there u wouldn't allow it haa???

  ReplyDelete
 42. ዳኒ ከአሁን በፊት አስተያየት ሰጥቸ አላውቅም:: ፅሁፎችህን ግን ሁል ጊዜ አነባለሁ:: ፅሁፎችህን ሳነብ ከያዙት ጥልቅ የቁምነገር ብዛት እየተደሰትኩ: እያደነኩ: እየተዝናናሁ እና እውቀት በነጻ እየሰበሰብኩ ሳለሁ ችግሩ በሀገራችን እያደረሰ ያለውን ጉዳት ሳይ እና ፅሁፉን አንብቦ ማን ወደ ተግባር ያውለዋል ብየ ስጠይቅ ግን ያስጨንቀኛል:: ዳኒ ይህን ፅሁፍ የሚያነበው ኢንተርኔት የሚያገኝ ብቻ ነው:: ስለዚህ በመጽሀፍ መልክ ብታዘጋጀው መልካም ነው እላለሁ:: እግዚአብሔር ይበልጥ ብርታቱን ይስጥህ:: በርታ !!!

  ReplyDelete
 43. Dani its my first time to give my comment but i'm regular follower of your blog. keep going you are creating a new generation.

  ReplyDelete
 44. yebesowa neger temechitagnalech "anonymous".
  Bante blog layi lela blog yemikeftutin meche anbiben linicherisew newu. Gena anjet mehonun say yidekimegnal. Yante gin keyetignawum kifil bijemer silemitim meche jemerku satil yalkal. Esti and belachew.

  ReplyDelete
 45. Birhan Bank is for protestants. Another Bank is under on progress for Muslims. Most protestants make business each other as I learnt during my stay in Addis. The muslims' business is known that they make from each other.

  ReplyDelete
 46. "...................ልጁ ሊቀጠር ወደ አዲስ አበባ ይመጣል፡፡ ታድያ መካሪዎች «ስትሄድ ጳጳሱ የሀገራቸውን ሰው ይቀጥራሉና ሀገርህ የት ነው ካሉህ ያንተን አትናገር የርሳቸውን ሀገር ተናገር» ብለው ይነግሩታል፡፡ ታድያ ጳጳሱ ፊት ሲቀርብ የሀገራቸው ስም ጠፋው አሉ፡፡

  እንደገባ ያ የተነገረው አልቀረም

  «ሀገርህ የት ነው?» አሉት

  «የርስዎ ሀገር» አላቸው፡፡

  «የኔ ሀገር የት ነው?» አሉት

  «ከኔ ሀገር» አላቸው አሉ፡፡ ምን ያድርገው፡፡

  አንዳንዶችማ ከዚህም ወርደው ወርደው የቆብ ዘረኛነትም ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሕጋውያን ካህናት ከታላላቅ አድባራት አስተዳዳሪነት እንዲወገዱ ዐዋጅ ያወጣው ማን ይሆን? ዛሬ ለሹመት ዋና መመዘኛው መመንኮስ ሆነና «መነኮሰ ሞተ» የሚለው ትርጓሜ «መነኮሰ በላ» ወደሚለው ዞረ፡፡ በዚህ የቆብ ዘረኛነት ምክንያትም መመንኮስ የሌለባቸው ለሥራ እና ለሹመት ሲሉ እንዲመነኩሱ አንዳንዶችም ሚስቶቻቸውን ደብቀው እንዲመነኩሱ አደረግናቸው፡፡ በተለይም የውጩ ሀገር ዕድል ሁሉ ከሕጋውያን ይልቅ ለመነኮሳቱ እጅግ ክፍት እየሆነ ሲመጣ፣ ያልገባቸው እና ያልተገባቸው መነኮሳት እየበዙ መጡ፡፡

  ከዚህም አልፎ ምንኩስናዊ ሕይወቱ ሳይሆን የት መነኮሰ? የሚለው የዘረኛነት መለኪያ እየሆነ ነው፡፡ እናም የት ብመነኩስ የምንኩስናን ተጋድሎ እፈጽማለሁ? መባሉ ቀርቶ የት ብመነኩስ ቶሎ ሹመት አገኛለሁ? ሆነ ጥያቄው፡፡..........."

  you guys! did you acumen what are you doing? What is your main aim? Are you free which you are talking about? I am really tiered about you guys. Congratulation! The fire you intentionally had been lighted up in to the church is burning our church and will have been damaging in the future.
  First, have a look the dirt which states inside of your mind. Then you can see to others whoever you want.

  ReplyDelete
 47. ለዚህ ርዕስ መጀመሪያ አስተያየት የሰጠሁት እኔ ነበርኩኝ፡፡ለምን እንዳለጠፍከው አልገባኝም፡፡አሁንም ከለጠፍከው በድጋሚ የመጀመሪያ አስተያየቴን እነሆ፡፡ካለጠፍከው ምን ማድረግ ይቻላል???ከመተዛዘብ ውጭ፡፡ማንነትህን በእርግጠኝነት ከማወቅ ውጭ፡፡እንደ ኢቲቪ የደጋፊዎችህን እና የአጨብጫቢዎችህን ጭፍን ጥላቻ እና ጭፍን ድጋፍ ብቻ እንደምታቀርብ ከታወቀብህ ቆይቷል፡፡ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ስንመለስ እንደኔ እንደኔ አገሪቷ አሁን ለገባችበት የዘረኝነት አዘቅት ብቸኛ እና ብቸኛ ተጠያቂው የእናንተው ሕወአት የሚባለው ፓርቲ ነው፡፡ወያኔ የዘራው የዘረኝነት ዘር በሁሉም ኢትዮጵያዊ የልብ ጎተራ ውስጥ ተከማቸ፡፡ጊዜና ቦታ ሲፈቅድለት ሁሉም ከልቡ ጎተራ ዘረኝነትን እያወጣ ደም ዘርቶ ደም ያጭዳል፡፡ይህ ደግሞ የከበቡንን ጥንተ ጠላታችን የሆኑትን የአረብ አገራት ከማስደሰት ውጭ ኢትዮጵያውያንን በምንም መልኩ አይጠቅምም፡፡መፍትሔውን ባትጠቁምም መፍትሔው ግን እውነት እና እውነተኛ እርቅ ብቻ ነው፡፡ፓርቲያችሁም ከኢኮኖሚያችን ላይ የጫነብንን ከባድ እጁን ያንሳልን፡፡የፖለቲካ ስልጣኑንም በብቃት እና በእውቀት ለሚበልጡ ሰዎች ይልቀቅ፡፡ዘረኝነት በወገንተኝነት ብቻ አይቆምም፡፡ዘረኝነት ፈርጀ ብዙ የሆነ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ጉዳት ያስከትላል፡፡በዘረኝነት የደረሰብንን ጉዳት ትተን የሚደርስብንን የከፋ ጉዳት ለመከላከል መንቃት አለብን፡፡ይህንን ማስተባበር/ማስጀመር ያለበት ደግሞ በዋነኛነት መንግስት ነው፡፡በምርጫ 97 የደረሰብንን ሰብዓዊ ኪሳራ ባንረሳውም የበለጠ ኪሳራ እንዳይደርስ መተማመኛ አግኝተን በሰላም መኖር እንደሚሻል ለማንም ግልጽ ነው፡፡ለዚህም ነው ያለፈው ይብቃ የምንለው፡፡ግን መንግስት ይህን መስማት አልፈለገም፡፡ዘረኝነትን አጠናክሮ በሁሉም መስክ ቀጠለበት እንጂ፡፡ችግርን ማንሳት ብቻ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡የባሰ ችግር እንዳይመጣ የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ መወያየት ነው የሚሻለው፡፡አዲስ አበባው ነኝ ከአሮጌው ቄራ፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. Dedeb ,megemeria ,ante kezergnet wta. There is no tplf government.We know only EPRDF.TPLF is one party.

   Delete
 48. Very nice article!!!!!!

  ReplyDelete
 49. አንተ አዲስ አበባው ከየት መጣህ ደግሞ አስተሳሰብህ የወረደና የሌለ ነው፡ጭፍን ነህ፡፡

  ReplyDelete
 50. አንተ አዲስ አበባው ከየት መጣህ ደግሞ አስተሳሰብህ የወረደና የሌለ ነው፡ጭፍን ነህ፡፡

  ReplyDelete
 51. Dear Daniel,

  I agree with most of the points you raised. Particularly your point on the issue of language has touched me a lot. Let me tell you my experience to illustrate your point.

  Once I was hanging out with my friends in our neighborhood in Addis. A young man, obviously an Ethiopian, came to us and said something in Oromiffa. But none of us knew Oromiffa, so the young man resorted to English since he can’t speak Amharic. He was asking for help for he was in a problem of some sort … There is no need of telling you the rest of the story.

  That experience shoved a bitter reality into my mind: that our educational system has failed to bring us together as Ethiopians. Imagine Ethiopians who couldn’t communicate with an Ethiopian language and who needed to use the language of a nation many miles away! This is a result of nothing but disrespect to oneself. Obviously, it is a crisis born out of hatred and grudge based on a misguided understanding of Ethiopia and its history. But who will save us from the nasty outcome this racism results in?

  ReplyDelete
 52. i really wonder you dan, that is fantastic story

  ReplyDelete
 53. Thank you Dany,

  where ,Why, how, when.....does "Zeregnet" Start? Yes if "Zeregnet" is translated in the way you observe and explain its side effect weights over the benefit. But think your self how different sections/groups are existing , it is because natural , and it becames now visible now because there was no chance to see them in the previouse . Ask your self why you write this topic in Amharic not in English?
  Most of the time I am surprised most who think nationality they forget the peaple in the nation.

  If you are worried about ETHIOPIA you have to worry about the peaple in ethiopia, if you are worried the culture , norms, valaues of ethiopian you have to consider all components of those who build up the nation regardless of how small or big their number may be.

  If we are against the differences we are opposing the nature.

  Currently what is the big problem is that the so called "experts" manuplating the differences for individual benefit only

  ReplyDelete
 54. አገር የምታድገው በብርቱ ባለ ሞያዎች፣ በተመራማሪ ወጣቶች፣ በለውጥ አምጭ ምሁራን፣ በችግር ፈቺ የፈጠራ ሰዎች፣ በሥጋት ሰባሪ ነጋድያን፣ በሃሳብ አመንጭ ሊቆች እንጂ በተሰባሰቡ ወገንተኞች አይደለም፡፡
  እኔ በጽሑፉ ተቃውሞ አለኝ አገር የምታድገው ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች ሳይሆን ፖለቲካንና ሥራን አብሮ ተያይዞ አብሮ ሲሄድ ነው እንጂ ከላይ የተባሉትማ የመጨረሻ ቦታ ማለትም ሁሉም ከተስተካከለ በኃላ የሚመጡ ናቸው.
  1. ፖለቲካ ካልተስተካከለ የፈለግነውን የተማሩ ሰዎች ብናስቀምጥ መፍትሔ አይመጣም
  2. ኢኮኖሚ (ሀብት ሳይኖር የተማረ ቢኖር አገር አያድግም)
  3. ማህበራዊ ጉዳዮች ( እዚህ ላይ ዘረኝነት ብለህ ያመጣኸው አማራ ኦሮሞ ሶማሌ አፋር ወላይታ ትግሬ ማለት አገር ያሳድጋል እንጂ ወደ ኃላ አይወስደንም) የቋንቋ ና የሶሻል ተማሪዎች ጠይቅ ምክንያቱም የተማረ የተመራመረ የትም ቦታ አይገኝም ህዝብ አዋቂ ነው የተማረው አይደለም
  4. የተማረ ኃይል (ተክኖሎጂው)የተማረ የተመራመረ
  እና ከላይ የተገለጹት ነገሮች ማለትም ፖለቲካው፣ኢኮኖሚው፣ ማህበራዊ ጉዳዮችና ተክኖሎጂ ሲሳኩ እድገት ይኖራል እንጂ እንደተባለው 4ኛው የተማረ ኃይል (ተክኖሎጂው)የተማረ የተመራመረ አስቀድመህ ፖለቲካው አስተካክላሉሁ ብትል ገደል ትገባለህ ሁለተኛ ሃብት ሳይኖር በተማረ ኃይል አገር አያድግም የተማረ የተመራመረ አገር ለቆ ይሄዳል እንጂ ገንዘብ ወዳለበት አገርን አያሳድግም

  ReplyDelete
 55. Endihnew>>>>>>>

  ReplyDelete
  Replies
  1. i really dont wanna belive this exists....but this is the ugly truth

   Delete
 56. most of the time you feel as you are not living and working in a home land as a result of xenophobia. No xenophobia against the Race. joro yalew yisma kena libonam yistew.

  ReplyDelete
 57. ዳኒ የድንግል ማርያም ልጅ ለዝች አገር በእኩልነት አገልግሎት ያሚሰጥ ፀሐይና ᎒ ጨረቃ እስካልሰጠን ድረስ የዘረኝነት በሽታ ውግዘት የሚያስቆመው አይመስለኝም:: ስለዚህ ምን እናድርግ ለሚሉህ የብዕር ጔደኞቸህ መልሱ የሚመሰለኝ 1)ጠንክሮ ሳይጠራጠሩ መጸለይ 2)በራስ ላይ ዘረኝነትን ለማስወገድ አንድ ብሎ መጀመር ነው::
  በነገራችን ላይ ከቅድስት አገር እንኮን በሰላም ወደአገርህ ተመለሰክ::

  ReplyDelete
 58. I REALLY HATE THIS WE MUST FIGHT TO THIS AND MAKE THINK AS ONE.

  ReplyDelete