Thursday, October 13, 2011

ጫካው ለዛፎች ብቻ

በአንድ ወቅት በጫካ ውስጥ ያሉ ዛፎች እንዲህ ሲሉ መከሩ፡፡
«እነዚህ አራዊት እኛ ለመጠለል ይመጣሉ፡፡ እኔ የእነርሱን ማንኮራፋት መስማት ሰልችቶኛል» አለ የዝግባ ዛፍ፡፡
«እኔ ደግሞ ከሁሉም የሰለቸኝ እኔ ላይ ወጥተው ሲራኮቱ እየቀነቁኝ ነው» ጽድ መለሰ፡፡
«ከሁሉም የሚብሰው የእኔ ነው» አለ ግራር፡፡ «ከሥሬ ይመጡና ኩሳቸውን ይጥላሉ፡፡ እኔ ሽታውን መቋቋም አቅቶኛል»
«አንዳንዶቹማ»አለ ዋርካ «ከኔ ሥር መጥተው ጉድጓድ ቆፍረው ይኖራሉ» ሁሉም ምሬታቸውን አወሩ፡፡
«ይህንን ያህል ካስመረሩን ለምን ዝም እንላቸዋለን? ድራሻቸውን ማጥፋት ነው» ዝግባ እየተንጎማለለ ፎከረ፡፡

«ልክ ነው የአንበሳ እና የነብር መራኮቻ መሆናችን ሊያበቃ ይገባል» ጽድ ግራ ቅርንጫፉን አንሥቶ ደገፈ፡፡
«ከዛሬ ጀምሮ አንድም አንበሳ እና ነብር እዚህ አካባቢ እንዳይደርስ መደረግ አለበት» ዋርካ በጎርናና ድምፁ አናወጠው፡፡
ከዚያም «ጫካው ለዛፎች ብቻ» የሚል መፈክር ቅርንጫፎቻቸው ላይ ሰቀሉ፡፡
«ይህንን ቦታ ጫካ እንዲሆን ያደረግነው እኛ ዛፎች ነን፡፡ በብርድ እና በፀሐይ እየተንገበገብን የታገልነው እኛ ነን፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ስንት መከራ አይተናል፡፡ እኛ በመሠረትነው ጫካ ማንም ሊጠቀም አይችልም፤ ጫካው ለዛፎች ብቻ» ይላል ከመፈክሩ ሥር የተፃፈው ማብራርያ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ወይራ ዝም እንዳለ ነው፡፡
«ምነው አንተ ያንን ክርፋታም ሽታ ወደኽዋል መሰል» አሉት በሽሙጥ፡፡
«እኔም እንደ እናንተ በአራዊቱ መኖር ችግር አለብኝ፡፡ ሽታውም፣ ጩኸቱም፣ መወዝወዙም፣ መሰበሩ መርሮኛል፤ ግን ደግሞ እነርሱ አራዊት ናቸው፡፡ ከዚህ ጠባያቸው ውጭ መሆን አይችሉም፡፡ ዛፍ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በችግሩ ላይ እስማማለሁ፤ በመፍትሔያችሁ ላይ ግን አልስማማም» አለ ወይራ፡፡
ሁሉም እየተመናቀሩ ከበቡት፡፡
«እና የማንም አውሬ መጨዋቻ እንሁን ነው የምትለው ዋርካ ጮኸበት፡፡
«እስኪ ንገረኝ አንበሳ እና ነብር መጡ፣ ቀሩ ምን ይጎድልብናል ግራር አፋጠጠቺው፡፡ «በዚች ምድር አንዱ ያለ ሌላው ሊኖር አይችልም፡፡ ልዩነቱ ያኛው የሚሰጠንን ጥቅም ልናውቀው ወይንም ላናውቀው መቻላችን ነው፡፡ ምንጊዜም የዚያኛውን ወገን ችግሩን ብቻ የምናየው ከሆነ ጥቅሙን የምናይበት ዓይን አይኖረንም፡፡ ቢያንስ እነርሱ የሚጥሉት ነገር ቢሸተንም አፈሩን ያዳብርልናል፤ ለኛም ምግብ ይሆነናል፡፡ ለምን ችግሩን ብቻ ታያላችሁ፡፡ እኛ መጠለያ እንሰጣለን፣ እነርሱ ደግሞ ምግብ ይሰጣሉ፤ ሌላም ዛሬ ያላወቅነው ነገር ያደርጉልንም ይሆናል፡፡ ተባብረን እንኖራለን፡፡ ሳይደጋገፉ መጥፋት ይቻላል፤ ሳይደጋገፉ መኖር ግን አይቻልም»
አንድ ጊዜ ሁሉም እንደ ብራቅ ጮኹበት፡፡
«የእነርሱ ማዳበርያ ጥንቅር ብሎ ይቅር፡፡» አለ ዝግባ፡፡ ሁሉም አጨበጨቡ፡፡
«እኔ ወስኛለሁ አንድ ነብር አንድ አንበሳ እዚህ ቢመጣ የማደርገውን ዐውቃለሁ፤ ጫካው ለዛፎች ብቻ» ዋርካ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ሌሎቹም አንገታቸውን እየነቀነቁ «ጫካው ለዛፎች ብቻ» እያሉ ፈክረው ተመለሱ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነብር መጣ፡፡ ዋርካው ላይም ወጣ፡፡ ያን ጊዜ የዋርካው ቅርንጫፎች እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ተርገፈገፉ፡፡ የሌሎቹ ዛፎች ቅርንጫፎችም እየተወራጩ ነብሩን በጥፊ ይመቱት ጀመር፡፡ በሁኔታው የተደናገጠው ነብር እግሬ አውጭኝ ብሎ ፈረጠጠ፡፡ ፈርጥጦም አልቀረ ወገኖቹን ሰበሰበና «እዚህ ጫካ ውስጥ አንዳች መዓት ወርዷል፤ «ጫካው ለዛፎች ብቻ» የሚል መፈክርም አይቻለሁ፡፡» እያለ ያጋጠመውን ነገር ነገራቸው፡፡ ከዚያም ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የነብር ዘር ጫካውን ጥለው ጠፉ፡፡
በማግሥቱ አንበሳ ከነደቦሎቿ መጣች፡፡ ከዝግባው ዛፍ ሥርም አረፈች፡፡ የዝግባው ዛፍ ሥሮቹን አወጣና ደበደባት፡፡ ሌሎቹ ዛፎችም ቅርንጫፎቻቸውን እያስጎነበሱ የማርያም ጠላት ብለው ጨፈጨፏት፡፡ አንበሲቷ አይታው የማታውቀው ነገር ስለገጠማት ደቦሎቿን ሰብስባ ሸሸች፡፡ ከዚያ በኋላም በጫካው ውስጥ አንበሳ አልታየም፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ አራዊቱን ሁሉ ገርፈው እና አስደንግጠው አባረሯቸው፡፡
ቀናት፣ ሳምንታት እና ወራት አለፉ፡፡ አንድም አውሬ ብቅ ሊል አልቻለም፡፡ ዛፎቹ ከሽታው ተገላገሉ፡፡ በላያቸው የሚዘል በሥራቸው የሚጠለል አውሬ የለም፡፡ ሁሉም የጀግንነታቸውን ውጤት በኩራት ይተርኩ ጀመር፡፡ እንዳሉትም ጫካው ለዛፎች ብቻ ሆነ፡፡ የሚያገሣ አንበሳ፣ የሚጮኽ ጅብ፣ የሚያስገመግም ነብር አልነበረም፡፡
ወይራ ግን በነገሩ ሁሉ አዘነ፡፡
አንድ ቀን አራት ሰዎች የሆነ ነገር ተሸክመው ወደ ጫካው መጡ፡፡ በቁመቱ ዘለግ ያለው ዝግባ በሩቁ ሲመለከታቸው ሊያውቃቸው አልቻለም፡፡ «አራት ሰዎች የሆነ ነገር ይዘው ወደ ጫካችን እየገቡ ነው» አለና አሰምቶ ጮኸ፡፡ ጽድ መጡ ወደተባለበት ሲዞር እውነትም አራት ሰዎች የሆነ ነገር ይዘው ገቡ፡፡
 «የያዙት ምንድን ነው ሁሉም ጽድን ጠየቁት፡፡ ነገር ግን በዚያ ጫካ ውስጥ አደን ለማደን የሚመጡ ሰዎች ከሚይዙት መሣርያ በቀር ሌላ መሣርያ ታይቶ አይታወቅምና ሊያውቁት አልቻሉም፡፡
ወይራ አሾልኮ ተመለከታቸው፡፡ ዐወቃቸውም፡፡ «የፈራሁት ይሄንን ነበር» አለ በኀዘን ድምጽ፡፡ ሁሉም ወደ እርሱ ዞሩ፡፡ «እነዚህ ሰዎች ዛፍ ቆራጮች ናቸው» አለ በቅርንጫፉ መሬቱን እየደበደበ፡፡
«እንዴት ሊመጡ ቻሉ አለ ዋርካ ፍርሃት እያራደው፡፡
«አያችሁ አራዊቱን አባራችሁ ዛፍ ቆራጮችን አመጣችሁብን፤ ለጊዜያዊ ሰላም ስትሉ ዘላቂ ሰላማችንን ነጠቃችሁን» አለ ወይራ፡፡
«የእነርሱን መምጣት እንዴት ከአራዊቱ መሄድ ጋር ታያይዘዋለህ፣ ምን ያገናኘዋል ጽድ አፈጠጠ፡፡
«እዚህ ጫካ ውስጥ አንበሳ፣ ነብር፣ ጅብ፣ ተኩላ፣ ቀበሮ ሌሎችም ነበሩ፡፡ ሰው ደግሞ አንበሳ እና ነብር ይፈራል፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ዛፍ ለመቁረጥ የሚመጣ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ጥቂቷን ሽታ መቋቋም አቅቶን አንበሳውን እና ነብሩን አባረርናቸው፡፡ አላወቅንም እንጂ እነርሱ ለኛ ጠባቂዎቻችን ነበሩ፡፡ የተከበርነው በእነርሱ ነበር፡፡ ጫካው ባዶ ሲሆን ዛፍ ቆራጮች መጡ» አለ ወይራ፡፡
«አሁን ምን ይሻላል ዋርካ ዕንባ ዕንባ አለው፡፡
«በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ
ይላሉ ሰዎች ሲተርቱ፡፡ አሁንማ ምን ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ዓለም አንዱ ያለ ሌላው ርዳታ መኖር አይችልም፡፡ ሁላችንም የሌላው ጥገኞች ነን፡፡ የማንፈልገው እንጂ የማያስፈልገን ነገር የለም፡፡ የማናደንቀው እንጂ የማይጠቅመን የለም፡፡ የኛ ህልውና ለብቻው ሊጠበቅ አይችልም፡፡ የኛ ህልውና ከሌሎች ህልውና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኛ ሰላም ብቻውን ሊጠበቅ አይችልም፤ የኛ ሰላም ከሌሎች ሰላም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን በሌሎች ላይ የደረሰውን የምንረዳው ሲደርስብን ብቻ ነው፡፡ ደግሞ ምንም ማድረግ የማይቻልበት ሰዓት ነው፡፡ ሌሎችን እንደሚያስፈልጉን ከተረዳን፣ ለሌሎች መብት እና ጥቅም መቆም አለብን፤ ሌሎቹም እንደኛው እንዲኖሩ መፍቀድ አለብን፤ መፍቀድ ብቻም አይደለም ለእነርሱ መኖር እኛ አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን፡፡
«ዕንቁራሪት ያለቺውን ታውቃላችሁ ጠየቀ ወይራ
«እስኪ ከመቆረጣችን በፊት ንገረን» አሉት፡፡
«እርሷ ኩሬ ውስጥ ሆና እያለ እዚያ ማዶ ቤት ይቃጠላል አሉ፡፡ እሳቱን እያየች ትጨነቃለች፡፡ እንዳጋጣሚ አንድ ሰው በአጠገቧ ሲያልፍ ወዳጄ «ለፖሊስ ልትደውልልኝ ትችላለህ ትለዋለች፡፡ ሰውዬውም ገርሞት «ምን ሆንሽ ብዬ ነው የምደውልልሽ» ይላታል፡፡ «ኧረ እባክህ እዚያ ማዶ እሳት ተነሥቷል ብለህ ደውል» አለቺው፡፡ ሰውዬውም «እሳቱ ያለው እዚያ ማዶ አንቺ ምን አስጨንቆሽ ነው ደውል የምትይኝ» አላት፡፡
«አየህ እሳቱን እዚያ እያለ ካላስቆምነው እዚህም ይመጣል፡፡ የአንዱ መቃጠል የሁላችንም መቃጠል ሆኖ ካልተሰማን በኋላ መከራው ለሁላችንም ይተርፋል» ትለዋለች፡፡ ሰውዬውም «አንቺ ያለሺው ውኃ ውስጥ እንዴት እሳቱ ያገኝሻል አላት፡፡ «እነዚያ ሰዎችኮ እሳቱ ከባሰባቸው ውኃ ለመቅዳት ይመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ እኔንም አብረው ሊወስዱኝ ይችላሉ፡» ስትል ትመልስለታለች፡፡ «ቀልደኛ ነሺ»ብሎ ትቷት ይሄዳል፡፡
«ከዕንቁራሪቷ እንደተለየ ሰውዬው መንገዱን ይዞ ጫካ ውስጥ ይገባል፡፡ ለካስ የቤቱ እሳት በርትቶ ጫካውንም ይዞት ኖሯል፡፡ መሐል ጫካ ከደረሰ በኋላ እሳቱ ይከብበዋል፡፡ ያን ጊዜ ዕንቁራሪቷ ያለቺው ትዝ አለው፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ ምንም ሊያደርግ በማይችልበት ጊዜ ነው ትዝ ያለው፡፡
«እኛኮ ለእነዚያ አራዊት ጥብቅና መቆም ነበረብን፡፡ ምንም እንኳን ሽታቸውን ባንወደው፣ ምን እንኳን አንዳንድ ችግር ቢኖርባቸው፡፡ ምንም እንኳን በኛ ላይ ወጥተው ቢራኮቱ ግን ደግሞ ያስፈልጉን ነበር፡፡ ከኛ የተለየው ሁሉ የኛ ጠላት አይደለምኮ፡፡ ችግር ያለበት ሁሉ የማያስፈልግ አይደለምኮ፡፡ እኛ ለእነርሱ ጥብቅና የምንቆመው ለእነርሱ ብቻ ብለን አይደለም፡፡ ለራሳችን ነው፡፡ አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል አሉ ሰዎች፡፡»
«ይኼ ታሪክ አንድ ነገር ትዝ አስባለኝ አለ ዋርካ፡፡ አንድ ጊዜ ሁለት አዳኞች እኔ ሥር ቁጭ ብለው ሲያወሩ የሰማሁት ነው፡፡ በአንድ ወረዳ አንድ ፍርድ ቤት ነበር አሉ፡፡ ታድያ ዳኛው ሥራ የማይወዱ ስልቹ ነበሩ፡፡ ሰዎች ወደ እርሳቸው እንዳይመጡ የማያደርጉት ጥረት አልነበረም፡፡ የሉም፣ ታመዋል፣ መንገድ ሄደዋል፣ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ ንጉሡ ጠርቷቸው ሄደዋል፣ ሱባኤ ይዘዋል እያስባሉ ሰውን ሁሉ አስመረሩት፡፡
በዚህ ምክንያት ሰው እየተማረረ ወደ እርሳቸው አይመጣም ነበር፡፡ እርሳቸውም ቀኑን ሙሉ ሲበሉ፣ ሲጠጡ እና ሲተኙ ይውሉ ነበር፡፡ እንዲህ አድርገው ለብዙ ዘመናት እንደ ቆዩ ንጉሡ ገንዘብ ያንሳቸዋል፡፡ እናም የዳኞችን ቁጥር ለመቀነስ ይፈለጋሉ፡፡ አማካሪዎቻቸውን በየዳኞቹ ዘንድ ያለውን ባለ ጉዳይ ቆጥረው እንዲነግሯቸው ላኩ፡፡ የእኒያ ዳኛ ወንበር ሲታይ አንድም ሰው በአካባቢው የለም፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ሲጠየቁ እርሳቸውን ስለማያገኟቸው ወደ ጎረቤት ዳኞች እንደሚሄዱ ተናገሩ፡፡ እናም እኒህ ዳኛ ከሥልጣን ወርደው የንጉሡ አልጋ አንጣፊ ሆኑ፡፡ ባለጉዳዮቻቸው ለመኖር አስፈላጊዎቻቸው እንጂ ችግሮቻቸው አለመሆናቸውን የተረዱት አልጋ ሲያነጥፉ ነው»
«የኛ ነገር ደርሶባቸዋላ» አለ ዝግባው፡፡
እናም ሁሉም ጸጥ አሉ፡፡ የሚሰማው ድምፅ ዛፍ ቆራጮቹ ዝግባውን በመጥረቢያ ሲመቱ የሚወጣው ድምፅ ብቻ ነበር፡፡
ሳንሆዜ፣ ካሊፎርንያ
©ህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።

24 comments:

 1. ይህንን ጽሑፍ ሳነብ በካህናትና በሰንበት ትምህርት ቤት መካከከል ያለው ክፍተት ትዝ አለኝ፡፡ ማለቴም በኢትዮጵያ፡፡ መቼ ይሆን መፍትሔ አግኝቶ በሌላ አገር እንዳሉት አገልጋይ ወንድሞቻችን አስፈላጊነታችን ታምኖበት በቤተ መቅደስ ውስጥ እንድንዘምር የሚፈቀድልን፡ እጅና ጓንት ሆነን የምናገለግለው መቼ ይሆን ሰንበት ተማሪ ከሆንክ ግብረ ዲቁና አላስተምርህም ቤተመቅደስ ገብተህ አትቀድስም የማንባለው ናፈቀኝ፡፡ ሁላችንንም ልብ ይስጠን፡፡

  ReplyDelete
 2. very interesting
  thank you...May God help us to get lesson from this post

  ReplyDelete
 3. Egezeyabher yebarkeh! Amelak ende enkurarit enaseb yerdan.
  Mamush,MN

  ReplyDelete
 4. ኦ በጣም አሪፍ ትምህርት ነው ፡፡ መቼም አያልቅብህም!
  አመሰግናለሁ በጣም ፡፡

  ReplyDelete
 5. ዳኒ አንተ መቼም ቁምነገር ያለው ተረት አያልቅብህም፡፡
  አንዱ ታዳሚህ ዳንኤል ክብረት የተረት አባት ብሎ ተስፋ አስቆርጦ ሊያስቀይምህ ቢፈለግም የተረት አባት መሆን መታደል መሆኑን ግን በደንብ ስላልገባው ነው፡፡ዛሬ ንግግራችንና ዘይቤያችን ሁሉ ፈረንጅኛ ጉራማይሌ ሆኖ ጀለሴ ወዘተ በሚሉ ለዛ ቢስ የአነጋገር ዘይቤዎች የተሞላ ሆነ እንጂ የተረት አባት መሆንስ መታደል ነበር፡፡ይህ አባባል አሁን በሀገራችን ያለውን አጠቃላይ የስርዓትና የትውልድ ውጥንቅጥና ዝቅጠት በደንብ የሚያሳይ ነገር ነው፡፡ኢትዮጵያውያን በባህላችን አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን አብሮ በመሆን ሀዘንን ደስታን ችግርን ማንኛውንም ነገር በማህበር በጋራ መካፈል ባህላችንና ታሪካችን ነበር፡፡ነገር ግን ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ እዚህ ሀገር የገባውን ጅኒ እንኳን እኔ የበቃ የሃይማኖት አባትም ጭምር በደንብ የሚያውቀው ያለ አይመስለኝም፡፡አጠቃላዩ ህይወት ያለው ነገር ሁሉ እርስ በርሱ እንደ ድር የተሳሰረ እነደሆነ ድሮ ባይሎጂ ስንማር Food-chain and food-Web እያልን ተምረን ነበር፡፡ነገር ግን ምን ያደርጋል ታዲያ ዛሬ ወሬ ብቻ ሆኖ ቀረ እንጂ፡፡ዛሬ በሀገራችንና በአለም ላይ እየተፈጠረና እየተመሰረተ ያለው ዋና መሰረታዊ ተቀዳሚ ተግባር የገንዘብና የስልጣን Food-chain and food-Web ነው፡፡ስለዚህም የሰው ልጅና ተያያዥነት ያለው አጠቃላይ ህይወት ያለው ነገር ህልውናና ደህንነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ከፋ አደጋ ላይ እየተጋለጠ ነው፡፡
  በዘፍጥረት ላይ እግዚአብሄር በአለም ላይ ወይንም በመሬት ላይ የፈጠረው አጠቃላይ ፍጥረትና ስራ ሁሉ መልካም እንደሆነ አየ ነው የሚለው፡፡ነገር ግን የሰው ልጅ ይህንን የፈጣሪ መልካም ስራ ከእለት እለት እያጠፋ የራሱን መልካም የመሰለውን ብልጭልጭና ጊዜያዊ ስራና ነገር እየተካበትና ወደ ጥፋት እያመራ ነው፡፡እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ወይንም እኔ ብቻ ከኖርኩ ለሌላው ምንቸገረኝ የዘመናችን አደገኛና አጥፊ መፈክር እየሆነ ነው፡፡ነገር ግን ይህ አይነቱ የሰው ልጅ አኩይና ስግብግብ ባህሪና አካሄድ በስተመጨረሻ የራስን መቃብር ከመቆፈር የተለየ አይደለም፡፡አፍንጫን ሲመቱት አይን ያለቅሳል በተቃራኒው ባለው አፍንጫን ሲመቱት ጥርስ ይስቃል በሚል እየተተካ ነው፡፡አንዳንዶች በሌሎች መቃብር ላይ ቤተ-መንግስት ለመገንባት ይፈልጋሉ የሚለው አባባልህ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡ነገር ግን በሚገነቡት ቤተ-መንግስት ወስጥ ከቶውንም እውነተኛ ህይወት ሊኖሩበት አይችሉም እንጂ፡፡ምክንያቱም እነሱ ቤተ-መንግስቱን ገንብተው ሲጨርሱት እራሳቸው ጭምር ከሞቱት በላይ ከኖሩት በታች በመሆን ወደ ቁም-ሙታንነት ስለሚቀየሩ ማለት ነው፡፡
  ስለዚህም በሌላው ጥፋትና ውድቀት የሚገኝ ማንኛውም ጥቅምና ስልጣን መጨረሻው ጥፋት ነው የሚሆነው፡፡ብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን አሁን ለደረስንበት አስከፊ ጥፋት ውርደት ችግርና ውድቀት የተዳረግነው ደግሞ ዛሬ በሌላው ወገናችን ወይንም ሀገራችን ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥፋት ውርደት ችግርና ውድቀት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወዲያውኑም ይሁን ይዋል ይደር በሰተኋላ ላይ የእያንዳንዳችን የራሳችን ጥፋት ውርደት ችግርና ውድቀት እንደሆነ ፈፅሞ ካለመረዳታችን የመነጨ ነው፡፡ዛሬ የገዛ ወገኑን ዘርፎ ገድሎ አደህይቶ ምርጥ ፎቆችንና ምርጥ ቪላዎችን ገንብቶ ምርጥ ዘመናዊ መኪናዎችን በከተማ አደባባዮች ለማሽከርከር የሚመኝ ምን አይነት ስብእናና ደስታ እንደሚጎናፀፍ ለመገመት ብዙም አያዳግትም፡፡ታላቁ የፊዚክስ ሊቅ “For every action force there is an equivalent reaction force.” እንዳለው ለምንሰራው ማንኛውም ክፉም ይሁን መልካም ስራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወዲያውኑም ይሁን ይዋል ይደር በሰተኋላ ላይ ምላሹን በሂሳብ ማወራረድ ስሌት መልሰን እናገኘዋለን፡፡አዎ ተፈጥሮና ህይወት ይህንን ያደርጉ ዘንዳ ግድ ነውና፡፡ምክንያቱም የተፈጥሮ ህግ በብልጣብልጥነትና በስግብግብነት ስሌት የሚሸወድና የሚታለፍ ስላለሆነ ማለት ነው፡፡አንድ ከተናገርከው ትልቅ ቁም ነገር ውስጥ “የማንፈልገው እንጂ የማያስፈልገን” ነገር የለም በማለት የተናገርከው ነገር ነው፡፡አጠቃላዩ ህይወትንም ልንመራበት የሚገባው በምነፈልገው ነገር ብቻ ተመስርተን ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ይበልጡኑ በሚያስፈልገን ነገር ላይ ተመስርተን ጭምር የመሆኑ ጉዳይ ነው እጅግ እንቆቅልሽና ፈታኝ ያደረገው፡፡ብዙዎችችንም ይህንን መሰረታዊ የተፈጠሮ እውነታ በስፋትና በጥልቀት ካለመረዳታችን በመነጨ ነው ዲሞክራሲ በሚባለው የሰለጠነው አለም ፋሽናዊ ዘይቤ ጭምር አጠቃቀሙንና አካሄዱን ስላላወቅንበት ነው እንደዚህ ባለ ደረጃ እጅግ ግራ የተጋባነውና ምስቅልቅላችን የወጣው፡፡ለዚህም ነው በቅዱስ መፅሀፍ ሁሉ ተፈቅዷል ሁሉ ግን ለበጎ አይሆንም የተባለው፡፡

  ReplyDelete
 6. After quenching my thirsty (reading the article), I have come up with the following possible connotation.

  1. It refers to the chaos of our church
  2. It is really epic article that let the Ruling party know the value of
  multi-party system and the indispensable contributions of
  opposition parties towards building one Socio-Political Nation.
  3. The increasing danger of deforestation and the apparent loss of
  the balanced eco system due to climate change. There is no action
  more devastating than human who makes the world very harmful.

  Thank You Daniel,
  May God Bless Ethiopia Amen

  ReplyDelete
 7. እነሆ ሰዎቹ ሁሉ ለጽሁፉ የተለያየ አንድምታ አወጡለት። የደራሲው አንጀት ራሰ። ጭንቅላቶች ስለሰሩ። በሳቅ

  ReplyDelete
 8. ዳኒ በጣም ጥሩና አስተማሪ ታሪክ ነው። የሰው ልጂ ሲባል አስቸጋሪና እውነትን በጸጋ ያለመቀበል ባህሪ ስለተጠናወተው እንጂ ማንም ይሁን አሁን የትኛውም ደረጃ ላይ ይገኝ እዚህ ቦታ የደረሰው በሰው ትከሻ ላይ ተረማምዶ ነው፣ ነገር ግን ልክ እንደ ጫካው ሁሉ አሁን ያለንበትን ብርሐን እኛው ያመጣነው ይመስለንና ኢምንት ጉድፍ ተራራ አሳክለን ያለችንን ስልጣን፡ እውቀት፡ ገንዘብ ...ተጠቅመን መልሰን ያንኑ ህብረተሰብ እንበዘብዛለን፡ እንቀማለን፣ እናሳድዳለን ሲብስም እንገድላለን።
  "ሳይደጋገፉ መጥፋት ይቻላል፤ ሳይደጋገፉ መኖር ግን አይቻልም" እንዳልከው ሁሉ ምክንያት እየፈለጉ ከመናጨት፡ ከመፋጀት ይልቅ ምክንያት እየፈለጉ መስማማትንና አብሮ የመኖር ጥበብን እግዚአብሂር ያድለን።

  ReplyDelete
 9. ለምን እንደሆነ አላውቅም አብዛኛዉ አስተያየት ሰጨ ሰዎች መልካምነትን ከመንግስት ስትጠብቁ ይገርመኛል መንግስት እኮ የኛግልባጨ ነው፡፡ ነገሮችን በጥሞና መመልከት እና አርቆ ማስተዋል ነው የሚጠቅመው ከራሳችን እንምር አስቲ

  ReplyDelete
 10. This is amazing and truly history so much thank you MAY GOD BLESS YOU..KALE HEYEWOT YASEMALIN BEDIME BETSEGA YAKOYLEN!!!!

  ReplyDelete
 11. እጅግ በጣም አስደናቂና አስገራሚ ትምህርት አዘል ታሪክ ነዉ የተጻፈዉ በእዉነት አምላኬን የምለምነዉ ረጅም እድሜ ከጤንነት ጋር እንዲሰጥህ ነዉ።እግዚአብሔር ይባርክህ።

  ReplyDelete
 12. Many thanks Dani! Medihanealem lehulachin Nitsuh Libn Yisten!

  ReplyDelete
 13. Dani betam arif tsihuf new. It will be very very interesting strory , if it is produced with animation film. Birtatun yistih.

  Akbari eheteh

  ReplyDelete
 14. tahadesom manoreo kamachawem balaye baagelegelote enedenebarata aderegonale

  ReplyDelete
 15. wede rasu HIWOT legelebetew bezu negerochin ymaral . . . teredechalehu . . . .wede tegbar enlewetewe zend melekam lebona yetadelen . .

  ReplyDelete
 16. it is really nice.

  ReplyDelete
 17. Thank you Dani. Yes, from the beginning.God created as interconnected. We, not only peo, le, but all creatures need one another. That is why we need to have respect to all. It is sad most of us are very discriminatory to do the right thing. We usually want to be nice for groups and things we felt belong to us but ignorant of, even cruel to, others whom we think are not related to us. But the fact is we ALL need each other. That is why we need you Dani as you need us! ! God bless you.

  ReplyDelete
 18. But, Danni,
  Why do you advocate for the elimination of other sebakians, elimination in every way in the name of Tehadiso zemecha, when they too have a conviction that they preach Jesus. It is you and your organization MK that instigate violence on them, no meimen had ever organized itself to launch such an ugly revolution. Yemitastemirew lela yemitseraw lela. Although I am fully with you in this article, I disagree to how you lead your Christian life. Libonahin yaknalih.

  ReplyDelete
 19. To "But, Danni,"

  I thought you are one of the so called Preachers or active activist of the Tehadiso Conspiracy.

  I have been growing up in Sunday School for the last 18years, but I have never get captured because of the preachings of the so called Sebakian.

  Those groups are always trying to give us what is called in journalism "News Flash." Any body can give us a lovely and well constructed narration of any thing. But Christianity is not Literature!!!

  ReplyDelete
 20. Dear Dn. Daniel Kibret:

  I'm just want to thank you for creating this site and may God bless you for that. Specially, since the day you added PDF format, I never missed any of you writtings. Most of them are very educational and helpfully. Honestly, the PDF format make it easy for us who regularly use iPod or iPhone to vist your site. Now, we have no problem to read any of the new posts. Once again, thank you and GOD bless you.

  Mr. Y

  ReplyDelete
 21. betam tiru timhirt new lene ,ye'egziabher bereket kantegar yihun

  ReplyDelete
 22. «ሳይደጋገፉ መጥፋት ይቻላል፤ ሳይደጋገፉ መኖር ግን አይቻልም» ታላቅ መልዕክት ነው።

  ReplyDelete
 23. Unity is power and difference is beauty.
  From Ethiopia, Addis Abeba

  ReplyDelete