ሴትዮዋ ልጃቸው ከቻይና ትወልዳለች አሉ፡፡ አንድ ወር እንደሞላት ልጂቱ ትሞትና ልቅሶ ይጠራሉ፡፡ ታድያ እያለቀሱ ወደ ድንኳኑ ሲገቡ ምን አሉ መሰላችሁ «እኔ ድሮም ጠርጥሬ ነበር፣ ጠርጥሬ ነበር፤ የቻይና ነገር ይኼው ነው አይበረክትም» አሉ ይባላል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሚዲያ ስማቸው ከሚነሣ ሀገሮች እና ሕዝቦች መካከል የቻይናን እና የቻይኖችን ያህል ቦታ ያለው የለም፡፡
በመንገድ ሥራ፣ በግድብ፣ በማዕድን ማውጣት፣ በቴሌ ኮሙኒኬሽን፣ በሸቀጣ ሸቀጥ፣ በፖለቲካ፣ ባህል ሁለ ነገራችን ቻይና ቻይና ይላል፡፡ የኢትዮጰያ ቴሌቭዥን እንኳን በቀን ውስጥ ቢያንስ አንድ የቻይና ዜና ሳያሳየን አይውልም፡፡ ጠላ ቤት፣ ጠጅ ቤት፣ ሥጋ ቤት፣ ጉልት ገበያ፣ መርካቶ፣ አትክልት ተራ፣ አጠና ተራ፣ በግ ተራ፣ ካዛንቺስ፣ ቺቺንያ ዘወር ዘወር ብትሉ ከአሥሩ ሰው አንድ ሦስቱ ቻይና ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡
እንዲያውም ከመብዛታቸው የተነሣ እንደ አንድ ብሔረሰብ ተቆጥረን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ወንበር ይሰጠን ብለዋል እየተባለ ይቀለድም ነበር፡፡