Tuesday, September 13, 2011

የዘመድ ቄስ ሀገራችን የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ ይባላል፡፡ ሰው ሲሞት ካህናት ይጠሩና ለሟቹ ጸሎት ያደርጋሉ፡፡ ይኼ ጸሎት «ፍትሐት» ይባላል፡፡ ለካህኑ ፍትሐት ማድረግ የክህነት ግዴታው ነው፡፡ ካህን ሆኖ የተሠማራበት፣ ምናልባትም እንጀራ የሚበላበት፣ ወይንም ደግሞ «ሥራው» ነው፡፡
ምንም ቢሆን ግን ሟች ዘመዱ ነውና ያለፈ ሕይወቱን፣ ውለታውን፣ አብረው ያሳለፉትን፣ መለየታቸውን እያሰበ ደግሞ ያለቅሳል፡፡ ዘመድ መሆኑ እንዳይፈታ፣ ካህን መሆኑም እንዳያለቅስ አያግደውም፡፡ ለዚህም ነው «እየፈታ ያለቅስ» የተባለው፡፡
ይህ አባባል ሁለት ነገሮችን አንድ አድርጎ የያዘ ነው፡፡ ኃላፊነትን ወይንም ሥራን እና ሰብአዊነትን፡፡ መፍታት ኃላፊነቱ ነው፡፡ የተሠማራበት ግዳጁ፡፡ ማልቀስ ሰብአዊነቱ ነው፡፡ ሰው መሆኑ፡፡ ሰው በማንኛውም ሥልጣን፣ በሞያ እና ክብር ላይ ሲቀመጥ በውስጡ ሰውነትን መርሳት የለበትም፡፡ ነገሮችን በሥልጣን መነጽር፣ በዕውቀት መስተዋት ወይንም በክብር መስኮት ብቻ ማየት የለበትም፡፡ በሰብአዊነትም ጭምር እንጂ፡፡ እርሱም ሰው ሆኖ የዚያኛውንም ወገን ሰውነት ሳይዘነጋ አንዳንዴም ራሱን በዚያኛው ጫማ ላይ አቁሞ ማየትም አለበት፡፡

በማንኛውም አደባባይ የዘመድ ቄስ ሲገኝ እንዴት መልካም መሰላችሁ፡፡ ፍርድ ቤት ተከሳችሁ ስትቀርቡ፣ በወንጀለኛ መቆሚያ ሳጥን ውስጥ ስትቆሙ፣ ዳኛው የዘመድ ቄስ ቢሆንላችሁ እንዴት በታደላችሁ፡፡ ይኼ ሰው ተጠርጣሪ ነው፡፡ ይህንን እና ያንን ወንጀል ፈጽሟል ተብሏል፡፡ ይህ ወይንም ቅጣት ይገባው ይሆናል፡፡ ግን ሰው ነው፤ የሰው ክብር ይገባዋል፡፡ እንደ ሰው ሊሳሳት ይችላል፤ ርቱዕ የሆነ ፍርድ ይገባዋል፤ ምናልባት ቤተሰብ ይኖረዋል፣ ልጆች ይኖሩታል፤ የሕግ ትምህርት እጥረት፣ የማስረዳት ችሎታ ማነስ፣ ዝም የማለት አባዜ ይኖርበት ይሆናል የሚል ሰብአዊነት ከዳኛው ካገኛችሁ እንዴት ታደላችሁ፡፡
አንድ ዳኛ ያጫወቱኝን ልንገራችሁ፡፡ በተዘዋዋሪ ችሎት እየዞርን እንፈርድ ነበር አሉ፡፡ አንድ ከተማ ወደ አሥር የሚጠጉ ሰዎች በአንድነት ተከሰው ሁለት ጊዜ ቀርበዋል፡፡ በሦስተኛው ቀጠሮ አንድ የባላገር ሰው በጋቢው ውስጥ እጁን ወጣ፣ መልሶ ገባ ያደርገዋል፡፡ በፍርሃት፡፡ አብሮን የነበረው ዳኛ «ይኼ ሰው ባለፈውም እጁን እንደዚህ ሲያደርግ አይቼዋለሁ ምንድን ነው አለን፡፡ እንጠይቀው ተባባልንና ጠየቅነው፡፡
«ጌታው» አለ ባላገሩ፡፡ «እኔኮ ስማቸው ከተጠሩት ሰዎች መካከል አልተጠራሁም» አለን፡፡ ደንግጠን ስሙን ጠየቅነው፡፡ እውነትም ስሙ ከሰዎቹ መካከል የለም፡፡ «ታድያ ለምን ትቀርባለህ አልነው፡፡ «አይ ዝም ብለው ነው የሚያመጡኝ» አለን፡፡ እጅግ በጣም አዝነን ሰውዬውን ወዲያው ፈትተን ፖሊሲቹን ቀጥተናቸዋል አሉኝ፡፡
የዘመድ ቄስ ሲገኝ እንዲህ ነው፡፡ ባላገር የባህል ነገር ይዞት፣ ያልተማርኩ ነኝ ብሎ አስቦ፣ ለፍርድ ቤት ምን እንደሚባል ባለማወቁ ወይንም ደግሞ ልናገር አልናገር በሚል ፍርሃት ይሆናል እጁን ወጣ መለስ የሚያደርገው፡፡ በሀገሩ ዳኛ መዳኘት ጥቅሙ የሀገሩን ሰው ልማድ እና ጠባይ እንዲያውቀው ነው፡፡ ሰብአዊነት እንዲኖረው፡፡
ሌላ እኔ በዓይኔ ያየሁትን ደግሞ ላውጋችሁ፡፡ አንድ ችሎት ተቀምጠን አንዲት በእድሜ ወደ ስድሳ የሚጠጉ ጎንበስ ብለው በመቋሚያ የሚሄዱ ጥቁር በጥቁር የለበሱ እናት አብረውን ነበሩ፡፡ የአንድ ወጣት ስም ሲነሣ ከመቀመጫቸው ተነሡ፡፡ ዳኛው «እርስዎ ምንድን ነዎት?» አላቸው፡፡ «እናቱ ነኝ፣ ዋሱ ነበርኩ፡፡» አሉ፡፡ «ባለፈው ችሎት ለምን አልቀረቡም? ልጅዎ በመጀመርያ ቀረ ከዚያ እርስዎም ቀሩ፣ ለዚህ ነው በፖሊስ ተይዘው ይምጡ የተባለው» አለ ዳኛው፡፡ «ልጄ ሞቶብኝ ነው የቀረሁት» ብለው ዕንባቸው ዱብ ዱብ አለ፡፡ ዳኛው ተቆጣ፡፡ «ታድያ መሞቱን ለፖሊስ ማስረጃውን ይሰጣሉ እንጂ ለምን ይቀራሉ» ሁላችንም ክው አልን፡፡
ለእኒህ እናት ልጃቸው ሞቶባቸዋል፡፡ እንዲያውም ጎበዝ ናቸው ሕግ አክብረው መምጣታቸው፡፡ ሊታዘ ንላቸው፤ ሊከበሩ እና ሊመሰገኑ ይገባ ነበር፡፡ የዘመድ ቄስ አጥተው ነው የተወቀሱት፡፡ ዳኝነት ኃላፊነት ቢሆንም ርኅራኄን እና ደግነትን አያጠፋምኮ፡፡ አይዞዎት፣ እግዜር ያጽናዎት፤ እንዲህ እና እንዲያ ያድርጉ ቢላቸው ምንኛ በመረቁት፡፡ የዘመድ ቄስ አጡ፡፡
ሐኪም ቤትስ የዘመድ ቄስ አይናፍቃችሁም፡፡ አንዳንድ የሕክምና ባለሞያዎች ታመው የማያውቁ፣ ወይንም የታመመ ወገን ኖሯቸው የማያውቅ ይመስል ለምን ኮስተር፣ ቆጣ ብለው ያክሙናል፡፡ በፊታቸው ላይ የሮቦት እንጂ የሰው መልክ ለምን የላቸውም? እህ፣ ሞትኩ፣ ተቃጠልኩ፣ ወገቤን ሸከሸከኝ፣ ራሴን ከተከተኝ፣ ሆዴን ናጠኝ እያልን ስንመጣ የማዘን፣ የመራራት ስሜት ቢያሳዩን ምናለ፡፡
በተለይ ወላድ ሆናችሁ፣ ብቻቸሁን አንድ ቤት ውስጥ ልጃችሁን ለመውለድ ስታምጡ፣ ስትጨነቁ እና ስትጮኹ፣ የሲቃም ድምጽ ስታሰሙ ምናለ እንደ ባህሉ ጠጋ ብለው፣ የኀዘን ስሜት ቢያሳዩዋችሁ፡፡ ቢያወሯችሁ ቢያጫውቷችሁ፡፡ «ይቺስ የባሰቺው ናት፣ ምነው በርታ በይ እንጂ፣ ገና ምኑን አይተሺው፣» እያሉ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን ከሚመስሉባችሁ፣ ሲብስም እንዴው በሰዓት እንደተሞላ ሮቦት ሰዓት ጠበቀው ጎርደድ እያሉ መጥተው፣ ምናምን ለክተው ለራሳቸው በራሳቸው ቋንቋ እያወሩ ጥለዋችሁ ከሚወጡ ምናለ የዘመድ ቄስ ቢሆኑላችሁ፡፡ እንደ ባለሞያ ያክሟችሁ፣ እንደ ሰው ደግሞ ቢያዝኑ፣ ቢያጫውቷችሁ፣ ቢያበረቱ፣ ቢረዷችሁ፡፡
አንዳንድ መሥሪያ ቤት ስትሄዱስ የዘመድ ቄስ አይናፍቃችሁም፡፡ ትልቁንም ትንሹንም፣ ወጣቱንም፣ ሽማግሌውንም «ምን ፈልገህ/ ነው» የሚል ጥበቃ አሁን እርሱ ከኢትዮጵያውያን ማኅፀን የወጣ ነው? አንቱታውን የት አድርሶት ይሆን? «ዱርዬ» የሚባሉት ወገኖች እንኳን ይህንን ባህል አይረሱትም፡፡ «ማዘር/ፋዘር» ቢሉም አንቱታን አልተውም፡፡
የለም፣ ነገ፣ ሌላ ጊዜ ጠይቅ፣ እየታየ ነው፣ ፋይል ጠፍቷል፣ አይቻልም፣ ስብሰባ ላይ ነን፣ የሚለው የቢሮ «ባለ ሥልጣን» እውነት ከሰው የተፈጠረ ነው? መመላለስ እንደ ሚያሰለች፣ የጉዳይ አለመፈጸም ተስፋ እንደሚያስቆርጥ፣ የፋይል መጥፋት ስንት ጣጣ እንዳለው፣ እርሱ በየቀኑ ሲሰበሰብ ስንት ሥራ እንደ ሚወዘፍ፣ ሰው እርሱ ቢሮ ሲመጣ ስንት ሥራ ጥሎ እንደሚመጣ ጠፍቶት ነው? ምነው የዘመድ ቄስ ቢሆንልን? እንደ ባለ ሥልጣንነቱ ይሥራ፣ ይወስን፡፡ ግን ደግሞ ሰውኮ ነው፡፡ እርሱምኮ ሌላ ቦታ ሄዶ ባለ ጉዳይ ይሆናል፡፡ የቦታ እና የጊዜ ጉዳይ እንጂ ባለ ጉዳይ የማይሆን ሰው የለምኮ፡፡ እኔ በዚህ ባለጉዳይ ቦታ ብሆን ተብሎ አይታሰብም እንዴ፡፡ ማዘን፣ መራራት አይገባም እንዴ፡፡
ግብር የሚወስኑ፣ ግብር የሚቆርጡ ወገኖቻችን፡፡ በሀገሪቱ ግብር ከፋይነትን ባህል ለማድረግ መሥራታችሁ፣ መውጣታችሁ እና መውረዳችሁ ደግ ነው፡፡ አዲስ ባህል እያመጣችሁ ነው፡፡ በአደገው ዓለም «እኔ ግብር ከፋይ ዜጋ ነኝ» ብሎ መናገር ክብር ነው፡፡ ግን የዘመድ ቄስ ሁኑ እባካችሁ፡፡ ስትወስኑ ርኅራኄ እና ቅንነት የሚባሉት የኅሊናችሁን ክፍሎች ተጠቅማችሁ ይሁን፡፡ እያለቀሳችሁ ፍቱ፡፡
ይኼ ሰው ለፍቶ፣ ጥሮ፣ ግሮ፣ ወጥቶ፣ ወርዶ የሚያድር ዜጋ ነው፡፡ ትናንት ብቻ ሳይሆን ነገም እንዲሠራ እንዲነግድ ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያ ሀገሩ ናት ግብር አይደለም ደሙን የሚሰጥላት፡፡ የጠላት ሀገር ዜጋ አይደለም፣ ወገናችሁ ነው፣ እርሱም ሳይመረር፣ ሀገሪቱም ሳትደኸይ የሚጓዙበትን መንገድ ፈልጉ፡፡ የዘመድ ቄስ ሁኑ፡፡
በየእሥር ቤቱ፣ በየ ወኅኒ ቤቱ ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ የዘመድ ቄስ ነው፡፡ እሥረኛውን ሰው ነው ብሎ የሚያስብ አሣሪ፡፡ የሰውነት መብቱን የሚጠበቅ፣ እንደ ሰው የሚያዝን፣ ይህ ሰው ተሳስቶ፣ አጥፍቶ፣ ቀን ጥሎት፣ መንገድ ስቶ እዚህ ቦታ መጣ እንጂ እንደ እኔ ነጻ ቢሆን የሚወድ ነው፡፡ የሚያበሳጨው፣ የሚያናግረው፣ ጠባ ዩን የቀየረው ሁኔታው ነው ብሎ የሚያስብ፡፡ ልጆች አሉት፣ ሚስት አለው፣ ባል አላት፣ እናት አላት ብሎ የሚያስብ፡፡ ይገባዋል፣ ይበለው፣ ደግ አደረገው ከሚለው ወጥቶ ባይሆን ጥሩ ነበር ብሎ ቅን የሚያስብ የዘመድ ቄስ፡፡ ሊረዳ፣ ሊያስረዳ፣ ሊረዳ የሚፈቅድ የዘመድ ቄስ፡፡ እያሠረ የሚያለቅስ፡፡
ፖለቲከኞችስ ብትሆኑ ፖለቲከኛ ብቻ አይደላችሁምኮ ሰውም ናችሁ፡፡ እንዲያውም ፖለቲከኛ የሁናችሁት ሰው በመሆናችሁ ነው፡፡ ስለሌላው የፖለቲካ ፓርቲ አባል፣ ስለሚቃወማችሁ ሰው ስታስቡ ምነው የዘመድ ቄስ ብትሆኑ? ያኛውም ወገንኮ ሃሳብ አለው፣ እንዲሰማለት የሚገባ ሃሳብ፣ ያኛውም ወገንኮ ስሜት አለው፣ ሊታወቅለት የሚገባ ስሜት፣ ያኛውም ወገንኮ ስሕተት አለበት፣ ሰው የመሆን ውሱንነት ያመጣው ስሕተት፡፡
ታድያ ስለዚያኛው ወገን ሰታስቡ ለምንድን ነው ስለ ሰው የማታስቡት? ስለ ጭራቅ፣ ስለ ሰይጣን ለምን ታስባላችሁ፡፡ እዚያኛውም ቤት ያሉት ሰዎች ናቸው፡፡ ግን በሃሳባቸው ከእናንተ የተለዩ ሰዎች፡፡ እዚያኛው ቤት ጥፋት፣ ችግር፣ መከራ፣ ሲደርስ ለምን ጉሮ ወሸባዬ ትጨፍራላችሁ፣ ለምን እየፈታችሁ አታለቅሱም፡፡
የሃይማኖት ሰዎች ነን የምንለውስ ቢሆን ምነው ከኛ ወገን የዘመድ ቄስነት ጠፋሳ፡፡ ስለዚያኛው ወገን ስናስብ ስለተሳሳተ፣ ከኛ በተለየ መንገድ ስለሄደ፣ ስለተለየ፣ ስለጠፋ ወገን ለምን አናስብም? መለየቱን፣ መራቁን፣ መጥፋቱን፣ መሳሳቱን ለምን በጭካኔ መንፈስ እናወራዋለን? የርኅራኄ ሀገርዋ ወዴት ነው? ማደርያዋስ ወዴት ነው? የኀዘን ማደርያዋ ወዴት ነው? ከመንፈሳውያን ወገን ከሌለች፣ ታድያ የፍቅር ሀገርዋ ወዴት ነው? ከሃይማኖተኞች ወገን ካልተገኘች፣ ታድያ የሰብአዊነት ማኅደርዋ የት ነው?
ምነው እየፈታን ብናለቅስ? ጥፋቱን፣ ውድቀቱ፣ ኪሳራውን፣ ድክመቱን፣ ውርደቱን፣ ሕመም እና ሞቱን ብቻ ለምን እናስበዋለን? እንደ ገባ ይውጣ፣ እንደወጣስ ይቅር ለምን እንላለን? እኔስ በርሱ ቦታ ብሆን ለምን አንልም፡፡
በአንድ የሶርያ ገዳም በአምስተኛው መክዘ ላይ አንድ መነኮስ ያጠፋል፡፡ በመነኮሱ ላይ የተሾመው ሌላው መነኮስ ያንን ጥፋተኛ መነኩሴ በሌሊት ከገዳሙ ያባርረዋል፡፡ አበ ምኔቱ ከብዙ ጊዜ በኋላ ሰምተው ያንን አባራሪ መነኮስ ያስጠሩትና ያደረገውን ይጠይቁታል፡፡ አባራሪውም «አስወጥቼ በሩን ዘጋሁበት» ይላቸዋል፡፡
እርሳቸውም «እኔ ማስወጣትህ እና በሩን መዝጋትህ አላሳዘነኝም የልብህን የርራኄ በር ዘግተህ ድርጊቱን እንደ ጀብዱ ማውራትህ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር በአዳም ከገነት መባረር የተደሰተ ይመስልሃል» አዘነ እንጂ፤ ለዚህ ነው ዳግም ተወልዶ ያዳነው፤ አንተ ግን የወንድምህን መጥፋት በጀግንነት ትናገራለህ፤ በዚህ ልብህ እንኳን መነኩሴ ክርስቲያን መሆን አትችልም» አሉት ይባላል፡፡ ምናለ እየፈታህ ብታለቅስ ማለታቸው ነው፡፡
የዘመድ ቄስ የት ነው ያለኸው? ስትቀጣ፣ ስትፈርድ፣ ስትሠራ፣ ስታሥር፣ ስትወስን፣ እያለቀስክ የምትፈታ ሩኅሩኁ ወገን፡፡ ሕግ፣ ሞያ፣ ሥራ፣ ወንበር፣ እውነት፣ ሀገር፣ ሆኖብህ በሰው ላይ ለምታደርገው ነገር ሁሉ በውስጥህ እርሱም እኮ እንደ እኔ ሰው ነው፣ ብቻ ሳይሆን እኔምኮ እንደ እርሱ ሰው ነኝ የምትለው የዘመድ ቄስ የት ነው ያለኸው? ያለህበትን ብትነግረኝ አንተ መጥቼ እታከም፣ እዳኝ፣ እገለገል፣ ግብር እከፍል፣ እታሠር፣ እቀጣ፣ ነበር፡፡
ወደ ዴንቨር ጉዞ፣ አየር ላይ ተጻፈ፡፡

42 comments:

 1. Wonderful analysis...

  ReplyDelete
 2. “ በሃሳባችንን በተግባራችን የህይወትን ክቡር አላማና ሰብአዊ ክብራችንን ከመዘንጋታችን በስተቀር ሁሉም ነገር ውብ ነው”ያለውን ሰው አስታውስከኝ ዳኒ…. እንዲህ ሁሌም ከሰውኛነት አደባባይ አንጣህ !!

  ፍቅር-ዓለም ከጆበርግ

  ReplyDelete
 3. Dn.Daneil! This is an interesting issue. Let we be this የዘመድ ቄስ for others and Let God prepare የዘመድ ቄስ for us too.

  ReplyDelete
 4. ድንቅ እይታ... ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!
  ምንተስኖት

  ReplyDelete
 5. እጅግ በጣም የሚጥም መልእክት ነው፡፡ እግዜር ይስጥህ….እንኳን አደረሰን…አመቱን የተባረከ፣ ጥሩ ነገሮችን የምንሰራበት ያድreግልን…አምላክ ሐገራችንን ይባርክልን፡፡ አሜን

  Harry from Addis

  ReplyDelete
 6. Dn.Daniel, good points. Thanks and keep up those articles like this and make yourself far from the dirty politics game.That is not for you.God bless your service.

  ReplyDelete
 7. +++

  Selam Dani. KHY Yasemalen Be Ewent. Be Tsega Be Edeme Yitebekelen.

  KeGermany Frankfurt

  ReplyDelete
 8. ዲ.ን ዳኒ በእውነት ትክክል ብለሃል፡፡ ለምሳሌ እናንሳ-በኢትዮጲያ ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የቤተክርስቲያን መሪዎች የደብር፣የቤተክህነት፣የሃገረ ስብከት፣የሲኖዶስ፣--- ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል መሪነት ደረጃ የወጡት እጅግ አስቸጋሪውንና ፈታኙን የአብነት ት/ት ቤት ህይዎት ቀምሰው ነው የሚል ሰፊ ግምት አለኝ፡፡
  ያለ ምግብ መማርን፣ያለመብራት ማጥናትን፣ያለጫማ መጓዝን፣ከቤተሰብ እርቆ መኖርን ---- ተለማምዶ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ለመሪነት የሚበቁት የቤተክርስቲያኗ ሰዎች ከስልጣን በኋላ ለተተኪዎቻቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ እና እንክብካቤ ስንመለከት በአብዘሃኛው እጅጉን የሚያሳዝን ነው፡፡ ተማሪዎች-ከቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ እንጨት ለቅመው ድርቆሽ እንዳይሰሩ፣መብራት እና ውሃ እያለ መብራት እና ውሃ እንዳይጠቀሙ የሚከለክሉት መሪዎች በእውነት የዘመድ ቄስነት ባህሪያት ይጎላቸዋል ባይ ነኝ፡፡
  ለእኔ አንድ ሰው ታላቅ ነው ብየ ልናገር የምችለው ያ ሰው ዛሬ ላይ ሆኖ ትናንትና ምን እንደነበረ ተገንዝቦ በእርሱ ትናንትና ማንነት ደረጃ ላይ ያሉትን የዛሬዎቹን ሰዎች መርዳት ሲችል ብቻ ነው፡፡እናም በየቦታው ሰውን የማንገላታት፣የማሰቃየት፣የመናቅ፣--ባህሪያቶች በዘመድ ቄስነት ባህሪያቶች ቢተኩ እጅጉን ጥሩ ናቸው እላለሁ፡፡
  ዳኒ መቸም በጡመራህ ብዙ ነገር ተጠቅመናል፣ተምረናል፣ተለውጠናል አሁንም ግን ብዙ የምንጠብቅ ቢሆንም ከተቻለህ ዳኒ ስለሰበካ ጉባኤ(የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያኑን) ማለቴ ነው አንድ ነገር ብትጽፍልን፡፡ይህንን ያልኩበት ታላቁ ነገር ዳኒ ምን መሰለህ ለቤተክርስቲያኒቱ እድገትም ሆነ ውድቀት ይህ ክፍል የጀርባ አጥንት ስለሆነ ነው፡፡
  ውብሸት ተንታው

  ReplyDelete
 9. etub ke dallas
  melkam eyita enam egig astemari new ena berta wendime daneal amlak behyweth yitebkh

  ReplyDelete
 10. There is no end to your intelligent posts! Expecting them in books soon??

  ReplyDelete
 11. ውይ! በውነት ይጥማል። እግዚአብሔር ይባርክህ።

  ReplyDelete
 12. በጣም ጥሩ መልእክት ነው እግዚአብሔር ያበርታህ "በአንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አታድርግ" እንደተባለው. ስለሆነም ሁሉም ለህሊ ናው ቢኖር ና ሁል ጊዜ መልካም ብቻ ቢያስብ ስለፍቅር ሁሉንም ብንተወው ከህሊና እዳ ነጻ እንሆናለን.

  ReplyDelete
 13. ይኼ ሰው ለፍቶ፣ ጥሮ፣ ግሮ፣ ወጥቶ፣ ወርዶ የሚያድር ዜጋ ነው፡፡ ትናንት ብቻ ሳይሆን ነገም እንዲሠራ እንዲነግድ ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያ ሀገሩ ናት ግብር አይደለም ደሙን የሚሰጥላት፡፡ የጠላት ሀገር ዜጋ አይደለም፣ ወገናችሁ ነው፣ እርሱም ሳይመረር፣ ሀገሪቱም ሳትደኸይ የሚጓዙበትን መንገድ ፈልጉ፡፡..Correct!!

  ReplyDelete
 14. Qale hiwot yasemalen betam tmhert sechi sehuf new Dani bezemen yohanes degmo yebelete endetesera yeqdus yohanes amelak bechernetu yerdahe.
  HG from GA

  ReplyDelete
 15. a good message,keep it up!!

  ReplyDelete
 16. ሃይ ዳኒ እንኳን አደረሰህ ጥሩና አስተማሪ ጽሁፍ ነው? ግን አንተው ራስህ የቄስ ዘመድ ነህ? የምትጽፈውን ለራስህ በመጀመሪያ ተጠቅመህ ነው? ምን ያህል አንተስ ርኅራኄ አለህ? እባክህን መጀመሪያ የራስህን ሕይወት በምትጽፈው ጽሁፍ ለመመልከት
  ሞክር ከዚያ በኃላ ፖስት አድርገው። በቅርቡ የጳጉሚን ወር የይቅርታና የምስጋና ቀን ብለህ ብዙ አልክ አንተ ግን በዚህ ወር የጥላቻና የበቀል ጽሁፎችን ጻፍክ። እባክህን ራስህን ሁን አለበለዚያ ሦስት ሰባት አባቶች ታጥምቁህ። አክባሪ ውንድም።

  ReplyDelete
 17. Hey Mr. Daniel. i am a big fan of yours. i have never missed any of your posts and i have read two of your books. But this one is my first comment on your page. i love the way you express your views but it doesn't mean i am always agree with you. since you write here your view of angle so i may sometimes see that idea on a different view of side but above all your passion to share your ideas to other makes you brave. i think i found this post one is so touchy and push me out to say something. once the American journalist said 'if each man or women could understand that every other human life is a full of sorrows, or joys, or base temptations, or heartaches, and of remorse as his own....how much kinder, how much gentler he would be' this is the fact that we luck on our country, able to see the other persons ups and down like the same we face everyday. the degree might differ but we all human face the same motions. we should know that its the act of humanity that kept our country through the wars, droughts and hunger. i can tell that humanity and kindness will go through heredity, our act humanity of will be a root which may plant to the next generation and make Ethiopia a better place to live for our children. while we are doing our jobs, tasks or anything we always have to remember that 'our most basic common link is that we all inhabit this small planet. we all breath the same air. we all cherish our children future. and we are all mortal' as John. F Kennedy once said. thank you to Mr. Daniel for your cherish ideas.
  Alemseged, USA

  ReplyDelete
 18. Excellent view!!!

  May God give us mind to think like "YEZEMED KESS"

  ReplyDelete
 19. Dn. Daniel 1oq.
  Venusia from Holeta

  ReplyDelete
 20. Dear Daniel,

  Thank you very much to your wonderful intervention. You taught us how we should be empathetic. I agree with you we should don't do something against another which we don't want to be done on us.

  ReplyDelete
 21. የዛሬው ጡማር ብሶት የወለደው ብዕር ነው የሚመስለው፤ በጣም ግሩም እኔ የምለው በስራ ላይም የዘመድ ቄስ ይናፍቃናል፤ ቢሮ ምቹ ወንበር ላይ ተቀምጦ በከረቫት ታንቆ ላፕቶፕ እየነካካ፤ ሃይላንድ እየተጎነጨ፤ ይህን አድርግ ይህን አታድርግ ይህን ቁረጠው፤ ይህንን ደግሞ ፍለጠው እያለ ትዕዛዝ ከሚሰጥ፤ ትዕዛዝ ከሚያበዛ፤ እንደ አጼ ምንሊክ ሱሪውን ሰብስቦ ጭቃ የሚያቦካ ሸሚዙን ሰብስቦ ግድግዳ ላይ የሚለስን አለቃም ይናፍቀናል። እንደ አሉላ ሁሌም ከፊት የሚቀድም አለቃ...

  ReplyDelete
 22. የዛሬው ጦማር ብሶት የወለደው ብዕር ነው፤ በጣም ግሩም እኔ የምለው በስራ ላይም የዘመድ ቄስ ይናፍቀናል፤ ቢሮ ምቹ ወንበር ላይ ተቀምጦ ፤ በከረቫት ታንቆ፤ ላፕቶፕ እየነካካ ሃይላንድ እየተጎነጨ ይህን አድርግ ይህን አታድርግ ይህን ፍለጠው ይህን ደግሞ ቁረጠው እያለ ትዕዛዝ ከሚሰጥ፤ ትዕዛዝ ከሚያበዛ እንደ አጼ ምኒሊክ ሱሪውን ሰብስቦ ጭቃ የሚያቦካ ሸሚዙን ሰብስቦ ግድግዳ ላይ የሚለስን አለቃም ይናፍቀናል እንደ አሉላ ሁሌም ከፊት የሚቀድም...

  ReplyDelete
 23. ወዳጄ ልቤ አየር ለላይ ሆነህ ስትጽፍ የበለጠ ይዋጣልሃል ልበል፣ ግሩም ሃሳብ አስተማሪ ጽሑፍ ነው፡፡ አሁንም ከፍ ከፍ እያልክ ስለሰማያዊውና ስለ መንፈሳዊው ነገር አብዝተህ ጻፍልን፡፡ እዚህ እታች ያለው ያታከተንና ያሰለቸንን አርቲ ቡርቲ ለባለቤቶቹ ተውላቸው፡፡

  ReplyDelete
 24. SEwoche Liyadergulachehu Yemetifelegutene Hulu enantem Endihu Adregualachewe.

  ReplyDelete
 25. May God give us mind to think like "YEZEMED KESS"

  Yidnekachew Tekle

  ReplyDelete
 26. Temechitehignal Dani, Berta, endebefitu beadissu ametim tibebun hulu amilak yadilik.

  "yezemed kess" mehon miyakil metadel new.

  ReplyDelete
 27. yemiketelew emnet yeleleghi behonim yehi keninet eyetwera yalew bezichi betekirstian bemehonu desibeloghale andand eminet tekomoche geni yeheni bemiyatefa melku waym telifobemetal akahed (scienceawye enadergew bemile ) menged bemastemarache yehe yethiopian megelecha yeneberw rehirunt eyetefa metole lealm mekiniyatochen benorutim
  lelaw degmo bezuhanu yamenebetin marageb limad eyaregnew bememtatachin new.manew esti yamenebetin tenagro yelelaw yemiyakebre yehenini senilemamd new yeleloche kusel yemigeban .meche new ende mahiteme gahandi aynet meri noroni yehenini kininet lelelochi araya yemihonilini.amesegnalehu
  eleni

  ReplyDelete
 28. እንዲህ ያለ አስተያየት ለጻፍከው :- " ሃይ ዳኒ እንኳን አደረሰህ ጥሩና አስተማሪ ጽሁፍ ነው? ግን አንተው ራስህ የቄስ ዘመድ ነህ? የምትጽፈውን ለራስህ በመጀመሪያ ተጠቅመህ ነው? ምን ያህል አንተስ ርኅራኄ አለህ? እባክህን መጀመሪያ የራስህን ሕይወት በምትጽፈው ጽሁፍ ለመመልከት
  ሞክር ከዚያ በኃላ ፖስት አድርገው። በቅርቡ የጳጉሚን ወር የይቅርታና የምስጋና ቀን ብለህ ብዙ አልክ አንተ ግን በዚህ ወር የጥላቻና የበቀል ጽሁፎችን ጻፍክ። እባክህን ራስህን ሁን አለበለዚያ ሦስት ሰባት አባቶች ታጥምቁህ። አክባሪ ውንድም።"
  ለምን በደንብ ፅሁፉን አታነበውም? ሃሳቡ ገብቶሃል? እኛ እያለ እኮ ነው የፃፈው! አስተያየት እንዴት እንደሚፃፍ የምታውቅ አልመሰለኝም! በቅንነት ማንበብ ይበጃል ! ብዙ ጊዜ አስተያየቶችህ ቅንነት ይጎላቸዋል! እንዴት እንዴት ነው የምታነበው? እሱ ስለጥላቻና በቀል ጽፎ ይሆናል እያበረታታ ግን አይደለም እባክህ በደንብ አንብብ::" አክባሪ ወንድም " እንዲህ አይጽፍም አጣሞ አያነብም!

  ReplyDelete
 29. ዳኒ የምናውቀው ግን ያላስተዋልነው በእኛነታችን ውስጥ ያለውን ትልቅ ነገር እንድናስተውል ስላደረከን እግዚአብሔር ይስጥህ፡፡ ይህ የዘመድ ቄስነት ከአንተ ምልከታ ውጪ በሆነ ሁኔታ ጥቅምላይ እንዳይውል ቢሰመርበት መልካም ይመስለኛል ፡፡ ምክንያቱም አድሎነት እንዳይበዛ!!! ኢዮብ ነኝ

  ReplyDelete
 30. I wonder if those who should read this would do so and say there saying ! i really wonder

  ReplyDelete
 31. ዳኒ ቃለሕይወት ያሰማልን።
  አምላክ ይስጠን የዘመድ ቄስ
  እየፈታ የሚያለቅስ።
  ብርሀነ ትንሳኤ።

  ReplyDelete
 32. d/n daniel EgziAbher yistln tiru tmhrt new yesetehn. gn ebakh kemenfesawiw alem yemilewm eresahew ende? kante bizu endnmar etebkalehu.yeDingl tbekawa ayileyih!
  tsion

  ReplyDelete
 33. ቃል ገባው ለራሴ በዚህ አዲስ ዓመት በተሰማራሁበት የስራ መስክ ሁሉን ወንድሜን ሁሉን ወገኔን በምችለው ብቻ ሳይሆን በማልችለውም ልረዳ፤ የዘመድ ቄስ ልሆነው። what a wonderful article man

  ReplyDelete
 34. የሃይማኖት ሰዎች ነን የምንለውስ ቢሆን ምነው ከኛ ወገን የዘመድ ቄስነት ጠፋሳ፡፡ ስለዚያኛው ወገን ስናስብ ስለተሳሳተ፣ ከኛ በተለየ መንገድ ስለሄደ፣ ስለተለየ፣ ስለጠፋ ወገን ለምን አናስብም? መለየቱን፣ መራቁን፣ መጥፋቱን፣ መሳሳቱን ለምን በጭካኔ መንፈስ እናወራዋለን? የርኅራኄ ሀገርዋ ወዴት ነው? ማደርያዋስ ወዴት ነው? የኀዘን ማደርያዋ ወዴት ነው? ከመንፈሳውያን ወገን ከሌለች፣ ታድያ የፍቅር ሀገርዋ ወዴት ነው? ከሃይማኖተኞች ወገን ካልተገኘች፣ ታድያ የሰብአዊነት ማኅደርዋ የት ነው?

  ReplyDelete
 35. ዛሬም ወንድሜ ዲያቆን ዳኒኤል ክብረት ይህ ጥሩ እና ድንቅ ምልከታ ነው፡፡ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፡፡መስማት ብቻ አይደለም ለለውጥ/ለበረከት እንድንሆን አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡እንዲህ ባሉ ኢትዮጵያዊ ጉዳዮች ላይ የምታነሳቸው ጉዳዮች ለለውጥ ያነሳሳሉ እራሴን እንደመለከት ያደርገኛል፡፡ለውጥ ከራስ ይጀምራልና፡፡ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡እግዚአብሔር አምላክ ረጅሙን የአገልገሎት እድሜ ከሙሉ ጤንነት ጋር ይስጥልን፡፡እንዲህ ያሉ ኢትዮጵያዊ እውነቶች ያግባቡናል፡፡አዲስ አበባው ነኝ፡፡

  ReplyDelete
 36. ሰሎሞን በርሔ ከአዋሳSeptember 25, 2011 at 1:49 PM

  ትምህርቱ በእውነት በውስጤ ተተክሎ እንዲቀር አድርገሀዋል
  ቃለ ሕይወት ያሰማህ

  ReplyDelete
 37. It is absolutely what every one needs in his day to day life, Thank u brother

  ReplyDelete
 38. የፃፍካቸው ፅሑፎች እጅግ አስተማሪ ናቸው፡፡ በዚሁ ቀጥል በርታ
  አንድ ዓይና ሆነሀ እንዳትቀር እፀልያለው፡፡
  ስማቸው ነኝ ከአዲስ አበባ

  ReplyDelete
 39. አንድ የጠባይ ለውጥ አስተማሪ በቅርቡ በመስሪያ ቤታችን ተገኝቶ በሰጠው ትምህርት ሰው ሦስት ነገሮችን ማሟላት አለበት ብሏል፡፡ እነዚህም አካል፣ አእምሮና መንፈሳዊነት ናቸው፡፡ በተለይ መንፈሳዊነት የሌላቸው ሰዎች በዚህ ጽሑፍ ዳንኤል ያስቀመጣቸው ሰዎችን ባህሪ የተላበሱ ናቸው፡፡ መንፈሳዊነት በውስጣቸው የሌለ ሰዎች የዘመድ ቄስ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
  ዳኒ እነዚህን ትምህርቶች ለሰፊው ህዝብ የምታቀርብትን መንገድ መፈለግ እንዳትረሳ፡፡
  ገብሩ ከአዲስ አበባ

  ReplyDelete
 40. Tank u d. danny i have no word give comment to this article.
  God give all things for u !


  daniel tesfaye adera from eepco

  ReplyDelete