Thursday, September 29, 2011

መርዙ


እነሆ ሁለት እና ሚስቶች መኖራቸው ተነገረ፡፡ ግን ፈጽሞ ሊስማሙ አልቻሉም ተባለ፡፡ ቤታቸው የትዳር ቤት ሳይሆን አፍጋኒስታን ይመስል ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ለምን ሊጋቡ እንደቻሉ ሁለቱንም ያስገርማቸዋል፡፡ አንድ ደራሲ Men from Mars and women from Venus የሚል መጽሐፍ ጽፏል፡፡ እንደተፈጥሯቸው እና ጠባያቸው ቢሆን ኖሮ ወንድ እና ሴት ተጋብተው መኖር የማይችሉ ፍጡራን ነበሩ ነው ጠቅላላ ሃሳቡ፡፡ የትዳር የዘለቄታ ፎርሙላም ይህንን እውነታ ከመረዳት ይመነጫል ባይ ነው፡፡
ታድያ እነዚህኞቹ ከዚህም የባሱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እና ጣልያን፣ እንግሊዝ እና አርጀንቲና፣ አሜሪካ እና ቬትናም፣ ይመስላሉ፡፡

Monday, September 26, 2011

የመጀመርያው የቁንጅና ውድድር በኢትዮጵያ


የዛሬ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን እንዲህ ሆኖ ነበር፡፡
የመስቀል በዓል በዋለ በሁለተኛው ቀን በዓሉን ምክንያት በማድረግ ምናልባት በኢትዮጰያ የመጀመርያው የቁንጅና ውድድር በጎንደር ከተማ ተደርጎ ነበር፡፡
ከልደታ ምሥራቅ ለአበራ ጊዮርጊስ ሰሜን  ከሆነችው በቀሃ ወንዝ አጠገብ ከምትገኘው አጤ ሰቀላ ከምትገኘው ኮረብታ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ ሸራ ድንኳን ተተከለ፡፡ ከጧቱ ከሶስት ሰዓት ጀምሮ በዓሉ ወደሚከበርበት ሜዳ የከተማውና የገጠሩ ሕዝብ ይጎርፍ ጀመር፡፡ 4 ሰዓት ሲሆን ምርጥ መሣርያ የያዙ ወታደሮች እና አጋፋሪዎች ሰለፈኛውን ለማስተናበር ጸጥታውን ለማስከበር በበዓሉ ሜዳ ተሠማሩ፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ፊታውራሪ ገብርዬ በሠራዊቱ ታጅቦ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ አጤ ሰቀላ ደረሰና የዙፋኑን አቀማመጥ ተመለከተ፡፡

Saturday, September 24, 2011

ሰበር ዜና


አዲስ ፊልም ቤት ተከፈተ
አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ፊል ቤት ተከፈተ፡፡ ፊልም ቤቱ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይባላል፡፡ የሚያሳየው ፊልም «ሽኝት» የተሰኘ ሲሆን ሃያ አራት ሰዓት ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ እንግዶች ሲወጡ እንዴት እንደሚሸኙ፣ ሲገቡ ደግሞ እንዴት አቀባበል እንደሚደረግላቸው ያሳያል፡፡
ከዚህ በፊት ቦታው አውሮፕላን ማረፊያ በነበረ ጊዜ የመግቢያ ዋጋው 3 ብር ነበር፡፡ አሁን ግን መግቢያው አሥር ብር በመድረሱ ፊልም ቤት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህንን ፊልም ቤት ከሌሎች ልዩ የሚያደርገው አሥር ብር ከፍሎ የፊልሙ ተዋናይም ተመልካችም መሆን ስለሚቻል ነው፡፡

Friday, September 23, 2011

ይሁንተኞች

በአንድ ሀገር ውስጥ አንደ የዝንጀሮ አለቃ ነበር አሉ ኦሮሞዎች ሲተርቱ፡፡ በመልክ እና በቁመት፣ በትከሻ እና በክብደት የሚመስሉት በዛ ያሉ ዝንጀሮዎች በመንጋው ውስጥ ነበሩ፡፡ ታድያ ለንጉሡ አጎንብሱ በሚለው መመርያ መሠረት የሚመሩ ጥቂት ዝንጀሮዎች አለቃቸውን ለማስደሰት አሰቡ፡፡ አስበውም አልቀሩ እንዲህ አሉት፡፡ «እርስዎን ከሌሎች ዝንጀሮዎች መለየት አልቻልንምና፣ ለየት የሚያደርግ ምልክት ያድርጉ» አሉት፡፡ እርሱም በራሱ ላይ የብረት አክሊል ለማድረግ ወሰነ፡፡
 እነዚያ እበላ ባይ ዝንጀሮዎች እየተከተሉ አባራ ሳይነካው ልብሱን ያራግፉለታል፡፡ ሳያስነጥሰው ይማርህ ይሉታል፡፡ ሳያመው ተሻለዎት? ብለው ይጠይቁታል፡፡ ሳይቀልድ ይስቁለታል፡፡ ሳያዝን ያለቅሱለታል፡፡ ያልተናገረውን ይጠቅሱለታል፡፡ ባልሆነው ነገር ያወድሱታል፡፡

Wednesday, September 21, 2011

አጉል ልማድ

በpdf ለማንበብ
ከአውሮፓ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አውሮፓዊ ገበሬ የጥንት መጽሐፍ አገኘ፡፡ መጽሐፉ አያሌ ምሥጢራዊ ነገሮች የተጻፉበት ባለ ብዙ ገጽ መጽሐፍ ነበር፡፡ ሰውዬው ግን ለማንበብ የቻለው በአንደኛው ገጽ የሚገኘውን አንድ አንቀጽ ብቻ ነበር፡፡
ያም አንቀጽ እንዲህ ይላል፡፡ «በጥቁር ባሕር ዳርቻ አንድ ልዩ ድንጋይ ይገኛል፡፡ ይኼንን ድንጋይ ማንኛውም ነገር ሲነካው የነካውን ነገር ወደ ወርቅነት ይቀይረዋል ይላል፡፡ ይህንን ድንጋይ ከሌሎች ተመሳሳይ ድንጋዮች ለይቶ ለማወቅ የሚቻለው በመንካት ነው፡፡ ድንጋዩ ከተመሳሳይ ድንጋዮች በተለየ ትኩስ እና ሲነኩትም የሚፋጅ ነው» ይላል፡፡

Monday, September 19, 2011

የልብን ከሰይጣን

በ pdf ለማንበብ
ቀደምት አበው እና እማት የሰይጣንን ማንነት በሚገባ ከማወቃቸው የተነሣ ሰይጣን መዋጋት እና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሰይጣንን ራሱን ያታልሉት ነበር፡፡ ይህም መንፈሳዊ ብቃታቸው እና ዕውቀታቸው የቱን ያህል ይደርስ ደነበረ ከሚመሰክሩት ነገሮች አንዱ ነው፡፡
የትምህርተ ኅቡዓት መተርጉማን «ሰይጣን የተነገረውን እንጂ የታሰበውን አያውቀውም» ይላሉ፡፡ ሰይጣን የሚችለው በሰው ልቡና የታሰበውን መገመት ብቻ ነው፡፡ በሰው ልቡና የተመላለሰውን ማወቅ ስለማይችል ሰዎች የልባቸውን ሁሉ እንዲናገሩ ይገፋፋቸዋል፡፡ ሔዋንን ስለ ዕጸ በለስ ያንን ሁሉ የጠየቃት ለማወቅ ወይንም ለመረዳት ፈልጎ ሳይሆን ሥላሴ በሔዋን ልቡና የጻፉትን ነገር ማወቅ ስላልቻለ ነው፡፡ ሔዋን ስትናገር ግን ሃሳቡን ዐወቀ፡፡ ዐውቆም ዝም አላለም ጠልፎ የሚጥልበትን ወጥመድ አዘጋጀ፡፡

Thursday, September 15, 2011

ገበያ ሲያመች

በድሮ ዘመን ነው አሉ፡፡ ልጂቱ ምጣድ ልትገዛ ገበያ ትወጣለች፡፡ ጥሩ ምጣድ መርጠው እንዲገዙላት እናቷን አስከትላለች፡፡ ገበያ ስትገባ እንዴው ሁሉም ነገር ቀልጧል፡፡ የማይሸጥ የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ «ምነው «ስትል ጦር ሊመጣ ነው ተብሎ ሁሉም ነገር ተወዷል» ይሏታል፡፡ «ምን ምን ይሸጣል ብላ ትጠይቃለች፡፡ «ምን የማይሸጥ ነገር አለ፡፡ ከብት ይሸጣል፣ ወርቅ ይሸጣል፣ እህል ይሸጣል፣ ልብስ ይሸጣል፣ ሰውም ይሸጣል» ይሏታል፡፡
«ደግሞ ሰው ለምን ይሸጣል ብላ ትጠይቃለች፡፡ «ባርያ መሸጥ መለወጥ ሊቀር ስለሆነ ሁሉም አሁን እየገዛ ነው» ትባላለች፡፡ እናቷን አንድ ጥላ ሥር አሳርፋ ሄዳ ስታይ እውነትም ልጅ ዐዋቂው፣ ባልቴት ሽማግሌው ሁሉ በባርያ ፈንጋይ እየተያዘ ይሸጣል፡፡ ስትሮጥ ሄደችና እናቷን ይዛ መጥታ በአራት ከብት ለወጠቻት፡፡ ነገሩን የሰማው የሀገሬ ሰው ጉድ ጉድ ብሎ ሲያበቃ «ገበያ ቢያመቻት እናቷን ሸጠቻት» የሚል ተረት አወጣላት፡፡

Tuesday, September 13, 2011

የዘመድ ቄስ ሀገራችን የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ ይባላል፡፡ ሰው ሲሞት ካህናት ይጠሩና ለሟቹ ጸሎት ያደርጋሉ፡፡ ይኼ ጸሎት «ፍትሐት» ይባላል፡፡ ለካህኑ ፍትሐት ማድረግ የክህነት ግዴታው ነው፡፡ ካህን ሆኖ የተሠማራበት፣ ምናልባትም እንጀራ የሚበላበት፣ ወይንም ደግሞ «ሥራው» ነው፡፡
ምንም ቢሆን ግን ሟች ዘመዱ ነውና ያለፈ ሕይወቱን፣ ውለታውን፣ አብረው ያሳለፉትን፣ መለየታቸውን እያሰበ ደግሞ ያለቅሳል፡፡ ዘመድ መሆኑ እንዳይፈታ፣ ካህን መሆኑም እንዳያለቅስ አያግደውም፡፡ ለዚህም ነው «እየፈታ ያለቅስ» የተባለው፡፡
ይህ አባባል ሁለት ነገሮችን አንድ አድርጎ የያዘ ነው፡፡ ኃላፊነትን ወይንም ሥራን እና ሰብአዊነትን፡፡ መፍታት ኃላፊነቱ ነው፡፡ የተሠማራበት ግዳጁ፡፡ ማልቀስ ሰብአዊነቱ ነው፡፡ ሰው መሆኑ፡፡ ሰው በማንኛውም ሥልጣን፣ በሞያ እና ክብር ላይ ሲቀመጥ በውስጡ ሰውነትን መርሳት የለበትም፡፡ ነገሮችን በሥልጣን መነጽር፣ በዕውቀት መስተዋት ወይንም በክብር መስኮት ብቻ ማየት የለበትም፡፡ በሰብአዊነትም ጭምር እንጂ፡፡ እርሱም ሰው ሆኖ የዚያኛውንም ወገን ሰውነት ሳይዘነጋ አንዳንዴም ራሱን በዚያኛው ጫማ ላይ አቁሞ ማየትም አለበት፡፡

Thursday, September 8, 2011

በምን እንግባባ?

 እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሁሉም የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የአስተሳሰብ እና የጎሳ ጎራዎች የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ሲያግባቧቸው የማያቸው ሦስት ነገሮች ነበሩ፡፡ ሰንደቅ ዓላማ፣ ሩጫ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፡፡ 

ሰንደቅ ዓላማ በብዙ ዘመናት ውስጥ የልዩነቶቻችንን ቋሚዎች አስደግፈን አንድ ጎጆ የሠራንበት ምሶሶ ነበር፡፡ በጎሳ፣ በእምነት እና በሥልጣን የተጣሉ መኳንንት እና መሳፍንት ለሰንደቅ ዓላማ ያላቸው ክብር፣ ፍቅር እና አመለካከት ተመሳሳይ ነበር፡፡ ከተለያዩ ወንዞች የተገኙ ወገኖች በማዕከላዊው መንግሥት አመራር እና አሠራር ባይረኩ፣ ባይስማሙ እና ባይደግፉ እንኳን ለሰንደቅ ዓላማ ያላቸው ክብር እና ፍቅር ግን አይለወጥም ነበር፡፡

Friday, September 2, 2011

የይቅርታ እና የምስጋና ሰሞን፡ ከጳጉሜ 1 እስከ 5
A Message to My Beloved Ethiopia and its people!


Dear brother  Daniel ,
Many thanks for the opportunity to say our "sorry s" and "thank you s".Just the title የይቅርታ እና የምስጋና ሰሞን itself was quite something to contemplate on.As I kept on thinking about the subject matter as a whole ,especially if there were any relevant "yeqrta's" I have to request and any earned " gratitude" I haven't so far thanked for.Many came to my mind from the spiritual realm to the material.My thoughts lead me to notice the hand prints of many in the life path I lead and the bridges built for me to walk on to the stages of life I walked to.In the coming days I will be calling few individuals to actually express my deepest gratitude  for their contribution in my life and being there  for me For some of them.I will never have enough life time to pay back their debt.