Monday, August 29, 2011

ነብር ያለ ጅራት


ሰውዬውን ይዘውት የመጡት የመንደሯ ታዋቂ ሰዎች ናቸው፡፡ በሌላኛው መንደር የሳለውን ሥዕል በማድነቅ ነው ያመጡት፡፡ በተለይም የዚችኛዋ መንደር ሰዎች አዳኞች በመሆናቸው የልዩ ልዩ እንስሳትን ሥዕል እንዲስልላቸው ይፈልጋሉ፡፡
ሰዓሊው ቀለሙን እና ሸራውን እስከገዙ ድረስ ማንኛውንም ሥዕል እግዜር እንደ ፈጠረው አድርጎ ሊስል እንደሚችል በኩራት ተናግሯል፡፡ መንደርተኞቹም ይህንኑ እስከሚያዩት ቸኩለዋል፡፡ አዳኞቹ ተሰብስበው መጀመርያ የየትኛው እንስሳ ሥዕል መሳል እንዳለበት ተከራከሩ፡፡ በመጨረሻም እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ነብርን እንዲስልላቸው ተስማሙ፡፡
 ሰዓሊው ሸራውን ወጠረ፡፡ ቀለሙን አዘጋጀ፡፡ ብሩሹንም ከነዳ፡፡ ሃሳቡነም ሰበሰበ፡፡ መሳልም ጀመረ፡፡ ማንኛውንም አስተያየት የሚቀበለው የመጀመርያውን ንድፍ ከጨረሰ በኋላ መሆኑን ገለጠ፡፡ እናም መንደርተኞቹ ምግብ እና መጠጡን አስቀምጠውለት ወደ የሥራቸው ሄዱ፡፡ ምን ዓይነት ነብር ሊሳል እንደሚችል የሚያስቡትን ሁሉ እያወጉ፡፡
ወደ ማታ ከሥራ መልስ ወደ ሰዓሊው አመሩ፡፡ እውነትም የነብሩ ንድፍ ወጥቷል፡፡ አንዳቸው ከግራ፣ ሌላቸውም ከቀኝ ቃኙት፡፡ ሌሎች ደግሞ ከፊት ለፊት ሆነው አፈጠጡ፡፡ መጀመርያ ያዩት አዳኞች የነብሩ ጅራት እጅግ መርዘሙን እና መቀነስ እንዳለበት ተስማሙ፡፡ ሰዓውም በትኅትና ሃሳባቸውን ተቀብሎ መቀነስ ጀመረ፡፡ ትንሽ ቆይተው ደግሞ ሌሎች አዳኞች መጡ፡፡ በነብሩ አሳሳል ቢደነቁም የነብሩ ጅራት መርዘም ግን አሁንም አልተዋጠላቸውም፡፡ መቀነስ አለበት ብለው ሰዓሊውን ሞገቱት፤ ሰዓሊውም እየተነጫነጨ ተቀበላቸው፡፡
ጅራቱን አስተካክሎ ሊጨርስ ሲል ደግሞ ሌሎች አዳኞች መጡ፡፡ እንዲህ ያለ ሥዕል ዓይተው እንደማያውቁ ካደነቁ በኋላ የነብሩ ጅራት መቀነስ አለበት ብለው ድርቅ አሉ፡፡ ሰዓው ፈጽሞ አይሞከርም አለ፡፡ እነርሱም እንግዲያማ የሠራህበትን አንከፍልህም ብለውት ሄዱ፡፡ ሰዓሊው ምንም ማድረግ ስላልቻለ እንደገና የነብሩን ጅራት ቀነሰው፡፡ ይህ ግን ሌሎች አዳኞች እስኪመጡ ብቻ ነው የሠራው፡፡
እንዴት ለአንድ ነብር ይኼ ሁሉ ጅራት ይሰጠዋል? ብለው ቡራ ከረዩ አሉ፡፡ ሰዓሊውም ከሦስት ጊዜ በላይ እንደቀነሰው በመግለጥ ያሁኑ ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ እንደማይችል ነገራቸው፡፡ አዳኞቹ ግን ጦራቸውን እያወዛወዙ ያሉትን ካልፈጸመ ወደ እሥር ቤት ሊወረውሩት እንደሚችሉ ዛቱ፡፡ ሰዓሊውም የነብሩን ጅራት አንድ ስንዝር አደረጋት፡፡
የመጨረሻዎቹ አዳኞች ሥዕሉ ላይ ቸግር አልነበረባቸውም፡፡ ምንም እንኳን ጦራቸውን ወጋ ነቀል እያደረጉ የሰጡት አስተያየት ከቁጣ የማይተናነስ ቢሆንም፡፡ ነገር ግን እነርሱም የነብሩ ጅራት አሁንም መቀነስ እንዳለበት ጦራቸውን ወደ ሰዓሊው ሸራ እየላኩ ተናገሩ፡፡ ሰዓሊው ሁሉንም ተቶ ቁጭ አለ፡፡ ቀጥሎም ቀለሙን መሰብሰብ፣ ሸራውንም ማጠፍ ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ አዳኞቹ «መንደራችን ድረስ መጥተህ፣ አንድ ነብር ሳትስል መውጣት እኛን መናቅ ነው፤ ተነሣና ሳል» አሉት፡፡ እምቢ አለ ሰዓሊው፡፡ «እምቢ ካልክ ለነብሩ የተዘጋጀው ጦር አንተ ላይ ይተከላል» አሉና ፍጻሜውን አመለከቱት፡፡ ሰዓሊው እንደ ሶስና በሁለት ነገር ተጨነቀ፡፡
«ቆይ እናንተ ሃሳባችሁ ነብሩን ያለ ጅራት ማስቀረት ነው እንዴ» አለ ሰዓሊው፡፡ አዳኞቹም ፈገግ ብለው «በአዳኝኛ እንደርሱ ማለት ነው ወንድም» አሉት፡፡
ለመሆኑ አዳኞቹ የነብሩን ጅራት ያልፈለጉት ለምንድን ነው? የነብር ጅራት ለነብር ህልውና ወሳኝ ነው፡፡ በሰዓት እስከ 65 ኪሎ ሜትር የሚፈተለከው ነብር እንዲያ ሲምዘገዘግ ሚዛኑን የሚጠብቀው በጅራቱ ነው፡፡ ጅራቱ ከሌለ ነብር እንደ ሚግ መተኮስ አይችልም፡፡ እተኮሳለሁ ካለም ሚዛኑን ስቶ ይወድቃል፡፡ በሀገራችን «የነብርን ጅራት አይዙም፣ ከያዙም አይለቁም» ይባላል፡፡ ነብር ጅራቱን ከያዙት የፈለገውን ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ነጭናጫ እና የሚያደርገውን የሚያሳጣው ፍጡር ይሆናል፡፡ ዒላማ አይኖረውም ቢኖረውም ይስተዋል፡፡ በመጨረሻም ይዳከምና ዝሎ ይወድቃል፡፡
ለነብር ጅራቱ ሚዛኑ ብቻ አይደለም፡፡ ቋንቋውም ጭምር ነው፡፡ አንዱ ነበር ከሌላው ነበር ጋር ከሚግባባበት መንገዶች አንዱ እና ዋነኛው የጅራቱ ንቅናቄ ነው፡፡ ችግር ሲገጥመው ግዳይ ሲጥል፣ አደን ሲቀናው ወዳጅ ዘመዶቹን ለርዳታም ሆነ ለድግስ የሚጠራቸው በጅራቱ ንቅናቄ ነው፡፡ ነብር ጅራቱ ከተያዘ አጋርም አያገኝ፣ ዘመድም አይረዳው፣ ሃሳቡንም አይገልጥ፣ እናም ለአዳኞቹ በሚገባ ይመቻቸዋል፡፡
ለዚህ ነው አዳኞቹ ነብሩን ያለ ጅራት ማስቀረት የፈለጉት፡፡
ለመሆኑ ሰው ማባበልን፣ ልመናን፣ ግፊትን፣ ምክርን፣ ማስጠንቀቂያን፣ ማስፈራርያን እና ጉርሻን እስከየት ድረስ ነው መቀበል ያለበት? ሰዓሊው «ዓላማችሁ ነብሩን ያለ ጅራት ማስቀረት ነወይ ያለውኮ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የአዳኞቹ ዓላማ ነብሩን ሚዛኑን በማሳት ለአደን ማመቻቸት ነውና፡፡
ኅሊና ሚዛን አለው፡፡ አባቶቻችን «መዳልወ ልቡና» ይሉታል፡፡ አንድን ነገር ለመቀበል ወይንም ላለመቀበል፣ ግፊትን ለመቋቋም ወይንም ለመቀበል፣ ሃሳብን እና እምነትን ይዞ በመከራ ውስጥ እንኳን ቢሆን ለመዝለቅ፡፡ በማባበልም ሆነ በጉርሻ አንድን ነገር ለመተው ወይንም ለመያዝ ይህ የኅሊና ሚዛን ወሳኝ ነው፡፡
የምንቀበለው ክብርም ሆነ ሀብት፣ ሥልጣንም ሆነ ሹመት እንደ ሰዓሊው ነብሩ ጅራት እንዳይኖረው የሚያደርግ ከሆነ ቢቀር ይመረጣል፡፡ ሰዓሊው መጀመርያ በማባበል፣ ቀጥሎ በገንዘብ በመግዛት፣ ከዚያም በእንጀራ ገመዱ ላይ በመምጣት፣ ከዚያም በማስፈራራት፣ አለፍ ሲልም በማሠር፣ በመጨረሻም በመግደል ነብሩን ያለ ጅራት ወደ ማስቀረት ደረሰ፡፡ ግን አንድ ሰው በጎም ይሁን ክፉ ተጽዕኖዎችን መቋቋም ያለበት እስከ የት ድረስ ነው? የሚል ጥያቄ ቢኖር «ነብሩ ጅራት እስካላጣለው ድረስ» መሆን አለበት መልሱ፡፡
የኅሊናውን የነብር ጅራት ለጥቅም፣ ለሥልጣን፣ ለጎሳ፣ ለሹመት፣ ለወንበር፣ እያለ ሲቀንሳት ሲቀንሳት ሲቀንሳት ስንቱ የተማረ የተመራመረ፣ ስንቱ ጨዋ እና ደኅና ሰው የሰዓውን ጥያቄ መጠየቅ አቅቶት ጅራት አልባ ነብር ሆኗል መሰላችሁ፡፡
 
ሰውኮ ሊሳሳት ይችላል፣ ሊታለል ይችላል፣ ግፊት ሊደረግበት ይችላል፣ መከራ ሊወርድበት ይችላል፣ የሚያጓጓው ነገር ሊቀርብለት ይችላል፣ በልጆቹ፣ በትዳር አጋሩ፣ በእንጀራው ሊመጣበት ይችላል፣ ሊታሠር እና ሊገደልም ይችላል ግን እስከየት ነው? የተባለውን ሁሉ ተቀብሎ ይዘልቀዋል፡፡ አንድ ቦታኮ «እናንተ ነብሩን ያለ ጅራት ልታስቀሩት ነው እንዴ ማለት ያስፈልጋልኮ፡፡
ለመሆኑ የሃሳብ ቀይ መሥመራችን የት ድረስ ነው? እንዴት ሙሉ ኅሊና ይሸጣል? ጥቂት ንጹሕ ኅሊና ለክፉ ቀን መትረፍ አለበትኮ፡፡ ጭፍን ደጋፊነትም ሆነ ጭፍን ተቃዋሚነት፣ አክራሪነትም ሆነ ጨለም ተኛነት፣ ሞኝነትም ሆነ ፍጹም ተጠራጣሪነት፣ ጅራት በሌለው የኅሊና ነብር ምክንያት የሚመጡ ናቸው፡፡ የምንማረው የሃይማኖት ትምህርትም ሆነ የምንከተለው የእምነት መሥመር ኅሊናችንን ጅራት አልባ ነብር አድርጎ ሚዛናችንን እስከሚያስተን መድረስ የለበትም፡፡
ጨፍኑ እና ተከተሉኝ፣ አትጠይቁ፣ አትመርምሩ፣ አታስቡ የሚለንን ሁሉ እስከየት ነው የምንከተለው? ነብሩን ያለ ጅራት እስከሚያስቀረው መመርያ መመርያ ነው፣ የበላይ ትእዛዝ ነው፣ የፓርቲ ሕግ ነው፣ የማኅበር ደንብ ነው፣ የሕዝብ ልማድ ነው፣ የሀገር ወግ ነው፣ የጎሳ ባህል ነው፣ የሚባሉትን ነገሮች እስከየት ድረስ ነው ኅሊናችንን እየቆረ ቆሩን ይሁኑ ብለን የምንቀበላቸው? ነብሩ ያለ ጅራት ቀርቶ ሚዛኑን እስከ ሚስትበት ነውን? ፈጽሞ፡፡
የኅሊና ሚዛን እና የተግባቦት ነጻነት የተያያዙ ናቸው፡፡ ሃሳብኮ በቃላት ብቻ አይገለጥም፡፡ በመሳቅ፣ በማልቀስ፣ በንግግር፣ በዝምታ፣ በገጽታ፣ በእጅ በእግር፣ በትካዜ፣ በቁዘማም ይገለጣል፡፡ ሰውኮ ከሰው ጋር ብቻ አይደለም ተግባቦት የሚፈልገው፡፡ ከራሱም ጋር፣ ከፈጣሪውም ጋር፣ ከሃሳቡም ጋር፣ ከልቡም ጋር፣ ከነፍሱም ጋር፣ ከሕይወቱም ጋር፣ ከሞቱም ጋር ተግባቦት ይፈልጋል፡፡
ሰው ይህንን ሲያጣ ኅሊና ሚዛኑን ይስታል፡፡ አሜሪካኖች መንግሥት የሃሳብ እና የፕሬስ ነጻነትን የሚገድብ ምንም ዓይነት ሕግ ማውጣት አይችልም ብለው የወሰኑት ወድደው አይደለም፡፡ ያለ ሃሳብ ነጻነት የኅሊና ነጻነት፣ ያለ ኅሊና ነጻነትም የኅሊና ሚዛን ስለማይኖር ነው፡፡
ነብሩ ጅራቱን ሲያጣ ሚዛኑንም ተግባቦቱንም አብሮ ነው የሚያጣው፡፡ ነጣጥሎ አይደለም፡፡ ማሰብ የማይችሉ ወይንም የማይፈቀድላቸው፣ ግን የሚታሰብላቸው፣ መግለጥ የማይችሉ ወይንም የማይፈቀድላቸው፣ ግን የሚገለጥላቸው፣ መሳቅ የማይፈቀድላቸው፣ ግን የሚሳቅላቸው፣ ማዘን የማይፈቀድላቸው፣ ግን የማይፈቀድላቸው፣ መደሰት የማይፈቀድላቸው ግን የሚደሰቱላቸው ሞልተዋል፡፡
በደርግ ጊዜ በቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር ዘመን አንድ ልጃቸው በነጭ ሽብር የሞተባቸው እናት እዬዬ ይላሉ፡፡ የልጁ አባት የገዝው ፓርቲ ሰው ነበር፡፡ ወዲያው በወቅቱ ገዥ የነበረው ፓርቲ ሰዎች ይመጡና «ማልቀስ አይፈቀድም፡፡ የተገደለውኮ ልጁ አይደለም ፓርቲው ነው፡፡ ሰዎቹ የርስዎ ጠላት አይደሉም የአብዮቱ ጠላቶች ናቸው፡፡ ማልቀስ ክልክል ነው፡፡ ለሁሉም በፓርቲው ስብሰባ የኅሊና ጸሎት ይደረግላቸዋል» ይሏቸዋል፡፡
እናትዬዋ በነገሩ ተበሳጭተው «እናንተም እንደ ፓርቲያችሁ አልቅሱ እኔም እንደ እናትነቴ አለቅሳለሁ» አሉ ይባላል፡፡ ነብሩን ያለ ጅራት ልታስቀሩት ነወይ? ነው የእናትዬዋ ጥያቄ፡፡
ሰው የኅሊና ሚዛኑን ሲስት ማንም በኅሊናው ላይ እንዲረማመድ፣ የቻለ ሁሉም የኅሊና ነጻነቱን እንዲደፈጥጠው፣ ብሶቱንም ለፈጣሪ እንኳን እንዳይናገር ያግተዋል፡፡ ሰው የኅሊና ሚዛኑን ሲስት መጀመርያ ኅሊና ይጨፈለቃል፣ ከዚያ ይታመማል፣ በመጨረሻም ኅሊና ይሞታል፡፡ የሞተ ኅሊና ደግሞ ጅራቱን እንዳጣ ነብር ወደወሰዱት ይሄዳል፣ የት? ለምን? እንዴት? መቼ? ማን? ብሎም አይጠይቅም፡፡ ሬሳ መች እንዲህ ጠይቆ ያውቅና፡፡ 
ዴልታ አውሮፕላን ላይ፣ ወደ አትላንታ ጉዞ

30 comments:

 1. Hey, dani that's is really an amazing article i really got a lesson.
  May GOD bless u& ur family keep it up ,,,,,,,,
  yoseph,
  Atl, GA

  ReplyDelete
 2. D/n Dani
  Thank you. I really like the message behind. We have to say "why" for unacceptable question and sayings. This will give us at least mind peace. There should be some limit to be pushed by others and it should be logical and convincing.

  ReplyDelete
 3. Dn. Daniel, Kale hiwot yasemalin Did you say on a Delta Airlines to Atlanta? does that mean we are going to hear you preach this Sunday? please...please...please stay until sunday service? Any way your writing is wonderful as usual. I always pray to GOD to give us religiuos fathers who don't shake up and sell their dignity when the devil tests them. Atlanta

  ReplyDelete
 4. selam dani betsam dese yemel eyeta newu
  Egezeabeher yabertah
  betekeristianen yale lejochuwa
  hageren yalewotsate
  lemasekeret jeratachenen lemekuretse
  letezegajut lebona yesetselen
  SOFONIYAS,A

  ReplyDelete
 5. Hello, Dn.Danial this is an amazing story! i learned a lot on this article thank you for sharing with us. Also it is an important and seasonal message keep it up. May God be with and and your Family.
  HG from GA.

  ReplyDelete
 6. Betam new yenkahegn dani problem is here God you keep. aklilu yibra h reyad

  ReplyDelete
 7. hi Dn. Daniel it is very interesting ur way of vision is amazing. betam new yemadenkh.
  may God bless you
  see u
  F.M
  A.A

  ReplyDelete
 8. Dani, This is A KEY QUESTION YOU RAISED. PLEASE EVERY BODY LET US ASK OUR SELVES BY SAYING:-''NEBRUN YALE JIRAT LINASKEREW NEW ENDE?''
  DANI EGZYABHER BE CHERNETU EMEBRHAN BAMALAJNETUA ATILEYIH!

  ReplyDelete
 9. it is really nice note..thank's dani for sharing your view...

  ReplyDelete
 10. Selam wedaje D Danieil that was a good article and deep message.God bless you more and more!!!

  DANY from marryland

  ReplyDelete
 11. ሃይ ዳኒ ሰላም ላንተ ይሁን።በጣም ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ፅሁፍ ነው።አግዚኣብሐር ይባርክህ።

  ReplyDelete
 12. Thanks Dani, it is an interesting view.

  It is nice specifying where you wrote your articles, it might be a good idea if you include the date you wrote the article (no posting as some articles may not be posted on the same day of the writing). Just little comment!.

  Berta Dani, I always love your articles.

  ReplyDelete
 13. Thanks Dani.Among the Ur best articles

  ReplyDelete
 14. I like it Dani, i got a good lesson. Thank you Dani.

  ReplyDelete
 15. wase from america gibi.
  Dani that was interesting story.i learn one thing from the story.that is each and every step of our journiy sheped by somebady when we lost our mind.FEAR YOUR DAETH SHADOW NOT SOME BADY WORDS.this my principle.GN.

  ReplyDelete
 16. This is the current issue in our country .there are so many "essawe" right now. We need to say that,this is the straw that breaks the camel`s back otherwise we became a cat even not a Tiger who lost the tail. Bravo Dani

  ReplyDelete
 17. ጭራ የሌለን ነብሮች እኛ ኢትዮያዊያን ነን!

  ReplyDelete
 18. በጣም ትምህርታዊ ዳንኤል ከሚያደንቁህ ኣንዱ ከኖርዌ

  ReplyDelete
 19. Dear Daniel,

  What a wonderful article is this. It is really gives insight. Enjoy your stay in Atlanta.

  ReplyDelete
 20. ኅሊናውን የነብር ጅራት ለጥቅም፣ ለሥልጣን፣ ለጎሳ፣ ለሹመት፣ ለወንበር፣ እያለ ሲቀንሳት ሲቀንሳት ሲቀንሳት ስንቱ የተማረ የተመራመረ፣ ስንቱ ጨዋ እና ደኅና ሰው የሰዓውን ጥያቄ መጠየቅ አቅቶት ጅራት አልባ ነብር ሆኗል መሰላችሁ፡፡ GIRUMM EYITA DADI, GOD BE WITH YOU FOREVER!

  ReplyDelete
 21. Tedeschebetaleh dani.egziabher chemro yigletleh.

  ReplyDelete
 22. ልጅ ዳንኤል እንዴት ድንቅና ጥሩ ነገር ብለሃል፡፡ሁላችንም ስጋ የለበስን ደካማ ፍጡሮች እንደሆንን ማማን አለብን፡፡የፈለገውን ያህል ጠንካራ ነን ብንል እንኳን የሆነ ቦታ ላይና የሆነ ሰዓት ላይ እንረታለን፡፡እንደዚሁም በተቃራኒው የፈለገውን ያህልም ደካማና የማንረባ ሰዎች ብንሆንም ደግሞ እንኳን በአርዓያ ስላሴ የተፈጠርን ክቡር ፍጥረቶች ስለሆንን ስለዚህ ትልቅ ቁምነገር ስንል በፈጣሪም እርዳታ ጭምር አንድ የተወሰነ መስመር ላይ አይሆንም ከእንግዲህስ በላይ የምንልበትና የሰውነት ሚዛናችንን የምንጠብቅበት ነጥብ አለ፡፡በቃ ሰው አንድ የሆነ የማንነቱ የመጨረሻ ሚዛን(Equilibrium) አለው፡፡ይህንን ሚዛን(Equilibrium) መጠበቅ ሳይችል ሲቀር ልክ ጭራ እንዳጣው እንደ ነብሩ ሰው የሚለው ስያሜ ይቀርና ሌላ ነገር ይሆናል፡፡በሀይማኖታችን አንድ ዘወትር የሚነገር ነገር አለ፡፡ይኸውም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ከፈጣሪው ድሮ ከተሰጠው ታላቅ ክብርና ሞገስ በእብሪቱ ስለወደቀ በተመሳሳይ መልኩ በቅናት መንፈስ መላው የአዳምን ዘርና የሰውን ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠንን ክብርና ሞገስ እንድናጣ ሊያስተን ዘወትር ያለመታከት ላይ ታች ይላል ይባላል፡፡እንደዚሁም የመጨረሻውን የህሊናቸውን እንጥፍጣፊ አለቅልቀው ለመድፋት ዳር ላይ የደረሱ እኩይና ራስ ወዳድ ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች መልካም ሰዎችን የራሳቸው ተመሳሳይ የጥፋት ጋሻ ጃግሬና ተከታይ ለማድረግ ሲሉ ሌሎች ሰዎችን እጅግ ክፉኛ በተለያየ መልክ በረቀቀ መልኩ ይፈታተናሉ፡፡እንደዚህ አይነት እኩይ ሰዎች በልቦናቸው ተፀፅተው በኛ ይብቃ ትውልድ ይዳን የሚለው አይነት እሳቤ ፈፅሞ የሌላቸውና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አህያ አይነት በእኩይ መንፈስ የሚመሩ ናቸው፡፡
  ልጅ ዳንኤል ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ሁላችንም እንጠንቀቅ፡፡ምናልባትም እንደ ነብሩ ጭራው በዋነኝነት ነብሩን ነብር የሚያስብለው እንደሆነ ሁሉ እኛም አስቀድመን በህገ ልቦና ጭምር የተገዛንበትና አስቀድመን ሰው ሆነን ስንፈጠር ጀምሮ ከፈጣሪ የተሰጠን ህሊናችንና ከዚህም ጋር ያለው መልካም ስነ-ምግባራችን ነው፡፡ይህንን ትልቅ መልካም ነገር ብኩርናውን በምስር ወጥ እንደለወጠው እንደ ኤሳው በብልጭና በጊዚያዊ ነገር ከለወጥነው ሰው ተብለን ከመጠራት ክብር ወርደን ወደ መካኒካል የሆነ ሮቦትነት ወይንም እንስሳነት ተቀየርን ማለት ነው፡፡ዘመኑ እጅግ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ሰይጣን ክርስቶስን በስተመጨረሻ የመጨረሻውን ካርድ መዞ የፈተነውና ሊያሰናክለው የፈለገው የዚህን አለም የመጨረሻውን ደረጃ ስልጣንና ጥቅም በምትሃት በማሳየት ነበር፡፡እግዚአብሄር ሁላችንንም በቸርነቱ ከዚህ ይጠብቀን፡፡

  ልጅ ዳንኤል እንዴት ድንቅና ጥሩ ነገር ብለሃል፡፡ሁላችንም ስጋ የለበስን ደካማ ፍጡሮች እንደሆንን ማማን አለብን፡፡የፈለገውን ያህል ጠንካራ ነን ብንል እንኳን የሆነ ቦታ ላይና የሆነ ሰዓት ላይ እንረታለን፡፡እንደዚሁም በተቃራኒው የፈለገውን ያህልም ደካማና የማንረባ ሰዎች ብንሆንም ደግሞ እንኳን በአርዓያ ስላሴ የተፈጠርን ክቡር ፍጥረቶች ስለሆንን ስለዚህ ትልቅ ቁምነገር ስንል በፈጣሪም እርዳታ ጭምር አንድ የተወሰነ መስመር ላይ አይሆንም ከእንግዲህስ በላይ የምንልበትና የሰውነት ሚዛናችንን የምንጠብቅበት ነጥብ አለ፡፡በቃ ሰው አንድ የሆነ የማንነቱ የመጨረሻ ሚዛን(Equilibrium) አለው፡፡ይህንን ሚዛን(Equilibrium) መጠበቅ ሳይችል ሲቀር ልክ ጭራ እንዳጣው እንደ ነብሩ ሰው የሚለው ስያሜ ይቀርና ሌላ ነገር ይሆናል፡፡በሀይማኖታችን አንድ ዘወትር የሚነገር ነገር አለ፡፡ይኸውም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ከፈጣሪው ድሮ ከተሰጠው ታላቅ ክብርና ሞገስ በእብሪቱ ስለወደቀ በተመሳሳይ መልኩ በቅናት መንፈስ መላው የአዳምን ዘርና የሰውን ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠንን ክብርና ሞገስ እንድናጣ ሊያስተን ዘወትር ያለመታከት ላይ ታች ይላል ይባላል፡፡እንደዚሁም የመጨረሻውን የህሊናቸውን እንጥፍጣፊ አለቅልቀው ለመድፋት ዳር ላይ የደረሱ እኩይና ራስ ወዳድ ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች መልካም ሰዎችን የራሳቸው ተመሳሳይ የጥፋት ጋሻ ጃግሬና ተከታይ ለማድረግ ሲሉ ሌሎች ሰዎችን እጅግ ክፉኛ በተለያየ መልክ በረቀቀ መልኩ ይፈታተናሉ፡፡እንደዚህ አይነት እኩይ ሰዎች በልቦናቸው ተፀፅተው በኛ ይብቃ ትውልድ ይዳን የሚለው አይነት እሳቤ ፈፅሞ የሌላቸውና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አህያ አይነት በእኩይ መንፈስ የሚመሩ ናቸው፡፡
  ልጅ ዳንኤል ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ሁላችንም እንጠንቀቅ፡፡ምናልባትም እንደ ነብሩ ጭራው በዋነኝነት ነብሩን ነብር የሚያስብለው እንደሆነ ሁሉ እኛም አስቀድመን በህገ ልቦና ጭምር የተገዛንበትና አስቀድመን ሰው ሆነን ስንፈጠር ጀምሮ ከፈጣሪ የተሰጠን ህሊናችንና ከዚህም ጋር ያለው መልካም ስነ-ምግባራችን ነው፡፡ይህንን ትልቅ መልካም ነገር ብኩርናውን በምስር ወጥ እንደለወጠው እንደ ኤሳው በብልጭና በጊዚያዊ ነገር ከለወጥነው ሰው ተብለን ከመጠራት ክብር ወርደን ወደ መካኒካል የሆነ ሮቦትነት ወይንም እንስሳነት ተቀየርን ማለት ነው፡፡ዘመኑ እጅግ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ሰይጣን ክርስቶስን በስተመጨረሻ የመጨረሻውን ካርድ መዞ የፈተነውና ሊያሰናክለው የፈለገው የዚህን አለም የመጨረሻውን ደረጃ ስልጣንና ጥቅም በምትሃት በማሳየት ነበር፡፡እግዚአብሄር ሁላችንንም በቸርነቱ ከዚህ ይጠብቀን፡፡

  ReplyDelete
 23. «እናንተም እንደ ፓርቲያችሁ አልቅሱ እኔም እንደ እናትነቴ አለቅሳለሁ» what an impressing message. Dani tebarek
  nurlen

  ReplyDelete
 24. Dani, this is z current Ethiopia. We must fight this syndrome aggressively. Thank u and may the almighity bless u.

  ReplyDelete
 25. Egziabher hulem tibeben na mastewalen ewketen yigletseleh.edmehen yarzemelen .manenetehen ayleweteben.amen

  ReplyDelete
 26. እግዚያብሔር ከአንተ ጋር ይሁን ተባረክ፡፡

  ReplyDelete
 27. "የኅሊናውን የነብር ጅራት ለጥቅም፣ ለሥልጣን፣ ለጎሳ፣ ለሹመት፣ ለወንበር፣ እያለ ሲቀንሳት ሲቀንሳት ሲቀንሳት ስንቱ የተማረ የተመራመረ፣ ስንቱ ጨዋ እና ደኅና ሰው የሰዓውን ጥያቄ መጠየቅ አቅቶት ጅራት አልባ ነብር ሆኗል መሰላችሁ"፡፡
  Dani its an interesting article

  ReplyDelete