Tuesday, August 16, 2011

የጠፋው ትምህርት ቤት


ዳዋ ውስጥ የሰማሁትን አንድ አስቂኝ ታሪክ ላውጋችሁማ፡፡ ነገሩ የተፈጸመው በአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ነው፡፡
ድርጅቱ አንድ የገጠር ትምህርት ቤት ለማሠራት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከውጭ ርዳታ ሰጭዎች ያገኛል፡፡ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ትምህርት ቤቱ ተሠርቶ፣ የተለያዩ ከፍተኛ አካላት ባሉበት ተመርቆ፣ የምረቃው ሥነ ሥርዓት ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ለለጋሾቹ ይላካሉ፡፡
በቪዲዮው ውስጥ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተወካዮች አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ሠሪዎቹን እና ለጋሾቹን ያመሰግናሉ፡፡ ወጣቶች የትምህርት ዕድሉ ወደ አካባቢያቸው በመምጣቱ የተሰማቸውን ደስታ ይገልጣሉ፡፡
ገንዘቡን የለገሱት ሰዎች አንድ ልማድ አላቸው አሉ፡፡ በዚያ ዓመት ገንዘብ ከሰጧቸው መካከል የተወሰኑትን መርጠው በአካል ይጎበኛሉ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖም በዚያ ዓመት የመጎብኘት ዕጣ ከወደቀባቸው አንዱ ይህ ትምህርት ቤት ይሆናል፡፡
«ልንመጣ ነውና ተዘጋጁ» ይላሉ ለጋሾቹ፡፡
«ምንም ችግር የለም ብቻ እናንተን ለመምጣት ያብቃችሁ» ብለው የበጎ አድራጎት ድርጀቱ ኃላፊዎች የሰጡትን አርኪ ምላሽ ይዘው ለጋሸቹ ከች ይላሉ፡፡ አቀባበል ይደረግላቸዋል፤ በግብዣ ይንበሸበሻሉ፡፡
በማግሥቱ ትምህርት ቤቱን ለማየት ወደ ቦታው መሄድ እንደሚፈልጉ ይገልጣሉ፡፡ የድርጅቱ ሰዎችም ቦታው እጅግ በጣም ሩቅ፣ ለመኪናም አስቸጋሪ መሆኑን፤ እዚሁ ቢሮ ውስጥ ያሉትን የአፈጻጸም እና የሂሳብ ሪፖርቶች ቢመለከቱ መልካም መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እነዚያኞቹ ግን በእግርም ቢሆን ለመጓዝ ፈቃደኞች መሆናቸውን ይገልጣሉ፡፡
መኪና ቀረበ፤ ሾፌር ተመደበ፤ ጉዞ ተጀመረ፡፡
ሲሄዱ፣ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ መንገዱ አለቀ፡፡ ሾፌሩም «ከዚህ በኋላ መኪና መሄድ አይችልም» ሲል ቁርጡን ተናገረ፡፡
«ታድያ ምን ይሻላል አሉ ለጋሾቹ
«እዚሁ ሆናችሁ በሩቁ ተመልከቱት» አለ ሾፌሩ፡፡
«የታለ ትምህርት ቤቱ»
« እዚያ ቆርቆሮው በፀሐይ ሲያብለጨልጭ የምታዩት ትምህርት ቤቱ ነው» አለ ሾፌሩ፡፡
«አይ ግድ የለም መኪናውን አቁመን በእግራችን እንሂድ» አሉ ለጋሾቹ
«መንገዱ አስቸጋሪ፣ ጸጥታው የማያስተማምን እና በተለይ ለፀጉረ ልውጥ አደገኛ ነው» አለ ሸፌሩ፡፡
«ምንም ችግር የለም የሆነውን እንሆናለን» ብለው ድርቅ አሉበት፡፡
ወዲህ ቢል ወዲያ ሊመለሱለት አልቻሉም፡፡ በመጨረሻ «ካላችሁማ እንሂድ» አለና ጉዞ በእግር ተጀመረ፡፡
እያለከለኩ በዚያ ፀሐይ ተጓዙ፡፡ እንደ ፓውላ ክሊፍ ጎንበስ ቀና እያሉ ሠገሩ፡፡ በመጨረሻም ደረሱ፡፡ ቆርቆሮው ከሩቅ ሲያንፀባርቅ ይታይ የነበረው ቤት የአንድ ገበሬ ቤት ሆኖ ተገኘ፡፡ ለጋሾቸ$ ግራ ገባቸውም፤ ተናደዱም፡፡
«የት አለ ትምህርት ቤቱ አፈጠጡ፡፡
ሾፌሩ በተረጋጋ ስሜት ሆኖ ፈገግ እያለ፣ በሁለት እጆቹም ከፊታቸው የተዘረጋውን ሜዳ እያሳየ «እዚህ ነበር የሠራነው» አላቸው፡፡
ደነገጡ፤ ግራም ተጋቡ፤ ጉንጫቸውም ተንቀጠቀጠ፡፡
«ታድያ የት አለ
«እኔ እንጃ ማን እንደወሰደው፤ እኛ ግን እዚህቺው ቦታ ነው የሠራነው»
«ትምህርት ቤት እኮ ነው ማን ይወስደዋል
«እኔ እንጃ፣ እዚህ ቦታ ላይ ሠርተን በሥነ ሥርዓት አስመርቀነው ነበር፤ ከፈለጋችሁ ቪዲዮውን ማየት ትችላላችሁ፤ የት እንደ ሄደ እንጃ» ይላል ሾፌሩ፡፡
«እንዴት ሊጠፋ ይችላል? ነቃቅለው ቢወስዱት እንኳን ፍርስራሹ ይኖር ነበር»
«የሚገርመው እርሱ ነው፡፡ እኛ ብዙ ጊዜ ይገጥመናል፤ ጤና ጣቢያ፣ ወፍጮ ቤት፣ የውኃ ጉድጓድ፣ ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ ሠርተን የጠፋብን ጊዜ አለ፤ የት እንደሄደ ግን ማወቅ አንችልም» እርሱ ይህንን ሲናገር ለጋሾቹ ድካማቸውን በንዴት ረስተው እንደ ፓውላ ጎንበስ ቀና ማለት ብቻ ሳይሆን ወደ መኪናቸው መሮጥም ጀምረው ነበር፡፡
ይህ ታሪክ «የጠፋው ትምህርት ቤት ታሪክ» እየተባለ ድሬ ዳዋ ውስጥ ይተረካል፡፡
ተሠርተዋል፤ ተመርቀዋል ሲባሉ የጠፉ ስንቶች አሉ፡፡ የሪፖርት ህያዋን፡፡
በመዋቅራቸው፣ በቢሮ መልካቸው፣ በቢል ቦርዳቸው፣ በሚያከብሯቸው በዓላት፣ በሚነገርላቸው ዝና፣ ያሉ የሚያስመስሏቸው ነገር ግን እቦታቸው ሄደው ሲያዩዋቸው ወይ ያልነበሩ፣ ያለበለዚያም የሌሉ ስንቶች ናቸው?
ስንት ተቋማት እየሠራን ነው፣ እየረዳን ነው፣ እየለወጥን ነው፣ ታሪክ እየሠራን ነው ሲሉን ፎቶ እና ቪዲዮ ሲያሳዩን፣ በኤግዚቢሽን እና በዐውደ ጥናት ሲያንበሸብሹን እውነታቸውን ነው እየሠሩ ነው ብለን አምነን ገንዘባችንንም ሕይወታችንንም ሰጥተናቸው ነበር፡፡ እስኪ የሠራችሁትን /ቤት እንየው ስንላቸው ግን «እዚህ ነበር ጠፋ» ይሉናል፡፡
ምን ምን የመሳሰለው ፓርቲ ፕሮግራሙን አሳትሞ፣ ምሥረታውን በቴሌቭዥን አስነግሮ፣ አባላቱን አስጨ ብጭቦ፣ ገንዘብ አዋጡልኝ ብሎ በቃ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲ በዴሞክራሲ ላደርጋት ነው፤ እያለ አጓጉቶ አጓጉቶ ከምርጫ ሰሞን በኋላ ድምፁ እልም ይላል፡፡ እኛም አንጀታችን አልችል ብሎ የት ሄደ እስኪ አሳዩን እንላለን፡፡
«አይ ፓርቲውኮ የለም» ይሉናል ሾፌሮቹ፡፡
«የት ሄደ» እንላለን ለጋሾቹ
«እዚህ ነበር አጣነው» ይሆናል መልሱ፡፡
እዚህ ሀገር፣ እዚህ መንደር ቤተ ክርስቲያን ልንተክል፣ ሰው ልናሳምን ነው እርዱን ባዩ ብዙ ነው፡፡ ፎቶ፣ ደብዳቤ፣ ቪዲዮ፣ ሪፖርት፣ ፕሮጀክት፣ ምናምን ያለያዘ የለም፡፡ እኛም አንጀታችን አሥረን ብር እናዋጣለን፤ ሪፖርት ይመጣል፤ በዓል ይዘጋጃል፤ ድግስ ይበላል፤ የምስጋና ደብዳቤ ይሰጣል፡፡
እንዴው ዕድል ገጥሞን ተሠራ የተባለውን ለማየት ብቅ ያልን ዕለት ከመፍረስ በላይ ወድቆ እናገኘዋለን፡፡ ከባሰም «ኧረ እንዲህ ያለ ወሬ አልሰማንም» ይሉናል የአካባቢው ሰዎች፡፡
እርር ድብን ብለን እኒያ ገንዘብ የሰጠናቸውን ሰዎች ፍለጋ ስንሄድ «ሠርተነው ነበር ጠፋ» ይሉንና ያርፋሉ፡፡
«የጠፋው ትምህርት ቤት» ስርቆት ከግለሰባዊ ጠባዩ ወደ ተቋማዊ ጠባይ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ስርቆት ገጠመኝ መሆኑ ቀርቶ የተጠና ፕሮጀክት መሆኑን ነው እያሳየን የመጣው፡፡ ድሮ በስርቆት ወሳጅ እንጂ ሰጭ አይረካም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ስርቆት ተሻሽሎ ሰጭውንም ወሳጁንም ማርካት ጀምሯል፡፡ ሰጭን በሪፖርት ወሳጅን በገንዘብ፡፡
አንድ ሌላ ቦታ ምን ሰማሁ መሰላችሁ፡፡ ሰውየው የአካባቢው ባለ ሥልጣን ናቸው፡፡ ለአንድ የሠፈር ጤና ጣቢያ የጥርስ ሕክምና መስጫ ዘመናዊ ማሽን ገባ ተብለው ሊመርቁ ይሄዳሉ፡፡ አመስግነው፣ ተደስተው ንግግር አድርገው ይመለሳሉ፡፡ በሳምንቱም ሌላው ጤና ጣቢያ ተመሳሳይ ዕቃ ማግኘቱን ይነገራቸውና ለማመስገን እና ለመመረቅ ይሄዳሉ፡፡ እንዲህ እያሉ አንድ አራት ጤና ጣቢያዎች ተመሳሳይ ዕቃ ለመመረቅ ይሄዳሉ፡፡
በኋላ እኒህ ባለ ሥልጣን መሣርያውን በደንብ እያዩት ይለምዱታል፡፡ በስድስተኛው ጤና ጣቢያ ሊመርቁ ተገኙና ጎንበስ ብለው መሣርያው ላይ ያለውን ትናንሽ $ጥር ሲያዩት ከዚህ በፊት የሚያውቁት ነው፡፡
ንግግር አድርጉ ተብለው ይወጣሉ፡፡ «ይህንን ማሽን ለስድስት ጊዜ ያህል እንደ ዓለም ዋንጫ እየተዘዋወረ ካየነው ይበቃል፤ በቀጣይ ደግሞ ሌላ ማሽን ለዝውውር እንዲበቃ ማደረግ ያስፈልጋል» ብለው ሰውን ሁሉ አሳቁት አሉ፡፡
ነገሮችን በልዩ ልዩ መንገድ ማቀናበር፣ ማሣመር እና እውነት እንዲመስሉ ማስቻል ቀላል በሆነበት በዚህ ዘመን ሪፖርቶች ብቻቸውን የእውነት ምስክሮች አይደሉም፡፡ ገባ ብሎ፣ ወረድ ብሎ፣ ገለጥ አድርጎ እውነታውንም ማየት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ፀጉራሙ ውሻ አለ ሲሉት ሞቶ እንዳይሆን፡፡
ሰው ዘመዱ ከሞተበት ቀን ይልቅ ዘመዱ መሞቱን በሰማበት ቀን ይበልጥ ይደነግጣል፡፡ ዘመዴ አለ ብሎ ያስብ ነበርና፡፡ ዘመዶቹም «አለ ደኅና ነው፣ ወጣ ብሎ ነው፣ ሥራ ላይ ነው፣ ትንሽ ነው አመም ያደረገው፣ ይሻለዋል» እያሉ እውነቱን ደብቀውት ይከርማሉ፡፡ ራቅ ያለ ሀገር ካለ ደግሞ ያማሩ ያማሩ ፎቶዎች እየላኩ ያጽናኑታል፡፡ ታድያ እንደ ድንገት መሞቱን የሰማ ዕለት፡
«ምነው ቀድሜ ዐውቄ ቢሆን፣ ይህን አደርግ ነበር፣ ያንን አደርግ ነበር» እያለ ያለቅሳል፡፡ አለ ብሎ የሚገምተውን ትምህርት ቤት ያጣውና እውነቱ ዱብ ዕዳ ይሆንበታል፡፡ ሟችም እርሱ ኗሪም እርሱ ይሆንና መከራውን ያያል፡፡
ዐፄ ምኒሊክ ዐርፈው ልጅ እያሱ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የምኒሊክ ሞት እንዳይነገር ተብሎ ነበር አሉ፡፡ ምኒሊክ ዐርፈው ሕዝቡ ግን በምኒሊክ አምላክ እያለ ይጣራ ነበር፡፡ ለምኒሊክ ቀረብ ያሉት መሞታቸውን ቀድመው አውቀው ማልቀስ ጀምረው ነበር፡፡ የግቢ ሰዎች ዝም አሰኟቸው፡፡ ትንሽ ራቅ ያሉት ደግሞ በጠና መታመማቸውን እንጂ መሞታቸውን አያውቁም ነበር፡፡ ከእነርሱ ራቅ ያሉትም አንዳች ነገር ከመጠርጠር ያለፈ መረጃው አልነበራቸውም፡፡ ሕዝቡ ግን ምኒሊክ አሉ ብሎ ያምን ነበር፡፡
በኋላ ግን ቆይቶ ሕዝቡ ውስጥ ለውስጥ መሞታቸው እየሰማ ማልቀሱን ቀጠለ፡፡ ወሬውም በአንድ ጊዜ ተዳረሰ፡፡ አንዳንዱም በይፋ ለምኒሊክ ፍትሐት ማስደረግ እና ልቅሶ መዋል ጀመረ፡፡ መጀመርያ ላይ በመቅጣት ለማስቆም ተሞከረ፤ ግን አልተቻለም፡፡ በኋላም ነገሩ ይበልጥ እየተሰማ ሲመጣ ልጅ እያሱ ዐዋጅ ማወጅ ግድ ሆነባቸው፡፡
«ያለንም እኛ የሞትንም እኛ ተረጋጋ» አሉ ልጅ እያሱ፡፡
ያለንም እኛ የሞትንም እኛ፡፡
አሌሳክንድርያ፤ ቨርጅንያ

35 comments:

 1. ያለንም እኛ የሞትንም እኛ፡፡

  ReplyDelete
 2. dani Egezeabehir yetsebekeh !!!
  alehu eyalu kememote yesewuren alen eyalu yemotutenem lebonachewun yemeleselen yalubeten endeyawuku Amelake yeredalen yeleluten wode menor yemeleselen!!!
  SOFONIYAS ,A

  ReplyDelete
 3. yalenem yemotenm! kale hiowat yasemalen dany.

  ReplyDelete
 4. impressive message dani! thanks.

  ReplyDelete
 5. "ነገሮችን በልዩ ልዩ መንገድ ማቀናበር፣ ማሣመር እና እውነት እንዲመስሉ ማስቻል ቀላል በሆነበት በዚህ ዘመን ሪፖርቶች ብቻቸውን የእውነት ምስክሮች አይደሉም፡፡ ገባ ብሎ፣ ወረድ ብሎ፣ ገለጥ አድርጎ እውነታውንም ማየት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ፀጉራሙ ውሻ አለ ሲሉት ሞቶ እንዳይሆን፡፡"

  Ejig betam grum new D/n Dani. Egziabiher Ejochihin yaberta. Tsegawunim yabizalih.

  ReplyDelete
 6. ደሳለኝ ወንድሙAugust 16, 2011 at 9:36 AM

  ሁሌም እንደዚህ ለእዉነት ለመቆም እንደምትሞክር እመቤታችን ከልጇ ጋር ትቁምልህ…ቀጥል እልሀለሁ፡፡ በያለንበት እንደዚህ ብንሆን ሁኔታዎችን መለወጥ እንችላለን…ምንጊዜም እዉነት ያሸንፋል፡፡

  ReplyDelete
 7. አይ ዳኒ “ያለንም እኛ የሞትንም እኛ ” አለክ? ምን እነሱ ይሞታሉ እኛን ገደሉን እንጅ፡፡ ጅቦች፡፡ የእናታቸውን ጓዳ በጭቃኔ ሚዘርፋ ጅቦች፡፡ በረሀብ እና ድንቁርና ጨለማ በሚማቅቅ ወገናቸው ስም ዳንኪራ የሚረግጡ የሰው ጅቦች፡፡ ኡኡኡኡኡ........ ግን ምን ይሻለናል?

  ReplyDelete
 8. ዳኒ በእውነት ትክክል ብለሃል፡፡ ምንም እንኳ ሙሉ መሙሉ ችግሩ አለ ባልልም በአሁኑ በአብዘሃኛው እውነተኛው ስራችን እና በአፋችን የምንናገረው የተመጣጠኑ አይደሉም፡፡ለምሳሌ፤-
  ከለጋሽ አካላት የተገኘን ገንዘብ በአካውንት እንዳስቀመጡ ለበርካታ ወራቶች እና ዓመታት ተቀምጠው የከረሙ የፕሮጀክት ኃላፊዎች እና ሰራተኞች ለጋሽ አካሉ ገንዘቡ ምን ደረጃ ላይ እንደዋለ በአይን በብረቱ ለማረጋገጥ ሲጠይቅ ሰው ሁሉ ምን እንደሚሰራ ለተመለከተ እጅጉንም በጣም የምንገረምባቸው ሁነቶች እንመለከታለን፡፡
  ለኢትዮጲያ መንግስት መስሪያ ቤቶች ሰኔ ወር እጂጉን የተለየች እንደሆነች ሁሉ በዶነር ድጋፍ ለሚሰሩ መያዶቻችን ደግሞ ልዩ ቀን የምትሆነው ለጋሾቹ በለገሱት ገንዘብ የተሰራውን ስራ ለመመልከት በጠየቁበት ቀን ነው፡፡ልዩነቱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቀን ሁል ጊዜ የታወቀች መሆኑ-ሰኔ ወር፤ የዶነሮች መምጫ እንደምጸዓት ቀን በእርግጠኝነት አትታወቅም ለማለት ቢከብድም እነርሱ በፈቀዱት ቀን፤ከፈለጉም ሌሎች ስራዎችን ጎን ለጎን ሰርተው ለመሄድ (ለምሳሌ ጉብኝት አድርገው) የሚያመቻቸውን ቀን መርጠው መምጣታቸው ነው፡፡
  ለጋሽ ድርጅቶቹን ለማስደሰት ተብሎ የሚሰሩ ስራችን ስንመለከታቸው ግርም ድንቅ ያስብለናል፡፡ የታሰረው ገንዘብ ከቋቱ ይለቀቃል፤ስልጠናው ይሟሟቃል፤ፎቶ እና ቪዲዮ ቀረጻው ይፋጠናል፤መረጃ ይጠናቀራል፤ለጋሾቹ ሲጠይቁ አቀላጥፈው መመለስ የሚችሉ "ተጠቃሚዎች" ይመለመላሉ፤ በሃላፊዎች መኪና ተረግጠው የማይታዎቁ ወረዳዎች፤ቀበሌዎች፤ጎጦች እና ሰፈሮች አንድ በአንድ ይዳረሳሉ፤ከሃላፊ እስከ ሴክሬታሪ ድረስ ሁሉም በየአቅጣጫው ዘመቻ ይዘምታል፡፡ነገሩ ዘመቻ ለእኛ ኢትዮጲያውያን አድስ ነገር አይደለም ምንም እንኳ ከጦርነት ዘመቻወቻችን ውጭ ሌሎቹ ውጤታማ ባይሆኑም፡፡
  እናም ስራዎቻችንን በእቅድ በመመራት ለእውነት ለመኖር በማሰብ ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛው ሰዓት ለሚመለከታቸው ማሳየት፤ማስረዳት ይጠበቃል ባይ ነኝ፡፡
  ውብሸት ዘተንታ

  ReplyDelete
 9. Hi Dani, there will be others cases and imagine how our statistic is working. You know, this school is considered for increasing education coverage in Dire as well as to the country.

  All Dire Dawa citizens, what is your reflection on this astonishing event?

  Thanks Dani,

  Temesgen, Dire Dawa

  ReplyDelete
 10. Truth is always a winner,, and the truth will come out soon,,wll Done dani..

  ReplyDelete
 11. ያለንም እኛ የሞትንም እኛ ክፉ ሆነ በጎ ሰሪወች ሁሉ እኛ....ሁሉ ነገር እኛ ያሳዝናል ያናድዳል ፡፡

  ReplyDelete
 12. Betam Yemigerm Tarik new breport bicha Yekeru bezu serawoch alu Berta .F.

  ReplyDelete
 13. tewoflos z debre bisratAugust 16, 2011 at 4:36 PM

  "...ስርቆት ከግለሰባዊ ጠባዩ ወደ ተቋማዊ ጠባይ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ስርቆት ገጠመኝ መሆኑ ቀርቶ የተጠና ፕሮጀክት መሆኑን ነው እያሳየን የመጣው፡፡ ድሮ በስርቆት ወሳጅ እንጂ ሰጭ አይረካም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ስርቆት ተሻሽሎ ሰጭውንም ወሳጁንም ማርካት ጀምሯል፡፡ ሰጭን በሪፖርት ወሳጅን በገንዘብ፡፡..."very impressive idea!!!first for those like me who don't have a chance of reading z magazine always it is nice to post it hear. such type of idea must run between man, believer and Christians. such የጠፋ ትምህርት ቤት is not only z product of huge NGO .u know some times I wonder to see even those employs who r working in these NGO's getting a salary in dollars but who r devil for there family not alone for such የጠፋው ትምህርት ቤት type of project in our country.we have so many other examples. I will post some when I got a chance. why r we or some of us become stone hurt human and christian?... thank you Dn. Daniel

  ReplyDelete
 14. wow it is interesting dani...thanks.

  ReplyDelete
 15. betam gerum eyeta new egzeabehere tsegawen abezeto abezeto yeseteh,enakeberehalen,enwedehalen. from,harar

  ReplyDelete
 16. Yigermal , thanks our brother

  ReplyDelete
 17. Betam arif new Dani berta. Benegerachin lay temesasayi neger Bahir Dar university Peda gibim tekestoal, andu Hintsa tefto Ye Federalu audit mesriya bet sifelig endeneber semtenal, yagignew weyim yitaw gin alsemanim, minalbat Abayi wesdot endehon enja.

  ReplyDelete
 18. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
  ሰላም ላንተ ይሁን መምህር ታሪኩ በጣም ይመስጣል አስቂኝ ታሪክ የሚለው አሳዛኝ በሚለው ይቀየርልን። ሌላው ደግሞ ምነው ጾም ነውና ይጠበቡ ይጨነቁ ብለህ ነው ወይ የዚህ ሰሞን ጽሁፎችህ ጸለምተኝነት በዛባቸው ለነገሩ ከየት ታመጣው ያለውን ነው የጻፍከው ቢሆንም ከየትም ከየትም ብለህ ለትንሳዔዋ የሚያጽናና ነገር ጻፍልን አይመስልህም ምክንያቱም አያሌ ጎደሏችንን አነሳህልን እስቲ ምን ቢከብድም ጭላንጭል መፍትሔዎችን እስኪ እንሞክር።
  ለዛሬ የተረክልንን ሰዎች የሚመስለ የቀድሞ አለቃየ አቃጥሎኝ የጻፍኳትን ግጥም እነሆ
  አንድ ተክል ሲሞት
  ልምላሜው ይደርቃል
  ቅጠሉ ይረግፋል
  ውበቱ ይከስማል
  የተጠለሉበት ያረፉበት ሁሉ
  ሌላ ጥግ ፍለጋ ጥለው ይነጉዳሉ
  ተቆርጦ ይጣላል
  ከሳት ይማገዳል
  ይነዳል ያነዳል
  አንድ ሰውም ሲሞት
  ትንፋሽ ይከዳዋል ልሳን ይርቀዋል
  ሙቀት ልምላሜው ፈጥኖ ይለየዋል
  የሚወዱት ሚወለዱት ሁሉ
  በመረረ ሃዘን ፍጹም ያነባሉ
  ስሙንም ቀይሮ በድን ሬሳ ተብሎ የወል ስሙን ለብሶ
  መኖር ይጀምራል አፈር ለብሶ ድንጋይ ተንተርሶ
  ሀገርም ስትሞት ሁነቱ እንዲሁ ነው
  መለያየት ነግሶ ይጠፋል ዉበቷ
  ያም ይህም ይቆርጣታል ካንገቷ ከባቷ
  እልፍ አእላፍ ልጆቿ ደም እንባ ያለቅሳሉ
  በርሃብ በችጋር በደዌ ያልቃሉ
  ጥቂቶች ቢተርፉም ጥለው ይሰደዳሉ
  ነዳ ታነዳለች እንደ በርሃ እሳት
  ኑሮዋም ይሆናል የመቃብር ሕይወት
  ከታችም ከላይም ዙሪያ ሚነግስባት
  ድንጋይ የማይገባው ጎርበጥባጣ ፍጥረት
  ይሆናል።

  ReplyDelete
 19. ጥሩ ቁም ነገር ነው፡፡ መቼም ሁሌም አስተውሎ ማድረግ በኋላ ከመጸጸት ያድናል፡፡ አንድ ነገር ግን አስረግጠህ መናገር ይኖርብሃል፡፡ ሳይሰሩ ሰራን እያሉ በሐሰት የሰውንንና የረጂዎችን ገንዘብ እንደሚሰበስቡ ሁሉ፡ ለዋሉለት ዓላማ ቃለቸውን አክበረው በመታመን እየሰሩ ያሉ ማኅበራትና ግለሰቦች አሉ፡፡ በዚህ ጹሁፍህ ላይ በግልጽ በመታመን እየሠሩ ያሉትን ቢያንስ አንተ የምውቃቸውንና ልትመሰክርላቸው የምትደፍረውን መግለጽ ይኖርብሃል፡፡ በተለይ በእምነት ተቋማት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱና በተጣናከረ ሁኔታ ገዳማትንና አስባራትን በመርዳት ያሉ ማኅበራት የሚያቀሩበት የምስልና የጹሁፍ የሥራ ሪፖርት ከበቂ በላይ ነው፡፡ ሁሉንም ከተጠራጠርን መቼውንም ሥራ አንሰራም፡፡ መፍትሄ መሆን ያለበትም እቦታው ድረስ እየሄዱ በማረጋገጥ ሳይሆን ( ተገባራዊ ለማድረግ ከባድ ነው) ታማኝ የሆኑትን ማኅበራት እና ግለሰቦች መለየትና እነርሱን በመደገፍ ነው፡፡ አሁን በመረጃ ዘመን እየኖርን እንደዚህ ማሰብ ያለብን አየመስለንም፡፡ ግን አንድን ነገር ጠቅለል ስታደርግ ( generalize ) ልዩ የሆኑትን (exceptional) ለይተህ ማውጣት ይኖርብሃል:: ቢያንስ አንተ የምታውቃችውንና የምታምንባቸውን ብትገልጽ የዳንኤል እይታዎች ያደርገዋል፡፡፡፡

  ReplyDelete
 20. ውድ ዲ.ን ዳኒኤል በትክክል ደርሰህበታል።ይህን የመሰሉ ብዙ አስገራሚ የሌብነቶች ድራማወች አሉ። በአንድ ወቅት በቅርብ የማውቀው አንድ የወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ «ለቤተ ክርስቲያን ችግኝ አስተክላለሁ» ብሎ በሽዎች የሚቆጠር ገንዘብ ከሀገረ ስብከቱ ያስፈቅድና ገንዘቡ ወጭ ተደርጎ ተሰጠው እና ይዞ ሄደ። ገንዘቡን ለማስፈቀድ ለተወሰኑ ሰወች ጉቦ መክፈሉን እሱ እራሱ ለሚቀርበው ጓደኛው ተናግሯል። ነገር ግን ይህን ደባ ሊቀ ጳጳሱ አያውቁም። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ይህ የወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ለሌላ የሥራ ጉዳይ ወደሀገረ ስብከቱ መ.ቤት መጣና ሊቀጳጳሱ በወሰደው ገንዘብ ምን ምን ሥራዎችን እንዳከናወነ ጠየቁት።እሱም በብዙ እሽወች የሚቆጠሩ የባህር ዛፍ ችግኞችን እንዳስተከለ ነገራቸው። እርሳቸውም እውነት መስሏቸው ደስ ኣላቸውና ችግኖቹን ሄደው ማየት እንደሚፈልጉ ይነግሩታል።እሱም«ብፁዕ አባታችን እርስዎ መጥተው ቢያዩልኝ ደስታውን አልችለውም» ይላቸውና በሐሳባአቸው መስማማቱን ገልጾ ተመልሶ ይሄዳል። በሌላ ቀን ሊቀ ጳጳሱ ችግኞቹን ለመጎብነት ቦታው ድረስ ይሄዳሉ።እሱም ቀደም ብሎ ተዘጋጅቶበት ጠብቃቸው።ጳጳሱ ቦታው ሲደርሱ ቀደም ብሎ ከጓደኞቹ ጋር ይመካከርና የቀበሌው ሕዝብ የተከለውን የባህር ዛፍ ችግን ለሊቀ ጳጳሱ ያስጎበናቸዋል። እሳቸውም እውነት መስሏቸው አመስግነውት ወደመንቨረ ጵጵስናቸው ተመለሱ የበተ ክርቲያኒቱም ገንዘብ በዚህ መንገድ ተዘረፈ። የህን ድራማ የነገረኝ ገንዘቡን አታሎ የወሰደው ሰው ጓደኛ ነው። እኔም ይህን የአንተን ጽሁፍ ሳነብ ያ የሰማሁት ድራማ ትዝ ስላለኝ እዚህ ላይ ጽፌዋእሁ፡፤

  ReplyDelete
 21. ሁል ጊዜ ለማን ልንገር የምለው ነገር ቢኖር ይሄ ነው እኛ ሀገር የትኛውም መስሪያቤት የሰራሄው ስራ ሳይሆን ዋሽተህ የጻፍከው ሪፖርት ተቀባይነት አለሁ ምንም ሳይሰራ ይህን ያህል ተሰራ ምንም ሳይገዛ ይሄ ይሄ ተገዝቶ በጀት አለቀ ብቻ ብዙ ብዙ አንድ ሰው በቀን 8 ሰዓት ሰርቶ ወደቤት ቢሄድ ይሻላል ወይስ ለሁለት ሰሃት ቢሮ ቆይቶ የወሸት ሪፖርት መጻፍ አለቆች ይህን መገንዘብ ተስንዋቸዋል እና ያስቡበት
  እንዳለ ዘ አጋሮ

  ReplyDelete
 22. Dear Dn. Daneal,
  Why don't post all the comments unless they are offincive. Why are you choosing only the comments that looks favor to you. I don't think you are in your mind. But the good things, you are reading it.
  You are totally wrong, There are a lot good assosation that are doing the job honestly. Your generalization is meaninggless unless you excluded the one doing the job honestly. In, the case of this associations, Vedio, Audio and written documnets are morethan sufficent.....
  I don't know what to say.....Please please, ... get time to see yourself..

  ReplyDelete
 23. wasihun,
  hi bro' that was so interesting and real in all over region.

  ReplyDelete
 24. ለ Anonymous,August 17, 2011 1:50 AM
  አስተያየትህ ጥቅም የሌለው ቢሆንም እንኳ ይኸው ፖስት ተደረገልህ አነበብነው ግን ምንም!!!! የሰለቸንን ውሸት ለማስነበብ ነው ይህ ሁሉ ወቀሳ? ለውሸት ለውሸትማ የሀገራችን ዋናው ዜና ማሰራጫ ኢቲቪ አለልን አይደል አንተን ምን አደከመህ፡፡ እኛ ስለማናውቃት ሌላ ኢትዮጵያ የሚያወራ እስኪመስል ድረስ ........ እና ባክህን የዳኒን ብሎግ ለቀቅ፣ ከነውሸትህ ኢቲሺ ዝለቅ ያስተናግዱሃል፡፡

  ReplyDelete
 25. I always appreciate how Brother Daniel express his ideas.He takes care his ideas to make all readers reach the same understanding.He doesn't side or incline.He is always in the Balance.I would like to be the same.

  ReplyDelete
 26. ዳኒ የምታቀርባቸው ፅኁፎች እጅግ በጣም ቁምነገር አዘል ናቸው፡፡
  ይህንን ስል ደግሞ ሁሉም ፍፁም ትክክል ናቸው ማለቴ ሳይሆን ለማለት የፈለግሁት የውስጥ ብሶታችንንና ስሜታችንንና አንገብጋቢ ሁኔታዎቻችንን ርእስ እድርጎ የሚያነሳና ብዙ ነገሮችን በጥልቀት እንድንጠይቅና እንደንመረምር የሚያደርግ ስለሆነ ማለት ነው፡፡
  “Success is sometimes the way you interpret and present it” የሚል አባባል አለ፡፡
  ከዚህ በመነጨም ዛሬ ዛሬ ሰዎች እንደ ትልቅ ስራ የሚያቀርቡት ነገር ሁሉ እጅግ ግራ የሚያጋባና የተሳሳተ እየሆነ እየመጣ ነው፡፡ችግሩ ደግሞ በዋነኝነት የሚመነጨው እንደ ህብረተሰብና እንደ ሀገር ከለንብት የንቃተ ህሊና ደረጃና ነገሮችንና ሁኔተዎችን የምንመዝንበት መመዘኛ መስፈርቶቻችን(Standards and Norms) ምን ደረጃ ላይ ከመሆናቸው ጋር የሚያያዝ ነው፡፡
  አንድ ሀገር ወይንም ህብረተሰብ ወይንም ህዝብ ወይንም ዜጋ እራሱን የሚያይበትና የሚመዝንበት የራሱ የሆነ System of Standards and Norms በሂደት ካልመሰረተ ወይንም ከሌሉት ኮምፓስ እንደሌለው አውሮፕላን ነው ማለት ነው፡፡ማለትም አንድን ነገር ትክክል ወይንም አግባብ እውነት ወይንም ሀሰት መሆኑንና አለመሆኑን የሚመዝነበትና ፍርድ የሚሰጥበት ነገር የለውም ማለት እኮ ነው፡፡ይህ ደግሞ ለአንድ ሀገር ወይንም ህብረተሰብ ወይንም ህዝብ ወይንም ዜጋ የመጨረሻው የውድቀትና የዝቅጠት ደረጃ ይመስለኛል፡፡እውነቴን ነው የምልህ አጠቃላይ የትውልድ ዝቅጠት (Generational Crisis) ውስጥ ያለን እንዳይሆን በጣሙን እፈራለሁኝ፡፡ምናልባት ይህንን ስል በዘመነ ግሎባላይዜሽን ብዙው የራሳችን ያልሆነን ነገር በተውሶ እንዲያው አግበስብሰን እንደሸቀጥ ስላስገባን ያን ያህል የሰለጠንና የተሻሻልን ወይንም ያደግን መስሎን ከሆነ በጣሙን እየተሳስንና እረሳችንንም እየዋሸነው እንዳይሆን እፈራለሁኝ፡፡እዚህ ላይ እያወራሁት ያለሁት ስለብዙሀኑ ነው፡፡I am not talking about a specific exceptionally good personalities or specific society. I am talking about the general populace.ይህ በፅሁፍህ ያቀርብከው ታሪክ እኮ በራሱ ያለንበትን አጠቃላይ ዘርፈ ብዙ ዝቅጠትና ውድቀት ጥልቀት ቁልኝ አድርጎ የሚያሳይ ነገር ነው፡፡ዛሬ እኮ ይህ አይነቱ አስነዋሪና አሳፋሪ ስራ እየተለመደ የመጣ የማንነታችን Standards and Norms እየሆነ መጥቷል፡፡በሀገራችን አባባል አፍ ሲያመልጥ ፀጉር ሲመለጥ አይታወቅም ይባላል፡፡እኛም እንደ ቀልድ እንደዋዛ ሳናውቀው እንደ አንድ ሀገር ወይንም ህብረተሰብ ወይንም ህዝብ ወይንም ዜጋ ምን ደረጃ ላይና ሁኔታ ውስጥ እንደደረስን ቆም ብለን በጥሞና ጠይቀንና መርምረን እናውቃለን?እኔ ይህንን የተወሰነ ክስተት አጠቃላይ የትውልድ ዝቅጠት መገለጫ ወይንም ምልክት (Index or Symptom)አድርጌ ነው የማየውና የምረዳው፡፡The very cause of the disease is very difficult to explain at this time or at this moment or it is some how not the right opportunity. However the very disease by itself is I call it “Generational Crisis”. The specific incident or phenomenon that is mentioned in your article is one of the symptoms of the very disease I called.

  ReplyDelete
 27. It is ME Part-2:

  ስለዚህም እንደዚህ አይነቶቹን ብዙ የበሽታ ምልክቶችን ማውራቱና መነጋገሩ በራሱ ጥሩ ነገር ቢሆንም ነገር ግን ከዚህ አይነት ሌሎችም የበሽታ ምልክቶች በስተጀርባ ወዳለ አንድ የተወሰነ ግንዛቤና ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መቻል ትልቁ ቁምነገርና አስተዋይነት ይመስለኛል፡፡ከእንደዚህ አይነት ብዙ ታሪኮችና እይታዎች በኋላ ዋነኛ የበሽታ(ዎች) መንስኤ(ዎች) ለመረዳት እስካልቻልን ድረስ ደግሞ ስለ ችግሮችና ስለበሽታዎች ብቻ እድሜ ልካችንን ብናወራ ያን ያህልም የምንፈይደው አንዳችም ትርጉም ያለው ጠቃሚ ነገር ለማግኘትና ወደ መፍትሄ ለመምጣት አንችልም፡፡አንድ ሀገር ወይንም ህብረተሰብ ወይንም ህዝብ ወይንም ዜጋ እንደዚህ አይነት አሳፋሪ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ ከገባና ከተዘፈቀ ትርጉም ባለው መንገድ ደረቱን ነፍቶና ቀና ብሎ እንዲህ ነኝ ወይንም አለሁ ብሎ ለማለት ድፍረት ሊኖረው አይገባው ወይንም አይችልም፡፡ይህ ክስተት እኮ አንደ ቀልድ የሚታይ ነገር አይደለም፡፡የ3 ሺህ ዘመን ታሪክና ሀይማኖት አለን እያልን ዘወትር ለውጪ ሀገራት ህዝቦች ለምናወራ ኢትዮጵያውያን ይህ እጅግ ትልቅ አሳፋሪና አሳዛኝ ውርደት ነው፡፡ታሪካችንና አሁን በተጨባጭ ያለው ስራችንና ምግባራችን ለየቅል እየሆነ ግራ የሚያጋባ ነገር እንዳይሆን በጣሙን እፈራለሁኝ፡፡እንደዚህ አይነቱንና ሌላም አይን ያወጣ አሳፋሪ ክስተት እኔ አላደረግሁትም ወይንም ሁሉ ሰው ይህንን አያደርግም እያለ አጉል ተልካሻ ምክንያት እየሰጠ ለመሸፋፈን ለማቃለልና ለመከላከል የሚያስብ ዜጋና ህበረተሰብ ወይንም መንግስት ካለ ሃላፊነት የሚሰማውና በቅጡ አርቆ የሚያስብና የሚያገናዝብ አስተዋይ አእምሮ ያለው ለመሆኑ በጣሙን እንድጠራጠረው ነው የሚያደረገኝ፡፡ኤች አይ ቪ ኤድስ እኮ እዚህ ሀገር መጀመሪያ ሲገባ የትና መቼ እንደሆነ በትክክል አልታወቀም ነበር፡፡ምክንያቱም የገባው በአንድ ወይንም በሁለት ወይንም በጣት በሚቆጠሩ ሰዎች አማካኝነት እንደ ቀልድ ስለሚሆን ማለት ነው፡፡ዛሬ ግን ምን ደረጃ ላይ ደረሰ?እኔ በበኩሌ ነገሮችን የማየው እንደዚያ ነው፡፡በእርግጥ ነገሮችን በሂደት እየተላመድናቸው ስለመጣን ምነም ላይምስለን ይችል ይሆናል፡፡ጤናማ ዜጋ ሀብረተሰብ ሀገርና መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ እንኳንስ እንደዚህ አይነት አይን ያወጣ ደፋርና አስነዋሪ የሆነ አሳዛኝ ስራ አይደለም አንድ ነብስ ያላወቀ ህፃን እንኳን በመንገድ ወይንም በትምህርት ቤት ወይንም በመዝናኛ ቦታ የሚያደርገው ከመስመር የወጣ ስነ-ምግባር የሌለው መጥፎ ስራ ልክ እንደ ትልቅ ነውርና አደጋ ተቆጥሮ አትኮሮት ተሰጥቶት በቤተሰብ ወይንም በሌላ የሚመለከተው አካል ሁሉ መነጋገሪያ ሆኖ በወቅቱ በእንጭጩ ትምህርት እርምትና ማስተካከያ ይደረግበታል፡፡ምክንያቱም እማዬ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ ኖሮ ያለው ልጅ አይነት ስለሆነ ማለት ነው፡፡ደግሞም ታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ “Injustice any where is injustice every where.” ነበር ያለው፡፡ማለትም በማንኛውም በአንድ የተወሰነ ጥቂት ቦታ ወይንም አካባቢ ላይ የተፈፀመ አንድ የተወሰነ ኢፍትሃዊነት ወይንም ጥፋት በሁሉም ቦታዎች ላይ እንደተፈፀመ ሆኖ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ዛሬ በሀገራችንም ሆነ በሌላው አለም ችግሮች በሂደት ቀስ በቀስ ተደማምረውና ተባብሰው ዛሬ ውስብስብና ልንቆጣጠረው ወደማንችለው ይህ አይነት ምስቅልቅልና ችግር ውስጥ የገባንበት አንዱ ምክንያት በዚህ አይነት ሁኔታ ነው፡፡
  ሀገራችንም በዚህ አይነት እጅግ አደገኛ ቫይረስ ዘርፈ-ብዙና ጥልቅ በሆነ መልኩ ስለተመረዘች መፍትሄውም እንደዚሁ እጅግ በጣም ውስብስብ እልህ አስጨራሽና አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
  ነገር ግን ቢያንስ ነገሮችንና ችግሮችን ለጊዜውም ቢሆን በዚህ አይነት መልኩ መነጋገሩና መወያየቱ እጅግ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ስለሆነ ዳኒ ይህንን አካሄድህንና እይታህን አጠናክረህ ቀጥልበት፡፡

  አድናቂህ ነኝ

  ReplyDelete
 28. To Anonymous,August 17, 2011 1:50 AM (if you read it): I think you are living in another Ethiopia (may be you created it at your own home), but this story is true, ofcorse there are honest organizations too. These situations are also known by the government, the govt. also created a law which can abide them (for example they have to be audited by the govt., they have to work on areas that need to support the community...). Sometimes we go blindly (መንግስትን የደገፍንና ታማኝ ለመምሰል ስንጥር ግን መንግስት ራሱ ስራዪ ብሎ የሚሰራቸውን ስራዎች እንነቅፋለን:: ኢሃዲግን እያበላሹ ያሉት ደሞ ዕንዲህ አይነት የደንቆሮ ደጋፊዎች ናቸው:: አልነቃ አለ እንጅ ቢነቃ ጥሩ ነበር::)Another thing, if you are watching Gemena in ETV, the same concept is being discussed (and that is also the reality). መደገፍ ብቻ ከሆነ አላማህ ዝምምም ብለህ ደግፍ:: ስህተት ሲኖር ግን የሚናገሩ ማስተካከያ አቅጣጫ የሚጠቁሙ እንፈልጋለን:: ቅቢ አንጉዋች አትሁን ወንድም:: እውነታውን አትሽሽ::

  ReplyDelete
 29. ይ ቅ ር ታ !

  የኔታ ወንበር ዘርግተው ንባብ ከትርጓሜ እያስተማሩ ሳለ አንዲት እናት በጉባኤ መሃል መቀነቷን ፈትታ ለተማሪዎች የሳንቲም ድቃቂ ታድላለች፡፡ በአድራጎትዋ የተበሳጩ ተመልካቾች ምስኪኗን እናት ጉባኤ ስለማቋረጧ ይከሷት እና ይወቅሷት ጀመር፡፡ የኔታ ግን እንዲህ አሉ ‹‹ ይህችን እናት ተዉአት፡፡ እኛ ሁላችን ንባቡን ስናሄድ እርስዋ በትርጓሜ ቀድማናለች!››

  ዳኒ ሁለት ጊዜ አሸነፍከን፡፡ አንዴ በዝግ ጉባኤ፣ ሁለተኛም በአደባባይ ይቅርታ ጠይቀህ፡፡ ንባቡን ብዙዎቻችን አሂደነው ነበር፡፡ በትርጓሜው ቀደምከን እንጂ፡፡ የመምህር ተግባር ይኽም አይደል??? በክስተቱ ውስጥ ያለፍን በሙሉ የየድርሻችንን እናነሳለን፡፡ እኛም ከልብ ይቅርታ እንጠይቅሃለን፡፡ ሃሳብህ ምንም ይሁን ምን እኛም ልናደምጥህ ይገባን ነበር፡፡ ይ ቅ ር ታ !

  ReplyDelete
 30. በዚህ አይነት ተግባራቸው እውነተኛውን ደሃ ሰው እንዳይረዳ እና አገር እንዳትለማ የሚያደርጉ ብዙ ናቸው:: አንተ ደግሞ አገላለጽህ ልዩ ነው እውነትን በትክክል አስቀምጠሃል:: እግዚአብሔር ይርዳህ

  ReplyDelete
 31. ይ ቅ ር ታ !

  የኔታ ወንበር ዘርግተው ንባብ ከትርጓሜ እያስተማሩ ሳለ አንዲት እናት በጉባኤ መሃል መቀነቷን ፈትታ ለተማሪዎች የሳንቲም ድቃቂ ታድላለች፡፡ በአድራጎትዋ የተበሳጩ ተመልካቾች ምስኪኗን እናት ጉባኤ ስለማቋረጧ ይከሷት እና ይወቅሷት ጀመር፡፡ የኔታ ግን እንዲህ አሉ ‹‹ ይህችን እናት ተዉአት፡፡ እኛ ሁላችን ንባቡን ስናሄድ እርስዋ በትርጓሜ ቀድማናለች!››

  ዳኒ ሁለት ጊዜ አሸነፍከን፡፡ አንዴ በዝግ ጉባኤ፣ ሁለተኛም በአደባባይ ይቅርታ ጠይቀህ፡፡ ንባቡን ብዙዎቻችን አሂደነው ነበር፡፡ በትርጓሜው ቀደምከን እንጂ፡፡ የመምህር ተግባር ይኽም አይደል??? በክስተቱ ውስጥ ያለፍን በሙሉ የየድርሻችንን እናነሳለን፡፡ እኛም ከልብ ይቅርታ እንጠይቅሃለን፡፡ ሃሳብህ ምንም ይሁን ምን እኛም ልናደምጥህ ይገባን ነበር፡፡ ይ ቅ ር ታ !

  Dani...Amaharic Metsafe Selemalechle Hasaben Mulu Lemulu yemigeletse Selagegnhu Copy Aderekut.

  ReplyDelete
 32. Yaleshi mesloshal
  Tebeltesh Alkeshal

  ReplyDelete
 33. "yemotnm egna yalenm egna" tiru meleikt new Dani enamesegnalen berta.

  ReplyDelete
 34. I hope our thanks giving day is going to be celebrated with the coming 13th month,so what if u remind the fans when the time arrives

  ReplyDelete