ብጹእ አቡነ ዘካርያስ በማኅበረ በዓለ ወልድ ሰባተኛ ዓመታዊ ጉባኤ ቺካጎ ላይ ተገኝተው እንዲህ አሉ፡፡
ወደ መዓርገ ጵጵስና ከመምጣቴ በፊት የሐዲሳት ትርጓሜ አስተምር ነበር፡፡ አንድ ቀን የዮሐንስ ራእይን ምእራፍ 19 ሳስተምር «በጉ እና የበጉ ሚስት» የሚለው ላይ ደረስን፡፡ የበጉ ሚስት ያልነው «መርዓተ በግዑ» የሚለውን ነው፡፡ ይህንን ለተማሪዎቹ አስተምሬያቸው ሊቀጽሉ ወደ ጫካ ገቡ፡፡ በጫካው አጠገብ መንገድ አለ፡፡ በመንገዱ አንድ ገበሬ ከሚስቱ ጋር ይሄዳሉ፡፡ የገበሬው ሚስት ቀደም ብላ ባሏም ተከትሏል፡፡
የሚቀጽሉት ተማሪዎች «በጉ እና የበጉ ሚስት» ሲሉ ሴትዮዋ ሰማችና ወደ ተማሪዎቹ ተጠጋች፡፡ «እናንተ ማንን ነው የበጉ ሚስት የምትሉት? እኔ ነኝ የበጉ ሚስት» ብላ ትውረገረጋለች፡፡ ይሄኔ ባልዋ ይደርሳል፡፡ «ምንድን ነው?» ብሎ ሲጠይቃት «የበጉ ሚስት እያሉ ይስቁብኛል» ትለዋለች፡፡ እርሱም ይባስ ብሎ «እናንተ ማንን ነው በግ የምትሉት» አለና በያዘው ሽመል ያንቆራጠጣቸው ጀመር፡፡
ልጆቹ ዱላው ሲብስባቸው «መምህራችን አስተምረውን ነው» ይሉታል፡፡ እንደ ተናደደ ሽመሉን ይዞ «እኔን በግ እያሉ የሚያስተምሯችሁ የትኛው መምህር ናቸው» እያለ መጣ፡፡ እኔም ሌላ ነገር ሳይከተል ብዬ ሸሸሁ፡፡ በኋላ የአካባቢው ሽማግሌዎች መጥተው ገላገሉን፡፡ መጽሐፍ ስመለከት ከዚህ ላይ ከደርስኩ አስታውሰዋለሁ፡፡
ችካጎ