ታች ክፍል እያለሁ የተማርኩት ትምህርት ሰሞኑን ትዝ አለኝ፡፡ ስለ ቁስ አካል ሳይንስ ያስተማረን ትምህርት፡፡ ቁስ ማለት ክብደት ያለው እና ቦታ የሚይዝ ነገር ነው የሚለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍ ካልኩ በኋላ የተማርኩትን ሌላ ነገር አብሮ አስታውሶኛል፡፡ «መንፈስ»፡፡ «መንፈስ የማይጨበጥ እና የማይዳሰስ፣ ክብደት የሌለው እና ቦታ የማይዝ ህልው ነው» የሚለው፡፡
አሁን እኛ ቁስ ነን ወይስ መንፈስ? እዚህች እንወዳታለን በምንላት ሀገር፣ ስሟ ሲጠራ ደማችን በሚሞቅላት፣ ነፍሳችን በምትግልላት ሀገር እኛ ቦታችን የት ነው? ልክ ነው እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሀገሬም ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያም የኔ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጭ የምለው፣ የምተኛው፣ የምኖረው፣ የማርፈው፣ የት ላይ ነው? ወይስ ቦታ አልባ መንፈስ ነኝ? አሁን አሁንኮ ሁለት ዓይነት ኢትዮጵያውያን እየታዩ ነው፡፡ መናፍስት ኢትዮጵያውያን እና ቁስ ኢትዮጵያውያን፡፡