Saturday, May 14, 2011

ቫቱ ይነሣልን ወይ ይቀነስልን

ወደ ግብጽ እየተጓዝኩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፡፡ አውሮፕላኑ ውስጥ መጨረሻ የደረስኩት እኔ ነኝ፡፡ ትኬቱን ከአየር መንገድ የትኬት ቢሮ ስወስድ ያልነገሩኝ ነገር በኋላ ተከሰተ፡፡ የቢጫ ወባ የክትባት ካርድ መያዝ ነበረባችሁ ተባልን፡፡ ምናለ ይህንን መረጃ ትኬት ስንወስድ ቢነግሩን ኖሮ፡፡
እኔ እድሜ ለባለቤቴ በአርባ አምስት ደቂቃ ከቤት አመጣችልኝ፡፡ ዘማሪ ዲያቆን እንግዳ ወርቅ ቀረ፡፡ ብጹዕ አቡነ ያሬድ ግን ከባድ ጥያቄ ጠየቁ፡፡ «ለመሆኑ ዓባይ ከኢትዮጵያ ወደ ግብጽ የሚሄደው በየትኛው የክትባት ካርዱ ነው
እየተጣደፍኩ በአየር መንገዱ ሠራተኞች ርዳታ አውሮፕላኑ ደረስኩ፡፡ የመጨረሻው ተሳፋሪ እኔ ነበርኩ፡፡

ቦታዬን ስይዝ ሁለት ወጣቶች ከአንድ ከቆመ ሌላ ወጣት ጋር ያወሩ ነበር፡፡ የበረራ አስተናጋጇ መናገር ስትጀምር የቆመው ልጅ ወደ ወንበሩ ተመለሰ፡፡ ያን ጊዜ ሁለቱ ተቀማጮች ማውራት ጀመሩ፡፡
«ይገርማል እኔኮ ይሄ ልጅ እንደዚህ መሆኑን አላውቅም ነበር» አለው አንዱ፡፡
«እንዴት ሌላኛው መለሰ፡፡
«እሳት የላሰ አይደል እንዴ»
«አመንከው»
«ምን ብዬ እጠራጠረዋለሁ»
«አታውቀውም ማለት ነው»
«እንዴት ችግር አለ»
«በጣም እንጂ»
«ሊዋሽ ይችላል»
«እርሱን ስትሰማኮ ቫቱን እየቀነስክ ካልሆነ ችግር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ቫቱ ከአሥራ አምስት ፐርሰንት ሊበልጥ ይችላል» ያኛው ሳቀ፤ እኔም እንዳይታወቅብኝ አድርጌ ሳቅኩ፡፡ ከዚያም የቱ የቱ ውሸት መሆኑን ይተነትንለት ገባ፡፡
ይኼ የቫት ነገርኮ ልጁ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ አንዳንድ ሰውም አንዳንድ መሥሪያ ቤትም ጋ፣ አንዳንድ ባለሥልጣንም ጋ፣ አንዳንድ ሚዲያም ይገኛል፡፡
አንዳንድ ሰው ስለ ራሱም ሆነ ስለ ሌላው የሚያወራውን ነገር ለማመን ከፍተኛው ችግርኮ ቫቱን ከዋናው ክፍያ መለየቱ ነው፡፡ አንዳንዱ ዋጋውን አሥር ብር አድጎ ቫቱን ሃምሳ ፐርሰንት ሊያደርገው ይችላል፡፡ ለምሳሌ የራሱን መልአክነት ሲነግራችሁ እናንተ ክንፉን፣ የብርሃን ክበቡን፣ ቅድስናውን፣ ሰማያዊነቱን፣ ሰይፉን፣ አውጥታችሁ ማየት መቻል አለባችሁ፡፡ እነዚህ ሁሉ የተጨመሩ ቫቶች ናቸው፡፡
የሰውን ጭራቅነት የሚያወራውንም ቢሆን የረዘመ ጥፍሩን፣ የገጠጠ ጥርሱን፣ የተዘረጋ ምላሱን፣ የተቀረደደ አፉን፣ የጎደጎደ ዓይኑን፣ የጨለመ ገጹን እያወጣችሁ የተነገራችሁን ሰው ማሰብ ካልቻላችሁ በቀር ቫቱን መክፈል ከባድ ይሆንባችኋል፡፡
አንዳንዱ ስለሚስቱ ወይንም አንዳንዷ ስለ ባልዋ የሚያወሩትን ስንሰማ አፍ ያስከፍታሉኮ፡፡ በዓለም ላይ የማይገኝ፣ በዕውቅ የተሠራ፣ ከመልአክ ዝቅ ከሰው ከፍ ያለ፣ ከአፉ ደግ እንጂ ክፉ የማይወጣ፣ ቢለጉሙት ፈረስ ቢጭኑት አህያ፣ ዓይኑ ፍቅር፣ አንደበቱ ትኅትና፣ እጁ ደግነት፣ እግሩ ችሮታ፣ ትከሻው ጋሻ፣ ጆሮው ምሕረት፣ ሆዱ ትዕግሥት የሆነ አንድ ባል እዚያ ቤት እንዳለ ወይንም የሆነች አንዲት ሚስት እዚያ ቤት እንዳለች የሚነገረን ግን እውነት ይሆን? እኔ የምፈራው ለኛ ቫት ተጨምሮ እየተሸጠልን እንዳይሆን ነው፡፡
በአደባባይ አብዝተው ስለ ትዳር አጋሮቻቸው የሚያወሩ ተጋሪዎች ግን ለብቻቸውም ለሚስቶቻቸው ወይንም ለባሎቻቸው እንዲያ ይሏቸዋል፡፡ ወይስ የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ የሚባለው ዓይነት ነው፡፡
እኔ ከባለ ትዳሮች በላይ መከራ እያሳየን ያለው የሀገራችን ማስታወቂያ ይመስለኛል፡፡ ቫቱ በዛብንኮ፡፡ ሳሙናው ገና ከሱቅ ሲመጣ ነው ቆሻሻው ቤቱን ጥሎ የሚጠፋው፡፡ ኦሞው ስሙ እንደ ድግምት ሲጠራበት የልብሱ ቆሻሻ እንደ ሰይጣን ለቀቅኩ ይላል፡፡ ዱቄቱ ከቫይታሚን እስከ ዜድ ማኅበር መሥርተው ተቀምጠውበታል፡፡ ፊልሙ የግራሚ አዋርድ ያመለጠው በስሕተት ዘግይቶ ስለተመዘገበ ነው፡፡ ሕንፃው በውስጡ መንግሥተ ሰማያት እና ገነት አሉ፡፡ ጫማው እንደ ታክሲ ቀጣና ሳይጠብቅ የፈለጉበት ቦታ ይዞ የሚሄድ ነው፡፡
ማበጠርያው እንኳን ፀጉር ያላቸው የሌላቸውም ቢያበጥሩበት ያሳምራቸዋል፡፡ ቅባቱ አንድ ጊዜ ከተቀቡት ከሞቱ በኋላ እንኳን አይለቅም፡፡ ለጋ ቅቤው የቅበላ ዕለት ቢበሉት ጾሙን አሳልፎ ከፋሲካ ያደርሳል፡፡ ቆርቆሮው ፀሐይ እና ዝናብ ሲወርድ የመልስ ምት ሰጥቶ ወደ ነበሩበት ይመልሳቸዋል፡፡ ኮሌጁ ገና ወንበሩ ላይ ሲቀመጡ ለሊቅነት አምስት ደቂቃ ይቀራችኋል፡፡ የምግብ ማሠልጠኛው እዚያ ሲገቡ እንኳን በእጅዎ በእግርዎ የሠሩት ምግብ እጅ ያስቆረጥምልዎታል፡፡ ጥርስ ቤቱ ሌላ ጥርስ የሚተክልላችሁ ከነ ፈገግታው ነው፣ እንዴት ነው ግን ሻቱ አልበዛም? የማስታወቂያ ድርጅቶች ለመንግሥት የሚከፍሉትን ቫት መልሰው ማስታወቂያው ላይ ይጨምሩታል እንዴ? ቸገረንኮ፡፡
ሚዲያውስ በዚያም በዚህም በኩል ሆኖኮ አንዱ የኩሸት ሌላው የጥላሸት ቫት እየጨመረ ማመን እንዳንችል አደረገንኮ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያ አድጋለች፣ ተመንድጋለች፣ ሄዳለች፣ በርራለች፣ ችግር ደኅና ሰንብት ብላለች፣ ይሄንንም እገሌ እና እገሌ የተባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መስክረውላታል ይለናል፡፡ በዕድገቱ ዋጋ ላይ የኩሸት ቫት ይጨምራል፡፡ አንዳንዴም ቫቱ ከዋጋው ሊበልጥ ይችላል፡፡
ሌላው ደግሞ ይነሣና ኢትዮጵያ ሞታለች፤ ወደ ኋላ በመንቀራፈፍ ላይ ናት፣ ከዓለም መጨረሻ ሆናለች፤ ረሃብተኛው በዝቷል፣ ሕዝቡ ኑሮ ሰልችቶታል፣ ዴሞክራሲ በቢሮክራሲ ተተክቷል፤ ይህንንም እገሌ እና እገሌ የተባሉ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች መስክረዋል እያለ የጥላሸት ቫት ጨምሮበት ያቀርብልናል፡፡ ቸገረንኮ፡፡ አንዳንዴ ቫቱ ከዋጋው ይበልጥና መለየት ተሣነን፡፡ ኧረ እባካችሁ ቫቱን አንሡልን ካልሆነም ቀንሱልን፡፡
አንዳንዱ ባለ ሥልጣን በአንድ የሕዝቡ ችግር ጉዳይ ተጠይቆ ሚዲያ ላይ ሲቀርብ ችግር የሚባል እንደሌለ፤ ከሕዝቡ የግንዛቤ ችግር ብቻ የመጣ እንደሆነ፤ መሥሪያ ቤቱ ራሱን በአዲስ የአሠራር ለውጥ እየመራ መሆኑን፤ አሁን ነገሮች ሁሉ በደቂቃ እንደሚ ያልቁ፤ ደንበኞችን ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው እንደሚቀበሉ መግለጫ ይሰጣል፡፡ እውነት ነው ብለን ስንሄድ ግን መግለጫው ቫት የተጨመረበት መሆኑን እናያለን፡፡ ምናለ ግን ሲሆን ዋጋው ብቻ ቢቀርብ፣ እርሱም ካልተቻለ እንደ ሆቴል ዋጋው እና ቫቱ ተለይቶ ቢነገረን፡፡
መግለጫው ብቻ አይደለምኮ በየ ቢሮው በር ላይ የተለጠፉ ቢል ቦርዶች አሉ፡፡ ራእይ፣ ተልዕኮ፣ ዓላማ ይላሉ፡፡ ዝቅ ብለው ይህንን ከፈለጉ እዚህ ይሂዱ፣ ይህንን ለመጨረስ ይህንን ያህል ደቂቃ ይላሉ፡፡ ዝርዝሩን ስታዩት ርካሽ ነው፡፡ እየበረራችሁ እዚያ ቢሮ ስትደርሱ ግን ጸሐፊዋ የለችም፣ መስኮቱ ተዘግቷል፣ በሌላኛው መስኮት ይጠቀሙ፣ ለሻሂ ወጥተዋል፣ ሲስተም አይሠራም፣ ኮምፒውተር ተበላሽቷል፣ የሚል ቫት ይጨመርትበታል፡፡ ያን ጊዜ ዋጋው አናት ላይ ይወጣል፡፡
ይሄ የቫት ነገርኮ ቤት አከራዮችም አለ፡፡ ቤቱ አራት መኝታ ቤት፣ የተሟላ ኪችን፣ ሻወር ቤት፣ ፈረስ የሚያስጋልብ ሳሎን፣ ሰርቢስ፣ አለው ተባሉና ልትከራዩ ትሄዳላችሁ፡፡ ሳሎኑን ገና ስታዩት እንኳን ፈረስ ሊያስጋልብ አይጥ ከጉድጓዷ ስትወጣ ተቃራኒው ግድግዳ ግንባሯን ይገጫታል፡፡ ምኝታ ቤቶቹ ጭንቅላታችሁን ብቻ ቤት ውስጥ አድርጋችሁ ሌላውን አካላችሁን ውጭ እንድታሳድሩ ይመክሯችኋል፡፡ ባኞ ቤቱ ውስጥ ያለው ሻወር ሦስት ቀዳዳዎች ያሉት «ውኃ ወላዋይ» እያለ የሚዘፍን ተረበኛ ነው፡፡ ኪችን የቱ ነው? ስትሉ ቀደምት ተከራዮች ምጣድ ይጥዱበት የነበረ በጭቃ የተሠራ ማድቤት ታያላችሁ፡፡ አንዳንዱን ግድግዳ ከተደገፋችሁት ጎረቤት ቤት ውስጥ ልትገኙ ትችላላችሁና መጠንቀቅ አለባችሁ፡፡
ቫቱ ይሄ ብቻ መሰላችሁ፡፡ ከሦስት ሰዓት በኋላ ማምሸት፣ ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ቀድሞ መውጣት፣ በኤሌክትሪክ ምግብ ማብሰል፣ የቤት ሠራተኛ መቅጠር፣ ውኃ ከአምስት ጠብታ በላይ ማፍሰስ፣ እንግዳ ማብዛት፣ የሴት ጓደኛ ይዞ መምጣት፣ ክልክል መሆኑ ይነገራችኋል፡፡ ይኼ ዓይነት ቫት ከርቸሌም የለ ትላላችሁ፡፡
ግን በዚህ አያበቃም፡፡
ባለቤቶቹን ስትገቡ እንዴት ዋላችሁ፣ ስትወጡ ደኅና ዋሉ ማለት፤ ልቅሶ ሲሆን መድረስ፣ ሠርግ ሲሆን ማገዝ፣ ሲታመሙ ተክዞ መጠየቅ፣ ቡና ሲሆን አፍልቶ መጥራት፣ ካልሆነም ሲጠሩ ከቱባ ወሬ ጋር መገኘት፣ የቤቱን ልጆች በፍቅር ማጫወት፣ በቤት ውስጥ ዕቃ ቢሰብሩ እንኳን መሳቅ፣ ፊልድ ከወጡ ከሰል፣ ቡና፣ ቅቤ፣ ማር ካልተገኘም እንጨት ጭኖ መምጣት የሚባሉ ቫቶች በኪራዩ ላይ ቆይተው ይጨመራሉ፡፡
አሁን የሟች አጭር የሕይወት ታሪክ ሲነበብ ከዋጋው ቫቱ አይበልጥም፡፡ መጀመርያ አጭሩን በማስረዘም ቫት ያስከፍሉናል፡፡ ከዚያም ሲወለድ በራእይ ታይቶ፣ ሲያድግ በክብካቤ፣ ሲማር አንደኛ እየወጣ፣ ሲሠራ እየተመሰገነ፣ ሲታመም እየተጠየቀ መሆኑን ይተርኩታል፡፡ መቼም ሲሞት ደግ፣ ሩኅሩኅ፣ ለሰው አዛኝ፣ የተራበ የሚያበላ፣ የተጠማ የሚያጠጣ፣ ለሰው ችግር ደራሽ፣ አገሩን ወዳድ የማይሆን የለም፡፡ ታድያ እዚህ ላይ ቫት መጨመሩን አትርሱ፡፡
አሁን አሁንማ «ከውጭ ሀገር ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከአውስትራልያ፣ ከቻይና፣ ከሩቅ ምሥራቅ ደውላችሁ ያጽናናችሁንን ሁሉ እናመሰግናለን» የሚል አዲስ ቫት ደግሞ መጥቷል፡፡ እኔ ግን ቫቱን ቀንሼ አዲስ አበባ አሜሪካን ግቢ፣ ፈረንሳይ ሰፈር፣ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ፣ የአውስትራልያ ጣውላ መሸጫ፣ የቻይና ሬስቶራንት ሠራተኞች፣ አጽናንተዋቸው ይሆናል ብዬ ዋጋውን ብቻ ከፍዬ እወጣለሁ፡፡
ቫት በዛ፡፡ ቢቻል ይቅር፣ ባይቻል ይቀነስልን፡፡ ይሄ አንዳንድ ሱቆች ስትሄዱ «በቫት ነው ወይስ ያለ ቫት» ብለው የሚጠይቋችሁ ነገር ለንግዱ ጥሩ ባይሆንም ለሌሎች ነገሮች ግን ቢሠራበት ምናለ፡፡ አገር ውስጥ ገቢስ ቢሆን ማንም እየተነሣ ቫት እየጨመረ ሲያስከፍለን ዝም ይላል እንዴ?
ግን ኧረ እነዚህ አካላት የሚጨምሩት ቫት መጨረሻ የት ነው የሚገባው? እርሱን ያዙልኝ፡፡

ከናስር ከተማ፣ ካይሮ ግብጽ


15 comments:

 1. «ለመሆኑ ዓባይ ከኢትዮጵያ ወደ ግብጽ የሚሄደው በየትኛው የክትባት ካርዱ ነው?»
  hahaha....Amazing! des yemil ababal...

  ReplyDelete
 2. 'እነዚህ አካላት የሚጨምሩት ቫት መጨረሻ የት ነው የሚገባው? እርሱን ያዙልኝ፡፡'
  ውድ ወንድሜ በተለመደው ንስራዊ እይታህ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ መረጃ በጣፈጠና ለዛ ባለው አቀራረብ ስላካፈልከን ከልቤ አመሰግናለሁ። ጀሮ ያለው ይስማ ነው ነገሩ። በተለይ ወሬን ከነ ቫቱ ማቅረብ ልማድ ለሆነባቸው። አንዳንዶቹማ ወሬውን በሌላ ጊዜ ደግመው ሲነገሩን ከሌላ ቀድመን ያልተስተካከለ ወሬ የሰማን እንኪመስለን ያደናብሩናል። እናም ቫት ጨምራችሁ ለምትነገሩን ጭማሪውን በጽሑፍ ያዙት። ካለበለዚያ መጨረሻው ካለምንም ማስረጃ በራሳችሁ አንደበት ቀላችሁ እንዳትገኙ።
  እውነትን የምናወራበት አንደበት የምናመልከው ፈጣሪ ይስጠን።

  ReplyDelete
 3. አንተም እዚህ ላይ ቫት ጨመርክ እኮ! እንዴ በስነጽሑፍ ሕግ ግነትን ለመግለጽ የቀድሞ ሰዎች አባባል መጠቀም ቢፈቀድም እዚህ ላይ ግን ቫት ብለህ እየተቸህ ቫት ማብዛት ጥሩ አልመሰለኝም::

  ምሳሌ: " ...ሳሎኑን ገና ስታዩት እንኳን ፈረስ ሊያስጋልብ አይጥ ከጉድጓዷ ስትወጣ ተቃራኒው ግድግዳ ግንባሯን ይገጫታል፡፡ ምኝታ ቤቶቹ ጭንቅላታችሁን ብቻ ቤት ውስጥ አድርጋችሁ ሌላውን አካላችሁን ውጭ እንድታሳድሩ ይመክሯችኋል፡፡ "

  ReplyDelete
 4. ጥሩ መልእክት የያዘ ጽሁፍ ነው:: ምንም እንኳ አንተን ለመተቸት የበቃሁ ባልሆንም እንዲያው የተሰማኝን አንድ ሁለት አስተያየት ለመሰንዘር ይፈቀድልኝ:: የስነ ጽሁፍ ችሎታ የለኝም ነገር ግን እንደ ተራ አንባቢ ገና ጽሁፉ ግማሽ ላይ ስደርስ እዚህ ላይም "ቫቱ" በዛ እያልሁ ነው የጨረስሁት:: ከተለያዩ የዘይቤ አይነቶች ግነት ዘይቤ አንዱ የአጻጻፍ ስልት እንደሆነ የአስረኛ ክፍል አማረኛ መምህራችን ጋሸ መኮነን ያስተማሩኝን አስታውሳለሁ:: አንተም በጽሁፍህ ውስጥ ብዙ ጊዘ ይሄንን የአጻጻፍ ስልት ስትጠቀምበት አስተውያለሁ:: ነገር ግን ግነቷም "ቫት" ሳይጨመርባት የቀረ አይመስለኝም:: ለማንኛውም ምን ለማለት እንደፈለግህ ስለገባኝ እኔም "ቫቱን" ቀንሸ ነው ያነበብሁት:: እኔ ሌላው የሚገርመኝ ነገር የቃላት አጠቃቀም ነገር ነው:: ብዙ ጊዘ ራሳችንን እንሁን እያልህ ትጽፋለህ ታስተምራለህም:: እኔም በጣም እስማማለሁ:: ነገር ግን በጣም በሚገርም ሁኔታ የአማርኛ ቃላትን መጠቀም በምትችልበት ቦታ እንኳ የእንግሊዘኛ ቃላትን ያለአግባብ የመጠቀም ሁኔታ አስተውያለሁ:: ለአብነት ለመጥቀስ "ኪችን" "ኦፍ ዘሪከርድ እንነጋገርና"(በ ኮኮነት ላይ የተጠቀምከው) እና ሌሎችም:: እንደኔ አስተያየት ከእንዳንተ አይነት ጸሃፊ እና አስተማሪ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ሳይ ትንሽ ግራ ያጋባኛል:: ለምን የራሳችንን መጠቅም እየቻልን ሌላ እንጠቀማለን? ይሄ ስልጣኔ መሆኑ ነው ወይስ ለ እንግሊዘኛ እጅ ሰጠን ማለት ነው? የሚሉ ጥያቄወች በአእምሮየ ይመላለሳሉ እርግጥ ነው ስናወራ እንቀላቅላለን (አንዳንዴ እንዲያውም ካልቀላቀልን ሰወች የማይረዱን አድርገን የምናስብ ነው የሚመስለው) ነግር ግን ይህች መጦመሪያ አማረኝ መጦመሪያ እስከሆነች ድረስ እና ራሳችንን እንሁን ብለን እስካመንን ድረስ በአማርኛችን መጠቀም አለብን ብየ አስባለሁ::ለዚያውም ቃላቱ በግልጽ እያሉን (ኪችን ከማለት ማድቤት ወይም ኩሽና ማለት ይቻላል:: "ኦፍዘሪከርድ እንነጋገርና" ከማለት ይልቅ በሹክሹክታ እናውራ ማለት ይቻላል:: እኔ ይሄን ያህል አማራጭ ካቀርብሁ አንተ ደግሞ በጣም የተሻለ መግልጽ የሚችሉ አማርኛ ቃላትን መጠቀም ወይም መፍጠር ትችላለህ ብየ አስባለሁ):: በተለይም ደግሞ እንደዚህ በብዙ ሰወች በምትጎበኝ ጦማር ላይ ሲወጣ ጥሩ አይደለም እና ወደፊት ቢታሰብበት:: ለዚህ ትኩረት መስጠትም አንዱ በተግባር ማስተማሪያ ነውና


  አመሰግናለሁ
  ሰማሀኝ
  ሲያትል

  ReplyDelete
 5. ዲያቆን ሃብታሙ ዘ ባህርዳር ፖሊMay 15, 2011 at 11:16 PM

  ኧረ እባካችሁ ቫቱን አንሡልን ካልሆነም ቀንሱልን፡፡ከተጻፈው ጽሑፍ ጀምሮ ባቱ ይቀነስ
  ጥሩ አይታ ነው ዲ/ዳንኤል
  አግዚአብሔር ቃለህይወትን ያሰማልን
  አሜን ።

  ReplyDelete
 6. Kale hiwot yasemalin Dn Daniel.
  Please readers, stop cutting and pasting. What is the meaning of posting in your comment part of what we have already read. Please stop it. it is very irritating. God Bless!!! Atlanta.

  ReplyDelete
 7. ቂቂቂቂ………"ባኞ ቤቱ ውስጥ ያለው ሻወር ሦስት ቀዳዳዎች ያሉት «ውኃ ወላዋይ» እያለ የሚዘፍን ተረበኛ ነው፡፡" ውኃ ወላዋይ /2/ ያንችም ልብ እንደ እኔ ይወልላይ ወይ? አይይይይ ዳኒ እንዲህ እያሳክ ልክ ልካችን ንገረን እንጅ፡፡ ሳር እስቃለሁ አለ ጓያ!!!!!

  ReplyDelete
 8. ወንድም ዳንኤል፤ "ቫቱ ይነሣልን ወይ ይቀነስልን "
  መቸም እንደተለመደው በጉጉት ከምጠብቃቸው እና አንጀቴን ከሚያርሱት ጽሑፎችህ መደብ እኩል የሚሰለፍ ነው። ያዘለውም ትምህርት እንደዚያው!

  ዛሬ ግን የሲያትሉ ሰማሀኝ ያቀረበውን አስተያየት በመደገፍ እኔም የአንተን የባዕዳውያን ቃላቶችን [የራስ ሳይታጣ] መጠቀም ቅራኔዬን ለማስፈር ነው የፈልግሁት። ይሄንን ጉዳይ በበቀደሙ 'ኮኮነት' አንቀጽህ አቅርበኸው እንደነበር እያስታወስኩ የአንባብያንህም ሠፊ ድጋፍ፤ ተከትለው የቀረቡት አስተያየቶች ይመሰክሩታል። እኔም እዚያው ላይ "አጉል መፈርነጅ በእሳት መጫወት እንዳይሆንብን እያንዳንዳችን በአስቸኳይ ኃላፊነቱን ወስደን መጀመሪያ እራሳችንን ከ'ኮኮነት' ግድፈት በመጠበቅ፤ በሌሎች ወገኖቻችንም ወንጀሉን ስንገነዘብ ከማረም፤ ከመገሰጽ ወደኋላ አንበል።" ባልኩት እምነት ነው የዚህን ግድፈት ለማውገዝ የፈልግሁት። መቸም አንተም ሆንክ አንባቢዎችህ በዚሁ መንፈስ እንደምትቀበሉት ተስፋ አደርጋለሁ።

  በበኩሌ በዚህም ጦማር ላይ ሆነ በሌላ መገናኛ የምታስተምረውን ከልብህ እንደምታምንበትና እንደምትተገብረው በማመን ነው የምከታተለው። አለበለዚያማ የምታሠፍራቸውን ቁም ነገሮች እንዲያው የመጻፍ ችሎታህን ለማሳየትና ተከታዮችን ለማፍራት ብቻ ነው ማለት ነው። ከሆነ ዋጋው ምኑ ጋ ነው?

  ሰይፈ ገብርኤል
  ከሎንዶን

  ReplyDelete
 9. በእውነት ወቅታዊ እይታ የተሟላ እና በአስገራሚ አገላለፅ የቀረበ ጽሁፍ ነው፡፡እኔ እንኳን በተሰጡ አስተያየቶች ላይ የደራሲውን ቃላት የመይገልጹ፤ ነገር ግን ገጸ- ባህሪያት የተናገሩትን እንዳለ ያሰቀመጣቸውን ቃላት በመውሰድ ደራሲው /ዲ. ዳንኤል/ የተተቸባቸውን ቃለት የራሱ ስላልመሰሉኝ ለመጠቆም ያክል ነው፡፡ ይኸውም ሰማኸኝ እንዳለው …..ለአብነት ለመጥቀስ "ኪችን" "ኦፍ ዘሪከርድ እንነጋገርና"(በ ኮኮነት ላይ የተጠቀምከው) እና ሌሎችም:: እንደኔ አስተያየት ከእንዳንተ አይነት ጸሃፊ እና አስተማሪ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ሳይ ትንሽ ግራ ያጋባኛል…….(ኪችን ከማለት ማድቤት ወይም ኩሽና ማለት ይቻላል:: "ኦፍዘሪከርድ እንነጋገርና" ከማለት ይልቅ በሹክሹክታ እናውራ ማለት ይቻላል:: እኔ ይሄን ያህል አማራጭ ካቀርብሁ አንተ ደግሞ በጣም የተሻለ መግልጽ የሚችሉ አማርኛ ቃላትን መጠቀም ወይም መፍጠር ትችላለህ ብየ አስባለሁ):: በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ሌላ አስተያየት ሰጭም ደግመውታል፡፡ነገር ግን ደ. ዳንኤል ባዕድ ቃላትን መቀየር አስከቻለ ድረስ እንዳለ መጠቀሙ በሁላችንም ዘንድ ተቀባይነት የማይሰጠው ቢሆንም በጽሁፉ ውስጥ ‹‹….ቤቱ አራት መኝታ ቤት፣ የተሟላ ኪችን፣ ሻወር ቤት፣ ፈረስ የሚያስጋልብ ሳሎን፣ ሰርቢስ፣ አለው ተባሉና ልትከራዩ ትሄዳላችሁ...፡፡›› በማለት የገለጸው አከራዮች ያላቸው ሰዎች የሚናገሩትን እንጅ ወደራሱ አነጋገር /አጻጻፍ/ ሲመለስ ግን ራሱም ‹‹ማድ ቤት›› የሚል ቃል ተጠቅሞ እናገኛለን ለምሳሌ ....ኪችን የቱ ነው? ስትሉ ቀደምት ተከራዮች ምጣድ ይጥዱበት የነበረ በጭቃ የተሠራ ማድቤት ታያላችሁ፡፡.... ይላል፡፡ ግነት የበዛበት ነው ከሚባል በስተቀር ባድ ቃላት ተጠቅሟል የሚለው ትችት ስላልተዋጠልኝ ነው፡፡

  ReplyDelete
 10. It's a good article that teaches us about the negative effect of exaggeration or just 'embellished lie'. I think that is a very real and frequent thing in our country where ever you go(except few areas). Do we have to try to change this bad culture, of course, but it starts from all of us, for that I agree with what "Shagiz" (one of the above commenter wrote)

  Peace

  ReplyDelete
 11. <<.....የሰውን ጭራቅነት የሚያወራውንም ቢሆን የረዘመ ጥፍሩን፣ የገጠጠ ጥርሱን፣ የተዘረጋ ምላሱን፣ የተቀረደደ አፉን፣ የጎደጎደ ዓይኑን፣ የጨለመ ገጹን እያወጣችሁ የተነገራችሁን ሰው ማሰብ ካልቻላችሁ በቀር ቫቱን መክፈል ከባድ ይሆንባችኋል፡፡....>>
  እረግጠኛ ነኝ በምትሔድበትም ይህ የቫት ጉዳይ እንደሚገጥምህ ከላይ እንዳልከው...ጥሩ ሰው መጥፎ መጥፎ ሰው ጥሩ ሆኖ በሰው አንደበት ብቻ የሚኮነኑበት አጋጣሚዎች አሉና አንተም ይህ ሊገጥምህ ስለሚችል ከሰዎቹ ቫት ይልቅ የራስህን ሚዛን እንደምትደፋ አምናልሁ። ጭራቅ የተባለው ቅዱስ.... ቅዱስ የተባለው ደግሞ ጭራቅ የሚሆንበትም አጋጣሚ አለና።

  ReplyDelete
 12. Wow!What a talent you have! There is nothing satisfaction than sensing the truth.

  ReplyDelete
 13. ሀሉንም ጽሁፎችክን ወድጃቸዋለሁ እወዳቸዋለሁ!! እያዝናኑ የሚያስተምሩ እያሳቁ ቁም ነገር የሚያስጨብጡ፡፡በጣም እናመሰግናለን እንዳንተ አይነት ጸሃፊያንን እድሚያቸውን ያርዝምልን፡፡

  ReplyDelete
 14. I'm afraid if you ask me my honest opinion, Daniel Kibret is boring, his way of presenting facts suits more for minors, the issues are not deep enough.....all in all; an experienced, demanding reader or critic can't stand it.....I sometimes wonder how can this kind of ordinary style be so popular(considering in modern society nobody tells nobody what to do and be sarcastic except putting facts reasonably and expressing owns opinion neutrally)?....I think this puts the intellectual standards of the audience in question.

  ReplyDelete