Sunday, May 29, 2011

ገዳመ አስቄጥስ (ካለፈው የቀጠለ)

መቼም አለማውቀን የመሰለ ደግ ነገር የለም፡፡ ዕንቅልፍ ለመተኛት፣ ሃሳብን ለመጣል፣ ከጨጓራ በሽታ ለመዳን እና ፀጉር ሳይነጭ እንዲኖር ለማድረግ ትልቁ መፍትሔ አለማወቅ ነው፡፡
ላላወቀ ሰው ሁሉም ነገር ሰላም ነው፡፡ ወንዞች ይፈስሳሉ፣ ነፋሳት ይነፍሳሉ፤ ፀሐይ ትወጣለች ፀሐይ ትገባለች፡፡ እርሱ ያለበት ዓለም «በዓለም አንደኛ በአፍሪካ ሁለተኛ ነው» እያለ ይጽናናል፡፡ የደረሰበትን ዕድገት የዕድገት ሁሉ መጨረሻ አድርጎ ይመጻደቃል፡፡

Thursday, May 26, 2011

ገዳመ አስቄጥስ

እየተጓዝን ነው፡፡ ክን በዓይናችን ለማየት፡፡ ስለ ገዳመ አስቄጥስ እና ስለ አባ መቃርዮስ በታሪክ መጻሕፍት ከማንበብ እና በትምህርት ከመስማት ያለፈ ነገር የለኝም፡፡ ግን እንደ በለዓም «አየዋለሁ፣ አሁን ግን አይደለም» እል ነበር በጉጉት፡፡ እነሆ ዛሬ ላየው ነው፡፡

በዋዲ ኤል ናትሩን ከሚገኙት ሰባት ገዳማት አንዱ ወደ ሆነውና ከካይሮ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወዳለው ወደ አባ መቃርስ ገዳም በመጓዝ ላይ ነን፡፡ ገዳሙ ከካይሮ ወደ እስክንድርያ በሚወስደው የበረሃ ጎዳና በስተ ምዕራብ በኩል ይገኛል፡፡
ለአራት ሰዓታት ያህል ከነዳን በኋላ መኪናችን ወደ ምዕራቡ አቅጣጫ ታጠፈ፡፡ ጭው ያለ በረሃ ነው የሚታየን፡፡ ያውም ነጭ በረሃ፡፡ ድንገት ግን በዛፎች የተሸፈነ መንገድ ውስጥ ገባን፡፡ ግራ እና ቀኝ ጥቅጥቅ ያለ ባሕር ዛፍ ከበበን፡፡ አብረውን ያሉ የካይሮ ልጆች አሁን ወደ ገዳሙ ክልል እየገባን ነው አሉን፡፡ በዚያ ደን ውስጥ ለሠላሳ ደቂቃ ከነዳን በኋላ አንድ ትልቅ ግቢ ከፊታችን ተነጠፈ፡፡

Monday, May 23, 2011

፩ ሚሊዮን አንባቢ

 በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱሳንም ምልጃ፣ በእናንተም ትብብር በዛሬው ዕለት የዚህ ጦማር አንባብያን ቁጥርሚሊዮን ደረሰ፡፡
  እስካሁን 80 ሀገሮች በአንድ ሚሊዮን ጎብኝዎች የተጎበኘው ይህ ጦማር ከግማሽ በላይ አንባብያኑን ያገኘው ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ኤስ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ካናዳ እና ኖርዌይ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለት እስከ አምስተኛ ያለውን ቦታ ይዘዋል፡፡

ከቀረቡት ጽሑፎች መካከል «ሰው በቁሙ ሐውልት ለምን ይሠራል የሚለው ጽሑፍ በመነበብ አንደኛ ሲሆን «እግር ያለው ባለ ክንፍ፣ የአንደ አባት ምክር፣ አለቃ ገብረ ሐና፣ የሚያሸንፍ ፍቅር» ከሁለት እስከ አምስት ያለውን ቦታ ይዘዋል፡፡
እንድንሠራ አግዙን፣ እንድንስተካከል አርሙን፣ እንድንበረታ ጸልዩልን፡፡

Sunday, May 22, 2011

የድኾች ጳጳስ


ከካይሮ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ወደ ሚርቅ ፈዩም ወደሚባል ቦታ በመጓዝ ላይ ነን፡፡ በቦታው የአባ አብርሃም ገዳም ይገኛል፡፡ ዓባይ ግራ እና ቀኛችንን እየተመላለሰ ያጠጣዋል፡፡ እርሻው ይመስጣል፡፡ ግብጽን አረንጓዴ ሆና ስታዩዋት በሰሐራ በረሃ ውስጥ ያለች ሀገር አትመስልም፡፡

ግብፃውያኑ ገበሬዎች በትንንሽ ትራክተሮች ያርሳሉ፣ ያጭዳሉ ይወቃሉ፡፡ በየእርሻው መካከል ተራራ የሚያህሉ በጆንያ የተሞሉ የእህል ክምሮችን ታያላችሁ፡፡ በየእርሻው ዳር በቦይ ከመጣው የዓባይ ውኃ በመሳቢያ ማሽን እየጨለፉ ወደ እርሻው ይለቅቁታል፡፡ ከዚያም ከሦስት እና አራት ኪሎ ሜትር በላይ ለሚሆን ርቀት እየተጓዘ ማሳውን ያረሰርሰዋል፡፡

Saturday, May 21, 2011

ዓባይን በካይሮ


«ወይ ዓባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሕታዊ ነኝ ብለህ በረሃ ለበረሃ፣ ሸለቆ ለሸለቆ ስትመንን የኖርክ ወንዝ እዚህ ካይሮ መጥተህ ከተሜ ትሆን? እንዴው ምን ቢያቀምሱህ ነው እንዲህ የከተማ ወንዝ የሆንከው ጃል አልኩት ካይሮ ላይ ዓባይን ሳገኘው፡፡

«ከሀገሩ ሲወጣ ምናኔውን ብሕትውናውን ያልተወ ማን አለ? እህል አንቀምስም፣ ልብስ አንለብስም፣ ጫማ አናደርግም፣ ሬዲዮ አንሰማም፣ ሰዓት አናሥርም ሲሉ የነበሩት ሁሉ ውጭ ሀገር ወጥተው አይደለም እንዴ ከተሜ ሆነው የቀሩት? ምን በኔ የተጀመረ ታስመስላለህ

«ቆይ ግን አንተ ይህንን ያህል ዘመን ኖረህ ኖረህ ዛሬ ልትገደብ መሆኑን ስትሰማ ምን ተሰማህ

«በርግጥ ደስ ይላል፡፡ እነ ዐፄ ሐርቤ፣ እነ ዐፄ ዳዊት ያሰቡት ሲሳካ ማየት እንደገና መወለድ ነው፡፡ አይተህኛል ካይሮ ላይ፡፡ ወንዝ ሆኜ እገማደላለህ፣ ኩሬ ሆኜ ዕታቆራለሁ፣ የቦይ ውኃ ሆኜ መንደር ለመንደር እዞራለሁ፣ የመስኖ ውኃ ሆኜ ገጠር ለገጠር እንከራ ተታለሁ፡፡ የቧንቧ ውኃ ሆኜ ቤት ለቤት አዞራለሁ፡፡ የቆሻሻ መውሰጃ ሆኜ ቱቦ ለቱቦ እሰቃያለሁ፡፡ ምን ያልሆንኩት አለ፡፡»

Friday, May 20, 2011

መዓልቃ

በተአምረ ማርያም መግቢያ ላይ «የምሥር ዕጣ ከምትሆን ከመዓልቃ» የተገኘ መሆኑን ይነግረናል፡፡ «ምሥር» የሚላት ግብጽን ነው፡፡ ዓረቦች ግብጽን ምሥር ብለው ነው የሚጠሯት፡፡ ግብጽ የሚለው ስያሜ ከግሪኩ ስያሜ የመጣ ነው፡፡

መዓልቃ ዛሬ በአሮጌው ካይሮ የምትገኝ ቦታ ናት፡፡ 12ኛው መክዘ ጀምሮ የእስክንድርያ ፓትርያርክ መንበር ሆና ነበር፡፡ አብርሃም ሶርያዊም የነበረው እዚያ ነው፡፡ ብዙ አባቶቻችን ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ የእስክንድርያውን ፓትርያርክ ለማግኘት ይመጡባት ነበር፡፡ በዚያም ብዙ የኢትዮጵያ መነኮሳት ስለነበሩ በአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ነበራቸው፡፡ እስከ አሁን «አል ሐበሽ» እየተባለ የሚጠራ የራሳቸው መቃብርም ነበር፡፡ አሁን በዐረብኛ «ሙዓለቃህ» ትባላለች፡፡ በቦታው የተንጠለጠለችው ቤተ ክርስቲያን እየተባለች የምትጠራ የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡