Thursday, April 7, 2011

የፍቅር መስዋእትነት

 ወገን ሀበሻ በፍቅር ስለ ፍቅር ጀግኖአል! ኢትዮጵያዊው አንደኛው ኩላሊቱን በነጻ በማበርከት የጓደኛውንና የወገኑን ህይወት የታደገበት አስደናቂ የፍቅር መስዋእትነት፤ በደቡብ አፍሪካ፥ፒተር ስበርግ ከተማ!!!
በፍቅር ለይኩን ከደቡብ አፍሪካ

በሎንግ አይላንድ ከተማ ኒውዮርክ ስቴት ነዋሪ የሆኑት ዶክተር ሪቻርድ ባታሊና ወይዘሪት ዳውኔል እኤአ 1990 ዓ/ም ድል ያለ ድግስ ደግሰው፤ በዘመዶቻቸውና በጓደኞቻቸው ፊት ሀብትሽ በሀብቴ፤ ጤንነትሽ ጤንነቴ፤ እስከሞት ድረስ የሚለየን ነገር አይኑር ብለው በህግ ተጋቡ። ከተጋቡ ከ11 ዓመታት በህዋላ የዶክተር ሪቻርድ ባለቤት ወይዘሮ ዳንዌል ለሞት የሚያደርስ የኩላሊት ህመም አደረባት። በዚህ ጊዜ ባለቤቷ ዶክተር ሪቻርድ ባቲላ አንዱን ኩላሊት በቀዶ ጥገና አስወጥቶ ለባለቤቱ ሰጣትና ከመሞት ተረፈች።
እነዚህ ጥንዶች ከተጋቡ ከ15 ዓመታት በህዋላ በ2005 ዓ/ም ተጣሉና ወይዘሮ ዳንዌል በፍርድ ቤት ፍቺ ጠየቀች። በዚህ ጊዜ ባለቤቷ ዶክተር ሪቻርድ ፍቺውን እቀበላለሁ። ነገር ግን "በፍቅራችን ጊዜ የሰጠሁዋትን ኩላሊት አስቀደማ ትመልስልኝ ወይም የኩላሊቴን ተመጣጣኝ ዋጋ የሆነውን 1.5 ሚሊዮን ዶላር ትክፈለኝ" በማለት በጠበቃው በዶምኒክ ባርባራ በኩል በሎንግ አይላንድ ፍርድ ቤት ማመልከቱን ከአንድ ታዋቂ ከሆነ በአሜሪካ አገር ከሚታተም መጽሄት ማንበቤ ትዝ ይለኛል። አዎ እኛ ሰዎች ፍቅራችን፣ ቸርነታችንና ልግስናችን ብዙውን ጊዜ፤ የኛ ፍቅር ተቀባዮች ከኛ ጋር ባላቸው ግንኙነትና ጥቅም ጋር የተቆራኘ ነው። በተደጋጋሚ የልግስናችንና የቸርነታችን መነሻ ምክንያት፤ በመለገሳችንና በመስጠታችን የተነሳ የምናገኘው ድብቅ ውጤት ስላለን ነው።

ይሄን በአሜሪካ ሀገር የተፈጸመ አስገራሚና የእኛን የሰው ልጆችን የፍቅር ልክ እስከምን ድረስ እንደሆነ የተንጸባረቀበትን አሳዛኝ ታሪክ ያነሳሁት በዛሬው ጹሁፌ በዚህ ባለሁበት በደቡብ አፍሪካ አንድ ወገናችን የሆነ ኢትዮጵያዊ ኩላሊቱን በነጻ በመለገስ የጓደኛውን ሕይወት የታደገበትን አስደናቂ የሆነ የፍቅር መስዋእትነት በተግባር የታየበትንና ልክ እግዚአብሔር ለእኛ በደልና ኃጢአት ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን የባህሪይ ልጁን ጌታችንንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ ለሞት አሳልፎ በመስጠት፣ የሰው ልጆችን ሁሉ ኃጢአትና በደል ይቅር ያለበትን ዘላለማዊ ፍቅርና ይቅርታ የሚያሳስብ፣ የዚህን ወንድማችንን  አስደናቂ ታሪክ ላካፍላችሁ ፈልጌ ነው። መቼም ፈርዶብን ሀበሾች/ኢትዮጵያውያን ስንባል በሄድንበት ሁሉ ዛሬ ዛሬ እየታወቅንበት ያለው መለያችን፦ ምቀኝነታችን፣ ፍቅር ማጣታችን፣ መለያየታችንና  እርስ በርስ በጎሪጥ የምንተያይ፣ ቅን የሆነ መንፈስ የማጣታችን ጉዳይ ከሆነ ሰንባብቷል።  

እንደውም ስለዚህ በደማችን ውስጥ ያለ ያህል ስለምንታማበትና ፍቅር የማጣታችንንና የምቀኝነታችንን ጥግና ክፋት በሚያሳይ መልኩ ተደጋግሞ የሚነገርው ቀልድ ቢጤ ትዝ አለኝ። አንድ ጊዜ እግዚብሔር ወደ ምድር ወረዶ ነው አሉ፦ እናም ከእያንዳንዱ ሀገር ዜጋ ሰዎችን በማግኘት የሚሹትን ነገር በመጠየቅ እንደመሻታቸው አደረገላቸው እናም በመጨረሻ ወደ አንድ ኢትዮጵያዊ በመምጣት "ለጎረቤትህ ለአንተ የምሰጠውን እጥፍ አሰጠዋለሁ፤ ስለዚህ ለአንተ ምን ልስጥህ ብሎ ይጠይቀዋል፣" ያ ኢትዮጵያዊም መልሶ "አንድ ዓይኔን አጥፋልኝ" በማለት ልመናውን ለአምላኩ እንዳቀረበ የሚተረተው ተረት ምን ያህል ምቀኝነት በደም ውስጣችን ተዋህዶ እንዳለና በእጅጉ ፍቅርንና ቅንነትን የተራብን፣ ሁሌም የሚያሳስበን የእኛ ማግኘትና ማጣት ሳይሆን የሌሎች ኑሮና ህይወት መሆኑን ጥሩ ማሳያ ነው:: የሚገርመው ይህ ባህርያችን ወደ ባህር ማዶ የተሻገርነውን ጭምር እያሰቃየን ያለ ክፉ የፍቅር ማጣት ደዌ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

በውጭ ዓለም ወጥተን እንኳ የምንኖርበት የውጩ ማህበረሰብ ለሌሎች ድካምና ልፋት እንዲሁም ስኬት የሚቸሩትን አድናቆትና ያላቸውን ቀና አመለካከት እንዲሁም የእንኳን ደስ ያለህና አመሰግናለሁ (Thank you) የምትለው የምስጋና ቃል እንኳን ለብዙዎቻችን የዳገት ያህል አስቸጋሪ እንደሆነች ብዙዎቻችን የምንተዋወቀው ጉዳይ ነው። ብዙ ጊዜም የሚያስጨንቀን የራሳችን ጉዳይ ሳይሆን የሌሎች ስኬትና የኑሮ መከናወን ነው እንቅልፍ ሲነሳን የሚያድረው፤ በዚህም የተነሳ በውስጣችን በሚፈጠር ሰይጣናዊ ቅናት እየተንገበገብን  ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የኑሮና የህይወት ስኬት መጥፎ የሆነ ስያሜ በመስጠት አናውቀውም፣ አናቃትም እንዴ በሚል ፈሊጥና ንቀት የስም ማጥፋት ዘመቻ (Character Assassination) የተቀዳጀነው ክፉ የባህሪያችን ልክ ለረዥም ዘመናት በጦርነት ሜዳ ታሪክ ካስመዘገብነው ጀብድ፣ ወኔና ጀግንነት ያልተናነሰ ብዙ ሊባልለት የሚችል ነው።

የዚሁ የምቀኝነታችንና እርስ በእርስ የመበላላታችን ምክንያቱ የፍቅር ርሃብተኞች የመሆናችን ጉዳይ ነው፤ ይሄ ባህሪያችን ደግሞ እንደ ጨው ዘር በተበትንበት በውጩ ዓለምም መታወቂያችን ነው፤ "ሀበሻ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መስራት አይችልም" እየተባለ መተርት ከጀመረም ሰነባብቷል፤ ለነገሩ  አብሮ  መብላቱም ይሄ ተረቱ በተተረተበት በዛ በአባቶቻችን ዘመን እንጂ ዛሬ ዛሬ አብሮ መብላቱም እየናፈቀን ያለበት በትዝታ የምናወጋው የትናት ታሪካችን የሆነ እየመጣ ይመስለኛል።

እናም ከዚህ ሌላው ዓለም እኛን ከተረዳበትና እኛም ለራሳችን ከሰጠነውና አምነን ከተቀበልነው ባህርያችን ጋር በማይገጥም መልኩ በዚህ በደቡብ አፍሪካ መላውን ሀበሻ ብቻ ሳይሆን ደቡብ አፍሪካውያንና የሌሎች ሀገራትን ዜጎችን ጭምር ያስደመመ አንድ ታሪክ በዚህ በብዛት ሀበሻ በሚኖርባት በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማና የንግድ ማእከል (Business Center) በጆሐንስበርግ ተከናውኗል፤ ወደ እዛ መልካም የምስራችና አስዳናቂ ታሪክ ከማለፌ በፊት ግን በድቡብ አፍሪካ ስላለው የስደት ህይወትና የሚበዛው ወገናችን ስለገባበት ፈርጀ ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥና ቀውስ በጥቂቱ የታዘብኩትን አንባቢዎቼ ያውቁት ዘንድ፤ በደቡብ አፍሪካ ስለ እኛ ሀበሾች ህይወት የኑሮ ውጣ ውረድ ትንሽ ነገር ማለት እፈልጋለሁ።

ቁጥሩን በትክክል ለመገመት ባይቻልም፣ በዚህ በደቡብ አፍሪካ ያለው ስደተኛ ሀበሻ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው። በሀገራችን በተንሰራፋው ድህነት፣ የስራ ማጣት ችግር፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተነሳ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ብዙ ወጣቶች በእግር፣ በመኪና በተለያዩ መጓጓዣ ዘዴዎች በመጠቀም ለሳምንታት አንዳንዴም ለወራት በሚፈጅ ጉዞ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር በማቋረጥ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይገባሉ። አንዳንድ ሰዎችን ለማነጋገር እንደሞከርኩት እነዚህ በገንዘብ ሃይል ተሳክቶላቸው በልስም ቀንቶቸው በመንገድ የሚገጥማቸውን ችግር ተቋቁመው በሰላም የሚደርሱት ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ህገ ወጥ በሆኑ ደላሎች 30000 እስከ 40000 ራንድ እየከፈሉ የሚመጡ ኢትዮጵያውያኖች አሉ፤ በዚህ በደቡብ አፍሪካ ያለው የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን የስደት ህይወት ባለ ብዙ ፈርጅና ባለ ብዙ ህብር ነው። በዚህ አጭር ጹሁፍ የህዝባችንን የኑሮ ውጣ ውረድና እንዲሁም ስኬት ለመተረክ የሚሞክር የሚታሰብም አይደለም። ምናልባት በሌላ ጊዜ እምመለስበት ይሆናል።

በአንጻሩ ደግሞ የሚበዛው ስደተኛው ህዝባችን እዚህ ከደረሰ በኃላ ኑሮን ለማሸነፍና ህልሙን ለማሳካት የሚኬድባቸው መንገዶች ብዙ መራር የሆነ ትግል የታከለበት ነው፤ ውጣ ውረዱ ብዙ ነው። በህዝባችን መካከል ያለው የእርስ በርስ ምቀኝነቱ፣ መለያየቱ፣ ቅናቱ፣ ዘርኝነቱና ሌብነቱ በዚህ ምድር የህይወት ሰልፍ ውስጥ ሌላኛው አሳዛኝ ትራጄዲ ነው። የሚበዛው በግል ንግድ (Business) የተሰማራው ህዝባችን የጥንቱን የኢትዮጵያዊ ማንነቱን፣ ባህሉን ኩራቱን፣ ወግና ሥረዓቱን የረሳ፤ ፍፁም ይሉኝታ የሌለው ወደ ሆነ ማኅበረሰብ እየተቀየረ ያለ ነው የሚመስለው። አንዱ አንዱን ጠልፎ ለመጣልና በአቋራጭ ለመክበር የሚኬሄድባቸው ውስብስብ መንገዶችና የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች ለሚሰማ በእጅጉ የሚያስደነግጥ ነው። ወንጀሎቹ የሚፈጸሙበት ውስብስብ የሆነው ሰንሰለታዊ እዝና ሴራ እንዲሁም ጭካኔ ለሚታዘብ እነዚህ በእርግጥ የምናውቃቸው ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ናቸው ወይስ የሲሲሊና የሜክሲኮ የማፈያ ቡድን ናቸው ያሰኛል።

በተጨማሪም በሀገሪቷ አንዳንድ ባለስልጣናት መካከል በተንሰራፋው ሙስናና ህገ ወጥነት የተነሳ በሀገሪቷ ያሉ ፖሊሶችና ባለስልጣኖች ሳይቀሩ በተደራጀ መልኩ አንዳንድ ወገኖቻችን እያካሄዱ ላለው ዝርፊያና ህገ ወጥ ሥራ በአስር ሺዎችና በመቶ ሺዎች በመደራደር ሽፋን ሰጪ መሆናቸው ወንጀሉ ምን ያህል ስር የሰደደና የተወሳሰበ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። በእርግጥ የሚበዛው ህዝባችን በዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች ያሉትን የንግድ ማእከላትና የንግድ ስራውን በግልም ሆነ በቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር በማዋል የሌሎች ሀገር ሰዎችን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ረገድ ከሚገባው በላይ ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል። እንዲሁም በአንጻሩ ደግሞ በቅንነት ሌት ተቀን ለፍተው አንቱ ለመባል የደረሱ የሚያኮሩ በርካታ ወገኖቻችን ጭምር እንዳሉም አንባቢያን ልብ እንዲሉልኝ እፈልጋለሁ። ሌት ተቀን ውጥተው ወርደው፣ በላባቸው ሰርተውና ለፍተው ምኞታቸውን ለማሳካት የሚጥሩት ወገኖቻችንም እንዳሉ ጭምር ሳይዘነጉ።

ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለማችን እያሽቆለቆለ እየሄደ ባለው ፍቅር ማጣትና መተሳሰብ  ምናልባትም ለጥቂት ገንዘብ ሲባል ወንድም ወንድሙን ለማጥፋት በሚያደባበት ሁኔታ፤ በገንዘብ የተነሳ ብዙ ቤተስቦች በተለያዩበት፣ አንዱ አንዱን ቀድሞ ለመክበር በሚደረገው ሩጫ ሥነ ምግባራዊ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ፈታኝ በሆነበት ሁናቴ በረቀቀ ወንጀልና ህገ ወጥ በሆነ ሥራ ውስጥ እየተሳተፈ ያለው የወገናችን ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ባለበት ደቡብ አፍሪካ ሊያውም የእናት ልጅ የማያደረገውን የጓደኛውን ህይወት ለማትረፍና ከስቃይ ለመገላገል ሲል አካልን/ኩላሊትን ያህል ነገር በነጻ አውጥቶ መስጠት ልብን በእጅጉ የሚነካ በጎ የፍቅር ተግባር ነው፤ አሁን ባለንበት ዓለም ይሄ የሚታሰብ አይደለም፣ የእናታችን ልጅ እንኳ ይሄን ያደረገዋል ለማለት የሚከብድ ይመስለኛል፣ እንደውም በሌላው ዓለም ሰዎች ኩላሊታቸውን በመሸጥ በብዙ መቶ ሺ ዶላሮች የሚንበሸበሹበትን የደራ የእንኩላሊት ገበያ የነገሰባትን ዓለማችንን ለሚታዘብ ይሄ ዓይነቱ ውለታ፣ የፍቅር መስዋእትነት እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል ወገኖቼ!?

በተሳካ ሁኔታና ደቡብ አፍሪካውያን በህክምናው ቴክኖሎጂ ልቀው በሄዱበት የልብና የኩላሊት የመቀየር (Heart and Kidney Transplantation) አስደናቂ ጥበብ የተከናወነው የዚህ ወገናችን ህይወት የተረፈበት ቀዶ ጥገና በእጅጉ የተሳካና ይሄ ህክምና የተደረገለት ወገናችንም በአስተማማኝ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የዚህ ወገናችን የንስኃ አባት የሆኑት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብና በምእራብ አፍሪካ ሀገር ስብከት የጆሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም ካቴድራል አስተዳዳሪ የሆኑት ቀሲስ አካሉ አድማሱ አጫውተውኛል፣ በተጨማሪም ከቀዶ ጥገናው በኃላ ለአንድ ዓመት መወሰድ ያለበትን በኢትዮጵያ ከ80000 ብር በላይ የሚፈጅ መድኃኒትና የህክምና ክትትል በነጻ እንዲያገኝ የጤንነቱን ሁኔታ የሚከታተለው የህክምና ተቋም እንደረዳውም ጭምር እኚህ አባት ነግረውኛል።

በዚህ መልኩ ለመላው ኢትዮጵያዊ እንዳስተላልፈው የንስኃ ልጃቸውን አስደናቂና ልብ የሚነካ ይሄን ታሪክ ያጫውቱኝን የጆሀንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም ካቴድራል አስተዳዳሪ የሆኑትን ቀሲስ አካሉን በራሴና በአንባቢያን ስም ላመሰግን እወዳለሁ። እንደዚሁም ለዚህ በጎ ለሆነ ሕይወትን የመታደግ የፍቅር መስዋእትነት ውድ አካሉን ሳይሰስት በመስጠት ታላቅ መስዋእትነት ለከፈለው ወንድማችን አድናቆትና ምስጋና ይገባዋል፣ ለዚህ መልካም የፍቅር ሥራ በምክራቸውና በጸሎታቸው አብረውት የነበሩት ባለቤቱ፣ የፒተርስበርግ ቅድስት ልደታ ለማርያም ጉባኤ ምእመናን፣ እና ጓደኞቹ ላደረጉት መልካምነት አድናቆት ይገባቸዋል። መጽሀፍ ወንድሞች ሆይ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ በማለት ይናገራል። [፩ዮሐ. ፫፥፲፩_፲፰]

አዎን ፍቅር የተግባር አንደበት አለው! የደከሙትን የሚያበረታበት፣ በተስፋ መቁረጥ ጽልመት ውስጥ ላሉ የጽድቅን ብርሃን የሚፈነጥቅበት፣ ፍቅር የተፈግመገሙትን የሚደግፍበት፣ የወደቁትን የሚያነሳበት፣ የቆሰሉ ልቦችን በፈውስ ዘይት የሚያክምበት፣ የተሰበሩትን የሚጥግንበት፣ ያዘኑትን የሚያጽናናበት፣ በሞት ጥላ ላሉ የሕይወትን መዓዛ ሽታ የሚያውድበት ፍቅር የተግባር የእውነት አንደበት አለው። በዚህ የጌታችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ታላቅ ጾም በምንጾምበት በሱባኤ ወራት እንዲህ ዓይነቱን የጌታችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ውለታ፦ ዘላላማዊ ምህረቱን፣ ቸርነቱን፣ ይቅርታውንና ፍቅሩን የሚያሳስብ፣ እንዲሁም የፍቅራችንና የበጎነታችን ብርሃን በዓለም ሁሉ ፊት የሚያበራበትን የፍቅርና የደግነት ሥራ መስራት እንድንችል የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን!!! ወገኖቼ ፍቅር የተግባር አንደበት አለው...!!!
ሠላም! ሻሎም!    


20 comments:

 1. ወንድሞች ሆይ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ

  ReplyDelete
 2. ኃ/ገብርኤል ከአራት ኪሎApril 7, 2011 at 5:03 PM

  ቃለ ሕይወትን ያሰማልን ወንድማችን።
  በእጅጉ የሚያስደንቅ ታሪክ ነው ያካፈልከን። እንዲህ ያለውን የፍቅር መስዋዕትነትን በተግባር የሚያስተምሩ ወገኖቻችንን ቅዱስ እግዚአብሔር በዕድሜና በጤና ይጠብቅልን። እንደዚህ ያሉ በጣት የሚቆጠሩ ልበ መልካሞችን አያሳጣን።

  ReplyDelete
 3. Touching story, GOD bless the person who volunteered to donate his kidney. I know GOD will replace him with much more wisdom and grace.

  For the person who has got the kidney donation, may GOD be with you always through out the full recovery.

  ReplyDelete
 4. እግዚያብሔር ቀሪ ዘመኑን ይባርክለት የሚያስደስት ፍቅር

  ReplyDelete
 5. Great article well written

  ReplyDelete
 6. እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን ያሉ በዚህ ዘመን ብዙዎች አሉ። የሰሩት ስራ ያልታወቀ ነገር ግን በእነርሱ እና በእግዚአብሔር ፊት የታወቀ::ይህም ወንድማችንም ከእነርሱ አንዱ ነው።

  ሰለ ሀበሻ ክፋት ምቀኝነት የጻፍከው ላይ...ይህንን ፅሁፍ የሚያነበው ምንም ስለ ሀበሻ ምንነት የማያውቅ ሰው ቢሆን እንዴት እንደሚጠላን ታየኝ...ባለፈው ሰለ አይን በተጻፈው ጽሁፍ ላይ ብዙ ቁም ነገሮችን አይግኝተናል "....በትልቅ ነጭ ሰሌዳ ላይ ጥቁር ነጥብ ብናይ ሙሉ ሰሌዳ ነጩን ከማየት ትንሿ ጥቁር ነጥብ አባብሰን ማየት እና ማጋነን እንወዳለን..." እና በተለይ በውጪው አለም ስለሀበሻ ከተነሳ አንድም እንኳን ጥሩ ነገር እንደሌለ ተደርጎ ለምን እንደሚወራ አይገባኝም።

  ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉ ብዙ ሰዎች ልክ ወንድማችን ያደረገውን አይነት ስንት ጥሩ ነገር የሰሩ አሉ። ሀበሻ ሁሉ መጥፎ አይደለም ሁሉም ጥሩም አደለም። በጣም ተጋኖ ሰለ ሀበሻ መጥፎነት ሲነገር ያሳዝነኛል። አንድ አባት 8 ልጆች ወልዶ ከስምንት ልጆች አንዱ ቢበላሽ ሁሉም ልጆች አብረው አይወቀሱም። ልክ እንደዛ ማለት ነው። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ በኬንያ ያለው አይነት ሌብነት እና ግልጽ የሆነ ዝርፊያ፣ቀማኝነት፣ግድያ፣ ከእኛ ዜጋ ጋር ሲወዳደር የሀበሻ ባህርይ ተመስገን ያስብላል። ይህ ልጅ ስላደረገው ነገር ሲነገር የሀብሻ ክፋት ሳይነሳ ስለ ጥሩ ኢትዮጵያውያን እየተነሳ የእርሱንም ጥሩነት ቢወሳለት የአባቶች ቅዱሳን ጥሩ ስራ እየተናገርክ የርሱንም ትልቅ ስራ ብትናገር። ንጽጽሩ ከመጥፎ አበሻ ጋር ባይሆን አልኩኝ።

  ReplyDelete
 7. ወንድሞች ሆይ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ. WOW can't say it any better, Amlakachin Hoy Teradan Be Fikir Endininor AMen

  ReplyDelete
 8. ewnetengafikir jerbaw lay menem medrawi tekim yelem menem!!
  betezewawari gen yagengewal.......
  enamesegnalen be fikr.

  ReplyDelete
 9. ሀበሻ ማነው? እናንተ ከኢትዮጵያ ውጭ ያላችሁ ብቻ ናችሁ? ኢትዮጵያዊስ ማነው? ከተማ ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ብቻ ነው? በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖረው ህዝብ እኮ አሁንም አብሮ እየበላ አብሮ እየሰራ ነው፡፡ “ደቦት” የሚባል አብሮ የመስራት ባህል እንዳለ አውቃለሁ፡፡ እረ በፈጠራችሁ አምላክ ሰድባችሁ ለሰዳቢ አትስጡን፡፡ በጣም በዛ ፡፡ ምነው ሀበሻ የሚወራ ጥሩ ነገር የለውም? ራሳችሁን ዋጋ እያሳጣችሁት እኮ ነው፡፡ እባካችሁ አንዳንዴ እንኳን ተሳስታችሁ ስለ ሀበሻ ጥሩ ነገር አውሩ እና ደስስስስ ይበለን፡፡

  ReplyDelete
 10. Since i work with those patient i understand how hard to get a kidney is.May God smooth their recovery.
  Dn Daniel i have a qustion about donation of body parts. i know saving someone's life is the best thing u can give. But some of my friends asked me if it is allowed in our church to be listed as a donor in your driving license & i do not have concrete answer for that.Please try to write some thing about it.

  ReplyDelete
 11. betam yemiyasdenek FEKER new!!! menm alalekum enes endezih aynet mesewaetenet ekefel yehon beye rasen teyekut .

  +++ወንድሞች ሆይ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ +++

  Qale hiwoten yasemalen !!!

  ReplyDelete
 12. ፍቅርተማርያምApril 11, 2011 at 2:08 PM

  እውነተኛ ፍቅር ማለት ይህ ነው፡፡
  ፍቅር የማያሸንፈው ነገር የለምና
  የአምላካችንን ፍቅር በውስጣችን ይዘን
  ለበጎ ነገር እንነሳ
  አምላክ ይርዳክ
  አሜን

  ReplyDelete
 13. ሀበሻው ማነው? ያልተብራራ ታሪክ.....

  ReplyDelete
 14. ወንድሞች ሆይ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ። [፩ዮሐ. ፫፥፲፩_፲፰]

  ReplyDelete
 15. እርሱ እውነተኛ ኣርበኛ ነው! ነጮቹ እንደሚሉት “Hero”. ፍቅር መስጠትን ሳይሆን መሠጠትን ይጠይቓልና!!
  ለኔ መሰል ብዙዎች ለማድነቅ እንጂ ሆነን ለመገኝት ጉልበትና ልብ ላጣን ምስኪኖች “ እገሌን ያየህ ወዲሀ በለው”
  እሚያሰኝ ነው!!
  አንተ ህይወት ሰጥተህ ህይወት የቀጠልክ ትፍ አልኩበህ፣ አንድዬ በዚህኛው በቻ ሳይሆን በዛኛውም አለም እንዲያኖርህ

  ፍቅር-አለም ከጆበርግ

  ReplyDelete
 16. ኤርምያስ/ሳንሆዜ/April 18, 2011 at 1:28 AM

  የፍቅር አምላክ ፍቅራችንን ያብዛልን! አስተማሪና አስገራሚ የፍቅር ተግባር ነው።

  ReplyDelete
 17. በተመሳሳይ መልኩ ለአንድ አላማ ከቆመን ተካክዶ አያ ክደቱ ሆነን ማስበላት እናቁም ፡፡ ይህ መፈራራት ነው እኮ መተባበር ያላስቻለን ፡፡ የ1969/70 የአንጃን ጠባሳ ያየ …. በፍቅር እንታገል፡፡
  ጓደኛውን ላለማስበላት ብሎ ራሱን የገደለም ነበር እኮ !!!

  ReplyDelete
 18. Let us be friendly to each other like our friends from RSA. But at least not be enemical

  ReplyDelete
 19. I have one question for Dkn. Daniel.
  I don't believe all Ethiopians are this bad (cruel, jelous, etc.).
  It is simply normal that some people are good and others are bad regardless of their origin.
  My question is what makes you think Ethiopians in general are jelous of each other. What about other nationalities? Europeans? Americans? Russians, Australians, name it. Just trying to be fair.

  ReplyDelete