Monday, April 4, 2011

የሶስት ሺ ዘመን ነጻነት ወይስ የሶስት ሺ ዘመን ... ???


በፍቅር ለይኩን  ከደቡብ አፍሪካ

ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል "ነጻነታችን ምን?" ብሎ ያነሳው አንገብጋቢ ርእሰ ጉዳይ ነጻነቱን የሚያፈቅር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊጠይቀው የሚገባ ጥያቄ ነው... በነጻነት መኖር፣ በነጻነት ማሰብ፣ በነጻነት መፈላሰፍ፣ በነጻነት መጻፍ እና መናገር እንችል ዘንድ የሶስት ሺ  ዘመን ነጻነታችን የፈየደልን ምንድን ነው... ይሄ በሚገባ ደግሞ ደጋግሞ መጠይቅ ያለበት ጥያቄ ነው ...


እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ ወገኖቼ... ግን በእውነት የነጻነታችን ዋጋው እምን ድረስ ነው? የነጻነታችንስ ክብር ከየት እስከየት ተብሎ ሊለካ ይችላል? በዓለም ፊት ደረታችንን ነፍተን የምንናገርለት ሌሎችም ጭምር የሚያስተጋቡልን፣ የአውሮፓውያኑን የቅኝ ገዢዎች ከንቱ ሩጫና ምኞት ያልገሰሰው የነጻነታችን ክብር በምን እንተምነዋለን? ይሄ በቀደሙ አባቶቻችን ክቡር ደምና አጥንት የዘመናትን ድልድይ ተሻግሮ ወደ እኛ የደረሰው ነጻነታችን ለእኛም ሆነ ለቀደመው ትውልድ ፋይዳው ምንድን ነው? ይሄ በቅኔያችን፣ በመዝሙራችን፣ በሥነ ጽሁፋችንና ኪነ ጥበባችን ብዙ ያልንለት፣ የተቀኘንለት፣ የዘመርንለት፣ ነጻነታችን ምን አተረፈልን... ምንስ አስገኘልን...? ይሄ ለራሳችን መልስ ልንሰጥበት የሚገባው የሁላችን ጥያቄ፣ የሁላችን የቤት ሥራ ነው... እኔ ግን በነጻነታችን ዙሪያ ትንሽ የተስማኝን ልበል.. 

የትናት የሺ ዘመናት አኩሪ ታሪክ፣ ነጻነት እና ሥልጣኔ ዳቦ አልሆነላችሁ እየተባልን ደግመው ደጋግመው ወዳጆጃችንም ጠላቶቻችንም የተሳለቁብብን አጋጣሚና ጊዜ በራካታዎች ናቸው. . . ትና የዳቦ ቅርጫት የተባልን፣ የነጻነትና የሥልጣኔ ምልክት የነበርን ኢትዮጵያውያን ዛሬ በነጋ ጠባ የልመና አቆፋዳችንን አንጠልጥለን ማንም ሳይቀድመን ለልመና የለጋሽ ሀገሮችን በር የምናኳኳ መሆናችን ጉዳይ በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች በውጭ ሀገራት የምንኖር ብዙዎቻችን አሸማቆን ከነጻነታችን ሰገነት በእፍረትና በቁጭት ወደ ታች አምዘግዝጎ እንድንወርድ ያደረገንን በርካታ አጋጣሚዎችን አላሳለፍንም እንዴ...!? እኛም በነጋ ጠባ የወዳጆቻችንም ሆነ የጠላቶቻችን ስድብና ውርጅብኝ የተነሳ፦ እውነት ነው! ኢትዮጵያ በሺ ዘመናት የሚቆጠር ነጻነትና ሥልጣኔ ያላት ሀገር ናት የሚለው ኩራታችን ወደ ምጸት ተቀይሮብን፤ ይሄ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስልጣኔ፣ ነጻነትና አኩሪ ታሪክ የተባለውና የሚባለው ሁሉ ጆሮአችንን እያሳከከን... ታዲያ ይሄ ነጻነታችን ዛሬ ምን አተረፈልን እያልን ያለፈውንና የቀደመውን ትውልድ የሞገትንበትንና የወቀስንበት ሁኔታ ከቀደመው ትውልድ ጋር አላኮራረፈንም ይሆን እንዴ...!? ዛሬስ ቢሆን እኛም ሆነ ትውልዳችንስ ከዚህ የመዋቀስና የመካሰስ አዙሪት ወጥተን፣ ወጥቶ ይሆን እንዴ...!?
ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል በጹሁፉ እንደጠየቀው፦ "ታዲያ ነጻ ህዝብ መሆኔ፣ [የሺ ዘመናት] ታሪክ፣ ባለ ቅርስ፣ [የራሴ]የሆነ ቋንቋ ባለቤት መሆኔ ልዩነቱ የቱ ላይ ነው። በነጻነት ማሰብ፣ በነጻነት መሥራት፣ በነጻነት መኖር፣ በነጻነት መፈላሰፍ ካልቻልኩ። ነጻነቴ ታሪክ ብቻ ነው ማለት ነው?" በማለት ያስተጋባው የውስጡ ጩኸት የሁላችንም የነፍስ እሪታ፣ የሁልጊዜ ጥያቄያችን ይመስለኛል፤ ወንድማችን ዳንኤል ጩኸታችንን ስለጮክልን፣ የዘመናት እንቆቅልሻችንን በማንሳት ዳግመኛ ራሳችንን እንድንጠይቅ ስላደረክን በአባቶቻችን ምርቃት "እራትና መብራት ይስጥልን!" ልልህ እወዳለሁ። ይሄን የዘመናት እንቆቅልሻችንን ያነሳው ጹሁፍህ በውስጤ በርካታ ጥያቄዎች ቢፈጥርብኝ ባነሳኸው የነጻነታችን ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ አንዳንድ ሐሳቦችን ከአንተና ከመጦመሪያ እድምተኞችህ ጋር በጨዋነት መንፈስ ውይይት ለማድረግ ብእሬን አነሳሁ።

ወንድማችን ዳንኤል ስለ ነጻነት ክቡርነትና ታላቅነት ያነሳኸው ሐሳብ ከዚህም ጋር በተለይ የሶስት ሺ ዘመናት ነጻነት እያልን የምናቆለጳጵሰውና የምንኮራበት ነጻነታችን ምን አስገኘልን? ብለህ ያነሳኸው ግዙፍ ጥያቄ የሁላችን ጥያቄ ይመስለኛል፤ በተለይም ሰለነጻነት ሲወራ ስለ ሀገሩ የረጅም ዘመናት ነጻነትና ተጋድሎ፤ ስለ ህዝቡ ኩራትና አይደፈሬነት፣ በሺ ዘመናት ሰለሚቆጠረው የሀገሩ ሉዓላዊነትና የስልጣኔ ታሪክ፣ ከህጻንነቱ ጀምሮ ሲተረክለት ላደገ ለእንደኔ ዓይነቱ ኢትዮጵያዊ የነጻነት ትርጓሜ፣ ታላቅነትና ጥልቅነት ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ነው። በተለይም ደግሞ የዚህ ጥልቅ የሆነው የነጻነት ትርጓሜና ክብር በዚህ የነጻ ትምህርት (Scholarship) እድል ባገኘሁባት በደቡብ አፍሪካ የዩኒቨርስቲ ቆይታዬ፤ ነጻነት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከቃላት ባለፈ አካል ገዝቶ ህያው ሆኖ የሚንቀሳቀስ እስኪመስለኝ ድረስ በአካል ተግንቼ ያየኍቸው የነጻነትን ክቡርነትና ውድነት የሚመሰክሩ የደቡብ አፍሪካውያን ጥቁር ህዝብ ህያው የነጻነት ተጋድሎ ታሪክና ቅርሶች፣ የነጻነትን ልዩ መንፈስ በፊደል ብቻ ሳይሆን ቃላት በቋንቋ ለመግለጽ እስኪሳናቸው ድረስ ትልቅ ምስልን በውስጤ የከስቱበትንየሀገሬን የረጅም ዘመናት የነጻነት ታሪክ እንዳስብ የተገደድኩበትን አጋጣሚዎች አልረሳቸውም።

የዛሬይቱ ደቡብ አፍሪካ ስለ ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ የምትለው የምታውጀው ብዙ ነገር አላት፤ በተለይም ደግሞ የዩኒቨርስቲ ቆይታዬ የደቡብ አፍሪካንና በአጠቃላይም የመላው ጥቁር ህዝቦችን የነጻነት ተጋድሎ፣ ፖለቲካ፣ ታሪክና ቅርስ ለማጥናት በወስድኳቸው ኮርሶች የተነሳ የዛሬው የ 92 ዓመት አዛውንት፣ የደቡብ አፍሪካ የነጻነት አባት፣ የጥቁር ህዝብ የነጻነት ዓርማ፤ የሰላም መልእክተኛ፣ የይቅርታና የፍቅር ተምሳሌት...ወዘተ ተብለው በሚሞካሹት የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ ለ 27 ዓመታት በእስር በቆዩበት በተባበሩት መንግስታት ድ/ት (UNESCO) ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ በተመዘገበው በሮቢን ደሴት በተደጋጋሚ ከዩኒቨርስቲው የክፍል ውስጥ ትምህርቴ ባሻገር ለመስክ ጥናትና ለጉብኝት በርካታ ቀናትንና ሌሊቶችን ማሳለፌ ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ለህዝባቸው ነጻነት በእንባቸው፣ በላባቸውና በደማቸው/በሕይወታቸው ጭምር የከፈሉት መስዋእትነት... ነጻነት ምን ያህል ክቡርና ውድ የሆነ የሰው ልጅ ክቡር ሀብት እንደሆነ በተግባር ለማረጋገጥ አስችሎኛል።

ወንድሞቻችን አፍሪካውያኑ ካለፉበት ጥቁሮችን በሙሉ ከእንሰሳ በታች ከሚመድበው፤ የጥቁር ዘር በሙሉ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ይሁን የኢኮኖሚ ተክለ ሰውነት የለውም የሚል እምነት ከነበረው የአፓርታይድ ሥርዓት ጋር የሞት ሽረት ትግል በተካሄደባት ደቡብ አፍሪካ፣ እጅግ ዘግናኝ የሆኑ የስብዓዊ መብት መደፈሮች፣ ኢሰብአዊ የሆኑ ስቃዮች፣ ሞትና እንግልት በጥቁር ሕዝቦች ላይ ደርሷል፤ ይሄን ታሪክ በጥቁር ማህደር የዘገበውን ዘግናኝ የታሪክ ጠባሳ በዚህ ጹሁፍ ለመዳሰስ የሚሞከር አይደለም፤ ግና የዚሁ የደቡብ አፍሪካውያን የነጻነት አኩሪ ተጋድሎ በሺ ዘመናት ከሚቆጠረው የሀገራችን ነጻነት ታሪክ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ታሪክ ስላለው ነው ላነሳው የወደድኩት፣ በተለይም ደግሞ የነጻነት ትግሉ በተፋፋመበት በ 1960ዎቹ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ማንዴላ Long Walk to Freedom በተባለው ተወዳጅ መጽሀፉ የሀገራችን የሺ ዘመናት የነጻነት ታሪክና ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ቆይታው በውስጡ የፈጠረበትን አፍሪካዊ ልዩ ስሜት የኢትዮጵያ ቆይታ ትዝታውን በመጽሐፉ እንዲህ ነበር የገለጸው፦

". . . we put dawn briefly in Khartoum, where we changed to an Ethiopian airways flight to Addis. Here I experienced a rather strange sensation. As I was boarding the plane I saw that the pilot was black. I hard never seen a black pilot before, and the instant I did I had to quell my panic. How could a black man fly a plane? But a moment later I caught myself: I had fallen into the Apartheid mind-set, thinking Africans were inferior and that flying was a white man job. I sat back in my seat, and chided myself for such thoughts. Once we were in the air, I lost my nervousness and studied the geography of Ethiopian, thinking how the guerrilla forces had hidden in these very forests to fight the Italian imperialists. "[1]

[2] በአንጻሩ ደግሞ የሺ ዘመናት የሥልጣኔ፣ የነጻነት ታሪክና ኩሩና አይደፈሬ የሆነ ሕዝብ ተባብሮ በሰላምና በአንድነት ይኖርባታል ብሎ በገመታት ኢትዮጵያ ያን ነጻነትና አኩሪ ታሪክ የሚዘክር ብሎም እንዲቀጥል የሚያደርግ የነጻነትና የዲሞክራሲ ተቋማት በኢትዮጵያ ቆይታው ለማየት ያልቻለው ማንዴላ ከሶስት ሺ ዘመን በኍላ ያገኛትን ኢትዮጵያን እንዲህ ነበር የገለጻት፦

“… Our first stop was Addis Ababa, the Imperial City, which did not live up to its title, for it was the opposite of grand, with only a few tarred streets, and more goats and sheep than cars. Apart from the Imperial Palace, the University and the Ras Hotel, where we stayed, there were few structures that could compare with even the least impressive buildings of Johannesburg. Contemporary Ethiopia was not a model when it came to democracy, either. There were no political parties, no popular organs of government, no separation of powers; only the [E]mperor, who was supreme.”[3]

እንግዲህ የሺ ዘመናት የነጻነት ታሪክ አላት ምትባለው ሀገራችን ከብዙ ዘመናት በኃላ እንኳን የህዝቦችን የአስተሳሰብ ነጻነትና መብት መከበር የሚያሳዩ እንጥፍጣፊ መረጃዎችና ለዚህም መብት የሚሟገቱ ተቋማት ያለመኖራቸውን እውነታ ነው ማንዴላ በአጭሩ የኢትዮጵያ ቆይታው የታዘበው፣ ምናልባትም ይሄ ያልጠበቁት እውነታ ለኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራቸውን ምስል በቆይታቸው በተግባር ካዩት ሐቅ ጋር ሳይጋጭባቸው እንዳልቀረ መገመት ይቻላል። የነጻነታችን ምስጢሩ በባእድ ያለመገዛታችን ብቻ ካልሆነ በቀር ለዘመናት በገዛ ዜጎቻችንን/ገዢዎቻችን መብታችን ተደፍጥጦ "የማሰብም ሆነ የመናገር መብት" ምን ማለት እንደሆነ እንኳን መገንዘብ ከማንችልበት ሁኔታ አቆልቁለን መገኘታችን አጉልቶ የሚያሳይን ሐቅ ላይ ስለመኖራችን ምስክር መቁጠር የሚያሻን አይመስለኝም።

እነዚህ የነጻነትን ውድና ክቡር እሴቶች በተግባር እንድናያቸውና ብሎም ተጠቃሚ እንድንሆንባቸውም የሚያስችሉ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ገና በሁለት እግራቸው ጸንተው ባልቆሙበትና እዚህንም የሚያፋጥኑ ሲስተምና ስትራክቸር በሌለበት ሁኔታ ወንድማችን ዳንኤል በጹሁፉ የተመኘልን:- በነጻነት ማሰብ፣ በነጻነት መናገር፣ መፈላሰፍና መስራት እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸው የግለሰብም ሆነ የቡድን የነጻነት መብትና እድገት ማውራት የምንችል አይምስለኝም፤ እናውራም ብንል ለዚህ የታደሉት ለሰቦች በጣም ጥቂቶቹ ወገኖቻችን ናቸው፤ 85% በላይ ህዝባችን ካለበት የጨለማ ህይወት አንጻር ዳኒ ያነሳቸው ከመዋቅርና ከተቋማት ማእቀፍ ወጥተን በነጻነት የማሰቡና እድገትን የመተለም መብቶች ገና በርቀት ያሉና በሰማይ ላይ የተንጠለጠሉ ሆነው ይሰሙኛል

በሀገራችን የዘመናዊ ትምህርት ጅማሮ አሃዱ ባለበት 1950ዎቹ እና ከዛም በኃላ በተነሱት ኢትዮጵያውያን ምሁራን የተነሳው ጥያቄም:- ኢትዮጵያን የነጻነትና የጀግንነት ሀገር እያሉ፣ ያለፈና የቆየ ሥልጣኔዋን እና ታሪኳን እየተረኩ፣ ነገር ግን ህዝቦቿ ያሉበትን ድቅድቅ የድንቁርናጨለማ እና ስልጣኔ አልባ ህይወት፣ የስብእናና የመብት መደፈር እንዳላዩ ሆኖ የሚታለፍበት ዘመን የሚያበቃበት ደወል በሀገራችን የመጀመሪያዎቹ ምሁራን ማስተጋባት የጀመሩት የእነዚህ ተቋማት ውልደትና ገት በረጅሙ የነጻነት ተጋድሎ ታሪካችን ያለመታየታቸው እውነታ በእጅጉ አስገርሟቸውና ትናት ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ነጻነታቸውን የተጎናጸፉ የአፍሪካ ሀገራት ካሉበት አንጻራዊ የስብዓዊ መብትና የነጻነት ሕይወት አንጻር እንኳን የእኛይቱ ኢትዮጵያ ከረጅም የነጻነትና የሥልጣኔ ታሪክ አንጻር በእጅጉ ወደኃላ መቅረታችን በእጅጉ አስግርሟቸውና አንግብግቧቸው ይመስለኛል።

"የኢትዮጵያ ህዝቦች ከረጅም፣ ውጣ ውረድ ከበዛው፣ ብዙ ችግር እና ፈተና ከሞላው ታሪካቸው፣ በእነዚህም ታሪኮች ውስጥ ካሳዩት ጀግንነት እና ከከፈሉት መስዋእትነት ጋር በማይመጥን የእውቀት እና የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ መገኘታቸው እጅግ የሚያንገበግበው ትውልድ መጣ። ይህ በአንድ በኩል በሀገሩ እና በህዝቡ ጀግንነት እና የነጻነት ፍቅር የሚኮራ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመብት፣ የፍትህ እና የብልጽግና ደሃ መሆኑ የሚያናድደው ትውልድ ግዙፍ የሆኑ በወቅቱ የዘውድ ሥረዓት ፈታኝ የሆኑ ጥያቄዎችን ያነሳ ትውልድ ለዘመናት "ንጉስ አይወቀስ ሰማይ አይታረስ" በሚል ባፈጀና ባረጀ አጉል እሳቤ ተቀፈድዶ የኖረውን የኢትዮጵያን ህዝብ ከተኛበት የቅዠት ሕይወት የሚያነቃ ለውጥ ፈላጊ ትውልድ ተነሳ..." [እንዳርጋቸው  ጽጌ]

የዚህን ለውጥ ናፋቂ ትውልድ መስዋእትነትና ለግለሰብም ሆነ ለቡድን ነጻነትና እድገት ያበረከ ታቸውንና ለስኬታቸውም የሄደባቸውን ጥልፍልፍ መንገዶች፣ ውጤቶቹንም ሆነ ውድቀቶቹን ለመግለጽና ለመተንተን ሳይሆን፤ የጹሁፌ ዓላማ በሀገራችን ታሪክ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ግንባታ እንዲሁም ለሰው ልጆች መብትና ነጻነት መከበር ድምጻቸውን ያሰሙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሺ ዘመናት ታሪካችን በነጻነት ማሰብ በነጻነት መናገርና መጻፍ መብቶች እንዲሁም ለእነዚህ መብቶች የሚሟገቱ ተቋማት ለምልክት ያህል ያለመኖራቸው እንቆቅልሽ ወደ ኃላ ተጉዘው ታሪካቸውን ለመፈትሽ የተገደዱበትን ሁኔታ ነው ሊፈጥር የቻለው።

ወደ ተነሳሁበት የጽሁፌ ማጠቃለያ ጭብጥ ስመለስ ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል ያነሳቸው በነጻነት ማሰብ በነጻነት መናገር በነጻነት መፈላሰፍና መስራት ከማውራታችን በፊት ወደዚህ የአስተሳሰብና የነጻነት ልእልና ሊያሻግሩን የሚችሉ ተቋማት ሊኖሩን ግድ የሚል ይመስለኛል፤ ይሄ እንደሰማይ በራቀበት ኢትዮጵያችን በእኔ አስተሳሰብ ወንድማችን ዳኒ ያነሳቸው በነጻነት አስቦ በነጻነት የመንቀሳቀስና የመስራት ወርቃማ እሳቤዎች እውን እንዲሆኑ ተጨማሪ መስዋእትነትና ረጅም ጉዞ የሚጠብቀን ይመስለኛል።

ወንድማችን ዳንኤል በጹሁፉ መዝጊያ ያነሳኸው ጥያቄ በእውነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊጠይቀው የሚገባ ጥያቄ ነው... "ታድያ ነጻ ሕዝብ መሆኔ፤ ባለ ታሪክ፣ ባለ ቅርስ፣ ባለ ቋንቋ መሆኔ ልዩነቱ የት ላይ ነው፡፡ በነጻነት ማሰብ፣ በነጻነት መሥራት፣ በነጻነት መኖር፣ በነጻነት መፈላሰፍ ካልቻልኩ፡፡ ነጻነቴ ታሪክ ብቻ ነው ማለት ነው?" ይሄን ሁላችንም በጥልቅ ልናስብበትና ልንጠይቀው የሚገባ የቤት ሥራችን ነው። እስቲ በዚህ ዙሪያ ሌሎችም ሐሳባችሁን አካፍሉን...
ሰላም! ሻሎም![1] Nelson Rolihlahla Mandela, Long Walk to Freedom, 1994, Great Britain, p. 347-348.
[2]  Ibid., p. 349.
[3]  Ibid.

2 comments: