ምክንያተ ጽሕፈት
ይህንን ጽሑፍ በዚህ ጊዜ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ ወዳጄ በዕውቀቱ ሥዩም ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ልዩ ልዩ አካላት የሚያቀርቧቸውን ሃሳቦች የሚተነትን አንድ ጥናታዊ ነገር እየሠራሁ ነበር፡፡ በመካከል ሐራሬ እያለሁ በዕውቀቱ «እግር አልባ ባለ ክንፍ» ብሎ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ አንድ ጽሑፍ አወጣ፡፡ የኛ ባህል ሃይማኖታዊ ሳይሆን ተክለ ሃይማኖታዊ ነው፤ ተክለ ሃይማኖታዊ ማለትም በሰማዩ ላይ ያለ ቅጥ በማንጋጠጥ ምድርን ማጣት፣ በዚህም ለድህነት መዳረግ ማለት ነው የሚል ነው ሃሳቡ፡፡
ይህ ጽሑፍ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ እና ማንነት የወቅቱ መወያያ እንዲሆን አደረገው፡፡ እኔም ይህንን እንዳዘጋጅ ምክንያት ሆነኝ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሌሎች አካላት የሚያነሷቸውን ሃሳቦችም ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ የበዕውቀቱን ሃብ ደግሞ ለብቻው፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ማናቸው?
አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ1186 ዓም በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ጽላልሽ ተወለዱ፡፡ አባታቸው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲያስተምሯቸው አካባበቢያቸው ደግሞ በዘመኑ የነበሩ ልጆች ይማሩ የነበረውን ፈረስ መጋለብን፣ ቀስት መወርወርን፣ እርሻን እና አደንን አስተምረዋቸዋል፡፡
በሰባት ዓመታቸው ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር በክህነት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መረጣቸው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ለክህነት መጠራት በዚህ ዓለም ትዳር መሥርቶ፣ የዓለሙንም ሥራ ሠርቶ መኖር አያስፈልግም ከሚል ፍልስፍና የመነጨ አይደለም፡፡ ከ8ኛው መክዘ ጀምሮ በሀገሪቱ የመንፈስ መቀዛቀዝ ይስተዋል ነበር፡፡ ዮዲት ጉዲት መንግሥቱን ይዛ በክርስትናው ላይ ከዘመተች በኋላ ሰሜኑ እና ደቡቡ ተቆራርጧል፡፡ የሃሳብን ልዕልና የሚያመጣው የመንፈስ ልዕልና ተዳክሟል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን የሚዋጅ ኢትዮጵያዊ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ነው የተክለ ሃይማኖት የጥሪ ምክንያት፡፡