Saturday, March 26, 2011

ያንተ እይታ


ኃይለ ገብርኤል ከአራት ኪሎ
ዺ/ን ዳንኤል ክብረት ሰላም ላንተ ይሁን።

ዲ/ን ዳንኤልየዳንኤል እይታዎች” በሚል ስያሜ የጡመራ መድረክ ከፍተህ እንደ ወንድም አሉላ አገላለፅ ‹‹ዛቲ ጦማር ትበጽሕ›› ብለህ ሥነ ጽሑፋዊ ምርትህን ‹‹ይድረስ ለኲሉ ዓለም›› ካልክ አነሆ አንድ ዓመት ሞላህ። ለባለቤትህ ለፅሉ ጌች እና ለዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ ምስጋና ይድረሳቸውና በአባቶች እግር ስር ቁጭ ብለህ የተከልከውና በንባብና ምርምር ያለመለምከው መልካም ተክል ፍሬው በዓለም እንዲበተንና የብዙዎችን ህይወት እንዲያጣፍጥ ሆነ። ዲ/ን ዳንኤል በዚህ የጡመራ መድረክ የምታቀርባቸውና እይታህን የሚያንፀባርቁት ስለ ሀገራችን ታሪክ፣ እምነት፣ ፖለቲካና ትውፊት የሚዳስሱት የብዕር ትሩፋቶችህ ብዙዎቻችንን ያስተማሩ፣ የመከሩና ራሳችንን ዞር ብለን እንድንፈትሽ ያደረጉ ናቸው። እንዲህ አይነቱ እይታ ሁላችንም ግንባር ላይ ካለው የስጋ እይን አይደለም። በውስጥ ካለውና በግብሩ እና በፍሬው እንጂ ፊት ለፊት በማየት ከማይታወቀው ከብሩህ ዓይነ ልቦና ነው። እግዚአብሔር አምላክ ጨምሮ፣ ጨምሮ፣ ጨምሮ ብሩህ ያድርግልህ።

በዚህ ባሳለፍነው የአንድ ዓመት እድሜ ውስጥ ከ 164 በላይ ፅሑፎች እጅግ በሚማርክና የአንባቢያንን ቀልብ በሚስብ  የአቀራረብ ስልት ቀርበዋል። ፅሑፎቹ እያንዳንዱ አንባቢ  ስለ ራሱ፣ ስለቤተሰቡ፣ ስለማኅበረሰቡ እንዲሁም ስለሀገሩ ያለውን የተዛባም ይሁን ቀና አመለካከት በግልፅ የሚያሳዩ መስታወቶች በመሆናቸው ተናፋቂም ነበሩ። ተደጋግመው ቢነበቡም የማይሰለቹ ስለሆኑም በተለይ እኔን የማጠቃለያ ፈተና (Final Exam) ላይ ይመጣል የተባልኩ ይመስል አያንዳንዱን ፅሑፍ እየከለስኩ እንዳነበው አድርጎኛል። ከዚህም በተጨማሪ የመጦመሪያ መድረኩ በተለያየ ቦታ ያሉ እኅቶችንና ወንድሞችን ያሉበት ቦታና ሆኔታ ሳይወስናቸው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በግልፅ እንዲወያዩና ሀሳብ እንዲለዋወጡ ከማድረጉም ባሻገር ሌሎች በአማርኛ የመጦመሪያ መድረኮች እንዲፈጠሩና ጠቃሚ ትምህርቶችን በአካል ለራቋቸው ወገኖች ባሉበት ሆነው እንዲያስተላልፉ  መነሳሳትን እንደፈጠረ ይሰማኛል። ለዚህም የመላከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን (የያሬድ ቤት)፣ የመላከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው (ቤተ ደጀኔ) እንዲሁም የ ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ (አደባባይ)  የጡመራ መድረኮች ለአስረጅነት ተጠቃሽ ናቸው።

በአጠቃላይ  በአንድ አመቱ  የጡመራ ሒደት ወስጥ የተገነዘብኳቸውን ቁም ነገሮች እንደሚከተለው ጨመቅ አድርጌ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ ያንተ እይታ  ወደፊትም ለብዙዎች መልካም አርዓያ እንደሚሆን እና ብዙ ወንድሞች እና እኅቶች የትውልድን እይታና አስተሳሰብ ሊቀይር የሚችል ሃሳብ እና ዕውቀት ሊያካፍሉ የሚችሉባቸው የጡመራ መድረኮች እንደሚፈጠሩ እምነቴ ነው። ስቀጥልም ያንተ እይታ ለእኔ ብቻ እና ለዛሬ ሳይሆን ለሁላችን እና ለነገ፣ ለተነገ ወዲያ ጭምር የህይወት ማጣፈጫና የመልካምነት ማበልፀግያ ነው። ያንተ እይታ ርግብን ከርግብ እንጂ ከእባብ እንቁላል እንዳንጠብቅ የሚያደርግ፣ ጠማማውን ጠማማ፣ ጎባጣውን ጎባጣ፣ ቀጥ ያለውንም ቀጥ ያለ እንጂ ጠማማውን ቀጥ ያለ፣ ጎባጣውን ደልዳላ፣ ቀጥ ያለውንም ጎባጣ እንዳንል የሚያደርግ የዓይን ብርሃን ገላጭ ነው።

 ያንተ እይታ እኛን ለሀገራችን፣ ለባህላችን፣ ለታሪካችን፣ ለሃይማኖታችን ያለንን የአስተሳሰብ አድማስ የሚያሰፋ ነው።

ያንተ እይታ  የሰው ትልቅነት መገለጫው አለባበሱ፣ አነጋገሩ፣ ፂሙ አልያም ሽበቱ ሳይሆን በጎ አሰተሳሰቡ፣ ቀና አመለካከቱ፣ አስተዋይነቱ፣ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ ማሰቡ፣ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለእናንተም ለእነርሱም ማለቱ፣ አሁን ላለዉ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድም መጨነቁ መሆኑን አስረግጦ የሚያስተምር ነው።

ያንተ እይታ  ሰዎች መልካም ነገርን ማየት ወይም ማግኘት ያለባቸው በሌሎች ተጋድሎ፣ በሌሎች መከራና ስቃይ፣ በሌሎች መስዋዕትነት ሳይሆን በገዛ ራሳቸው የችግሩ፣ የመከራው  ወይም የትግሉ ሙሉ ተዋናይነት መሆን እንዳለበትና እያንዳንዱ የራሱን ኃላፊነት ራሱ መወጣት እንደሚገባው የሚያሰስገነዝብ ነው።

ያንተ እይታ የምሁርነት መገለጫው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማስተማር፣ በንግግር መሃል እንግሊዝኛ ጣል ማድረግ፣ የምርቃት ሰርተፊኬትን ማብዛት፣ የምርቃት ፎቶን በፍሬም አድርጎ ግድግዳ ላይ መስቀል፣ ያልተማረውን የበታች አድርጎ ማየት፣ ለተማሪዎችን ከባድ ፈተና በማውጣት ማጨናነቅ፣ ከ 80 ተማሪዎች መሀከል ቆጥበህ ተጠቀም የተባለ ይመስል 3 A ብቻ መስጠት ሳይሆን የተማረውን ትምህርት በመጠቀም ለራሱ፣ ለቤተሰቡ፣ ለማኅበረሰቡ ብሎም ለሀገሩ አርዓያነት ያለው ስራ መስራት፣ ዛሬ እርሱ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ነገ እርሱ የደረሰበትና ከዚያም በላይ እንደሚደርሱ ጠንቅቆ ማወቅ፣ የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያቱ ከእነርሱ ዕውቀት ማነስ ብቻ ሳይሆን የእርሱም የማስተማር ችሎታ፣ የማጣቀሻ መፃሕፍቱ ይዘትና ብዛት፣ እርሱ ለሙያው ያለው ክብርም ጭምር ማሳያ መስታወት መሆኑን ማስተዋል  መሆኑን የሚገለፅ ነው።

ያንተ እይታ ባለስልጣን ማለት ራሱን ስዩመ እግዚአብሔር ብሎ የሚጠራ፣ ከጅብ ቆዳ እንደተሰራ ማሲንቆ እንብላው እንብላው የሚል፣ አንገቱን በክራቫት አንቆ የሚውል፣ መኪና የሚያቀያይር፣ ባለጉዳዮች ተሰልፈው እርሱ ቢሮውን ዘገቶ የኮምፒውተር ጌም የሚጫወት፣ ህሊናው በጉቦ፣ በዘር፣ በጎጥና በወንዝ ተሸብቦ ውሳኔዎቹ እውነትን የፊጥኝ ያሰሩ፣ ሀሰትንና አድልዎን ያነገሱ ሳይሆን ከተቀመጠበት ወንበር ጀርባ ትልቅ የህዝብ ኃላፊነት እንዳለ የሚያውቅ፣ ለእያንዳንዱ የሀሰትና የአድልዎ ስራ ነገ ተጠያቂ መሆኑን የሚገነዘብ፣ የተሸከመውን የህዝብ ኃላፊነት በታማኝነት የሚወጣ፣ እግዚአብሔር በዕድሜ ላይ ዕድሜ ጨምሮ የሰጠው በእንግድነት ዘመኑ  መልካም እንዲሰራ  እንጂ ሌሎችን እያሳዘነ እና አንገት እያስደፋ እንዲኖር እንዳልሆነ አውቆ በዚሁ መሰረትም ስልጣኑን በአግባቡ የሚጠቀም እንደሆነ አብዝቶ የሚመክር ነው።

ያንተ ዕይታ ሃብታም ማለት ድሃን እርሱ  እንደፈጠረው አድረጎ የሚቆጥር፣ ከማግኝት በኋላ ማጣት ያለ የማይመስለው፣ እርሱ ከበላ እና ከተመቸው ለሌላው ደንታ ቢስ የሚሆን፣ በገንዘቡ የሚመካና በገንዘቡ የፈለገውን ማድረግ የሚችል የሚመስለው ሳይሆን ሰውን በድህነቱ የማይንቅ፣ ገንዘቡ የራሱን የዕለት ተዕለት ኑሮውን ማሳለጫ እንጂ ቀን ጥሎት ዛሬን እየተቸገረ ነገን በተስፋ የሚጠብቀውን ወገኑን የበታች ራሱን የበላይ አድርጎ የሚያይበት እንዳልሆነ የሚያስተውል፣ በማጣቱ ምንም ቢጎዳ ምንም ቢጎሳቆል የራሱን ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን አክብሮና ጠብቆ ያለውን ድሃ ወገኑን የሚያከብር፣ ዕውቀትና ገንዘቡን በመጠቀም ድሃው ወገኑ ራሱን እንዲችል የሚረዳ፣ የዕለት ጉረስ ያጡትን የሚያበላ፣ የታረዙትን የሚያለብስ፣ የእርሱ ሕልውና እንዲጠበቅ የድሃው ወገኑ ሕልውና መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን የተረዳ ሰው መሆኑን የሚያስጠነቅቅ ነው።

ያንተ እይታ  የሃይማኖት አባት  ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግስት ዘንግቶና ሰማያዊውን ፀጋና ክብር ከምድራዊና ኃላፊ ከሆነ ብልጭልጭ ኮተት ጋር የቀላቀለ፣ መንጋውን በመጠበቅ ፋንታ የተገላቢጦሽ በመንጋው የሚጠበቅ፣ ተኩላን የበግ ለምድ አልብሶ ከመንጋው ጋር የሚያሰማራ ሳይሆን “እኔ በየትም ቦታ፤ በማንኛውም ጊዜ የምወክለው ሃይማኖቴንና ምእመናንን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ወኪል የመሆን ተልዕኮ የለኝም፤ እንዲኖረኝም አልፈልግም፡፡”  በማለት የተሰጣቸውን ሰማያዊ ፀጋና ኃላፊነት በምድራዊ ነገር ሳይበረዙ ከዘርና ከፖለቲካ ራሳቸውን አፅድተው ለመንጋው የሚያስቡ፣ በተሰጣቸው ፀጋ በንፅህና እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ፣ ለመንፈስ ልጆቻቸው መንፈሳዊ አርዓያ የሚሆኑ፣ ለሃይማኖታቸው ፍፁም ታማኝና ለቤተ ክርስትያን ህግና ስርዓት ተቆርቋሪ ማለት እንደሆነ አጉልቶ የሚያሳይ የእምነት መነፅር ነው።

ያንተ እይታ  ሀገርን መውደድ ማለት ኢትዮጵያዊ መባል፣ ጋራ ሸንተረሩን ሜዳና ገደሉን ማድነቅ፣ ለወንዙ ለተራራው ዘወትር መቀኘት፣ ጥንት አባቶቻችን እንዲህና እንዲያ አደረጉ እያሉ መኩራራት፣ የራሳችን ፊደል የራሳችን ቁጥር የራሳችን የዘመን አቆጣጠር አለን እያሉ መኮፈስ ሳይሆን ለእያንዳንዱ ዜጋ ክብር መስጠት፣ በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤት ተኮር ስራን መስራት፣ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት፣ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ፀጋ ውስጣዊ ውበት ማውጣትና ጥቅም ላይ ማዋል፣ ጥንት አባቶቻችን የህይወት ዋጋ የከፈሉበትን ሉዓላዊነት በእጅ አዙር ሳያረክሱና ከፉከራ ባለፈ ስማቸውን ከመቃብር በላይ ሊያውል የሚችል ስራን ለመስራት ሌት ተቀን መትጋት . . . ወዘተ መሆኑን  ልብ ያለው ልብ ይበል የሚል ነው።
ያነተ እይታ . . . . . . .

እግዚአብሔር አምላክ ረዥም ዕድሜን ከሙሉ ጤና ጋር ከነ ሙሉ ቤተሰብህ ይስጥልን በቀጣዩ ጊዜም እንደ እግዚአብሔር አምላክ መልካም ፈቃድ ብዙ አይተህ ብዙ ታሳየናለህ።

እንኳን ለአንደኛ ዓመት  ዝክረ ‹‹የዳንኤል ዕይታዎች››አደረሰህ፡፡

ቸር ያሰማን።

7 comments:

 1. ዳቆን ዳንኤል በጣም እናመሰግናለን እ/ር ከአንተጋር ነውና በርታ

  ReplyDelete
 2. Amen! wendeme bemigerem eyeta new yayehew Egeziabebeher antenem abezeto yebarakehe leke endante hulachenenem astewaye yaderegen!!!

  ReplyDelete
 3. you perceive good from Daniels view I also the one that appreciate & trying to implement in my practical life.Amlake Kidskin Anbeben Yemintekem yadergen.

  ReplyDelete
 4. ውድ ወንድሜ ኃይለ ገብርኤል! ለዲ/ን ዳንኤል ክብረት የጡመራ መድረክ የሰጠኸው አስተያየት እጅግ የሚደነቅ እና የሚያስደስት ነው። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከዚህ ብሎግ ያገኘናቸውን ጥቅሞች እኔ በቃሌ መግለጽ ያልቻልኩትን አንተ በጥሩ አማርኛ ገልጸኸዋል። እግዚአብሔር ይስጥህ!

  ReplyDelete
 5. Amen Qale hiwoten yasemalen !!!!!!! EGZIABHER TSEGAWEN YABEZALEH wendemachen hayle GEBEREL endet aderege bemigeba agelalt endegeletekew ye Wendemachenen D.Daniel ye teufochun hasb .

  Melekam andegega amet lulachenem le anebabeyan yeuenelehn beketayem anebeben tetekamiwoch endenehon EGZIABHER yeredan Amen !!!!!!!!

  ReplyDelete
 6. ግሩም ምልከታ ከማለት በላይ ነው፡፡ 164 ጽሑፎችን በአንድ ገጽ አጠቃልሎ በዚህ መልክ አንድ ዓመትን መከለስ እጅግ ከባድ ይመስለኛል፡፡ ኃይለ ገብርኤል አሉህ? እውነትም ኃይለኛ፡፡ በበኩሌ በጣም ነው ያመሰገንኩህ፡፡

  ለመሆኑ ይህን ጡመራ በአገር ውስጥ ካለው ዜጋ ምን ያህሉ ያውቀዋል? እኔን የሚያሳስበኝ የዘወትር ጥያቄ ነው? ይህንን ብርዶ በእጅጉ ሊበላ የሚገባው የአገሬው ነዋሪ ነው፡፡ እምነት፣ ግብረ ገብነት(ሥነ ዜጋ)፣ የፖለቲካ ተጠያቂነት፣ የቢሮክራሲ ትብታብና ያስከተለው ጥፋት፣ የከሠረ ባሕል በከበረው ላይ የሚያደርገው ወረራ፣ የዜጎች የፈጠራ ክህሎትና የልማት ወሳኝነት እነዚህ ሁሉ ልዩነት ሳያደርጉ የሚሰበኩበት ዓውደ ምሕረት ነው፡፡ ታዲያ ይህን አደባባይ መንግሥትስ ቢሆን ቢቀር ቢቀር ለጸረ ሙስና ትግሉ ቢጠቀምበት መልካም ዜጋ ለማፍራት ቢያስተምርበት ምን ክፋት አለው?

  በእውነቱ ጡመራው የቀረው ነገር ቢኖር ከኢትዮጵያም ሆነ ከየአህጉራቱ የሚገባውን ታዳሚ በቁጥር የሚያስቀምጥ፤ እልፎም በአንድ ጊዜ በኦን ላይ የተገኘውን የሚያሳይ መረጃ ሰጪ ሶፍትዌር መጠቀም አለመቻሉ ነው፡፡

  ይህም ቢታሰብበት እላለሁ፡፡

  መልካም አዲስ ዓመት ለጡመራህ

  ReplyDelete
 7. ዲ.ን ዳንኤል እንኩዋን አደረሰህ! በሆነው ነገር ሁሉ ልገልጸው የማልችለዉ ደስታ ተሰምቶኛል አብሮህ የተሰማራዉን እግዚአብሄርንም አመስግኛልሁ:: እኔ ለዚያ ነዉ ብዬ አምናለሁ ከዘራኸው ሁሉ ጋር የሰማይ አምላክ አብሮህ ስላለ ነዉ መከርህ የበዛው! እንዲያ ባይሆን ኖሮማ ስንቶች ተሰልፈዉ ነበር:: በ እርግጥ አንተ ትክክለኛ ቦታህ ላይ ያለህ ትክክለኛ ሰዉ ነህ አንዳንዴ ቦታን ማወቅ የስኬት መጀመሪያው ነው::ከ አምላክህ ቀጥሎ ከሁዋላህ ያሉ ሰዎች ወሳኞች ናቸው ለዚህም ባለቤትህ ቀዳሚዋ ናት ለእሱዋም ምስጋናዬ ይድረሳት::
  በርታልን ወንድማችን ድንግል አብራህ ትሁን::

  ReplyDelete