Wednesday, March 30, 2011

ዝክረ የዳንኤል እይታዎች

ኃይለ ገብርኤል ከአራት ኪሎ
የተከበራችሁ እኅቶችና ወንድሞች እንደምን አላችሁ? ሰላመ ልዑል እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።

ሁላችሁም እንደምታውቁት መጋቢት 18 የዳንኤል እይታዎች የተጀመረበት አንደኛ ዓመት በአኽሱም ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከብሯል። በለቻለ መጠንም ዝግጅቱን በቀጥታ ለማስተላለፍ ተሞክሯል። ይሁን እንጂ በኢንተርኔት መቆራረጥና በስራ ምክንያት ፕሮገራሙን ላልተከታተላችሁት ሁሉ በዝክረ የዳንኤል እይታዎች በዓል ላይ የነበረው ዝግጅት ምን ይመስል ነበር? የሚለውንና በዝግጅቱ ላይም ያየሁትንና የታዘብኩትን እስኪ ከብዙ በጥቂቱ አጠር አድርጌ ላካፍላችሁ፡

እንደ ወላድ ማታ ማታ ስንት ቀን ቀረው እያልኩ ሳሰላው የነበረው  በዓል እነሆ ወር ወርን፣ ሳምንት ሳምንትን፣ ቀንም ቀንን፣ ሰዓት ደቂቃ እና ሰከንድም እንዲሁ እርስ በረሳቸው እየተተካኩ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብኖር እካፈለዋለው ያልኩት መረሃ ግብር ሊካሔድ የ 30 ደቂቃ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ። አራት ኪሎ ላይ ሆኜ ወደ የክብረ በዓሉ ቦታ (አኸሱም ሆቴል) ለመሔድ የ 22 ትን ታክሲ እየተጠባበኩኝ ነው። 

22፣ ውሃ ልማት እያሉ የሚጣሩ የታክሲ ረዳቶች ድምፃቸው ጠፋብኝ አሁንም አሁንም ሰዓቴን እመለከታለሁ። እንደ አጋጣሚ አንድ ታክሲ መጣ ነገር ግን ረዳቱ “22” ብሎ ከአፉ ሳይጨርስ ታክሲው ሞላ። ሌላ መጠበቅ ግድ ሆነብኝ ሰዓቴን ተመለከትኩኝ 7፡15 ይላል። ኮንትራት ታክሲ ለመያዝ ሳስብ አንድ ሌላ ታክሲ ሲመጣ እንደምንም ተጋፍቼ ገባሁ፤ ተመስገን አልኩ። 

ደግነቱ ታክሲው ቶሎ ስለሞላ ወዲያው ተንቀሳቀሰ። ኡራኤል ስንደረስ መብራት አስቆመን ሰዓቴን ተመለከትኩ 7፡25 ። መብራቱ ሲለቀን ታክሲውን እኔ አለመያዜ እንጂ እንዴት እንደማፈጥነው አውቅ ነበር ደግነቱ የታክሲው መሪ ያለው በሾፌሩ እጅ ነው። አኽሱም ሆቴል ስደርስ 7፡29 ሆኗል ታዳሚዎች ገና እየገቡ መሆናቸውን ስመለከት ተረጋጋሁና ፍተሻውን አልፌ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ። የማየውን ታዩ የምሰማውንም ትሰሙ ዘንድ አብራችሁኝ ዝለቁ።

ከፊቴ ያሉትን ታዳሚዎች ተከትዬ አዳራሹ ወዳለበት ፎቅ ስወጣ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ብሮሸር ተመለከትኩኝ፤ ትልቅ፣ በደማቅ ቀለማት ያሸበረቀና የሚያምር ብሮሸር ቆም ብዬ አነበብኩት። ቆሜ ማንበቤ ግራ ገብቶኝ አንጂ አየተራመድኩ ማንበቡ ተስኖኝ አልነበረም። አንድም የሌላ ዝግጅት ብሮሸር ስለመሰለኝ አንድም ደግሞ ዝግጅቱ ከጠበኩት በላይ መሆኑን ወስጤ እየነገረኝ ስለነበር ነው። 

በአዳራሹ መግቢያ ላይ ሁለት ወጣቶች የስም ዝርዝር የያዙ ወረቀቶችን ይዘው ለመግቢያ የተሰጠንን ቁጥር አየጠየቁ በስማችን አጠገብ ምልክት እያደረጉ ሲያሳልፉን በመግቢያው በር በስተ ገራ ባለው ኮሪደር ላይ ሆኖ ቪዲዮ የሚቀርፅን አንድ ወጣት ተመለከትኩ የውስጤ ጥርጣሬ እየጨመረ ሄደ። ወደ ውስጥ ስገባ መታተሙን በ መጦመሪያ መድረኩ ላይ ያየሁት መፅሓፍ(ጠጠሮቹ እና ሌሎችም)፣ የሁለቱ ሓውልቶች ወግ መፅሓፍ፣ የዕለቱን መርሃ ግብር የያዘ ወረቀት እንዲሁም ዕለቱን በማስመልከት የተዘጋጀ በራሪ ወረቀት በበሩ በስተ ግራ በኩል ከሁለት እኅቶች ፊት ለፊት ተቀምጧል። ቆመው በሚያስናግዱ ወንድሞች አማካኝነት የመርሃ ግብሩን ወረቀትና በራሪ ወረቀቷን አንስቼ አዲሱንም መፅሓፍ ይዤ ቦታዬን ያዝኩና ዙርያ ገባውን መቃኘት ጀመርኩ።

ውጪ ላይ ያየሁት ብሮሸር በአዳራሹ ውስጥም ፊት ለፊት ባለው መድረክ ከላይ በኩል ተሰቅሎ ለመድረኩ ልዩ ግርማ ሞገስን አጎናፅፎታል። በብሮሸሩ ላይ በመጦመሪያው መድረክ ላይ ከወጡት ውስጥ አንዳንድ የተመረጡ ፀሑፎች በተለያዩ ቀለማትና ቅርፆች ታትመዋል። በመድረኩ ፍት ለፊት ላይ የካሜራ በለሙያዎች ካሜራዎቻቸውን ያስተካክላሉ። በግራ እና በቀኝ ደግሞ ኮምፒውተሮች ላይ ስራዎችን የሚያከናውኑ ወጣቶችን ተመለከትኩ። 

መድረኩ ላይ ሆነው እነ ኤልያስ የዋሽንት፣ የክራርና የማሲንቆ ቅኝታቸውን ያስተካክላሉ። ዲያቆን ምንዳዬ ብርሃኑ፣ አሉላ ጥላሁን እና ሌሎች በስም የማላውቃቸው ወንድሞች ከግራ ወደ ቀኝ ከላይ ወደ ታች ይላሉ። በአዳራሹ ውስጥ ካሉት መቀመጫዎች ውስጥ በሰው ያልተያዙት ለዓይን እያነሱ ነው። ዞር ብዬ ታዳሚውን ብቃኘው ከጥቂት በጣት ከሚቆጠሩት ውጪ ሁሉም ወጣቶች ናቸው። ልብ በሉ እስከ አሁን ድረስ የዝግጅቱ ምክንያት የሆነውን ዲያቆን  ዳንኤልን አላየሁትም። እርሱ በሌለበት ይሆን እንዴ በዓሉ የሚካሔደው? ውስጤ የተፈጠረ ጥያቄ ነበር። ለጥያቄዬ መልስ ሳልሰጥ ቀና ብዬ ከመድረኩ በስተ ግራ በኩል ካሉትና ዝግጅቱን በቀጥታ በመላው ዓለም ላሉት ወንድሞች እና እኅቶች ለማስተላለፍ ከላፕ ቶፕ ኮምፒውተሮች ጋር ከሚታገሉት መካከል ፈለኩት አገኘሁትም።

ዲያቆን ዳንኤል ከባለቤቱ ከፅላት ጌታቸው ጋር ሙሉ ነጭ በነጭ ለብሰው እንዴት አምሮባቸዋል መሰላችሁ። የበኩር ልጃቸውን ለመዳር ሁሉን አዘጋጅተው የሙሽራውን መምጣት ብቻ የሚጠባበቁ እናት እና አባት ይመስላሉ። እሱ ዝግጅቱን በቀጥታ ለማሰተላለፍ ከሚታገሉት ጋር አብሮ ሲታገል ፅሉ ደግሞ ግራ እና ቀኝ እያለች ሌሎችን እያስተባበረች እንግዶችን ትቀበላለች። እንዲህ ነው ባልና ሚስት አልኩኝ በሆዴ። 

ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች የሚባለውም በጭንቅላቴ አንቃጨለ። አሁንም ዓይኔ አላረፈም ወዲህ ወዲያ ስቃኝ ነጭ በነጭ የለበሱ ሶስት ወንዶች ልጆችን ተመለከትኩኝ (በኋላ ላይ የዳኒ እና የፅሉ የእግዚአብሔር ስጦታዎች መሆናቸውን ተነገሮናል) እነሱም ግራ እና ቀኝ አንዳንዴም በታዳሚው መካከል እየተመላለሱ በአቅማችን ለበዓሉ ድምቀት የበኩላችንን እንወጣለን የሚሉ ይመስላሉ።

በመርሐ ግብሩ መሰረት ከ7፡30 – 8፡00 ሰዓት ድረስ የእንግዶች መቀበያ እና የበዓሉ ታዳሚዎች ምዝገባ በመሆኑ ይህ እየተከናወነ ነው። እነ ኤልያስም ከመድረክ ላይ ሆነው ቅኝታቸውን ካስተካከሉ በኋላ የዲያቆን እንግዳወርቅ በቀለን ምስጉን ነው የተመሰገነ የሚለውን መዝሙር በመሳሪያ ብቻ(በዋሽንት፣ ክራር እና ማሲንቆ) ለስለስ አድርገው ለታዳሚው ማሰማት ጀመሩ ቀጥለውም እንድ ሌላ ቆየት ያለ መዝሙር አከሉበት። ልክ 8፡00 ሰዓት ሲሆን ኢዮብ ሥዩም መነጋገሪያውን ይዞ ወደ መድረክ ብቅ አለና እድምተኞችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካለ በኋላ የዕለቱን መረሐ ግብር በመድረክ ላይ ሆነው የሚመሩት የሸገር  FM 102.1 ጋዜጠኛ አንዱዓለም ተስፋዬ እና የአዲስ አድማሷ ጽዮን መሆናቸውን ገለፆ ስለ ሁለቱም በለሙያዎች አጠር ያለ ማብራርያ ከሰጠ በኋላ ሁለቱንም ወደ መድረክ ጋበዘ።

የመድረክ መሪዎቹም ቦታቸውን ከያዙ በኋላ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው በአዳራሹ ለተሰበሰበው እድምተኛ ሰላምታ፤ ለዲያቆን ዳንኤል ደግሞ ምስጋናን አቅርበው ስራቸውን አንድ ብለው ጀመሩ።  በዕለቱ ለመሰባሰባችን ምክንያት የሆነውን የወንድም ዳንኤልን ማንነት እንደው ለመግቢያ ያክል ዓባይን በጭልፋ እንዲሉ እየተቀባበሉ ነካ ነካ አደረጉት ጊዜ ለመቆጠብ ብለው እንደሆነ እገምታለሁ። 

በገለፃቸው ወቅት ዲያቆን ዳንኤል ፅሑፍን የጀመረው ገና 4ኛ ክፍል የሚማር የ10 ዓመት ብላቴና እያለ እንደሆነ በወቅቱም በመድረክ ላይ ያቀረበው ግጥም መሆኑንና ባቀረበው ግጥምም ምክንያት ምናልባትም ለቀጣይ አካሔዱ መነሳሳትን የፈጠረለትን ሽልማት እንዳገኘ ነገሩንና አስደመሙን። እኔ ግን የ 10 ዓመት ልጅ እያለ ግጥሙን አቀረበ እንጂ መፃፍ የጀመረው ከዚያ በፊት ምናልባትም የ7 እና የ8 ዓመት ልጅ እያለ ሳይሆን እንደማይቀር በውስጤ አሰብኩኝ። 

አንዱዓለምና ፅዮን ቀጥለውም ስለ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ እንዲሁም በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተማሪ እያለ ለመድረክ ያበቃቸውን የስነ-ፅሑፍ ስራዎቹን እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስለነበረው የትምህርት ቆይታ አጠር አጠር አድርገው ገለፁልን። ቀጥለውም በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች መስራቱን፣ በስሙ ከ13 በላይ መፃህፍት እና ሁለት መፃህፍትን ደግሞ ከሌሎች ጋር በመሆን  ለህትመት እንዳበቃ ለታዳሚው በንባብ አሰሙ። በማስከተልም የአጫብር ወረብ በመሰረታዊ የቅዱስ ያሬድ ዜማ በዘመናችን ዘማርያን ለታዳሚው እንዲቀርብ ዘማርያኑን ወደ መድረክ ጋበዙ። ዘማርያኑም በመቋሚያ ብቻ በመጠቀም ወረቡን ለታዳሚው ህሊናን በሚመስጥ መልኩ አቀረቡልን እኛም ዝማሬ መላዕክትን ያሰማልን አልን።

በመርሓ ግብሩ መሰረት ቀጥሎ ያለው የትረካ ክፍለ ጊዜ ስለነበር አንዱዓለምና ፅዮን ከዳንኤል ስራዎች መካከል በየተራ አንድ አንድ ፅሑፎችን እንደሚያቀርቡልን ገልፀውልን ወደዚያው አመሩ። የመጀመሪያውን ትረካ የተረከልን አንዱዓለም ነበር። አንዱዓለም በሸገር FM 102.1  የተለያዩ ፕሮገራሞችን የሚያቀርብ ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነው። በተለይ የአዘቦት ተረግ በሚለው ፕሮግራም ላይ በሚተርካቸው ትረካዎች ይታወቃል። ይኸው ጋዜጠኛ 171ኛው ሆስፒታል የሚለውን  ፅሑፍ ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ ተረከልን።

ምንም እንኳን ፅሑፉን አስቀድሜ ያነበብኩት ቢሆንም እንደ አዲስ ነበር ትረካውን ስከታተለው የነበረው። አነዱዓለም እንደጨረሰም ፅዮን የተራኪነቱን ተራ ተቀበለችና የኔ ጀግና እሷ ናት የሚለውን ፅሑፍ በኤልያስ ዋሽንት አጃቢነት በጥሩ ሁኔታ ተረከችልን። እኔ ለዚህ ፅሑፍ በተለይ ልዩ ስሜት አለኝ። ገና በብሎጉ ላይ እንደወጣ ሁል ጊዜ እንደማደርገው ኮፒ አድረጌ ወደ pdf ቀይሬ በተለያየ ቦታ ላሉ ወዳጆቼ እመይልላቸዋለሁ። ከወዳጆቼ መካከል ታዲያ አንዱ ምን እንዳለኝ ታውቃላቸሁ? ዳንኤል እኔ ሳልነግረው እንዴት የእኔንና የቤተሰቦቼን ሕይወት አወቀው? በፅሑፉ ላይ ያለው ያ ሰው እኔ ነኝ ነበር ያለኝ እንባ እየተናነቀው። ለዚህም ይመስለኛል ለፅሑፉ ልዩ ስሜት አለኝ። በተለይ ፅዮን በሴትነት ቅላፄ ስትተርከው ተጨማሪ ውበት ፈጠረችለት።

ቀጣዩን ጊዜ የወሰደው ደግሞ ዲያቆን ዳንኤል የመጦመርያ መድረክ ከፍቶ ላለፈው አንድ ዓመት ለመድረኩ እድምተኞች ሲያቀርባቸው በነበሩት ፅሑፎች ላይ ከተለያዩ ቦታዎች በመጡ አምስት ምሁራን አስተያየት መስጠት ነበር። ለዚሁ ጉዳይም ጥሪ የተደረገላቸው አምስቱ ምሁራን በመድረክ መሪዎቹ ግብዣ ወደ መድረክ ወጡ። ስለ ምሁራኑም መጠነኛ ገለፃ ተደረገልን በመድረክ መሪዎቹ።

በማስከተልም ምሁራኑ የፅሑፎቹን ይዘት፣ የአፃፃፍ ዘይቤ እና በአጠቃላይ ፅሑፎችን በተመለከተ በተለያየ አቅጣጫ ከስነ-ፅሑፍ መሰረታዊ ሃሳብ ጋር በማነፃፀር ለአስረጂነትም አንዳንድ የዳንኤል ፅሁፎችን እየጠቃቀሱ የየራሳቸውን ትንታኔ ለታዳሚው እያዋዙ አቀረቡ። በተለይ እኔ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ በመሆኔ የምሁራኑ ንግግር ሁሉ ለኔ አዲስ በመሆኑ በተመስጦ ነበር የምከታተላቸው። በምሁራኑ የተሰጡትን ትንታኔዎች ዳንኤል ራሱ ይመለስበታል ለእኔ ግን ከአቅሜ በላይ በመሆኑ አሱን አልነካካም።

ይህንን የምሁራኑን አካዳሚያዊ ትንታኔ ተከትሎ በአዳራሹ ካለው ታዳሚ በምሁራኑ ሃሳብ ላይ እና በዳንኤል እይታዎች ዙርያ አስተያየቶች ወደ መድረኩ መፍሰስ ጀመሩ። በመጀመሪያ አንድ አንድ ሆኖ ይታይ የነበረው የታዳሚው እጅ ወዲያው ለመድረኩ መሪዎች ዕድል ለመስጠት  እስከሚያስቸግር ድረስ ጨፈቃ መሰለ። ቢቸግራቸው ለሴቶች እድሉን እንስጥ እያሉ ባስ ሲልባቸውም ቅድም ከፊት ለፊት ላሉ ዕድሉን ሰጥተናል አሁን ደግሞ ከመሃል ሲቀጥሉም ከኋላ እያሉ ሃሳቦችን ተቀበሉ። እኔን ጨምሮ ብዙዎች ግን ዕድሉን ሳናገኝ ቀረን። ምሁራኑ ከታዳሚው ለተነሱ አንዳንድ አስተያየቶች ማብራርያ ሰጡና ጊዜ ገድቧቸው ከመድረክ ወረዱ።

ከዚያም በመድረኩ መሪዎች ግብዣ ዲያቆን ዳንኤል ወደ መድረክ መጣ የፕሮገራሙ ታዳሚዎችም ሞቅ ባለ ጭብጨባ ተቀበልነው። መነጋገሪያውንም እንደጨበጠ ጥሪውን አክብረው ለመጡት እንግዶችና ታዳሚዎች አክብሮቱን ከገለፀ እና ልባዊ ምስጋናውን ካቀረበ በኋላ የዕለቱ ዝግጅት ባማረ መልኩ ያዘጋጁትን፣ የፕሮገራሙን ሙሉ ወጪ የሸፈኑትን በኖርዌይ የሚኖሩ ሁለት አባቶችን አባ ቴዎድሮስ አካሉ ከስታቫንገር እና አባ አብርሃም ከኦስሎ፣ በብሎጉ ላይ ለሚወጡት ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጥራት ማማር የአንበሳውን ድርሻ ለወሰዱት ላሰቬጋሶች፣ በተለያዩ የዓለማችን ሀገሮች ሆነው የሱን ፅሑፎች የሚከታተሉና በስልክና በ ኢ-ሜይል ገንቢ አስተያየታችውን ለለገሱትሁሉ እና በዕለቱም በፐሮገራሙ ላይ ለተገኘነው ሁሉ በታላቅ ትህትና አመስግኖ እኔ አቅም የለኝም ነገር ግን ሁሉን ያደርግ ዘንድ የሚቻለው ልዑል እግዚአብሔር እርሱ ብድራታችሁን ይክፈላችሁ በማለት መርቋል። በተለይ የዝግጅቱን ሙሉ ወጪ ለሸፈኑት ሁለቱ አባቶችና ለላሰቬጋሶች መላው ታዳሚ ያለውን አክብሮትና አድናቆት ሞቅ ባለ ጭብጨባ ገልጿል።

ቀጥሎም ባለቤቱ ፅሉ የዕለቱ ዝግጅት እንዲሳካ ላደረጉት ወንድሞች ያዘጋጀችው ስጦታ እንዳለ በመግለፅ ስጦታዋን ይዛ ወደ መድረክ እንድትመጣ ጋበዛት ከዚያም ለዐሉላ ጥላሁን፣ ለኢዮብ ሥዩም፣ ለመንግሥተ አብ አራንሺ፣ ለዲያቆን ታደሰ እና ለአሸናፊ ደምሴ ከብር የተሠራ የቁልፍ መያዣ አበርከተችላቸው። በዚሁም አጋጣሚ ለዳንኤል ስኬት እና እንደ አምፑል እንዲያበራ ካደረጉት ጀነሬተሮች መካከል ባለቤቱ ፅላት የአንበሳውን ድርሻ እንደምወስድና እንደሚገባትም በእጅጉ ተገነዘብኩ ጥሩ ትምህርትም ተማርኩበት። ይህንንም ተከትሎ ልጆቹ አና ባለቤቱ ለዲያቆን ዳንኤል ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት መግለጫ ይሆናቸው ዘንድ ስጦታ አበርክተውለታል።

በመጨረሻም የአኽሱም ሆቴል ሰራተኞች ለዲያቆን ዳንኤል ያላቸውን አድናቆት ለመግለፅ ግሩም ጣዕም ያለውን የውሃ ዳቦ (ሕብሽቲ) አዘጋጅተው አቅርበዋል። ዳቦውም ተቆርሶ ለታዳሚው ቀርቧል። ከዚህ ቀጥሎ የነበረው የሻይ ቡና እና የ ፎቶ ፐሮገራም ነበር በዚህም ላይ ተካፈልኩኝና  ዳኒን እና ፅሉን እንደማንኛውም ታዳሚ ተሰናብቼ ባመጣኝ ታከሲ ጉዞ ወደ ራት ኪሎ ሆነ እላችኋለሁ።

በአጠቃላይ በእለቱ የነበረው የበዓሉ ዝግጅት 12፡00 ሰዓት ላይ ተጠነቀቀ። ይሁን እንጂ ከነበረው የተሳታፊ ብዛት እና የብሎጉን ተደራሽነት ከማስፋት አንፃር በብሎገሩ ወደፊት ሊወሰዱ ስለታቀዱ እርምጃዎች እንዲሁም የዕድምተኞች ተሳትፎ ምን መምሰል እንዳለበት አመላካች የሆኑ ውይይቶችን ለማድረግ ሰዓቱ በጣም ነው ያጠረው የሚል የግል አስተያየት አለኝ። ምናልባትም ፐሮገራሙ ቢቻል ቀን ሙሉ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ (አንድ የማገር እንጨት እንኳን ላያግዝ አስፍተህ ስራ ይላል ይላሉ ወላይታዎች) ከውይይቶቹ የሚገኙትን ፍሬ ሐሳቦች ፈልጌ እንጂ ፐሮገራሙ ቀን ሙሉ ቢሆን አብረውት የሚመጡትን ተያያዥ ችግሮች ዘንግቼ እንዳልሆነ ግን ልብ በሉልኝ።

ቸር ያሰማን።  

9 comments:

 1. ዲያቆን ዳንኤል ከባለቤቱ ከፅላት ጌታቸው ጋር ሙሉ ነጭ በነጭ ለብሰው እንዴት አምሮባቸዋል መሰላችሁ። የበኩር ልጃቸውን ለመዳር ሁሉን አዘጋጅተው የሙሽራውን መምጣት ብቻ የሚጠባበቁ እናት እና አባት ይመስላሉ።

  ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች::

  አንድ የማገር እንጨት እንኳን ላያግዝ አስፍተህ ስራ ይላል ይላሉ ወላይታዎች

  ReplyDelete
 2. Qale hiwoten yasemalen wendemachen Hayle GEBEREL !!!! beteru agelalet yeneberewn huneta new yegeletekelen betemeseto hoge begugut new yanebebekut bemecherescham menew enem be akal ezaw benebberku beye temegew !!!

  esey enkuan beseket ena beteru menfes alefe !!!!!!!!

  le ametu degemo beselam yaderesen Amen !!!!!

  ReplyDelete
 3. God Bless All Of you.

  ReplyDelete
 4. ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች "
  ይህ ትልቅ እዉነታ ነዉ ለወንድ ልጅ መዉደቂያዉም ሆነ መነሻዉ ሴት ናት፡፡

  ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡


  ወልደአማኑኤል ከሚኒሶታ -አሜሪካ

  ReplyDelete
 5. ኃይለ ገብርኤል ቃለ ህይወትን ያሰማልን፡፡ በዕለቱ በፕሮግራሙ ላይ ብገኝም እንደአዲስ አፌን ከፍቼ ነው ያነበብኩት ካሁን በፊትም የምትጽፋቸውን አስተያየቶች ደጋግሜ አንብቤአለሁ ጥሩ የመግለጽ ችሎታ እንዳለህም ተንዝቤአለሁ በርታ ነው የምለው ወደፊትም ብዙ አስተያየቶችን/እይታዎችን/ እንደምታስነብበን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ልዑል እግዚአብሔር አንተንም እኛንም ይጠብቀን፡፡ የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡

  ReplyDelete
 6. ጥቁር ነኝ ግን ውብ ነኝ ማለት እንዲህ ነው። የማያውቁትን በግልፅ አላውቅም ወይም ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ እቅጩን መናገር እንዴት ደስ ይላል!! በቦታው ላይ በስራ ምክንያት ላልተገኘነው በጥሩ ሁኔታ ነው ያቀረብክልን። ዝግጅቱን በአካል የተካፈልነው እንዲመስለን አድርገሃል ብዬ ብናገር ያጋነንኩ አይመስለኝም። ቃለ ሕይወትን ያሰማልን።

  ReplyDelete
 7. Hayle Gebrea k 4 kilo

  Ant koy Ye hameer 'mengedengaw Tsahfi neh'? betam yewdiw ye hameer kifl new

  Berta wendme

  ReplyDelete
 8. ዳንኤልን እንወደዋለን እናከብረዋለን ነገር ግን እንደዚ ያለ እጅግ የተጋነነ አቀራረብ ዳንኤልን አይጠቅመውም ዳንኤልን ብንወደውም ብናከብረውም ፀጋ ያደለውን እግዚአብሔርን ነው የምናመሰግነው:: ከዳንኤልን ብዙ ነገር ስለምንጠብቅና ዳንኤልንም ስለምንፈልገው እንደዚህ የተጋነነ እና ስሜታዊነት የበዛበት ነገር ጥሩ አይደለም:: ለዳንኤል ምስክሮቹ ስራዎቹ ናቸው::

  ReplyDelete
 9. Seblewengel,Addis ababaApril 6, 2011 at 3:03 PM

  ameseginalehu H/Gibreal
  be bealu laye balemesatefe betam azigne nabire ke aqime belaye hona nawu yeqarehute gine le fetare misegana yideresawu biyanse kibera bealu mini endamimesile ke tsewufehe teredichalehu.dani Egizeabihare rajeme edeme yadilehe .tsewufochehe betam asitimare nachewu
  KEEP IT UP

  ReplyDelete