Saturday, March 26, 2011

አንድ ድፍን የአዝመራ ዓመት

ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር)
ካልጋሪ፤ ካናዳ 

ለመጻፍ የተነሳሁት የዳንኤል ዕይታዎች የጡመራ ገበታ አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ነው። ይሁንና ቅድመ ከዊን ወደነበረ ጊዜ ሄጄ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ትንሽ ልበል።

ጊዜው የዛሬ ሁለት ዓመት። ቦታው ፓሪስ ከተማ። የአውሮፓ ስብከተ ወንጌል ጉባኤ ለመሳተፍ ከየአገሩ ተሰባስበን ነበር። ወዳጆቼ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና ዲያቆን ብርሃኑ አድማስም በመምህርነት ከአዲስ አበባ መጥተው ነበር። በወቅቱ ዳንኤል አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ አምደኛ ነበር። ከፓሪሱ ጉዞ ከወራት በፊት ለአጭር ጊዜ አዲስ አበባ በሄድኩበት አጋጣሚ የአምዷ ደንበኛ አንባቢ ነበርኩ። 

ቅዳሜ ቅዳሜ መፍቀሬ-ንባብ የሆነው አባቴ ጋዜጣዋን መግዛቱ  እንደማይቀር እያወቅኩ ተሽቀዳድሜ እገዛ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዳሜ ሳይገባደድ ሁለት የጋዜጣው ኮፒ እቤታችን ይገባ ነበር።  የኢትዮጵያ ቆይታዬ አልቆ ወደ ውጪ ስመለስ ቅዳሜ በመጣ ቁጥር ብቻ ሳይሆን ቅዳሜ ሊመጣ ሲል “አምዷ ከየት ትገኝ”… የሚመላለስብኝ ጥያቄ ነበር። አንድ ሁለቴ በድረ ገጽ “ስካን” የተደረገ አንብቤአለሁ። የተወሰነ ቀናትም ከራሱ ከዳንኤል በኢሜይል ከማግኘት ውጪ በመደበኛነት ማግኘት የሚቻል አልነበረም።

ስዊድን (ያኔ እዛ ነበርኩ) ውስጥ ከግማሽ ደርዘን ከፍ፤ ከደርዘን ዝቅ ከሚሉ ወዳጆቼ ጋር እናደርግ በነበረው ሳምንታዊ ውይይታችን ሳይቀር በተወሰኑ ጽሑፎች ውስጥ የተነሱትን ሃሳቦች መነሻ አድርገን ተወያይተንባቸው ነበር። በዚህና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ በአምዱ የሚያወጣቸው ጽሑፎች በዝርወት ካለነው አማርኛ አንባቢዎች ድረስ መድረስ ከቻሉ በማኅበራዊ በሌሎች አገራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጎ አስተሳሰብ ከማስረጽ አንጻር አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የሚል እምነትና ሃሳብ ነበረኝ።

እናም ፓሪስ ሃሳቤን ለዳንኤል በአካል ለማካፈል ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረች። ስለጽሑፎቹ እያገኛቸው ስለነበሩ አስተያየቶችና በተለያዩ አካላት ስለነበረው ተቀባይነት ትንሽ ካወጋን በኋላ “ጽሑፍህ በድረ ገጽ ቢወጣስ” ነገር አልኩት (አዲስ ነገር ድረ ገጽ ይከፍታል ተብሎ ሳይሳካ ቀርቶ ነበር)። “ጥሩ ነዋ” ነገር አለኝ። እንዲያዉም ለአንድ ዓመት ያህል በጋዜጣው ያወጣቸውን ጽሑፎች ወደ ፋላሽ ሜሞሪ ገለበጠልኝ። ተመሳሳይ ሃሳብ ያቀረበለት ሌላ ሰው እንዳለም ጠቆመኝና ከሱ ጋር ተነጋግረን እንድናዘጋጀው ነገረኝ። ከተጠቆምኩት ሰው ጋር ስንወያይ እሱም ሌላ ሰው በተራው ጠቁሞኝ  የተጠቆመው ሰው ሳይችል ቀርቶ እንደገና ሁለታችን ስንወያይ…. ጊዜው ተጓተተ።

ፓሪስ በተገናኘን በዓመቱ …ዳንኤል አሜሪካ በመጣ ጊዜ እንደኛ ውይይታቸውን ባላራዘሙ ሰዎች ብርታትና ሥራ የዳንኤል ክብረት ዕይታዎች ድረ ገጽ ብርሃንዋን አየች። እነሆ እኔና እኔን መሰሎች ደግሞ ከያለንበት ጽሑፎቹን መኮምኮም ያዝን።

ይህ ከሆነም እነሆ አንድ ዓመት ሆነው።ተጻፈ ተነበበ፤ ተጻፈ ተነበበ። አንድ ድፍን የአዝመራ ዓመት። አዲስ አበባዎች (በእርግጠኝነት) እንዲሁም ዋሽንግተኖች(መሰለኝ) ቀኑን ለማክበር እድል አገኙ ብዙም ሊወያዩ ነው። ከዛ ውጪ ያለነው ደግሞ በየቤታችን እናስበዋለን።

የዳንኤልን ጡመራ እወደዋለሁ። የሚወዱትን ነገር ለምን ወደድኩት ብሎ መጠየቅና መልስ ማግኘት ደስ ያሰኛል (የሚጠላውን ነገር ለምን እንደሚጠላ ደስ እያለው የሚናገር ሰው ያለ አይመስለኝም)። አዎ ደስ ያሰኛልና  ጡመራውን ለምን ወደድኩለት ብዬ ራሴን ጠየቅኩ።  በስፋት ሊጻፍላቸው የሚችሉ ግን በመዘርዘር ብቻ የተውኳቸው የሚከተሉት አምስት ምክንያቶችን አገኘሁ -ለዛሬ። 

፩) በኃይለ ሃሳብ የራሰ ይዘት
ሁል ጊዜ ቀልብ የሚገዛ ይዘት ያለው ጽሑፍ ነው የሚወጣበት። በኃይለ ቃል የደረቀ ሳይሆን በኃይለ ሃሳብ የራሰ የረሰረሰ ይዘት አለው-ጡመራው።

፪) ከስሜት የራቀ አቀራረብ
የሚያስቆጭ የሚያበሳጭ የሚያንገበግብ ጉዳይ አንስቶ እንኳን የስሜት አረም አንቆ ሳይዘው መልእክቱ ዘለግ ብሎ እንዲወጣ የሚያደርግ አቀራረብ ልዩ ምልክቱ ነው።

፫) ሁሉን የሚነካ ማንንም የማይናደፍ
ከሞላ ጎደል እያንዳንዱ ጽሑፍ ከላይም ከታችም ከግራም ከቀኝም ከውጪም ከውስጥም ያለነው ሰዎች ሁሉ የየድርሻችን እንድናነሳ ግድ የሚለን ነው። የሚመለከተው መልእክት የማደርሰውና የማይነካ አካል ያለመኖሩን ያህል በጽሁፉ የሚነደፍ አካል ግን የለም። 

፬)ዘላቂውን መንገድ የሚጠቁም
ነገን ብቻ ለመጠቀምና ዛሬን ብቻ ለመደሰት ሲባል ከነገ በኋላ ያሉትና ዘላለማዊነትን ያህል የረዘሙ ጊዜያትን በሙሉ የሚያጨልም አካሄድ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን እናውቃለን። ይሁንና የአጭር ጊዜውንና የአሁኑን ብቻ በማየት ማሰብ መናገር መጻፍና መሥራት አላቆምንም።  የዳንኤል ጦማሮች ግን የወደፊቱን መንገድ የሚታትሩ ናቸው።

፭)ከኃላፊነት ጋራ በኃላፊነት የሚጻፉ
ተጽፎለት ሊገኝ ፤ተደውሎለት ሊመልስ፤ መንገድ ላይ ታይቶ ሊለይ በሚችልበት ሁኔታ ስሙን ኢ-ሜይል አድራሻውን፤ ስልክ ቁጥሩንና ፎቶውን ከለጠፈ ጸሐፊ የተገኙ ጽሑፎች ናቸውና ከኃላፊነት ጋር በኃላፊነት የሚጻፉ ናቸው።

ስለጡመራ ገበታው ጽፌ ራሱን ሆኖና ችሎ ስለሚጦምረው ጦማሪው ትንሽ አለማለት ያጎድላል። ዳንኤል በጣም ያነባል። ዳንኤል ያያል። ዳንኤል ያስተውላል።ያነበበውንና ያየውን አይረሳም። ምንም ያንብብ ምንም ይይ ምንም ይስማ ሊጻፍ ወደሚችል ነገር ይቀይረዋል። የሰማውን ያይውንና ያነበበውን ነገር በቀላሉ አበሻ አበሻ እንዲል አገር አገር እንዲሸት ማድረግ ይችላል። ያነበብውን ያየውንና የሰማውን ነገር ከአገራችንና ከሕዝባችን ሁኔታ፤ ታሪክና እጣ ፈንታ ጋር ማዛመድ ሲበዛ ያውቅበታል።

ለዚህ ማሳያ ከሆነኝ አላውቅም እንጂ ቢያንስ በፓሪስ የጀመርኩትን ክታብ በፓሪስ ለመደምደም ስለሚረዳኝ አንድ አጋጣሚ እነሆ - ስለ ዳንኤል ልዩ ችሎታ።  ፓሪስ በተገናኘን ጊዜ በሆነ ጨዋታ ተነስቶ ኖኅ በዚህ ዘመን በአሜሪካ አገር ቢኖር ኖሮ መርከቡን ለመሥራት እንዲያሟላ ስለሚጠየቀው መስፈርትና እንዲያወጣ ስለሚጠበቅበት  የፈቃድ ብዛት ያነበብኩትን አጭር ነገር አወራሁት። ጊዜው ወደ ማታ አካባቢ ነበር።እሱ ማምሻውን ሰዎችን ለማወያየት መርሀ ግብሮች ነበሩትና ተለያየን። 

እኔም በማግስቱ ጠዋት ወደ ስቶክሆልም በረርኩ። በእለቱ ኢ-ሚይሌ ውስጥ ለአዲስ ነገር አምዱ ከተለያየን በኋላ የጻፈው ጽሑፍ ልኮልኝ አገኘሁ።  የአገራችንን መጠነ ሰፊና ውጥንቅጥ የቢሮክራሲና ሌሎች ችግሮች በዝርዝር ነገር ግን ፈገግ እያሰኘና እያስደመመ በሚገልጽ ቋንቋና አቀራረብ “ኖኅ በኢትዮጵያ” ሚል ርዕስ የጻፈው ነበር። ጽሑፉን አንብቤ ስጨርስ ማታ የሆነውን እያሰብኩ “ከመቼው” እያልኩ በምን ፍጥነትና በምን ሁኔታ እንደ ከሸነው  እየገረመኝ  “ዓይናማ አያልቅበት ልዩ ጸሐፊ” ብዬ ተደመምኩ።
በመጨረሻም…..

በመጪው ጊዜ ጽሑፎቹ በድምጽ ተቀርጸው የሚቀርቡበት መንገድ እንዲመጣ እመኛለሁ - ኅብረተሰባችን ከማንበብ ወደ መስማት ያዘነብላል ከሚል እሳቤ ነው። አንድ ያጣላል ካላችሁ…. ሁለተኛ ምኞት… የዳንኤል ባለቤት ጽሉ በአንድ ወቅት እንዳለችው ጽሑፎቹ በእንግሊዝኛ ተተርጉመው የሚቀርቡበትና እንግሊዝኛ አንባቢ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እንዲፈጠር እመኛለሁ።
ለዛሬ ግን…. መልካም አንደኛ ዓመት ለዳንኤልና ቤተሰቡ….. ቤተ-ጡመራው ለሆነው ለአንባቢያኑም እንዲሁ..

11 comments:

 1. ግሩም አስተያየት ፡፡ አቤት እግዚአብሔር በየቦታው ስንት ልጆች አሉት፡፡
  ተመስገን ነው፡፡

  ReplyDelete
 2. I have become "DBA" Daniel Bolg addict because I love his work. Every time I logged in to my computer the webpage I check are my emails and daniel's blog. Dr Getachew you have really summarized the contents of his blog.

  Congratulations Daniel. Your starting is awesome and keep that awesomeness.

  GOD be with all of us!

  ReplyDelete
 3. Docter leke belehale tebareke.....egame yehene negere lemayet betam new ena yemenegogowe Egeziabehere benegerochu hulu kedemo yehen negere endiyasaka enmegalen!!!

  ReplyDelete
 4. ዲን ዳንኤል፡ ዶር ጌታቸው፡

  አንድ ቃል - ተባረኩ!

  ያሬድ ጌጡ፡፡

  ReplyDelete
 5. eagle eyed, it is a gift from the holy sprite. may God keep the gift with him and bless all of us.

  dr. and dn. kalehiwot yasemalin

  ReplyDelete
 6. Congra Dani!
  It was amazing!, It remind me alot..I was student... Dani in Markos church ..AAU sidist kilo... and he teached us..Bible ...the way u taught is critical on things...He keeps that sprit and strength until now..It was good experince to apperciate people for good work on his life time.Thanks Dr.Getachew for precise and concise comment.
  Ephrem(Toronto)

  ReplyDelete
 7. Thank You Dr Getachew. God Bless You .

  ReplyDelete
 8. Daniel, I testify that you can see things from different persepectives. Moreover, you are highly analytical in all terms. Because of this, I become your permanent audience. I wish you all the best and God Bless you.

  Abebe M. Beyene

  ReplyDelete
 9. በመጪው ጊዜ ጽሑፎቹ በድምጽ ተቀርጸው የሚቀርቡበት መንገድ እንዲመጣ እመኛለሁ

  Danielen ketsehufochu bebelete be sibketochu ewedewalehu. Sibketochun besemahu kutir yemisemagne liyu simet ale. "le tifat yetazezech ketema negarit bigosem atisema" ena lelochu liben yemineku sibketoch alut.

  Daniel Egziyabher abzito yibarkeh.
  Woldesilase ke Finland

  ReplyDelete