Tuesday, March 15, 2011

ሚኒስትሩ ሰርቀው


ሰሞኑን ጀርመንን ከናጧት ዜናዎች መካከል የአካባቢ ምርጫ እና የመከላከያ ሚኒስትሯ ነገር የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ አንጀላ ሜርኬል በአካባቢ ምርጫ የበላይነትን ለመያዝ ላይ ታች በሚኳትኑበት ጊዜ እነዚህ የማያርፉ ጋዜጠኞች እና የኢንተርኔት ጎርጓሪዎች አንድ ጉድ አፈሉ፡፡
ለሰባት ዓመታት በጥናት «ደክመው» የሕግ ዶክተር ለመባል የበቁት የጀርመኑ የመከላከያ ሚኒስትር ጉተንበርግ (Karl-Theodor zu Guttenberg) «ዶክትሬቱ አይገባቸውም» የሚል ክርክር ተነሣባቸው፡፡ እርሳቸውም «ስሜን አታጥፉት» እያሉ ለመከራከር ጀመሩ፡፡ ጋዜጠኞቹ እና የኢንተርኔት ጎርጓሪዎቹ «ሰውዬው ጥናታቸውን ሲሠሩ ከጋዜጦች፣ ከልዩ ልዩ ጥናቶች እና ከሰዎች ንግግሮች ባለቤቶቻቸውን ሳይጠቅሱ እንደ ራሳቸው ሥራ አድርገው አቅርበዋል፤ ይኼ ደግሞ ስርቆት Plagiarism ነው እያሉ» ያብጠለጥሏቸው ጀመር፡፡
ቆየት አሉና ደግሞ የትኛውን የጥናታቸውን ክፍል ከየትኛው ጋዜጣ፣ የትኛውን ከየትኛው ንግግር፣ የትኛውን ደግሞ ከየትኛው ጽሑፍ እንደ ወሰዱ ብልት በብልት እያወራረዱ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ሰውዬውንም ዕረፍት ነሷቸው፡፡ እርሳቸውም በመጨረሻ «ከባድ ስሕተት ሠርቻለሁ» ብለው አመኑ፡፡ የዶክትሬት ማዕረጋቸውን መልሶ እንዲወስደውም የሰጣቸውን የባየር ኡት ዩኒቨርሲቲ (University of Bayreuth) ጠየቁ፡፡
ፕላጃሪዝም በዕውቀት ሽግግር ውስጥ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ይህ ወንጀል በሁለት መንገድ ይፈጸማል፡፡ በማወቅ እና ባለማወቅ፡፡ ያነበብናቸው፣ የሰማናቸው፣ ያቀነቀናቸው፣ ያወራናቸው ነገሮች በአእምሯችን ውስጥ ለረዥም ጊዜ ከመቆየታቸው የተነሣ የራሳችን አዲስ የፈጠራ ሥራዎች መስለው የሚሰሙን ጊዜ አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች በጽሑፎቻችን፣ በዜማዎቻችን እና በንግግሮቻችን ውስጥ ልክ እንደ ራሳችን ውጤቶች ሆነው ሳናስባቸው ይወጣሉ፡፡
ምናልባት ችግር መፍጠራችንን ወይንም መሳሳታችንን የምናውቀው ሌሎች ሰዎች ሲጠቁሙን እና ከኛ በፊት ነገር የተባለ፣ የተዜመ ወይንም ቃል በቃል የተጻፈ መሆኑን ስናውቀው ነው፡፡ በተለይም በእነዚህ ንግግሮች፣ ዜማዎች እና ድርሰቶች የምንመሰጥ ከሆነ ከእኛ ጋር የመዋሐዳቸው፣ የኛ መስለውም መልሰው የመውጣታቸው ነገር ይጨምራል፡፡
ለዚህ ነው ምን ጊዜም ቢሆን አጥኝዎች፣ ደራሲዎች፣ የአደባባይ ንግግር አድራጊዎች እና የዜማ ባለሞያዎች ድርሰቶቻቸውን ሊያዩላቸው እና እንዲህ ከመሰለው በዕውቀት ላይ ከሚፈጸም ወንጀል የሚጠብቋቸው አትርታእያን የሚያስፈልጓቸው፡፡ እነዚህ አርታዕያን የሰዎችን ድርሰት ከራሳችን ድርሰት በመለየት፣ ለሰዎች ውጤቶች ተገቢውን ቦታ እና ዕውቅና እንድንሰጥ እና ከከባዱ ሌብነት ወደ ተመሰገነው ዋጋ ሰጭነት እንድንሸጋገር ያደርጉናል፡፡
ሁለተኛው እና ከምንም የከፋው ደግሞ ሆን ተብሎ የሚፈጸመው ፕላጃሪዘም ነው፡፡ የሰዎችን ዜማ፣ ቃላት፣ ሃሳቦች፣ አባባሎች እና መሠረተ ሃሳቦች ለባለቤቶቹ ምንም ዓይነት ምስጋና እና ዕውቅና ሳይሰጡ፣ ልክ እንደ ራሳቸው አድርገው የሚያወጡ፣ የሚሸጡ፣ የሚሸለሙ እና የሚመሰገኑ የዕውቀት ወንጀለኞች አሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች የጥናት ውጤቶችን፣ የጋዜጣ እና መጽሔት ጽሑፎችን እና ሃሳቦችን፣ የሰዎች ንግግሮችን፣ ዜማዎችን እና ቅንብሮችን ገልብጠው የራሳቸው ያደርጋሉ፡፡ እጅግ ሲከፋ ደግሞ በእነዚህ የተሰረቁ ሥራዎች ዕውቅናን፣ ሽልማትን እና ክብርን ያገኛሉ፡፡
ይህ አካሄድ ሁለት ዓይነት ጉዳት ያመጣል፡፡ በመጀመርያ ፈጠራን ያጠፋል፡፡ ሰዎች እንደ ነዳይ ቋጠሮ ከዚህም ከዚያም ቃርመው፣ ገለባብጠው እና አገላብጠው፣ በሰው የጥበብ ሀብት የሚያድጉ ከሆነ ለምን ይፈጥራሉ? ለምንስ አዲስ ነገር ለማግኘት ይተጋሉ፡፡ አንዱን ከቦሌ አንዱን ከባሌ፣ አንዱን ከመቀሌ፣ሌላውን ከሞያሌ ገጣጥመው፤ አዲስ ሥራ አስመስለው በማቅረብ ከለፋው በላይ የሚያገኙ ከሆነ ልፋት ለምናቸው?
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሠራተኛው ዋጋውን እንዳያገኝ ያደርጋሉ፡፡ አንድ የጥበብ ባለ ሀብት በሁለት መንገድ ዋጋውን ያገኛል፡፡ በዓይነት እና በምስጋና፡፡ ጠቢቡ ለጥበቡ ዋጋ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ ወይንም በጥቅማ ጥቅም ሊከፈለው ይችላል፡፡ ያለበለዚያም ደግሞ ስም፣ ክብር፣ ዕውቅና እና ምስጋና ያገኝበታል፡፡ ስሙ ለትውልደ ትውልድ ይጠራበታል፡፡ ይህ ደግሞ ሌሎች ጠቢባንን ወደ ጥበብ ማዕድ ይጠራቸዋል፡፡
የጀርመኑ የመከላከያ ሚኒስትር ጀርመናዊ ሆነው፣ በጀርመን ሀገርም ተገኝተው ነው እንጂ እኛ ሀገር ቢሆኑ ኖሮ እንዲህ በቀላሉ «ዶክትሬቴን መልሱና ውሰዱት» አይሉም ነበር፡፡ ደግሞስ ማን ደፍሮ ተሳስተዋል ይላቸው ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲውስ ቢሆን መልሳችሁ ውሰዱልኝ ሲሉት «በኛም ላይ ተመሳሳይ ጣጣ ሊያመጡበን ነው» ይል ነበር እንጂ እንዴት መልሶ ይወስድባቸዋል? አይ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመሆንዎ፤ እንዴት አድርጎ ጎዳዎት መሰለዎ፡፡
በየዩኒቨርሲቲው ያሉት የመመረቂያ ጥናቶቻችን እስኪ ይታዩ? በየዐውደ ጥናቱ የሚቀርቡት ጥናቶች እስኪ ይመርመሩ? የበታቾች ለበላዮቻቸው የሚያቀርቧቸው የየመሥሪያ ቤቱ ጥናቶች እስኪ ይፈተሹ? እውነት አቅራቢዎቹ ባለቤቶቻቸው ናቸው? ሃሳቦቹ፣ ዐረፍተ ነገሮቹ፣ መሠረተ ሃሳቦቹ፣ ጥናቶቹ፣ ግኝቶቹ አዲስ ናቸው? ለመሆኑ ባለቤቶቻቸው ተመስግነውባቸዋል፣ ፈቃዳቸው ተጠይቋል? አይ የጀርመኑ ሚኒስትር ጉተንበርግ እኛ ነበር መምጣት የነበረብዎ፡፡
በአደባባይ የሚታተሙ ጋዜጦች የጸሐፊዎቹን ፈቃድ ሳይጠይቁ፤ ሲብስባቸውም ስማቸውን ሳይገለጡ፣ ያለ ሃፍረት በሚያሳትሙባት ሀገር፡፡ በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በመጽሐፍ የቀረበ ጽሑፍ በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን «እግዜር ይስጥልን» እንኳን ሳይባል ግልብጥ ተደጎ በሚቀርብባት ሀገር፡፡ በአንድ መጽሐፍ የወጣ ሃሳብ ከነ ቃሉ፣ ከነ ዐርፍተ ነገሩ፣ ከነ ነጠላ ሰረዙ፣ ከነ አራት ነጥቡ ተገልብጦ መልሶ በሚታተምባት ሀገር ቢኖሩ ኖሮ እርስዎ ዶክትሬቴን ልመልስ አይሉም ነበር፡፡ ክፉ አገር ገጥሞዎት ነው እንጂ፡፡
«ጎጃም ደኅና ነው ወይ» ተብሎ የተዘፈነን ዘፈን «ጎንደር ደኅና ነው ወይ» ብሎ መልሶ ዘፍኖ «አዲስ ዘፈን በታዋቂው እገሌ» በሚባልባት ሀገር አለመኖርዎ፤ ከኢንተርኔት ግልብጥ ተደርጎ ምንጭ ሳይጠቀስ ለቀረበ የጥናት ጽሑፍ በሚጨበጨብባት ሀገር ቢኖሩ ኖሮ፤ የፓርቲ መሪዎች የሰዎችን ሃሳቦች እንደ ራሳቸው ሃሳብ አድርገው በድፍረት ሲናገሩባት በሚሰማባት ሀገር፤ ከነባር የሀገሪቱ መጻሕፍት የተገለበጠ ጥበብ እና ሃሳብ እንደ አዲስ ግኝት ሲቀርብ ጉድ በሚሰኝባት ሀገር ቢኖሩ ኖሮ ለመሆኑ ማን ያብጠለጥልዎት ነበር፡፡ ጀርመን የሚባል ክፉ ሀገር፣ አይይይይ፡፡
ደግሞስ የትኛው ጋዜጠኛ፣ የትኛውስ ምሁር፣ የትኛውስ ኢንተርኔት ጎርጓሪ የሰው ሃሳብ ወሰዱ ብሎ ይጮኽብዎት ነበር፡፡ «እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ ተካክለው በደሉ» አለ የትርጓሜ መጽሐፍ፡፡ ሁሉ በዚህ ነገር ተስማምቶ እየመነተፈ ማን ይናገርዎት ነበር፡፡
አንድ ጊዜ የአንድን የጎጃም ሰው ቅኔ አንድ እሳት የላሰ ሞጭላፊ ላጥ ያደርግና ትግራይ ገብቶ እንደ ራሱ ቅኔ ሰተት አድርጎ ቅኔ ማኅሌት ላይ ይዘርፈዋል አሉ፡፡ ሊቃውንቱ ሰሙት ሰሙትና «ቅኔያቸውስ ደርሶናል ለመሆኑ የኔታ ደኅና ናቸው አሉት ይባላል፡፡ ልክ እንደ እርስዎ ሀገር ጋዜጠኞችና ምሁራን ስርቆቱን አሠረቁበት፡፡
ለዚህ ነበር አድያም ሰገድ ኢያሱ የጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴን «ደብረ ብርሃን ልበለው» ብለው ሲነሡ ሊቃውንቱ «ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ቀድመውዎታል» ያሏቸው፡፡ «ታድያ ምን ይሻለኛል ቢሉ «ይጠይቋቸው ደብረ ብርሃኖችን» አሏቸው፡፡ ጠየቁ ንጉሡ፡፡ ከፈለጉ ወርቅ ከፍለው ይውሰዱ አሏቸው፡፡ ሁለት መክሊት ወርቅ ከፍለው ስሙን ወሰዱ ይባላል፡፡ መቼም እነዚህ ጀርመኖች መሆን አለባቸው፡፡
ለምን መሰለዎት፡፡ ውርደት እየመሰላቸው እኮ ነው፡፡ ክርስቶስ አገልጋዩን ሙሴን ሲጠቅስ ያልተዋረደውን አሁን እነርሱ ሌሎችን ቢጠቅሱ ይዋረዳሉ? እንዲያውም የሚሰሙ፣ የሚያስተውሉ፣ ዋጋ የሚሰጡ፣ ውለታ የማይበሉ፣ በሐቅ የሚኖሩ መሆናቸውን ያስመሰክራሉ እንጂ፡፡
ይሄው እርስዎ ዐውቀውም ይሁን ሳያውቁ የሰው ሐቅ ነክተው አይደል ሰባት ዓመት ሙሉ የለፉበትን ዶክትሬት ይመለስ ያሉት) ምን ይደረግ የሰው ወርቅ አያደምቅ፡፡ ስንቶቹ ተመስግነው፣ ተሸልመው ከሞቱ በኋላ ጉድ እየፈላ አይደል እንዴ) ይህንን ከዚህ፣ ያንንም ከዚያ ነው ያመጣው እየተባለ ማበረታቻ ወስዶ እንደ ሮጠ አትሌት ክብራቸውን እየተነጠቁ አይደል እንዴ፡፡
በኛ ሀገርማልዎ ካስተማሯቸው ተማሪዎች ሀሳብ እና ጥናት ሰርቀው ራሳቸው እንደ ሠሩት አድረገው የሚያቀርቡ መምህራንም አሉ ይባላል፡፡ ለተማሪዎቹ በሚሰጡት ጥናት አንዳች አዲስ ነገር ካገኙ ላጥ አድርገው ወደ ኮፈረንስ መሮጥ ነው፡፡ «የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ» ያለው ተማሪ ሳይሆን ይቀራል፡፡
እና ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ስሕተትዎንም ማወቅዎ፤ ይቅርታም መጠየቅዎ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የዶክትሬቱ ክብር ቢቀርብዎ እንኳን የትልቅ ሰውነት ክብር ያገኛሉ፡፡ እንዴው የርስዎ ስለተገለጠ እንጂ ከእርስዎ የባሰ ሳይኖር ይቀራል? ሲጠራበት ከመስማት በቀር ከየት እንዳገኘው፣ ምን አጥንቶ እንደ ተሰጠው፣ ያጠናው ጥናት የት እንዳለ የማይታወቅ ስንት አለ፡፡
የጀርመኑ ዩኒቨርሲቲም ቢሆን ይህንን ያህል ባይከፋ ጥሩ ነው፡፡ እንዴው እርሳቸው አጥፍቻለሁ ስላሉ በወደቀ ዛፍ ምሣር ስለሚበዛ፣ አገሩም ጀርመን ስለሆነ ነው እንጂ ተሸፋፍኖ የቀረ ስንት አለ አይደለም? ተው እባካችሁ ብዙ አታናግሩን፡፡
ቫሌታ፣ ማልታ
© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ .የተወሰነ የግ. በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።

26 comments:

 1. Dani, kesir degmo masatem aygebam yemilew ''link'' maregin mechem aykelekilim aydel? malet face book lay linkun metkes ena linkun teketlo anbabi blogun bianebew min kifat alew? kechalk bitmelisilign.

  ReplyDelete
 2. አትስረቅ የሚለው ህግ ሲሻር-ከሰማያዊው ቅጣት ባሻገር የሚያመጣው ምድራዊ መዘዝ!

  ReplyDelete
 3. ወይ ዳንኤል!

  እኔ ግን እኚህ ሰው ትልቅ የዶክትሬት ድግሪ እንደሰሩ ነው የምረዳው:: ለምን መሰለህ በስምንተኛው ሺህ ተሳስቻለሁ ድግሪአችሁን ተቀበሉኝ ማለትኮ ልዩ ግኝት ነው:: ግን ችግሩ "እሰይ ደግ ሠራህ፧ እፁብ ድንቅ ግኝት" ብሎ የሚያረጋግጥላቸው አልተገኘም እንጂ:: ምን እንከን ይወጣዋል አሁን ይሄ ድግሪ?

  አንድ ጊዜ ጠቅላይ ምኒስትራችንን ጋዜጠኞች የጠይቋቸዋል እንዲህ ብለው: "የትምህርት ጥራት ቀንሷል ተማሪ 'ኮፒ' ማድረግ አብዝቷል እና በዚህ ላይ ያልዎትን አስተያየት..." ሲባሉ፦ " 'ኮፒ' የሚያደርግማ ቢኖር ሀገራችንን በሰለጠነው ዓለም ተርታ ማሰለፍ በቻላችሁ ነበር" ብለው መለሱላቸው::

  እናም እንደው ኮፒ ተደርጎስ መች ለውጤት አበቃነው ነው የኔ ነጥብ:: ብቻ ጽሑፍህን ወድጄዋለሁ:: በተለይ በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ቢያገኙት ጥሩ ነገር ይመስለኛል:: ይህን ያልኩበት ምክንያት አለኝ:: አብዛኛውን ጊዜ የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ክፍለሀገር ላሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አማካሪ ሆነው ያገለግላሉ:: የምርምር ሥራ ንድፈ ሃሳብ (proposal)ለተማሪዎቹ አቅርቡ ሲባሉ አንድ ዓይነት ርዕስ ሦስት ዩኒቨርሲቲ ላይ ይበተናል:: መቼስ ደረጃ መዳቢ የለ፡ ጥራት ተቆጣጣሪ የለ፡ ዩኒቨርሲቲዎች የመረጃ ልውውጥ የላቸው፡....ብቻ እነርሱ በአንዷ ርዕስ ላይ ሦስት ተማሪ ያለምንም የአሠራር ልዩነት ቁጭ አድርገው በደፈና ማስመረቅ ነው:: አንዳንዴ ከመጨረሻ የመመረቂያ ጽሑፍ በኋላ ተመራቂዎቹ ሳያውቁ 'ዎርክሾፕ' ላይ በተመሳሳይ ርዕስ ሲቀርቡና የታዳሚ ውርጅብኝ ሲጎርፍባቸው ይስተዋላል:: ብቻ ይህ ነገር ብዙ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው ለወደፊት:: ያንተን የጡመራ መድረክ ብዙ የሚያነብ የምሁራን ክፍል ስላለ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነውና ከግምት እናስገባ በዕለት ከዕለት ሥራችን ውስጥ:: ይህ ከመንግሥት ሳይሆን ከእኛ ነውና እላለሁ::

  ቸር ይግጠመን

  ReplyDelete
 4. ዳኒ

  እግዚአብሄር እውቀትን ያብዛልህ..

  አሁን እኮ የተቸገርነው "ምን አለበት ..." የሚሉት የዛገ አስተሳሰብ በየስርቻው መንገሱ ነው::ከልካይ ጠፋ'ኮ:አንዳንዴ ሳስበው ውሸት ሲበዛ ሀይል ተጨምሮበት እውነት ይሆናል አይነት ገዳይ አስተሳሰብ የተጠናወተን ይመስለኛል::የአንድን ነገር እውነትነት ለማረጋገጥ ምን ያክል ሰው እውነት ብሎል በሚል የሚያፈስ መስፈሪያ መስፈር ለከፋ ውድቀት እንደሚዳርግ ማን ያስረዳልን ????? እንዴ.... በቃ'ኮ ይህ ነው እየተደረገ ያለው::ለምንም ጉዳይ:ለምንም አይነት ውሳኔ እጃችሁን አንሱ ነው... እጅ ይቆጠር ነው:: ይሄ አካሄድ ለሰለጠነ ማህበረሰብ እንጅ ለኛ ይጠቅማል ብየ አላምንም::ብዙ ሰው'ኮ አንድን ነገር እውነት ነው ብሎ የሚከተለው ህሳቡን በማመዛዘንና : በራስ በመተማመን ላይ ተመርኩዞ አይደለም::በቃ....ስለሚፈራ ወይም የዛሬ ሆዱን ለመሙላት እውነት ነው ከማለት የተሻለ አማራጭ የለም ብሎ ስለሚያስብ ነው:: አሁን አሁን "ይሄ አይገባኝም : ይሄን አልችልም ..." ማለት የነውር ያህል እየተቆጠረ'ኮ ነው::ያልተማሩትን የሚያስተምሩ : ባላዩት ባልሰሙት የሚመሰክሩ: በሰው ስቃይ የሚበለጽጉ...ብዙ ናቸው'ኮ::

  አንድየ መፍትሂውን ይስጠን..

  ReplyDelete
 5. Dani,Tebarek Dengele Ateleyehe//////

  ReplyDelete
 6. እንደምን ዋልክ ዲ/ዳንኤል እግዚአብሄር መቸም አድሎሀል በዚህዘመን እውነትን ሰውለመናገር አይደለም ለማወቅ እንካን በሚፈራበትና በሚሸሽበት ወቅት አንተ የሰውን ሁሉ አይንና አንደበት ለመሆን በመቻልህ ጡመራህን በጉጉት በሚያነበው ምእመን ሁሉ ላመሰግንህ እወዳለሁ
  እረዴተ እግዚአብሄር አይለይህ ካንተ ደፋርነትንና ለእውነት መቆምን ላባቶቻችንም ይስጥልን አሜን

  ReplyDelete
 7. selam lanete yihun dani wentem mengest wenetun ayeto new leka tench goshem adergo yasarefhe leka ye poletika sew nehe tadeya minew atewedaderm gin ashmur lekereseteyan teru ayedelem ayeee tilku dabo lit hone ato daneal

  ReplyDelete
 8. አይ ዳንኤል፡-

  ደግሞ ምኑን አመጣኸው

  እንደዚህ ከሆነ ነገሩ እኛ አገር ያሉ መሪዎች በሙሉ ከትምህርት ብቻ ሳይሆን ከሥልጣንም ሊወርዱ ነው ማለት እኰ ነው፡፡

  ከኦፕን ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝ፣ከአኩኩሉ ዩኒቨርሲቲ፣ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሲቪል ሰርቪስ፣ከጥቂት ጥራታቸውን ለማስጠበቅ ከሚታገሉ የግል ዩኒቨርሲቲዎች በቀር ሌሎቹ፣ከሥራ አመራር ኰሌጅ በሙሉ የሚመረቁት ሁሉ ሊመልሱ ነውና፡፡ ለዚህ እኰ ሌላ አስመላሽ መሥሪያ ቤት ሊቋቋም ነው ማለት ነው አለበለዚያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አስመልሶ መጨረስ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

  የመንግሥት አመራሮቹ ከኦፕን፣ ሲቪል ሰርቨስ፣ ከተከታታይ የክረምት ትምህርት ከየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚመረቁት በሙሉ አፍ አውጥተው ጓደኞቻቸውን መመረቂያውን ብቻ አይደለም፥ የቤት ሥራ ሁሉ ሲያሰሩ አይቼ ተገርሜአለሁ፡፡

  ለዚህ ሳይሆን ይቀራል የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ሥዕል መገለጫው ነው የሚባለው፡፡ ከታች እስከ ጭኑ ድረስ በትምህርት ጥራት እጦት መንምኖ ቀጥኖ ከላይ በዩኒቨርሲቲና መሰል ተቋማት ቁጥር ገዝፎ ቅንጥስ ብሎ ሊወድቅ እየመሰለን የሚያሰቅቀን፡፡

  ድንቄም ትምህርት፣ ድንቄም ምሑራን፡፡ እንደ ቁራ የሚጮሁ አንባቢዎች የተፈለፈሉባት አገር ኢትዮጵያ! ለማንኛውም ዶ/ር ዳኛቸው ከሸገር ኤፍኤም ጋር ያደረጉት የሸገር ካፌ ውይይትና የዳንኤል ምልከታ አንድ ሳይሆኑ ይቀራል ያልሰማችሁ አድምጡ፥ አድራሻው የሚከተለው ነው http://shegerfm.com/index.php?view=article&catid=40%3Aarchived-gallery&id=1433%3Asheger-cafe-dr-dagnachew-july-11-2010-part-one&option=com_content

  ReplyDelete
 9. አይ ዳኒ ጥሩ ብለሃል በዚህ በውጭ አገር አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይቆዩና ደጅ ጥናት ወደ ኢትዮጵያ ደግሞ ይመጣሉ። አንዳንድ እንጊሊዘኛ ቃላትን ጣል ጣል ያደርጋል። በዚህ ቲዮሎጂ ዩንቨርስቲ ተምሬ መጣው ይላሉ። ግብር በላዎችም ይህንንው ያናፍሱታል። በዚህ አይነት ባልዋሉበት ውለናል ብለው ያልተማሩትን ተምረናል ብለው ድግሪና ማስትሬት ዲግሪ እንዳላቸው የሚያስወሩትን ቤቱ ይቁጠራቸው። ማን ነው የት ነበርክ ብሎ መረጃ የሚጠይቃቸው። በእርግጥ ጠንካራ የሆኑና የተማሩ አባቶችን አይመለከትም ነጋዴዋችንና የሌላቸውን አለን የሚሉትን እንጂ። ጎንደር ደብረ ብርሃን ለሰሙ መሰየም መክፈሉን ስሰማ ለመጀመሪያ ነዋ። ግሩም ነው።

  ReplyDelete
 10. Beka yehe newe lehelina menore malete. Bewente ministru talake sewe nachewe .. bezuochachen tefatachen mamene be sewe fete yekedenale. Yegane Gudayema "Bete yekuterew". .

  abraham
  Addis Ababa

  ReplyDelete
 11. Thank you Dani.It is very interesting that 'Adyam Seged Eyasu asked Atse Zara Ya'kob permission to name Gonder Selassie Debre Birhan,that the people told Eyasu Zara Ya'ekob had named a place so in Shewa before him, and that Eyasu asked permission from the 'Atse'.

  This is very interesting.You mean that Eyasu did not commit plagiarism not only because he was loyal but also because his people had information about things said and done at different places. Let's follow their footsteps-the Eyasu, writers, the people, readers and critics.

  ReplyDelete
 12. Thank you Dani. You told us that writers, as Eyasu gave gold to Zara Ya'ekob, must acknowledge people from whom they take information.

  Thank you once more, and may God give us the courage to acknowledge our forefathers.

  ReplyDelete
 13. Dn Daniel, we thank you very much for your criticism. You told us that Eyasu asked Zara Ya'ekob permission for the name Debre Birhan, only a phrase.

  How many times should we acknowledge our forefathers for the many things we received from them?

  ReplyDelete
 14. How many times should we acknowledge our forefathers from whom we took both material and spiritual possessions, Dani?

  ReplyDelete
 15. ስንት አለ እውነትህን ነው ዳኒ። በቅርቡ በቤተክርስቲያናችን ቁንጮ ላይ ቁጭ ያሉት አባ ኅይለማሪያም መለሰስ ቢሆኑ ዱክትርናውን ከየት ሞጭልፈውት ይሆን ከ ኖርዌይ ማስተርስ በግድ በእርዳታ ጨረሱ በተባለ በሁለት ዓመቱ ዶክተር ተብለው ደግሞ ሰማናቸው ፤አነበብናቸው። ይገርማል።

  ReplyDelete
 16. Truly teachable for those who listen.

  ReplyDelete
 17. "እና ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ስሕተትዎንም ማወቅዎ፤ ይቅርታም መጠየቅዎ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የዶክትሬቱ ክብር ቢቀርብዎ እንኳን የትልቅ ሰውነት ክብር ያገኛሉ፡፡"ዳኒ በጣም ደስ ይላል

  ReplyDelete
 18. ጠቅላይ ምኒስትራችንን 'ኮፒ' የሚያደርግማ ቢኖር ሀገራችንን በሰለጠነው ዓለም ተርታ ማሰለፍ በቻላችሁ ነበር" ያሉት ቻይና እንዲት እዚህ ደረጃ እንደደረሰች ሰለሚያውቁ ይመስለኛል። እናም በቅርቡ ጊዜ በምኖርብት ከተማ የተለያዩ ጋዜጣ ላይ እንደተጻፈው ፡ ቻይና በተለያኡ አገሮች ቴክኖሎጂ፤ መረጃና እውቀት የሚሰርቁ ሰላዪች አሉዋችው።

  ለምሳሌ ቻይና በጣም ፈጣን ባቡር ከፈረንሳይ እገዛለው ብላ ብዙ ኢንጅነሮቿን ለስልጠና ብላ ወደ ፈረንሳይ ላከች ከጥቂት ጊዜ በሃላ ተመሳሳይ የወነ ፈጣን ባቡር ሰርታ አወጣች። እንዲያሁም ጃፓን እንኳን ለብዙ ዘመናት ከምራባውያን ኮፒ አድርጋ እያሻሻለች ለዚህ ስልጣኔ እንደበቃች የሚያቱ አሉ፡፤ Plagiarism ሰፋ ያለ ትርጉም ብኖርዉም፤ የለላውን ኮፒ በማድረግ ደርጃ አገርንና እራስን መጥቀም በዚህ ዘመን ተስፋፍቶ የሚገኝ ጉዳይ ነው። በነገራችን ልይ የFacebook ባለቤት እንኳን የሎችን ሃሳብ ሰርቆነው ይባላል። የPlagiarism ሌላ መልኩ ደግሞ industrial espionage ብዙ አገሮችንና ድርጅቶችንን በጣም እያሳሰበ ያለ ጉዳን ነው። የብዙ አገር ሰላዪች ጊዜአቸውን በዋናነት የሚያውሉት የአገራቸውን ኢኮኖሚ ለመጠበቅ ነው እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ/አባል/ የት ገባ የት ወጣ በማለት አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ጨርታ ለማሸነፍ አገሮች እና ካምፓኒዎች ጨረታ ያወጣውን ወገን መረጃ አንዲት ሳትቀር በማወቅ ጨረታውን ለማሸነፍ የማያዳግም ጥረት መተለያየ መንገድ ያደርጋሉ። የእኛ አገር ደርጅቶች ጨርታ ሲያወጡ እነሱ የሰሩት የዋጋ ዘርዝር በውጭ አገር ድርጅቶች ተሰርቆ ጨርታውን ለማሸነፍ ሊተቀሙበት እንደለሚችሉ አቀው ምን ያህል አንደሚጠነቀኩ እነርሱ ያወቁታል!! ለምሳሌ አንድ ነገር ብጠቅስ በዚህ http://www.scribd.com/doc/43400771/Managerial-for-Ceo ገብታቹ ብታዩ የመብራት ሃይል ሰራተኞች ስማቸው፤ ጾታ፡ የስራቸው መደብ በ 62 ገጽ ተዘርዝሮ ይገኛል። ይህ መረጃ ማን እንድተቀምበት ነው በኢንተርነት የተለቀቀው??

  ReplyDelete
 19. ጥሩ ዕይታ ነው ዲያቆን ዳንኤል፤
  የቴክኖሎጂ ኩረጃ ግን ለሀገር ዕድገት ከሆነ ብንቀጥልበትስ?

  ReplyDelete
 20. @Anonymous-Plagiarism-በሳይንሱ አለም ከፍተኛ ወንጀልና የሞራል ድቀት ነው። እንድ ጊዜ ተፈልስፎ ወደ ስራ የገባን ቴክኖሎጂ ኮፒ አድርጎ ወይም አስመስሎ ከመስራትም ይለያል። Plagiarism-የሚያጠነጥነው አንድ ሰው ያፈለቀውን ሃሳብ የራስ አድርጎ መውረስ ላይ ነው። ምሳሌ የአምፖልን ሃሳብ አፍላቂ ቶማስ ኤዲሰን ነው። ሃሳቡን በተግባርም አሳይቷል። ከዚያ በኳላ የተለያዩ ቴኪኮችን በመጠቀም በተግባር ያሳየውን ሃሳብ በማስፋት የተለያዩ ሃገራት ጥቅም ላይ እያዋሉት ይገኛሉ። ይህ ቢሆንም የሃሳብ አፍላቂውን ስራ ማንም አልነጠቀም እየጠቀሱና እያመሰገኑ ይጠቀሙበታል እንጂ። ይህን ስል ተሽሎክልኮ አንድን ቴክኖሎጂ ኮፒ ማድረግ ፍጹም ትክክል ነው ማለቴ አይደለም። ቢቻል የራስን ቴክኖሎጂ ማፍለቅ ልዩ አማራጭ ነው። ካልሆነ ግን ቴክኖሎጅን በተለያዩ መልኮች ወደ ራስ አመቻችቶ መስራት ወይም ኮፒ ማድረግ ይቻላል። እንደ ጠቀስኸውም እነ ቻይና ህንድ ለዚህ በጣም ተጠቃሚዎች ነው። ነገር ግን ቴክኖሎጂንም ኮፒ መላድረግ ልዩ ጥበብና እውቀት ያስፈልገዋል ምን አልባትም ከማፍለቁ በተለየ። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡-ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ታላላቅ ቤቶች የክሪስማስ ዛፍ ይተከላል። ይህ ዛፍ ፈጽሞ ሊያፈራ አይችልም። በተፈጥሮ የማፍራት ችግር ኖሮበት ሳይሆን ኩባንያው ሆን ብሎ በጀነቲክ ኢንጅነሪንግ መካን እንዲሆን አድርጎታል። የዚህን ዛፍ ሎክ የተደረገበትን ዘረ-መል እንዲመለስ ማድረግና ዛፉን በሃገሪቱ ማባዛት መቻል ታላቅ ገቤ ያስገኛል። ዋናው ማን ይሰራዋል ነው። እናም አንዳንዴ ኮፒ ማድረግ እንደ ቃላቶቹ አጭር አይደለም። ይህን ካነሳን ኢትዮጵያ ውስጥ Plagiarism ና ቴክኖሎጂ ኮፒ ማድረግ ተዘባርቀው የሚገኙ ይመስለኛል። አሁን ያለውን Plagiarism ዳንኤል ጥሩ አድርጎ አስቀምጧል። ይህም የመጣው አገሪቱን በተሎ ለማሳደግ ቴክኖሎጂ ኮፒ እናድርግ የሚባል ከወደ መንግስት ሽው መደረጉ ነበር። አንዳንድ መስሪያቤቶችም ብሔራዊ የቴክኖሎጂ ሾፒንግ ኮሚቴ አዋቅረው መንቀሳቀስ ጀምረው ነበር። ግን ባሁኑ ዘመን ኮፒ ለማድረግ እራሱን የቻለ ዕውቀት ስለሚጠይቅ ተግባር ላይ ሳይውል ቀረ። እናም የሌሎቹን ጆርናል ኮፒ በማድረግ ማሳተም እንደ ተራ ነገር ተቆጠረ። ይች እንግዲህ Plagiarism ናት። አንዳንድ ቦታ ወደ ሰሜን የተሰራውን ምርምር ምንም ሳይቀይሩ ደቡብ ወይም ምዕራብ ላይ ወስዶ ይሰራና ፎርም የመሙላት አይነት የህትመት ስራም እየወጣ ዝም ተብሏል። ምርምር በቦታ ቢደገም ይበረታታል ነገር ግን መጀመሪያ ሃሳቡን ያፈለቀውን ሰው በግልጽ አመስግኖ በተለየ ቦታ ቢታይ ምን ያህል ወጥነት ይኖረዋል የሚለው ታሳቢ በማደግን ነው መድገም ያሰፈልገው ሳይባል የራስ አስመስሎ መስራት አደጋ ነው። ይህ ለሳይንስ ልዕልና መጥፍ ነው። ሃገሪቱንም እንዲያውም እንዲህ ነሽ እንኳንስ ዘምቦብሽ ሊያሰኛት ይችላል።

  እናም አስተያየት ሰጭው ነገሩን በደምብ አይተው ቢሰጡ ጥሩ ነው።

  ReplyDelete
 21. ጥሩ ብለሃል ዳኒ!!!!!

  ይህ ጉዳይ እኛ አገር ቢመጣ እኮ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ብቻ አይደሉም የተሰጣቸውን የትምህረት ደረጃ (ዲግሪ፣ ማስተርስ….) የሚመልሱት ዘፋኞቻችንም ዘፈኖቻቸውን ይመልሱ ነበር፡፡ዘፋኞች ግጥሞችን ከገጣሚያን ከፍ ባለ ገንዘብ ይገዙና ልክ እንደራሳቸው ግጥም በራሳቸው ስም ግጥም እና ዜማ እገሌ ብለው የራሳቸውን ስም ያወጣሉ…..የሚገርመው እኮ ዘፋኞች ብቻ አይደሉም ግጥም የሚገዙት አገሪቷ አሉኝ የምትላቸው ገጣሚያንም ጭምር እንጂ…..እኔ እንኳን በቅርበት ከማውቀው ገጣሚ ይወስዱና የማውቀውን ግጥም በሌላ ሰው ስም ወጥቶ አየዋለሁ……አሁን እንደው ማን ይሙት እስከዛሬ ግጥም እና ዜማ ደርሰው የማያውቁት ዘፋኞቻችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሲዲያቸው መሸፈኛ ላይ ግጥም እኛ ዜማ ብለው የራሳቸውን ስም የሚጽፉት በሰላም ነው ትላላችሁ? እንደው ደረሱ እንኳን ቢባል ሙሉውን?…….ይሉኝታ የሚባል ነገር እንኴን የለም እንዴ?.....ታድያ እንኳን ጀርመን አልሆናችሁ አያሰኝም ዳኒ?

  ሀሪ ከአዲስ

  ReplyDelete
 22. @Anonymous-ፈጠራ ይሉሃል ይሄ ነው። በደምብ እንከታተለውና እያንዳንዳችን ራሳችንን እንፈትሽ።
  http://www.youtube.com/watch?v=jMp0GqeD5e0&feature=player_embedded

  ይህን ልጅ መጠቀም ቢቻል አገራችን የት ትደርስ ይሆን? ይህ ልጅ ሌላ አገር ቢወለድ እስካሁን ስንቱን ተጠቅመውበት ይሆን። አሁንም አልረፈደም እንደ አይናችን ብሌን ተንከባክበን ብዙ ነገሮችን ከእሱ ማግኘት እንችላለን። ካልሆነ እንደ ሳይንቲስት ቅጣው የሌሎች አገራት መጠቀሚያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚፈለስፋቸው ስራዎች ተቋማዊ አድርገው አድበሳብሰው ሊያስቀሩበት ይችላሉ። ስለዚህ ካለፈው እንማር

  ReplyDelete
 23. Dani

  ychi enkua antenim timeleketalech. Be carful.

  ReplyDelete
 24. የኛን ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ማን ይተንፍስልን ። ጊዜ ነው እንጂ ሁሉም ነገር እማ ተደፋፍኖ አይቀርም
  ላሜዳ ከአአ

  ReplyDelete
 25. Dear Dani,
  I hope all is well with you. This comment is probably too little too late for the article above but as the saying goes “better late than never" I decided to send you this message. In my humble opinion, your writings have a unique style that is not seen before among our writers and historians. It brings the core idea to life by using different styles from satires and irony to direct quotation and fictional presentations. All these without loosing track of the original idea, narrating it in a beautiful flow that would carry the reader in a great anticipation up until the last word. In addition, you have a unique role and place in our beloved church (አምላከ ቀዱሳን ያስፈፅምሕ) As a result of this; you have earned a place among its great intellectuals, spiritual leaders, social commentators, thinkers, historians and philosophers of our Ethiopian society. For this, it is just enough to site recent examples of your appearances in major Ethiopian local media during various holidays to explain the significance of the holiday from the Ethiopian Orthodox Tewahdo church perspective. This brought to my mind growing up listening to the late አለቃ አያሌው ታምሩ on major religious holidays on Ethiopian radio
  ( በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተተኩልሽ እንዲል መፃፍ)
  The Ethiopian intellectuals agreed to give a unique name for our beloved writer Laureate Tsgeay G/Medigin's style of poem as it can’t be categorized on the most common poetic styles of Ethiopian literature calling it “የፀጋዬ ቤት”. I am for one, hoping someone would study your style of writing more and classify it as “የዳኤል ቤት” or something in recognition of your contribution to modern Ethiopian literature and thought.

  My comment is directly related to the core idea of the article above i.e. plagiarism. Few weeks ago I was listening to your recorded sermons. On couple of occasions you failed to mention, at least, just in a single sentence, that you borrowed the idea and some of it word for word including the examples cited and even the title of the sermons and the bible verses. The sermons in question are “የስው ልጅ ድሕነት በቅጽበት ውይስ በሂደት” (posted on www.tewahedo.org) which mirrors H.H. Pope Shenouda III book “The Heresy of Salvation in a Moment” and ‘ደቀ መዝሙርነት” (sold in a compilation 10 of your sermons from MK under the title ድምፀ ተዋሕዶ) which mirrors the book by His Holiness entitled “Discipleship”. I listened to both sermons to make sure that I didn’t miss out the citation but that didn’t happed. I don’t know whether citation of the original author of the sermons was not appropriate under the circumstances involved or we don’t need to do that for religious teachings as they all are inspired by the Holly Spirit. If that is the case I would love to hear back from you. If your sermon makes me think one of your articles about plagiarism under the title: ሚኒስትሩ ሰርቀው about the defense minister of Germany, I thought you should know about it.
  “በተራራ ላይ የተሰራች ከተማ ልተደበቅ አይቻላትምና”
  Sincerely,
  Mulugeta Mulatu Woldetsadik
  Courtenay, Vancouver Island, Canada

  ReplyDelete