Saturday, February 5, 2011

ለማጠቃለያ - ሦስት ነገሮች ብቻ


የትዳር ጉዳይ በዚህ የጡመራ መድረክ ከተነሣ በኋላ 35አሳዛኝ ታሪኮች በጽሑፍ ሃያ ሁለት ደግሞ በስልክ ደርሰውኛል፡፡ አንዳንድ ከጋብቻ ማማከር ጋር የተያያዘ አገልግሎት ያላቸው ወንድሞች እና እኅቶችም ገጠመኞቻቸውን እና የመፍትሔ ሃሳቦቻቸውን አጫውተውኛል፡፡

ሁሉንም በዚህ መድረክ ለማቅረብ ቦታ እና ጊዜ ይጠብበናል፡፡ ወደፊት ግን ጋብቻን እና ፈተናዎቹን በተመለከተ ልዩ ልዩ አካላት የተሳተፉበት መድረክ እንደሚያስፈልግ ሁኔታው ይጠቁማል፡፡ ይህ ውይይት ከተደረገ በኋላ ተጋጭተው ወደ ወንድሞች ጋር ለሽምግልና የመጡ ባል እና ሚስት ነበሩ፡፡ ሚስት አይሆንም እያለች የለም ታረቁ ታረቁ ተብለው ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ማታ ባል ሚስቱን በሽጉጥ ገደላት፡፡ እናም ነገሮች ከምንገምተው በላይ ሥር እየሰደዱ መሆኑን እያመለከቱን ይመስለኛል፡፡

እኔ በዚህ የማጠቃለያ ጽሑፍ ሦስት ነገሮች ብቻ አቀርባለሁ፡፡

1/ ጋብቻ መልካም ብቻ ነውን?

ብዙ ጊዜ ስለ ጋብቻ የሚነገሩ ነገሮች ክፉውን ወይንም በጎ ገጽታውን ብቻ የሚያመ ለክቱ ናቸው፡፡ መጋባትን መወሰን እና ለመጋባት ዝግጁ መሆን በራሱ አዎንታዊ ርምጃ እና ውሳኔ ነው፡፡ ተጋብቶ መኖር ግን መልካም ብቻ ሳይሆን አሉታዊ ገጽታዎችም አሉት፡፡

ጋብቻ የሌላን ሰው ጠባይ መልመድ እና መቻልን ይጠይቃል፡፡ የሌላኛው ጠባይ እስኪ ታረም መቻል እና መታገሥን ይጠይቃል፡፡ ከማያውቁት እና ካልለመዱት ሌላኛው ቤተሰብ ጋር ተስማምቶ መኖርን ይፈልጋል፡፡

ትዳር እንደ ማር የሚጣፍጥበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ እንደ እሬት የሚመርበት ጊዜም አለ፡፡ አንዲት ባለ ትዳር እኅት ባልዋን «እንደ እርሱ የምወድደውም ሆነ የምጠላው ሰው የለም» ስትል የገለጠችው እውነት የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ የትዳር አጋርን በሰላሙ ጊዜ የምንወድደውን ያህል አንዳች ነገር ሲያጋጥመን በሌላው ሰው ላይ የማይኖረን ንዴት፣ ኩርፊያ እና ጥላቻ በእርሱ ላይ ይኖረናል፡፡ ሌላው ሰው ቢያደርገው የማይገርመን ነገር በአጋራችን ላይ ሲሆን ያቆስለናል፡፡

እንኳን አገባሁ የምንልበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ ምነው ባላገባሁ የምንልበት ጊዜ ያጋጥማል፡፡ ሳይለያዩ ሁለት ሦስት ቀን የሚዋልበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ ተኳርፎ ሳይነጋገሩ ሁለት ሦስት ቀን የሚያልፍበት አጋጣሚም ይመጣል፡፡ ለመጎራረስ የምንሽቀዳደምበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ የተዘጋጀውን ምግብ የሚበላ ጠፍቶ ማዕድ እንደ ተዘረጋ የሚያድርበት ሰዓት ይኖራል፡፡

ዋናው ችግር የእነዚህ ነገሮች መከሰት አይደለም፡፡ ፍጹማን አይደለንምና ሊከሰቱ ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን እንዴት ነው የምንፈታቸው? ነው፡፡

ጋብቻ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ተጋድሎም ነው፡፡ አንድ መነኩሴ በገዳም ገብቶ በበኣት እንደሚጋደለው ሁሉ አንድ ባለ ትዳርም ጋብቻ በሚባል ገዳም ገብቶ ትዳር በሚባል ዋሻ ውስጥ በኣት አጽንቶ ይጋደላል፡፡ ጋብቻ የመኖርያ ብቻ ሳይሆን የመጋደያ መስክም ነው፡፡ የአንድ መነኩሴ ዋናው ፈተና ከበኣቱ የመውጣት ፈተና ነው፡፡ ስለሆነም መጻሕፍት ሁሉ «አጽንዖ በኣት»ን ይመክራሉ፡፡ ለአንድ ባለ ትዳርም ከባዱ ፈተና ትዳር ከሚባለው በኣቱ የማስወጣት ፈተና ነው፡፡

እናም ባለ ትዳሮች በዚህ የማያቋርጥ የተጋድሎ ጉዞ ውስጥ እያለፉ መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው፡፡ በዚህ ተጋድሎ ውስጥ አራት ዓይነት ፈተናዎች አሉ፡፡ ባል ለሚስት ወይንም ሚስት ለባል፤ ሁለቱም ለትዳራቸው፤ ቤተሰብ ለባል እና ሚስት እንዲሁም ውጫዊው ማኅበረሰብ ለትዳሩ ፈተና ይሆናሉ፡፡

በትዳር ውስጥ አንዱ ለሌላው ፈተና የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ ኢዮብ ከሰይጣን ቀጥሎ የተፈተነው በሚስቱ ነበር፡፡ ኢዮብ ሚስቱን ገሥፆ ተጋድሎውን ቀጠለ እንጂ ሚስቱን ወደ መፍታት አልሄደም፡፡ የሚፈትን ሰው ወድዶ ሳይሆን አስቀድሞ እርሱ ራሱ በፈተናው የወደቀ ሰው ነው፡፡ እናም በመጀመርያ ሊፈረድበት ሳይሆን ሊታዘንለት ይገባል፡፡ ሊጎዳ ሳይሆን ሊረዳ ይገባል፡፡ ሊከስሱት ሳይሆን ሊታገሡት ይገባል፡፡ ዋናው ጥያቄ እስከ መቼ? የሚለው ነው፡፡ ይህንን የሚመልሱት ሕግ፣ ሃይማኖት እና የሰው ዐቅም ናቸው፡፡

የየሀገሩ ሕግጋት የሚደነግጓቸው አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርሰው ፈተና ጣርያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ፈተናዎች አካላዊ እና ሥነ ልቡናዊ አደጋ የሚያስከትሉ፤ የማይቀለበስ ጥፋት የሚያመጡ፤ ነፍስንም እስከ ማሳጣት የሚደርሱ ከሆነ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች ይደነግጋሉ፡፡

የሃይማኖት ሕግጋትም እንደዚሁ፡፡ ሰው ሰውን የት ድረሰስ ሊታገሠው ይግባል? አንድ ሰው ለሌላው ፈተና ሆኖ እንዲቀጥል የሚፈቀድለትስ የት ድረስ ነው? ምን ዓይነት የትዳር ፈተናዎች በትእግሥት ሊታለፉ ይገባል? እነዚህ ነገሮች በአብዛኛው በግልጽ ትምህርት ባይሰጥባቸውም በመጻሕፍት ግን ተደንግገዋል፡፡

ለምሳሌ ፍትሐ ነገሥት ባል ወይንም ሚስት አንዳቸው ለአንዳቸው መገናኘትን ፈጽሞ መከልከል እንደማ ይችሉ ይደነግጋል፡፡ ከሁለት አንዳቸው መገናኘትን ለሌላው ቢከለክሉ ግን ጋብቻው እንደሚፈርስ ያዘዛል /አንቀጽ 24፣941/፡፡ እንደዚሁም አንዱ ከሌላው ተለይቶ ቢሄድ ወሬውም ቢጠፋ፣ የማይመለስበትም ምክንያት ቢኖር ለአምስት ዓመታት ያህል ታግሠው ጋብቻው እንደሚፈርስ ይደነግጋል /ዝኒ ከማሁ፤ አንቀጽ 24፣ 952፣954/፡፡ አንደኛው በሌላኛው ሕይወት ላይ ክፉ የሚያደርግ እና የሌላውን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋልጥ ከሆነ ሌላኛው ወገን ጋብቻውን ሊያፈርሰው ይችላል /አንቀጽ 24፣ 944/፤ ጋብቻውን ከማፍረሱ በፊት ግን መጀመርያ ወደ ንስሐ አባቱ፣ ቀጥሎ ከፍ ወዳለው ካህን፣ ከዚያም ወደ ኤጲስ ቆጶሱ መሄድ አለበት፡፡ በዚህ ሁሉ ተመክሮ አንደኛው ወገን የማይሰማ መሆኑ መረጋገጥ አለበት /አንቀጽ 24፣956/፡፡

ከባል ወይንም ከሚስት ወገን ደንበኛውን የጋብቻ ግንኙነት ለመፈጸም የማያስችል፣ ከጋብቻ በፊት ያልታወቀ አካል በአንደኛው ላይ ቢገኝ ሌላኛው ወገን ፈተናውን እንዲቋቋም አይገደድም /አንቀጽ 24፣946/፡፡

በሌላም በኩል የሰው ዐቅምም ወሳኝ ነው፡፡ ከአስተዳደግ፣ ከትምህርት እና ከመንፈሳዊ ጥንካሬ ደረጃ የሚመነጨው የሰው አቅም ችግሮችን ለመቻል የየራሱ መጠን አለው፡፡ አንዳንዱ ችግሮችን ሁሉ ተቋቁሞ ያልፋል፤ ሌላው በቀላሉ ይሸነፋል፤ አንዳንዱ ምንም ነገር አይበግረውም፣ ሌላው በትንሽ ዕንቅፋት ይወድቃል፡፡ የሚመክሩ እና የሚያስታርቁ ሰዎች ሕግ የሚለውን መንገር ብቻ ሳይሆን ሰው በዐቅሙ ሊያደርገው የሚችለውንም ማቅረብ ይገባቸዋል፡፡ ያለ በለዚያ ደግሞ የሰውዬው ዐቅም የሚያድግበትን ነገር ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

በትዳር ውስጥ ሁለቱም ጋብቻቸውን የሚፈትኑበት ጊዜም አለ፡፡ ጋብቻ የመሠረቱበትን አቁዋም እና ዓላማ ረስተው ሳያውቀየትም ይሁን ዐውቀው የራሳቸውን ጋብቻ ለማፍረስ የሚጥሩበት ጊዜ ያጋጥማል፡፡ ሁለቱም ጉዳያቸውን ከሌላ ሰው ጋር እየመከሩ፤ ሀብት እያሸሹ፣ አንዱ አንዱን ለማጥቃት እየታገሉ፤ ገመዱን በሁለት አቅጣጫ ይጎትቱታል፡፡ ማሸነፋቸውን እንጀ የሚያሸንፉት ራሳቸውን መሆኑን አላወቁትም፡፡ ይሄኔ መልካም መካሪ ካለቸው መንገዳቸውን በደንብ ያሳያቸዋል፡፡ ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ የሌለበት ጦርነት ውስጥ መሆናቸውን ያመለክታቸዋል፡፡ ልብ ሲገዙም እነርሱም ያዩታል፡፡

የቤተሰብ እና የማበረሰቡ ፈተና ብዙ ጊዜ ተነግሮለታልና ይብቃን፡፡

2/ ጋብቻና እና ትምህርት

ሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን አገዘ ጋብቻን በተመለከተ የሚሰጡ ትምህርቶች ሦስት ነገሮችን መያዝ አለባቸው ይላሉ፡፡ የጋብቻን መሠረታዊ ዓላማዎች፣ በጋብቻ ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እና የፈተናዎቹን መፍቻ መንገዶች፡፡ እነዚህም ሰው ወደ ጋብቻ መግባት ያለበት እንዴት ነው? በጋብቻ ውስጥ መኖር ያለበትስ እንዴት ነው? እና ጋብቻውን መቀጠል የማይችለበት መንገድ ቢያጋጥመው ከጋብቻ የመውጫ መንገዱስ እንዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስን ይጠይቃል፡፡

ሰዎች ወደ ጋብቻ ሲገቡ በጋብቻ ምድራዊም ሰማያዊም ዋጋ እንደሚያገኙበት፤ የማይተመን ደስታ እንደሚያገኙበት፣ በዚህ ምድር የተሰጣቸውን ሰዋዊ ኃላፊነት እንደሚወጡበት፣ እንደሚፈተኑበት፣ እንደ ሚያሸንፉበት፣ ዐውቀው መግባት አለባቸው፡፡ ያኛው ወገን ፍጹም ስለሆነ አይደለም ያገቡት፤ ተባብረው ፍጹማን ሊሆኑ እንጂ፡፡ ያኛው ወገን እንከን አልባ ስለሆነ አይደለም ያገቡት፤ ተባብረው እንከኖችን ሊያስወግዱ እንጂ፡፡

ሰው መኖር ያለበት በተምኔት ሳይሆን በእውነት ነው፡፡ ርግጠኛውን ነገር ተቀብሎ እንጂ ያልሆነውን ነገር እንደሆነ አድርጎ መኖር የለበትም፡፡ መከራ እያለበት ሰላም እንደ ሆነ፤ እየተፈተነ ችግር እንደሌለ፤ እየተሰቃየ ደስተኛ መስሎ አይደለም መኖር ያለበት፡፡ የሆነውን ነገር አምኖ መፍትሔ ነው መፈለግ ያለበት፡፡

አንዳንዶች ከማግባታቸው በፊት ስለ ጋብቻ ክፉ ነገር ከሰሙ ይቅርብን ይላሉ ወይንም ደግሞ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብለው መስማትም ለመስማትም አይፈልጉም፡፡ ትዳር እንደ ዚህ ከሆነ አናገባም የሚሉትም ፈሪዎች እና ምንም ዓይነት ፈታናን ለመቋቋም የማይፈልጉት ናቸው፡፡ ፈተና እንደሆነ አገቡም አላገቡም የማይቀር ነው፡፡ ነገር ግን ውጊያ የማይቀር ከሆነ በሕግ በሥርዓት እንዋጋ ወይስ ያለ ሕግ ያለ ሥርዓት እንዋጋ? ነው ጥያቄው፡፡

ምንም ነገር መስማት አንፈልግም የሚሉት ደግሞ በጭፍን ፍቅር ወይንም ስሜት ጭልጥ ብለው ለመግባት የተዘጋጁ ናቸው፡፡ እነዚህ ድንጉጦች ናቸው፡፡ በኋላ በሚያጋጥማቸው ነገር ይደናገጣሉ፡፡ ለፍቺም ይቸኩላሉ፡፡

የሚያዋጣው እርግጡን ዐውቆ ተዘጋጅቶ መግባት ነው፡፡ ይህ ዕውቀት የምናገባውን ሰው ከመምረጥ ጀምሮ እንድንጠነቀቅ ያደርገናል፡፡ አብሮን የሚፈተነውና አብሮን የሚያሸንፈው ማነው? ወንዶች ሁሉ ባል፣ ሴቶች ሁሉስ ሚስት መሆን ይችላሉ? መዋደድ ብቻውን መጋባትን ማምጣት ይችላል? ከጋብቻ በፊት ምን ዓይነት ውይይት፣ ምን ዓይነትስ ትውውቅ መደረግ አለበት?  እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች መመለስ የሚቻለው ስለ ጋብቻ አስቀድመን የተገነዘበን ከሆነ ብቻ ነው፡፡

በጋብቻ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች እንዴት መፈታትስ አለባቸው? የትዳር ጸሎት፣ የትዳር ውይይት፣ የትዳር አማካሪ፣ ለትዳር ያላቸው ጠቀሜታስ? ጓደኞቻችን፣ ቤተሰቦቻችን በትዳር ውስጥ ያላቸው ቦታስ? እነዚህ ነገሮች መታወቃቸው እና መወሰናቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

የትዳር ውይይቶች በትዳር ወስጥ ችግር ሲፈጠር ብቻ ሳይሆን በየጊዜው እና በታወቀ ቦታ እና ሰዓት ቢደረጉ መልካም ነው፡፡ ችግር ሲፈጠር የሚደረጉ ውይይቶች ችግሩን ብቻ ፈትተው ያበቃሉ እንጂ ሌላ እንዳይመጣ አያደርጉም፡፡ በየጊዜው የሚደረጉ ውይ ይቶች ግን ያለፈውንም ፈትተው ለሌሎች ችግሮችም መንገድ ይዘጋሉ፡፡ ለውይይት ግን ልምድ እና ትዕግሥት ይጠይቃል፡፡ መወያየት ማለት መጨቃጨቅ አይደለም፡፡ መነ ታረክም አይደለም፡፡ በሥነ ሥርዓት በጉዳዮች ላይ መነጋገር ማለት እንጂ፡፡ እንዲ ያውም በሆኑ ነገሮች ላይ ከመነጋገር በሃሳቦች እና በጉዳዮች ላይ መወያየቱ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ በሆኑ ነገሮች ላይ መወያየት ብዙ ጊዜ ማነው ጥፋተኛ) የሚለውን ስለሚያመጣ፡፡

ጋብቻን ይበልጥ የሠመረ ለማድረግ በራስ ብቻ የማይቻል ከሆነ አማካሪዎችን መጠቀምም መልካም ነው፡፡ በዕውቀት፣ በመንፈስ እና በልምድ ከኛ የተሻሉ አራቱ ጠባያት የረጉላቸውን ሰዎች ለጋብቻችን አማካሪዎች አድርገን ብንጠቀም ታላቅ እገዛ እናገኛለን፡፡ ሰው በጠባዩ የሚያቅቱት ነገሮች አሉ፡፡ ላንዱ ያልተቻለው ለሌላው ይቻላል፡፡ አንዳንዴ አማካሪዎችን መጠቀም ምሥጢር እንደማውጣት ተደርጎ የሚነወርበት ጊዜ አለ፡፡ ችግሩን የሚከላከለው አለ መጠቀም አይደለም፤ ምሥጢር ጠባቂዎችን መምረጥ እንጂ፡፡

የመልካም ሰው ኅሊና ዳኛ ይፈልጋል፡፡ በጋብቻ ውስጥ እነዚህን ዳኞች መምረጡ እና በፈቃዳችን ሃሳባቸውን ሰምተን መመራቱ የፈተናውን ፆር ያቀልልናል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የአንዳንድ ጓደኞ ቻችንን የፈረሰ ትዳር ከመፍረሱ እና ችገሩ ከመባባሱ በፊት ደርሰን ቢሆን ኖሮ አንዳች ለውጥ እናመጣ ነበር ብለን የምንቆጭበት ጊዜ አለ፡፡ በኋላ የሚመጡ ምክሮች እና ውይይቶች፣ ማስታረቆች እና ሽምግልናዎች ሁሉ ቀድመው መጥተው፣ ከዚህም በላይ በየጊዜው ተደርገው ቢሆን ኖሮ መልካም ፍሬ ባፈሩ ነበር፡፡

ከበደ ሚካኤል ከጻፉዋቸው ግጥሞች አንዱ ጽጌረዳ እና ደመና ይላል፡፡ በፀሐይ የነደደች ጽጌረዳ ደመና በላይዋ ሲያልፍ እባክህ የዝናብ ጠብታ ጣልልኝ፤ በድርቀት ልሞት ነው አለችው፡፡ እርሱ ግን ጊዜ የለኝም ብሎ ሄደ፡፡ ሲመለስ ጽጌረዳዋ ደርቃለች፡፡ እንደደረሰ የዝናሙን መዓት አፈሰሰው፤ ግን ደርቃለችና ልታለመልም አልቻለችም፡፡ እንዲያውም ጎርፍ ሆኖ ወሰዳት፡፡

በትዳርም እንደዚሁ ነው፡፡ በየጊዜው የሚሰጥ ምክር እና ማስታረቅ፣ እገዛ እና ተግሣጽ ያለመልመው የነበረውን ትዳር በስተመጨረሻ የሚመጣው የሽማግሌ፣ የጓደኛ፣ የአስታራቂ እና የቤተሰብ ጎርፍ አይመል ሰውም፡፡ ነቅሎ ይወስደው ካልሆነ በቀር፡፡ አንዳንዴ የምን ደርሰው መድረስ ካለብን ሰዓት በጣም ዘግይተን ነው፡፡

3/ የመውጫ መንገዱ

በዚህም ተብሎ በዚያ ትዳሩ አልሆነም እንበል፡፡ ምን ይደረግ?

አንዳንድ ጊዜ በትዳር የመጨረሻ ሰዓታት እንደርስና ዓላማችን ችግሩን መፍታት ሳይሆን ማስታረቅ ብቻ ይሆናል፡፡ ተው፣ ተው፣ ታረቁ፣ ታረቁ፣ በቃ ተዪው፣ ተዋት ይባላል፡፡ የሽማግሌዎቹም ዓላማ ቶሎ ብለው ወደ ቤታቸው መመለስ ነው፡፡ ይህ ግን ችግርን ማዳፈን እንጂ መፍታት አይደለም፡፡ ትዳሩን የሚያጸናው ሰንኮፉን መንቀል እንጂ ማስታረቅ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይማ አንደኛው ወገን ታጋሽ፣ ሰሚ እና አሺ ባይ ከሆነ እርሱን ተጭነን እሺ ማሰኘት ችግሩን መፍታት ይመስለናል፡፡ ግን አይደለም፡፡

መጀመርያ ሰውን እንስማ፤ እንረዳ፣ የችግሩን ምንጭ እንፈልግ፣ ከቻልን ሥሩን እንን ቀለው፡፡ ምናልባት ችግሩን እስክንደርስበት እና እስክንፈታው ጊዜ ካስፈለገን እንኳን የማይጸና ዕርቅ ከምናወርድ ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጥተን ችግሩን እናብርድ፡፡ ለምሳሌ ለተወሰነ ጊዜ ተለያይቶ መቆየት፣ በቤታቸው ውስጥ ሁለቱም የሚያምኑት ሰው እንዲ ኖር ማድረግ፤ የችግሩ መነሻ ነው የተባለውን ነገር ማገድ፣ የችግሩ መነሻ ሌላ ሰው ከሆነ ያንን ሰው ራቅ አድርጎ ማቆየት፤ ወዘተ፡፡

የጋብቻን ችግሮች በምንፈታበት የመጨረሻው ሰዓት ላይ የመጀመርያው ጥንቃቄ መደ ረግ ያለበት አካላዊ አደጋን መከላከል እና አንደኛው ወገን የማይቀለበስ ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ ማድረግ ነው፡፡ በሰላም ከቤቷ ወጥታ ራስዋን ያዳነችውን ሚስት በእጅ በእግር ብሎ ወደ ቤቷ በማስገባት ለችግር መዳረግ ሲያፀፀት የሚኖር መከራ ያመጣል፡፡ አንደኛው ወገን ሀብት እንዲያሸሽ፣ የራሱን መንገድ እንዲያመቻች ዕድል የሚከፍትን መፍትሔ መስጠት በሌላኛው ወገን ቂም ያረገዘ ጥላቻን ያስከትላል፡፡

ይህ ሁሉ ተደርጎ የማይቻል ከሆነ ጉዳት ሳይከተል፤ ልጆች ለተጨማሪ መከራ ሳይዳረጉ፣ ቤተሰብ ቂም ሳይያያዝ፣ ከጋብቻ ወደ ጥላቻ ሳንጓዝ በሰላም መለያየት ነው፡፡ እምነታችን፣ ሕጋችን፣ ባህላችን እና በጎ ልማዶቻችን ያስተማሩንን ተጠቅመን በፍቅር እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መለያየት ነው፡፡

ምናልባት አንድ ቀን ልባችን ይመለሳል፣ በልጆቻችን አማካኝነት ተገናኝተን መልሰን እንታረቅ ይሆናል፡፡ ወይንም ደግሞ በሌላ ጋብቻም ኖረን እኅት ወንድም ሆነን እንቀጥላለን፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚያመቻቸው ግን ያለ ቂም በቀል በሰላም መለያየቱ ነው፡፡ መጋደለን፣ መደባደበን፣ መጠቃቃትን፣ መነጣጠቅን ምን አመጣው? በሕግ ወንጀል ሠርተን፣ በሃይማኖት ኃጢአት ውስጥ ገብተን፣ በባህል ነውር ውስጥ ተዘፍቀን ስንፀፀት እና ስንወገዝ ከመኖር በሰላም መሰነባበት፡፡

ማኅበረሰባችን ፍቺን ማውገዙ፣ አለማበረታታቱ እና አለመቀበሉ መልካም ነው፡፡ ግን ይህ ነገር ከረር እያለ ከሄደ ሰዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ የማይሆን ርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌላኛውን ወገን ማሳጣት፣ የሌላኛውን ወገን ኃጢአት ማውራት፣ ራስን ነጻ ለማድረግ የሚያስችሉ የብልጣብልጥ መንገዶችን መጠቀም፤ ከሀገር ጥሎ መውጣት ወዘተ፡፡

አንዳንዴም ተስፋ ከመቁረጥ እና የሚኖረውን ጫና ለመቋቋም ካለመቻል የጭካኔ ርምጃዎችንም ወደ መውሰድ ይጋዳረጋሉ፡፡ ሁሉም ሰው «ተው ተው» ብቻ ሲላቸው የሚረዳን የለም ብለው ጉዳዩን ለሽምግልና ወደሚያስቸግር ደረጃ ያደርሱታል፡፡ መደባደብ፣ መጋደል፣ መካሰስ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈጸም፤ ወደ ሌላ ወገን መሄድ፣ እምነትን መቀየር፣ የመሳሰሉት የሚከሰቱት በዚህ ጊዜ ነው፡፡

የጋብቻ መፍረስ ያጋጠማቸውን ወገኖች ከመረዳት እና ከመርዳት መጀመር አለብን፡፡ ከመውቀስ እና ከመክሰሳችን በፊት፡፡ እኛ ራሳችንስ በዚያ ውስጥ ብንኖር እንችለው ነበር? ብለንም መጠየቅ አለብን፡፡ ከእነርሱ ሕይወትም ትምህርት መቅሰም አለብን፡፡

የጋብቻ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ አያልቅም፡፡ ወደፊት በየራሱ አንዳንዱን ጉዳይ እያነሣን እንወያያለን፡፡ ለዛሬ ግን እባካችሁ

ስለ ጋብቻ ዓላማ እና ፈተና አስቀድመን ዕንወቅ፤ ዐውቀን እንግባበት፣ በጋብቻ ሆነን ጋብቻን ለማጽናት እንጋደል፤ ለችግሮች ሁሉ በጊዜያቸው መፍትሔ እንስጥ፤ የማይሆን ደረጃ ላይ ከምንደርስ ደግሞ በሰላም ሌላ አደጋ ሳይከተል እንለያይ፡፡

ቻርለስ ደጎል አውሮፕላን ማረፊያ፣ፓሪስ

27 comments:

 1. Dear Dn Daniel

  kalehiwot yasemalin

  The post gives a concrete lesson on how to manage the issue. and it will also gives a relife for those brothers and sisters whom we took their case to come to this discussion.

  Abiot k oldenburg

  ReplyDelete
 2. Dear Dn Danieal

  I was expecting this strong conclusion. Thank you very much. I hope you will prepare one book on marriage, which is supported by cases like USA books.

  ReplyDelete
 3. በጋብቻ ዙሪያ እንዲህ ያለ ተከታታይ ትምህርቶች ቢኖሩ እጅግ ብዙ ሰው ሊጠቀም ይችላል።ብዙ ሰዎች በክርስትናው ውስጥ ጋብቻ የመሰረትን ግን እውቀቱና መንገዱን ለማናቅ እጅግ ይረዳናል እባክህ ተክታታይ የሆነ ጥልቅ እውቀት የሚያስጨብጠንን ትምህርት በቅርቡ ጀምርልን። በጣም ደስ የሚል እውቀት የሚሰጥ ምክር ነው ቃለ ህይወት ያሰማህ።

  ReplyDelete
 4. Dear Dakon Daniel,

  Lets god bless you & all your message are too important and valid not only to improve relationship with two partners (husband & wife, but also to establish and build up better relationship to our relatives, neighbors, friends and e.tc.

  Best regards,

  Temesgen Kassa, Dire Dawa

  ReplyDelete
 5. +++
  በጣም እጅግ አስተማሪ ነው:: የበሽታ ጉዳይ አልተነሳም:: ምናልባት የባለሙያ ምክር ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል::አንድ ጓድኛዬ የገጠመውን እውነተኛ ታሪክ በአጭሩ...ከላይ እና ከዚያ በፊት የተዘረዘሩት ሁሉ ዋና ዋና ዎቹ ነገሮች ገጥመዉታል:: አባቶች ጓድኞች ሁሉ እንዲፋቱ ወስነው ሊፋቱ ስል ጭንቀት ታመመ እና ሐኪም ጋ ሄደ ታሪኩን ተናግሮ ባለቤትህን አምጣ ተብሎ ስትመረመር ውሃ በቀጠነ የሚያስጮህ ሰላም የሚነሳት በአጠቃላይ አንድ መንድማችን ከላይ የገጠመውን የምታደርግ መሆኗን ተነገራቸዉ እሷም ወዲያውኑ መድሃኒት እንድትጀምር ተደረገ እርሱም አውቆ አምኖ እንዲችል በባለሙያም በአባቶችም ተነገረዉ ግን አልቻለም ባይፋቱም እግዚአብሔርን ከ እርሷ የራቀ ሥራ ስጠኝ ብሎ ሌት ቀን መማጸን ጀመረ እግዚአብሔርም ፈጸመለት የውጭ ሥራ አግኝቶ ሄደ በሰላም እየኖርኩነዉ አለን:: በ6ወር 14 ቀናት ብቻ ልጆችን አጫዉቶ ይመለሳል:: ስላደረገለት ሁሉ እግዚአብሔር :: ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማገኝት Hyperthyroidism or Superthyrodism በማለት ጠይቅ ብዙ ሃሳብ ታገኛለህ ወይም ሃሳቡን ከአወከው ማውጣቱ ጥሩ ነው እላለሁ::

  ከዝዋይ

  ReplyDelete
 6. Quite a conclusion!I hope more is coming under similar topics.For now have bon voyage, wherever you are heading!
  Mulugeta(Vancouver)

  ReplyDelete
 7. EJEG BETAM TERU MATEKALEYA NEW WENDEMACHEN EDME YESTELEEN. KEZIH BEFIT ANDAND ASTEYAYETOCHEN ANBEBE NEBER ANTE MENFESAWI SEW ENDEMEHONEH ENDIH AYENET MEKER MESTET EMDELELEBEH YETESETU MALET NEW ERGETEGNA NEGN ENEZIH ASTEYAYET TDECHIWOCH ESKEEZAREW MATEKALEYA DERES KETEKETATELUT NEGEROCHEN BEAND AKETACHA BECHA SAYEHONE BETELEYAYE MENGED MAGENAZEB ENDALEBACHEW YEREDALU BEYE AMENALEHU.

  ReplyDelete
 8. Really nice conclusion. Thank you Dn. dani. Its from the Holy spirit. Its the last solution from the very beginning of marriage life. Bewunet Kale Hiwotn Yasemaln.

  ReplyDelete
 9. Dear DAKON DANIAL

  Kalehiwot yasemalen

  I don't have any word. you prevent my life thank you very much. I hope you will post more

  San Francisco

  ReplyDelete
 10. Dear DAKON DANIAL

  Kalehiwot Yasemalen!!

  A great-full conclusion! Great lesson!

  ReplyDelete
 11. Thank u!! Dakon Daniel it is a very interesting idea, that will help to learn more for all married couples now and then how to react and solve problems through out our life.
  DM

  ReplyDelete
 12. Generally i can say its a good conclusion but as the topic is very delicate(because it involves both logical thinking and emotion) it needs to be dealt in much depth once it's started. otherwise it will end up giving the wrong lesson to most people. For eg the things u mentioned from feteha negest...weren't as such discussed in public previously and may be the only thing mostly told is that u can get divorced when only one dies or go after another. but now if this kind of details r coming, its good to know, but needs to be dealt in a really deep way one by one and case by case rather than being mentioned as an example. Otherwise most probably everyone is gonna use his/her own subjective judgment which leads to a wrong interpretation and result of the right purpose u raise this idea for. Therefore better if u can go deep so fast, because i believe u have the potential . Thanx for all.

  ReplyDelete
 13. የጽኁፉን መልእክት በማድነቅ ብቻ ለውጥ አይመጣም ዋናው ነገር ምክሩን ወደ ተግባር መቀየር ይጠበቅብናል፡፡

  ዳኒ ተባረክ
  አቤል

  ReplyDelete
 14. kalehiwot yasemalen ! erasene endayena tedarne madese endalebge betam tesemetogale.

  Dengel Mariam tebrakeh Dn Daniel.

  abraham

  ReplyDelete
 15. rejeme edemiee dear bro!!! i had a good lesson to see deep into myself

  ReplyDelete
 16. Why didnt u post this one on z fbook page?
  I think its worth sharing.

  ReplyDelete
 17. ቀጣይነት ቢኖረው መልካም ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ መወያየት ቢለመድ ጥሩ ነው

  ReplyDelete
 18. it is a very nice advice.
  please continue on related topics also,
  such as what are the things we have to
  take care in pre-marriage relationships and other
  issues in detail

  ReplyDelete
 19. እመቤቴ ኣማላጅዋ ትርዳችሁ ከነልጅዋ
  D. Daniel kibret and other who give a comment in this.

  ReplyDelete
 20. ዳንኤል እግዚያብሔር ይስጥልን፡፡
  ብዙ ነገሮችን ተምሬበታለሁ
  It is a very nice advice. Please continue on related topics also.

  ReplyDelete
 21. e/r ye agelegelot gezehen yebarekew

  ReplyDelete
 22. please write your views on ethics.

  ReplyDelete
 23. dani,this good view realy.it is very important for all people who worrey about marrage.we are lisene alot of negative thing on marrage i think that was stress us for do not marred.
  Wasihun form amircan gibi.

  ReplyDelete
 24. ዳንኤል እግዚአብሄር በሰጠህ ጥበብ(እውቀት) አመስግነው፡፡
  ለብቻው ስለትዳር ብቻ የሚወራ አንድ ክፍል ቢከፈትና ሁሉም ሰው ቢወያይበት መልካም ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሄር ካንተ ጋር ይሁን፡፡ ተባረክ !!!

  ReplyDelete