በጋብቻ ጉዳይ የተነሣውን ጉዳይ እያየሁት ነው፡፡ ችግሩ ካለመዋደድ እና ከችግር የሚመጣ ብቻ አይደለም፡፡ ስለ ጋብቻ ካለው ትምህርት እና ከሚነገረው ጭምር ነው፡፡ ጋብቻ ለምለም ገነት፣ እንከን አልባ ጉዞ፣ የሚያጓጓ ሕይወት ተደርጎ ብቻ ይነገራል፡፡
በውስጡ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች አይነገሩም፡፡ ችግሮችንም እንዴት መፍታት እንደሚቻል ትምህርት አይሰጥም፡፡
ለምሳሌ የኛን ቤት የሚመሩት አንድ ባሕታዊ ናቸው፡፡ ለምሳሌ እኒህ ባሕታዊ ሱባኤ ካዘዙ ሦስት ወር ሆኗቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እኔና ባለቤቴ በአልጋ ከተለያየን ሦስት ወራችን ነው፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ይታይህ፡፡ በሰባቱ አጽዋማት፣ ቅዳሜ እና እሑድ፣ እሷ በምታከብራቸው አሥራ ሁለት በዓላት እንደገና ባሕታዊው በሚያዙት ሱባኤ ምክንያት እኔና ባለቤቴ አብረን ከምናድርበት እርሷ ገዳም የምትዞርበት ጊዜ ይበልጣል፡፡
እንዴት ነው ግን ሰው በየቀኑ ራእይ ያያል እንዴ፡፡ ደግሞስ ሁሉም ሱባኤ ባልና ሚስት ማለያየት ብቻ ነው እንዴ፡፡ ጓደኞቻችን መከሩን፣ የንስሐ አባታችን መከሩን፣ ወላጆቻችን መከሩን፤ እርሷ ግን ከኒያ ባሕታዊ በቀር የምትሰማው የለም፡፡
ልጆቼ እንኳን በሱባኤው ምክንያት ሥጋ እና ዕንቁላል መብላት ካቆሙ ቆዩ፡፡ ለመሆኑ አንድ ባሕታዊ በሚያዘው ሱባኤ አሥር ዓመት ያልሞላቸው ልጆች መጎዳት አለባቸው?
ልመሆኑ ባል እና ሚስት በሁሉም በዓላት እና ሱባኤዎች ሁሉ መለያየት አለባቸው? ፈተናውስ ይቻላል? እኔ በሁለት ነገር እየተፈተንኩ ነው፡፡ በአንድ በኩል ውስጤ ይፈተናል፤ በሌላ በኩል በትዳራችን ሌላ ሰው ማዘዙ ያናድደኛል፡፡ ልክ ነው ባለቤቴ ዝሙት ትፈጽማለች ብዬ አላምንም፡፡ ግን እርሷ ደንበኛውን የባል እና ሚስት ግንኙነትም ትታዋለች፡፡ ታድያ ምን ትላታለህ?
ይኼይስ ከናዝሬት