Saturday, January 22, 2011

ለቤተ መጻሕፍትዎ


የኢትዮጵያ ታሪክ  ከአለቃ ተክለ ኢየሱስ

አዘጋጅ- ሥርግው ገላው (/)
የታተመበት ዘመን- 2002
የገጽ ብዛት- 301
ዋጋ         50

ስለ አዘጋጁ- ሥርግው ገላው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡ በተለይም የግእዝ ቅኔያትን በማሰባሰብ እና በማሳተም፣ የግእዝን መዝገበ ቃላትን እና ክብረ ነገሥትን በአማርኛ በማዘጋጀት፣ ይታወቃሉ፡፡
አለቃ ተክለ ኢየሱስ- 1864 ዓም አካባቢ ምሥራቅ ወለጋ ኩታይ ውስጥ የተወለደው አለቃ ተክለ ኢየሱስ አባቱ ዋቅጅራ እናቱ ገላኔ ይባላሉ፡፡ ወለጋ ተወልዶ ጎጃም ያደገው ተክለ ኢየሱስ የቤተ ክህነቱን ትምህርት ተምሮ የገናዢ ማርያም ዲያቆን ሆነ፡፡ ይበልጥ የሚታወቀው ግን በሠዓሊነቱ እና በታሪክ ጸሐፊነቱ ነው፡፡
አለቃ ተክለ ኢየሱስ የዲማን፣ የደብረ ማርቆስን፣ የደብረ ዘይትን፣ የጥያሜን፣ የደልማ አማኑኤልን፣ አብያተ ክርስቲያናት በሥዕል አስጊጧል፡፡ በደብረ ማርቆስ የሚገኘውን ወንጌል፤ የንጉሡን ቤተ መንግሥት፣ የራስ ኃይሉን መኖርያ ቤት የሳላቸውም እርሱ ነው፡፡
አለቃ ተክለ ኢየሱስ ከሰዓሊነቱ በተጨማሪ እርሱ «የጎጃም ታሪክ» ብሎ የጻፈውን እና ሥግርው ገላው «የኢትዮጰያ ታሪክ» ብሎ ያሳተመውን ድንቅ የታሪክ መጽሐፍ ጽፎልናል፡፡ በተለይም በቃል ብቻ ይተላለፉ የነበሩትን፣ እርሱ ከልዩ ልዩ መዛግብት ያገኛቸውን እና በዘመኑም በዓይኑ ያያቸውን በሰፊው አሥፍሯል፡፡
በአፃፃፉ ላይ ሰዓሊነቱ ይነበባል፡፡ ነገሮችን ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ሲገልጻቸው በቦታው ተገኝተን ያየናቸው ያስመስላቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በዘመኑ ለነበረው ሥነ ቃል ትኩረት በመስጠት እረኞች፣ ወንዝ ወራጆች፣ አልቃሾች፣ ገበሬዎች፣ መንገደኞች ወዘተ የገጠሟቸውን ግጥሞች መዝግቦ አቆይቶልናል፡፡
አለቃ ተክለ ኢየሱስ ይህንን መጽሐፍ ከጻፈልን ከሦስት እና አራት ዓመታት በኋላ 1917 እስከ 20 ባለው ዘመን መካከል እንዳረፈ ይገመታል፡፡
በዘመኑ የነበረውን ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ የፖለቲካ ሥርዓት እና የሀገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ ለማወቅ የፈለገ ሰው የአለቃ ተክለ ኢየሱስ መጽሐፍ አንዱ ምንጭ ነው፡፡ ተክለ ኢየሱስ ታሪኩን ሲጽፍ ከደሴተ ዝዋይ፣ ከዘጌ ገዳማት፣ ከናርጋ ሥላሴ እና ከደቅ እስጢፋኖስ ከተገኙ የታሪከ ነገሥት መጻሕፍት ቀድቷል፡፡ የኦሮሞን አፈ ታሪክ ከአለቃ ዐፅሜ፤ የዐፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ከደብተራ ዘነብ እና ከአለቃ ወልደ ማርያም፣ የዐፄ ዮሐንስን ታሪክ ከሊቄ መርዐዊ እያገኘ ጽፏል፡፡
የጎጃምን ታሪክ እና የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ታሪክ ከአለቃ ብሩ፤ በዘመኑም ከነበሩት ከራስ ደስታ፣ ከደጃች ተድላ ጓሉ እና ከሌሎች መሳፍንት ወስዷል፡፡ በዘመኑ ከነበሩት ሽማግሌዎች እየጠየቀ መረዳቱን «ከአሮጌ ልጅ ወገኛ፣ ከጀግና ልጅ አርበኛ፣ ዘምቶ ከአረጀ፣ በልቶ ካፈጀ እየጠየቀ ከቀዳማዊ ራስ ኀይሉ እስከ ዳግማዊ ራስ ኀይሉ ድረስ በእውነት እንበለ ሐሰት፣ ውዳሴ ከንቱ ሳይጨምር ታሪክ ጻፈ» ይላል፡፡
መልካም ንባብ
 

5 comments:

 1. ጸጋውን ጌታ ያብዛልህ፡ ስለ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዛሬ ገና ነው ያነበብኩት። እንደሳችው ያሉትን በዚህ ዘመንንም ከተለያዩ የአገርቱ ክፍሎች አምላክ ስለሚያስነሳ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

  ReplyDelete
 2. you are the special one!!!!!

  ReplyDelete
 3. ጤና ይስጥልኝ ዳኒ እንደምን አለህ!የመፃህፍት ጥቆማዎችህን እወዳቸዋለሁ።ለዛሬ ስለ አንድ መፅሀፍ ያለህን አስተያየት ልጠይቅህ ወደድኩ።መፅሀፉ የ Grham Hankok 'the sign and the seal' ወይም ታቦተ ፅዮንን ፍለጋ' የሚባለዉ ነዉ።ይሄ መፅሀፍ ታቦተ ፅዮን ስለምትገኝበት ቦታ ጥናት ለማድረግ በተነሳ ሰዉ እንደተፃፈ ይታወቃል።በርግጥ ፀሀፊዉ ታቦተ ፅዮን ኢትዮጲያ እንደምትገኝ ቢቀበልም ስለ አመጣጡ ያቀረበዉ ንድፈ ሀሳብ ክብረ ነገስት ላይ ካለዉ የተለየ ነዉ።በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ብዙ የታሪክ ተመራማሪዎች ለምሳሌ እንደ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኡለንዶርፍ ያሉት መፅሀፉን ቢያጣጥሉትም እኔ በበኩሌ ግን እጅግ የመሰጡኝ ነጥቦች በመፀሀፉ ዉስጥ አግንቻለሁ።(it is my all time best book!) በእርግጥ ግርሀም ካቀረባቸዉ በርካታ መላ ምቶች ዉስጥ አንዳንዶቹ ባይስማሙኝም (እንደ አንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ እና እንደ አንድ ተራ አንባቢ፥) በተለይ በመካከለኛዉ ዘመን፣ በ14 ኛዉ፤ በ15ኛዉ እና በ16ተኛዉ መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ሀገራችንን ስለ ጎበኙት የዉጪ ዜጎች (like James Bruce and christopher Da Gama) ድብቅ አላማ የገለፀበት ክፍል እጅግ አስገርሞኛል። ዳኒ መቼም ብዙ ምንጮች እንዳሉህ እገምታለሁ እና በተለይ ስለ ጀምስ ብሩስ ጉብኝት የምታዉቀዉን እና በጥቅሉ ስለ ግርሀም መፀሀፍ ያለህን አስተያየት እንድታካፍለን በትህትና ልጠይቅህ።

  ReplyDelete
 4. SELAM LANTE YIHUN DANI YEMITITOKIMEN METSAF BETAM TIRU NEW. LEHITSANAT YEMIHON METSAF (SILE ETHIOPIA HISTORY) KAL NIGEREN KELELE GIN BITITSIFILIN... THANKS!

  ReplyDelete