Monday, January 17, 2011

አይጧ


ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ማኅበር ጽ/ቤት የተፈጸመ ታሪክ ነው፡፡ እንዲህ ልንገራችሁ፡፡

በዚህ ማኅበር ጽ/ቤት ውስጥ በጽዳት ሠራተኛነት የምትሠራ እኔ ለጊዜው ስሟን ራሔል ብዬ የምጠራት ልጅ አለች፡፡ ሲፈጥራት አይጥ የሚባል ነገር ትጠላለች አሉ፡፡ ምን እርሷ ብቻ ብዙዎቻችን ስለ አይጥ እየተነገረን ካደግነው ተረት እና ምሳሌ አንፃር ነው መሰል አይጥን ማየት እና መንካት ቀርቶ ማሰብም ይከብደናል፡፡

መቼም እንጀራ የማይጥለው ነገር የለም፡፡ የወደዱትን አስትቶ የጠሉትን ያስይዛል፤ በሚያናድደው አስቆ፣ በሚያስቀው ያስለቅሳል፡፡ ደግሞ በኛ ሀገር የሰዎችን ሥነ ልቡናዊ የኋላ ጫና እና አመለካከት ተረድቶ ከሥራቸው ጋር ማጣጣም የሚባል ነገር እምብዛም አልተለመደም፡፡ በአንዳንድ የሠለጠኑ ሀገሮች እንዲህ ለማድረግ ባህሌ አይፈቅድም፣ ሃይማኖቴ ይከለክላል፣ ለዚህ እና ለዚያ አለርጂ ነኝ፣ እንዲህ እና እንዲያ ያለ ነገር ያስደነግጠኛል ብሎ አስቀድሞ መናገር ወይንም በኋላ ማስረዳት ይቻላል፡፡

ባይሆን ችግሩ ሥነ ልቡናዊ ችግር ነው ብለው ካመኑ የሚቀርፉበትን መንገድ አለቆች ይፈጥራሉ፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ ለሠራተኛው የሥራ ደኅንነት በሚያመች መንገድ ያሠማሩታል፡፡

ራሔል ያለችው እዚህ ሀገር ነውና ይህ አልገጠማትም፡፡

ከዕለታት በአንድ ቀን ከምታጸዳቸው ክፍሎች በአንዱ አይጥ ትሞታለች፡፡ መጀመርያ የሚገርመው እዚያ ትልቅ ሕንፃ ውስጥ አይጥ መግባቷ፤ በሰላም ኖራ ወልዳ ከብዳም መሞቷ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እንደታየው ድራማ ድመት ለመግዛት የአሠራር ሂደቱ አላስኬድ ብሎም ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ የስንት ሰዎችን ፋይል በልታ፣ ጠግባ፣ ሞተች፡፡

መቼም የእንጀራ ነገር አንዳንድ ጊዜ አያመጣው የለምና ራሔል አገር ደኅና ነው ብላ ጠዋት ወደ ሥራዋ ስትገባ የአይጧን ሞት አረዷት፡፡ እናትሽ ሞተች የተባለች ያህል ክው ነበር ያለችው፡፡ ያስደነገጣት የአይጧ ትዝታ አይደለም፡፡ አይጧን ከዚያ ቢሮ ውስጥ ማን ያወጣታል? የሚለው ጥያቄ ነው እንጂ፡፡

እንደ ገባች የጽዳት ዕቃዎቿን የምታስቀምጥበት ክፍል ገብታ ጸጥ አለች፡፡ አይጧ እርሷ ክፍል የሞተች ይመስል አሁንም አሁንም ትባንን ጀመር፡፡ አንዳንድ ጊዜም በእጃቸው አንጠልጥለው xM_tW የሚሰጧትም መስሏት መዳፏን በመዳፏ ታራግፋለች፡፡ ጠፍታ ወደ ቤቷ ልትመለስም አሰበች፡፡ ነገር ግን የእንጀራ ገመዷ በመኪና ክር ተንጠልጥላ ታየቻት፡፡

በሯ ተንኳኳ፡፡ አይጧ ራሷ ያንኳኳች መስሏት ነፍሷ ልትወጣ ነበር፡፡ መጀመርያ የበሩን እጄታ ሳይሆን የበሩን የወለል ክፍተት ነበር ያየችው፡፡ አይጧ በዚያ በኩል የምትገባ መስሏት፡፡ «ራሔል» የሚል ጥሪ ሰማች፡፡ አለቃዋ ነው፡፡ ራሔል ደግሞ አይጥ ትጠላለች፣ አለቃ ትፈራለች፡፡ አቤት ብላ ልትመልስ ፈለገ ችና አይጧ በከፈተችው አፏ በኩል ብትገባስ ብላ ፈራችና ዝም አለች፡፡

አለቃዋ መልሶ ተጣራ፡፡ እንደ ምንም «አቤት» አለች፡፡ ከዚያም በሩን ቀስ ብላ ከፈተችው፡፡ መሬት መሬት እያየች፡፡ አሁንም እርሷ አይጥ ነው የምታስሰው፡፡

«እንዲህ አይነት ክፍል ውስጥ አይጥ ሞታለችና በቶሎ አውጫት» አላት አለቃዋ

«እ!» ነፍሷ ጉሮሮዋ ሥር ደርሳ ተመለሰች፡፡

«በአስቸኳይ ትውጣ፤ ቅዳሜ እና እሑድ እዚያ ስለከረመች ሸትታለች»

«እኔ ላወጣት!» አለች በደመ ነፍሷ፡፡

«ታድያ ማን ሊያወጣ ነው፤ በይ ፍጠኝ»

«እኔ አይጥ እፈራለሁ፤ ሌላ ሰው ያውጣልኝና ሌላውን እኔ ልጥረገው»

«እንደዚህ የሚባል አሠራር የለም»

«እኔ ልክፈልና ሌላ ሰው ያውጣት፤ እኔ ያመኛል»

«ትእዛዝ ትእዛዝ ነው» ሄደ አለቃዋ፡፡ እርሷ እና ድንጋጤዋ ብቻ ቀሩ፡፡ ምን ታድርግ? ትሂድ? ነፍሷ እግሯን ያዘቻት፡፡ ትቅር? እንጀራዋ አግሯን ገፋቻት፡፡ ምን ትሁን? እንደ ምንም ወጣችና በአካባቢዋ ያሉትን አንዳንድ የሥራ ባልደረቦቿን ለመነቻቸው፡፡ የራሔልን ፍርሃት ያውቁታል፡፡

እንዲያውም በአርሷ መቀለድ ሲያምራቸው «አይጧ መጣች? ይሏታል፡፡ ከዚያ በኋላ ዓይኗ ከአይጧ በላይ ይፈጥጣል፡፡ አይጥ ከተጠራች ሳትበላ ውላ ታድራለች፡፡

አንዳንዶች ሊረዷት መጡ፡፡ ነገር ግን አለቃዋ የሞተችውን አይጥ ከእርሷ ውጭ ማንም ሊያወጣት እንደማይችል መመርያ ሰጠ፡፡

«ይህ ትዕቢት ነው፤ አለመታዘዝ ነው፤ ሥራን አለማክበር ነው» አለና በአንድምታ ተረጎመው፡፡

ራሔል ከእንጀራዋ ፍርሃቷ በለጠባትና አላወጣትም አለች፡፡

እነሆ የሚከተለው ነገር ሆነ፡፡

የራሔል አለቃ ወደ ቢሮው ገባና የቅጣት ደብዳቤ ጻፈ፡፡

«እንዲህ በተባለው ቢሮ ውስጥ አይጥ ሞታ እያለ፤ አንቺም የጽዳት ሠራተኛ ሆነሽ ተቀጥረሽ እያለ፤ አይጥ እፈራለሁና አላወጣም ብለሽ የማኅበሩን ሥራ በማስተጓጎልሽ ከደመወዝሽ ይህንን ያህል ተቀጥተሻል፡፡ ከዚህ በኋላም ሥራሽን በአግባቡ የማትሠሪ ከሆነ ማኅበሩ አግባብ ነው ያለውን ርምጃ እንደሚወስድ አሳውቃሁ» የሚለው ደብዳቤ ከአይጧ ሸሽታ ክፍሏ ውስጥ ተመልሳ እንደተቀመጠች ደረሳት፡፡

ድሮም ቢሆን አይጥ እንኳን ሞታ በቁሟም ለራሔል አትቀናትም፡፡ «በውሻ ራት ውሻ ቆሞባት፤ ከአባ ቆፈር እርሻ እሸት ተበልቶላት፤ ከመላጣ ፀጉር ለልቅሶ ተነጭቶለት» የሚሉትን የሀገሯን ተረቶች እያስታወሰች አልቅሳ ሌሎችን ቢሮዎች ስታጸዳ ዋለች፡፡

የአይጧም ሬሳ በዚያው በጉድጓዷ እያለ ቤቱ የባለሞያዎች ቤት ነውና ባለሞያዎች ተጠርተው አይጧ እዚያው ጉደጓዷ ውስጥ ብትቀበር የተሻለ መሆኑን በስብሰባ ወሰኑ፡፡ ሲሚንቶ እና ጠጠር መጥቶ፣ በግንበኛም ተቦክቶ፣ እዚያው ቢሮ ውስጥ ተቀብራ በሲሚንቶ መቃብሯ ተሠራላት፡፡ ምናልባትም በታሪክ ውስጥ በቢሮ ውስጥ የተቀበረች የመጀመርያዋ አይጥ እርሷ ልትሆን ትችላለች፡፡ ሌላው ቢቀር ደግሞ በዚያ ገና ባላለቀ ሕንፃ ውስጥ ግብዐተ መሬቷ የተፈጸመ የመጀመርያዋ ፍጡር ተብላ ሕንፃው ሲመረቅ ሊነገርላትም ይችላል፡፡ ራሔል ተጎዳች እንጂ አይጧስ ታድላለች፡፡

የሚገርመው ግን ለሲሚንቶ እና ለጠጠር ብሎም ለግንበኛው ከወጣው ወጭ ሩቡን ብቻ በመክፈል ራሔል የተቀጣችበትን ሥራ በሌላ አካል ከፍሎ ማሠራት ይቻል እንደ ነበር የሚያስበው አለማግኘቱ ነው፡፡

እንዲህ እንደ ራሔል ያለ አይጥ የመፍራት እና የመጥላት ዓይነት ልማድ ከልጅነት የሚቀረጽ እንጂ እንደ ሐዋርያው ታዴዎስ እርሻ ዕለቱን ተዘርቶ፣ ዕለቱን በቅሎ፣ ዕለቱን የሚታጨድ አይደለም፡፡ ስንሰማቸው በኖርናቸው ተረቶች፣ ታሪኮች፣ አባባሎች አማካኝነት ተፀንሶ፤ በባህላችን ውስጥ ነገሮች በያዙት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ቦታ ረዳትነት አድጎ፤ ሌሎች ቀደምቶቻችን ሲያደርጉት ባየነው፣ በቀሰምነው እና በወረስነው የአኗኗር ዘይቤ በኩልም ጎልብቶ ለወግ ለማዕረግ የሚበቃ ነው፡፡

የሀገሬ ሰው «ተፈጥሮን ተመክሮ አይመልሰውም» የሚል ብሂል አለው፡፡ ተፈጥሮ የሚለው የአንድ ሰው የተፈጥሮ ጠባዩ አይደለም፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከሽበት እስከ ኩተት እየያዘው ያደገውና በመጨረሻም የእርሱ መገለጫ እስከ መሆን የደረሰውን መሠረታዊ ጠባዩን ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር በአንድ ምሽት ምክር ብቻ አይለወጥም፤ ተከታታይ የሆነ ሊለውጥ የሚችል ሥራን ይጠይቃል፡፡ «አብሮ የኖረ ሰይጣን በአንድ ሱባኤ አይወጣም» ይባል የለ፡፡

መመሪያዎች፣ ሕጎች እና ደንቦች ሰዎችን የመቀየር ዐቅማቸው ከባህል እና ልማድ አንፃር ሲታዩ አነስተኛ ነው፡፡ ለሕጉ እና ለደንቡ የሚሆን ዜጋ የሚፈጥር ባህል እና የአኗኗር ሥርዓት በሌለበት ሕጉ ብቻውን ከዕውቀት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

በተራ ቅደም ተከተል መስተናገድን አሜሪካውያን ከልጅነታቸው ጀምረው የሚያድጉበት ባህል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ማንኛውም ሕፃን ልጅ የትም ቦታ ሲሄድ ተራውን ጠብቆ ይስተናገዳል እንጂ ልጅ ነኝና ልቅደም አይላችሁም፡፡ ይህ ባህላቸው ሆኗል፡፡ እኛ ሀገር ስትመጡ ደግሞ ተራን ጠብቆ፣ ቅድሚያ ለመጣው ቅድሚያ ሰጥቶ አገልግሎት ማግኘትን ከልጅነታችን ጀምሮ አልለመድነውም፡፡ ወይ አልቅሰን፣ ወይ አኩርፈን ነው አንድን ነገር የምናገኘው፡፡

ታድያ ይህ የሁለታችንም አስተዳደግ ውጤት በቀላሉ የትራፊክ መንገድ አጠቃቀም ላይ ይታያል፡፡ ከአሜሪካን የመንገድ መተላለፊያዎች ውስጥ ብዙውን ቦታ የሚሸፍኑት በመስቀለኛ መንገዶች ላይ ከአራት አቅጣጫ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች በመጡበት ቅደም ተከተል መሠረት ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስ ተላልፉበት መተላለፊያ ነው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የትራፊክ ፖሊስ የለም፤ መብራትም የለም፡፡ ያለው ቁም /STOP/ የሚል በአራቱም መንገዶች ላይ የተቀመጠ የትራፊክ ምልክት ብቻ ነው፡፡ ከአራቱም አቅጣጫ የመጡ መኪኖች ራሳቸው ለቀደመው ቅድሚያ እየሰጡ ይተላለፋሉ፡፡

እኛ ሀገር ደግሞ እንምጣ፡፡ መብራት የሌለባቸው የመተላለፊያ መንገዶች ብቻ ሳይሆን መብራት በጠፋባቸው የመተላለፊያ መንገዶች ላይ የሚሆነውን አስቡት፡፡ ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጡ መኪኖች እኔ መቅደም አለብኝ በሚል ስሜት ብቻ ወደ መካከል ይመጡና ተዘጋግተው ጡሩንባ ሲነፉ መዋል ነው፡፡

ምናልባት ከአራቱም አቅጣጫ በየተራ ቢተላለፉኮ ቆመው የሚያጠፉትን ጊዜ ያህል አይወስድባቸውም ነበር፡፡ ሕጋችን ስላላዘዘ ነው? ነገሩ ክፉ ስለሆነ ነው? ፈጽሞ፡፡ ግን ያላደገባቸውን ከየት ያምጡት፡፡ መጽሐፈ መነኮሳት «ከሰይጣን ይልቅ ልማድን ፍራ» ይላል፡፡ ሰይጣን በሦስት ሱባኤ ጠበል ይለቃል፡፡ ልማድ ግን እንዲህ በቀላሉ ተነቅሎ አይሄድምና፡፡

ሕግ እና ቅጣት አጥፊዎችን ለማረም አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አብረውን የሚያድጉ ነገሮችን የመለወጥ ዐቅማቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ እናም በየቢሮው የዲሲፕሊን ኮሚቴ፣ የቅጣት እና ርምጃ ኮሚቴ፣ የግምገማ ኮሚቴ ከማቋቋም የሠራተኞቻችንን አብሮ አደግ የልማድ እና የጠባይ ችግሮች ከመሠረቱ እየለየ የሚቀርፍ ኮሚቴ ቢኖረን ኖሮ ችግሩን ከምንጩ ስሕተቱንም በእንጭጩ እንቀርፈው ነበር፡፡

የቢሮ አለቆችም ልክ ልኩን እሰጠዋለሁ፣ እቆነድደዋለሁ፣ አስገባለታለሁ ከማለታቸው በፊት ችግሩ ምንድን ነው? እስኪ መጀመርያ ልረዳው፣ ከዚያም ልርዳው፣ ከዚያም ልሞርደው፣ ካልተሳለ በመጨረሻ ልቆንድደው ቢሉ ለሀገሪቱ የተስተካከለ የሰው ኃይል ያፈሩላት ነበር፡፡

ቅጣት የማረምን ያህል በቂ ውጤት አያስገኝም፡፡ ሃያ ሠላሳ ዓመት የኖረበትን ልማድ፤ በእድሜው ሙሉ ሲከተለው የኖረውን የአኗኗር ዘይቤ በአንድ ደብዳቤ ማስተው ተአምራዊ ችሎታን ይጠይቃል፡፡ ታረፍዳለህ እየተባለ እየተቀጣ ከማርፈድ የማይመለስ ስንት ሰው አለ፡፡ ይህ ሰውኮ ማርፈድ ወድዶ ላይሆን ይችላል፤ ግን አቃተው፡፡ ታድያ ከገደል መውጣት ፈልጎ ለመውጣት ግን ያቃተውን ሰው እዚያው እያለ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በመላክ እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል እንዴ? ጎትቶ በማውጣት እንጂ፡፡

እርሱን እዚያ ገደል የጨመሩትኮ አስተዳደጉ፣ አኗኗሩ፣ ልማዱ፣ ባህሉ፣ የወላጆቹ እና የአካባቢው አስተሳሰብ፣ ሲሰማው የኖረው ነገርና ሌሎችም ተደማምረው ነው፡፡ ራሱ ሰውዬውምኮ ከእነዚህ ጥቃቅን ነገሮች ነው የተሠራው፡፡ ታድያ የተሠራበትን ካልቀየርንለት እንዴት ከተሠራበት ውጭ ሊሆንልን ይችላል?

ምስኪኗ ራሔል ይህንን የሚረዳላት አለቃ እና አሠራር አጥታ ነው የተቀጣችው፡፡


ይህ ጽሑፍ በሮዝ መጽሔት ላይ የወጣ ነዉ

23 comments:

 1. Kale hiwot yasemalin Dn Daniel. Atlanta.

  ReplyDelete
 2. "በተራ ቅደም ተከተል መስተናገድን አሜሪካውያን ከልጅነታቸው ጀምረው የሚያድጉበት ባህል ነው ማለት ይቻላል". You don't need to mention about Americans to to tell an Ethiopian about this point.I am tired of Ethiopian writers trying to criticize their society based on what they see in the Western world. We need to focus on fostering our own culture that can solve the issues you mentioned.

  ReplyDelete
 3. It is very interesting,Dani. We usually see mistakes as signs of failure-failure to obey,failure to perform,failure to admire,etc.-not as signs of learning.Thus, when we see someone doing sth wrong,we immediately criticize them,giving it special meaning in relation to our position.However,mistakes have three stages,according to language learning theories.

  The first is pre-systematic stage.This contains random errors which are made subconsciously and that take longer time to correct because of insufficient knowledge.

  The other one is systematic stage in which errors are made as part of the learning process.The learner can correct soon when he is told to,because the source is not ignorance but over generalization.Because these are made consciously,they do not take much time to correct.

  The last stage is called stabilization in which fossilized errors happen.These errors take longer time to correct as they are as hard as a fossil.However many feedbacks the learner receives,he cannot correct them;he has made them part of himself through continuous use.

  Dani,I think Rahel's mistakes are of the third type.And we are all like Rahel in somebody's eyes.We do have lots of fossilized errors in our personal,professional,spiritual,and social lives.We need to remember that the case is not person-/status-specific.This is what we lack these days.

  I remember your article entitled FEREKA to seat ourselves in somebody's seats,whatever they are.

  I thank you very much.

  ReplyDelete
 4. በተራ ቅደም ተከተል መስተናገድን አሜሪካውያን ከልጅነታቸው ጀምረው የሚያድጉበት ባህል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ማንኛውም ሕፃን ልጅ የትም ቦታ ሲሄድ ተራውን ጠብቆ ይስተናገዳል እንጂ ልጅ ነኝና ልቅደም አይላችሁም፡፡ ይህ ባህላቸው ሆኗል፡፡ እኛ ሀገር ስትመጡ ደግሞ ተራን ጠብቆ፣ ቅድሚያ ለመጣው ቅድሚያ ሰጥቶ አገልግሎት ማግኘትን ከልጅነታችን ጀምሮ አልለመድነውም፡፡ ወይ አልቅሰን፣ ወይ አኩርፈን ነው አንድን ነገር የምናገኘው፡፡

  Des Yemil Tsihuf new Dani! Ende Bahil yeyazinachewu melkam yehonu negeroch lezih maregagecha nachew. So we need to work on keeping good ways of doing things and change the bad ones.

  ReplyDelete
 5. ዳኒ በጣም የሚያስቅ ነው የዛሬው ጡመራህ:: አይጧን ግን እዚያው ባይተዋት ጥሩ ነበር:: በጣም የሚገርሙ ናቸው.... ስንፍናኮ' ነው:: በልጅቷ ሁኔታ ግን የራሴን ተሞክሮ አስታውሼ በጣም ነው የሳኩት:: ለአለቅየው እግዚአብሔር ልቦና ይስጠው::
  መልካም በዓል ይሁንልህ::

  አክባሪ እህትህ::

  ReplyDelete
 6. Dn. Daniel thanks. And thank to Almighty God Who give it to you all this views If we are realy wise we can Lern alot from this article. Thanks again. Keep it up. T. Tesfaye.

  ReplyDelete
 7. "መጀመርያ የሚገርመው እዚያ ትልቅ ሕንፃ ውስጥ አይጥ መግባቷ፤ በሰላም ኖራ ወልዳ ከብዳም መሞቷ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እንደታየው ድራማ ድመት ለመግዛት የአሠራር ሂደቱ አላስኬድ ብሎም ሊሆን ይችላል፡፡"

  I know very well that there is a room for improvement at all times. However, I feel this paragraph is inserted deliberatly to be negatively critical for the said mahiber and to promote your ego. This was not you thought us and this is not we, your disciples(students) excpect from you.

  ReplyDelete
 8. Thanks Dn Daniel about this very important issue! I wonder about the message of the anonymous 'I am tired of Ethiopian writers trying to criticize their society based on what they see in the Western world'. It is funny to see your tiredness. Please write and show us your skill of writings. I think it is not a problem to take good lessons from others countries culture as well. Do not forget we have also bad cultures/habits which should be removed via awareness creation campaign or education! So my anonymous brother or sister do not accept all our countries culture and also do not reject all other countries culture as well. Use your brain to filter out what is good and bad!!

  ReplyDelete
 9. ያስተምራል!

  ReplyDelete
 10. loved it so interesting thank u bro.

  ReplyDelete
 11. Kalehiwot Yasemalin!
  Ameha Giyorgis - DC

  ReplyDelete
 12. "Astemari yetefabet zemen!", i am really sorry dani, God given you his grace just for the sake of the gosple, i am sorry to say, but you are just using it to critisize and blame...why????? please think what you are doing again. This is not what we expect and this is not what you used to thought us. Sometimes i am tring to figure things out and i even got some falasies. onetime you are saying it is in the kitchen that the gratest service is, and another time i heard you are saying somebody make educated people serve in the kitchen...bla bla bla. Plz stop your critisizm and teach us how can we get to heaven, that is the most important thing and i guess that is also why God gave his grace to do.thanx

  ReplyDelete
 13. ይኼ አለቃ ‹‹ ጥፍር ሲያንቀጫቅጩ ሮጣ ከቢሮ የምትወጣ ›› ፀሃፊ ቢያጋጥመው ምን ሊቀጣት ነበር?

  ReplyDelete
 14. I wounder why you focus on the tiny winy issues while there are many things to bring on board . You always want to creat scene as your intention is to be too much on the screen . What we must be able to realize here is that we need to concentrate on the good ones and also pick good things that we can share with others rather than simply picking the negative ones . The reason why Daniel has written this story is because he was one of the higher ups of this Mahiber and moved out thinking that things would get messed up in his absence . To the contrary, the Mahiber is gaining momuntum and nobody gives an ear to him . This made him feel left out and trying to be a center of attention by wasting his time on the nity grity . To cut a long story short , we should know that nobody is important as the world can afford to pop up with new leader better than what we have now . It is good for all of us to be humble and down to earth and let our deed talk more than our word . After all ,this is in the heart of christianity .
  With humble regards ,
  Dekike Estifanos be "Hige Amilak "

  ReplyDelete
 15. Why i need approval for posting my comment ? This is an instrument for suppressing people's freedom ! You are a sinner preacher !

  ReplyDelete
 16. አባት ሆይ እባክህ ማረን ። ወንድሞቼን ጠብቅ።አሜን

  ReplyDelete
 17. Yibel! Zeygerim! Antumu Seb'a Alem Tehasesu Serwehom Leahawikum. Wemeshafe Hiywothi Yizenewena Kem Nawtsi Qidme Serwe emaynine.
  Dekike Estifanos, Behigamlak!

  ReplyDelete
 18. Now with this essay u really do confused me.i mean 1st i thought the mahiber is to be blamed for miss handling the accidental situation(the rat) which is cool point and understandable.in fact i agree with u,because i faced the same kind of problem in the so called mahiber,i tell them a job that i will do best and they ask of me some thing that i may not do passionately.2nd u almost washed the hands of the people in the mahiber by giving the "blame" to our Ethiopian culture.now am not the kind of person that says "there is nothing wrong with us!!and don't appreciate the Americas!!bla,bla..".i do believe we as a nation may have psychological problems.but this problem of ours is not going to be responsible for the aleqa's miss management.if we blame the nation for such kind of problem.the problem is not going to be solved at least till the general population is revolutionized,which can only COME IN TIME.none of us can bring a solution by blaming the society.country like America had society just like those in Europe its those few heroes(aleqas) like Washington,Jefferson,Lincoln,...who shaped the system,which in turn shaped the society.so if u had to blame some body blame the aleqa who was supposed to be better than the society.

  ReplyDelete
 19. ከሰይጣን ይልቅ ልማድን ፍራ

  ReplyDelete
 20. Ewunetin befikir yeminager andebet keyet yigegn yihon...ANTEM...YASAZINAL...YEZIHIN GETEMEGN HULUNEGER SILEMAWUKI...SILEATARAHUM SILEEWUSHETU AZENIKU. Can we write just to write? is that christanity

  ReplyDelete
 21. ከሰይጣን ይልቅ ልማድን ፍራ

  ReplyDelete
 22. ዲ/ን ዳንኤል የምታይበትን መነፅር በጣም ወድጀዋለው። ለየት ያለ ስለሆነ ብዙ አዋቂዎች ተማክረው ብዙ መስዋትነት ከፍለው የሰሩት እንደሆነ የምታያቸው ነገሮች ይመሰክራሉ። የንስርም ሌንስ ነው የገባለት የሚሉም አሉ። በሳቅ /LOL/። ወደቁምነገሩ እንመለስ እና እኔ አሁን ያለውን ማንነቴን የምገመግመው በአስተዳደጌ ሆነና ዙሪይው ገደል ሆነብኝ። ቅዱስ ሚካኤል (በባእድ አገር ያወቅኹት ያገሬ ታቦት) ከጎኔ ባይቆም ኖሮ ዛሬ ትቢያ ሆኜ በቀረው ነበር። ያድግሁት በቀላቢና በመዶሻ ነው። አባቴ ስራው በረኃ ለበረኃ ስለሆነ ያለመካሪ አባት አደኩ በለው። እናቴ ደግሞ መዶሻዋ ነች። እንኳን ሰው ይቅር እና እንሶቹ እንኳን ድንገት ወደሷ እየሮጡ እሷ መሆኗን ሲያውቁ ሰው ሊገጭ እንዳለ መኪና ፍሬን ይዘው ወደ መጡበት ነው የሚመለሱት። ታዲያ እኛ ቤት የተሰጠህን ትበላለኽ (ዱላም ጭምር ነው) የታዘዝከውን ታደርጋለህ። አለቀ። ይህ ሁሉ ከአይጣ ጋር ምን እንደሚያገናኘው መገመት ባያዳግትህም ግን እነሆ። አኔ በልጅነቴ የአምሮ ብሩኽነት ባያንሰኝ እንኳ ጨዋታ በጣም ያጥቃኝ ስለነበረ ነገሮችን በአግባቡ የማድረግ ችሎታው እና ልምዱ የለኝም። ታዲይ ይኽ ድክመቴ ትምህርት ቤት አልማጭ እንድሆን አደረገኝ። ታዲይ አርብ ጠዋት ሲመጣ ቴስት ከወደቁ ተማሪዎች ጋር ተሰልፌ በጉንጉን ገመድ መጠብጠቤ እንደ ዲዘረት ነገር ነው። እቤቴ ስገባ ኳስ ብይ ቴኒስ ወደም ማን ይጫወትልኝ ማንስ ደብተር አቅፎ ያውራልኝ (ግን ልጅ እንደሆንኩ አሁንም አትዘንጋ)። ታዲይ ቤት ወስጥ ደደብ እና ሰነፍ ከሚሉት ምርቃት እና "እኔ በእናንተ ልጆች ምክንያት እዛ ትምህርት ቤት እንደተመላለስኩ" ከሚለው የእናቴ ማማረርና የታላላቆቼ ክርኩም እና ስድብ በስተቀር በስተቀር ማንም ጠጋ ብሎ ጉድለቴን ሞልቶ ከድካሚ ሊያሳርፈኝ የሞከረ የለም። እዚህ ጋር የፈጠረኽ አይርሳህ ብሎ የመረቀኝ ፃድቅ እንዳለ እሙን ነው፤ አምላኬ በላውቀውም ስለሚያውቀኝ ከብዙ ነገር ሰውሮኛል እና። እናም የነ አፄ ልጆጅ ሆነን ማገናዘብ ስለተሳነን ከመገናዘብ ይልቅ መፈራረድ በስራ ቦት ብቻ ሳይሆን በየቤቱም ጎልቶ ይታያል። እኔ እነዚህ ነገሮች እና ብዙ የብዙ ብዙ ኢሰብአዉ ነገሮችን (ከአምልኮተ እግዚአብሔር መከልከል ጭምር፡ እዚህ ጋር ካለማወቅ የመጣ ስህተት ነው) ሰለባ ብሆንም የፈጠረኝ ስላልረሳኝ ዛሬ የባለፈውን እየገመገመገምኩ ወደፌት ከአምላኬ ጋር ለመጓዝ ግብ ግብ ላይ ነኝ። እናም ይህን ሁሉ ሳስብ ለሕፃናት ስነ ልቡና በጣም እንድቆረቆር አነሳሳኝ እንጂ ወደ ክፉ እንዳልመነዝር የፈጠረን ብዚህ አልረሳኝም። ግን ስንቶች ናቸው የልጅነት ጨለማን መወጣት አቅቷቸው ሴተኛ አዳሪ ጎዳና ተዳዳሪ የሆኑት። የገመድ እራት የአይጥ መርዝ ሰለባ የበረኪና መጫወቻ የኖኑት። ብዙ በልጅነት የሚደርሱ ጥቃቶች የሰውን ማንነት በአሉታዊ መልኩ ይቀይሩታል። እንኳን ሰው ሰውን ለመቀየር ይቅር እና እኔ እንኳ አገናዝባለው የምለው ይህው ስድስት አመት ሙሉ እጅ እና እሬን በእሳት መንዶ አስሮ ይዞኛል። በእግዚአብሔር እረዳትነት እንደምወጣው ግን የለጥርጣሬ በተስፋ አለኹ። ቸር ይግጠመን

  ReplyDelete