አዘጋጅ፡ መንግሥቱ ለማ
የታተመበት ዘመን 1959
የገጽ ብዛት 271
ዋጋ 120 ብር /ከአሮጌ መጻሕፍት ተራ/
ስለ አዘጋጁ፡
መንግሥቱ ለማ በቴአትር እና ግጥም ድርሰቶቻቸው የታወቁ ደራሲ ናቸው፡፡ ያደጉት የቤተ ክህነቱን ትምህርት በሚገባ ተምረው በመሆኑ ድርሰቶቻቸው ነባሩን የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የተዋረሱ ናቸው፡፡
ይህ መጽሐፋቸው በሀገራችን ሥነ ጽሑፍ በዓይነቱ ለየት ያለ አቀራረብን ያስተዋወቀ ነበር፡፡ በስድስት የኢትዮጵያ ነገሥታት ዘመን የኖሩትን አባታቸውን በቴፕ ሪከርደር ከአንድ ሺ በላይ ጥያቄ እየጠየቁ ከአርባ ስምንት በላይ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ቃለ መጠይቅ አድርገው ያስቀሩትን የአባታቸውን ትረካ በመጽሐፍ መልክ አስቀርተውልናል፡፡ ስለ እርሳቸው በሰፊው ማወቅ የፈለገ ሰው «ድማሙ ብዕረኛ» የሚለውን መጽሐፍ ቢያይ ይጠቀማል፡፡
መንግሥቱ ለማ በ1955 ዓም ይህንን ሲያደርጉ በዘመኑ የነበረው የመቅጃ መሣርያ አሁን ካሉት መሣርያዎች አንፃር እጅግ ኋላ ቀር ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ በእነዚያ ኋላ ቀር መሣርያዎች አማካኝነት ይህንን የመሰለ ታሪክ ሲያስቀሩልን ዛሬ ላይ ቢኖሩ ኖሮ ምን ነገር እንደሚሠሩ እንድንገምት ያደርገናል፡፡ ዛሬ እጅግ በተሻሻሉት እና ለሥራ ቀላል በሆኑት ዘመናውያን የመቅጃ መሣርያዎች ይህንን የመንግሥቱ ለማን ጅምር አለማጠናከራችን ትዝብት ላይ የሚጥለን ይመስለኛል፡፡
በብራናም ሆነ በጽሑፍ የተጻፉ መጻሕፍት እና መዛግብት በመጠኑም ቢሆን በአብያተ መጻሕፍት እና በአብያተ መዛግብት እየተሰባሰቡ ተቀምጠዋል፡፡ ለትውልድም ተርፈዋል፡፡ በቃል ያሉ መዝገቦቻችን ግን ከታላላቅ ሽማግሌዎቻችን ጋር አብረው እየተቀበሩ ነው፡፡ እነዚህን የሚያሰባስቡ የድምፅ እና የምስል አብያት የተቋቋሙ አይመስለኝም፡፡ ምናልባት በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን ጣቢያዎቻችን በየአጋጣሚው የተቀረፁት ይገኙ ካልሆነ በቀር፡፡ ይህ ነገር በዩኒቨርሲቲዎቻችን እና በአብያተ መዛግብቱ ሊታሰቡባቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል ይመስሉኛል፡፡
በተለይ በዚህ ዘመን ያለን ወጣቶች አንዱ ተግባራችን ይህ መሆን አለበት፡፡ በቀላል ዋጋ የሚገዛውን የመቅጃ መሣርያ ተጠቅመን በቀላል ዋጋ የማይሸጥ ታሪክ መሥራት እንችላለን፡፡ በየአካባቢያችን የሚገኙ ታሪክ እና ባህል ዐዋቂ ሽማግሌዎችን እየቀረጽን ብንቀርሳቸው ትናንትን ከመጥፋት እናድነዋለን፡፡
ስለ መጽሐፉ
በአፍሪካ ውስጥ አንድ ሽማግሌ ሞተ ማለት አንድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ተቃጠለ ማለት ነው ይባላል፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው የአፍሪካ ታሪክ በጽሑፍ ሳይሆን በቃል የሚወረስ ነውና፡፡ የኢትዮጵያም እንደዚሁ ነው፡፡ ትምህርቶቻችን፣ ታሪኮቻችን እና ይትብሃሎቻችን ከጽሑፍ ይልቅ ገና በቃል የሚገኙ ናቸው፡፡
መጽሐፈ ትዝታን የሚያነብብ ሰው ከአንድ ባለ ብዙ ዕውቀት፣ ባለ ብዙ ታሪክ እና ባለ ብዙ ወግ ሽማግሌ የምናዋራ ነው የሚመስለን፡፡ መንግሥቱ ለማ ከአባታቸው የቀረፁትን ታሪክ እንደ ወረደ ነው ያቀረቡልን፡፡ ልክ አለቃ ለማ እንደሚያወሩት አድርገው፡፡
አረጋዊው ሲፈልጉ ሐረር፤ ሲሻቸው ጎንደር፣ ደስ ሲላቸው ሸዋ፣ ከባሰም አገራቸው መቄት እየገቡ ያለ ገደብ ያወጉናል፡፡ ከቴዎድሮስ ዘመን ጀምረው ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ያደርሱናል፡፡ ይጸልያሉ፣ ይቀድሳሉ፣ ይማራሉ፣ ይተረጉማሉ፣ ይቀኛሉ፣ ይቀልዳሉ ይተቻሉ፤ ያመሰግናሉ፤ ምን የማያደርጉት አለ፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የቀደምት ትውልዶችን የዘር አስተሳሰብ፣ የጥንቷን ኢትዮጵያ መልክዐ ምድር፣ የሕዝቡን አኗኗር፣ የቤተ መንግሥቱን ወግ፤ የቤተ ክህነቱን አኳኋን፤ የተለያዩ ሊቃውንትን እና መኳንንትን ታክ፣ የአድባራት እና የገዳማትን ታሪክ እናገኝበታለን፡፡
አለቃ ለማ ሲያወጉን እየሰማን ሳያወጉን ያለፉትን አረጋውያን እያሰብን እንቆጫለን፡፡ አረጋውያኑን እስካል ሰማናቸው ድረስ ስለ ኢትዮጵያ የምናውቀው ነገር ምሉዕ ሊሆን እንደማይችል እንረዳለን፡፡ አለቃ ለማ ሌላ ቦታ ያልሰማናቸውን ታሪኮችም ያወጉናል፡፡
ለምሳሌ ሐዲስ ዓለማየሁ በፍቅር እስከ መቃብር ድርሰታቸው ዲማ ላይ ከፊታውራሪ መሸሻ ቤት ጉዱ ካሣ የሚባል ሰው አስተዋውቀውን ነበር፡፡ ታድያ ሐዲስ ዓለማየሁ ይህንን በድርሰታቸው አሳምረው የሳሉትን ሰው ያገኙት ዲማ ውስጥ ከነበረ ቀደምት ታሪክ መሆኑን አለቃ ለማ ናቸው የሚነግሩን፡፡
«ካሣማ የዲማ ደብተራ ነው፡፡ የሽማግሌ ልጅ ነው፡፡ ዛዲያ ካሣ ጉዱ ይሉታል፡፡ ጉዱማ የሞጋሣ ስሙ ነው፡፡» ገጽ 95
ጎንደር በደርቡሽ በተቃጠለ ጊዜ የሆነውን ሁኔታ፤ በክፉ ቀን ጊዜ የተደረገውን ነገር፤ ሐረር በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረችበትን ሁኔታ እንዲሁም ስማቸውን ሰምተነው የማናውቀውን ሊቃውንትን ታሪክ ይነግሩናል አለቃ፡፡
መንግሥቱ ለማ በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ዛሬ እንኳን በብዙዎቹ መጻሕፍት የማናገኘውን «መጠቁም» ሠርተውልናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን የአገልግለት ቃላት የሚተረጉም ሙዳየ ቃላትም አካትተውበታል፡፡ የአባታቸው ድንቅ የሆኑ ቅኔያትም ከነ ትርጉማቸው ቀርበዋል፡፡
መጽሐፉ እንደ አንድ ታሪካዊ እና ትውፊታዊ መጽሐፍ በአንድ ቤት ውስጥ በቅርስነት ሊቀመጥ የሚገባውና ወላጆች እና ልጆች በየዘመናቱ ሊያነብቡት የሚገባ መጽሐፍ ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ወላጆች ለልጆች ቢያነብቡላቸው የትናንቷን ሀገራቸውን ከዛሬዋ ጋር ለማነፃፀር ያመቻቸዋል፡፡ ብዙ ዕውቀትም ይገበዩበታል፡፡
መልካም ንባብ
ዲ/ን ዳንኤል ስለመጽሐፎች የምትሰጣቸው ጥቆማዎች የሚያበረታታ ነው በተለይ እንደዚ ያለ ታሪክ የያዘ መጽሀፎች ያገራችንን ማንነት ስርዓት ህግ ወጎችን ብዙ የሚያሳይ ነውና አሁንም በርታ ነው የምለው ሌሎችም ያልታተሙ ታሪካዊ ጽሁፎች የሚወጡበት ዕድል ይኖራልና የመታተም ዕድል ያላገኙ ታሪካዊ ጽሁፎችም የሚወጡበት ዕድል ይፈጠራል
ReplyDeleteዘየረር
ReplyDeleteበጣም ደስ የሚል መጽሐፍ ነው፡፡ ስለ ቀድሞ ነገር ፍለጋ አድርጎ ያጣ መጽሐፉን ቢያነብ ብዙ ነገር ያገኝበታል፤ እኔ በሌላ መጽሐፍ ላይ ፈልጌ ያጣሁትን ታሪክ አግኝቼበታለሁና፡፡ በተረፈ ግን ዲን.ዳንኤል አልሰማህ ይሆናል እንጅ ደስ የሚለው ነገር መጽሐፉ ድጋሚ ታትሟል፤ በብዙ መጻሕፍት መሸጫም ይገኛል፤ወጋውም ፷(፸) ብር ቢሆን ነው፨
Selam Dn Danieal
ReplyDeleteCan you post us your research about Tamre Mariam please? So many confusing article are published in cyber.
ዲ. ዳንኤል ይህን መጽሐፍ በበኩሌ ላገኘው እፈልጋለሁ ብዙ ታሪክ ያመቀ ነው መሰለኝ፡፡ የመጽሐፉን ክፍል በአንድ አጋጠሚ አንብቤው ነበር፤ የመንግስቱ ለማና የአባታአው አለቃ ለማ ኃይሉ የሕይወት ታሪክ ብዙ የሚነግረን የሀገር ቅርስ ነውና ሁላችንም ልናነበው ለትውልድ ልናስተላልፈው ይገባናል፡፡
ReplyDeleteዘየረር ጥሩ መረጃ ሰጠኸኝ አመሰግናለሁ
ReplyDelete